Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all 665 articles
Browse latest View live

ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን ምርጫና ጠቅላላ ጉባዔ አገደ

$
0
0

  የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ እንዳይካሄድ እንቅፋት ነበሩ ከተባሉ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች መካከል አንዱ የሆነው፣ የአገር አቀፉ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ያካሄደው ጠቅላላ ጉባዔና የአመራሮች ምርጫ ተሰርዞ አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ ተወሰነ፡፡  

የዘርፍ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ እንዲታገድና አዲስ ምርጫና ጠቅላላ ጉባዔ እንዲካሄድ የተወሰነው፣ የዘርፍ ምክር ቤቶችን ጉዳይ በቀጥታ ከሚመለከተውና ጉዳዩን ሲያጣራ በቆየው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነው፡፡

ሰኞ የካቲት 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተጻፈው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፣ አገር አቀፉ የኢትዮጵያ ዘርፍ ምክር ቤት ያካሄደውን ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ያገደው የምርጫ ሒደቱ ሕጋዊ ጥሰቶች ያሉበት መሆኑ በመረጋገጡ ነው፡፡ በተለይ ከዘርፍ ምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ ውጭ ከሁለት የምርጫ ዘመን በላይ በተደጋጋሚ የተመረጡ ግለሰቦች መኖራቸው ምርጫውን የሚያስደግም በመሆኑ፣ አዳዲስ አመራሮችን ለመምረጥ ድጋሚ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲጠራ ሊወሰን ችሏል፡፡ በተለያዩ ደረጃዎች የተዋቀሩ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችን ወቅታዊ ችግር በተመለከተ ንግድ ሚኒስቴር ለመጀመሪያ ጊዜ ማክሰኞ የካቲት 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ የዘርፍ ምክር ቤቱ ምርጫ ስለመታገዱ አረጋግጧል፡፡

ይኸው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ደብዳቤ ላለፉት አሥር ዓመታት ዘርፍ ምክር ቤቱን በፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩትን አቶ ገብረ ሕይወት ገብረ እግዚአብሔርን ጨምሮ፣ አምስት የቦርድ አባላትን በስም በመጥቀስ ከመተዳደሪያ ደንባቸው ውጭ በተደጋጋሚ መመረጣቸው የሚያሳይ የሕግ ጥሰት መፈጸሙን የሚያመላክት ጭምር ነው  ተብሏል፡፡

በንግድ ሚኒስቴር የአክሲዮን ማኅበራትና የንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኑረዲን መሐመድ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ የኢትዮጵያ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የቀረበበትን አቤቱታ ይከታተል የነበረው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባደረገው ማጣራት የመጨረሻ ውሳኔውን ሰጥቷል ብለዋል፡፡ ዕርምጃው የተወሰደውም ከዘርፍ ምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንቡ ውጪ ከሁለት ጊዜ በላይ በምርጫ የተመረጡና ወደ አመራር የመጡ እንዳሉ በማረጋገጡ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ዘርፍ ምክር ቤቱ ሁሉ ከታች ያሉ ምክር ቤቶች በአግባቡ ሳይወከሉ ወደ አመራር መጥተዋል ተብለው ቅሬታ በቀረበባቸው ንግድ ምክር ቤቶች ላይ ተመሳሳይ ዕርምጃ ተወስዷል ያሉት አቶ ኑረዲን፣ ከነዚህም ውስጥ በቀዳሚነት የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን ጠቅሰዋል፡፡ የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምርጫን በተመለከተ በተደረገ ማጣራት፣ የምርጫ ሕግንና የንግድ ምክር ቤቱን የምርጫ ደንብ ያልጠበቀ መሆኑን የአማራ ክልል ንግድ ኢንዱስትሪና ትራንስፖርት ቢሮ በማረጋገጡ፣ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ምርጫው እንዲደገም ከሦስት ሳምንታት በፊት ውሳኔ ስለመሰጠቱም አስታውሰዋል፡፡

እነዚህ እንቅስቃሴዎች የሚያሳዩት በተዋረድ ከታች ያሉ ምክር ቤቶች ምርጫ ያለመከናወኑ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ በሆነ አሠራር ያላለፉ መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡ አሁን ግን በማጣራቱ ሥራ የተወሰነውን ውሳኔ ተከትሎ ምርጫዎቹ ከሥር ጀምሮ ይካሄዳሉ ተብሏል፡፡

ምርጫዎቹንም ለማካሄድ ንግድ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና የክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮዎች በጋራ በመሆን የተዋረድ ምርጫዎችን እንዲያስፈጽሙ ውሳኔ ላይ መደረሱን የገለጹት አቶ ኑረዲን፣ ለዚህም አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል ብለዋል፡፡

የሕግ ጥሰት ታይቶባቸዋል የተባሉት ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ድጋሚ ምርጫ የሚያኬዱትም በንግድ ምክር ቤቶች መቋቋሚያ አዋጅና በንግድ ምክር ቤቶቹ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ይሆናል፡፡

ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴሮች እንዲሁም የአማራ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ እንዲህ ያለው ውሳኔ ላይ የደረሱት ከየንግድ ምክር ቤቶቹ አባላት በተደጋጋሚ የቀረቡትን ቅሬታዎች በመመርመር ነው፡፡ ከየክልሉ በቀረቡ ቅሬታዎች ምክንያት የዋናው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምርጫ ሊካሄድ አልቻለም ያሉት አቶ ኑረዲን፣ ጠቅላላ ጉባዔውና ምርጫው ታግዶ እንዲቆይ የተወሰነው በአዋጁ በግልጽ እንደተቀመጠው በተዋረድ ምርጫዎች ባለመደረጋቸው ነው ብለዋል፡፡ ከታች በወረዳ፣ በዞንና በከተማ የሚገኙ ምክር ቤቶች ፍትሐዊና አሳታፊ የሆኑ ምርጫዎች መካሄዳቸው ሲረጋገጥም የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምርጫ ይደረጋል ተብሏል፡፡ ከታች ያሉት በአግባቡ ምርጫቸውን ሳያካሂዱ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን ምርጫ ማካሄድ ስለማይቻል፣ ንግድ ምክር ቤት ጥር 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ሊካሄድ የነበረውን ጉባዔና ምርጫ ንግድ ሚኒስቴር ማገዱን አስታውሰዋል፡፡

ንግድ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔው እንዳይካሄድ ምክንያት የሆኑትን ጉዳዮች በማጥራት ከ15 እስከ 30 ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ ጉባዔውን እንዲካሄድ የሚያደርግ መሆኑንም ንግድ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በአንዳንድ ወገኖች ንግድ ሚኒቴርም ሆነ የክልል ንግድ ቢሮዎች በንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ጉዳይ ጣልቃ መግባት የለባቸውም የሚለውን አስተያየት ትክክል አለመሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ 341/95 እነዚህን ማኅበራት የማደራጀት፣ የመከታተልና የመቆጣጠር ሥልጣን የተሰጠው ለንግድ ሚኒስቴር በመሆኑ፣ ሚኒስቴሩ ይህንን ሥልጣኑን መጠቀም ይቻላል ተብሏል፡፡

በ2003 ዓ.ም. ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለሁለት ሲከፈል በአስፈጻሚ አካላት ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ደግሞ የንግድ ዘርፉን በተመለከተ ንግድ ሚኒስቴር፣ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ደግሞ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዲመራ መደረጉን ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል፡፡

ስለዚህ ካለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ጀምሮ እስከ ነሐሴ 2009 ዓ.ም.  ድረስ አምስት የሚሆኑ የንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶች አባላት በአዋጁ መሠረት ምርጫ አለማድረጋቸውንና በተመዳደሪያ ደንባቸው መሠረት ሕጉን ሳይጠብቁ ምርጫዎች እየተካሄዱ ያለመሆኑን የሚገልጹ አቤቱታዎች የቀረቡትም በሕግ መሠረት የሚያገባው ንግድ ሚኒስቴር በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡

ቅሬታ የቀረበባቸውም የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ የአዲስ አበባ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ የትግራይ ክልል ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ የደቡብ ንግድ ምክር ቤት ምርጫዎች እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡ የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሌላ በቀሪዎቹ ላይ ተመሳሳይ መረጃ እየተሰበሰበ ስለመሆኑም ከገለጻው ለመረዳት ተችሏል፡፡

የአገሪቱ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች አሁን ያሉበት አቋም በርካታ ችግሮች የሚታይባቸውም ነው ተብሏል፡፡ ችግሮቹን ለመፍታት ግን ንግድ ሚኒስቴር አልዘገየም ወይ?  የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ኑረዲን፣ ንግድ ሚኒስቴር እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን መከታተል የጀመረው በሰኔ ወር 2007 ዓ.ም. ነው ብለዋል፡፡ ከዚያ በፊት ንግድ ሚኒስቴር ሲሠራ የነበረው ምርጫዎች ሲደረጉ መካሄዳቸውን፤ ከ2003 ወዲህ ደግሞ የጋራ መድረኩን የመምራት ሥራ ብቻ ነበር፡፡

አሁን ግን ባለፉት ሁለት ወራት የምናያቸው ነገሮች ንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶች ከማቋቋሚያ አዋጁና ከራሳቸውም ደንብ የወጡ መሆናቸውን ነው ብለዋል፡፡ ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ንግድ ሚኒስቴር የመጨረሻ ውሳኔ እየሰጠ ነው ያሉት አቶ ኑረዲን፣ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው በመሆኑም ምርጫ እንዲራዘም ጭምር ውሳኔ እስከመስጠት ደርሰዋል ብለዋል፡፡ ለውሳኔው መዘግየታቸውን ግን አምነዋል፡፡

የንግድ ኅብረተሰቡን የሚወክሉ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች አሉባቸው የተባሉትን ችግሮች ለመፈተሽ በማጣራት ሥራው ላይ ብዙ ችግሮች እንደገጠሟቸው የገለጹት አቶ ኑረዲን፣ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ግን ንግድ ሚኒስቴር አስፈላጊውን ዕርምጃ ሁሉ እንደሚወስድና በትክክል ምርጫዎች እንዲካሄዱ ያደርጋል ብለዋል፡፡

በአንዳንድ ንግድ ምክር ቤቶች ያሉ አመራሮች ዕውን  ትክክለኛ ነጋዴዎች ናቸው ወይስ አይደሉም? የሚለው ጉዳይ የችግሩ ዋና ምንጭ መሆኑን በመጥቀስም፣ በንግድ ምክር ቤቶች አደረጃጀቶች ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመድፈን የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ ትኩረት እንደሚደረግም በመግለጫቸው ገልጸዋል፡፡ አንዳንድ ንግድ ምክር ቤቶች አሉን የሚሏቸው አባላት ላይም የሚታዩ ችግሮች መኖራቸውን በማረጋገጥ፣ ከዚህ በኋላ አደረጃጀታቸው እንዲስተካከል ይደረጋል ብለዋል፡፡ አሁን ግን ምክር ቤቶች ላሉባቸው ችግሮች አንዱ የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ መሆኑ ግንዛቤ ተወስዷል፡፡

ስለዚህ ይህንን አዋጅ ለማሻሻል የመጀመሪያው የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቷል፡፡ በቅርቡም ውይይት ተደርጎበት እንዲፀድቅ ይደረጋል፡፡ ይህም በተደጋጋሚ የሚፈጠሩ ችግሮችን ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአማራ ንግድ ኢንዱስትሪና ትራንስፖርት ቢሮ ዕገዳ የተጣለበት የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባላት በተሰጣቸው ጊዜ ገደብ ምርጫቸውን ለማካሄድ አልቻሉም፡፡

የተሰጠው የጊዜ ገደብ አንድ ሳምንት የቀረው ቢሆንም፣ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አለመደረጉ ታውቋል፡፡ እንደውም በአቶ ጌታቸው አየነው የሚመራው  ቦርድ ቢሮው ይደገም ያለውን ትዕዛዝ በመቃወም ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይህ ደግሞ የክልሉን ምርጫ በተሰጠው የጊዜ ገደብ እንዳይካሄድ እንቅፋት ሆኗል እየተባለ ነው፡፡ የንግድ ሚኒስቴር ግን በሕጉ መሠረት በክልሉ ንግድ ቢሮ በኩል ምርጫው በአጭር ጊዜ እንዲካሄድ ይደረጋል ብሏል፡፡ ካልሆነም በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የምዝገባ ሰርተፍኬቱን እስከመሰረዝ የሚደርስ ዕርምጃ ሊወሰድ ይችላል ተብሏል፡፡

አሁን በተሰጠው ውሳኔ መሠረት ግን የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና የክልሉ ንግድ ቢሮ ከንግድ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ምርጫውን ለማስፈጸም ይሠራሉ ተብሏል፡፡

 

Standard (Image)

የአንድ ኪሎ ቲማቲም ዋጋ 40 ብር ደርሷል

$
0
0

ከሁለት ሳምንታት በፊት በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ከስምንት እስከ 12 ብር ሲሸጥ የነበረው አንድ ኪሎ ቲማቲም ሰሞኑን ከ32 እስከ 40 ብር እየተሸጠ ነው፡፡  ለአንድ ኪሎ ቲማቲም የዚህን ያህል ዋጋ መሰጠቱ የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉት ቢገለጽም፣ የዋጋው መወደድ ጊዜያዊ እንደሆነ እየተገለጸም ነው፡፡

በአገሪቱ በከፍተኛ የቲማቲም አምራችነታቸው ከሚታወቁ አካባቢዎች አንዱ ከሆነው ከመቂ ባቱ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒየን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ሰሞኑን በከፍተኛ ደረጃ የቲማቲም ዋጋ ሊጨምር የቻለው የምርት እጥረት በመፈጠሩ ነው፡፡

150 የኅብረት ሥራ ማኅበራትን የያዘው የመቂ ባቱ ዩኒየን ከፍተኛ የቲማቲም አምራቾች የሚገኙበት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከአካባቢው መቅረብ ያለበትን ያህል ቲማቲም ለማቅረብ ያልተቻለው በቲማቲም በሽታና በአየር ንብረት ለውጥ ምርቱ ላይ ተፅዕኖ ስላሳደረ እንደሆነ ገልጿል፡፡

በመቂና በአካባቢው ባሉ አምራቾች የቲማቲም እርሻ ላይ ከአንድ ወር በፊት ቱታ አብሱሉታ የተባለው የቲማቲም በሽታ ያስከተለው ጥፋት ምርቱን ቀንሶታል፡፡ ከበሽታው ከተረፈው ምርትም የተወሰነው ከጥቂት ሳምንታት በፊት በተፈጠረ ውርጭ ምክንያት፣ በቂ ምርት ለገበያ ባለመቅረቡ የተፈጠረ ችግር ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት በመቂና አካባቢው ያሉ አምራቾች በጅምላ ዋጋ አንዱን ኪሎ ቲማቲም አራት ብር ድረስ ይሸጡ እንደነበር የሚያስታውሱት የዩኒየኑ ኃላፊዎች፣ አሁን ግን እጥረቱ የጅምላ መሸጫው ዋጋን ሳይቀር ከ25 ብር እስከ 30 ብር ሰቅሎታል፡፡ ቲማቲም ዋጋ በዚህን ያህል ዋጋ የተሸጠበት ጊዜ እንዳልነበርም ገልጸዋል፡፡ ዩኒየኑ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ላሉ ትላልቅ ተቋማት በየዕለቱ ለማቅረብ የተዋዋለውን ቲማቲም አሁን ባለው የገበያ ዋጋ እየገዛ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ይህ ችግር ግን ጊዜያዊ መሆኑን የሚጠቁሙት የዩኒየኑ የሥራ ኃላፊዎች፣ አዲስ የሚደርሰው የቲማቲም ምርት በ15 ቀን ውስጥ ስለሚወጣ ዋጋው ይወርዳል ተብሏል፡፡

ሆኖም ግን ከመቂ አካባቢ ውጭ ያሉ የቲማቲም አምራቾች የገጠማቸው ችግር ባይኖርም፣ እየሸጡ ያሉበት ዋጋ አጋጣሚውን በመጠቀም ዋጋው እንዲሰቀል ምክንያት እንደሆነም እየተነገረ ነው፡፡ 

Standard (Image)

ንግድ ባንክ በውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ ለሚሰማሩ ያለ ማስያዣ ብድር ለማቅረብ እየመከረበት ነው ተባለ

$
0
0

- ከፍተኛ ገንዘብ ወጥቶባቸው የተቆፈሩ ጉድጓዶች ብክነት እየታየባቸው መሆኑ ተገለጸ

 በከርሰ ምድር የውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ ለተሰማሩ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችና ባለሙያዎች ለማሽነሪዎች መግዣ የሚሆን ብድር ያለ ተጨማሪ ማስያዣ ሊያገኙ የሚችሉበትን አሠራር ለመተግበር የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር እየመከረ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የከርሰ ምድር ውኃ ቁፋሮ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅና የማሽኖች ዋጋ ውድ የሚባል በመሆኑ፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ውስን ናቸው ተብሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለማሽኖች መግዣ ከባንክ ብድር ለማግኘት ተበዳሪዎች ከማሽኖቻቸው ውጪ ተጨማሪ ማስያዣ ስለሚጠየቁ፣ ባለሙያዎችም ሆኑ ባለሀብቶች በዘርፉ ለመሰማራት ፈታኝ እንደሆንባቸው የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

ባለፈው ሳምንት የካቲት 25 ቀን 2009 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በአዳማ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ የተሳተፉ የውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ ባለሙያዎችና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች፣ ከብድር አቅርቦት ጋር ያለባቸውን ችግር በሰፊው ገልጸዋል፡፡ የሚኒስቴሩ ኃላፊዎችም ማሽኖቻቸውን ብቻ በማስያዝ ያለ ተጨማሪ ማስያዣ ብድር ማግኘት የሚያስችል አሠራር እንዲዘረጋ በባንኮች ጉዳዩን እየተፈተሹ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሚኒስቴሩ የከርሰ ምድር ውኃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ ተስፋዬ ታደሰ በምክክር መድረኩ ላይ ብድርን አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ፣ በዘርፉ ለመሰማራት ከፍተኛ የገንዘብ አቅም ስለሚጠይቅ ጥቂት ገንዘብ ያላቸው ባለሀብቶች እንጂ ሙያው ያላቸው አልሚዎች በብድር እንኳ በኢንቨስትመንቱ ውስጥ መሳተፍ አልቻሉም በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹በተለይ ባለሙያዎች ዕውቀታቸውን ጨምረው በኢንቨስትመንቱ (በከርሰ ምድር ውኃ ቁፋሮ) ለመሰማራት ትልቅ ፈተና አለባቸው፡፡ ምክንያቱም የመቆፈሪያ ማሽኖች ውድ ናቸው፤›› ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ ለምሳሌ ከ500 እስከ 600 ሜትር ጉድጓድ መቆፈር የሚችል ማሽን ለመግዛት ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ይጠይቃል ብለዋል፡፡

አክለውም ሥራው በቀላሉ ኪሳራ ሊያመጣ የሚችል ቢሆንም አትራፊም እንደሆነ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ በአንድ ጉድጓድ ከ60 እስከ 65 በመቶ ትርፍ ሊገኝበት እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ አልፎ አልፎ ግን ማሽኑ በቁፋሮ ላይ እያለ ተደርምሶበት ሊጠፋም የሚችልበት አጋጣሚ መኖሩን በመጥቀስ፣ አትራፊነቱንና ሥጋቱን ለማመላከት ሞክረዋል፡፡

 በነዚህና መሰል ምክንያቶች ባንኮች ማሽኑን ብቻ ይዘው ብድር ለመስጠት አለመቻላቸውን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን ከጥቂት ጊዜ ወዲህ በተለይ ንግድ ባንክ ማሽኖችን ወይም ሊብሬዎችን ብቻ በመያዝ ብድር መስጠት የሚችልበትን መንገድ ማጥናት ጀምሯል፤›› ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ የብድር አቅርቦቱን ለመጀመር ግን የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት የዘገየ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙ ባለሙያዎች እንደገለጹትም፣ በጥልቅ የከርሰ ምድር ውኃ ቁፋሮው የዓመታት ልምድና ዕውቀት ቢኖራቸውም፣ ከገንዘብ አቅም ውሱንነት ጋር በተያያዘ በራሳቸው አቅም ኢንቨስት አድርገው መሰማራት አለመቻላቸውን ነው፡፡ በአንፃሩ ዕውቀቱና ልምዱ ሳይኖራቸው ገንዘቡ ብቻ ስላላቸው በቁፋሮ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ተቀጥረው ለመሥራት ብቻ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህ ደግሞ በባለሙያዎችና በባለሀብቱ መካከል ችግሮችን ማጫሩ ስለማይቀር፣ ብዙውን ጊዜ በከፍተኛ ወጪ የሚቆፈረው ጉድጓድ የታሰበውን ያህል የአገልግሎት ጥራት እንደማይኖረው የተናገሩት ባለሙያዎች፣ አልያም የአገልግሎት ዕድሜው ላይ እንከን እየፈጠረ መሆኑን ጨምረው ጠቁመዋል፡፡

ከከርሰ ምድር ውኃ ጋር ተያይዞ ከሚነሱ ‹‹አንገብጋቢ›› ከተባሉ ችግሮች መካከል፣  በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ቀደም ብለው የተቆፈሩ ጉድጓዶች ከፍተኛ ወጪ ቢወጣባቸውም የሚፈልገውን ያህል አገልግሎት እየሰጡ አለመሆናቸው ይገኝበታል፡፡ እንዲሁም የውኃ ጉድጓዶች በአግባቡ አለመያዛቸውና በቂ መረጃና የመረጃ ቋት (ዳታ ቤዝ) የሌላቸው በመሆኑ፣ መልሶ ለመጠገንና ጥናት ለማካሄድ አስቸጋሪ አድርጎታልም ሲሉ ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ፡፡ በአዳማው የምክክር መድረክ ላይ የመወያያ መነሻ ሐሳብ በማቅረብ በዘርፉ የዓመታት  ልምዳቸውን ካቀረቡ ባለሙያዎች አንዱ የሆኑት አቶ ሁሴን እንድሬ እንደገለጹት፣ ረዘም ላለ ጊዜ አገልግሎት ላይሰጡ ወይም የአገልግሎት ጊዜያቸው የሚጠበቀውን ያህል ሳይቆይ የተበላሹ የውኃ ጉድጓዶች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ይገኛሉ፡፡ ሌሎችም ባለሙያዎች ከዚሁ ችግር ጋር ተያያዥነት ያላቸውን አስተያየት የሰጡ ሲሆን፣ መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ ሳያሳስቡ አላለፉም፡፡

Standard (Image)

ማስተርካርድ ፋውንዴሽን ኢትዮጵያን ጨምሮ የ11 አገሮች አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የፋይናንስ ድጋፍ አደረገ

$
0
0

 

 ማስተርካርድ ፋውንዴሽን በአፍሪካ 11 አገሮች ውስጥ ለሚገኙ 1.1 ሚሊዮን አርሶ አደሮች የምርታማነት ማሻሻያና የገበያ ትስስር መፍጠሪያ ፕሮግራሞችን በሚያራምዱ ተቋማት በኩል ድጋፍ ማደረጉን አስታወቀ፡፡

ፋውንዴሽኑ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ ይፋ እንዳደረገው፣ በአፍሪካ አነስተኛ ገበሬዎችን ለመደገፍ ከሚንቀሳቀሱ፣ የፋይናንስ እንዲሁም የአግሪ ቢዝነስ አገልግሎቶችን ለገበሬዎች ለማዳረስ ከሚጥሩ ሦስት ድርጅቶች ጋር ፋውንዴሽኑ ባደረገው ስምምነት መሠረት የ38.3 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡

ቡርኪናፋሶ፣ ኮትዲቯር፣ ኢትዮጵያ፣ ጋና፣ ማላዊ፣ ሞዛምቢክ፣ ሩዋንዳ፣ ሴኔጋል፣ ታንዛንያ፣ ኡጋንዳ እንዲሁም ዛምቢያን የሚያካትተው የማስተርካርድ ፋውንዴሽን ድጋፍ፣ ለአነስተኛ ገበሬዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት ምርታማነታቸው እንዲጨምር በማገዝ ከእጅ ወደ አፍ የሆነውን አሠራራቸውን ለመቀየር እንዲቻል ለማድረግ ያለመ መሆኑን፣ የማስተርካርድ ፋውንዴሽን ፋይናንሺያል ኢንክሉዥን ዳይሬክተሯ አን ማይልስ አስታውቀዋል፡፡

ከአንድ ሚሊዮን በላይ ገበሬዎች የፋይናንስና ሌሎችም ድጋፎችን ማግኘት እንዲችሉ ለማድረግ በአፍሪካ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ ሦስት ኩባንያዎች ጋር በመዋዋል 38 ሚሊዮን ዶላሩን እንዲያንቀሳቅሱ የተመረጡት ‹‹አፍሪካ አግሪካልቸር ዲቨሎፕመንት ካምፓኒ››፣ ‹‹ሩት ካፒታል›› እንዲሁም ‹‹አይሲሲሲኦ ኮኦፕሬሽን›› የተባሉ ሦስት ድርጅቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ኢትዮጵያን ጨምሮ በ11ዱም አገሮች ውስጥ ለሚገኙ ገበሬዎች የሥልጠናና ጥራት ያላቸው የግብርና ግብዓቶችን ማቅረብ፣ የሞባይል ቴክኖሎጂዎችን መተግበር፣ ከ150 ሺሕ እስከ 300 ሺሕ ዶላር ካፒታል የሚጠይቁ ነገር ግን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ለሚታመንባቸው የግብርና ነክ ቢዝነሶችን ከመደገፍ በተጨማሪ ሌሎችም ተግባራትን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡

ማስተርካርድ ፋውንዴሽን እስካሁን በአፍሪካ ለሚገኙ አነስተኛ ገበሬዎች ከ300 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችለው ገንዘብ መመደቡን አስታውቆ፣ ከዚህ ውስጥ 175 ሚሊዮን ዳላሩ በገጠር አካባቢዎች እንዲሁም በግብርና መስክ ፋይናንስ የሚያቀርቡ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ የሚውል ድጋፍ እንደሆነ ገልጿል፡፡

ማስተርካርድ ፋውንዴሽን ከአሥር ዓመት በፊት በካናዳ የተቋቋመ የበጎ አድራጎት ተቋም ሲሆን፣ የፋይናንስ ተካታችነትን፣ የትህምርትና ሥልጠናን፣ የወጣቶች ኑሮ መሻሻልን መሠረት አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው፡፡

ይኸው ተቋም ከጥቂት ወራት በፊት በኢትዮጵያ ከ12 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች በንብ ማነብ እንዲሁም በሐር የፈተል ክር የምርት ሥራ ላይ መሳተፍ የሚችሉበትን የሥልጠናና የቢዝነስ ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል የፋይናንስ ድጋፍ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

 

 

Standard (Image)

ዮቤክ ኩባንያ ከስዊዘርላንዱ ሞቨንፒክ ጋር የባለአስምት ኮከብ ሆቴል ስምምነት ፈጸመ

$
0
0

በስዊዘርላንድ ሆቴል በማስተዳደር አገልግሎት ከሚታወቁ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው ሞቨንፒክ ሆቴልና ሪዞርት በኢትዮጵያ ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ የሚፈጀውን ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ለማስተዳደር ከዮቤክ ኢንተርፕራይዝ ጋር ስምምነት ተፈራረመ፡፡

ባለአምስት ኮከብ ሆቴሎችን በማስተዳደር የሚታወቀው ሞቨንፒክ ሆቴልና ሪዞርት ኩባንያ፣ በኢትዮጵያ የሆቴል ኢንዱስትሪ ውስጥ ተሳታፊ የሚያደርገውን ይህንን ስምምነት ከዮቤክ ኢንተርፕራይዝ ጋር ሐሙስ የካቲት 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ተፈራርሟል፡፡

አዲሱ ስቴዲየም እየተገነባ በሚገኝበት ገርጂ አካባቢ በዮቤክ እየተገነባ ያለውን ባለ 14 ፎቅ ሆቴል ለማስተዳደር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ ስምንት ኩባንያዎች ሲያወዳደሩ ቆይተው፣ ሞቨንፒክን ሊመርጥ እንደቻለ ሁለቱን ኩባንያዎች በማደራደር ወደ ስምምነት ያመጣው የኦዚ ቢዝነስ ኤንድ ሆስፒታሊቲ ግሩፕ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ቁምነገር ተከተል ገልጸዋል፡፡

ሞቨንፒክ ሆቴል ዋና መቀመጫውን በስዊዘርላንድ በማድረግ በተለያዩ የዓለም ከተሞች የሚገኙ ሆቴሎችን በጋራ የማስተዳደር ስምምነት መሠረት እንደሚያንቀሳቅስ የሚታወቅ በመሆኑ እንደተመረጠ ተገልጿል፡፡ ሞቨንፒክ በዓለም አቀፉ የሆቴል ኢንዱስትሪ ውስጥ በተለይም ባለአምስት ኮከብ ደረጃ ባላቸውና ለላይኛው ወይም ውድ በሚባለው የሆቴል ደረጃ መሠረት አገልግሎቶችን በማቅረብ ትልቅ ስም ካተረፉ የሆቴል ብራንዶች መካከል አንዱ እንደሆነም ተነግሯል፡፡

የዮቤክ ኢንተርፕራይዝ መሥራችና ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኔ ግደይ እንደገለጹት፣ ኩባንያቸው ሞቨንፒክን የመረጠው መልካም ስምና ዝናው ከመመልከት ባሻገር በሆቴል አስተዳደር ሥራ መስክ ያላቸውን መርኅ እንዲሁም ዝርዝር የሥራ አመራር ልምዶችን የሚገልጹ መረጃዎችን በማጥናት ነው፡፡ በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ የሞቨንፒክ ሆቴሎችን በአካል በመጎብኘት ጭምር ምዘና ማድረጋቸውን የገለጹት አቶ ብርሃኔ፣ የሞቨንፒክ ብራንድ ለሆቴላቸው ተመራጭ ሆኖ እንዳገኙት ገልጸዋል፡፡

