Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all 665 articles
Browse latest View live

የኬሚካል ኢንዱስትሪዎች 12 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ ምርቶችን አገር ውስጥ በማምረት ከውጭ የሚገቡትን እየተኩ ነው ተባለ

$
0
0

 

  • ስድስት የፔትሮኬሚካል ማጣሪያዎች ይገነባሉ

በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ከ350 ያላነሱ የኬሚካልና የኬሚካል ውጤቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች በአሁኑ ወቅት ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸውን ምርቶች በማምረት ከውጭ የሚገቡትን እየተኩ እንደሚገኙ ተገለጸ፡፡

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሥር የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪዎች ልማት ኢንስቲትዩት ኃላፊዎች፣ ሐሙስ ሚያዝያ 12 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ይፋ እንዳደረጉት፣ በአገሪቱ በኬሚካልና ተዛማጅ ምርቶች ዘርፍ የሚንቀሳቀሱ ፋብሪካዎች 12 ዋና ዋና ምርቶችን በማምረት ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ደያሳ ለታ እንዳብራሩት ከሆነ፣ በአሁኑ ወቅት አገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ትልቅ ተቀባይነት እያገኙ ከመምጣታቸውም ባሻገር፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በመተካት በኩልም ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ነው፡፡

የፕላስቲክ፣ የጎማ፣ የፐልፕና ወረቀት፣ የህትመትና የማሸጊያ ምርቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እያሳዩ ከመምጣት አልፈው የአገሪቱ ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር እንደ ጎማ ያሉት ምርቶችም ወደ ጎረቤት አገሮች መላክ እንደተጀመሩ አቶ ደያሳ ጠቅሰዋል፡፡

በኢንስቲትዩቱ የፕላስቲክና ተዛማጅ ዘርፎች ዳሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ዮናስ አባተ እንደሚገልጹት፣ ከፕላስቲክና ከጎማ ምርቶች 12 ቢሊዮን ብር ያህል ወጪ ማዳን የተቻለው በአገር ውስጥ በብዛት መመረት በመጀመሩ ነው፡፡ እንደ አቶ ዮናስ ከሆነ፣ በአፍሪካ ጎማና የጎማ ውጤቶችን የሚያመርቱ አገሮች አራት ብቻ ናቸው፡፡ ቀደም ብሎ 12 ያህል ፋብሪካዎች በአፍሪካ በጎማ አምራችነት ቢመዘገቡም በተለያየ ምክንያት ዘርፉን እየለቀቁ በመውጣታቸው በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ አራት ብቻ አምራቾች ቀርተዋል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሆራይዘን አዲስ ጎማ ከ30 እስከ 35 በመቶውን የጎማ ምርት ድርሻ እንደያዘ የጠቀሱት አቶ ዮናስ፣ በመንግሥም ሰፋፊ የጎማ ዛፍ እርሻዎችን የማስፋፋት ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡ መንግሥት በሚዛን ተፈሪ አካባቢ ቀደም ሲል በ5,000 ሔክታር መሬት ላይ ሲያካሂደው የነበረውን የጎማ ዛፍ እርሻ ሥራ በማስፋፋት ተጨማሪ 5,000 ሔክታር መሬት በመረከብ እርሻ ለመጀመር መዘጋጀቱን አቶ ደያሳ አስታውቀዋል፡፡  

ከዚህም ባሻገር በአገሪቱ ወደፊት የሚተከሉ ስድስት የፔትሮኬሚካል ማጣሪያዎች የአገሪቱን የፕላስቲክ ጥሬ ዕቃ ፍላጎት በእጅጉ እንደሚቀርፉት ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡ አቶ ደያሳ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት የእንግሊዝ ኩባንያ ጥናቱን እያካሄደ እንደሚገኝና በቅርቡም አጠናቆ በሚያቀርብበት ወቅት ከተፈጥሮ ጋዝ የሚገኙ ዋና ዋና የፕላስቲክ ጥሬ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ በማምረት ለፋብሪካዎች ማቅረብ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ ሥራውን የሚከታተለው የኢትዮጵያ ኬሚካል ኮርፖሬሽን የተሰኘ መንግሥታዊ ግዙፍ ተቋም መቋቋሙ ሲገለጽ፣ ይህ ተቋም የያዩ ማዳሪያ ፋብሪካን፣ የሙገር ሲሚንቶንና የመሳሰሉትን ትልልቅ ፋብሪካዎች በሥሩ እንደሚመራም አቶ ደያሳ ጠቅሰዋል፡፡

በኦጋዴን የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት በማልማት በቱቦ አማካይነት ወደ ድሬዳዋ የመውሰድ ሥራዎችን ለማከናወን እንቅስቃሴዎች እንዳሉ፣ የተፈጥሮ ጋዙን በመጠቀም የኬሚካል ማዳበሪያ ለማምረት የሞሮኮ ግዙፍ ኩባንያ የሆነው ኦሲፒ አፍሪካ ከመንግሥት ጋር ስምምነት መፈራረሙን አቶ ደያሳ አስታውሰዋል፡፡ ከኬሚካል ማዳበሪያ በበለጠ ግን ፖሊኢትሊን እንዲሁም ፖሊፕሮሊን የተሰኙ ንጥረኬሚካሎችን ከተፈጥሮ ጋዝ በማጠንፈፍ ወይም ከጋዝ ወደ ፍሳሽነት በመቀየር የሚገኘውን ፈሳሽ ፔሮሊየም ጋዝ ለልዩ ልዩ ፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻነት ለማዋል እንደሚያስችል ኃላፊዎቹ አስገንዝበዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት 126 ሺሕ ቶን የፖሊፕሮፕሊን ጥሬ ዕቃ ወደ አገር ውስጥ መግባቱን የጠቀሱት አቶ ዮናስ፣ ይህ ጥሬ ዕቃ ከፍተኛ ወጪ ከሚጠይቁት ውስጥ እንደሚመደብ ገልጸዋል፡፡

ይሁንና በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚመሩ 12 ዋና ዋና የፕላስቲክ ውጤቶች ገበያው ላይ ትልቅ ድርሻ በመያዝ ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡ የበርና መስኮት ፕሮፋይሎች፣ የኮርኒስና የግድግዳ ማካፈያዎች፣ የአልሙኒየም ፍሬሞች፣ የለስላሳ መጠጦች፣ የመድኃኒትና የውኃ ማሸጊያዎች፣ የስፖንጅ ውጤቶች፣ ሲንቴቲክ የቆዳ ምርቶች፣ የፕላስቲክ ብሩሾችና የመሳሰሉት በርካታ ምርቶች አገር ውስጥ መመረታቸው ወደ አገር ውስጥ በገፍ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን ለመቀነስ እንዳስቻለ አቶ ዮናስ ይናገራሉ፡፡ ከአራት ዓመት በፊት በብዛት ከውጭ ይገቡ የነበሩ የውኃና የለስላሳ መጠጦች ማሸጊያዎች በአሁኑ ወቅት አገር ውስጥ እንደልብ እየተመረቱ ነው ብለዋል፡፡

በኢንስቲትዩቱ የወረቀት፣ ፐልፕ፣ የሕትመትና የምርት ማሸጊያ ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ረጋሳ በበኩላቸው፣ በአገሪቱ የቆየ ታሪክ ያለው የሕትመት ኢንዱስትሪ ምንም እንኳ ዕድገት እያሳየ ቢመጣም አሁንም በአገሪቱ ያለውን የጥራትና የአቅርቦት ፍላጎት ማሟላት አልቻለም፡፡ ከሕትመቱ ባሻገርም የማሸጊያ ምርቶች ፍላጎት ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ እንደሚገኝ ጠቅሰው ወደፊት የአገሪቱ ፈታኝ ችግር ሊሆን እንደሚችል ሥጋት መኖሩንም ገልጸዋል፡፡ በግብርና ዘርፍ የአግሮ ኢንዱስትሪዎች መምጣት የማሸጊያ ምርቶችን ፍላጎት በከፍተኛ መጠን ሊጨምሩ ከሚችሉት ውስጥ ዋነኛው ሆኖ ተገኝቷል፡፡

የወረቀት አንዲስትሪውም ቢሆን ገና በጅምር ላይ እንደሚገኝ አቶ ግርማ አስታውሰው፣ በጥራትና በብዛት ምርቱን የሚያቀርቡ ፋብሪካዎች እንደ አሳታሚዎች ፍላጎት ባለመኖራቸው መጻሕፍት ወደ ውጭ እየተላኩ እንደሚታተሙ አብራርተዋል፡፡ ይሁንና የወረቀትና ተዛማጅ ኢንዱስትሪው ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል የሚንቀሳቀስበት ዘርፍ እንደሆነም አስታውሰዋል፡፡

በዚህ መልኩ የተገለጹትን የኢንዱትሪው ንዑሳን ዘርፎችን እንደሚያስተዋውቅ የታመነበት፣ በወረቀት፣ በፐልፕ፣ በማሸጊያ፣ በሕትመት እንዲሁም በፔትሮኬሚካል ዘርፎች ላይ ያተኮረው የንግድና የኢንቨስትመንት ዓውደ ርዕይ ለስድስተኛ ጊዜ ሊካሄድ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል ተብሏል፡፡ ‹‹ኢትዮ5ፒ›› የተሰኘውን ዓለም አቀፍ ዓውደ ርዕይ ማዘጋጀቱን ያስታወቀው ሻክረክስ ንግድና ኤቨንት ማኔጅመንት የተባለው አገር በቀል ኩባንያ ነው፡፡

የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ አቶ አክሊለ በለጠ እንደገለጹት፣ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል፣ ከሚያዝያ 21 እስከ ሚያዝያ 24 ቀን 2009 ዓ.ም. በሚካሄደው ዓውደ ርዕይ ለመሳተፍ እስካሁን 67 ያህል የውጭ ኩባንያዎች ተመዝግበዋል፡፡ ከግብፅ የሚመጡትን 38 ኩባንያዎች ጨምሮ ከጀርመን፣ ከቻይና፣ ከጃፓን፣ ከካናዳ፣ ከፈረንሳይ፣ ከህንድ፣ ከቱርክ፣ ከኬንያና ከሌሎችም አገሮች ለመሳተፍ የተመዘገቡ ኩባንያዎች ሲኖሩ በአገር የሚታደሙትን ጨምሮ በጠቅላላው ከ100 በላይ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ዓውደ ርዕይ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡     

 

Standard (Image)

የአዲስ አበባ ሆቴሎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት የ380 ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንደደረሰባቸው ይፋ አደረጉ

$
0
0

 

- የዚህ ዓመት ትርፍ ግብር ይነሳልን አለያም የብድር መክፈያ ጊዜ ያራዝምልን ብለዋል

- ዓመታዊው የአዲስ አበባ ቱሪዝም መጽሔት ለሁለተኛ ጊዜ ታትሟል  

በአዲስ አበባ የሚንቀሳቀሱ ሆቴሎች በአገሪቱ በተከሰተው ሕዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይህንን ተከትሎ አገሮች ባወጡት የጉዞ ክልከላና ማስጠንቀቂያ ሳቢያ በዚህ በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ብቻ የ380 ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንዳጋጠማቸው አስታወቁ፡፡

በአዲስ አበባ ከሚገኙ 150 ሆቴሎች ውስጥ 105ቱ የሚወከሉበት የአዲስ አበባ ሆቴሎች ባለንብረቶች የዘርፍ ማኅበር ኃላፊዎች፣ ሚያዝያ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ይፋ እንዳደረጉት በአገሪቱ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅና አገሮች ያወጧቸው የጉዞ ክልከላዎች ባደረሱት ጫና ምክንያት ሆቴሎች ከዚህ ቀደም የነበራቸውን የ67 በመቶ የክፍል ተከራዮች ቁጥር በአማካይ በ20.5 በመቶ እንዲቀንስባቸው ምክንያት ሆነዋል፡፡

ይህንን በማስመልከት ሆቴሎቹ ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አጥንተው አቅርበው እንደነበር የገለጹት፣ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ቢኒያም ብሥራት ናቸው፡፡ የጁፒተር ኢንርናሽናል ሆቴል ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ቢኒያም እንዳብራሩት ከሆነ፣ በሆቴል ዘርፉ ብቻም ሳይሆን በኢኮኖሚው ውስጥ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ የደረሰውን ጉዳት ሁሉም እንደሚገነዘበው ጠቅሰው፣ በቱሪዝም መስክ የደረሰውን ጉዳት ያባባሰው ግን አገሮች ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ የሚከለክሉና የሚያስጠነቅቁ ማሳሰቢያዎችን ማውጣታቸው ነው፡፡

በዚህ ምክንያት ከመጀመሪያው ሩብ ዓመት ጀምሮ አሁንም ድረስ የሆቴሎች ደንበኞች ቁጥር በቀነሰበት አሐዝ መጠን ላይ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ቢኒያም፣ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የደረሰውን ጉዳት አሳውቁኝ ባለው መሠረት በወቅቱ እንዲያውቀው መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡ ይሁንና የደረሰውን ጉዳት በራሱ ለማጣራት በመፈለጉ እስካሁንም ድረስ ለቀረበው ጉዳት ምላሽ እንዳልተሰጠበት አስታውቀዋል፡፡

ሆቴሎች ደርሶብናል ያሉትን ኪሳራ ለማካካስ መንግሥት ማድረግ ይገባዋል ያሏቸውን ጥያቄዎችም ይፋ አድርገዋል፡፡ በዚህ በጀት ዓመት መክፈል የሚጠበቅባቸውን የንግድ ትርፍ ግብር እንዲነሳላቸው ማድረግ አንደኛው አማራጭ እንደሆነ የገለጹት አቶ ቢኒያም፣ ከዚህ ባሻገር አብዛኞቹ ሆቴሎች ያለባቸውን የባንክ ዕዳ ከነወለዱ የመክፈያ ጊዜ በአንድ ዓመት እንዲራዘምላቸው ማድረግም ሌላኛው አማራጭ ተደርጓል፡፡ ወይም ደግሞ የደረሰውን ኪሳራ የሚያካክስ ገንዘብ እንዲሰጣቸው ማድረግ ለመንግሥት የቀረቡ የኪሳራ ማካካሻ መፍትሔዎች ቢሆኑም እስካሁን የመንግሥት ምላሽ ይጠናል የሚል እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል በአገሪቱ የሆቴል ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚታየውን የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ለማቃለል የሆቴል ባለሙያዎች ማሠልጠኛ አካዴሚ ለመመሥረት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ አቶ ቢኒያምና ሌሎች የማኅበሩ ኃላፊዎች አስታውቀዋል፡፡ የአካዴሚው አጠቃላይ ሁኔታ በመጪው ነሐሴ ወር ይፋ እንደሚደረግ የጠቀሱት ኃላፊዎቹ፣ ይህም የማኅበሩን 20ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በማስታከክ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ሆቴሎች በሰው ኃይል እጥረት ሳቢያ እርስ በርስ ከመነጣጠቅ ባሻገር፣ ልዩ ልዩ የምርት ግብዓቶችን የማግኘት ችግር እያጋጠማቸው እንደሚገኙም የማኅበሩ ምክትል ሰብሳቢና የኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዜናዊ መስፍን ገልጸዋል፡፡

ከ20 ዓመት በፊት በ15 ሆቴሎች የተመሠረተው ማኅበር ቀደምት ስያሜው የአዲስ አበባ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች አሠሪዎች ማኅበር እንደነበር ሲጠቀስ ሆኖም በየጊዜው በከተማው ውስጥ እየታየ ካለው ለውጥና ሆቴሎችም ከሚገኙበት ዕድገት አኳያ ለብቻቸው በመውጣት የአሁኑን ማኅበር ለመመሥረት እንዳበቃቸው ጠቅሰዋል፡፡   

እንደ አቶ ቢኒያም ትንታኔ ባለፉት ስምንትና ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ በየወሩ አንድ ሆቴል እየተገነባ መቆየቱን፣ በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥም በየሦስት ወሩ ሁለት ሆቴሎች እየተገነቡ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአገሪቱ በግንባታ ሒደት ላይ የሚገኙ ከ100 ያላነሱ ሆቴሎች እንደሚገኙ የጠቀሱት አቶ ቢኒያም ከእነዚህ ውስጥ እስከ 25 በመቶ የሚገመቱት ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው የውጭ ሆቴሎች እንደሆኑ አስታውቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማኅበር ባለፈው ዓመት ማሳተም የጀመረውን የአዲስ አበባ ቱሪዝምና ሆቴሎችን የሚያስተዋውቅ መጽሔት ሁለተኛ ዕትም ይፋ አድርጓል፡፡ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ባለሙዎች ተሰናድቶ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ የሚታተመው ‹‹አዲስ አበባ ቱሪዝም ጋይድ 2017›› የተሰኘው መጽሔት፣ በአገር ውስጥ ለሚገኙ ኤምባሲዎችና ቆንፅላዎች፣ ለተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች፣ እንዲሁም ማኅበሩ በሚሳተፍባቸው ዓለም አቀፍ ንግድ ትርዒቶችና የንግድ ለንግድ መድረኮች እንደሚያሠራጨው ታውቋል፡፡ 

Standard (Image)

የአማራ ክልል ንግድ ምክር ቤት አመራሮች የምርጫ ቀን ተወሰነ

$
0
0

ለወራት ሲያወዛግብ የቆየው፣ ለኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ በወቅቱ አለመካሄድና መጓተት አንዱ ምክንያት ሆኖ ሲጠቀስ የነበረው የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔና የአመራር አባላት ምርጫ በመጪው ዓርብ፣ ሚያዝያ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲካሄድ ተወሰነ፡፡

የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅን በተፃረረ አኳኋን ወደ አመራርነት ቦታ መጥተዋል የተባሉትን ኃላፊዎች በአዲስ ተመራጮች ለመተካት በማለት ይካሄዳል የተባለውን ጠቅላላ ጉባዔ የጠራው በቅርቡ በአማራ ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ አማካይነት የተዋቀረው የምርጫ አመቻችና አደራጅ ኮሚቴ ነው፡፡

የምርጫ አደራጅ ኮሚቴው ያሰራጫው ደብዳቤ የአማራ ክልል የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ያካሄደው ስድስተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ የሕግ ጥሰት አለበት በማለት ከተለያዩ ምክር ቤቶች የቀረበውን ቅሬታ በማስታወስ ይጀምራል፡፡ የተነሱት ቅሬታዎች መሠረት በማድረግ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የንግድ፣ ኢንዱስትሪና የገበያ ልማት ቢሮ በሕግ ባለሙያዎች በመታዝ ጉዳዩን ሲከታተል መቆየቱን ይጠቅሳል፡፡ በመሆኑም መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. የተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔና የአመራር አባላት የምርጫ አካሄድ ላይ ችግር መኖሩ እንደተረጋገጠ ደብዳቤ ያትታል፡፡