ሆቴሉ 252 የተለያዩ ደረጃ ያላቸው የእንግዳ ክፍሎች የሚኖሩት ሲሆን፣ ከፕሬዚደንሻል እስከ ስታንዳርድ ክፍሎችን ያካተተ ዘመናዊ ሆቴል እንደሆነም ተገልጿል፡፡ ከመንታ ክፍሎች ባሻገር ሦስት የምግብ አዳራሾች፣ አንድ የሙሉ ጊዜ ምግብ ቤትንም ያካትታል፡፡ ሁለት የጣልያንና የእስያ ምግብ ቤቶች፣ ሦስት የመጠጥ አገልግሎት መስጫ ባሮች፣ 1,600 ሰው መያዝ የሚችል የስብሰባ አዳራሽና ስድስት የተለያዩ ስፋት ያላቸው የስብሰባ አዳራሾች እንደሚያካትትም ተጠቅሷል፡፡ 1,350 ካሬ ሜትር ስፋት ያለውና በወር እስከ 300 ተገልጋዮችን ማስተናገድ የሚችል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማካሄጃ ጂም በሆቴሉ ግንባታ ውስጥ ተካቷል፡፡

ከ140 በላይ መኪኖችን የሚያስተናግድ ማቆሚያ የያዘ ስለመሆኑም አቶ ብርሃኔ ተናግረዋል፡፡ የሆቴሉ ሕንፃ ግንባታ በአሁኑ ወቅት 60 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ቀሪውን የፊኒሺንግና አጠቃላይ የመገልገያ መሣሪያዎች የገጠማ ሥራ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ተሟልተው ሆቴሉ በ2011 ዓ.ም. አገልግሎት እንደሚጀምር ገልጸዋል፡፡ ሆቴሉ ለ700 ቋሚና 450 ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም ይጠበቃል፡፡

ዩቤክ በአዲስ አበባ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይሠራል ተብሎ ከተጠበቀው ሆቴል በተጨማሪ በመቐለ ከ160 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቅ ባለአራት ኮከብ ሆቴል ግንባታ በማጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ ዮቤክ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተባለው የፒፒ ከረጢት፣ ኮንድዊት፣ ፒቪሲ ቧንቧና የኤሌክትሪክ ኬብሎች ማምረቻና ልዩ ልዩ የኤሌክትሪክ ዕቃዎች አስመጪና አከፋፋይ መሆኑን የኩባንያው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በ1999 ዓ.ም. የተመሠረተው ዮቤክ፣ በ2004 ዓ.ም. ወደ ሪል ስቴት ልማት በመግባት በአዲስ አበባ ከተማ ለተለያዩ የንግድና የቢሮ አገልግሎት የሚውሉ ባለ 14 ፎቅ መንትያ ሕንፃዎችን በሰንጋተራ አካባቢ አስገንብቶ፣ ለአገልግሎት ማብቃቱም ይታወሳል፡፡  

ሞቨንፒክ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ከፍተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት አላን ኦዲዬ ስምምነቱን በፈረሙበት ወቅት እንደገለጹት፣ የሞቨንፒክን ብራንድ ሆቴል በኢትዮጵያ ለማስተዳደር የሚያስችላቸውን ስምምነት የፈረሙት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ባሻገር በሞሮኮ፣ በቱኒዝያ፣ በኬንያ፣ በናይጄሪያ እንዲሁም በኮትዲቯር ከዚህ ቀደም የሞቨንፒክ ብራንዶች መከፈታቸውን ምክትል ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡

በዓለም 35 አዳዲስ ሆቴሎችን በመክፈት ለማስተዳደር የሚጠባበቀው ሞቨንፒክ፣ በዓለም ላይ የሚያስተዳድራቸው ሆቴሎች ብዛት 83 እንደሆኑ ሲገልጽ፣ በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥም ከ100 በላይ እንደሚያደርሳቸው ይጠበቃል ተብሏል፡፡

 

Standard (Image)

እህል ነጋዴዎች በቆሎና ማሽላ ላይ በተጣለው ዕገዳ ምክንያት ወደ ውጭ መላክ አልቻልንም አሉ

$
0
0

 

ከምሥራቅና ከደቡባዊ አፍሪካ የመጡ ገዥዎች ከኢትዮጵያ ግዥ ፈጽመዋል                                                                                                                                                                                                                       የጥራጥሬ፣ የብርዕ፣ የአገዳና የሌሎችም የግብርና ሸቀጦችን ወደ ውጭ የሚልኩ ድርጅቶች ባለፈው ዓመት በተጣለውና እስካሁንም ባልተነሳው የበቆሎና የማሽላ የወጪ ንግድ እገዳ ምክንያት መላክ እንዳልቻሉ ገለጹ፡፡

ሰሞኑን በአዲስ አበባ በተካሄደውና ከአሥር የምሥራቅና የደቡባዊ አፍሪካ አገሮች የተውጣጡ የእህል ነጋዴዎች በተሳተፉበት መድረክ ላይ እንደተገለጸው፣ ምንም እንኳ የአፍሪካ አገሮች ከኢትዮጵያ የበቆሎ የማሽላ ምርቶችን ጨምሮ ሌሎችንም የጥራጥሬ፣ የቅመማቅመም እንዲሁም የቅባት እህሎችን የመግዛት ፍላጎት ቢያሳዩም በተለይ በቆሎና ማሽላ መላክ እንዳልቻሉ ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከቡሩንዲ፣ ከኬንያ፣ ከታንዛኒያ፣ ከኡጋንዳ፣ ከማላዊ፣ ከኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ እንዲሁም ከደቡብ ሱዳን የተውጣጡ የእህል ነጋዴዎች በአዲስ አበባ በመገኘት የእርስ በርስ ግብይት ለመፈጸም የሚችሉበትን መድረክ አካሂደው ነበር፡፡ በመድረኩ ከፍተኛ ፍላጎት ከታየባቸው መካከል የበቆሎ ግዥ ፍላጎት ትልቁን ድርሻ ይዟል፡፡ ይሁንና ይህንን ምርት ከአገር ውጭ መሸጥ በመከልከሉ ምክንያት መንግሥት ይህንን ዕገዳ ያነሳ እንደሆነም ጥያቄ ሲቀርብ ተደምጧል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ የእህል ነጋዴዎች ምክር ቤት ባካሄደው ስብሰባ ወቅት፣ የዕገዳውን መነሳት ጥያቄ ያቀረቡት የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ኩባንያን በመወከል በስብሰባው የታደሙት አቶ ይልማ አበበ ናቸው፡፡ ጥያቄያቸው ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ መንግሥት ያስቀመጠውን ዕገዳ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊያነሳ ስለማሰቡ ማወቅ ባይቻልም ሪፖርተር ባደረገው ማጣራት ግን መንግሥት ዕርምጃውን የወሰደው፣ በኤልንኖ ምክንያት በአገሪቱ ተክስቶ የነበረው ድርቅና ያስከተለውን የምግብ ዕጥረት ለመከላከል በማሰብ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ከንግድ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃም ዕገዳው እስከመቼ ሊቆይ እንደሚችል ባይገልጽም፣ በበቆሎና በማሽላ ላይ የታጣለው ዕገዳ ግን አሁንም እንዳለ ያስረዳል፡፡

በአብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች በተከሰተው የአየር ንብረት መዛባት ሳቢያ በተለይ የበቆሎ ምርት እጥረት ተከስቷል፡፡ ኢትዮጵያ በመጠኑም ቢሆን ከሌሎች አገሮች ይልቅ የተሻለ የበቆሎ ምርት ማስዘገብ መቻሏም ሲጠቀስ ተደምጧል፡፡ ከበቆሎ ባሻገር አኩሪ አተር፣ ስንዴ፣ ባቄላ፣ አተር፣ ሽንብራና ሌሎችም የእህል ምርቶችን ከኢትዮጵያ ለመግዛት ፍላጎት መኖሩ ታይቷል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ የእህል ነጋዴዎች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ጄራልድ ማካው ማሲላ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ምክር ቤቱ በአፍሪካ የእርስ በርስ የንግድ ትስስር እንዲጠናከር ማሳያ መድረክ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ ይሁንና በአገሮች መካከል የሚታየው ሕገወጥ የድንበር ዘለል ንግድ እንቅስቃሴ፣ ከዚህም ባሻገር በድንበር አካባቢ የሚታየው ሙስና፣ ተደራራቢ ታክስ፣ የመሠረተ ልማት መጓደል፣ ወደኋላ ተመልሰው የሚተገበሩ ሕጎችን መጠቀም፣ የንግድ ፍሰትን የሚገድቡና አሠራሮችና የፖሊሲ ጣልቃ ገብነቶች በአገሮች መካከል ሊኖር የሚገባውን ያህል የንግድ ትስስር እንዳይኖር እያስገደደ እንደሚገኝ ምክር ቤቱ ያቀረበው ሪፖርት ይጠቁማል፡፡

ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳና ታንዛንያ በጅምላ ያመረቱት የበቆሎ ምርት 17.2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እንደነበር የምክር ቤቱ ሪፖርት አሳይቷል፡፡

ከበቆሎና ከማሽላ ባሻገር ለዓመታት የዘለቀ ዕገዳ በጤፍ ላይ ተጥሎ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ መንግሥት በጤፍ ላይ ማዕቀብ ለመጣል ከተገደደባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ በጤፍ የአዕምራዊ ንብረት ባለቤትነት ላይ እየተነሳ የሚገኘው ሙግት ይገኝበታል፡፡ ከግሉቲን ነፃ በመሆኑ እንዲሁም በብረት ማዕድን ይዘቱ በዓለም ላይ ዕውቅና እያተረፈ የመጣው ጤፍ፣ ከወደ ሆሊውድ መንደርም ተቀባይነትን ያተረፈ ተስማሚ የምግብ ዘር ለመሆን በቅቷል፡፡ ይሁንና ጤፍ ላይ የተጣለው ማዕቀፍ ቢነሳ ከቡና ይልቅ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ሊያስገኝ እንደሚችል የሚገልጹ አሉ፡፡

በአንፃሩ እንደ አዲስ የተዋቀረውን የአካባቢ ጥበቃ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴርን እንዲመሩ የተሾሙት አዲሱ ሚኒስትር በብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ላይ ጽኑ አቋም ያላቸው በመሆናቸው እንደ ጤፍ ያሉ አገሪቱ ሕዝብ መደበኛ የምግብ ምንጭ የሆኑ ውጤቶችን በቀላሉ ለዓለም ገበያ እንዲውሉ ይፈቅዳሉ ተብሎ አይታሰብም፡፡

 

 

Standard (Image)

የሰባት ወራት የወጪ ንግድ አፈጻጸም ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ቅናሽ አስመዘገበ

$
0
0

የ2.4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ሲጠበቅ 1.4 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል

በበጀት ዓመቱ ሰባት ወራት የታየው የወጪ ንግድ አፈጻጸም እንደወትሮው ማሽቆልቆል አሳይቷል፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ይጠበቅ የነበረው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከ2.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ቢሆንም፣ አፈጻጸሙ ግን ከ1.4 ቢሊዮን ዶላር ብዙም ፈቅ ሳይል ቀርቷል፡፡

ከንግድ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ በሰባት ወራት ውስጥ ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርናና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ውጤቶችን ለዓለም ገበያ በማቅረብ በጠቅላላው 1.423 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ ይህ ገቢ ግን በሰባት ወራት ውስጥ ይገኛል ተብሎ ከታቀደውም ሆነ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አኳያ ዝቅተኛ ሆኖ መገኘቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባለፈው ዓመት ሰባት ወራት ውስጥ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 1.521 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡

‹‹በበጀት ዓመቱ ሰባት ወራት 2.488 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ በአፈጻጸም የተመዘገበው 1.423 (57.19 በመቶ) ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህ አፈጻጸም ባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወራት ከተገኘው 1.521 ቢሊዮን ዶላር ሲነፃፀር በ37.516 (6.46 በመቶ) ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ አሳይቷል፤›› የሚለው የሚኒስቴሩ ሪፖርት፣ በተያዘው ዕቅድ አኳያ የ50 በመቶ በታች ቅናሽ ካስመዘገቡት የወጪ ንግድ ምርቶች ውስጥ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ ዓሣ፣ ሰም፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች፣ ቅመማ ቅመምና የመሳሰሉት ሲጠቀሱ፣ ወርቅ፣ የቁም እንስሳት፣ የሥጋ ተረፈ ምርት ብረታ ብረትም ከግማሽ በላይ ቅናሽ ያሳዩ ሆነው ተገኝተዋል፡፡

ዋና ዋና ከሚባሉት የወጪ ንግድ ሸቀጦች መካከል ቡና ቀዳሚው ነው፡፡ በቡና ወጪ ንግድ ዘርፍ ባለፉት ሰባት ወራት ውስጥ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 360.8 ሚሊዮን ዶላር ሆኗል፡፡ ይጠበቅ ከነበረው የገቢ መጠን አኳያ ማከናወን የተቻለው ከዕቅዱ 4.2 በመቶ ብቻ እንደሆነ ታይቷል፡፡ ምንም እንኳ ዓምና በተመሳሳይ ወቅት ከታየው ይልቅ ዘንድሮ የ14.67 ሚሊዮን ዶላር የገቢ ጭማሪ ቢመዘገብም፣ በመጠን ግን ለአራት ሺሕ ቶን የቀረበ ቅናሽ ተመዝግቧል፡፡

ዘንድሮ ለውጭ ገበያ የቀረበው የቡና መጠን 96.6 ሺሕ ቶን ነው፡፡ ዓምና በሰባት ወራት ውስጥ የቀረበው የቡና መጠን ግን ከ100 ሺሕ ቶን በላይ መሆኑን የንግድ ሚኒስቴር ሪፖርት ያሳያል፡፡

‹‹በዚህ ወርና በአጠቃላይ በሰባት ወራት በመጠንና በገቢ የቀነሰበት ምክንያት በቡና አብቃይ ክልሎች በቂ የቡና ምርት እንዳለ ቢታወቅም፣ ይህንን ሁኔታ ገዢዎች በመረዳት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋጋ በታች እየሸጡ በመሆኑ በዋጋ ላይ መግባባት ባለመቻሉ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በቂ ኮንትራት አልተገባም፣ ገዢዎች ምክንያት እየፈጠሩ የሚላክላቸውን ናሙና ውድቅ በማድረግ L/C ከፍቶ ለመላክ በማዘግየታቸው ነው፤›› በማለት ቡና የታሰበውን ያህል ውጤታማ ያልሆነው የውጭ ገዢዎች የሚሰጡት ዋጋ ከአገር ውስጥ የምርት ገበያ ዋጋ አንሶ መገኘቱ ዋናው ምክንያት እንደሆነ ሚኒስቴሩ ይገልጻል፡፡

ይሁንና በወጪ ንግድ ዘርፍ እየታየ ላለው ደካማ ውጤት ከሚጠቀሱት መካከል በአገሪቱ የተከሰተው ሕዝባዊ ተቃውሞና ይህንንም ተከትሎ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያስከተለው የገበያ መናጋት እንደሆነ በቅርብ ጉዳዩን ከሚከታተሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአገሪቱ በመደበኛ መንገድ ለውጭ ገበያ መቅረብ የሚጠበቅባቸው ምርቶች በአብዛኛው በኮንትሮባንድ እየወጡ መሆናቸው ችግሩን እንዳባባሰው ሲገለጽ ይደመጣል፡፡ ከዚህ ባሻገር ሰሞኑን ንግድ ሚኒስቴር ከላኪዎች ጋር ባደረገው ዝግ ስብሰባ፣ አብዛኞቹ ከምርት ገበያው ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ምርት ማግኘት እንዳልቻሉ መግለጻቸው ተሰምቷል፡፡

ከኮንትሮባንድ ወደ ውጭ እየወጡ እንደሚገኙ ከተገለጹ ምርቶች መካከል ወርቅ ይገኝበታል፡፡ የወርቅ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ዝቅተኛ ሊሆን የቻለው የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ከመኖሩ ባሻገር ዘመናዊ አምራቾችም ቢሆኑ በዕቅዳቸው መሠረት አከታትለው መላክ ባለመቻላቸው ምክንያት ዝቅተኛ ውጤት ሊያስመዘግብ እንደቻለ ንግድ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ከወርቅ ይጠበቅ ከነበረው ገቢ የ26 በመቶ ቅናሽ በማሳየት፣ የ111 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተመዝግቧል፡፡

የወጪ ንግዱ ዘርፍ እንዲህ ባለው ደረጃ እየተንሸራተተ መምጣቱ አገሪቱ የንግድ ሚዛን ጉድለት እያባባሰው መምጣቱን የዓለም የገንዘብ ድርጅት ሪፖርት አስታውቋል፡፡ ድርጅቱ ባለፈው ዓመት ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንደሚጠቅሰው፣ አገሪቱ የከረንት አካውንት ጉድለት 7.4 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ሲሆን ይህም ከአገሪቱ ኢኮኖሚ (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ) የ10 በመቶ ድርሻ ይዞ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል እ.ኤ.አ. ከ2006 እስከ 2016 ባሉት ዓመታት ውስጥ በአገሪቱ ገቢና ወጪ ንግድ መካከል የታየው የንግድ ሚዛን ጉድለት በአማካይ ሁለት ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡ በተለይ ዓምና የነበረው የንግድ ሚዛን ጉድለት ከ3.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደነበርም ተመልክቷል፡፡ 

 

 

Standard (Image)

የሐዋሳ ንግድ ምክር ቤት ዋና መሥሪያ ቤቱን የሚገነባበት ቦታ ተረከበ

$
0
0

 

የሐዋሳ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃውን ለመገንባት የሚችልበትን ቦታ ከሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ማግኘቱን አስታወቀ፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ የራሱን ሕንፃ ለመገንባት ቦታ እንዲሰጠው ጥያቄ ካቀረበ ዓመታት ቢቆጠሩም፣ በቅርቡ ከሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ምላሽ አግኝቷል፡፡ ለሕንፃ ግንባታው ምቹ በተባለ የከተማዋ ክፍል 800 ካሬ ሜትር ቦታ በአነስተኛ ሊዝ ዋጋ እንደተረከበ አስታውቋል፡፡ የቦታው የሊዝ ዋጋ 1.12 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ቦታው ላይ ይገነባል ለተባለው ሕንፃ ቅዳሜ መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. የመሠረት ድንጋይ መቀመጡን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ለሕንፃ ግንባታው የተቀመጠውን የመሠረት ድንጋይም የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ  አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ ያስቀመጡ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትና የከተማው ንግድ ምክር ቤት አመራሮች በሥነ ሥርዓቱ ላይ መገኘታቸውም ተገልጿል፡፡

የሐዋሳ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሚልኪያስ አንዴቦ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ንግድ ምክር ቤቱ በተሰጠው ቦታ ላይ በአጭር ጊዜ የሕንፃ ግንባታ ሥራውን ይጀምራል፡፡ እንደ አቶ ሚልኪያስ ገለጻ፣ ሊገነባ የታሰበው ሕንፃ ስድስት ወለሎች የሚኖሩት ሲሆን፣ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ሊጠይቅ እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ለግንባታው የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች የሚዘጋጁ ሲሆን፣ የመሠረት ግንባታውን ግን በራሱ አቅም ለመጀመር መታቀዱን የምክር ቤቱ ኃላፊዎች አስታውቀዋል፡፡

በንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት እንዲሁም በመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ፣ በሐዋሳ ከ14 ሺሕ በላይ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች እንደሚኙ ጠቅሰዋል፡፡ ከተማው ከሚያሰባስበው ገቢ ውስጥ አንድ ቢሊዮን ብር የሚደርሰው ገቢ በአብዛኛው ከንግዱ ማኅበረሰብ እንደሚሰበሰብ ተናግረዋል፡፡

የከተማው አስተዳደር ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳለው የተናገሩት ከንቲባው፣ በተለይ ታማኝ ግብር ከፋዮች እንዲበራከቱ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱ በትጋት መሥራት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱን ለማጠናከር የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የሚጠበቅበትን ድርሻ እንደሚወጣ አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ጥያቄ ሲቀርብበት ለነበረው የሐዋሳ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና መሥሪያ ቤት መገንቢያ ቦታ አስተዳደሩ 800 ካሬ ሜትር ቦታ መስጠቱን በእማኝነት ጠቅሰዋል፡፡

ወደፊትም ለሕንፃ ግንባታው ከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ ከንቲባው ቃል ገብተዋል፡፡ የበርካታ ዓመታት ጥያቄ ለነበረው የጽሕፈት ቤት ሕንፃ መሥሪያ ቦታ በማቅረብ አስተዳደሩ ምላሽ በመስጠቱ፣ ከፍተኛ ውጣ ውረዶችን በማለፍ ለስኬት እንዲበቃ የሚያስችል መሆኑን አቶ ሚልኪያስ ጠቅሰዋል፡፡ የሕንፃ ግንባታው የንግዱን ማኅበረሰብ አባላት በማሳተፍና ከመንግሥት ጋር በመሆንም ጭምር እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡

ምክር ቤቱ ውስጣዊ አደረጃጀቱን ለማጠናከር እየሠራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሚልኪያስ፣ ለምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ሥልጠናዎች በመስጠት ላይ እንደሚገኝ፣ የንግድ ትስስሮችን የመፍጠር ሥራዎችንም እንደሚያከናውን ጠቁመዋል፡፡ ምክር ቤቱ የአባላትን ቁጥር ለማሳደግ አዳዲስ አባላትን የማፍራት ሥራ እንደሚሠራም አቶ ሚልኪያስ አስታውቀዋል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ የራሱን ሕንፃ መገንባት መቻሉ አቅሙን ከማጎልበት በተጨማሪ ለአባላቱ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማበራከት ያስችለዋል ብለዋል፡፡ የሐዋሳ ንግድ ምክር ቤት ከ600 በላይ አባላት እንዳሉት ተገልጿል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ባሻገር የክልል ከተሞች ውስጥ የራሱ የጽሕፈት ቤት ሕንፃ ያለው የአዳማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የድሬዳዋ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በቀድሞ ጊዜ የተወረሰበትን ሕንፃ ለማስመለስ እየንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትም የራሱን ሕንፃ ለመገንባት የሚችልበት ቦታ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲሰጠው ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ከ70 ዓመታት በላይ ዕድሜ ባስቆጠረው የአገሪቱ የንግድ ምክር ቤቶች ታሪክ ውስጥ፣ አብዛኞቹ ምክር ቤቶች የራሳቸውን የጽሕፈት ቤት ሕንፃ መገንባት ሳይችሉ ቆይተዋል፡፡ 

Standard (Image)

የሜትር ታክሲዎችና የትራንስፖርት ባለሥልጣን ፍጥጫ አላባራም

$
0
0

 

‹‹ሳይሞከር እንዴት ነው አያዋጣም የሚባለው?››

ትራንስፖርት ባለሥልጣን

  • ‹‹በማን ኪሳራ ነው የሚሞከርብን?››

የሜትር ታክሲ ማኅበራት                                                                                                                                                                                                                                                                                    መንግሥት ከቀረጥ ነፃ በሰጠው ዕድል አማካይነት ከ1,000 በላይ ሜትር ታክሲዎች አዲስ አበባ ከገቡ መንፈቀ ዓመት አስቆጥረዋል፡፡ ታክሲዎቹን ጨምሮ ከ500 ያላነሱ አውቶቡሶችም በቀረጥ ነፃ እንዲገቡ በመወሰኑ ከ60 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደተመደበም ይታወሳል፡፡

በመሆኑም ቀረጥ ሳይከፈልባቸው በገቡት ታክሲዎች ላይ የታሪፍ አገልግሎት ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል፡፡ እንደውም ከየካቲት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በአስገዳጅነት በወጣላቸው ታሪፍ መሠረት እንዲሠሩ የሚያሳስብ መመርያ ተላልፎ፣ ከገቡት 1163 ያህል ታክሲዎች ለአግልግሎት ብቁ ናቸው በተባሉት 750ዎች ላይ የስምሪት ትዕዛዝ ወጥቶ እንዲሠሩ ተብሏል፡፡ በፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የወጣውን የታሪፍ መመርያ እንዲያስፈጽም ሥልጣን የተሰጠው የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ከወር በፊት መግለጫ ማውጣቱም ይታወሳል፡፡ በመግለጫው መሠረት በወጣው ታርፍ የማይሠሩት ታክሲዎች ላይ ከገንዘብ ቅጣት ጀምሮ እስከ የፈቃድ ንጥቂያ የሚደርሱ ዕርምጃዎች እንደሚወሰዱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል፡፡

ከመነሻው ጀምሮ ተቃውማቸው ሲያሰሙ የከረሙት 26ቱም የሜትር ታክሲ ማኅበራት፣ መንግሥት ያወጣውን ታሪፍ እንዲያስተካክል ሲሞግቱና ሲቃወሙ ቆይተዋል፡፡ ፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ያወጣው ታሪፍ የባለንብረቶቹን ጥያቄ አላገናዘበም፣ አዋጭነትና ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን አርቆ አላየም የሚሉ ትችቶች እየቀረበበት ይገኛል፡፡

በአጨቃጫቂው ታሪፍ መሠረት ለሊፋን ሥሪት 750 ታክሲዎች በኪሎ ሜትር አሥር ብር እንዲሠሩ ተወስኗል፡፡ በአንፃሩ ቶዮታ ሠራሽ አቫንዛ ሞዴል ታክሲዎች በኪሎ ሜትር 13 ብር እንዲሠሩ ተብሏል፡፡ በመሆኑም ታክሲዎቹ ከመንቀሳቀሳቸው በፊት ታሳቢ የሚደረገውን መነሻ ሒሳብ (ለሊፋን አሥር ብር፣ ለአቫንዛ 13 ብር) ታክሎበት፣ ተሳፋሪው የተሳፈረበትን ርቀት ልክ በሚለካው ሶፍትዌር አማካይነት እንዲከፍል ይጠበቅበታል፡፡ ይህም ማለት ሁለት ኪሎ ሜትር የሚጓዝ ተሳፋሪ በሊፋን ታክሲዎች ከሆነ ለተጓዘበት ርቀት 20 ብር እንዲሁም ለመነሻው የተቀመጠውን አሥር ብር አካቶ 30 ብር ይከፍላል ማለት ነው፡፡ የአቫንዛዎቹም በተመሳሳይ ስሌት እንደሚተገበር ተገልጾ ነበር፡፡

ይህ ታሪፍ ግን ከመነሻው ጀምሮ ተቃውሞ እየቀረረበበት ሲሆን፣ ታክሲዎቹም ቢሆኑ እስከቅርብ ጊዜው አስገዳጅ መመርያ ድረስ ከታሪፉ ይልቅ በድርድር መሥራቱን ሲያስቀድሙ ይታዩ ነበር፡፡ አስገዳጁ መመርያ ከወጣ በኋላ ታክሲዎቹ ከጎዳና መጥፋት አብዝተው ከርመዋል፡፡ እስከቅርብ ጊዜ ድረስም በዚሁ አኳኋን ሰነባብተዋል፡፡ ከሰሞኑ ግን በየመንገዱ መታየት ጀምረዋል፡፡ የዚህ ምክንያቱም መንግሥት በተደጋጋሚ የታክሲ ማኅበራቱ የሚያቀርቧቸውን ጥያቄዎች ችላ በማለት መንግሥት የራሱን አቋም በማራመዱ እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል፡፡

ከማኅበራቱ መካከል ሪፖርተር ያነጋገራቸው አዲስ ሜትር ታክሲ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮናስ ሙላቱ እንዲሁም የ‹‹ዚ ሉሲ›› ሜትር ታክሲዎች ማኅበር ኃላፊ አቶ አንተነህ ትሪሎ ተመሳሳይ አቋም አላቸው፡፡ መንግሥት እንዲተገበር ያደረገው አስገዳጅ ታሪፍ የታክሲዎቹን ባለንብረቶች መሠረታዊ ጥያቄዎች ከግምት ያላስገባ እንደሆነ ሁለቱም ይገልጻሉ፡፡ በቅርቡ ለሌላ ጉዳይ በተጠራው ስብሰባም ይኸው የታሪፍ ጉዳይ በታክሲ ባለንብረቶች ተነስቶ አብዛኞቹ ስሜታዊ ሆነው ሲናገሩ እንደነበረ ታውቋል፡፡

ከወር በፊት ሪፖርተር በዚህ ታሪፍ ጉዳይ ላይ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ያነጋገራቸው አቶ አንተነህ እንዲህ ብለው ነበር፡፡ ‹‹በታሪፉ ላይ ቅሬታ ነበረን፡፡ የታሪፍ አሞላሉ ቅሬታ አሳድሮ ነበር፡፡ በተለይ የተሳፋሪው ቆይታ ጊዜ ማለትም በጉዞ ወቅት ወርዶ ጉዳዩን ፈጽሞ የሚመለስ ተሳፋሪ የሚስተናገድበት አሠራር የለውም፡፡ የነዳጅ ታሪፍ ለውጥ ሲኖር፣ በዝናብ ጊዜ፣ እንደ አፍሪካ ኅብረት ያለው ስብሰባ በሚኖርበት ወቅት ለሚፈጠረው የመንገድ መዘጋጋት ምላሽ የሚሰጥ ሥርዓት አልተዘጋጀም፤›› ያሉት አቶ አንተነህ፣ አሠራሩ ከውጭ እንደ መግባቱ መጠን እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን ለማስተናገድ የሚችል መሆን ሲገባው ይህን አላደረገም ብለው ነበር፡፡

ከወር በኋላ ሪፖርተር ዳግም ታክሲዎቹ ስለሚገኙበት ሁኔታ ባደረገው ማጣራት የተለወጠ ነገር እንደሌለ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ መንግሥትም በአቋሙ እንደፀና ሲሆን፣ ታክሲዎቹም በመንግሥት አካሄድና ውሳኔ ላይ ያደረባቸው ቅሬታም አልተነሳም፡፡ በመሆኑም የሁለት ጎራ ሆነው ቀጥለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጅ አቶ ምትኩ አማረ ከዚህ ቀደም በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ ታክሲዎቹ በተወጣላቸው ታሪፍ መሠረት እንዲሠሩ፣ በሥራ ሒደት እየታየም መሻሻል ያለበት ነገር ይሻሻላል ማለታቸው ይታወሳል፡፡ ሆኖም ታክሲዎቹ የወጣው ታሪፍ አያዋጣንም ቢሉም፣ ከአቶ ምትኩ ማብራሪያ ግን ታክሲዎቹ በቀን በአማካይ 120 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ርቀት በመጓዝና በየአቅጣጫው ገደብ ሳይኖርባቸው እንዲሠሩ የሚችሉበት ስሌት መነሻ ተደርጎ በዚሁ ስሌት መሠረት እንዲሠሩ መወሰኑን ጠቅሰው ነበር፡፡ በዚህ ስሌት መሠረት ቢያንስ 75 በመቶውን ርቀት ተሳፋሪ በማጓጓዝ ቢሸፍኑት የቀን ገቢያቸው (የሊፋን ታክሲዎች) ከ750 ብር በላይ ይሆናል ማለት ነው፡፡ 

ይሁንና ይህንን ታሪፍ በመቃወም አነስተኛ ብቻም ሳይሆን ካለብን የባንክ ዕዳ ከመሳሰሉት ወጪዎች አኳያ አያዋጣንም ቢሉም፣ አቶ ምትኩ ግን ‹‹ታሪፉ ያንሳል ይበዛል ለማለት መሞከርና ውጤቱ መታየት አለበት፤›› የሚል አቋም አራምደዋል፡፡ በመሆኑም ‹‹አንድ ነገር ሳይሞከር እንዴት ነው አያዋጣም የሚባለው?›› በማለት የታክሲዎቹን ባለንብረቶች ጥያቄ በጥያቄ አስተናግደዋል፡፡ ይህንን ቢሉም ታሪፉ ወደፊት ማሻሻያ እንደሚደረግበትም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

      ምንም እንኳ የታሪፍ ማሻሻያ ይደረጋል መባሉን አቶ አንተነህ ቢቀበሉትም፣ ‹‹እስከዚያው ግን በወጣው ታሪፍ መሠረት ሥሩ መባላችን በማን ኪሳራ ነው እኛ ላይ የሚሞከረው?›› የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ‹‹ታሪፉ መሞከር ካለበት በተወሰኑ ናሙናዎች ላይ እንጂ 751 ታክሲዎች ላይ መሆኑ አግባብ አይደለም፤›› ያሉት አቶ አንተነህ፣ እንዲህ ያለው አሠራር በርካቶቹን ባለታክሲዎች ህልውና አደጋ ላይ እንደሚጥልም አብራርተዋል፡፡ በርካቶቹ ታክሲዎቹን የገዙት ባለንብረቶች የነበሯቸውን የቀደሙ ታክሲዎች ሸጠው፣ ተበድረውና ተለቅተው በመሆኑ ታሪፉ ከግንዛቤ ያላስገባቸው በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ መንግሥት ሊገነዘብ እንደሚገባው ጠይቀዋል፡፡

      ከዚህ ባሻገር ግን በተጠቃሚዎች ዘንድ የተፈጠረው ብዥታም ላለመግባባት ምክንያት እየሆነ እንደሚገኝ አቶ አንተነህ ገልጸው፣ መንግሥት ታክሲዎቹን በነፃ ያደለ እስሊመስል ድረስ የተዛባ አመለካከት እየተንፀባረቀ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡ ይሁንና መንግሥት ከቀረጥ ነፃ ዕድል ከመስጠቱ ውጭ የታክሲዎቹን የ30 በመቶ ቅድሚያ ክፍያና የ70 በመቶ የባንክ ብድር ዕዳ በመክፈል የታክሲዎቹ ባለቤቶች ግለሰቦቹ እንጂ መንግሥት እንዳልሆነ መታወቅ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ታክሲዎቹ የሚመሩበት የአሠራር ሥርዓት ማኑዋል ባለመዘጋጀቱም የሜትር ታክሲዎች አሠራርና ስምሪት ችግር እንደሚታይበት ገልጸዋል፡፡

      የታሪፉን ጉዳይ በሚመለከት አቶ ዮናስ እንደሚገልጹት በማኅበራቸው በኩል ለመንግሥት ቀርቦ የነበረው ዋጋ ከ20 ብር በላይ እንደነበር፣ ከዚህ በታች ቢደረግ ግን ለታክሲዎቹ የወጣውን ገንዘብ ለመመለስም ሆነ ለባለንብረቶቹ ማስገኘት የሚገባቸውን ጥቅም ሳያስገኙ በኪሳራ ለመሥራት እንደሚያስገድዱ ተገልጾ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

      በጠቅላላው ሜትር ታክሲዎቹ በመንግሥት ታሪፍ ለመሥራት የተገደዱት መንግሥት በ‹‹ጉልበት›› እንዲሠሩ ስላስገደዳቸው እንጂ አዋጭ ሆኖ እንዳልሆነ እየገለጹ ቢሆኑም፣ መንግሥት ወደ ሥራ ግቡ እያለ ይገኛል፡፡ በሁለቱ ወገን አለመግባባት የሜትር ታክሲዎች አገልግሎት እንደታሰበው ሊሆን አልቻለም፡፡ አሁንም ድረስ በርካቶቹ በድርድር ዋጋ ተስማምተው እየሠሩ እንደሚገኙ ታይቷል፡፡ የአቫንዛ ታክሲዎች በወጣው ታሪፍ መሠረት እንዲሠሩ ለማኅበር አባላት መገለጹንና በዚሁ መሠረት እየሠሩ እንደሚገኙ አቶ ዮናስ ቢከራከሩም፣ ተጨባጭ እውነታው ግን ይህን አያሳይም፡፡

      ‹‹የውበት እስረኞች›› የሚል ስያሜ የወጣላቸው የሜትር ታክሲዎች በገቡበት አግባብ  አገልግሎት ሊሰጡ ባለመቻለቻው፣ በመንግሥትና በታክሲዎቹ ባለንብረቶች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት አንዳንድ ማኅበራትን ለባንክ ውዝፍ ዕዳ እንዳበቃቸው እየተነገረ ነው፡፡ ከቀረጥ ነፃ ለገቡት ሁሉም ሜትር ታክሲዎች ብድር ካቀረበው ብርሃን ባንክ መረጃ ለማግኘት የተደረገው ጥረት ባይሳካም፣ የዕዳ ማስጠንቀቂያ የጻፈላቸው ማኅበራት እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡ አንዳንድ ባለንብረቶችም ታክሲዎቹን ባንኩ እንዲረከባቸው እየጠየቁ እንደሚገኙ አቶ አንተነህ ገልጸዋል፡፡

የሳሎን ታክሲዎች ስምሪት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አስተዳደር ወቅት እንደተጀመረ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የታክሲ አገልግሎት ማኅበራቱ በደርግ መንግሥት ወቅት እንዲበተኑ ሲደረግ በርካታ የታክሲ ባለንብረቶችም ተወርሰው ነበር፡፡ በኢሕአዴግ መንግሥት ወቅት የቀደሙት የሥርዓቱ መሥራቾች እንዲፈቀድላቸው በመጠየቅ ተደራጅተው መሥራት እንደጀመሩና በአብዛኛውም በኤርፖርትና በሆቴሎች አካባቢ ሲሠሩ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Standard (Image)

ስምንት ቢሊዮን ብር ገደማ የሚጠይቁ ተጨማሪ መንገዶች ሊገነቡ ነው

$
0
0

 

የቻይና ተቋራጮች አሁንም የበላይነቱን ይዘዋል                                                                                                                                                                                                                                                          የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በ2009 ዓ.ም. እንዲገነቡለት በዕቅድ ከያዛቸው ትላልቅ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ ከ7.98 ቢሊዮን ብር በላይ ይጠይቃሉ የተባሉ የሰባት መንገዶችን የግንባታ ውሎች ከስድስት ኮንትራክተሮች ጋር ተፈራርሟል፡፡ ሰኞ መጋቢት 4 ቀን 2009 ዓ.ም. በባለሥልጣኑ ጽሕፈት ቤት ስምምነት የተፈጸመባቸው እነዚህ ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ 468 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያላቸውና ሁሉም በአስፓልት ኮንክሪት ደረጃ እንደሚገነቡ ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡

ከሰባቱ ፕሮጀክቶች አምስቱን አራት የቻይና ተቋራጮች ሲረከቡ፣ ሁለቱን ደግሞ የአገር ውስጥ ተቋራጮች አግኝተዋል፡፡ መንገዶችን ለመገንባት በጨረታ አሸናፊ መሆናቸው ተገልጾ ስምምነት ያደረጉት የቻይና ኩባንያዎች፣ ቻይና ሬል ዌይ ቁጥር ሦስት፣ ቻይና ኮንስትራክሽንና ኮሙዩኒኬሽንስ ኩባንያ (ሲሲሲሲ)፣ ቻይና ውይ ኢንተርናሽናልና ሲጂሲኦሲ ግሩፕ ኩባንያ ሊሚትድ የተባሉ ተቋራጮች ናቸው፡፡ እነዚህ አራት ተቋራጮች በጠቅላላው የተረከቧቸው ፕሮጀክቶች ከ4.2 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው አምስት የመንገድ ግንባታዎች ናቸው፡፡ ሰንሻይንና ገምሹ በየነ የተባሉት ሁለት አገር በቀል ተቋራጮችም የ3.7 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ሁለት መንገዶችን ለመገንባት የሚያስችሏቸውን ስምምነቶች ፈርመዋል፡፡

የቻይና ሬልዌይ የ1.65 ቢሊዮን ብር መንገድ

ሰኞ መጋቢት 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ከተፈረሙት ሰባት የመንገድ ግንባታ ስምምነቶች ውስጥ ሁለቱን ፕሮጀክቶች ለመገንባት የተስማማው ቻይና ሬልዌይ ቁጥር ሦስት ኢንጂነሪንግ ኩባንያ የቻይና ተቋራጭ ነው፡፡

ቻይና ሬል ዌይ ቁጥር ሦስት፣ በጨረታ አሸናፊ ሆኖ ግንባታቸውን ለማከናወን ከተረከባቸው ሁለት መንገዶች አንዱ የጭኮ-ይርጋ ጨፌ 60 ኪሎ ሜትር መንገድ ፕሮጀክት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ 58 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የሙከጡሪ-ኮከብ መስክ መንገድ ነው፡፡ የጭኮ-ይርጋ ጨፌ መንገድን ለመገንባት የተስማማበት ዋጋ 889 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ የሙከጡሪ-ኮከብ መስክ መንገድን ለመገንባት ውለታ የፈጸመበት ዋጋም 768.6 ሚሊዮን ብር መሆኑ ታውቋል፡፡ ተቋራጩ ሁለቱን መንገዶች እንዲገነባ በጠቅላላው ከ1.65 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ይከፈለዋል ማለት ነው፡፡

ቻይና ሬል ዌይ ቁጥር ሦስት ከሚገነባቸው መንገዶች አንዱ የሆነው የጭኮ-ይርጋ ጨፌ መንገድ ግንባታ ሥራ በልዩ ሁኔታ እንደሚታይ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ግርማይ በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል፡፡

መንገዱ ከሌሎቹ ግንባታዎች የሚለይበት ዋነኛ ምክንያትም 10,288 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውንና ትራንስ አፍሪካን ሃይ ዌይ ኔትወርክ ተብሎ የሚጠራው ፕሮጀክት የሚያስተሳስራቸው የተለያዩ አገሮችን የሚያቋርጠው ግዙፍ የመንገድ ፕሮጀክት አካል በመሆኑ ነው፡፡

የጭኮና ይርጋ ጨፌ ከተሞችን ከማገናኘት ባሻገር ድንበር ዘለል ጠቀሜታ እንዳለው የተገለጸው ይህ ፕሮጀክት፣ የሞምባሳ-አዲስ አበባ ኮሪደር እንደመሆኑ መጠንም ኢትዮጵያ ላሙ እየተባለ የሚጠራውንና የምሥራቅ አፍሪካ አገሮችን የሚያገናኘውን የወደብ ፕሮጀክት በአማራጭነት ለመጠቀም እንዲያስችላት ለያዘችው ዕቅድ ተግባራዊነት፣ ዋነኛው የመሠረተ ልማት አካል ሆኖ እንደሚያገለግል የዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡

ይህ መንገድ በኬንያና በኢትዮጵያ መካከል ለሚኖረው ድንበር ተሻጋሪ የንግድ ልውውጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የተገለጸ ሲሆን፣ ከኬንያ ባሻገር ወደ ደቡብ አፍሪካዋ ኬፕታውን፣ ከኢትዮጵያ ወደ ግብፅ ከተማ ካይሮ ከሚዘልቀው መንገድ ጋር እንደሚያስተሳስር የሚጠበቅ ነው፡፡

ትራንስ አፍሪካ ሃይ ዌይ ኔትወርክ የተባለው የመንገድ መሠረተ ልማት ፕሮጀክት፣ ከሰሜንያዊቷ ካይሮ በመነሳት ወደ በደቡባዊቷ ኬፕታውን ከተማ የሚዘልቅ ሲሆን፣ መንገዱ የሚያልፍባቸው አገሮች በየራሳቸው በኩል የሚኖረውን የመንገድ ድርሻ በመገንባት ግዙፉን ፕሮጀክት እውን እንደሚያደርጉት ይታሰባል፡፡ ኢትዮጵያም ከትራንስ አፍሪካ ሃይ ዌይ ኔትወርክ ጋር የሚገናኘውን የመንገድ መስመር እንድትሠራ ከሚጠበቅባት መካከል አንዱ ይኼው የጭኮ-ይርጋ ጨፌ መንገድ ነው፡፡ የሰሜን፣ የምሥራቅና የደቡብ አፍሪካ አገሮችን የንግድ ልውውጥ ለማቀላጠፍ ይረዳል የተባለው የዚህ ግዙፍ ኔትወርክ አካል የሆነው የጭኮ-ይርጋ ጨፌ የመንገድ ፕሮጀክት ግን፣ አሁን ለቻይና ኮንትራክተር ከመሰጠቱ በፊት ሃዋክ ኢንተርናሽናል በተባለ ተቋራጭ ግንባታው ሲካሄድ የቆየ ነበር፡፡

በዚሁ መሠረትም የመንገዱ ግንባታ ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ ሲጠበቅ፣ ሃዋክ ፕሮጀክቱን አጓቷል በሚል ከኮንትራክተሩ ጋር የነበረውን ውል አቋርጦ ሥራው ቆሞ የነበረ ፕሮጀክት ነው፡፡ ከሃዋክ ኩባንያ ጋር የነበረው ስምምነት እስኪቋረጥ ድረስ ከ60 ኪሎ ሜትሩ ውስጥ 45 በመቶ የሚሆነው የመንገድ ሥራ ግንባታ መከናወኑ እንደተገለጸ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ በሦስት ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረውን የጭኮ-ይርጋ ጨፌ መንገድን ለመገንባት ሃዋክ የተረከበበት የግንባታ ዋጋ 700 ሚሊዮን ብር እንደነበርም ይታወሳል፡፡ ይሁንና ሃዋክ ሳያጠናቅቅ የቀረውን ሥራ ለመጨረስ ቻይና ሬል ዌይ ቁጥር ሦስት አሸናፊ የሆነበት ገንዘብ መጠን 889 ሚሊዮን ብር መሆኑ ፕሮጀክቱ ከታሰበለት በላይ በእጥፍ ወጪ ከመጠየቁም ባሻገር ተጨማሪ ጊዜ መጠየቁን ያመላክታል፡፡

በሰኞው ስምምነት ወቅት እንደተገለጸው ይኸው የቻይና ተቋራጭ ቀሪውን ግንባታ በ22 ወራት ውስጥ ማጠናቀቅ ይጠበቅበታል፡፡ ይህም ሆኖ ፕሮጀክቱ አሁን በተደረሰው ስምምነት መሠረት የሚጠናቀቅ ከሆነ፣ በጠቅላላው ከሰባት ዓመታት በላይ ይፈጃል ማለት ነው፡፡ የፕሮጀክቱ ወጪ የሚሸፈነው የአፍሪካ ልማት ባንክ በሰጠው ብድርና በኢትዮጵያ መንግሥት በጀት እንደሆነም ታውቋል፡፡

የሲጂሲኦሲ ግሩፕ የ999.3 ሚሊዮን ብር መንገድ

ሲጂሲኦሲ ግሩፕ የተረከበው የመንገድ ሥራ ከፊንጫአ-መነቤኛ-ሻምቡ (ኮንትራት ሁለት) የተሰኘውን የመንገድ ፕሮጀክት ሲሆን፣ 65.5 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለውን ይህንን መንገድ እንዲገነባ የተዋዋለበት ዋጋ 999.3 ሚሊዮን ብር መሆኑ ተገልጿል፡፡ ይህ ተቋራጭ ከዚህ የመንገድ ሥራ ባሻገር በእጁ ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው  ፕሮጀክቶችም ይገኛሉ፡፡ የመነቤኛ-ሻምቡ መንገድን ለመገንባት የተረከበው ዋጋ 4.58 ቢሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡ 

የሲሲሲሲ የ1.06 ቢሊዮን ብር መንገድ

በኢትዮጵያ የመንገድ ግንባታ ሥራ ውስጥ በርካታ ፕሮጀክቶችን በመረከብ ከሚጠቀሱ የቻይና ተቋራጮች በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ቻይና ኮንስትራክሽን ኮሙዩኒኬሽንስ ኩባንያ (ሲሲሲሲ) ነው፡፡ ይህ ኩባንያ ከመንገድ ግንባታ ባሻገር በሌሎች ግንባታ መስኮችም በቢሊዮኖች ብሮች የሚገመቱ ፕሮጀክቶችን የገነባና አሁንም በመገንባት ላይ የሚገኝ ነው፡፡

ተቋራጩ በይበልጥ የሚታወቅበት የመንገድ ሥራ የአዲስ አበባ የፍጥነት መንገድ ሲሆን፣ ከዚህ መንገድ ጋር የሚያያዙና ወደ አዲስ አበባ የሚዘልቁ ሁለት መንገዶችን መገንባቱም ይታወሳል፡፡ በቅርቡም ከቃሊቲ ቂሊንጦ ሁለት ኮሪደሮች ያሏቸውን መንገዶች በ4.7 ቢሊዮን ብር በላይ ለመገንባት የሚያስችለውን ስምምነት አድርጓል፡፡

ኩባንያው የተረከባቸው ፕሮጀክቶች ከ23 ቢሊዮን ብር ብላይ ወጪ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ ከኢትዮጵያ የመንገዶች ባለሥልጣን ብቻ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው አራት የመንገድ ፕሮጀክቶች በእጁ ይገኛሉ፡፡

በተጨማሪም ከጅግጅጋ ገለልሽ-ደገህመዶ-ሰገግ ያለውን 55.4 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመገንባት ከትናንት በስቲያ አዲስ ውል ፈጽሟል፡፡ መንገዱንም በ1.06 ቢሊዮን ብር እንደሚገነባው ተገልጿል፡፡ ይህ ተቋራጭ በዚህ በጀት ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ የተረከበው ፕሮጀክት መሆኑ ነው፡፡

የቻይና ውይ ኢንተርናሽናል የ1.68 ቢሊዮን ብር መንገድ

 ከተፈረሙት የመንገድ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ዋጋ ያለውን የመንገድ ፕሮጀክት በመውሰድ ውለታ የፈጸመው ሌላኛው የቻይና ኩባንያ ቻይና ውይ ኢንተርናሽናል የተባለው ተቋራጭ ነው፡፡ ተቋራጩ ስምምነት የፈጸመበት የመንገድ ፕሮጀክት ከየደዬ-ጪሪ-ናንሰቦ ድረስ ያለውን መንገድ ለመገንባት ሲሆን፣ መንገዱ 73.35 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ነው፡፡

ቀደም ሲል በጠጠር ደረጃ የነበረው ይህ መንገድ፣ የ10 እና የ12 ሜትር ስፋት ያለው ትከሻ ይኖረዋል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ይህ መንገድ ቻይና ውይ በ2009 በጀት ዓመት የፈረመው ሁለተኛው የግንባታ ስምምነት ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የመንገድ ግንባታ ሥራ ውስጥ መሳተፍ የጀመረውም በዚህ በጀት ዓመት እንደሆነ ታውቋል፡፡

ተቋራጮችን በተመለከተ ዋና ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፣ ገምሹ በየነ፣ ሰንሻይን፣ ሲሲሲሲ፣ ቻይና ሬል ዌይ ቁጥር ሦስት እንዲሁም ሲጂሲኦሲ ግሩፕ ከዚህ ቀደም የተለያዩ መንገዶችን ገንብተው አስረክበዋል፡፡ ቻይና ውይ የተባለው ተቋራጭ የመጀመሪያው ቢሆንም፣ በሌሎች አገሮች ውስጥ ባከናወናቸው ሥራዎች በቂ ልምድ እንዳለው በጨረታ ግምገማ መታየቱን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ 

የገምሹ በየነ የ1.28 ቢሊዮን ብር መንገድ

ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን በበጀት ዓመቱ ሁለተኛ የሆነውን የመንገድ ግንባታ ለማከናወን የሚያስችለውን ዕድል አግኝቷል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ከትናንት በስቲያ ከፈረማቸው ሰባት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ የሆነውን የዓለም ከተማ-ደጎሎ ኮንት መንገድ ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን በ1.28 ቢሊዮን ብር ለመገንባት ተፈራርሟል፡፡ 85 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን ይህንን መንገድ ለመገንባት የሚያስፈልገው ወጪ በኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚሸፈንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

የዓለም ከተማ-ደጎሎ ኮንት የመንገድ ፕሮጀክት በ36 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለ ሲሆን፣ መንገዱ የ10፣ የ12 እና የ14 ሜትር ትከሻ ኖሮት የሚገነባ ነው፡፡ በርካታ ፉካዎችና ሰባት አነስተኛ ድልድዮችም አካቶ እንደሚገነባ ባለሥልጣኑ ገልጿል፡፡ ተቋራጩ ከአንድ ወር በፊት የወንጪ ካቺሌ-ጨለቲ መንገድን በ846.2 ሚሊዮን ብር ለመገንባት ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል፡፡

የሰንሻይን የ1.29 ቢሊዮን ብር መንገድ

ከአገር ውስጥ ተቋራጮች የመንገድ ግንባታ ውል የፈረመው ሰንሻይን ኮንስትራክሽን በጨረታ የተረከበው ከደጎሎ-ከላላ ኮንት (ሁለት) መንገድን ለመገንባት ነው፡፡ ይህ የመንገድ ፕሮጀክት 71 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለውን ሲሆን፣ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን መንገዱን ለመገንባት ውለታ የፈረመበት ዋጋ 1.29 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ በ36 ወራት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለው ይህ የመንገድ ግንባታ ወጪ የሚሸፈነው በኢትዮጵያ መንግሥት እንደሆነ ተገልጿል፡፡  

ስምምነቶቹን የተፈራረሙት በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በኩል አቶ አርዓያ ግርማይ ናቸው፡፡ በኮንትራክተሮቹ በኩል ሚስተር ዡ ዮንግ ሸንግ የሲሲሲሲ ሥራ አስኪያጅ፣ ሚስተር ታአ ቦ የቻይና ሬል ዌይ ቁጥር ሦስት ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ፣ በቻይና ውይ ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ በኩል የሥራ ተቋራጩ ተወካይ ሚኒስተር ካይ ሃዩሎንግ፣ አቶ ሳሙኤል ታፈሰ የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ፣ አቶ ገምሹ በየነ የገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም በሲጂሲኦሲ በኩል ሚስተር ጋዎ ሊ ናቸው፡፡ 

 

           

 

Standard (Image)

‹‹የውኃ ታሪፍን ለመጨመር የተሻለ አገልግሎት መስጠት የግድ ይላል››

$
0
0

 

አቶ ዋና ዋኬ፣ የውኃ ሀብት ልማት ፈንድ ዋና ዳይሬክተር

አቶ ዋና ዋኬ በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነት ቦታዎች ለዓመታት አግልግለዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት የውኃ ሀብት ልማት ፈንድ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ከመሾማቸው ቀድሞ ለስምንት ዓመታት ያህል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ነበሩ፡፡ አባል ብቻም ሳይሆኑ በበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢነት ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከአውሮፓ ኅብረት፣ ከፈረንሣይና ከጣልያን መንግሥታት የተገኘውን የ75 ሚሊዮን ዩሮ ብድር (በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በኩል የተገኘ) መነሻ በማድረግ ለዓመታት ተስተጓጉሎ የቆየውንና የ15ቱ ከተሞች የውኃ ፕሮጀክት በመባል የሚታወቀውን ፕሮጀክት በስምንት ከተሞች አማካይነት ዳር ለማድረስ የሚመሩት የውኃ ልማት ፈንድ የብድር ስምምነት አድርጎ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከ15 ከተሞች ስምንት ብቻ የሆኑት ከ75 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ የቀሪዎቹ ሰባት ከተሞች በአማራ ክልል በጀት የፕሮጀክት ወጪያቸው ተሸፍኗል፡፡ ለስምንት ከተሞች ተቋሙ የ189 ሚሊዮን ብር ብድር እንዲያገኙ በማድረግ፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የመጠጥ ውኃ ለሕዝብ ማድረስ እንዲጀምሩ ስምምነት ተደርጓል፡፡ ከዚህም ባሻገር መንግሥት ከዓለም ባንክ የሚያገኘው የ450 ሚሊዮን ዶላር ብድር በአብዛኛው ለከተሞች የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ እንደሚውል አቶ ዋና ከሪፖርተር ጋር ከጥቂት ሳምንታት በፊት ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል፡፡ ተቋሙ ለከተሞች ከሚያቀርበው ብድር ምን ያህል ወለድ እንደሚያገኝ፣ የብድር መክፊያ ጊዜ፣ ፕሮጀክቶች በምን መመዘኛ ተቀባይነት እንደሚያገኙና በሌሎችም ነጥቦች ላይ ብርሃኑ ፈቃደ ከውኃ ልማት ፈንድ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዋና ዋኬ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- የውኃ ልማት ፈንድ ለከተሞች የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶችን የሚደግፍ ነው፡፡ ዋና ዋና ሥራዎቹ ምንድን ናቸው?

አቶ ዋና፡- የውኃ ልማት ፈንድ ከ15 ዓመታት በፊት የውኃ ዘርፍ አስተዳደር ፖሊሲ ወጥቶለት ነበር፡፡ የሚገነቡት መሠረተ ልማቶች የወጣባቸውን ዋጋ በማስመለስ መርህ ላይ ተመሥርቶ እንዲሠራ የሚል እሳቤ ተይዞ የውኃ ልማት ፈንዱ ተመሥርቷል፡፡ ይኼ ለምን ይጠቅማል? ካልን አንደኛው ለከተማውም ሆነ ለገጠሩም እንዲህ ያለው ሰፊ ፍላጎት ያለበትን ኢንቨስትመንት በነፃ ማቅረቡ ይሻላል ወይስ ከአንዱ የከተማ ፕሮጀክት በኋላ ሌሎች ባዷቸውን የሰነበቱ፣ የውኃ አቅርቦት ችግር ያልተቀረፈላቸው በተራቸው እንዲጠቀሙ ለማድረግ ዋጋ በማስመለስ መሥራት ይሻላል የሚለውን መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ከዚሁ ጎን ከውጭ በሚመጡ ብድርና ዕርዳታዎች ላይም ከምናማትር በራስ ወጪ ፕሮጀክቶችን እየገነባን ለመቀጠል በማሰብ ነው ፈንዱ የተቋቋመው፡፡ ከውጭ የሚመጡ ብድሮች ወይም ዕርዳታዎች እንደየሰጪዎቻቸው ከበስተኋላቸው የሚመጡ የተለያዩ ፍላጎቶችን ይዘው የሚመጡ ናቸው፡፡ የከተሞች መስፋፋት በጣም እየጨመረ መጥቷል፡፡ ገጠር የነበሩ አካባቢዎች ከተማ እየሆኑ በመምጣታቸው የውኃ አቅርቦት ፍላጎት እየጨመረ ነው፡፡ ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ ይገኛሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ለውጦችን ለማዳረስ በውጭ ብድር ብቻ የሚዘለቅ ስላልሆነ የራሳችን ፈንድ ብናቋቁም ግን ለእነዚህ ጥያቄዎች በተሻለ ፍጥነት መድረስ የምንችልበትን አቅም ይሰጠናል፡፡

ሪፖርተር፡- ፈንዱ ለከተሞች የሚሰጠው ብድር በምን መልኩ ነው ተመላሽ የሚደረገው?