ይህንን ተከትሎም የምክር ቤቱ ሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ሰርተፍኬትም በምዝገባውን ባካሄደው አካል መሰረዙን፣ ሆኖም የክልሉ የዘርፍ ምክር ቤት በአዋጅ የተቀመጠውን የአደረጃጀት ሥርዓት ተከትሎ ምክር ቤቱን በድጋሚ ሊያደራጅ እንደሚገባው በመታመኑ በመጪው ዓርብ የተጠራው ጉባዔ መሥራች ጉባዔ እንደሚሆንም አስታውቋል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ የሕጋዊነት መሠረት የሆነውን ሰርተፍኬት በድጋሚ ማግኘት እንዲችል ክልላዊ መሥራች ጉባዔ ማካሄድ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ የመሥራች ጉባዔውና የአመራር አባላት ምርጫው በመጪው ዓርብ እንደሚካሄድ መወሰኑንም ቢሮውና አደራጅ ኮሚቴው የጻፏቸው ደብዳቤዎች ጠቅሰዋል፡፡

አደራጅ ኮሚቴው በተሰየመ በአጭር ጊዜ ውስጥ ባለፈው ሳምንት ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት፣ አባል ምክር ቤቶች በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ለመሳተፍ ሊያሟሉ ይገባቸዋል ያላቸውን መሥፈርቶች በማካተት ጥሪውን አስተላልፏል፡፡ እያንዳንዱ አባል ምክር ቤት በጠቅላላው ጉባዔ ወቅት በምን ያህል ተወካዮች እንደሚወከል ጭምር በማስላት፣ በዚሁ መሠረት ተወካዮቹን እንዲልክ ማሳሰቢያ እንደተሰጠ ለማወቅ ተችሏል፡፡

እያንዳንዱ ተወካይ በጉባዔው ዕለት ይዞ እንዲቀርብ ከተጠየቀው ማስረጃዎች መካከል የታደሰ የንግድ ፈቃድ፣ ማንነትን የሚገልጽ መታወቂያ፣ በከተማው የንግድ ምክር ቤት ቦርድ ተወክሎ ስለመላኩ ውሳኔ የተሰጠበትን የቃለ ጉባዔ ግልባጭ የማመሳከሪያ ደብዳቤ ወዘተ. የሚሉት ይገኙበታል፡፡ የክልል ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ተወካዮች ከከተማና ከወረዳ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትም ከየክልሉ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ተወክለው ስለመላካቸው ለማረጋገጥ፣ የተወከሉበትን የቦርድ ስብሰባ ቃለ ጉባዔ ግልባጭ መያዝ እንደሚጠበቅባቸው በተላለፈው ጥሪ ወረቀት  ተገልጿል፡፡ የአባልነት ግዴታውን መወጣቱን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዲያቀርብም ተጠይቋል፡፡ በመሥራች ጉባዔው በመገኘት ተካፋይ የሚሆኑት፣ ሕጋዊ አባልነታቸውን በማስጠበቅ የቦርድ አመራር አባላት ባይሆኑም እንኳ በጉባዔው መሳተፋቸው ብቻም ሳይሆን በምርጫው ተወዳዳሪ ቢሆኑ የሚጠቅም ስለመሆኑ ከታመነበትም፣ የከተማው ወይም የወረዳው ምክር ቤት አባሉን ለምርጫ ወክሎ ሊልክ እንደሚችል ታውቋል፡፡

ከእነዚህ መሥፈርቶች ውስጥ ሁሉንም ሳያሟላ የሚመጣ የንግድ ምክር ቤት ተወካይ፣ በጠቅላላ ጉባዔ መሳተፍ እንደማይፈቀድለት አደራጅ ኮሚቴው የጻፈው ደብዳቤ ይጠቅሳል፡፡

እንደ ምንጮች ገለጻ ከሆነ፣ ከስምንት ዓመታት በላይ በአመራርነት ቆይተዋል የተባሉት አቶ ጌታቸው አየነውን ጨምሮ በቦርድ አባልነት ሲያገለግሉ የቆዩ ሌሎችም ግለሰቦች ዓርብ በሚካሄደው ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ላይ እንደማይሳተፉ ይታመናል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ቀድሞም ቢሆን በአባልነት ከተመዘገቡት ንግድ ምክር ቤቶች በተገቢው መንገድ ተወክለው ያልመጡ በመሆናቸው ሲሆን፣ አሁንም በሕጉ አግባብ ተወክለው ይመጣሉ ተብሎ ስለማይታሰብ መሆኑን ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በአባልነት የተመዘገቡባቸው የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች የሚወክሏቸው ከሆነ ግን የመሳተፍ መብት እንደሚኖራቸው የጠቀሱም አሉ፡፡

የአማራ ክልል የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በአሁኑ ወቅት ሕጋዊ አባሎቼ ናቸው በማለት ያስመዘገባቸው የአባላት ቁጥር የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት መሥራች ምክር ቤቶች ካሏቸው አባላት ቁጥር አብላጫውን እንደያዘ ሲጠቀስ ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከሰባት ወራት በፊት ማካሄድ ይጠበቅበት የነበረበው የቦርድ አመራሮች ምርጫ ለመዘግየቱ አንዱ ምክንያትም አባል ንግድ ምክር ቤቶች ያስመዘገቧቸው አባላት ቁጥርና ሕጋዊነት በትክልል ሊታወቅ አለመቻሉ፣ ጥቂት የማይባሉትም አጠራጣሪ ሆነው በመገኘታቸው ማጣራት ያስፈልጋል በሚሉ ወገኖች የተፈጠረው አለመግባባት ለምርጫው መራዘም መንስዔ እንደሆነ ይታወሳል፡፡

የንግድ ምክር ቤቶቹ ያስመዘገቧቸው አባላት ብዛት ትክክለኛነት እንዲጣራ ከመደረጉ በፊት ከ260 ሺሕ በላይ አባላት እንዳሉት አስታውቆ የነበረው የአማራ ክልል የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ ማጣራት ከተካሄደበት በኋላ ግን የአባላቱ ቁጥር ከ100 ሺሕ በላይ ቀንሶ ተገኝቷል፡፡

በባህር ዳር ከተማ በመጪው ዓርብ እንደሚካሄድ በሚጠበቀው ምርጫም፣ በዚሁ የአባላት ቁጥር መሠረት የክልሉ የጠቅላላ ጉባዔ ውክልና እንደሚደረግ ይታሰባል፡፡ በዚህ ምርጫ ላይ ከክልሉ 11 ዞኖች፣ ከሁሉም አንድ አንድ ዕጩዎች ተውጣጥተው እንደሚቀርቡ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ትልልቅ ከሚባሉት ከተሞች ውስጥ የጎንደር፣ የደሴና የባህር ዳር የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ግን ከእያንዳንዳቸው ሁለት ዕጩዎች ለምርጫ ሊቀርቡ እንደሚችሉ እየተነገረ ነው፡፡

በጠቅላላው ለፕሬዚዳንትነትና ለምክትል ፕሬዚዳንትነት ስድስት ዕጩዎችን፣ ለቦርድ አባልነት ደግሞ 15 ዕጩዎችን በማቅረብ ምርጫውን ለማካሄድ እንደታሰበ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡ 

የዓርቡ ምርጫ ውጤት ከታወቀ በኋላ፣ የክልሉን ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ወክለው በኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ የሚሳተፉ ተወካዮች እነማን እንደሚሆኑ ለመለየት እንደሚቻል ይጠበቃል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኢንዱስትሪና የገበያ ልማት ቢሮ በበኩሉ፣ የክልሉ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ያካሄደው ስድስተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ የሕግ ጥሰት አለበት የሚሉ ቅሬታዎችን መነሻ በማድረግ ጉዳዩን ሲከታተል መቆየቱን ገልጾ፣ በወቅቱ የተካሄደው ጉባዔ ችግር እንዳለበት በመገምገም ጉባዔው በድጋሚ እንዲካሄድ መወሰኑን አስታውሷል፡፡ ቢሮው በአደራጅነት የመረጣቸው የኮሚቴ አባላት ከኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ ከደብረ ብርሃን የንግድ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ ከደብረ ማርቆስ የንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እንዲሁም ከባህር ዳር ከተማ የንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተውጣጡ ናቸው፡፡ አደራጅ ኮሚቴውን በሰብሳቢነት እንዲመሩ የተሰየሙት ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተወከሉት የንግድ ምከር ቤቱ ምክትል ዋና ጸሐፊ አቶ ውቤ መንግሥቱ ናቸው፡፡

 

 

 

Standard (Image)

የግል ባንኮች ከ4.9 ቢሊዮን ብር በላይ አተረፉ

$
0
0

 

የአገሪቱ የግል ባንኮች ለዓመታት በአትራፊነታቸው የዘለቁ መዝለቅ የቻሉ ሲሆን፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራትም በጠቅላላው ከታክስና ከሌሎች ተቀናሽ ወጪዎች በፊት ከ4.9 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገባቸው ታውቋል፡፡