አቶ ዋና፡-የፈንዱ የወጪ ማስመለስ አሠራር ሙሉ በሙሉ ተመላሽ ማድረግ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ለመሠረተ ልማቶች ዝርግታ የሚወጣው ወጪ ሙሉ በሙሉ ተመላሽ ማድረግ ቢባልም እስካሁን ገና አልጀመርንም፡፡ በከፊል ነው እያስመለስን የምንገኘው፡፡ ሌላው ከተጠቃሚ ከተሞች፣ ከክልሎቻቸው ወይም ከከተማ አስተዳደሮች ወይም ከውኃ አገልግሎቶች የሚዋጣ ገንዘብ እያጋጨን በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡ ስለዚህ የሚመለሰው ከእኛ በብድር የሚሄደው መጠን ነው ማለት ነው፡፡ የሚሄደው ገንዘብ ግን የዕርዳታ ክፍልም አለው፡፡ እኛ እንዲመለስልን የምጠይቀው ግን የብድሩን ክፍል ብቻ ነው፡፡ የከተሞች ውኃ አገልግልቶች በምንፈልገው ብቃት ደረጃ ላይ አለመገኘታቸው አንዱ ትልቅ ችግር ነው፡፡ በሙሉ ኃይላቸው ተጠቅመው አገልግሎቱን ለሚፈልገው ሕዝብ የማዳረስ ሥራና አቅም በታሰበው ጊዜ ውስጥ የማቅረብ ሒደት ችግር ይታይበታል፡፡ ይኽም የሰው ኃይሉ ላይ የሚታይ ነው፡፡ አሁን ያለውን ዘመናዊ ማኅበረሰብና ፈጣን የውኃ አቅርቦት ጥያቄን የሚያስተናግዱ፣ በቂ ዕውቀትና ክህሎት ኖሯቸው የውኃ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች የማይገኙበት አጋጣሚ ይበዛል፡፡ ስለዚህ ይኼ አንዱ የጉዳት አካባቢ ነው፡፡ ከክልሎች ጋርም የምንነጋገርበት ርዕስ ነው፡፡ የውኃ መሐንዲሶች ያስፈልጋሉ፡፡ የውኃ ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ሶሺዮ ኢኮኖሚስቶች ያስፈልጋሉ፡፡ ዘመናዊ የሒሳብ አያያዝ ሥርዓትን የሚተገብሩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የደገፈ አሠራሮች ያስፈልጋሉ፡፡ የተሟላ መዋቅር ሊኖር ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ ጉድለት አለ፡፡ የተሻለ የአሠራር ሥርዓት ያልተዘጋላቸው አካባቢዎች አሉ፡፡ በአብዛኛው ከውኃ መዋቅሩ ጋር የጠበቀ ግንኙነት የሌላቸው ናቸው፡፡ ከከተማ መዋቅሩም ጋር ቢሆን የአሠራር አለመጣጣም የሚታይባቸው፣ ለእያንዳንዱ የሚሠሯቸው ሥራዎች የሕጎችን መጣጣም ለማስፈን ዕውቀት ያላቸውን ሰዎች የመጠቀም ችግር ይታይባቸዋል፡፡ የሰው ኃይል ፍልሰትም ችግር እየሆነ ቆይቷል፡፡ ፕሮጀክቶች ሲጠኑ ጀምሮ የነበሩ ሰዎች ወደ ተግባር ሊገባ ሲል ይለቃሉ፡፡ በአሁኑ አሠራር ግን መላ አስቀምጠናል፡፡ እነዚህ ክፍቶች ባሉበት ወደ ሥራ እየተገባ ችግሮች ይታያሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ዋጋ ወደ ማስመለሱ ሥራ እየገባን ያለነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፡፡ ወደዚህ አስተሳሰብ መሻገር መቻል ትልቅ ዕመርታ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም በሰው ውስጥ ያለው አስተሳሰብ ዕርዳታ ላይ የተመረኮዘ በመሆኑ፣ ብድርና ብድርን በመመለስ ሥራ ላይ ሲተኮር ፈንዱን ለሌሎች አካባቢዎችም እንዲውል ለማድረግ ያስችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ብድር የሚሰጥበት የወለድ ምጣኔ ምን ይመስላል? የሚመለስበት አሠራርስ እንዴት ነው የሚተገበረው?

አቶ ዋና፡- ብድር ሲባል ውኃ ልማት ፈንድ በዓመት ከሦስት በመቶ ያልበለጠ ወለድ በማስከፈል የሚሰጠው ነው፡፡ ይህ ግን የራሱን አስተዳደራዊ ወጪ እንኳ የማይተካ ነው፡፡ በዋጋ ንረት ገንዘቡ የሚያጣውን የመሸመት አቅም እንኳ አይተካም፡፡ የሚሰጠው ብድርም ከ25 እስከ 40 ዓመታት ባሉት ጊዜያት ውስጥ የሚከፈል ነው፡፡ ስለዚህ ብድር ሊባል የሚችል ገንዘብ አይደለም የምንሰጠው፡፡ ይልቁንም ከተሞች ከውኃው አቅርቦት የሚገኘውን ጥቅም አጣጥመው ሲሄዱ ትልቅ የኢኮኖሚ ለውጥ ስለሚኖር የምንሰጣቸውን ገንዘብ ለመተካት ምንም አይቸግራቸውም፡፡ ከዚህ ቀደም ያጋጥመን የነበረው ችግር ብድር ስንሰጥ አመላለሱን ለማረጋገጥ የሚያስቸለን አሠራር አልነበረም፡፡ ይህ ተቋም እንደ ንግድ ባንኮች የሚታይ ቢሆንም የብድር ማስያዣ አይጠይቅም፡፡ ከዚህ ቀደም በእምነት ላይ ተመሥርቶ የሚሰጠው ብድር አሁን ግን በክልሎች ዋስትና እየተገባበት መሰጠት ተጀምሯል፡፡ ክልሎች ተጠያቂነት እንዳለባቸው አውቀው፣ ሕዝቦቻቸውን ውኃ የማጠጣት ኃላፊነት እንዳለባቸው አውቀው ክትትል እንዲያደርጉ የሚያግዝ ነው፡፡ ከተሞቹ የወሰዱትን ብድር መመለስ በሚያቅታቸው ወቅትም ክልሎች እንዲያግዟቸው ከበጀታቸው የመተካት አሠራር እንዲኖር ለማድረግ የሚረዳ አሠራር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ክልሎች ለከተሞች ዋስትና መግባታቸው ብድር እንዲመለስ የሚረዳ ነው ከተባለ ዋስትናው እንዴት ያለ ነው?

አቶ ዋና፡-ክልሎች የሚገቡት ዋስትና የሰነድ ዋስትና ነው፡፡ የሰነድ ግዴታ ነው፡፡ ብድሩ እንዲመለስ የሚያስችል ትኩረት እንዲሰጡ፣ እንዲከታተሉ ለማድረግ በማሰብ እንጂ የማቴሪያል ወይም የገንዘብ ዋስትና አይደለም የሚጠየቁት፡፡ ቢያንስ በሥነ ልቦና ደረጃ ይህ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል ኃላፊነትን ለመጫር እንጂ እንደ ባንኮች የብድር አከፋፈል በሚዛነፍበት ጊዜ ማስያዣ የተደረገውን ንብረት ወደ ገንዘብ የመለወጥ አሠራር የለንም፡፡

ሪፖርተር፡- እንግዲህ የውኃ አቅርቦት ሥራዎች በምትሰጡት ብድር የሚከናወኑ ከሆኑ የታሪፍ ለውጥም ይኖራል ማለት ነው፡፡ ይህ አንዴት ነው የሚስተናገደው?

አቶ ዋና፡-ውኃ እንዲሁ በተፈጥሮ የሚገኝ በመሆኑ ሊከፈልበት አይገባም፤ ማኅበራዊ የወል ሀብት ነው የሚል አስተሳሰብ የሚያራምዱ አሉ፡፡ ውኃ የተፈጥሮ ፀጋ መሆኑ ትክክል ነው፡፡ ማልማቱ ግን ውድ ነው፡፡ የልማት ወጪው ከፍተኛ ነው፡፡ ውኃውን በተሻለ አገልግሎት ሰዎች በሚፈልጉት ልክ ለማቅረብ የተሻለ መክፈል ይኖርብናል፡፡ የተሻሻለ አገልግሎት የሚሰጥ መዋቅር መኖር አለበት፡፡ ችግር ሲፈጠር ወዲያኑ መፍታት የሚችል መዋቅር ካለ፣ አመልክተህ ወዲያው ምላሽ የምታገኝበት አሠራር መኖሩ ግድ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ የተሻለ አገልግሎት ሲኖር የተሻለ ክፍያ መኖሩ ግድ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ግን ታሪፍ መከለስ ይኖርብናል፡፡ በአብዛኛው በየሁለት ዓመቱ ታሪፍ መከለስ አለበት ይባላል፡፡ የዕቃ ዋጋ ይጨምራል፡፡ የሰው ኃይል፣ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ መሠረተ ልማት መስፋፋት ሲኖር ይህንን ሁሉ የሚመጥን የውኃ መስመሮች ዝርጋታ መስፋፋት ሲኖር ተጨማሪ ወጪ ስለሚመጣ ተጨማሪ መክፈል ይጠበቃል፡፡ ለውኃ የሚከፈል ወጪ ለሕይወት የሚከፈል በመሆኑ ዋጋ ያንሰዋል የሚል አመለካከት አለ፡፡ በሕዝቡም ዘንድ ይህ አስተሳሰብ አለ፡፡ ጭማሪ መኖሩ መደበኛ እንጂ እንደ ችግር የሚታይ አይደለም፡፡ የተሻለ አገልግሎት ሳይሰጥ ታሪፍ ብትጨምር ግን ትክክል አይሆንም፡፡ ይህ የመልካም አስተዳደር ጥያቄን ያመጣል፡፡ የውኃ ታሪፍ ለመጨመር የተሻለ አገልግሎት መስጠት የግድ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በብድር አመላለስ ወቅት የማፈግፈግ ችግር አያጋጥማችሁም? ብድር ስትሰጡ አንደኛው መመዘኛችሁ አዋጭ ፕሮጀክት መሆኑን ማጣራት ነው፡፡ ይህንን ስታደርጉ በሌላ በኩል ይዛችሁ የተነሳችሁት ዓላማ ንፁህ የመጠጥ ውኃን ለሁሉም ማዳረስ የሚል በመሆኑ እንዴት ነው እነዚህን የምታስማሙት?

አቶ ዋና፡-የማፈግፈግ ሁኔታ የምርጫ ጉዳይ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ ከተሞች በራሳቸው በቂ አቅም ኖሯቸው እነዚህን ሥራዎች መሥራት ከቻሉ እሰየው ነው፡፡ በከተሞች የሚዘረጉ መዋቅሮችን መዘርጋት ቀርቶ የተበላሹ መስመሮችን መጠገን ፈተና እየሆነባቸው ፈስሶ የሚባክነው ውኃ ብዙ እኮ ነው፡፡ ከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ዕውቅና የሰጣቸው 1,000 ያህል ከተሞች አሉ፡፡ በተለያየ የከተማ ደረጃ የሚመደቡ ናቸው፡፡ በማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲም የተለዩ ከ900 በላይ ከተሞች አሉ፡፡ ይህ እንግዲህ ከሁለት ወይም ሦስት ዓመት በፊት የነበረ መረጃ ነው፡፡ ከተሞች በተለያየ ብቃትና ደረጃ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው፣ ብቃትና አቅሙ የሌላቸው ከተሞች ከውኃ አቅርቦት ችግራቸው እንዲወጡ የሚያስላቸውን የፋይናንስ ድጋፍ እናቀርባለን፡፡ ነገር ግን ከውኃ ችግራቸው ከወጡ በኋላ ከሌሎች ችግሮቻቸው የመውጣት ዕድላቸው ሰፊ ይሆናል፡፡ የውኃ አቅርቦት ንግድ እንዲስፋፋ ይረዳል፡፡ አገልግሎቶች እንዲበራከቱ ፋብሪካዎች እንዲበዙ ይረዳል፡፡ ከሻይ ቤት ጀምሮ ትልልቅ የንግድ እንቅስቃሴዎች እንዲፈጠሩ ያግዛል፡፡ እዚህ የተስፋፋ እንቅስቃሴ የተፈጠረላቸው ከተሞች የተሻለ ገቢ ማግኘታቸው ስለማይቀር፣ ከዚህ ገቢያቸው ላይ ብድር መክፈል ብዙም ከባድ አይሆንም፡፡ ለመበደር ፕሮጀክት አጥንተው የማይጠይቁ ከተሞችን ተበደሩ ብለን አናስገድድም፡፡ ፕሮጀክት አጥንተው፣ የከተማውን ሁኔታና የውኃ ምንጭ መገኛ መኖሩ፣ ዋጋውስ ምን ያህል ወጪ ይጠይቃል? ከየትኛው የገንዘብ ምንጭ ብድሩ መከፈል ይችላል? ታሪፍስ መቼ ነው የሚከለሰው? በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ምን ያህል ደንበኞች ይኖራሉ? ምን ያህል የውኃ ቆጣሪዎች ይኖራሉ? ምን ያህል የጋራ የቦኖ ውኃ አቅርቦቶች ይኖራሉ? የሚሉት ሁሉ በፕሮጀክት ጥናት ሰነድ ውስጥ ከቢዝነስ ፕላን ጋር አብሮ ተካቶ ለብድር ጥያቄው ይቀርባል፡፡ በዚህ መሠረት ፈቃደኛ ሆነው ገንዘቡን ለመመለስ የሚችሉበት አስተማማኝ ምንጭ እንዳላቸው፣ የሚያቀርቡት ውኃም በጥራቱና ለሰው ልጅ ጤና አስተማማኝ መሆኑ የመሳሰሉትን የሚያካትት ትልቅ የጥናት ሰነድ አካተው ሲያቀርቡና የብድር ማመልከቻ ሲያስገቡ እኛም ጥያቄውን መመልከት እንጀምራለን፡፡ አንዱ ከተማ ውኃ አግኝቶ ሌላውም እንዲደርሰው ለማድረግ በማሰብ ነው በብድር የሚሠራው፡፡ ለልማት ሲባል ችለን የምናልፋቸው ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡ የማይመለስ የተበላሸ ብድር ይኖራል፡፡ ለምሳሌ መንግሥት ለልማት ሲል ከ70 እስከ 80 በመቶ ብድር በማቅረብ ቀሪዋን እንዲያወጡ በማድረግ ባለሀብቶችን ወደ ልማት ያስገባል፡፡ ይሁንና አደጋዎች አሉበት፡፡ ሕልም ተፈርቶ ሳይተኛ እንደማይታደረው ሁሉ አደጋውን ለመቀነስ ስልት ታበጃለህ እንጂ ብድር ላይመለስ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች ይኖራሉ፡፡ ወደፊት ሥራው እየተስፋፋ ሲመጣም አደጋውም ሊጨምር ይችላል፡፡ ይሁንና የሕግ ማሻሻያ እንዲደረግልን ለመጠየቅ አስበናል፡፡ የምንሰጠው ብድር አነስተኛና ተዘዋዋሪ ነው፡፡  ለሁሉም ለማዳረስ እንዲቻል፣ ላልደረሳቸው እንዲደርስ ለማድረግ ግን ተጠቃሚዎች ማገዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በራሳቸው ብቃት ማነስና ድክመት ገንዘቡን አጥፍተው ቁጭ የሚሉ ከሆነም ከክልሉ በጀት ተቀንሶ ለውኃ ልማት ፈንድ እንዲውል ለማድረግ የሚያስችል የሕግ አሠራር እንዲኖር ለማድረግ አስበናል፡፡ ይህ ሲሆን ለሁሉም ክልሎች እያዳረስን እንድንሄድ ሊረዳን ይችላል፡፡ ፍላጎት በጣም እየጨመረ ነው፡፡ ለ20 ዓመታት ታስቦ የተሠራው ሳይታሰብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያልቅና ተጨማሪ መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ለማሟላት ፈንድ መኖር አለበት፡፡ ኢትዮጵያ የከፍተኛ ብድር ዕዳ ጫና ካለባቸው አገሮች ተርታ ወጥታለች፡፡ ይህ በመሆኑም በአብዛኛው የብድር ምንጫችን ኮሜሪሺያል አበዳሪዎች እየሆኑ ነው፡፡ ከወለድ፣ ከዕፎይታና ብድር ከመመለሻ ጊዜ አኳያ ይህ ለእኛ ከባድ ስለሚሆን መበደር አንችልም፡፡ በአገር ውስጥ የራሳችን ገንዘብ ካለን ግን የውስጥ ችግሮቻችንን የምንፈታበት አቅም ይኖረናል፡፡ ዛሬ የምንሰጣት ጥቂት ፈንድ የምትጠፋ ከሆነ፣ የዕርዳታ አመለካከት ካለ እንደ ውድ ነገር መቁጠር እንደሚበላሽና ጉዳት እንደሚያደርስ ነገር መቁጠር ስለማይኖር ተመላሽ በሚደረግ ገንዘብ እንዲሠሩ ማደረጉ ጥቅም አለው፡፡ የእኔነት ስሜትም ያሳድራል፡፡ የምከፍልበት ነው፣ የራሴ ንብረት ነው የሚል አመለካከት ሲኖረው በአግባቡ የመጠቀም ልማድ ይመጣል፡፡

ሪፖርተር፡- የግንባታ ወጪ እየናረ መጥቷል፡፡ አንድ ጉድጓድ ለመቆፈር የሚጠየቀው ወጪ ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የሚሰጠው ብድርና የሚሠራው ሥራ እንዴት ይገመገማሉ?

አቶ ዋና፡-የእኛ ቡድን ፕሮጀክቶቹ በሚሠራበት ቦታ ሄዶ ክትትል ያደርጋል፡፡ ያረጋግጣል፡፡ በፕሮጀክት ሰነዱ ላይ ያቀረቡት ምንጭ እውነትም አለ ወይ? የሚለውን እናያለን፡፡ አንዳንዱ የውኃ መሠረተ ልማት ከተሠራለት በኋላ አልከፍልም እንዳይል የሚያስገድደው በየጊዜው የሚጨምር የተጠቃሚው ሕዝብ ፍላጎት አለ ወይ? የሚለውን እናያለን፡፡ አንዳንዱ የምንጭ ውኃ ስላለው እኛ ፕሮጀክቱን ከሠራንለት በኋላ ብድር ላለመክፈል እንዳያንገራግር ክትትል እንደርጋለን፡፡ የተለያዩ መለኪያዎችና መጠይቆች ተሠርተው ነው ብድሩ የሚለቀቀው፡፡ የተሠራው ሥራና ወጪው መመጣጠናቸው ይታያል፡፡ ፕሮጀክቱ መክፈል የሚችልባቸው መለኪያዎችን የሚሠሩ ቀመሮች አሉን፡፡ ቀመሩ በሚሰጡት መለኪያዎች አማካይነት እስከምን ያህል መጠን ድረስ ተበዳሪው መሸከም እንደሚችል ያመላክታሉ፡፡ መሸከም ከሚችለው በላይ የሆነበትን የፕሮጀክት ወጪ ጥያቄ እኛ በብድር በማቅረብ ፕሮጀክቱን እናግዛለን፡፡ እኛ የምናቀርበው አስተማማኝ የሆነው መጠን ላይ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ ወጪ ምን ያህል እንደሚሆን ከዚህ ወጪ ውስጥ እኛ በብድር ማቅረብ የምንችለው መጠን ምን ያህል እንደሆነ፣ የተቀረውን አዋጥተው እንዲሸፍኑ ይደረጋል፡፡ መመለስ የማይቻለውን የወጪ ክፍል ተበዳሪ ከተሞች እንዲሸፍኑ በማድረግ ለሁለት አጋጭተን ለሕዝቡ ንፁህ ውኃ እንዲቀርብ ለማድረግ እንሞከራለን፡፡ ይሁንና የዋጋ ውድነት ከእኛ ቁጥጥር ውጭ ነው፡፡ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች በተለይ ከዓለም አቀፍ ገበያ ተገዝተው የሚመጡ በመሆናቸው ዋጋቸው ከእኛ ቁጥጥር ውጭ ነው፡፡ ወደፊት በአገር ውስጥ ምርቶች የመጠቀም አዝማሚያም አለን፡፡

ሪፖርተር፡- 1,000 ያህል ከተሞች እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ለ15 ከተሞች የተመደበ ፕሮጀክት ነበር፡፡ ይሁንና በውኃ ልማት ፈንድ በኩል ለስምንት ከተሞች የሚውል ብድር ከውጭ አበዳሪዎች የተገኘ ገንዘብ በቅርቡ እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡ ይሁንና የታሰበውን ያህል ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ይህ የሆነበትን ምክንያት ቢያብራሩልን?

አቶ ዋና፡-ለ15ቱ ከተሞች የሚለው የቀድሞው ስምምነት በውኃ ልማት ፈንድ የተፈጸመ አልነበረም፡፡ ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክና ከአውሮፓ ኅብረት በተገኘ ገንዘብ ከአሥር ዓመት በፊት ከመንግሥት ጋር የተደረሰውን ስምምነት መሠረት በማድረግ ነበር 15ቱ ከተሞች የተመረጡት፡፡ በወቅቱ ግን በብድር አቅራቢያዎች በኩል በነበረ ግፊት ይመስለኛል አንድ ዓለም አቀፍ ተቋራጭ የ15ቱንም ከተሞች የውኃ መስመሮች እንዲዘረጋ የሚል አሠራር ተፈጥሮ ነበር፡፡ ይሁንና ወደ ሥራው ሒደት ሲገባ 15ቱ ከተሞች በአራት ክልሎች የሚገኙ ትልልቅ ከተሞችን የሚያካትት በመሆኑ፣ በወቅቱ በሚፈለገው ሒደትና ፍጥነት ሊሄድ አልቻለም ነበር፡፡ ከብዙ ጉትጎታም በኋላ ከአውሮፓው ተቋራጭ ጋር ሥራውን መቀጠል እንዳልተቻለ የኢትዮጵያ መንግሥት በመገንዘቡ ስምምነቱን አቋርጦታል፡፡ ጉዳዩ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤትም ደርሶ ክርክር ተደርጎበት ነበር፡፡ በመጨረሻው ለኢትዮጵያ መንግሥት ተፈርዶ አሁን ነገሮች መልክ የያዙበት መንገድ ተፈጥሯል፡፡ በወቅቱ በተገባው ስምምነት መሠረት ሊሠራ ባለመቻሉ ግንባታዎች ተቋርጠው ቆይተዋል፡፡ በአገር ውስጥ ተቋራጮች አማካይነት ሥራዎች ተከፋፈለው ሥራው ተሰጥቶ ነበር፡፡ ከ15ቱ ከተሞች ፕሮግራም ውስጥ ውኃ የማምረትና ዋና ዋናዎቹን መስመሮች የመዘርጋት ሥራ እንጂ ወደ ተጠቃሚው የማዳረስ ሥራ የፕሮጀክቱ አካል አልነበረም፡፡ በቅርቡ በተደረገው ስምምነት መሠረት የተመረተው ውኃ ለተጠቃሚው የሚደርስበትን የመጨረሻውን ሥራ ለመሥራት የሚያስችል ሥራ የሚሠራበት ወቅት ነው፡፡ ከመነሻው በገንዘብ ዕጥረት ምክንያት ከመጀመርያው ፕሮጀክት ተቀንሶ የነበረውን ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ፣ ከፈረንሣይና ከጣልያን መንግሥታት ጋር ባደረግነው ስምምነት መሠረት ለመጨረሻው ተጠቃሚ የሚውል ውኃ ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ቀድሞ ከስምንት ከተሞች ጋር ተፈራርመናል፡፡ ከ15ቱ ከተሞች ውስጥ ሰባቱ በአማራ ክልል፣ አራቱ በኦሮሚያ ክልል፣ ሁለቱ በደቡብ እንዲሁም ሌሎች ሁለት በትግራይ ክልል የሚገኙ ከተሞች ነበሩ፡፡ የቀድሞው ፕሮጀክት መስተጓጎል ባስከተለው መጓተት ምክንያት አማራ ክልል በራሱ ፋይናንስ ሥራዎችን ዳር አድርሷል፡፡ ፕሮጀክቶቹ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ በሦስቱ ክልሎች የሚገኙት ስምንቱ ከተሞች ውስጥ ግን ፕሮጀክቶቹ ስላልተጠናቀቁ ፋይናንስ አፈላልገን ሥራውን ዳር ለማድረስ መንቀሳቀስ ጀምረናል፡፡

ሪፖርተር፡- ለውኃ ፕሮጀክቶች የሚውለው ብድር ከሦስት የውጭ አበዳሪዎች መገኘቱ ይታወቃል፡፡ የተገኘው የ75 ሚሊዮን ዩሮ ገንዘብ በምን መልኩ ነው ለከተሞቹ የሚከፋፈለው?

አቶ ዋና፡-የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ 40 ሚሊዮን ዩሮ አበድሮናል፡፡ የፈረንሣይ መንግሥት 20 ሚሊዮን ዩሮ ገደማ እንዲሁም የጣልያን መንግሥት 15 ሚሊዮን ዩሮ አበድረዋል፡፡ ይህ ገንዘብ አሁን ባለው ምንዛሪ ወደ 1.8 ቢሊዮን ብር ገደማ የሚገመት ነው፡፡ ብድሩ በአንድ ቋት የሚተዳደር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 189 ሚሊዮን ብር ነው ለስምንቱ ከተሞች የሚሰጠው፡፡ ከተሞቹ የራሳቸውን መዋጮ ያክሉበታል፡፡ እኛ የምንሰጣቸው ገንዘብ እንዲሁም እነሱ የሚዋጡት ገንዘብ ተዳምሮ ጠቅላላ የፕሮጀክቱ ወጪ 335 ሚሊዮን ብር ይደርሳል፡፡ በብድር የሚተላለፈው ግን 189 ሚሊዮን ብሩ ነው ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቀደመው የ15 ከተሞች ፕሮጀክት ተመድቦ የነበረው የገንዘብ መጠን ምን ያህል ነበር?

አቶ ዋና፡-በእርግጥ እኔ የምመራው ተቋም አልሠራውም፡፡ ሆኖም ገንዘቡ ምን ያህል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ለአብነት ለስምንቱ ከተሞች ተመድቦ የነበረውን የገንዘብ መጠን መጥቀስ ካስፈለገ 1.2 ቢሊዮን ብር አካባቢ ነበር፡፡ ይህ የመጀመርያው ብድር ሲሆን፣ በዚሁ ፕሮጀክት ወቅት አብዛኞቹ የግንባታ ሥራዎች ተጠናቀዋል፡፡ አሁን የምንሠራው የቀደመውን ፕሮጀክት ወደ መጨረሻው ምዕራፍ የማድረስ ሥራ ነው፡፡ የአሁኑ ወጪያቸው ጠቅላላ ወጪ 335 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- የብድር መጠይቆችን የማያሟሉ ከተሞች ከተጠቃሚነት ውጭ ይደረጋሉ ማለት ነው?

አቶ ዋና፡-የብድር መስፈርቶችን የማያሟሉ ካሉ ለብድር አሰጣጡ ብቁ ስለማይሆኑ እንዲቀሩ ይደረጋሉ፡፡ ይሁንና ግን ከታች ጀምሮ እንዲያሟሉ ድጋፍ አድርገን ስለምናመጣ የሚያልፉ ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ እናደርጋለን፡፡ ዋናው ዓላማ ሕዝቡ ውኃ በአግባቡ እንዲያገኝ፣ ሥራውም የማይስተጓጎልበትን ምቹ መንገድ መፍጠር ነው፡፡ ተቋማችን የልማት ዓላማ ያለው በመሆኑም የሚሰጠው ብድር ተግባር ላይ ውሎ ጥቅም እንዲሰጥ የማድረግ እንጂ፣ ለሚሰጠው ብድር የሚያስከፍለው ወለድና የእፎይታ ጊዜ እንዲሁም የማስከፊያ ጊዜ ሲታይ ብድሩ በተበዳሪ ከተሞች ላይ ጫና የሚፈጥር አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ተቋሙ በብድር የሚያገኛቸውን ገንዘቦች በምን መልኩ ነው የሚያመጣው? መንግሥት ዋስትና ገብቶለት ነው ወይስ በመንግሥት በኩል ነው የሚያገኘው?

አቶ ዋና፡-ከውጭ ምንጮች የመበደር ሥልጣኑ በጠቅላላ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ነው፡፡ ሚኒስቴሩ ከተበደረ በኋላ ለእኛ ማስተላለፍ የሚችልበት የስምምነት አሠራር ስላለ በዚያ መሠረት ነው የብድር ገንዘቡ የሚደርሰን፡፡ ተቋሙ መጀመርያ በአዋጅ የተቋቋመ ሲሆን፣ የመነሻ ገንዘብ ተሰጥቶት በሒደት ግን ከሚያገኛቸው ብድሮችና ዕርዳታዎች እያጠረቃቀመ እንዲጠቀም በሚል እሳቤ ነው የተመሠረተው፡፡

ሪፖርተር፡- በተባለው ሒደት መሠረት የማይፈጸሙ ፕሮጀክቶችን እንዴት ነው የምትከታተሉት?