የባንኮችን የዘጠኝ ወራት የሥራ ክንውን የሚያሳየው የመጀመርያ ደረጃ ግርድፍ ሪፖርት፣ 16ቱም የግል ባንኮች ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ያስመዘገቡት፣ የትርፍ መጠን ከዓምናው ዘጠኝ ወራት ይልቅ ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው ያመለክታል፡፡

እንደ መረጃው ከሆነ፣ 16ቱም ባንኮች አትራፊ ቢሆኑም አራት ባንኮች በዘጠኝ ወራት ያስመዘገቡት ትርፍ፣ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ካገኙት ትርፍ ጋር ሲነፃፀር ቅናሽ አሳይቷል፡፡

ባንኮቹ ከስድስት ሚሊዮን እስከ 248 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ጭማሪ ትርፍ እንዳስመዘገቡ መረጃው ይጠቁማል፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ያስመዘገቡት ግን ባንኮች አዋሽ፣ ዳሸንና አቢሲኒያ ናቸው፡፡

እንደ ሪፖርቱ ከሆነ፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ከ986 ሚሊዮን ብር፣ ዳሸን ባንክ ከ814 ሚሊዮን ብር፣ አቢሲኒያ ባንክ 502 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፍ ችለዋል፡፡ ሦስቱ ባንኮች በዘጠኝ ወራት ውስጥ ያስመዘገቡት የትርፍ መጠን ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር፣ በተለይ ዳሸን ባንክ ከ248 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው ትርፍ ማግኘቱን ያሳያል፡፡ አዋሽ ባንክ ያገኘው ትርፍ ከዓምናው ዘጠኝ ወራት ጋር ሲነፃፀር ከ183 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳሳየ ለመረዳት ተችሏል፡፡ አቢሲኒያም የ129 ሚሊዮን ጭማሪ ትርፍ አግኝቷል፡፡

ከሦስቱ ባንኮች ባሻገር፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከፍተኛ ትርፍ ያስመዘገበው፣ ወጋገን ባንክ ነው፡፡ ወጋገን ባንክ በዚህ ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ከታክስና ከተቀናሾች በፊት ከ467 ሚሊዮን ብር በላይ አትርፏል፡፡

ይህ የትርፍ መጠኑ ከዓምናው ይልቅ ከ166 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው የሚጠቁም ነው፡፡ ይህም ከዳሸንና ከአዋሽ ቀጥሎ የትርፍ መጠኑን በማሳደግ በሦስተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አድርጎታል፡፡

የትርፍ መጠናቸውን ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ማሳደግ የቻሉት ሌሎቹ ባንኮች ብርሃን፣ ሕብረትና ንብ ናቸው፡፡ እንደ መረጃው ከሆነ፣ ሕብረት ባንክ ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት 352 ሚሊዮን ብር፣ ንብ 435 ሚሊዮን እንዲሁም ብርሃን 351 ሚሊዮን ብር ማትረፍ መቻላቸውን ይኸው ግርድፍ ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡

የአገሪቱ የግል ባንኮች በ2008 ሙሉውን በጀት ዓመት በጠቅላላው ያስመዘገቡት ትርፍ ከ6.05 ቢሊዮን ብር በላይ እንደነበር ይታወቃል፡፡

በዚህ ዓመት ሦስተኛው ሩብ ዓመት መጨረሻ ድረስ የግል ባንኮች ጠቅላላ ሀብት መጠን ከ220 ቢሊዮን ብር በላይ ሊደርስ መቻሉ ታይቷል፡፡ ከፍተኛ ሀብት ካስመዘገቡት ውስጥ አዋሽ ባንክ በቀዳሚነት ሲቀመጥ፣ አጠቃላይ ሀብቱም 36.8 ቢሊዮን ብር ሆኗል፡፡ ዳሸን 32.3 ቢሊዮን ብር፣ አቢሲኒያ 23.4 ቢሊዮን ብር፣ ወጋገን 20.5 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ሕብረት ባንክ 20.8 ቢሊዮን ብር ያስመዘገበ ሀብት ማፍራት መቻላቸው ተጠቁሟል፡፡

እነዚህ ባንኮች በሦስተኛው ሩብ ዓመት መጨረሻ ያሳዩት የብድር ክምችትም ማደጉ ታይቷል፡፡ አዋሽ ባንክ 21.2 ቢሊዮን ብር ሲያስመዘግብ፣ ዳሸን 17.8 ቢሊዮን ብር፣ አቢሲኒያ 13.4 ቢሊዮን ብር፣ ወጋገን 10.12 ቢሊዮን ብር፣ ሕብረት 11.01 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ንብ ባንክ 10.6 ቢሊዮን ብር ያስመዘገበ የብድር ክምችት እንዳላቸው ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያሳያል፡፡  

Standard (Image)

ዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ተቋም ዓለም የሚጠቀምበት ዘመናዊ የጂን ባንክ በአዲስ አበባ መሠረተ

$
0
0

 

  • ለኢትዮጵያ እንስሳት መኖ አቅርቦትና ለብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ተስፋ ተጥሎበታል

ከመላው ዓለም የተሰባሰቡና አገሮች የተስማሙባቸው፣ ከ1,000 በላይ የዕፅዋት ዝርያዎች ያሏቸውን 19,000 ያህል ጂኖች ያሰባሰበና ለመላው ዓለም አገልግሎት የሚሰጥ ዓለም አቀፍ የእንስሳት መኖ ጂን ባንክና ባዮ ሳይንስ ማዕከል በአዲስ አበባ ተመሠረተ፡፡

ዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት (International Livestock Research Institute- ILRI) የገነባው ዘመናዊ የጂን ባንክና የባዮ ሳይንስ ማዕከል፣ ከኢትዮጵያ የ20 በመቶ የጂን አቅርቦት እንዳገኘ የተቀረውን ግን ከመላው ዓለም ማሰባሰቡን ሰኞ ሚያዝያ 16 ቀን 2009 ዓ.ም. የተቋሙ ሥራ መጀመር ይፋ በተደረገበት ወቅት ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ የኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር ጄኔራል ተወካይ ሲቦኒሶ ሞዮ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአዲስ አበባ ተቋሙ በሚገኝበት ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገነባው አዲሱ ዘመናዊ የጂን ባንክ ለኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ለመላው ዓለም አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡ በተቋሙ የተሰባሰቡት ዝርያዎች ንብረትነታቸው የዓለም ሕዝብ እንደሆነ እንዲሁም በምግብና በግብርና መስክ በተደረጉ ዓለም አቀፋዊ የተክሎች የጂን ሀብት ስምምነቶች መሠረትም ለመላው ዓለም በነፃ የሚቀርቡ የጂን ሀብቶች እንደተካተቱበት ሚስተር ሞዮ አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም የተክሎችን ውጤታማነትና ምርታማነት ለማሻሻል ብሎም ለረዥም ጊዜ ጠብቆ ለማቆየት በአዲስ መልክ የተገነባ ማከል መሆኑ ተገልጿል፡፡

የዕፅዋት ዝርያና ዓይነታቸውን በመሰነድ፣ ዕፅዋቱ ከአካባቢ ሁኔታዎች ጋር ስላላቸው ተዛምዶና ስለሌሎችም ጉዳዮች ምርምር በማካሄድ የመመዝገብና የመጠበቅ ሥራዎች ቀድሞም ተቋሙ ውስጥ ለዓመታት ሲተገበር የቆየ ሲሆን፣ ይህንን በማሻሻል በዘመናዊ መሣሪያዎችና በዘመናዊ ሕንፃ የተደራጃ ማዕከል በመገንባት ለሥራ ማብቃቱን ሚስተር ሞዮ ገልጸዋል፡፡

ሁለት ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገበት አዲሱ ማዕከል፣ ለኢትዮጵያ የዕፅዋት ምርምርና ጥበቃ ላይ ስለሚያደርገው አስተዋጽኦ ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳሬክተር መለስ ማሪዮ (ዶ/ር) እንደሚጠቅሱት፣ በኢትዮጵያ ሁለት የብዝኃ ሕይወት ጥበቃ የሚሰጡ ተመሳሳይ የጂን ባንኮች መኖራቸውን ገልጸው በሦስተኛነት በተለይም በእንስሳት መኖ መስክ የሚሠራ የጂን ባንክ መምጣቱ የኢትዮጵያን የብዝኃ ሕይወት ሀብት ጥበቃ እንደሚያጠናክረው ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

በሙያቸው የአግሮ ባዮ ዳይቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ዋና ዳይክተሩ፣ ኢንስቲትዩቱ በብዝኃ ሕይወት ጥበቃ መስክ ከሚጠበቁበት ተግባራት መካከል ማንበር (ማቆየት)፣ ዘላቂ ቆይታ እንዲኖር ማድረግና መጠቀም እንዲሁም የኅብረተሰቡ ተጠቃሚነትና የጥቅም ተካፋይነት አራት ትላልቅ ተግባራት ማከናወን ሲሆኑ፣ በእንስሳት፣ ለምግብነት በሚውሉ አዝርዕትና ሆርቲካልቸር እንዲሁም በማይክሮ ባዮሎጂካል ዘርፍ የብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ሥራዎች ላይ በማተኮር የሚሠራው የብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት፣ በዓለም አቀፉ የእስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት አዲስ የጂን ባንክ ተጠቃሚ የሚሆንባቸው ዕድሎች መፈጠራቸው ተፈላጊ ዕፅዋትን ለመጠበቅ ብቻም ሳይሆን ለሚካሄዱ ልዩ ልዩ ምርምሮችም አጋዥ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በተክሎችና በዕፅዋት መስክ በከብቶች መኖነት የሚያገለግሉ ተክሎች ላይ በተለይ ድርቅ በሚመላለስባቸው አካባቢዎች ላይ ውኃ አጠር በሆኑ፣ በቶሎ የማይደርቁ ሰፋፊ ቅጠሎች ያሏቸውን የመኖ ዕፅዋት በመጠበቅ ብቻም ሳይሆን አልምቶ ለመጠቀም የሚረዱ ሥራዎችን ለማከናወን አዲሱ የጂን ባንክ ብዙ ጥቅም እንዳለው አቶ መለሰ አብራርተዋል፡፡

በተለይም በጂን ጥበቃ ረገድ ከዚህ ቀደም በተለያዩ አገሮች የተፈጸሙ ስርቆቶችንና የተወሰዱ የጂን ሀብቶችን በማስመለስ ረገድ ተቋማቸው፣ ከአንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩቱ ጀምሮ እንደ ጀርመን ባሉ አገሮች የተወሰዱትን ሲያስመልስ መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ዓለም አቀፍ ተቋም እንደመሆኑ በሌሎች አገሮች የሚገኙ ልዩ ልዩ የብዝኃ ሕይወት ሀብቶችን አገር ውስጥ በማላመድ፣ ከኢትዮጵያ ሥነ ምኅዳር ጋር በመስማማት የኢትዮጵያ ሀብት ሆነው መመደብ የሚችሉበት ሰፊ ዕድል እንደሚኖርም ጠቅሰዋል፡፡ ይህም ሆኖ ወራሪ ዕፅዋትን የመከላልና የመቆጣጠር ሥራዎችን በመሥራት ያልታሰቡ ጉዳቶች እንዳይደርሱ የሚደረጉ ጥበቃዎች እንዳሉም አብራርተዋል፡፡ 

ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ በደረሰባት ጉዳትና ዘረፋ ሳቢያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የብዝኃ ሕይወት ሀብቶችን ለመጠበቅ ተብሎ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ሀብቶቿን ለመስጠት ፈቃደኛ ሳትሆን መቅረቷን አቶ መለስ አውስተዋል፡፡ በሰሜናዊ ንፍቅ ግዙፍ የብዝኃ ሕይወት ጥበቃ የሚደረግባት ማዕከል ቢቋቋምም፣ ኢትዮጵያ በማዕከሉ ሀብቶቿን ለማስቀመጥና ለማስጠበቅ የቀረበላትን ጥያቄ ሳትቀበለው ቀርታለች ብለዋል፡፡ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ በሰሜናዊ ንፍቅ ጫፍ ጥበቃ በሚደረግበት የጂን ባንክ ውስጥ ሀብቶቿን ከማስቀመጥ ይልቅ በአዲስ አበባ የሚገኘውን የጂን ባንክ አምሳያ በፍቼ ከተማ መመሥረቱን ያብራሩት አቶ መለስ፣ ይኽም ያልታሰበ የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሠራሽ አደጋዎች ተከስተው አንደኛው የጂን ባንክ ውስጥ የተሰባሰቡት ሀብቶች ጉዳት ቢደርስባቸው በሌላው የሚገኙት ተመሳሳይ ሀብቶች ምትክ እንዲሆኑና ከጥፋት ለመታደግ በማሰብ አምሳያው ማዕከል መተከሉን ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የእንስሳት ሀብት ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር ጌትነት አሰፋ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ በተቋሙ የተከፈተው አዲሱ የጂን ባንክ ለኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች በቅርብ የማይገኙ የነበሩ ቴክሎጂዎችን በቀላሉ ለማግኘት እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል፡፡ 

የአገሪቱ ሕዝብ ቁጥርና የእንስሳት ሀብቱ ብዛት በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ ለዚሁ ቁጥር የሚመጥን የዕፅዋትና የተክሎች አቅርቦት መኖር እንደሚያፈልግ ሲያረዱም፣ በተለይ በአገሪቱ በሰፊው ለሚገኙት እንስሳት የሚውል መኖ በብዛትና በጥራት ለማቅረብ በምርምር የተደገፈ ልማት ለማካሄድ አዲሱ የጂን ባንክና የባዮ ሳይንስ ማዕከል መመሥረቱ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡ በመሆኑም ገበሬዎች ከዚህ ቀደም ሲያከናውኑ ከነበረው የመኖ አመራረት በተጓዳኝ በሰፊው ለማልማት የሚችሉበት መደበኛ የመኖ እርሻ መጎልበት እንደሚኖርበትም አሳስበዋል፡፡

በአቶ ጌትነት ሐሳብ የሚስማሙት ሚስተር ማዮ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ተኮር የእንስሳት መኖ እርሻዎች መለመድ እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡ በእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩቱ የማይክሮ ባዮሎጂቱ ክሪስ ጆንስ (ዶ/ር) እንዲሁም የመኖና የመኖ ሀብት ፕሮግራም ኃላፊ ሲሆኑ፣ የአዲሱ ማዕከል ተግባራ ከሆኑት ውስጥ ለገበሬው ተስማሚ የመኖ ዝርያዎችን በማቅረብ እንዲጠቀሙ ዕድል መፍጠር የሚለው ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠው ገልጸዋል፡፡

 

 

 

Standard (Image)

አዋሽ ባንክ የንግድ ምልክቱንና ስያሜውን ለወጠ

$
0
0

 

ከደርግ ውድቀት በኋላ የመጀመሪያው የግል ባንክ በመሆን የኢትዮጵያን የፋይናንስ ኢንዱስትሪ የተቀላቀለው አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ የንግድ ምልክትና የስያሜ ለውጥ ማደረጉን አስታወቀ፡፡

ባንኩ ላለፉት 22 ዓመታት ሲገለገልበት የነበረውን የኩባንያ አርማና ምልክት መቀየሩን ባለፈው ዓርብ ሚያዝያ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ይፋ አድርጓል፡፡ ሥራ ላይ የዋለው አዲሱ የንግድ ምልክትና ማሻሻያ የተደረገበት ስያሜ ይፋ ሲደረግ እንደተገለጸው፣ ከዚህ በኋላ አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ የሚለው የባንኩ መጠሪያው ተሻሽሎ ‹‹አዋሽ ባንክ›› ብቻ እየተባለ እንደሚጠራ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው ገልጸዋል፡፡

የአርማ ለውጡን በተመለከተም፣ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ የሚለው መጠሪያው ሲጻፍ በተለይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ (AIB) የሚል ምህጻረ ቃል የነበረበትን አርማ በማስቀረት በአዲስ አርማ ተክቷል፡፡ እስካሁን በሥራ ላይ የነበረው አርማ በኅብረተሰቡ ዘንድ የሰረፀ ቢሆንም፣ ለውጥ ማድረጉ ባንኩን ወደተሻለ የዕድገት ደረጃ ለማሸጋገር ብሎም እ.ኤ.አ. በ2025 በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ አሥር ምርጥ የግል ባንኮች መካከል ለመሰለፍ የሚችልበትን መንገድ ለመፍጠር ከሚረዱት መካከል የአርማና የስያሜ ማሻሻል አንዱ መንገድ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ባንኩ ‹‹ራዕይ 2025›› የሚል ስያሜ የሰጠውን ጥናት አካሂዷል፡፡ በጥናቱ መሠረትም አዋሽ ባንክ አሁን የደረሰበትንና መጪውን ጊዜ ማዕከል በማድረግ ለውጡ መተግበሩም ተገልጿል፡፡

ባንኩ ያስጠናውን ጥናት ለመተግበር ከሚያስፈልጉት መካከል በየጊዜው እያደገ የመጣውን የደንበኞች ፍላጎት በዘመናዊ አገልግሎትና በሰፊ ተደራሽነት ማርካት እንዳለበት አመላክቷል፡፡ በኢትዮጵያ ባንኮች መካከል እየተጠናከረ የመጣውን ብርቱ ውድድር፣ ወደፊትም ከውጭ ባንኮች ሊመጣ የሚችለውን ከፍተኛ ፈተና ባንኩ መቋቋም የሚችልበት አቋም ላይ እንዲደርስ ግንዛቤ በመውሰዱ ጥናቱን ማካሄዱና ለውጦችን መተግበር መጀመሩን አቶ ፀሐይ ተናግረዋል፡፡

የባንኩን የወደፊት አቅጣጫ በዘመናዊ መንገድ ለመምራትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማድረግ እየሠራ መሆኑ የተነገረለት አዋሽ ባንክ ይፋ ያደረገው አዲስ አርማ የቀደመውን እንዲተካ ያማከረው ‹‹KMPG›› የተባለው ኩባንያ ሲሆን፣ ለለውጡም ኩባንያው ያቀረበው ሐሳብ መነሻ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ አርማው ከመጽደቁ በፊት በባንኩ እንደተመከረበትም አስታውቀዋል፡፡ ባንኩ አርማዬ ይሆናል ያለውን አዲሱን የንግድ ምልክት ለማሠራት አምስት የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎችን አወዳድሯል፡፡ አርማው ለማሠራት በወጣው ጨረታ ያሸነፈው፣ ዋና መሥሪያ ቤቱን በናይሮቢ ያደረገው የኬንያው ብራንድ ኢንተግሬትድ የተባለ ኩባንያ ነው፡፡ እንደ አቶ ፀሐይ ገለጻ፣ ኩባንያው ልዩ ልዩ የንግድ አርማዎችን በመሥራት ልምድ ያለው ነው፡፡ በአምስት የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ባንኮች አርማዎችን መሥራቱም ተገልጿል፡፡