አቶ ዋና፡- የፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም ሒደት በተለያዩ አካላት ነው የሚታየው፡፡ የእኛ ሥራ ፋይናንሱን ማቅረብ ነው፡፡ እርግጥ የፕሮጀክት አተገባበር ላይ የሚታዩ ችግሮች አሉ፡፡ አንደኛው የኮንትራት አስተዳደር ብቃታችን እንደ አገር ገና ነው፡፡ ሁለተኛ ጥናቶች ሲሠሩ ከመጀመርያውም በጥልቅ እስከሚፈለገው ደረጃ ድረስ ያለመሄድ ችግርም አለ፡፡ ጥናት የሚሠሩ አማካሪዎች የተሟላና ተፈጻሚነት ያለው ሰነድ የማቅረብ አቅምና ችሎታ ገና አልዳበረም፡፡ ወደ ፕሮጀክት ትግበራ ከተገባ በኋላ ብቅ እያሉ የሚያስቸግሩ ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡ የኮንትራት ሰነዶችን ካዘጋጀን በኋላ ለማስተዳደርም በአገር ደረጃ ትልቅ ችግር አለበት፡፡ አሁን ግን እየተሻሻለ ይገኛል፡፡ የፕሮጀክት ባለቤቶችም ወጥረው ይዘው በመከታተል ውጤታማ እንዲሆኑ የማድረግ እንቅስቃሴ ላይም ደካማ ሆነው ይታያሉ፡፡ በአጠቃላይ ሲደመር የማስፈጸም አቅም ድርሻ አለው፡፡ በተቀመጡ ሕጎች መሠረት መሥራት፣ ፋይናንስ አቅራቢዎችም የየራሳቸው መጠይቆች ስላሏቸው እንዲህ ያሉትና ሌሎችም ጉዳዮች ፕሮጀክቶችን ሊያጓትቱ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ 

 

Standard (Image)

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ኢኮኖሚያዊ ድርሻ እያደገ መምጣቱ ተገለጸ

$
0
0

 

  • 170 የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች የተሳተፉበት ዓውደ ርዕይ ነገ ይጠናቀቃል

 የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በአማካይ 28.7 በመቶ ዕድገት እየተመዘገበበት እንደመጣና የኢኮኖሚ ድርሻውም 8.5 በመቶ መድረሱን የኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ወ/ሮ አይሻ መሐመድ (ኢንጂነር) ገለጹ፡፡

  ሚኒስትሯ ይህንን የገለጹት አምስተኛውን ‹‹ኮንስትራክሽን ለኢትዮጵያ ህዳሴ›› የተሰኘውን ዓውደ ርዕይ ሐሙስ፣ መጋቢት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን በከፈቱበት ወቅት ነበር፡፡  

ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ አገሪቱ በምትከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት፣ የኮንስትራክሽን ዘርፉ እያንሰራራ መምጣቱን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፣ በአሁኑ ወቅት በጠቅላላው ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ትልቁን ሚና ከሚጫወትበት ደረጃ ላይ መድረሱንም አውስተዋል፡፡

ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት እያበረከተ ካለው አስተዋጽኦ ባሻገር፣ ከ1994 ዓ.ም. ወዲህ በመኖሪያ ቤቶች፣ በመንገድ፣ በኃይል፣ በባቡር መሠረተ ልማት፣ እንዲሁም በሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች ውስጥ የዘርፉን ተሳትፎ ያሳደጉና አገሪቱን ተጠቃሚነት ያጎሉ ውጤቶች መታየታቸውንም ወ/ሮ አይሻ አመልክተዋል፡፡

በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ የሚከናወኑ ሰፋፊ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች በሥራ ዕድል መስክ ያላቸው ሚና እያደገ በመምጣቱ፣ በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪው የሚያሳትፈው የሰው ኃይል ብዛት 1.2 ሚሊዮን መድረሱን ገልጸዋል፡፡

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ለማሳደግና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲወጣ ያስችላሉ የተባሉ እንቅስቃሴዎችን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው እየሠራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ በዋናነት እየተሠሩ ናቸው ካሉዋቸው መካከል የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የማስፈጸም አቅም ግንባታ ፕሮግራም አንዱ ነው፡፡

ሚኒስቴሩ ለአቅራቢዎች፣ ለተቋራጮች፣ ለአማካሪ ድርጅቶችና በአጠቃላይ በኢንዱስትሪው ውስጥ ለሚገኙ ተዋንያን የአቅም ግንባታ የሚሰጥበት ፕሮግራም መቅረጹን ወ/ሮ አይሻ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ጠቅሰዋል፡፡ የግንባታ ዘርፉን ለማሳደግ ሚኒስቴሩ እንደሚተገብራቸው ከሚጠበቁት መካከል እንደ ሕንፃ አዋጅ ያሉትን ሕግጋት፣ የተሻሻሉና አዲስ የወጡ መመርያዎችና ደረጃዎች ተዘጋጅተው ወደ ተግባር መቀየር እንደጀመሩም ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ደረጃ አንድ ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ያዘጋጀውና ለአምስት ቀናት የሚቆየው ዓውደ ርዕይ 170 የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች የተሳተፉበት ነው፡፡  የማኅበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሳሙኤል ታፈሰ እንደገለጹት፣ ዓውደ ርዕዩ ላይ ኢንዱስትሪውን የሚመሩና የሚያስተባብሩ እንዲሁም የተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ተቋራጮች፣ አማካሪዎች፣ አገልግሎት ሰጪዎች፣ አከፋፋዮች፣ አምራቾችና የመሳሰሉት ታደመውበታል፡፡ እነዚህን በአንድ ላይ በማሰባሰብ ኢንዱስትሪው የደረሰበትን ደረጃ ከማመላከት በተጓዳኝ አማራጭ የገበያ መረጃዎችንም ለመለዋጥ እንደሚረዳ አቶ ሳሙኤል ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ደረጃ አንድ ተቋራጮች ማኅበር በአሁኑ ወቅት የደረጃ አንድ ግንባታ ፈቃድ ያላቸው ከ45 በላይ አባላትን አቅፎ የሚንቀሳቀስ የሙያ ማኅበር ነው፡፡ 

Standard (Image)

በረሀብ ቸነፈር የተመቱ ሕዝቦች በአስከፊ ዕልቂት አፋፍ ላይ ይገኛሉ

$
0
0
  • ኢትዮጵያ ለ5.6 ሚሊዮን ሰዎች ዕርዳታ የሚሰጠኝ አላገኘሁም ብላለች

በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በኬንያ፣ በኢትዮጵያ እንዲሁም በየመን የተንሰራፋው ችግር ወደ ችጋርና ረሀብ በመሻገር የሰውና የእንስሳት ነፍስን እያጠፋ ይገኛል፡፡ የየመን ጉዳይ በጦርነት ሳቢያ የተቀሰቀሰ የሰብዓዊ ቀውስ ሲሆን፣ በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የተከሰተው የምግብ ዕጥረት እየተባባሰ በመምጣት ወደ ረሀብነት መሸጋገር የጀመረው ግን በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ነው፡፡ በዚህ የተነሳም ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለአስቸኳይ የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ፈላጊ ለመሆን ተገደዋል፡፡

ሶማሊያ በረሀብ ቸነፈር መመታቷን ባወጀች ማግሥት በሁለት ቀናት ውስጥ ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች አልቀዋል፡፡ አሁንም በርካቶች ሰዎች ሕይወታቸውን እያጡ ይገኛሉ፡፡ በተለይ በሕፃናትና በሴቶች ላይ ስቃዩ በርትቶ በሚታየው ድርቅ፣ ደቡብ ሱዳናውያንም ገፈት ቀማሽ ሆነዋል፡፡ በእርስ በርስ ጦርነት በርካቶች በሚማገዱባት ጨቅላዋ አገር፣ ረሀብ የሚፈጃቸው ሰዎች ከቀን ወደ ቀን በመጨመር ላይ ይገኛል፡፡

በተመድ ትርጓሜ መሠረት ሕዝቦች በአንድ አገር ውስጥ የረሀብ ቸነፈር የሚታወጀው ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ከሆናቸው ሕፃናት ውስጥ 30 በመቶው ለከፋ የምግብ ዕጥረት (ለተመጣጠነ) ሲዳረጉ፣ ከአሥር ሺሕ ሰዎች መካከል በየቀኑ ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች የሚበሉት በማጣት ለሞት የሚዳረጉ ከሆነና ሌሎችም መሠረታዊ መመዘኛዎች ከተሟላ በአንድ አገር ውስጥ ረሀብ ወይም ችጋር ተከስቷል ብሎ ለማወጅ የሚያበቁ ምክንያቶች ይሆናሉ ማለት ነው፡፡

በኬንያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለአስከፊው የድርቅ አደጋ መዳረጋቸውን ብቻም ሳይሆን፣ ወደ ረሀብ አፋፍ እየተንደረደሩ እንደሚገኙ በመገንዘብ የአስቸኳይ ጊዜ እንዲያውጅ መንግሥቱን ግድ ብሎታል፡፡ ናይጄሪያም በድርቅ ከተመቱ አገሮች ተርታ ለመሰለፍ መገደዷን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ይሁንና እስካሁን በአኅጉሪቱ ከታየው የድርቅ ክስተት በቁጥር ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው የዘንድሮው ድርቅና ያስከተለው ረሀብ ከሌላው ጊዜ ይልቅ የብዙዎችን ትኩረት ያጣ፣ ጉዳት እየደረሰባቸው ለሚገኙ ወገኖች የሚሰጠው ድጋፍም እንደሌላው ጊዜ ቸል የተባለ ሆኗል፡፡ በርካታ አገሮችም እንደቀድሟቸው ለዕርዳታ የሚሰጡት ምላሽ ተቀዛቅዞ በመታየቱ የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች ሥጋቱን በማስተጋባት የጉዳቱን መጠን ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ኃላፊው ስቴፈን ኦብራየን በቅርቡ ይፋ እንዳደረጉት በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በየመንና በናይጄሪያ የተከሰተውን ረሀብና ቸነፈር እስከመጪው ሐምሌ ብቻ ለመቋቋም በጥቂቱ 4.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ በመግለጽ አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበው ነበር፡፡

ኦብራየን በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ወቅት ተገኝተው ለዓለም ይፋ እንዳደረጉት፣ ዓለም አይታ የማታውቀው የሰብዓዊ ቀውስ ተጋርጦባታል፡፡ በእነዚህ ጥቂት አገሮች ውስጥ ለአደጋ የተዳረጉት ሕዝቦች ተመድ ከተመሠረተ ጀምሮ ታይቶ የማይታወቅ መሆኑን በማጉላት አስከፊውን አደጋ ለማሳየትና ሳይረፍድ መነሳት እንደሚገባ ለማስጠንቀቅ ሞክረዋል፡፡ ‹‹ዓለም ተባብሮ ካልተረባረበ በቀር በርካቶች በረሀብ ጦስ ያልቃሉ፡፡ ጥቂት የማይባሉ ሰዎችም ለበሽታ ስቃይና ለሞት ይዳረጋሉ፤›› በማለት ለፀጥታው ምክር ቤት ስለአስለፊው አደጋ አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዓምና ለዕለት ደራሽ ዕርዳታ ከተዳረጉት 10.2 ሚሊዮን ሰዎች መካከል ዘንድሮም በዕርዳታ ለመኖር የተገደዱ በርካቶች ናቸው፡፡ በአገሪቱ የዝናብ ዕጥረት ያስከተለው ድርቅ ዘንድሮም ከ5.6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በሚገኙበት የበልግ አብቃይ የአርብቶ አደር አካባቢዎችን ለድርቅ አደጋ አጋልጧል፡፡

ሐሙስ መጋቢት 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የመንግሥታቸውን የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ይህንኑ ገልጸዋል፡፡ በዝናብ ዕጥረት ምክንያት በአገሪቱ የደቡብ ምሥራቅ አካባቢዎች ነዋሪ የሆኑ 5.6 ሚሊዮን ሰዎች ለዕለት ደራሽ ምግብ ዕርዳታ ከመዳረጋቸውም ባሻገር፣ እነዚህን ሰዎች ለመታግ የሚያስፈልገው ገንዘብ ከ948 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነም ለፓርላማው አስታውቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጠቀሱት ገንዘብ ውስጥ 600 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ለምግብ አቅርቦት የሚለው ሲሆን፣ ቀሪው 350 ሚሊዮን ዶላሩ ደግሞ ምግብ ነክ ላልሆኑ አቅርቦቶች ማሟያ ይውላል፡፡

በብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ የሎጂስቲክስና አቅርቦት ዳይሬክተር አቶ ኢድሪስ ሐሰን ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳብራሩት፣ 948 ሚሊዮን ዶላሩ ለ920 ሜትሪክ ቶን የምግብ እህሎች ግዥ  ይውላል፡፡ ከዚህ ውስጥ 745 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ፣ 74,400 ሜትሪክ ቶን ጥራጥሬ፣ 22,320 ሜትሪክ ቶን የምግብ ዘይት እንዲሁም 78,150 ሜትሪክ ቶን አልሚ ምግቦች ተገዝተው ለድርቅ ተጎጂዎች መቅረብ አለባቸው ያሉት አቶ ኢድሪስ፣ ይህም ሆኖ መንግሥት ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ያቀረበው የዕርዳታ ድጋፍ ጥሪ ያገኘው ምላሽ ቀዝቃዛ ሆኗል ብለዋል፡፡ ከዓለም ምግብ ፕሮግራም እንዲሁም በጣት ከሚቆጠሩ ሌሎች ተራድዖ ድርጅቶች በቀር ለአገሪቱ ተጎጂዎች የዕርዳታ እጃቸውን የዘረጉ አገሮች አልተገኙም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት ሪፖርት፣ የዓለም ትኩረት በመካከለኛው ምሥራቅ፣ ወደ ምዕራብ አፍሪካ እንዲሁም ወደ ጎረቤት አገሮች ያነጣጠረ በመሆኑ የኢትዮጵያ ጥሪ ችላ መባሉን ጠቅሰዋል፡፡ እንደ ሶሪያ፣ ኢራቅ፣ የመን፣ ደቡብ ሱዳን ያሉ የጦርነት አውድማ የሚንጣቸው አገሮች የዓለም አትኩሮት በመሳባቸው ዓለም ወደ እነዚህ አገሮች ፊቱን በማዞሩ የሚፈለገውን ድጋፍ ማግኘት እንዳልተቻለ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ አቶ ኢድሪስ ከሰጡት ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ በመሆኑም የፌደራል መንግሥት አንድ ቢሊዮን ዶላር በመመደብ በድርቅ የተጎዱ ሰዎችንና እንስሳትን ለመታደግ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝም አቶ ኃይለ ማርያም ተናግረዋል፡፡

አምናም ተመሳሳይ ችግር አጋጥሞ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከዓለም አቀፍ ለጋሾች የተገኘው ዕርዳታ የሚፈለገውን ያህል እንዳልነበር መንግሥት ደጋግሞ አስታውቋል፡፡ ድርቁ ባስከተለው ጫና ምክንያት የግብርና ዘርፉ ዕድገት አሽቆልቁሎ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ከስምንት በመቶ በላይ እንደሚያድግ ሲጠበቅ የነበረው የግብርናው ኢኮኖሚ ወደ ሁለት በመቶ ዝቅ ብሎ እንደነበር በሪፖርታቸው  አውስተዋል፡፡ ይህ በመሆኑም በጠቅላላ ኢኮኖሚው ዕድገት ላይ ያስከተለውን ተፅዕኖም ጠቅሰዋል፡፡ የድርቁ ተፅዕኖ ግን ይህን ያህል አሳሳቢ አይደለም የሚል መግለጫ በተለያዩ የመንግሥት ሹማምንት ሲሰጥ እንደነበር የሚታወስ ቢሆንም፣ የአገሪቱ ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ) በ11 ከመቶ ያድጋል ተብሎ ሲጠበቅ ወደ ስምንት በመቶ ዝቅ እንዲል ማስገደዱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አምነዋል፡፡ 

እንደ ኦብራየን ማብራሪያ፣ በየመን ጦርነት ሳቢያ ለዕለት ደራሽ የምግብ ዕርዳታ ከተዳረጉ 18.8 ሚሊዮኖች ውስጥ ሰባት ሚሊዮን ሰዎች ለረሀብ አለንጋ ተዳርገዋል፡፡ በየመን ጦርነት መባባስ እጃቸውን እንዳለበት የሚነገርላቸው እነ ሳዑዲ ዓረቢያና ሌሎች አገሮች ለሰብዓዊ ቀውሱ መባባስ ጣት ቢቀሰርባቸውም፣ የየመን ሕፃናት ግን በረሀብ ከመርገፍ የሚታዳጋቸውን ድጋፍ ለማግኘት ይጠባበቃሉ፡፡ ይሁንና 12 ሚሊዮን የመናውያንን ከረሀብ እልቂት ለመታደግ በትንሹ 2.1 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ኦብራየን ጠቅሰዋል፡፡

በደቡብ ሱዳንም 7.5 ሚሊዮን ሕዝቦቿ ለዕርዳታ የተዳረጉባት ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት በ1.4 ሚሊዮን የተረጂዎች ቁጥር የጨመረባት፣ ከ3.4 ሚሊዮን በላይ ከቀዬያቸው የተፈላቀሉባት ደቡብ ሱዳን፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሕፃናቶቿ ለአስከፊ የምግብ ዕጥረት ተዳርገውባታል፡፡

ሶማሊያ የ6.2 ሚሊዮን ተረጂዎች ብዛትን ከማስመዝገቧም በላይ 2.9 ሚሊዮን የረሀብ ተጎጂዎችን ከሞት ለመታደግ ድረሱልኝ በማለት ላይ ትገኛለች፡፡ በሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ የተከተሰው ረሀብም በዓለም አራተኛዋን ነዳጅ አምራች አገር ከተረጂዎች ተርታ አሰልፏታል፡፡ በጽንፈኛው አሸባሪ ቦኮ ሃራም አበሳዋን የምታየው ናይጄሪያ፣ ከተገደሉባት 200 ሺሕዎችና ከተሰደዱባት 2.6 ሚሊዮን ዜጎቿ ባሻገር ሚሊዮኖቿ ለረሀብ አደጋ ተጋልጠውባታል፡፡

እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ተመድ ከተመሠረተ ወዲህ ታይቶ አይታወቅም ያሉት ኦብራየን፣ የምሥራቅ አፍሪካ ሕዝቦች በተለይ የድርቅና የረሀብ አለንጋ እየሸነቆጣቸው እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ምንም እንኳ አደጋው የቱንም ያህል አስከፊ ቢሆን ለዕርዳታ ሥራ ዝግጁ ነን በማለት ለዓለም ልዕለ ኃያላን አገሮች የገለጹት የተመድ ሰብዓዊ ጉዳዮች ኃላፊ፣ የነፍስ አድን ጥሪያቸው ግን ተገቢውን ምላሽ ያገኘ አይመስልም፡፡ እንደውም በተቃራኒው ምላሹ ተስፋ አስቆራጭ መሆኑ የሚነገረው አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለተመድ የሚደረገው ድጋፍ ይቀነሳል በማለታቸው ጭምር ነው፡፡

አነጋጋሪው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶላንድ ትራምፕ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤኣይዲ)ን ጨምሮ ሌሎችም በልማት ትብብር መስክ የሚንቀሳቀሱ የአሜሪካ መንግሥታዊ ተቋማት በጀት ይቀነሳል በማለታቸው፣ ከተመድ ኤጀንሲዎች አብዛኞቹ ሥጋት ውስጥ ወድቀዋል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ብቻውን የሁለት ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ከአሜሪካ ያገኝ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ዕርዳታዎች ከምንጊዜውም ይልቅ ዘንድሮ በሚያስፈልጉበት ወቅት አሜሪካ እጇን ለመሰብሰብ ማሰቧ ቀውሶችን እንደሚያባብስ ሥጋታቸውን የገለጹት በአፍሪካ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ቃል አቀባይ ካሊስ ማክዶናሁ ናቸው፡፡ በደቡብ ሱዳን በአሁኑ ወቅት ከአውሮፕላኖች የሚጣል የዕለት ደራሽ የምግብ ዕርዳታ እየተሰራጨ ይገኛል ያሉት ቃል አቀባዩ፣  በረሀብተኞችና በሞት መካከል ያለው ብቸኛው መድን ይኸው ዕርዳታ ነው በማለት ዕርዳታው ቢቋረጥ በሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች ለሞት እንደሚዳረጉ አበክረው በመግለጽ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የያዙትን አቋም ተችተዋል፡፡

ዓለም በድርቅና በረሀብ ጦስ ለሚረግፉ ሚሊዮኖች እያሳየ የመጣው ቸልተኝነት እየተባባሰ መምጣቱን የሚያመላክቱን ፕሬዚዳንት ትራምፕ ብቻም ሳይሆኑ አኅጉራዊ ተቋማትም ጭምር ናቸው፡፡ ከስድስት ዓመት በፊት በምሥራቅ አፍሪካ በርካቶች ለረገፉበት የረሀብ አደጋና ሰብዓዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት የተሰናዳው የዕርዳታ ጥሪ በአሁኑ ወቅት አይታይም፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ኤርትራ፣ ጂቡቲ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያና ታንዛንያን ያካለለው ድርቅ ከ14 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ የዳረገ እንደነበር ሲታወስ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ለሕልፈት ሕይወት መዳረጉም አይዘነጋም፡፡

የዘንድሮው ድርቅ ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ሕልውና ለአደጋ አጋልጦ እየተሰጠው ያለው ትኩረት ግን ዝቅተኛ መሆኑ እየታየ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሊከሰት የሚችለው ዕልቂት ከወዲሁ እየተስተጋባም ቢሆን፣ እንደ አፍሪካ ኅብረት ያሉት አኅጉራዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ሳይቀሩ ዝምታን መርጠዋል፡፡ 14 ሚሊዮኖች ለአስቸኳይ ዕርዳታ በተጋለጡበት ወቅት የአፍሪካ ኅብረት የዕርዳታ ማሰባሰቢያ ጉባዔ በመጥራት አንድ ቢሊዮን ዶላር ለተረጂዎቹ አገሮች አሰባስቦ ለማከፋፈል ሲንቀሳቀስ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይሁንና ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ከአንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር ያልበለጠ ገንዘብ ማሰባሰቡና የዕርዳታ ቴሌቶኑም ሳይሳካለት መቅረቱ አይዘነጋም፡፡ ዘንድሮ ካለፈው የተሻለ ለማገዝ የሚችልበትን እንቅስቃሴ ማድረግ ሲጠበቅበት፣ ኅብረቱ ዝምታን መምረጡ አስገርሟል፡፡

 

Standard (Image)

የወጪ ንግዱ ያሳየው ማሽቆልቆል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትን በስብሰባ ወጥሯል

$
0
0
  • ላኪዎች ነገ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ለስብሰባ ተጠርተዋል    
  • የንግዱ ማኅበረሰብ በጥናት ላይ የተመረኮዘ መትፍሔ እንዳቀርብ ዕድሉን አላገኘሁም ይላል

የአገሪቱ የወጪ ንግድ እያሳየ ያለው ማሽቆልቆል እየተባባሰ በመምጣቱ፣ መንግሥት አስቸኳይ መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችሉ የአጭር ጊዜ ዕርጃዎችን መውሰድ እንደሚጀምር በመግለጽ ላይ ይገኛል፡፡ ይህንኑ ለማድረግም የተለያዩ ስብሰባዎችን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

ከጥቂት ቀናት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ አቶ አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) የተመራ ስብሰባ ተጠርቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ መንግሥት በተለይ ላኪዎችን ባነጋገረበት ወቅት በአገሪቱ ለሚታየው አሳሳቢ የወጪ ንግድ ማሽቆልቆል መንስዔው ምን እንደሆነና መትፍሔውንም ያመላከተ ውይይት ማድረጉም ታውቋል፡፡

በስብሰባው ወቅት እንደተነሱ ከተገለጹ ነጥቦች መካከል የመንግሥት ቢሮክራሲያዊ አሠራር የፈጠራቸው ችግሮች ትልቁን ድርሻ ይዘዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር በተለይ ቡና ላኪዎች በአሻጥር የፈጸሙት ተግባር ተብሎ የቀረበውና በአገር ውስጥና በዓለም ገበያ መካከል ያለውን የዋጋ ክፈተት መንስዔ በማድረግ ወደ ውጭ ከመላክ የተቆጠቡ ነጋዴዎች መታየቸው በመንግሥት ሲገለጽ ተደምጧል፡፡ በዘንድሮው ስድስት ወራት ውስጥ ከወጪ ንግዱ ዘርፍ ይጠበቅ የነበረው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 2.5 ቢሊዮን  ዶላር ገደማ ነበር፡፡ ይሁንና የተገኘው ግን 1.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ይህ አፈጻጸም በዕቅድም ከዚህ ቀደም ሲገኝ ከነበረውም ያነሰ ሆኗል፡፡

ምንም እንኳ ላኪዎችና ገዥዎች በዋጋና በዓለም አቀፍ ገበያ መቀዛቀዝ ምክንያት የተፈጠረ እንደሆነ ቢገልጹም፣ በአገሪቱ የተከሰተው የፀጥታ ችግር፣ በፀጥታው መናጋት ምክንያት የተፈጠረው ሥጋትም ለወጪ ንግዱ መቀዛቀዝ ዋቢ ተደርጓል፡፡ ነገሮች በዚህ አኳኋን ከቀጠሉ አገሪቱ የወጪ ንግድ ክፉኛ አደጋ እንደተጋረጠበት የተረዳው መንግሥት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የዘርፉን ችግሮች ይቀርፉልኛል ያላቸውን ያልተጠበቁ የመፍትሔ ሐሳቦችን እያቀረበ ይገኛል፡፡

በመንግሥት ከቀረቡት ሐሳቦች መካከል የኢትዮጵያ ምርት ገበያን እንዲሁም የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች አገልግሎትን የሚመለከቱ ለውጦች ይገኙበታል፡፡ ላኪዎች ከሁለቱ ተቋማት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሊለውጥ የሚችል አሠራር እንደሚተገበር ከሚጠቅሰው የመንግሥት ምልከታ አንዱ እንደሆነ የሚጠቀሰው፣ ላኪዎች በመኪና የጫኑት ጭነት በቀጥታ ኤክስፖርት መደረግ የሚችልበትን አሠራር ለማምጣት የሚያስችል አማራጭ ማቅረቡ ተነግሯል፡፡ ይህ አሠራር የወጪ ንግዱን የተቀላጠፈ ለማድረግ ያሰበ ሲሆን፣ ሌሎችም በርካታ ለውጦች እንደሚደረጉ የቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳኒ ረዲ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

እነዚህን ለውጦችና ሌሎችም የአሠራር ማሻሻዎች በአጭርና በረጅም ጊዜ ውስጥ ለመተግበር የተነሳው መንግሥት፣ ከሁለት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ላኪዎችና ሌሎች የሚመለከታቸውን ተዋንያን ለማነጋገር ነገ ስብሰባ ጠርቷል፡፡ የስብሰባው ዓብይ አጀንዳ ምን እንደሆነ ለማወቅ ሪፖርተር ሞክሮ በአብዛኛው ከወጪ ንግዱ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ እንደሚሆን ተረድቷል፡፡

ስለዚሁ ጉዳይ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰሎሞን አፈርቅንም ለማነጋገር ተሞክሯል፡፡ አቶ ሰሎሞን እንደገለጹት የንግዱ ማኅበረሰብ በተለይም ላኪዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ለስብሰባ ተጠርተዋል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱም ለተሳተፎ መጋበዙን ገልጸዋል፡፡

ይሁንና መንግሥት በጊዜያዊ ጉዳዮች ላይ የሚያደርገውን ርብርብ በዘላቂ መፍትሔዎች ላይ በማድረግ ለውጥ እንዲኖር መሥራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡ የአገሪቱ የወጪ ንግድ ለውጥ እንዲያሳይ ከግብርና ሸቀጦች ላኪነት ወደ ፋብሪካ ውጤቶች ላኪነት መለወጥ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ መንግሥት በአገር ውስጥ እየታየ ያለውን ከፍተኛ የፍላጎት ዕድገት ከማሟላት ባሻገር ትርፍ ምርት በማምረት ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚችልበትን የተሟላ መሠረተ ልማት መዘርጋት እንደሚጠበቅበትም ጠቅሰዋል፡፡

አገሪቱ ዘንድሮ የሚጠበቀውን የወጪ ንግድ አፈጻጸምና የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማግኘት ካልተቻለባቸው አንኳር ጉዳዮች መካከል የአገሪቱ የፀጥታ ችግር እንዲሁም ከቦታ ቦታ ምርት ለማዘዋወር ያለው ሥጋት ተጠቃሽ እንደሆነ አቶ ሰለሞን ጠቅሰዋል፡፡ የዓለም ኢኮኖሚ ያሳየው መዳከምና ለሸቀጥ ዕቃዎች የታየው የገበያ መቀዛቀዝም ምክንያት እንደሆኑ አስታውቀው፣ መንግሥት ከቢሮክራሲው ባሻገር በአገር ውስጥ ለሚመረቱ የፋብሪካ ውጤቶች ትኩረት መስጠት እንደሚጠበቅበት፣ የሜካናይዝድ እርሻን በማስፋፋት ልማዳዊውን የግብርና ስልት መቀየርም የመንግሥት የቤት ሥራዎች እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡

‹‹ዋናው መሠረታዊ ለውጥ ትርፍ ምርት እንዲመጣ ማድረግ፣ አዲስ ምርት ወደ ኢኮኖሚው ማምጣት መቻል እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ ምርቶች የሚተኩ ምርቶችን በአገር ውስጥ ማምረት መቻል ነው፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ስንዴ ከውጭ እያስመጡ ያንን ለየዱቄት ፋብሪካዎች ሰፍሮ በመስጠት ለውጥ አይመጣም ብለዋል፡፡ ይልቁንም መንግሥት ከገበሬው የሚተርፈውን አነስተኛ ምርት ከመጠበቅ ይልቅ ትርፍ ማምረት የሚያችሉ አሠራሮችን በመዘርጋት ለፋብሪካዎች እንደልብ ማቅረብ የሚቻልባቸውን ለውጦች ማምጣት መቻል እንዳለበትም መክረዋል፡፡

ይሁንና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ነገ እንደሚደረግ ለተጠራው ስብሰባ የንግድ ምክር ቤቱ የተጠራው እንዲሁ ለተሳትፎ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሰለሞን፣ ከዚህ ይልቅ ግን የጉዳዩ ባለቤት የንግድ ማኅበረሰቡ እንደመሆኑ መጠን ውክልናው ያለው ተቋም በጥናት ላይ የተመሠረተ የመፍትሔ ሐሳብ ይዞ መቅረብ የሚችልበት ዕድል ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡ መንግሥትም ‹‹ነገሩን ለባለቤቱ›› በመተው የችግሩን ምንጭ ከነመፍቻው አጣቅሰው እንዲቀርቡ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

 

Standard (Image)

ንግድ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ላይ የሚያሳልፈው ውሳኔ እየተጠበቀ ነው

$
0
0

 

-የአማራ ክልል ንግድ ምክር ቤት ዕግድ ወጥቶበታል

የአገሪቱን የንግድ ማኅብረሰብ የሚወክለው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት  ምክር ቤት ሲያወዛግብ የቆየውን ጠቅላላ ጉባዔ ለማካሄድ የንግድ ሚኒስቴርን ውሳኔ እየተጠባበቀ እንደሚገኝ ገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ሰሎሞን አፈወርቅ ለወራት እየተስተጓጎለ ለዘለቀው የንግድ ጠቅላላ ጉባዔና የአመራር አባላት ምርጫ ጋር በተያያዘ ስለተፈጠረው ችግር ለመጀመርያ ጊዜ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው፡፡

አቶ ሰሎሞን መጋቢት 14 ቀን 2009 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል በሰጡት መግለጫ፣ ምክር ቤቱ የገጠመውን ችግር ለመፍታት የተለያዩ አማራጮችን ሲጠቀም ቆይቷል፡፡ በመጨረሻም ንግድ ሚኒስቴር ጣልቃ ገብቶ በመፈተሹ የተፈጠሩት ችግሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ እልባት አግኝተው ጠቅላላ ጉባዔው በቅርቡ ይጠራል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ የሚኒስቴሩ ውሳኔ ከምርጫ ሥነ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ችግር እንዳለባቸው የተገለጹ የንግድና የዘርፍ ምክር ቤቶች፣ በሕጉ መሠረት ምርጫ ካካሄዱ በኋላ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡ ይህን ለማድረግ ግን የንግድ ሚኒስቴር ውሳኔ እየተጠበቀ እንደሚገኝ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ የዘገየውን ጠቅላላ ጉባኤና አዲስ የአመራር አባላት ምርጫ ሥነ ሥርዓትም ከሁለት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሊካሄድ እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡

አሁን ያለው የንግድ ምክር ቤቱ አመራር የሥልጣን ዘመኑ መስከረም 2009 ዓ.ም. እንዳበቃ ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ ሁለት ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤውን ለመጥራት በማሰብ ጥቅምት 9 እና ጥር 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ሊደረጉ የነበሩ ፕሮግራሞች ተሰርዘዋል፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤና ምርጫ ያልተካሄደባቸው ምክንያቶች ናቸው ብለው ከጠቀሷቸው መካከል አንዱ የንግድ ምክር ቤቱን መተዳደሪያ ደንብ የመጣስ ድርጊት መፈጸሙ ነው፡፡

የተወሰኑ ንግድ ምክር ቤቶች በአዋጁና በሕገ ደንቡ መሠረት ምርጫ ማካሄድ ሲገባቸው ይህንን በሕጉ መሠረት ባለማድረጋቸው ምንክያት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባኤውን ማካሄድ ተስኖት ቆይቷል፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮች ቀድሞም ሲያጋጥሙ እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ ሰሎሞን፣ ይህንን ለማስተካከል ዕርምጃ ወደ መውሰድ ሲገባ የተፈጠረና ሲንከባለል የመጣ ችግር ያስከተለው ውጤት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ አሁን ወደ ተፈጠረው ውስብስብ ችግር ውስጥ ከመገባቱ በፊት ንግድ ምክር ቤቱ የራሱን የማተካከያ ዕርምጃዎች መውሰድ ለምን አልቻለም? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ሰሎሞን፣ በሕገ ደንቡ መሠረት ዕርምጃ መውሰድ ይቻል እንደነበር ይናገራሉ፡፡ የምክር ቤቱን ሕገ ደንብ ያላሟላ አካል አይሳተፍም ማለት እንደሚቻል የጠቀሱት አቶ ሰሎሞን፣ ሆኖም ‹‹በፌዴራል አደረጃጀት ሥርዓት የምንመራ እስከሆነ ድረስ አንዳንድ ግለሰቦች በፈጠሩት ችግር ምክንያት የሚወሰደው ዕርምጃ ብዙ አባላቶች  ያሏቸውን ተቋማት ማግለል እንዳይሆን በማሰብ ዕርምጃውን አዘገይቷል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ጣልቃ የገባውም የተቀመጡ ሕጎች ባለመተግበራቸው እንደሆነ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ የተፈጠሩት ችግሮች እስኪፈቱ ድረስ መንግሥት ጠቅላላ ጉባኤው እንዳይካሄድ የሚያግድ ዕርምጃ እንዲወስድ አስገድዶታል፡፡ የመንግሥትን  ጣልቃ ገብነት በማስመልከት ጨምረው በሰጡት ማብራሪያ፣ መንግሥት በአዋጅ እንዲቋቋም የሚያስችል የዕውቅና ሰርተፍኬት የሚሰጥ በመሆኑ ‹‹ሕገወጥነት ሲኖር፤ ተቋሙ ለወከለው አካል አገልግሎት ከመስጠት ውጪ የውዝግብና የራስ ፍላጎት ማስፈጸሚያ ሆኖ ሲገኝ ወይም አዋጁን ሲጥስ ጣልቃ የመግባት ሥልጣን አለው፤›› በማለት የሚኒስቴሩን ጣልቃ ገብነት ተገቢነት እንዳለው አብራርተዋል፡፡

‹‹አዋጁንና መተዳደሪያ ደንባችሁን ጥሳችኋል ብሎ ካመነም ጣልቃ ይገባል ወይም ያገባኛል ማለት ይችላል፤›› ያሉት አቶ ሰሎሞን፣ ይህ ማለት ግን በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ይገባል ማለት እንዳልሆነም አጽንዖት ሰጥተውበታል፡፡ አሁንም ጣልቃ የገባው በቀጥታ እሱን የሚመለከቱ ጉዳዮች በማጋጠማቸውና የመጨረሻው መፍትሔም ከእሱ እንዲመጣ በማስገደዳቸው ምክንያት ጣልቃ እንዲገባ ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ ባጋጠሙት ችግሮች ውስጥ በአብዛኛው የግለሰቦች ተፅዕኖ ጎልቶ መታየቱም ተገልጿል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱን መጠቀሚያ የሚያደርጉ ሰዎች ለችግሩ መባባስ ምክንያት ሆነዋል ተብሎ ለቀረበው ጥያቄም፣ ‹‹በየጊዜው ከሚታየው ነገር መገመት የሚቻለው በዚህ አመራር ቦታ የሚቀመጥ አካል ራሱን እንደ ባለሥልጣን የማየት ፍላጎት መኖሩን እንዲሁም ለራስ ጥቅም እናገኛለን በማለት አንዳንድ ግለሰቦች ችግሩ እንዲባባስ አድርገዋል፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡  

ሌላው ለችግሩ መባባስ የተጠቀሰው የላላ የቁጥር አሠራር መኖሩ ነው፡፡ እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፣ አሁን ለችግሩ መንስኤ ነበሩ የተባሉት በርካታ አባላት የያዙ እንደ አማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ምክር ቤቶች ከምርጫ ጋር በተያያዘ በታየባቸው ክፍተት ምክንያት ከዚህ ቀደም ያካሔዷቸው ምርጫዎች እንዲደገሙ ተወስኗል፡፡  

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለጠቅላላ ጉባኤው የዚህን ያህል መዘግየት ምክንያት ከነበሩና ድጋሚ ምርጫ እንዲያካሂዱ ከተወሰነባቸው መካከል አንዱ የሆነው የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ምርጫ እንዲደረግ የአማራ ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ ያስተላለፈው ውሳኔ አልተተገበረም፡፡

ቢሮው የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሕግን የተከተለ ምርጫ ባለማካሄዱ፣ መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. የተደረገውን ምርጫ በመሻር አዲስ ምርጫ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ዳግመኛ እንዲያካሂድ በደብዳቤ ያሳወቀው የካቲት 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ነበር፡፡ ሆኖም ይህ ቀነ ገደብ ካለፈ አንድ ወር አስቆጥሯል፡፡ በአቶ ጌታቸው አየነው የሚመራው እና የተሻረው ቦርድ አባላት የቢሮውን ውሳኔ መቃወማቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ቢሮው ግን ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራና ምርጫ እንዲደረግ ያስተላለፈው ውሳኔ በማን አስፈጻሚነት እንደሚከናወን አለመገለጹ ክፍተት እንደሆነም ሲገለጽ ነበር፡፡ ዳግመኛ ይካሄድ የተባለው ምርጫ ቀነ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት የተሻረው ቦርድ በአቶ ጌታቸው ስም ደብዳቤ በጻፈው መሠረት የክልሉ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት መጋቢት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ ለአባላቱ ጥሪ አስተላልፎ ነበር፡፡

ይህ ቦርድ ጠቅላላ ጉባኤ ለመጥራት ሥልጣን የለውም እየተባለ እንዴ ሊጠራ ቻለ? የሚለው ጥያቄ አነጋገሪ ቢሆንም፣ ይህንን የስብሰባ ጥሪ ግን የክልሉ ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ መጋቢት 16 ቀን 2009 ሊካሄድ ታስቦ የተላለፈውን የጉባኤ ጥሪ ያውቅ እንደነበር ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ ሆኖም ከዕውቅና ውጭ የተሰራጨ ጥሪ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች ሲወጡ ግን መጋቢት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. ሊደረግ የነበረው ጉባኤ መካሄድ እንዳይችል ተደርጓል ተብሏል፡፡

ከዚህ ባሻገር የንግድ ቢሮው የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የምዝገባ ሰርተፍኬት እንዲታገድ መወሰኑም ታውቋል፡፡ የዕውቅና ሰርተፍኬቱ እንዲሰረዝ ከሚለው ውሳኔ ባሻገር፣ ጠቅላላ ጉባኤው ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን ቢሮው ይፋ አድርጓል፡፡

በተመሳሳይም የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምርጫ እንዲደገም ንግድ ሚኒስቴር ቢወስንም፣ እስካሁን ግን ምርጫውን ለመድገም የሚያስችል ጥሪ ለአባላት አልተላለፈም፡፡

 

Standard (Image)

የአገር ውስጥ ተቋራጮች በመንገድ ግንባታ ከፍተኛውን ድርሻ ቢይዙም በገንዘብ የውጭዎቹ ብልጫውን ወስደዋል

$
0
0

 

 

  • አገር በቀሎቹ የ92 ቢሊዮን ብር ሲደርሳቸው የውጮቹ የ114 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክቶችን አግኝተዋል

በዳዊት ታዬ

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ከ1989 ዓ.ም. ጀምሮ እስካለፈው ሳምንት መጨረሻ ድረስ በጠቅላላው 604 የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ለውጭና ለአገር ውስጥ ተቋራጮች በማስተላለፍ አስገንብቷል፤ እስገነባም ይገኛል፡፡

እንደ ባለሥልጣኑ መረጃ፣ እስከ 2008 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ በውጭና በአገር ውስጥ ተቋራጮች ተገንብተው ያለቁና በመገንባት ላይ የሚገኙት ፕሮጀክቶች 579 ናቸው፡፡ በ2009 በጀት ዓመት ስምንት ወራት ውስጥም 25 አዳዲስ ፕሮጀክቶች  ውለታ የተገባባቸው በመሆኑ የፕሮጀክቶቹን ቁጥር 604 አድርሰውታል፡፡

እስከ 2008 መጨረሻ ድረስ የነበሩት 579 ፕሮጀክቶች ጠቅላላ ወጪያቸው 184 ቢሊዮን ብር ያህል የነበረ ሲሆን፣ በ2009 የታከሉት 25 ፕሮጀክቶች ሲካተቱበት አጠቃላይ የፕሮጀክቶቹ ወጪ ከ206 ቢሊዮን ብር በላይ ይደርሳል፡፡

ይህንን ያህል ወጪ ከጠየቁት ፕሮጀክቶች ውስጥ የአገር ውስጥ ተቋራጮች 470ዎቹን በማሸነፍ የበላይነቱን ወስደዋል፡፡ ይህም ባለፉት 20 ዓመታት ለተቋራጮች ከተሰጡት ፕሮጀክቶች 78 በመቶ ያህሉን ድርሻ እንዲይዙ ያስቻሏቸው መሆናቸውን የባለሥልጣኑ መረጃ ያስረዳል፡፡

ቀሪዎቹ 134 ፕሮጀክቶች ወይም ወደ 22 በመቶ የሚሆነው በውጭ ተቋራጮች መያዛቸው ታውቋል፡፡ እንደ ባለሥልጣኑ መረጃ ከሆነ፣ አብዛኛውን ፕሮጀክቶች የአገር ውስጥ ተቋራጮች ቢረከቡም ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁትን ሥራዎች ግን የውጭ በተለይም የቻይና ተቋራጮች ተረክበዋል፡፡ የባለሥልጣኑ መረጃ በሚያሳየው መሠረት እስከ 2008 ዓ.ም. መጨረሻ ለግንባታ ከተሰጡት ፕሮጀክቶች ውስጥ ከ102.7 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን ሥራዎች ወስደዋል፡፡ በ2009 ዓ.ም. የተላለፉት ኮንትራቶች ሲታከሉባቸው የውጭ ተቋራጮች 114 ቢሊዮን ብር ያህል ዋጋ ያላቸውን ሥራዎች እንዳገኙ መረጃው ያመለክታል፡፡

የአገር ውስጥ ተቋራጮች የወሰዷቸው ፕሮጀክቶች ደግሞ ዋጋ 2008 መጨረሻ ላይ ከነበረው 82.2 ቢሊዮን ብር በተጨማሪ በ2009 በጀት ዓመት የተፈረሙት ታክለውበት ከ92 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ፕሮጀክቶችን እንዳገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በውጭ ተቋራጮች ከተሠሩትና በመሠራት ላይ ከሚገኙት መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን የወሰዱት የቻይና ተቋራጮች ናቸው፡፡ ባለፉት ሰባት ወራት ውስጥ ባለሥልጣኑ ለውጭ ኩባንያዎች ከሰጣቸው 11 ፕሮጀክቶች ውስጥ አሥሩን ቻይና ኮንትራክተሮች እንደወሰዱ መገለጹ ይታወሳል፡፡ ከቻይናዎቹ ባሻገር በኢትዮጵያ የመንገድ ግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች የሠሯቸውና አሁንም እየገነቧቸው የሚገኙት መንገዶች ብዛት 14 ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሐዋክ የተባለው የየመን ኩባንያ ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር የሚጠይቁ ሦስት ፕሮጀክቶችን ከመውሰዱ ውጭ ሌሎቹ በአንድና በሁለት ፕሮጀክቶች ተወስነዋል፡፡

አንዳንዶቹ የቻይና ተቋራጮች እንደውም ከሁለት  በላይ ፕሮጀክቶችን ተረክበው የሠሩና በመሥራት ላይ የሚገኙም አሉ፡፡ ከአምስት በላይ ፕሮጀክቶችን የተረከቡ የቻይና ተቋራጮም እንዳሉም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የመንገድ ግንባታ ሥራ ውስጥ በመሳተፍ ላይ የሚገኙ የቻይና ተቋራጮች ብዛት ከ20 በላይ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከሦስት በላይ ፕሮጀክቶችን የወሰዱት ሲጂሲኦሲ፣ ቻይና ኮሙዩኒኬሽንስ ኤንድ ኮንስትራክሽን ካምፓኒ (ሲሲሲሲ)፣ ቻይና ሬልዌይ ቁጥር 3፣ ቻይና ሬል ዌይ ቁጥር 17 እንዲሁም ቻይና ሲኖ ሃይድሮ የተባሉት ተቋራጮች ይጠቀሳሉ፡፡ ከቻይኖቹ ባሻገር የህንድ፣ የኮርያ፣ የግብፅ፣ የየመን፣ የስፔንም ድርሻቸውን ይዘዋል፡፡ በዚህ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የሩስያ ተቋራጭ መምጣቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በመንገድ ግንባታ ሥራ የቻይና ተቋራጮች የገንዘብ ድርሻ ሲተመን ከፍተኛውን መጠን ሊይዙ የቻሉት በራሳቸው አገር የፋይናንስ ተቋማት የሚታገዙ በመሆናቸው ጭምር ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው ጨረታ ውስጥ የሚቀመጠው የመወዳደሪያ መስፈርት የአገር ውስጥ ተቋራጮን የሚገድብ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ የሚጠይቋቸውን መሥፈርቶች ማሟላት የማይችሉ በመሆናቸው በውጭ ኩባንያዎች ብልጫው እየተወሰደባቸው እንደሚገኙ የባለሥልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ይገልጻሉ፡፡

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ መንግሥት በጀት የሚገነቡ መንገዶችን የአገር ውስጥ ኩባንያዎች እንዲወሰዱ እያደረገ መሆኑን የገለጹት አቶ ሳምሶን፣ በዚህ ምክንያት በየዓመቱ በአገር በቀል ኮንትራክተሮች የሚያዙ የመንገድ ፕሮጀክቶች ቁጥር እየጨመረ እንደመጣ ጠቅሰዋል፡፡ በአገር ውስጥና በውጭ ኮንትራክተሮች የተሠሩና እየተሠሩ ስላሉ ፕሮጀክቶች የተመለከተው የባለሥልጣኑ መረጃ፣ እስከ 2003 መጨረሻ ድረስ ለኮንትራክተሮች ከተሰጡ ፕሮጀክቶች 58 በመቶ የሚሆኑት ለአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች የተላለፈ ሲሆን፣ ይህ መጠን በ2007 ዓ.ም. 76 በመቶ እንደደረሰም ይጠቁማሉ፡፡ አሁን ደግሞ 79 በመቶ መድረሱ ዕድገቱን ያሳያል፡፡

በተመሳሳይ መንገድ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በሚያወጣቸው የመንገድ ግንባታ ጨረታዎች ላይ ተሳታፊ የነበሩ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች መጠን በየዓመቱ እየጨመረ ነው ተብሏል፡፡ ለዚህም እንደማሳያ የሚቀመጠው በ2003 ዓ.ም. በመንገድ ግንባታ ዘርፍ ይሳተፉ የነበሩ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች 15 ብቻ ነበሩ፡፡ በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ ደግሞ 75 ደርሰዋል፡፡ አሁን ከ90 በላይ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች በመንገድ ግንባታ ዘርፍ እንደገቡ ተጠቅሷል፡፡

በመንገድ ግንባታ ዘርፍ የሚሰማሩ አዳዲስ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች እየገቡ ስለመሆናቸውም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ አጠቃላይ የመንገድ አውታር 8.2 በመቶ ዕድገት እያሳየ ነው ተብሏል፡፡ በ2008 መጨረሻ ላይም የአገሪቱ የመንገድ ሽፋን መጠን 113,066 ኪሎ ሜትር ደርሷል፡፡

ይህ የመንገድ ሽፋን በ2007 ዓ.ም. 110,414 ኪሎ ሜትር የነበረ ሲሆን፣ በ1989 ዓ.ም. ደግሞ 18,810 ኪሎ ሜትር ብቻ እንደነበር መረጃው ያመለክታል፡፡ ከዚህ መንገድ ውስጥ 72 በመቶ የሚሆነው በጥሩ ይዞታ ላይ የሚገኝ እንደሆነም ይገለጻል፡፡ 

Standard (Image)

የቱሪዝም አባት አቶ ሀብተሥላሴ ታፈሰ የሚታወሱበት የ13 ወር ፀጋ መለያ

$
0
0

‹‹እኔ ያደግሁት ውጭ አገር ነው፡፡ የትም ዓለም ላይ 13 ወር የለም፡፡ ፒራሚድ ሲታይ ግብፅ ነው፡፡ አይፈልታወር ሲታይ ፈረንሣይ ነው፡፡ የነፃነት ሐውልት ሲታይ አሜሪካ አለ፡፡ እኛ የምንታወቅበት የለንም ነበር፡፡ ሁሉ ነገር ከዘር፣ ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ሳላውቀው አንድ ወቅት ላይ የ13 ወር ደመወዝ ይሰጠን ብዬ ጠየቅሁ፡፡ ወዲያው ይህንን ሐሳብ ወደ ቱሪስት መሳቢያነት መቀየር እንደሚቻል አሰብኩ፡፡ ሌላው ሁሉ ከዘር ከሃይማኖት ጋር የሚያያዝ ነበር፡፡ ላሊበላን ባደርግ ኢትዮጵያ በሙሉ ክርስቲያን ባለመሆኑ ችግር ነበረበት፡፡ የአሥራ ሦስት ወር ፀሐይ ግን ከምንም ነገር ጋር አይገናኝም፡፡ ምንም የፖለቲካና የሃይማኖት ንክኪ የለውም፡፡ አሁን ከዚያ የበለጠ ከተገኘ ደግሞ ቶሎ መተካት ነው፡፡ ምንም ችግር የለበትም፡፡››በማለት በአንድ ወቅት ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የተናገሩት አቶ ሀብተሥላሴ ታፈሰ በኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ መሥራች፣ የአሥራ ሦስት ወራት ፀጋ (13 Months of Sunshine)በሚል መጠሪያ የአገሪቱ ቱሪዝም ለዘመናት ሲያስተዋውቅ የኖረውን መለያ የፈጠሩና በዘርፉ በርካታ ሥራዎችን ያስተዋወቁ፣ የተገበሩ የቱሪዝም አባት ናቸው፡፡ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ይህንን ውለታቸውን ቆጥሮ ዕውቅና በመስጠት ለመጀመሪያ ጊዜ ሽልማት አበርክቶላቸዋል፡፡ ሰሞኑንም ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እጅ ለሁለተኛ ጊዜ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ በቱሪዝም መስክና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሔኖክ ያሬድና ብርሃኑ ፈቃደከጥቂት ዓመታት በፊት አነጋግረዋቸው ነበር፡፡ ይኸው ቃለ ምልልስ ለትውስታ ይሆን ዘንድ እንዲህ ቀርቧል፡፡  

ሪፖርተር፡- በዘርፉ በጠቅላላው ኢትዮጵያን ለምን ያህል ጊዜ አገልግለዋል?

አቶ ሀብተሥላሴ፡- ከመጀመሪያው እ.ኤ.አ. ከ1954 ጀምሮ አገልግያለሁ፡፡ ያኔ ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣሁ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ እሠራ ነበር፡፡ ከዚያ በግድ ይህንን ሥራ [ቱሪዝምን] እንድሠራ አዘዙኝ፡፡ ገባሁበት፡፡ ከባድ ሥራ ነው፡፡ ያን ጊዜ ካሜራ ወደ ኢትዮጵያ አይገባም ነበር፡፡ ሲገባም ጉምሩክ ይይዘዋል፡፡ ፈቃድ ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ማውጣትም ያስፈልግ ነበር፡፡ በዚህ ሰበብ ሁለት ጊዜ ታስሬያለሁ፡፡ ፎቶግራፍ ለምን ታነሳለህ ብለው ነው ያሰሩኝ፡፡ ያን ጊዜ ፎቶግራፍ የሚያነሳ ሰው ሰላይ ተደርጐ ይታሰብ ስለነበር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቱሪዝም ሙያዎ ኢትዮጵያን ምን ያህል ያውቋታል?

አቶ ሀብተሥላሴ፡- ያልደረስኩበት ቦታ የለም፡፡ በእግር፣ በፈረስ፣ በግመል፣ በሄሊኮፕተር፣ በአውሮፕላን ሁሉ ተዘዋውሬ ከ100 በላይ ሰው ያልረገጣቸው የኤርትራ ደሴቶችን አይቻለሁ፡፡ ትልቅ ሀብት ናቸው፡፡ ቢያውቁበት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መሰብሰብ ይችሉ ነበር፡፡ በጋምቤላ በኩል ጂካው ድረስ ሄጃለሁ፡፡ የደቡብ ሱዳን ጠረፍ ነው፡፡ በኤርትራ በኩል ቤንአመር ድረስ ወዳለው የጠረፍ ቦታ ደርሻለሁ፡፡ ቤንሻንጉልን በሙሉ እስከ ሱዳን ድረስ አዳርሻለሁ፡፡ መሥራት ካስፈለገ ማየት፣ ማወቅ ግድ ይሆናል፡፡ ካየን፣ ካወቅን በኋላ ማውራት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት እርስዎ ብዙ ሠርተዋል፡፡ ከሠሯቸው መካከል አሁንም ድረስ የሚታወቀው ኢትዮጵያ የአሥራ ሦስት ወር ፀጋ የሚለው አገሪቱ መጠሪያ ነው፡፡ ይህ የኢትዮጵያ መለያ ለብዙ ጊዜ ያገለገለ ነው፡፡ አሁን መቀየር አለበት የሚሉ አሉ፡፡ ይቀየር ቢባል ምን ይሰማዎታል?

አቶ ሀብተሥላሴ፡- ሁልጊዜ አንድ ነገር ሲፈጠርና የሚበልጠው ሲገኝ ያንን ማየቱ ተገቢ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ምክትል አፈንጉሥ ገብረ ወልድ ፎቅ ቤት ሠርተው ነበር፡፡ ያን ጊዜ በንጉሡ ዘመን የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ነበር፡፡ መንግሥቱ ንዋይ ደግሞ ጠንሳሽና የእኛም ዘመድ ነበር፡፡ ሰውየው ሰማይ ጠቀስ ፎቅ ሠርተሃል ተብለው ታሰሩ፡፡ ይህ ከሆነማ አፍርሱት ሲሏቸው የለም አንተን ነው የምናፈርሰው ብለው ገደሏዋቸው፡፡ አሁን ደግሞ በተገላቢጦሽ ሰማይ ጠቀስ ፎቅ እንዲሠራ ነው የሚፈለገው፡፡

ሪፖርተር፡- የአሥራ ሦስት ወር የፀሐይ ፀጋን እንዴት መረጡት?

አቶ ሀብተሥላሴ፡- እኔ ያደግሁት ውጭ አገር ነው፡፡ የትም ዓለም ላይ 13 ወር የለም፡፡ ፒራሚድ ሲታይ ግብፅ ነው፡፡ አይፈልታወር ሲታይ ፈረንሣይ ነው፡፡ የነፃነት ሐውልት ሲታይ አሜሪካ አለ፡፡ እኛ የምንታወቅበት የለንም ነበር፡፡ ሁሉ ነገር ከዘር፣ ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ሳላውቀው አንድ ወቅት ላይ የ13 ወር ደመወዝ ይሰጠን ብዬ ጠየቅሁ፡፡ ወዲያው ይህንን ሐሳብ ወደ ቱሪስት መሳቢያነት መቀየር እንደሚቻል አሰብኩ፡፡ ሌላው ሁሉ ከዘር ከሃይማኖት ጋር የሚያያዝ ነበር፡፡ ላሊበላን ባደርግ ኢትዮጵያ በሙሉ ክርስቲያን ባለመሆኑ ችግር ነበረበት፡፡ የአሥራ ሦስት ወር ፀሐይ ግን ከምንም ነገር ጋር አይገናኝም፡፡ ምንም የፖለቲካና የሃይማኖት ንክኪ የለውም፡፡ አሁን ከዚያ የበለጠ ከተገኘ ደግሞ ቶሎ መተካት ነው፡፡ ምንም ችግር የለበትም፡፡

ሪፖርተር፡- ዛሬም ድረስ መሥራት የሚፈልጓቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡

አቶ ሀብተሥላሴ፡- መርዳት ነው የምፈልገው፡፡ መሥራት ያለባቸው የተመደቡት ሰዎች ናቸው፡፡ እነርሱን ለመርዳት ዝግጁ ነኝ፡፡ አምስት ያህል ፕሮጀክቶች አሉኝ፡፡ ፍልውኃን በአግባቡ አልተጠቀምንበትም፡፡ ወንዶገነትና ሶደሬ አካባቢ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ነገር ግን ከ3,000 በላይ ፍልውኃ በየቦታው አለን፡፡ ያ የማያልቅ፣ ከወርቅና ከከበረ ድንጋይ ሁሉ የበለጠ ሀብት ነው፡፡ ነገር ግን አልተሠራበትም፡፡ እኔጋ ጥናቱ አለ፡፡ ዩኔስኮ ውኃውን ጨምሮ ያገኘው ጉዳይ አለ፡፡ ጥናቱ በእጄ ስላለ ለመንግሥት እሰጣለሁ፡፡ ይሠሩበታል ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁን ቱሪስቶች ያሉት እዚሁ ከጐናችን ነው፡፡ ዱባይ፣ ኤምሬቶች አሉ፡፡ ድሮ ዓረብ ድሃ ነው፡፡ አሁን ዓለምን የያዙ እነሱ ናቸው፡፡ ፍልውኃ አረንጓዴያማ መስክ ይወዳሉና አቅሙ ላላቸው ባለሀብቶች መስጠት ከተቻለ ሰው ይመጣል፡፡ ከዱባይ አዲስ አበባ የሦስት ሰዓት በረራ ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ሰው ይመጣል ብሎ መጠበቅ ከባድ እየሆነ ነው፡፡ ቀውስ ላይ ናቸው፡፡ የቅርብ አገሮች ግን መምጣት የሚችሉበት አቅም አላቸው፡፡ በግብፅ ለሁለት ዓመት ቆይቻለሁ፡፡ አባቴ አምባሳደር ነበሩና በዚያ ኖረናል፡፡ በጣም ቃጠሎ ነው፣ ሲበዛ ሞቃት ነው፡፡ በክረምት ብቻ ወደ አሌክሳንድርያ እንሄድ ነበር፡፡ አሁንም በጣም ሞቃት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ የአሥራ ሦስት ወር ፀጋ ብለው ነበር ብዙ ፀጋ አለን ማለት ነው?

አቶ ሀብተሥላሴ፡- ደመወዝ የለውማ፡፡ የአሥራ ሦስት ወር ደመወዝ አይከፈልበትም፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ ኬንያ ያሉት አገሮች ግን የዱር እንስሳት ሀብት ብቻ እያላቸው ነገር ግን ብዙ የተጠቀሙበት ሁኔታ አለ፤

አቶ ሀብተሥላሴ፡- እነሱ ስላሠሩ ነዋ፡፡ እኛ አንሠራም፡፡ አንዱ ሲሠራ አሥሩ ወደኋላ ይጐትታል፡፡ ምቀኝነት አለ፡፡ የሐበሻ ፀባይ አብሮ መሥራት ስለሌለው መድረስ ያለብን ቦታ አልደረስንም፡፡

ሪፖርተር፡- አየር በዕቃ ሞልተው ለመሸጥ የሞከሩበት ጊዜ እንደነበር ይነገራልና ስለእርሱ ቢነግሩን?

አቶ ሀብተሥላሴ፡- የኢትዮጵያ አየር የትም ዓለም ላይ አይገኝም፡፡ አንድ ጊዜ ንጉሡ ጋር ገባሁና አየር ይሸጣል አልኳቸው፡፡ ገንዘብ ሚኒስትሩ መጡና ምን ይለፈልፋል ብለው አጣጣሉኝ፡፡ አጋጣሚ ሆኖ እ.ኤ.አ. በ1970 በኦሳካ ኤግዚቢሽን ነበርና ወደ ቶኪዮ ዞር ዞር ብዬ ለማየት ሄድኩ፡፡ አንድ ቦታ ላይ የፊጂ ተራሮች የሚል ጽሑፍ ያለበት ቆርቆሮ አየሁ፡፡ ሳነሳው ባዶ ነው፡፡ ውስጡ ያለው የፊጂ አየር ብቻ ነው፡፡ ሰው ገዝቶ በአፍንጫው መማግ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ገዛሁና ወደ ንጉሡ አመጣሁት፡፡ ስጦታ አምጥቼሎታለሁ አልኩና ሰጠኋቸው፡፡ አንስተው ሲያዩ ምንም የሌለው መስሏቸው ምን ትቀልዳለህ አሉኝ፡፡ አየር ይሸጣል ያልኩዎትኮ ይኼ ነው፤ ገዝቼ መጣሁ አልኳቸው፡፡ ገንዘብ ሚኒስትሩን ጠሩና ታስታውሳለህ ያልከውን ይኸውልህ አየር ይሸጣል አሏቸው፡፡ ይኼንን አሁንም ማድረግ ይቻላል፡፡ አየር በዕቃ ሞልቶ እንዲማግ ማድረግና መሸጥ ይቻላል፡፡ ውኃ በፕላስቲክ እየተሸጠ እኮ ነው፡፡ ሰው ግን አያምንም፣ አይቀበልም፡፡ አገሪቱን ያጠቃት በምቀኝነት፣ በዘር፣ በሃይማኖት መከፋፈላችን ነው፡፡ አንድ ሆነን ካልሠራን ከባድ ነው፡፡ አሁን ብዙ ለውጥ መጥቷል፡፡ ከሞት የተመለስኩ ያህል የሚሰማኝ ጊዜ አለ፡፡ ሴቱ ሁሉ እንደ ልቡ ነው፡፡ ወደ ዱባይ ወደ መሳሰሉት አገሮች ሲሄዱ፣ ሲሠሩ የሚታዩ ቆነጃጅቶች ብዙ አሉ፡፡ በእኛ ጊዜ እንዲህ አይታሰብም፡፡ ብዙ ለውጥ አለ፡፡ የሰው አስተሳሰብ ተቀይሯል፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ኒውዝላንዳዊ ሚሊየነር ኢትዮጵያን በሄሊኮፕተር ጐብኝቶ መደነቁን ሲናገሩ ነበርና ስለእርሱ ቢገልጹልን?

አቶ ሀብተሥላሴ፡- ፓይለቱ የሰውየው ልጅ ባል ነው፡፡ ሰውየው ደግሞ ባለሄሊኮፕተር ነው፡፡ የእርሱ አስጎብኚ ከእኔ ጋር የሚሠራ ነውና ተዟዙሮ አይቶ እኔን ማየት ፈለገና እራት ጋበዘኝ፡፡ ተኝታችኋል አለኝ፡፡ በሄሊኮፕተር እየተዘዋወርን ከ125 በላይ አገሮች አይተናል እንደ ኢትዮጵያ የሚሆን ግን አላየንም አለኝ፡፡ ሰውየው የምንም ፍላጎት የላቸውም፡፡ ለጥቅም ብለው ነው እንዳይባል አገራቸው ኤምባሲ እንኳ እዚህ የላትም፡፡ ሰውየው ደግሞ እጅግ ባለጠጋ ናቸው፡፡ ቢሊየነር በመሆናቸው ለጉብኝት ብቻ ነው የመጡት፡፡ ያዩትን አይተው ተኝታችኋል አሉኝ፡፡

ሪፖርተር፡- የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሽልማት ሲሰጥዎ፣ በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሽልማት ተጠራሁ ብለዋል፡፡ ለምንድን ነው ከዚህ በፊት ይህን ሁሉ ሠርተው ያልተሸለሙት?

አቶ ሀብተሥላሴ፡- ምቀኞች ስለሆንን፡፡ ሁሌም ሲጠሩኝ ለአንድ ወቀሳ ነው፡፡ ቤተክህነት ተጠርቼ በቴሌቪዥን ለምን እንዲህ ተናገርህ እባላለሁ፣ የአገር ውስጥ ገቢ ይጠሩኝና እወቀሳለሁ፡፡ ያን ጊዜ ከቀረጥ ነፃ ሱቅ ከፍተን ነበር፡፡ የእኛ ቢሮ ከመንግሥት ቢሮዎች ሁሉ ሀብታም የሚባለው ነበር፡፡ ያን ጊዜ ቱሪዝም በጀት 220 ሺሕ ብር ስለነበር በዚህ በጀት እንዴት አገርን ማሳደግ ይቻላል እያልሁ ከጃንሆይ ጋር እጨቃጨቅ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ቁልፉን ይዤ ሄድኩና ጃንሆይ ይኼንን መሥሪያ ቤት ለሒሳብ ሹም ይስጡት ደመወዝ ከመክፈል ውጪ ሌላ ሥራ መሥራት አልቻልኩም አልኳቸው፡፡ የዲውቱ ፍሪ ፈቃድ ስጡኝ ብዬ ጃንሆይን ጠየቅሁ፡፡ ኋላ ላይ ገንዘብ ሚኒስትሩ መጡና እኛ ኮንትሮባንድ መቆጣጠር አቅቶናል፣ ሀብተሥላሴ ደግሞ አናታችን ላይ ኮንትሮባንድ ለመፍጠር ይፈልጋል አሉኝ፡፡ ንጉሡም ሥራህ መቆጣጠር ነው እንጂ ሥራ አይሥራ ነው የምትለው ወይስ መቆጣጠር አልችልም ነው? ብለው ጠየቋቸውና ተፈቀደልኝ፡፡

ሥራው ሊጀመር ሲል ደግሞ ገንዘብ ስለጠፋ የአባቴን ካርታ ወስጄ ለአንድ እብድ ሰጠሁና 5,000 ዶላር ተበደርኩ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ማግኘት ተቻለን፡፡ በአንድ ወቅት ከመላው ኢትዮጵያ የእኛ መሥሪያ ቤት ነበር ሀብታም የነበረው፡፡ አንድ ሚኒስትር ሲሾም በጊዜው እንዲነግድ አይፈቀድለትም ነበር፡፡ ለእኛ ተፈቅዶ ነበርና ብዙ ገንዘብ አስገብተናል፡፡ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ሕንፃ ተሠርቶ ሥራ ሲጀምር የእኛ መኪኖች ነበሩ የሚያገለግሉት፡፡ 46 ያህል ነበሩን፡፡ እኔ እንደ ሾፌር፣ እንደ አስጐብኚ፣ እንደ ፎቶግራፍ አንሺ እየሆንኩ ሠርቻለሁ፡፡ በኋላ ምቀኛ በዛና የዲውቲ ፍሪ ገንዘብ ወደ መንግሥት ይግባ አሉ፡፡ ያ አሠራር ዛሬ ቆይቶ ቢሆን ኖሮ አሥር ሚሊዮን ሰዎች በተሰማሩበት ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- በጊዜው ሴቶችን ፎቶግራፍ ያነሱ ነበርና ከንጉሡ ዘንድ የገጠመዎት ጉዳይ አለ ይባላል፤

አቶ ሀብተሥላሴ፡- አዎ፡፡ አንዲት የጋምቤላ ሴት ፎቶግራፍ አንስቼ ነበር፡፡ ሴትየዋ ጡቷ ቆንጆ ነበርና አንስቼ ፖስተሩ ከመታተሙ በፊት ናሙናውን ለንጉሡ አስገብቼ ጠረጴዛ ላይ እደረድር ነበር፡፡ ንጉሡ መጥተው ሲያዩ ይኼ ምንድን ነው አሉና ጠየቁኝ፣ አይ ቱሪስቶች እንዲህ ማየት ይወዳሉ ስላቸው፣ አንተም ትወዳለህ ይባላል አሉኝ፡፡ በኋላ ታትሞ ሲወጣ ሳንሱር ይደረግ ነበር ራቁት እያሳየ ነው ብለው ንጉሡ ጋር መልሰው ይዘው መጡ፡፡ ንጉሡም አይተናል አሉና መለሷቸው፡፡ ከዚያ በኋላ የቱንም ነገር ከመሥራቴ በፊት ቀድሜ ለንጉሡ ስለማሳይ አይተናል እያሉ ሚኒስትሮችን ይመልሷቸው ነበር፡፡ ብዙ መሥራት አንወድም፡፡ ስንሠራ ደግሞ ምቀኛው ወደኋላ የሚጐትት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እሰጣለሁ ካሏቸው ፕሮጀክቶች አንዱ አንድ ብር ቢያንስ በአንድ ዶላር መመንዘር የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡ ይኼ አስማት አይደለም ሲሉም ሰምተናልና እንዴት ነው ይኼ የሚሆነው?

አቶ ሀብተሥላሴ፡- ይኼ አስማት አይደለም፡፡ እንዴት እንደሆን የምንነግረው ግን ለሚኒስትሩ ነው፡፡ እሳቸው ከተስማሙ በኋላ የእሳቸው ፕሮጀክት ይሁን፡፡ አሁን መናገሩ ጊዜው አይደለም፡፡ 

Standard (Image)

ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለኦሞ ኩራዝ ስኳር ፕሮጀክቶች የመስኖ ግንባታ ሊካሄድ ነው

$
0
0
  • ንግድ ባንክ ለፕሮጀክቱ አሥር ቢሊዮን ብር አበድሯል

በደቡብ ክልል በመስኖ ልማት ዘርፍ ትልልቅ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ እንደሆነ የተጠቀሰውና 185 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው የኦሞ ኩራዝ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ዋና የቦይ፣ የመስኖ ካናሎችንና ተያያዥ ግንባታዎችን ለማከናወን ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለው ስምምነት ተፈረመ፡፡

በግዙፉ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ባለቤትነት ይህንን ሜጋ ፕሮጀክት እንዲገነቡ ከተመረጡት ውስጥ ሦስቱ በኮርፖሬሽኑ ሥር የሚተዳደሩት የግድብና መስኖ አውታር ልማት ዘርፍ፣ የውኃ መሠረተ ልማት ኮንስትራክሽን ዘርፍና የትራንስፖርት ኮንስትራክሽን መሠረተ ልማት ዘርፍ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሦስቱ ባሻገር የግንባታ ሥራው የተሰጣቸው ሌሎች ሁለት ተቋማት ደግሞ የደቡብ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራከሽን ኢንተርፕራይዝና የቻይናው ጂያንግዚ ኃይድሮፓወር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል መሆናቸው ታውቋል፡፡

ግንባታውን እንዲያካሂዱ የተመረጡት እነዚህ ተቋማት 185 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን የኦሞ ኩራዝ የቦይ፣ የመስኖ እንዲሁም የመዋቅር ግንባታ ፕሮጀክቱን ተከፋፍለው የሚሠሩ ሲሆን፣ አጠቃላይ የግንባታ ሥራዎቹን በአሥር ወራት አጠናቀው ለማስረከብ በመስማማት ቅዳሜ፣ የካቲት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. ከኮርፖሬሽኑ ጋር የግንባታ ውል ተፈራርመዋል፡፡  

ከፕሮጀክት ውስጥ የቻይናው ጂያንግዚ ኃይድሮፓወር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር 4.1 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚጠይቀውን የቦይ ግንባታ፣ የፕሮጀክቱን የውኃ መቆጣጠሪያና መሰል መዋቅራዊ ግንባታዎች ያከናውናል፡፡

 የኦሞ ኩራዝ መስኖ ልማት ፕሮጀክት አካል የሆኑትን ሁለት የመስኖ ቦይ መስመሮች ግንባታዎችን በኮርፖሬሽኑ ሥር እንደ እህት ኩባንያ የሚታየው የውኃ መሠረተ ልማት ኮንስትራክሽን ዘርፍ ከ1.49 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለመገንባት ፊርማውን አኑሯል፡፡ የዚሁ ፕሮጀክት አካል የሆነውን ሦስተኛውን የመስኖ ቦይ መስመር ግንባታም ይኸው የውኃ መሠረተ ልማት ኮንስትራክሽን ዘርፍ በ485 ሚሊዮን ብር እንደሚገነባ ስምምነቱ በተደረገበት ወቅት ተገልጿል፡፡

የፕሮጀክቱን አራተኛና አምስተኛ የሥራ ክፍሎች ደግሞ የደቡብ ውኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ኢንተርፕራይዝ በ1.97 ቢሊዮን ብርና በ394 ሚሊዮን ብር እንደሚገነባ ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት ተነግሯል፡፡

ስድስተኛው የፕሮጀክቱ ክፍል የሆነውን የመስኖ ቦይ ግንባታ እንዲሠራ የተመረጠውና ቅዳሜ ስምምነት የፈጸመው የትራንስፖርት መሠረተ ልማት ዘርፍ የተባለው ሌላኛው በኮርፖሬሽኑ ሥር የሚገኝ የግንባታ ዘርፍ ተቋም ነው፡፡ ይህ ተቋም የተረከበው ሥራ በጠቅላላው 584 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚጠይቅ ታውቋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይለ መስቀል ተፈራ (ኢንጂነር) እንደገለጹት፣ ከተለመደው የኮንትራት አሰጣጥ በተለየ መልኩ በ‹‹እደላ›› ሥርዓት ለግንባታ የተላለፉት ሥራዎች ላይ ከተሳተፉትና የኮንትራት ውል ከፈጸሙት ውስጥ ሦስቱ በኮርፖሬሽኑ ሥር የሚተዳደሩ፣ ነገር ግን ለየብቻቸው ራሳቸውን ችለው በተቋምነት የተዋቀሩ የተቋራጭ ሥራዎችን የሚያከናውኑ አካላት ናቸው፡፡

ያለጨረታ በእደላ ሥርዓት የግንባታ ሥራዎቹ የተሰጣቸው እነዚህ ተቋማት ከዚህ ቀደም የነበራቸው የሥራ አፈጻጸም ተገምግሞ በነበራቸው ጥሩ አፈጻጸም እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በአገር በቀል ኮንትራክተሮች ሊሠሩ የማይችሉና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ክፍተት ይኖርባቸዋል የተባሉትን ሥራዎች እንዲያከናውን  የቻይናው ኩባንያ እንዲሳተፍ መደረጉ በዕለቱ ከተሰጠው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በበጀት ዓመቱ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሠራ የተፈለገው የኦሞ ኩራዝ የመስኖ ቦይ እንዲሁም የውኃ መስመር ግንባታ ዋናው ዓላማ በአካባቢው የተገነቡት የስኳር ፋብሪካዎች ለአገዳ ልማት የሚያስፈልጋቸውን የውኃ አቅርቦት ለማድረስ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት ከስኳር ልማት ባሻገር በአቅራቢያው የሚካሄዱ ሌሎች ሥራዎችንም ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ በአገሪቱ የግብርና ሥራዎች በተለይም ለሰፋፊ እርሻዎች ልማት አዲስ ሞዴል አሠራር ሊሆን እንደሚችል የኮርፖሬሽኑ የግንባታና መስኖ ልማት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙላቱ ታፈሰ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ የቦይና የውኃ መስመሮች ግንባታውን ከማካሄድ ባሻገር ከአሥር ወራት በኋላ እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀውን ፕሮጀክት ተረክቦ በማስተዳደር ለስኳር ፋብሪካዎቹ ውኃውን በሽያጭ ያቀርባል ተብሏል፡፡ ስኳር ልማቱ የሚፈልገው የውኃ መጠን ምን ያህል እንደሆነ፣ ውኃ መቼ እንደሚፈልግ እንዲሁም ለስኳር ልማቱ የሚቀርበው ውኃ በምን ያህል ዋጋ እንደሆነና ሌሎችም ዝርዝር ጉዳዮች ተጠንተው ከስኳር ኮርፖሬሽን ጋር የውኃ ሽያጭ ስምምነት የተፈረመበት ፕሮጀክት እንደሆነም አቶ ኃይለ መስቀል ተናግረዋል፡፡ ሥራ አስፈጻሚው፣ የስኳር ፋብሪካዎቹ ለሚቀርብላቸው ውኃ ተገቢውን የአገልግሎት ዋጋ እንዲከፍሉ ይደረጋል ይበሉ እንጂ በሽያጭ ለሚቀርበው ውኃ ምን ያህል ዋጋ እንደተተመነለት ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

የመስኖ ፕሮጀክቱ 125 ሺሕ ሔክታር መሬት ውኃ ገብ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል ውኃ የመሸከም አቅምና አስተማማኝ ፍሰት እንዲፈጠር የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡ ከዚህ ውስጥ በመጀመርያው ምዕራፍ 25 ሺሕ ሔክታር በማልማት ለኦሞ ኩራዝ ስኳር አንድ፣ ሁለትና ሦስት ፋብሪካዎች የሸንኮራ አገዳ ለማቅረብ ያስችላል፡፡  ከዚያም 93 ኪሎ ሜትር ተጉዞ 50 ሺሕ ሔክታር የመስኖ መሬት በማልማት ለስኳር ፋብሪካ ቁጥር አምስት ሸንኮራ አገዳ ማቅረብ የሚያስችል አቅም ይኖረዋል፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሚገኝ ብድር የሚሸፈን ይሆናል፡፡ እንደ አቶ ኃይለ መስቀል ገለጻ፣ ለዚህ ፕሮጀክት ባንኩ አሥር ቢሊዮን ብር ብድር መፍቀዱ ታውቋል፡፡

ፕሮጀክቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የኦፕሬሽንና ጥገና ሥራዎችን በማከናወን የኮርፖሬሽን ግድብና መስኖ አውታሮች አስተዳደር ዘርፍ ባለቤት ሆኖ ከሚሸጠው ውኃ ብድሩ ተመላሽ ያደርጋል ተብሏል፡፡ ባንኩ ብድሩን የፈቀደውም በኢትዮጵያ የሚተገበረው የመስኖ የውኃ ሽያጭ ብድሩን ለማስመለስ የሚያስችል ገቢ እንደሚያገኝ በማመኑ እንደሆነም ተነግሯል፡፡

ፕሮጀክቱ ከአሥር ሺሕ በላይ ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎች በመፍጠር የአካባቢውን አርብቶ አደር ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው፣ የመስኖ ውኃው ለአካባቢው አርብቶ አደሮችና አርሶ አደሮች ጥቅም እንደሚሰጥ ጠቅሰዋል፡፡

ይህንን ፕሮጀክት ልዩ ከሚያደርገው አንዱ የመስኖ ግንባታው በሚከናወንበት ክልል የሚገኙ ፓርኮች ተፈጥሮአዊ ይዞታቸው ተጠብቆ እንዲቆይ፣ የውኃ ማስተላለፊያ መስመሩ ከ50 ኪሎ ሜትር በላይ በልዩ ግንባታ ተሸፍኖ እንዲሠራ ዲዛይን መደረጉ ነው ተብሏል፡፡ የዲዛይኑም ሆነ የግንባታው ሒደት ተፈጥሮን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ከፍተኛ ጥንቃቄ የተደረገበት ምሳሌያዊ ፕሮጀክት መሆኑን ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል፡፡ የማማከር ሥራውን የፌዴራል የኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ሥራዎች ኮርፖሬሽንና የደቡብ ዲዛይንና ኮንስትራክሽን ቁጥጥር ኢንተርፕራይዝ ተረክበዋል፡፡

የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከአንድ ዓመት በፊት ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ካፒታል መቋቋሙ ይታወቃል፡፡ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ግዙፍ መንግሥታዊ ኩባንያ ለመፍጠር ታስቦ ሲቋቋም፣ ቀደም ብለው በተናጠል ሲንቀሳቀሱ የነበሩትን የኢትዮጵያ መንገድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ የውኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ የትራንስፖርት ዲዛይንና ቁጥጥር ሥራዎች ድርጅትን በማዋሃድ ነው፡፡

በአገሪቱ ከሚገኙ ግዙፍ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች አንዱ ሆኖ የመጣው ይህ ኮርፖሬሽን፣ በዚህ ዓመት መጀመርያ የኢትዮጵያ የተገጣጣሚ ሕንፃ አካላት ማምረቻ ድርጅትንም መጠቅለሉ አይዘነጋም፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከ15 ሺሕ በላይ ሠራተኞችንና በተመሳሳይ ሥራ ዘርፍ ውስጥ የነበሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን አዋህዶ እንዲይዝ ከተደረ በኋላ የትራንስፖርት፣ የውኃ፣ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችና መሣሪያዎች አስተዳደርና አቅርቦት ሥራዎችን ማከናወን ጀምሯል፡፡ የሕንፃ ቴክኖሎጂና መሰል የሲቪል ግንባታዎችን እንዲያናውን ኃላፊነት የተሰጠው ይህ ተቋም፣ አሁን ደግሞ ግዙፍ የመስኖ ግድብ ሥራዎችን የመገንባትና የማስተዳደር ሥራም ተረክቧል፡፡

በተለይም የመስኖ ውኃ ሽያጭ ሥራ የሚሠራ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ሥር የነበሩ አሥር የመስኖ ግድቦችን ተረክቦ በማስተዳደር ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ ኮርፖሬሽን ከኢትዮጵያ ውጭም በግንባታና በመሳሰሉት መሠረተ ልማት ሥራዎች ላይ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚጠበቅበት ከተሰጠው ተልዕኮ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ባለፈው ቅዳሜ የተካሄደውን የግንባታ ስምምነት በኮርፖሬሽኑ በኩል ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ሙላቱ፣ ግንባታዎቹን ለማከናወን የትራንስፖርት መሠረተ ልማት ኮንስትራክሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዓለማየሁ አስፋው፣ የውኃ መስኖ ልማት ኮንስትራክሽን ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አታክልቲ ተካ፣ የጂያንግዚ ሃይድሮፓወር ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚ/ር ዋንግ ዩፒንግና የደቡብ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤልያስ ኪሮ ተፈራርመዋል፡፡

 

Standard (Image)

መፍትሔ ያጡ በካይ ወንዞችና አትክልቶች

$
0
0

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና መሠረት ትልቅ ሃይማኖታዊ መሠረት ካላቸው አንዱ የዓቢይ ፆም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ፆመ እኩሌታው ተጋምሶ ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ በሚገኘው በዚህ የፆም ወቅት፣ ምዕመናን ነፍሳቸውንና ሥጋቸውን በመጎሰም ለንስሐና ለመልካም ዋጋ የሚተጉበት ጊዜ ነው፡፡ ስለ ፆሙ መተንተን ሳይሆን በፆሙ ወቅት ስለሚበሉ ምግቦችና በምግቦቹ ምክንያት ስለተጋረጠው የጤና አደጋ መዘገብ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ነው፡፡

በሁዳዴ ፆም የጡልላት (እንደ ሥጋ፣ ወተት፣ እንቁላል ወዘተ. ያሉ) ምግቦች ከገበታ የሚርቁበት በአንፃሩ እንደ አትክልት፣ ፍራፍሬና ጥራጥሬ ያሉት ምግቦች የሚዘወተሩበት ጊዜ በዚሁ ለ55 ቀናት በሚፆመው ትልቁ ፆም ወቅት ነው፡፡

ከወዲህ ደግሞ ሌላም ክስተት እየተስፋፋ በመምጣት ላይ ይገኛል፡፡ የአትክልት ተመጋቢነት ልማድ ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ዕምነት ባሻገር ያሉትንም የሚያካትት የአመጋገብ ዘይቤ ሥርዓት እየሆነ መጥቷል፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከጊዜ በኋላ ለበሽታ ጠንቅ እየሆኑ የሚገኙ ምግቦችን ከምርጫ ዝርዝራቸው ገሸሽ ለማድረግ እየሞከሩ ነው፡፡ የኮሌስትሮል፣ የደም መርጋት፣ የደም ግፊትና ሌሎችም ከአመጋገብ ሥርዓት ጋር ግንኙነት ያላቸው የበሽታ ዓይነቶች መበራከት ወደ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲያዘነብሉ እያስገደዷቸው መጥተዋል፡፡ ከክብደት መጨመርና ከሌሎችም መሰል ሥጋቶች ለመራቅ ምርጫቸውን  ወደ አትክልት ተራ ያደረጉ በርካቶች ናቸው፡፡

አደገኞቹ ወንዞችና አደገኞቹ ምርቶች

ይህ እየሆነ ባለበት ወቅት በከተማው ስለ አትክልቶች የሚባለውና የሚታየው ለየቅል እየሆነ ከመጣ ሰነባብቷል፡፡ ቀበና፣ ባንተ ይቀጡ፣ ቁርጡሜ፣ መከተያ፣ ቀጨኔ፣ ግንፍሌ፣ ቡልቡላ፣ ጆሞ፣ አቃቂ ወዘተ. የተባሉ ወንዞችን ጨምሮ በአዲስ አበባ ከሚገኙ አምስት ዋና ዋና ወንዞችና እስከ 76 ከሚገመቱ ገባሮቻቸው እንዲሁም አቃቂ ትንሹና ትልቁ እየተባሉ ከሚታወቁ የመዳረሻ ወይም የመካተቻ ወንዞች ዳርቻ የተመተሙ የአትክትል ማሳያዎች ጉዳይ አሳሳቢ ከሆነ ሰነባቷል፡፡ የአዲስ አበባ ወንዞች ለምንም ዓይነት አገልግሎት እንዳይወሉ የሚከለክል ማሳሰቢያ ከወጣ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ይሁን እንጂ የወንዞቹን ዳርቻዎች ተከትለው አትክትልክት፣ የግቢ ማስዋቢያ ዓጸዶችንና ልዩ ልዩ ችግኞችን በማምረት የሚተዳደሩ ከአሥር ሺሕ በላይ አባወራዎች እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአንድ አባወራ ቤት በአማካይ ከአምስት እስከ ስድስት የቤተሰብ አባላት ይኖራሉ በሚል ስሌት ይህንን አኃዝ ብናበዛው፣ ከ50 እስከ 60 ሺሕ የሚገመቱ ሰዎች ኑሯቸው የተመሠረተው በዚሁ የጓሮ አትክልት በማልማትና በመሸጥ ሥራ ላይ ሆኖ እንናገኘዋለን ማለት ነው፡፡  

ይሁንና የወንዞቹ የብክለት ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት በመምጣቱ በወንዞቹ ውኃ አማካነት የሚመረተው አትክልትም፣ ለልዩ ልዩ ብክለት መጋለጡ እየጨመረ መምጣቱ የማይታበል ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በአዲስ አበበ ከተማ አስተዳደር በመተባበር ባካሄዱት ጥናት መሠረት የአዲስ አበባ ወንዞች ከቤት ውስጥ በሚወጣ በካይ ፍሳሽ ብቻም ሳይሆን በኢንዱስትሪ ዝቃጭ መበከላቸው ታይቷል፡፡ ከኢንዱስትሪ የሚለቀቁት ዝቃጮችም ለጤና ጠንቅ የሆኑ እንደ አርሴኒክ፣ ኮባላልት፣ ካድሚየም፣ክሮሚየም፣ ኮፐር ወይም መዳብ፣ ሜርኩሪ፣ ኒኬል፣ ዚንክና የመሳሳሉት የብረት ይዘት ያላቸው ሲውል ሲያድር በጤና ላይ ከባድ ችግር የሚያስከትሉ ኬሚካሎች ወደ ወንዞች ይለቀቃሉ፡፡

እንደውም በአንድ ወቅት ፍስሐ ኢታና የተባሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባዮሎጂ ትምህርት ክፍል ባልደረባ ‹‹ሜታልስ ኢን ሊፊ ቬጂቴብልስ ግሮውን ኢን አዲስ አበባ ኤንድ ቶኢኮሎጂካል ኢምፕሊኬሽስን፤›› በሚል ርዕስ ባካሔዱት ጥናት መሠረት እነዚህ ከባድ የብረት ይዘት ያላቸው ኬሚካሎች ወደ ወንዝ እየተለቀቁ ልዩ ልዩ አትክልቶች በመመረታቸውና ለተመጋቢም በመቅረባቸው ካንሰር፣ የተዛባ አፈጣጠር እንዲከሰትና ፅንስ እስከማጨናገፍ ወይም ማስወረድ ያሉ በሽታዎች እንዲከሰቱ እንደሚያደርጉ አሳይተዋል፡፡ በተለይ በቄራና በአቃቂ ወንዞች ላይ በተደረገ ጥናት አርሴኒክ፣ ክሮሚየም፣ አይረን የተባሉ ብረት ያለባቸው ኬሚካሎች እንደሚገኙባቸው፣ በእነዚህ ወንዞች የተመረቱ አትክለቶችም አስከፊ የጤና ጉዳት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ በጥናታቸው አስጠንቅቀው ነበር፡፡

የአዲስ አበባ ወንዞች የሚደፋባቸው የፋብሪካ ዝቃጭ ቆሻሻ መጠን ከ4.8 ሚሊዮን ሜትር ኩብ በላይ ብዛት ያለው መሆኑን የሚያመላክቱ ጥናታዊ መረጃዎች አሉ፡፡ በተለይ ፋብሪካዎች ለልዩ ልዩ የምርት አገልግሎት የተጠቀሙበት ውኃ ሲወጣ ከ80 በመቶ በላይ ተበክሎ እንደሚወጣ የሚገልጹት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወንዞች፣ የወንዝ ዳርቻዎች ልማት የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣም ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋለልኝ ደሳለኝ ናቸው፡፡ እንደ አቶ ደሳለኝ ማብራሪያ፣ ይህን ያህል ድርሻ ያለው የፋብሪካ ቆሻሻ ወደ ወንዞች ቢለቀቅም ከሚለቀቀው በካይ ቆሻሻ ውስጥ ከየመኖሪያ ቤቱ የሚወጣው፣ ከወንዞች ጋር በቱቦና በሌሎች መስመሮች አማካይነት የሚደፋው ቆሻሻ ግን አሁንም ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ይህም ቢባል ግን በአዲስ አበባ ወንዞች ውስጥ የፋብሪካ ዝቃጭ በመልቀቅ ትልቅ ድርሻ ካላቸው ውስጥ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች፣ የምግብና የመጠጥ ኢንዱስትሪዎች፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች አምራቾች በተለይ ጫማ ፋብሪካዎች፣ ቆማ ፋብሪካዎች፣ ብረታ ብረት አምራቾች በአበይትነት ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይም ጨርቃ ጨርቅ፣ ምግብና መጠጥ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ከ4.8 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ዝቃጭ ቆሻሻ ውስጥ 96 በመቶውን ያመነጫሉ፡፡ ከፋብሪካዎቹ በተጨማሪ የሆቴሎች፣ የሆስታሎች፣ የማተሚያ ቤቶችና የመሳሰሉት ሲታከልበት የበካይ ንጥረ ነገሮች ልቀት መጠን ከፍተኛ እየሆነ እንዲሄድ፣ በአደገኛነቱም ይበልጡን እየጎላ እንዲመጣ አድርጎታል፡፡

ይህ በመሆኑም ሳቢያ በከተማው ተፈጥሯዊ ይዞታዎች ላይ በሰዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ አማካይነት እየደረሰ ያለው የብክለት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ተመራማሪዎች በየጊዜው የሚያስተጋቡት እውነታ ቢሆንም፣ የሚታየው ለውጥና የሚወሰደው ዕርምጃ ግን አዝጋሚ ይመስላል፡፡ በከተማው የውኃ አካላት ላይ የተደረጉት ጥናቶች የባዮሎጂካል፣ የኬሚካል እንዲሁም የአካላዊ ለውጦችን መለኪያ ዘዴዎች በመጠቀም ምርምር አድርገው ያገኟቸው ውጤቶች የሚያመላክቱት፣ በወንዝ ውኃ የሚመረቱ ልዩ ልዩ የምግብ ምንጮች ለረጅም ጊዜ በምግብነት በሚወስዱ ሰዎች ጤና ላይ የሚደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ስለመሆኑም በጥናት ሲያመላክቱ ቆይተዋል፡፡

በአንፃሩ የከተማይቱን የአካባቢ ብክለት በመከታተል በሰው ጤናና ሕይወት ላይ ጠንቅነት ያላቸውን ዝቃጮች ወደ ከባቢ አየር እንዳይለቀቁ እንዲቆጣጠር ሥልጣን የተሰጠው የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ለዓመታት ያልሠመረለትን ሙከራ ሲያከወናውን ቆይቷል፡፡ በጥቂቱ ለስምንት ዓመታት ያህል በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ እሮሮ ሲቀርብባቸው የኖሩትን በካይ ፋብሪካዎች በተለይም የቆዳ ፋብሪካዎች አደብ ለማስገዛት ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ፣ የፍሳሽ ማጣሪያ ሥርዓት እንዲዘረጉ ቀነ ገደብ ሲያስቀምጥ ሰንብቷል፡፡ ከ33 ያላነሱ የቆዳ ፋብሪካዎች ይገኛሉ፡፡

አብዛኞቹም በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የሚገኙ ናቸው፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች በጋራ የሚጠቀሙበትን የፍሳሽ ማጣሪያ እንደሚገነቡ ሲያስተጋቡ ዓመታት አልፈዋቸዋል፡፡ አንዳቸውም ተግባራዊ አላደረጉም፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ከፍተኛ ኢንቨስትመንትን የሚጠይቅ ሆኖ በመገኘቱ ነው የሚል ነው፡፡ ይህ እውን እስኪሆን ግን የየራሳቸውን የመጀመሪያ ደረጃ የፍሳሽ ማጣሪያ ገንብተው፣ ከተጠቀሙበት በኋላ በልዩ ልዩ በካይ ዝቃጮች የተሞላውን ፍሳሻቸውን አጣርተው እንዲለቁ የሚያስገድድ መመርያ ከወጣ ሰነባብቷል፡፡ በጥቂቱ ሁሉም ፋብሪካዎች የመጀመሪያ ደረጃ ማጣሪያ በግዳጅ እንዲገነቡ፣ ይህን በማደርጉት ላይ የመዝጋት ዕርምጃ ይወሰዳል የሚለው ማስጠንቀቂያና ቀነ ገደብ ካለፈ እንኳ ሦስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ይሁን እንጂ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን ድጋፍ ከጀርባቸው ያደረጉት እነዚህ ፋብሪካዎች አብዛኞቹ ይህንን ማስጠንቀቂያ ችላ ብለውታል፡፡ በህዳር ወር ገደማ አዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ይፋ ባደረገው መሠረት ደጋግሞ ማስጠንቀቂያ የሰጣቸው ፋብሪካዎች ማስጠንቀቂያውን ወደጎን ብለውት ነበር፡፡ የባለሥልጣኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፀጋዬ ገብረማርያም ይፋ እንዳደረጉት፣ ከ20 ጊዜ በላይ የጻፏቸው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤዎች ምንም ሊፈይዱ አልቻሉም፡፡ ይህንን ዝቅተኛውን የማጣሪያ ደረጃ እንዲገነቡ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ካለፈም ወደ አራተኛ ዓመቱ እየተጠጋ ይገኛል፡፡

በአንፃሩ ከ10 ሺሕ በላይ የሚገመቱት አባወራዎች በፋብሪካዎቹም ሆኑ ከየቤቱ በሚለቀቀው በካይ ፍሳሽ በተጋለጡት ወንዞች አማካይነት የዕለት ኑሯቸውን ያሸንፋሉ፡፡ እንደ አቶ ዋለልኝ ማብራሪያ ከሆነ፣ እነዚህ አባወራዎች ከ4000 ሔክታር በላይ በወንዞች ዳርቻ የሚገኝ መሬት በአትክልት በማልማት ይተዳደራሉ፡፡ አዲስ አበባ የከተማ ግብርና የሥራ ሒደት የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ከ3,000 በላይ አልሚዎች በ340 ሔክታር መሬት ላይ ከ2,400 ቶን በላይ ልዩ ልዩ የጓሮ ለምግብነት የሚውሉ አትክልቶችን አልምተዋል፡፡

‹‹ብክለቱ መጣብን እንጂ አልመጣንበትም››

አቶ ዋለልኝም ሆኑ አምራቾቹ እንደሚገልጹት፣ በአዲስ አበባ ወንዞች ዳርቻዎች አትክልትና ሌሎች ችግኞችን ማልማት የተጀመረው በጣልያን የአምስቱ ዓመት ቆይታ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ በዚህ ወቅት የአዲስ አበባ ወንዞች ለብክለት ብዙም ያልተጋለጡ ከመሆናቸው ባሻገር፣ አብዛኞቹም ለመጠጥነት ይውሉ እንደነበር  ይታመናል፡፡ የጣልያኖችን መውጣት ተከትሎ አብረዋቸው ይሠሩ የነበሩ የአገር ሰዎች በእግራቸው ተተክተው በወንዝ ዳርቻ የተጀመሩትን የአትክልት ልማት ሥራዎች አስፋፍተው ቀጥለዋል፡፡ በአዲስ አበባ የወንዞች ዳርቻዎችን በመንተራስ ከሚያለሙ ማኅበራት መካከል ቀደምት እንደሆነ የሚነገርለት የመካኒሳ፣ የጎፋና የሳሪስ አካባቢ የአትክልት አምራቾች የገበያ አገልግሎት ኅብረት ሥራ ማኅበር ነው፡፡ የማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ ኃይሉ ወልደ ኢየሱስ እንደሚገልጹት፣ የማኅበሩ ይዞታ በሆኑ አካባቢዎች የአትክልት ልማት ሥራ የተጀመረው ከ90 ዓመታት ቀድሞ ነው፡፡ ከግሪኮችና ከጣልያኖች በውርስ ቅድመ አያቶቻቸው የአትክልት እርሻዎችን በማልማት ለገበያ ሲያቀርቡ ኖረዋል፡፡ ዋናው መተዳደሪያቸው በመሆን ወንዞቹ ዛሬም ድረስ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

ይሁንና ሕጋዊ ዕውቅና ያለው ማኅበር በመሆን በኢትዮጵያ መንቀሳቀስ የጀመረው ከ41 ዓመታት በፊት እንደሆነ፣ ይህም መሬት በማኅበር እንጂ በግል መያዝ አይቻልም የሚል አዋጅ በመውጣቱ ማኅበራት ማደራጀት ሲጀመር በዚሁ አግባብ ተደራጅተው በአትክልት አልሚነት እንደቀጠሉ አቶ ኃይሉ ይገልጻሉ፡፡ ከዚህም በሻገር በአዲስ አበባ ከተማ፣ በቀድሞው ክልል 14 ግብርና ቢሮ በኩል በማኅበር በመደራጀት ሕጋዊ ሠርቲፊኬት የተሰጠው ቀደምት ማኅበር፣ ይኸው አቶ ኃይሉ የሚመሩት የመካኒሳ፣ ጎፋና ሳሪት አካባቢ ማኅበር እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም ማኅበሩ ሲመሠረት በ210 ወንዶችና፣ በ34 ሴቶች በጠቅላላው በ244 አባላት ተመሥርቶ በአሁኑ ወቅት የመሥራቾቹ ተተኪዎች እያስተዳደሩት የሚገኘው ይህ ማኅበር፣ በነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ ሦስት፣ አራት፣ አምስት፣ ስድስት፣ 11 እና 12 ውስጥ በ54.3 ሔክታር መሬት ላይ አትክልቶችን በማልማት የአዲስ አበባን 75 በመቶ የአትክልት ፍላጎት በማሟላት እንደሚገኝ አቶ ኃይሉ ይናገራሉ፡፡ ይሁንና የመሬት ይዞታቸው በግል ኩባንያዎች እየተቀነሰባቸው፣ በርካታ በካይ ሥራዎችን የሚሠሩና ብክለትን ወደ ወንዞች የሚለቁ ድርጅቶች እያስፋፉ መምጣታቸው ለህልውና ሥጋት እንዳስከተለባቸው አቶ ኃይሉና የማኅበሩ አመራሮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ለአትክልት ልማት የሚጠቀሙባቸው ወንዞች ንፁህ እንደነበሩ፣ አልፎ ተርፎም የአካባቢው ነዋሪዎች ለልብሳቸውና ለገላቸው መታጠቢያነት የሚገለገሉባቸው እንደነበሩ የሚናገሩት አቶ ኃይሉ፣ ብክለቱ የመጣው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደሆነ ይልቁንም በአካባቢው የሚገኘው ቆዳ ፋብሪካ ትልቁን ድርሻ በመያዝ ወንዞችን እየበከለ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡ ሌሎችም እንደ አረቄ ፋብሪካ፣ ጥጥ ፋብሪካ፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ተደራጁ ሳሙና አምራቾች፣ ጋራዦች፣ መኪና የሚጥቡ ሰዎች፣ እንጨት መሰንጠቂያ ድርጅት ወደ ወንዝ በሚለቁት ባካይ ቆሻሻ ምክንያት ለዘመናት የሚተዳደሩት የአትክልት ምርት እየተመናመነ መምጣቱን አቶ ኃይሉ በቁጭት ይገልጹታል፡፡

‹‹የአትክልቱ ምርት በከፍተኛ መጠን ቀንሶ የህልውና ችግር ፈጥሯል፡፡ አካባቢ ጥበቃ ብዙ ጊዜ ጥያቄ ቀርቦለት አንድም መፍትሔ አላመጣም፤›› ያሉት አቶ ኃይሉ፣ የማኅበሩ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ትዕግሥቱ ገብረ እግዚአብሔር በበኩላቸው ‹‹በልማት ሰበብ መሬት እየተወሰደብን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በከተማው ግብርና ቢሮ የተመዘገበ 54.3 ሔክታር ነበረን፡፡ አሁን ግን በተለያየ ምክንያት ገበሬዎች ምትክ ቦታ እንኳ ሳይሰጣቸው እየተወሰደባቸው ነው፡፡ ይህ ትልቅ ችግር ነው፡፡ ለከተማ ግብርና ሥራ ምንም ዓይነት ትኩረት አይሰጡም፤›› በማለት ማኅበራቸው የሚደርሱበትን ጫናዎች አብራርተዋል፡፡

የማኅበሩ አመራሮች በአትክልት አምራችነት ወደፊት መዝለቅ ፈታኝ እየሆነ መምጣቱን አጽንዖት ሰጥተው ይገልጹታል፡፡ ‹‹ለውጥ እንፈልጋለን፡፡ በዶሮና በከብት ርቢ እንዲሁም የገበያ ማዕከል በመገንባትና ሌሎች ምርቶችን ለማምረት የሚረዱ ሼዶችን በመሥራት የገበሬውን ሕይወት መለወጥ እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን ለመሥራት ስንነሳ ፈቃድ የማግኘት ችግር አጋጥሞናል፤›› በማለት ሌሎች ያገኙትን ዕድል ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡

ይልቁንም በማኅበሩ አባላት ይዞታ ሥር የሚገኝ መሬት ላይ አንድ አረቄ ፋብሪካ የገበሬውን ማሳ በመግፋት የማስፋፈፊያ ግንባታ በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ ሲገልጹ፣ ዋቢ ያደረጉት ‹‹እኛን ለአረንጓዴ ቦታ ማስፋፊያነት እያሉ ይዞታችንን ሲቀንሱ በጎን በኩል ግን ፋብሪካዎች ወንዝ ላይ እንዲገነቡ ይፈቅዱላቸዋል፡፡ ጥቃቅንና አነስተኛዎችን እያደራጁና ቦታ እየሰጡ ሲያሠሩ እኛ ግን ባለን ይዞታ ላይ እንኳ መሥራት እንዳንችል ያደርጉናል፤›› በማለት የፍትሕና የርትዓዊነት ጥያቄ በመንግሥት ላይ አቅርበዋል፡፡

ይህን ቢሉም ግን በወንዞች ላይ የሚካሔደው ብክለትና አትክልቶችም መመረታቸውን ሳያቋርጡ እንደቀጠሉ ይገኛሉ፡፡ ይብሱንም ይኸው ማኅበር የሚከተለው የአመራረት ዘዴ በራሱ ለወንዞች ብክለት አስተዋጽኦ እንዳለው ለመመልከት ተችሏል፡፡ አብዛኞቹ አትክልት አምራቾች ከማኅበሩ የኬሚካል ማዳበሪያ በመውሰድ ችግኞች አፍልተው የሚያለሙ መሆናቸውን ለመታዘብ ተችሏል፡፡ ማዳበሪያው ወደ ወንዙ በቀላሉ እንደሚቀላል ለማረጋገጥም ሳይሳዊ አመክንዎ ሳይጠይቅ በጉልህ የሚታይ  ነው፡፡

የአዲስ አበባ አስተዳደርም ሆነ የፌደራል መንግሥት ስለ አካባቢ ክብካቤና ስለ ብክለት መጠን በሚገልጹት ልክ እንደማይሠሩ የሚያሳብቁት የአዲስ አበባ ወንዞች ናቸው፡፡ ይሁንና ባለፈው ዓመት ተቋቁሞ ወደ ሥራ የገባው የወንዞች፣ የወንዝ ዳርቻዎች ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣም ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት፣ የተበከሉ ወንዞች እንዲያገግሙ፣ እንዲፀዱ፣ አዳዲስ ፓርኮች ተገንብተው አረንጓዴነት እንዲስፋፋ የማድረግ ሥራዎችን ማካሄድ ጀምሬያለሁ ብሏል፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ዋለልኝ እንደገለጹትም በአሁኑ ወቅት 65 ሚሊዮን ብር ወጭ ተደርጎባቸው ግንባታቸው እየተጠናቀቀ የሚገኙ ሰባት ፓርኮችን በቀበና ወንዝ፣ በጀሞ፣ በጉለሌ ሸክላ አፈር ማውጫ አካባቢ፣ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን አካባቢ፣ እንጦጦ አካባቢ እንዲሁም ሻንቅላ ወንዝ ተብለው የሚጠሩ የውኃ አካላትን መሠረት ያደረጉት ፓርኮች ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ግንባታቸው እንደሚጠናቀቅ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ወንዞችና ዳርቻዎችን የማፅዳት ዘመቻ በወጣቶች አማካይነት እየተካሄደ እንደሚገኝ፣ ይህም 5000 ኪሎ ሜትር ርቀትን የሚያዳርስ ሥራ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ በዚህ አኳኋን የከተማውን ብክለት ለመቀነስ የሚረዱ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ፣ 54 ሔክታር መሬት በማስመለስ ከብክለት ነፃ ለማድረግ ከመንቀሳቀስ ባሻገር፣ ለጎርፍና ለናዳ የተጋለጡ፣ ለሕዝቡም ለመሠረተ ልማቶችም ሥጋት የሆኑ የወንዝ ዳርቻዎችን በመለየት የመጠበቅ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

ይህ ሥራ ግን አምራቾቹ እንደሚገልጹት፣ አቶ ዋለልኝም እንደሚናገሩት ቀላል እንደማይሆን እየታየ ነው፡፡ በተለይ ሰዎችን ከወንዞች ዳርቻዎች የማንሳት፣ የእርሻ ቦታዎችን የመለወጥ እንዲሁም ለልዩ ልዩ ምርት ሥራ የሚውሉ እንደ ሸክላ አፈር ማውጫ ያሉ አካባቢዎችን ወደ ጥብቅ ቦታነት የመቀየር ዕርምጃ ቅሬታና ተቃውሞ እያስከተለ የሚገኝ መሆኑ ከዚህ ቀደም እንደታየ አቶ ዋለልኝ ይጠቅሳሉ፡፡ በዚህም ተባለ በዚያ የአዲስ አበባ ወንዞች ብክለትን የሚገታ ነገር ሊመጣ አልቻለም፡፡ አትክልቶችም መመረታቸው አልቀረም፡፡ ሕዝቡም መመገቡን አልተወም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ለዚህ ዘገባ ሶፎኒያስ ታደሰ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

 

 

 

 

 

Standard (Image)

በኢትዮጵያ የግብርና ኤክስቴንሽን መስክ ፈር ቀዳጁ ሳሳካዋ ግሎባል

$
0
0

በጃፓናዊው ምግባረ ሰናይ ዮኢሺ ሳሳካዋ አማካይነት የተመሠረተው ሳሳካዋ አፍሪካ አሶሲዬሽን እንዲሁም በሥሩ የሚተዳደሩ ሳሳካዋ ግሎባል 2000 እየተባሉ በየአገሮቹ የሚንቀሳቀሱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን በመመሥረት በአፍሪካ መንቀሳቀስ ከጀመረ 30 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ተቋሙ ወደ አፍሪካ እንዲመጣ ምክንያት የሆነው በምሥራቅ አፍሪካ በተለይ በኢትዮጵያና በሱዳን የተከሰተው ድርቅና ያስከተለው የረሀብ ቸነፈር እንደነበር ይጠቀሳል፡፡

ለአፍሪካ የረሀብ ተጎጂዎች ለዕለት ደራሽ የሚውል ዕርዳታ ለመስጠት በመጡበት ወቅት አንደኛቸውን ዘላቂ ዕገዛ መስጠጥ የሚችሉበትን ሐሳብ እንደጠነሰሱ የሚነገርላቸው ሚ/ር ሳሳካዋ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ15 አገሮች ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ድጋፍ የሚሰጥ የበጎ አድራጎት ድርጅት አስፋፍተው መሥራት እንደጀመሩ ከታሪካቸው ይጠቀስላቸዋል፡፡

በዚህ ወቅት ከታዋቂው የአረንጓዴ አብዮት ጠንሳሽ ኖርማን ቦርሎግ ጋር ሊገናኙ እንደቻሉና ከእኚሁ ምሁር ጋር ጥምረት በመፍጠር፣ በላቲን አሜሪካና በእስያ የተገኘውን የአረጓዴ አብዮት ውጤት በአፍሪካም ዕውን ለማድረግ መሥራት ጀምረው እንደነበርም በታሪካቸው ተመዝግቧል፡፡ ይሁንና በግብርናው መስክ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በመጠቀም፣ የተለያዩ ግብዓቶችን በማካተት ብዙ ምርት ማፍራትና ውጤታማ መሆን የሚለው የአብዮቱ መርኅ ግን ሊሰምር አልቻለም፡፡ በርካታ ምክንያቶች ለዚህ ቢቀርቡም፣ ሳሳካዋ ግሎባል 2000 በተለይ በኢትዮጵያ ስኬታማ ከሆነባቸው መስኮች መካከል የኤክስቴንሽን አገልግሎት ተጠቃሽ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ በኡጋንዳ፣ በማሊ እንዲሁም በናይጄሪያ ውስጥ ብቻ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው ሳሳካዋ ግሎባል፣ ለመጪዎቹ አምስት ዓመታት የሚመራበትን ስትራቴጂክ ዕቅድ ነድፏል፡፡ በአፍሪካ 30ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን አካቶ፣ በኢትዮጵያ ቆይታውም 24ኛ ዓመቱን አስታኮ በአዳማ ከተማ መጋቢት 21 እና 22 ቀን 2009 ዓ.ም. የሁለት ቀናት ዓውደ ጥናት አካሂዷል፡፡

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ ኢያሱ አብርሃ (ዶ/ር)፣ በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊው አቶ ስለሺ ጌታሁን የታደሙበት ዓውደ ጥናት ላይ የሳሳካዋ በኢትዮጵያ አጀማመርና አሁን የሚገኝበት ደረጃ ተወስቷል፡፡ ሁለቱ ኃላፊዎች እንደገለጹት ሳሳካዋ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በአገሪቱ ተከስቶ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ያለቀበት ድርቅ መገባደጃው ሰሞን ነበር፡፡ ይህ ወቅት አገሪቱ የግብርና ዘርፍ ዝቅተኛውን የምርት ውጤት እያስመዘገበ የነበረበት እንደነበር አውስተዋል፡፡

የሳሳካዋ ግሎባል 2000 ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አበራ ደበሎ (ዶ/ር) እንዳስታወሱት፣ በወቅቱ በሄክታር አንድ ቶን ያህል ምርት የሚገኝበት ወቅት አሁን ላይ በአምስት እጥፍ ሊጨምር ችሏል፡፡ የሳሳካዋ ግሎባል ትልቅ አስተዋጽኦ ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል በተለይ በአገሪቱ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትን ማስፋፋት ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ የሠርቶ ማሳያ ጣቢያዎችን በማስፋፋት፣ የግብርና ባለሙያዎችንና አምራች ገበሬዎችን በማሰልጠን ውጤታማ ሥራዎች እንዲስፋፉ ዕገዛ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡

የመጀመሪያው ምዕራፍ በጀመረ በሁለት ዓመት ውስጥ ለውጦችን ማስመዝገብ የቻለው ሳሳካዋ፣ በተለይ በሁለተኛው ምዕራፍ እንቅስቃሴው ማለትም እ.ኤ.አ. ከ1995 እስከ 2003 ባለው ጊዜ ውስጥ በተመዘገበው ለውጥ አማካይነት ባሳየው ለውጥ ምክንያት ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ የተዘዋዋሪ ፈንድ መንግሥት በመመደብ ለገበሬዎች ምርጥ ዘር ተገዝቶ እንዲያሰራጭ ያነሳሳ አካሄድ ተፈጥሯል፡፡ ይህ ከመሆኑ ቀድሞ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋባዥነት በኢትዮጵያ የኤክስቴንሽን አገልግሎትን እንዲያስተዋውቁ የተጋበዙት ሚ/ር ሳሳከዋ፣ በኢትዮጵያ መሠረቱን የዘረጋ ተቋም እንዲመሠረት አድርገዋል፡፡

በሁለተኛው ምዕራፍ የሳሳካዋ ግሎባል እንቅስቃሴ ከዝቅተኛ የምርት መጠን ወደ ከፍተኛ የምርት ዕድገት አገሪቱ መሸጋገር በመጀመሯ፣ ሌሎች ስጋቶች እየተፈጠሩ መምጣታቸውን አቶ አበራ አስታውሰዋል፡፡ ይህም ድኅረ ምርት አሰባሰብ ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮች ስጋት መፍጠራቸው ነው፡፡ የምርት ማካማቻዎች እንደልብ አለመኖራቸው ምርት እንዲባክን ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ ይሁንና በወቅቱ የነበሩ የተቋሙ ኃላፊዎችና የመንግሥት ባለሥልጣናት የምርት ማከማቻዎችና ሌሎችም ምርት ሳይበላሽ እንዲቆይ የሚያስችሉ አሠራሮችን ማስተዋወቅና ማስፋፋት ጀምረው ነበር፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት የሚታየው የድኅረ ምርት አሰባሰብ ብክነት በአማካይ እስከ 30 በመቶ ይገመታል፡፡

ከዚህ ባሻገር የአገሪቱ አነስተኛ ገበሬዎች በአማካይ የሚያርሱት መሬት አንድ ሔክታርና ከዚያ በታች በመሆኑ እንደ ሜካናይዜሽን፣ እንደ የተሻሻሉ ግብዓቶችን የመጠቀም፣ ዘመናዊ ማረሻዎች፣ የምርት መሰብሰቢያዎች፣ መውቂያና ማበጠሪያዎች የመሳሰሉትን በማስተዋወቅ እንዲተገበሩ ማድረጉ ለአነስተኛው ገበሬ ካለው የመሬት ይዞታ አኳያ አዋጭነቱ እንዴት ይታያል ለሚለው ምላሽ የሰጡት አቶ አበራ፣ እንዲህ ያሉት ግብዓቶች በገበሬው አቅምና ችሎታ ጋር ተመጣጥነው በፍላጎቱ ላይ ተመሥርተው ይቀርባሉ የሚል ነው፡፡

ከዚህም ባሻገር ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲተገበር የቆየና በአነስተኛ የገንዘብ አቅራቢ ድርጅቶች አማካይነት ለገበሬ ማኅበራት ኅብረት ሥራ የኒየን አባላት በብድር መልክ የሚሰጥ የተዘዋዋሪ ፈንድ መድቦ እያንቀሳቀሰ የሚገኝበት ሥራ ለሳሳካዋ ግሎባል 2000 ተጠቃሽ ከሆኑት መካከል የሚመደብ ነው፡፡ የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ በሬቻ ቱሪ ለሪፖርተር እንዳብራሩት በነፍስ ወከፍ እስከ 70 ሺሕ ብር ለአንድ ዩኒየን የሚዳረስበትን የአሥር ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ በመመደብ እያገዘ ይገኛል፡፡ ይህ በመሆኑም በስምንት ክልሎች ውስጥ በ149 ወረዳዎች በኩል ገንዘቡ እንዲዳረስ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ አብዛኞቹ ገበሬ ማኅበሮች በሁለት ዓመት ውስጥ የወሰዱትን ብድር መመለስ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ እንደ ሥራቸው ውጤትና ክብደት እየታዩም ወደ ሦስት ዓመት የተራዘመላቸው እንደሚገኙም ጠቅሰዋል፡፡ በተለይ በጉራጌ ዞን የወሰዱትን ብድር ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ከመለለስ አልፈው የምርት ማከማቻ መጋዘን በመገንባት ለውጥ ያሳዩ ገበሬዎችን ዋቢ ያደረጉት አቶ በሬቻ ፈንዱ በዚህ መልኩ እየተዘዋወረ፣ በዚያው አነስተኛ ገበሬዎች እየተጠቀሙበት የሚቀር እንደሚሆን እንጂ ሳሳካዋ መልሶ የማይወስደው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በተለይ የግብርና ባለሙያዎችን በማሰልጠን ረገድ ትልቅ ድርሻ የሚወጣው ሳሳካዋ የኤክስቴንሽን አገልግሎት ፈንድ (ሴፍ) የሚባለው ተቋም በአሁኑ ወቅት ከዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ማለትም ከሀሮማያ፣ ከጅማ፣ ከአዳማ፣ ከሰመራ፣ ከጂግጂጋ፣ ከባህር ዳር፣ ከሐዋሳ፣ ከመቐለ እንዲሁም ከወሎ ዩኒቨርሲተዎች ጋር በመስማማት የሁለት ዓመት ተኩል ሥልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ ከዚህም በተጓዳኝ በተለይ ለአርብቶ አደር አከባቢዎች የሚስማሙ ሥልጠናዎችን ለመስጠት በማሰብ ከጂግጂጋና ከሠመራ ዩኒቨርሲዎች ጋር በመተባበር አርብቶ አደር ተኮር ሥርዓተ ትምህርት መዘርጋቱን አስታውቋል፡፡

ይህ ሁሉ ቢጠቀስም የአገሪቱ የግብርና ዘርፍ ግን ሕዝቡን በበቂ መመገብ አላስቻለም፡፡ ይልቁንም ባለፈው ዓመት በተከሰተው ድርቅ 10.2 ሚሊዮን ሕዝብ ለዕለት ደራሽ ምግብ ዕርዳታ ተዳርጎ ነበር፡፡ በዚህም ዓመት በቆላማ አገሪቱ ክፍሎች በተከሰተው ድርቅ 5.6 ሚሊዮን በምግብ ዕርዳታ ተዳርጓል፡፡ ይህም ቢባል ግን አገሪቱ ሌላው ቢቀር ከውጭ ዕርዳታ ይልቅ የራሷን ችግር በራሷ አቅም ለመመከት የምትችልበት ደረጃ ላይ መድረሷም ቸል የማይባል ለውጥ እንደሆ አቶ አበራ ያሳስባሉ፡፡

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒኒስትሩ በበኩላቸው ግብርናው በብዙ ችግሮች የተውተበተበ በመሆኑ እግሩ ጸንቶ በሚገባ ለመቆም እንደ ሳሳካዋ ግሎባል ያሉ አጋሮቹ ሊያግዙት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ገበሬዎች ግብዓት ለማግኘት የሚያዩት ውጣ ውረድ፣ ደካማ የገበያ ትስስር፣ የክህሎት ማነስ፣ ተደጋጋሚና አሳሳቢ የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት እጥረት እና ሌሎችም አገሪቱን የሚፈታተኑ ችግሮች እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

ይህ ሁሉ ችግር ቢኖርም የአገሪቱ ምርት አሁን ካለበት ከ270 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 400 ሚሊዮን ኩንታል ማደግ እንደሚጠበቅበት፣ በተለይ የዋና ዋና ሰብሎች ምርት በ52 በመቶ ማደግ እንደሚያስፈልገው፣ የኤክስቴንሽን አገልግሎትም በያመቱ የስምንት በመቶ ዕድገት ማሳየት እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡ ይህንን ሁሉ ለማሟላት ደግሞ እንደ ሳሳካዋ ያሉ ድርጅቶች የሚደርጉት አስተዋጽኦ ይጠበቃል ብልዋል፡፡

መንግሥት የሚማራባቸውን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተንተርሶ የሚንቀሳቀሰው ሳሳካዋ ግሎባል ከመንግሥት ጋር አብሮ ለመሥራት መነሳቱንና እ.ኤ.ኤ 2017 ጀምሮ እስከ 2021 ድረስ የሚመራበትን አዲስ ስትራቴጂክ ዕቅድ ይፋ አድርጓል፡፡ በዕቅዱ መሠረትም ኢትዮጵያን ጨምሮ በሚንቀሳቀስባቸው አራት አገሮች ውስት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ሥራዎችም ለይቷል፡፡  

 

Standard (Image)
Viewing all 665 articles
Browse latest View live