የባንኩ ስያሜ ከበፊቱ አጥሮ፣ አርማውም ቀላል በሚባል ዲዛይን ተቀይሮ መቀረጹን የባንኩ ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል፡፡ ስለስያሜ ለውጡ ማብራሪያ ሲሰጥ እንደተባለው ‹‹አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ›› ከሚለው መጠሪያ ይልቅ አዋሽ ባንክ የሚለው በአጭሩ ባንኩን ገላጭ ሆኖ ስለተገኘ ተፈላጊነቱ ተብራርቷል፡፡ እንደ አቶ ፀሐይ ገለጻ፣ ኅብረተሰቡም ከዚህ ቀደም በነበረው ልማድ መሠረት ባንኩን የሚጠራው ‹‹አዋሽ ባንክ›› እያለ በመሆኑም ጭምር የተደረገው ለውጥ ተገቢ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ አማካሪ ኩባንያውም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሠሩ ባንኮች ሳይቀሩ ኢንተርናሽናል የሚል ቅጽል እንደሌላቸው፣ ይህም የባንኮቻቸው ስያሜ በቀላሉ በደንበኞቻቸው ዘንድ እንዲሰርጽ ለማድረግ እንደሚያግዝ በማመላከቱ፣ በዚሁ መሠረት የባንኩ መጠሪያ አዋሽ ባንክ ብቻ እንዲሆን ተደርጓል ተብሏል፡፡

የባንኩ የብራንድ ቃል ኪዳንም (Brand Promise) ለኅብረተሰቡ ግልጽና ቀጥተኛ መልዕክት የሚያስተላልፍ፣ የባንኩን ራዕይና ሥራ በሚያንጸባርቅ መልኩ እንዲሠራ መደረጉን ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡ በባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድና በሥራ አመራሩ መካከል ውይይት ተደርጎም በአዲሱ የብራንድ ጥናት መሠረት የባንኩ የብራንድ ቃልኪዳን ከአዋሽ ወንዝ ጋር እንዲያያዝ ተደርጓል፡፡ ይህም አዋሽ ባንክ ልክ እንደ አዋሽ ወንዝ ኅብረተሰቡን የሚያገለግል፣ አሳዳጊና ለስኬት የሚያበቃ እንደሆነ ለማመላከት የተደረገ ነው በማለት አቶ ፀሐይ አብራርተዋል፡፡

የባንኩ የኮርፖሬት ቀለሞችም ጥልቅ ሰማያዊና ብርቱካናማ እንዲሆኑ፣ የባንኩን ምልክት በግልጽና በቀላሉ ለመረዳት እንዲያስችሉ፣ ማንኛውም ሰው በቀላሉ ሊያስታውሰው ታስቦበት እንደተሠራ ተብራርቷል፡፡

አዋሽ ባንክ ኅዳር 1987 ዓ.ም. በ486 ባለአክስዮኖች በ23.1 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመ የግል ባንክ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ3,600 በላይ ባለአክስዮኖች ያሉት ይህ ባንክ፣ የተከፈለ ካፒታሉ 2.7 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በሀብት መጠኑ፣ በብድር ክምችቱና በዓመታዊ የትርፍ መጠኑ ከ16ቱ የግል ባንኮች ከመጀመሪያዎቹ ተርታ የሚሰለፍ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት 1.04 ቢሊዮን ብር በማትረፉ ቀዳሚ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ይህም ከግል ባንኮች ከታክስና ከተንቀሳቃሽ በፊት ዓመታዊ ትርፉን አንድ ቢሊዮን ብር በማድረስ የመጀመሪያው ባንክ እንዳደረገውም መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ከ293 በላይ ቅርንጫፎች ያሉት አዋሽ ባንክ፣ ከ6,400 በላይ ሠራተኞችንም ያስተዳድራል፡፡

ባንኩ እስካሁን ሲጠቀምበት የነበረውን አርማውንና ስያሜውን በአዲሱ አርማና ስያሜ በየቅርንጫፎቹ የመተካት ሥራም ከዚህ ሳምንት ጀምሮ እንደሚጀመር ሲያስታውቅ፣ በዚሁ ወቅትም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ጥሩነህ ኢጣፋ፣ የባንኩ የሥራ ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለአክስዮኖች በመገኘት አዲሱን የባንኩን መለያ አርማ ይፋ አድርገዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

Standard (Image)

የግል ባንኮች ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ በማውጣት የብሔራዊ ባንክን ቦንድ ገዙ

$
0
0

 

የኢትዮጵያ የግል ባንኮች ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስገዳጅ ቦንድ ግዥ ያዋሉት የገንዘብ መጠን ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ ሲታወቅ፣ በ2009 ሦስተኛው ሩብ ዓመት መጨረሻ በጠቅላላው የሰጡት የብድር ክምችት ከ127.7 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

የግል ባንኮች ከሚሰጡት እያንዳንዱ ብድር ላይ 27 በመቶ እየቀነሱ ለብሔራዊ ባንክ የቦንድ ግዥ እንዲያውሉ በሚያስገድደው መመሪያ መሠረት፣ ባንኮቹ የገዙት የቦንድ መጠን ከ50.7 ቢሊዮን ብር በላይ የደረሰው በስድስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ የባንኮቹን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም የሚያመለክተው ግርድፍ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ከ16ቱ የግል ባንኮች ውስጥ ከፍተኛውን የቦንድ ግዥ የፈጸመው ዳሸን ባንክ ነው፡፡ በ2009 ሦስተኛው ሩብ ዓመት መጨረሻ ድረስ ዳሸን ባንክ በአጠቃላይ 7.72 ቢሊዮን ብር ዋጋ የሚያወጣ የቦንድ ግዥ ፈጽሟል፡፡  

አዋሽ ባንክ በበኩሉ 6.3 ቢሊዮን ብር ግምት ያላቸውን ቦንዶች ሲገዛ፣ አቢሲኒያ ባንክ አምስት ቢሊዮን ብር፣ ወጋገን ባንክ 4.9 ቢሊዮን ብር፣ ሕብረት ባንክ 4.6 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ንብ ባንክ 4.6 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን ግዥዎች ፈጽመዋል፡፡

ከእነዚህ ባንኮች ውጭ ያሉት በተናጠል ከ404.7 ሚሊዮን ብር እስከ 3.1 ቢሊዮን ብር ለቦንድ ግዥ እንዳዋሉ መረጃው ያሳያል፡፡ ከ16ቱ ባንኮች ለቦንድ ግዥው ከአንድ ቢሊዮን ብር በታች ያዋሉት ሦስት ባንኮች ሲሆኑ ሌሎቹ ባንኮች ግን ከ1.8 ቢሊዮን ብር በላይ ለቦንድ ግዥ ያዋሉ ስለመሆናቸው ተመልክቷል፡፡

የግል ባንኮቹ ለቦንድ የሚያውሉት ገንዘብ ሦስት በመቶ ወለድ ታስቦበት ለብሔራዊ ባንክ ገቢ የሚደረግ ሲሆን፣ ብሔራዊ ባንክም በቦንድ ሽያጭ አማካይነት የሰበሰበውን ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ ልማት ባንክ እንዲዛወር በማድረግ በመንግሥት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ፕሮጀክቶች ብድር እንደሚውል ይታወቃል፡፡

ባንኮቹ ለቦንድ ግዥ ካዋሉት ገንዘብ አምስት ዓመት ሲሞላው፣ የሦስት በመቶ ወለድ ታክሎበት እንደሚመለስላቸው መደንገጉ ይታወቃል፡፡ ሆኖም አምስት ዓመት ያስቆጠረ ቦንድ ያላቸው የተወሰኑ ባንኮች ዓምና የተመለሰላቸው ሲሆን፣ ከአምስቱ ዓመት ውስጥ ለአንድ ዓመት የቦንድ መግዣ ያዋሉት ገንዘብ ተመላሽ እንደተደረገላቸው አይዘነጋም፡፡

 በግርድፉ መረጃ መሠረት 16ቱ የግል ባንኮች በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ለአገልግሎት ያዋሉት አጠቃላይ የብድር መጠን ከ127.7 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ ይህ የብድር መጠን ዓምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 88.6 ቢሊዮን ብር መጠን ጋር ሲመሳከር፣ ከ39 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው፡፡ በ2008 በጀት ዓመት በጠቅላላው የነበራቸው የብድር ክምችት 93.3 ቢሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡

የ16ቱን የግል ባንኮች አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ በተመለከተም በ2009 ዓ.ም. ዘጠኝ ወር ጊዜ ውስጥ 180.2 ቢሊዮን ብር ሊደርስ እንደቻለ ታውቋል፡፡ ይህ መጠንም ዓምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበራቸው 137.4 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር በ46 ቢሊዮን ብር ከፍ ያለ ነው፡፡ በ2008 በሙሉ በጀት ዓመት ባንኮቹ ያስመዘገቡት የተቀማጭ ገንዘብ ክምችት 146 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡

በ2007 ዓ.ም. በሦስተኛው ሩብ ዓመት መጨረሻ ላይ የሁሉም ባንኮች (የመንግሥትና የግል) ቅርንጫፎች ቁጥር በጠቅላለው 2,516 እንደነበር የሚያመላክተው የብሔራዊ ባንክ መረጃ፣ በዓምናው ዘጠኝ ወራት ውስጥ ግን ወደ 3,045 ማድረስ መቻሉን ነው፡፡ በ2009 ዓ.ም. ዘጠኝ ወራት ውስጥ የሁሉም ባንኮች ቅርንጫፎች ቁጥር ከ4,300 በላይ ሆኗል፡፡ ከዚህ ውስጥ 2,527 የግል ባንኮች የከፈቷቸው ቅርንጫፎች እንደሆኑ መረጃው ያሳያል፡፡  

የ16ቱ የግል ባንኮች የሀብት መጠንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንደመጣ የሚያሳየው መረጃ፣ በ2009 ሦስተኛው ሩብ ዓመት መጨረሻ ድረስ አጠቃላይ የተመዘገበው ጠቅላላ ሀብታቸው ከ237.3 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ በ16ቱ ባንኮች መካከል ያለው የሀብት መጠን ግን ሰፊ ልዩነት እየታየበት መጥቷል፡፡ የባንክ ኢንዱስትሪውን በመቀላቀል ቀደምት የሆኑት ባንኮች የሀብት መጠን በያመቱ እያደገ ገበያውን ዘግይተው ከተቀላቀሉ ባንኮች አኳያ ሲታይ ያፈሩት የሀብት መጠን ልዩነቱ ሰፊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ከ16ቱ ባንኮች ውስጥ ስምንቱ በዚህ ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ያስመዘገቡት ሀብት ከ1.5 እስከ 9.4 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ የቀሪዎቹ ስምንት ባንኮች መጠን ግን ከ14.6 እስከ 36.3 ቢሊዮን ብር ሆኗል፡፡

ሀብታቸውን ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ ከቻሉት ስምንቱ ባንኮች ውስጥ የአዋሽ 36.6 ቢሊዮን ብር፣ የዳሸን 32.3 ቢሊዮን ብር፣ የአቢሲኒያ 23.4 ቢሊዮን ብር፣ የሕብረት ባንክ 20.8 ቢሊዮን ብር፣ የወጋገን 20.5 ቢሊዮን ብር፣ የንብ 19.4 ቢሊዮን ብር፣ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ 17.3 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ 14.6 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡  

Standard (Image)

ታክሲዎችን በሦስት ጎራ የከፈለው አሠራር አለመግባባቶችን አባብሷል

$
0
0

-‹‹130 ሚሊዮን ብር ወጪ ካደረግን በኋላ በህልውናችን ላይ አደጋ ተደቅኗል›› ያሉ የቦሌ ታክሲዎች አቤቱታ ፍርድ ቤት ደርሷል

-አቫንዛ ታክሲዎች ወደ ቦሌ እንዳንገባ የተከለከልነው ሆን ተብሎ በሚደረግ ጫና ነው ይላሉ

መንግሥት ከቀረጥ ነፃ ዕድል በመስጠት ያስገባቸው 1,163 ታክሲዎች ብዙም ሳይቆዩ አነጋጋሪ ሆነው መቆየታቸው ታይቷል፡፡ ከሰሞኑ የመገናኛ ብዙኃንን የአየር ሰዓት የተቆጣጠረው ጉዳይም ከእነዚሁ ታክሲዎች ጋር የሚያያዝ ነው፡፡

ላለፉት 26 ዓመታት በአዲስ አበባ ቦሌ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት ውስጥ የቱሪስት ታክሲ አገልግሎት በመስጠት ሲያገለግሉ የቆዩ የታክሲ ባለንብረቶች ከሰሞኑ የፍርድ ዕግድ በማውጣት የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ያወጣውን የስምሪት ድልድል መቃወማቸው ይታወሳል፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣም ዕግዱን በማስመልከት መዘገቡ አይዘነጋም፡፡ ዘገባውን ተክትሎም በቦሌ ኤርፖርት የቱሪስት አገልግሎት የሚሰጡ አባላት ያደራጇቸው ማኅበራት አመራሮች ከሪፖርተር ጋር ዕግዱን ማውጣት ስላስፈለገበት ምክንያት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በኤርፖረቱ የቱሪስት አገልግሎት እንዲሰጡ የተደራጁ 454 አባላትን የሚወክሉ ስድስት ማኅበራት ሲኖሩ፣ እነዚህን ማኅበራት የሚያስተባብር የጥምረት አሠራርም አላቸው፡፡ አቶ ሳሙኤል አመነ የጥምረቱ ምክትል ሰብሳቢና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሲሆኑ፣ እዮብ ወልዳይ እና አቶ አቤሴሎም መኮንን፣ በጥምረቱ የስምሪት እንዲሁም የምክትል ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊነት ድርሻዎችን በመያዝ ይሠራሉ፡፡ ስኬት፣ መቅደላ፣ ወንድማማቾች፣ ህዳሴ፣ ጥምረትና አንድነት የተባሉትን ስድስት ማኅበራት የሚወክሉት ኃላፊዎቹ እንደገለጹት ከሆነ፣ በቅርቡ በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን እንዲሁም ከዚህ ቀደም በኤርፖርት ውስጥ አብራቸው ይሠሩ በነበሩና አቫንዛ ሜትር ታክሲዎችን ለመግዛት የወጡ ከ100 በላይ ባለንብረቶች የፈጠሯቸው ጫናዎች በህልውናችን ላይ አደጋ ጋርጠዋል ይላሉ፡፡

ይኸውም ባለሥልጣኑ ከፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን በተሰጠው ውክልና መሠረት በ2007 ዓ.ም. ‹‹የሳሎን ሜትር የከተማ ታክሲ ተሽከርካሪዎች›› ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ለመፍቀድ የወጣውን መመሪያ አላከበረም የሚል ቅሬታ እየቀረበበት ይገኛል፡፡ በቀድሞው ትራንስፖርት ሚኒስትር፣ የአሁኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ተፈርሞ የወጣው መመሪያ ቁጥር 8/2007 በግንቦት ወር ወደ ሥራ ሲገባ የታክሲ አገልግሎትን በአራት መደቦች የሚፈርጅ ትርጓሜ አስቀምጦ ነበር፡፡

በመመሪያው መሠረት፣ ‹‹የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጓሜ የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር›› በማለት የሚጀምረው ትርጓሜ፣ ‹‹ሳሎን ሜትር ታክሲ››፣ ‹‹ቱሪስት ታክሲ››፣ ‹‹አውቶሞቢል ታክሲ››፣ እንዲሁም ‹‹ሚኒባስ ታክሲ›› በማለት የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡትን ተሽከርካሪዎች መድቧል፡፡ በመሆኑም ‹‹ሳሎን ሜትር ታክሲ ማለት ከ4 እስከ 7 መቀመጫ፣ የተሳፋሪውን ሻንጣ ለመጫን የሚያስችል ቦታ ያላቸው፣ ካብ ሜትር የተገጠመላቸውና በስልክ ወይም በሬዲዮ መገናኛ ወይም በአካል ጥሪ/ጥያቄ በከተማው ክልል ውስጥ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ናቸው፤›› ይላቸዋል፡፡

‹‹ቱሪስት ታክሲ ማለት በአውሮፕላን ማረፊያና በባለኮከብ ሆቴሎች በመቆም በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ዕውቅና ባገኙ ማኅበራት፣ በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የሙያ ፈቃድ አግኝተው ለቱሪስቱ በስምምነት በሚወሰን ታሪፍ መሠረት በውል የታክሲ አግልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ናቸው፤›› ሲል ስለ ቦሌ ታክሲዎች ትርጓሜ ይሰጣል፡፡ መመሪያው ነጭና ሰማያዊ ቀለም የተቀቡ፣ አራት ሰው የመጫን አቅም ያላቸውንና በተለምዶ ላዳ ታክሲ የሚባሉትን አውቶሞቢል ታክሲዎች ይላቸዋል፡፡

እነዚህ ከላይ የቀረቡት ሁለት ትርጓሜዎች ናቸው በከተማው አስተዳደር ሥር የሚገኙትን የትራንስፖርት ባለሥልጣንና የባህልና ቱሪዝም ቢሮን ካለመግባባት ውስጥ ከመክተታቸውም ባሻገር፣ ከቀረጥ ነፃ በገቡት ታክሲዎችና በቦሌዎቹ የቱሪስት ታክሲዎች መካከል እንዲሁም እነዚህ ሁለቱም ከባለሥልጣኑ ጋር በየፊናቸው ያልተግባቡባቸው ነጥቦች እንዲከሰቱ ምክንያት የሆነው ይኸው መመሪያ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡

ቢጫዎቹ የቦሌ ታክሲዎች አቋም

እነ አቶ ሳሙኤል እንደሚከራከሩት ከሆነ በሕጉ መሠረት በግልጽ በተጠቀሰ ቦታ፣ በተወሰነ ክልል በመቆም የቱሪስት አገልግሎት እንዲሰጡ በመደረጉ ምክንያት እንደሌሎቹ ታክሲዎች በከተማው እየተዘዋወሩ መሥራት የማይፈቀድላቸው ናቸው፡፡ በመሆኑም በኤርፖርትና ሆቴሎች አካባቢ በሚወጣ ድልድል አማካይነት የሚሠሩ፣ የየራሳቸው ሕግና ደንብ ያላቸው፣ በደንብ ልብስ የታገዘ አገልግሎት የሚሰጡ፣ የዲስፕለን ቁጥጥር በማድረግ ጭምር አባሎቻቸውን ለሥነ ሥርዓት ተገዥ በማድረግ እንደሚሠሩና የዲስፕሊን ግድፈት የፈጸሙትንም እስከ ሁለት ሳምንት በሚደርስ ቅጣት ከስምሪት የሚያግዱበት አሠራር የዘረጉ መሆናቸውን ሁሉ ይጠቅሳሉ፡፡

ይሁንና እንዲህ እየሠሩ ባሉበት ወቅት፣ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ያወጣውን መመሪያ በሚሽር አኳኋን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን አዲስ አሠራር ማምጣቱ ከስጋት በላይ የህልውና ጥያቄ እንደጋረጠባቸው ይናገራሉ፡፡ በአዲሱ አሠራር መሠረት ሁሉም ታክሲዎች ወደ ኤርፖርት በመግባት መሥራት ይችላሉ የሚለው የባለሥልጣኑ አቋም ችግር ፈጥሮብናል ይላሉ፡፡ በቅርቡ በወጣው ድልድል መሠረትም ኤርፖርቱ በቀን ማስተናገድ የሚችለው ታክሲ 150 በመሆኑ፣ ይህንኑ መነሻ በማድረግ በእኩል ድርሻ የሜትር ታክሲዎችም የቦሌዎቹም እንዲሠሩ መደልደሉ ፈጽሞ ተቀባይነት የለው ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ በአዲሱ ድልድል መሠረት የስድስቱ የቦሌ ታክሲዎች ማኅበር አባላት በዙር የሚደርሳቸው በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ አንድ ሳምንት ብቻ እንደሆነ በማብራራትም የባለሥልጣኑን ስምሪት አጣጥለውታል፡፡

ከዚህም ባሻገር ባለሥልጣኑ ባወጣው አስገዳጅ አሠራር ሳቢያ አሮጌ መኪኖቻቸውን በ2002 ሞዴልና ከዚያ በላይ ባሉ መኪኖች እንዲተኩ በመባሉም አብዛኞቹ የሊፋን 520፣ 530 ሞዴሎችን፣ የቶዮታ ኤክዚኪዩቲቭ መኪኖችን በመግዛት እንዳሠማሩ የሚናገሩት የጥምረቱ ኃላፊዎች፣ እነሱም እደሌሎቹ የቀረጥ ነፃ ተጠቃሚዎች ባነሰ ዋጋ መግዛት ሳይፈልጉ ቀርተው ሳይሆን፣ የትራንስፖርት ሚኒስቴር መመሪያ የሥራ ክልልና መደባቸውን ለይቶ በማስቀመጡ፣ በዚያ ዕድል በሕጉ መሠረት ስለማይፈቀድላቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ይልቁንም በማኅበር ከቀረጥ ነፃ ተጠቃሚ መሆን እንደማይቻል መንግሥት ግልጽ ባመደረገው መሠረት ከተጠቃሚነት ውጭ ለመሆን መገደዳቸውን የሚገልጹት የቦሌ ታክሲዎች፣ ሸጠው በወጡ የቀድሞ የቦሌ ታክሲዎች የሚደረገው እንቅስቃሴ ከሕግ ውጭ ነው ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

በመሆኑም የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን በመስከረም ወር ረቂቅ መመሪያ ሲያዘጋጅ፣ ቀድሞ ሥራ ላይ የነበረውን መመሪያ 8/2007 የሚቃረን በመሆኑ አስተያየት እንደማይሰጡበት በመግለጽ እንዳልተሳተፉ ገልጸዋል፡፡ ይህን ቢሉም አዲሱ መመሪያ ወደ ስምሪት ተለውጦ ሁሉንም በእኩል ማስተናገድ የሚል አካሄድ ይዞ በመምጣቱ መመሪያው እንዳይተገበርባቸው ወደ ፍርድ ቤት ማቅናታቸውን የጥምረቱ ኃላፊዎች ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡ ‹‹የዘርፍ ልዩነት መደበላለቅ የለበትም አልን እንጂ ሌሎች ታክሲዎች ደንበኞቻቸውን ኤርፖርት አድርሰው እንዳያወርዱም ሆነ እንዳይገቡ አልከለከልንም፤›› በማለት ተከራክረዋል፡፡

የአቫንዛ ታክሲዎች ቅሬታ

የቶዮታ ኩባንያ ሥሪት የሆኑትን አቫንዛ መኪኖች ከቀረጥ ነፃ በማስገበት የሚንቀሳቀሱ ከ100 በላይ ባለንብረቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እነዚህ በሁለት ማኅበራት ማለትም ቦሌ ሜትር ታክሲ አክሲዮን ማኅበርና አዲስ ሜትር ታክሲ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በሚሉ አደረጃጀቶች የተዋቀሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ባለንብረቶች ቀድሞውንም በቦሌ ኤርፖርት ውስጥ ይሠሩ የነበሩ ናቸው፡፡ ይሁንና መንግሥት ከቀረጥ ነፃ መኪኖችን እንዲያስገቡ በፈቀደው መሠረት አዳዲስ መኪኖችን ለመግዛት የነበሯቸውብ አሮጌ መኪኖች እንደሸጡ ይገልጻሉ፡፡ የአዲስ ሜትር ታክሲ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮናስ ሙላትም ሆኑ ምክትላቸው አቶ ፍቃዱ መስፍን ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ከመነሻውም ከቀረጥ ነፃ ዕድሉን በመጠቀም አቫንዛ ሞዴል ሰባት ሰው የሚጭኑ ታክሲዎችን የገዙት የኤርፖርት አገልግሎትን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡

በመሆኑም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ድረስ የቀረጥ ነፃ ዕድል ለቦቴ ታክሲዎች እንዲመቻች ጥያቄ ሲቀርብ መቆየቱን አቶ ዮናስና አቶ ፍቃዱ ይናራሉ፡፡ በ2007 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተጻፈ ደብዳቤም ‹‹ቁጥር አንድ ቦሌ ኢንተርናሽናል፣ ቦሌ አለምአቀፍ ኢንተርናሽናል፣ መቅደላ፣ ስኬት እንዲሁም ህዳሴ የተባሉ ማኅበራት በስም ተጠቅሰው የቀረጥ ነፃ ዕድል ሊሰጣቸው እንደሚገባ መጠየቃቸውን አመሳክረዋል፡፡ 

ላለፉት አራት ዓመታት ከቀረጥ ነፃ ዕድል እንዲፈቀድ በቦሌ ኤርፖርት የጥምር ኮሚቴው ሰብሳቢ በነበሩበት ወቅት ጥያቄ ሲቀርብ መቆየቱን የሚገልጹት አቶ ዮናስ፣ ጥያቄው ተፈቅዶ መኪኖቹ ከገቡ በኋላ ግን በከተማው ተዘዋውራችሁ ሥሩ መባላቸው ከአቫንዛ መኪኖች ጋር የማይሄድ እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹ለቱሪስት አገልግሎት እንጂ ለሕዝብ አገልግሎት አስበን አልነበረም ጥያቄ ያቀረብነው፡፡ ለዚያ ቢሆንማ ኑሮ ተደራጅተን ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ አውቶቡሶችን እንገዛ ነበር፤›› ያሉት አቶ ዮናስ፣ የቱሪስት አገልግሎት ለመስጠት ስላልተፈወደላቸው ግን አቫንዛ መኪኖችን የገዙ አባላት ‹‹ባልለመዱት የሥራ መስክ›› በከተማው እየዞሩ አገልግሎት እንዲሰጡ መገደዳቸውን ኮንነዋል፡፡ በዚህም ሳያበቃ የባንክ ብድር ዕዳ መክፈል እየተሳናቸው እንደሚገኙም አክለዋል፡፡

በዚህም ሳያበቁ በቅርቡ የፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጀምሮ በተዋረድ እስከ አዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ይመለከታቸዋል ላላቸው ተቋማት የሜትር ታክሲዎች በቦሌ ኤርፖርት ውስጥ ገብተው እንዲሠሩ ትብብር እንዲያደርጉላቸው፣ በሜትር ታክሲዎቹ ጠያቂነት ደብዳቤ ጽፏል፡፡ ሆኖም ይህ የትብብር ደብዳቤ ምላሽ ማግኘት እንዳልቻለ አቶ ዮናስ ገልጸው፣ አስፈጻሚው አካል ማን እንደሆነ ግራ እያጋባቸው እንደመጣ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ በአክሲዮን ማኅበርና በኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩንባንያ ለመደራጀት የተገደዱትና መኪኖቻቸውን ለመሸጥ የተገደዱት አባላት በማኅበር ከቀረጥ ነፃ ማስገባት አትችሉም የሚል መመሪያ ከመንግሥት ስለተላለፈባቸው መሆኑን ያስታወሱት አቶ ዮናስ ይህንን በመከተል ከቦሌ በመውጣት የዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን የበቁት ተመልሰው መግባት እንደሚችሉ ቃል ስለተገባላቸው መሆኑንም አስረግጠው ይናገራሉ፡፡ ሆኖም የመንግሥት ቃል ከታች ሲወርድ ሊተገበር ባለመቻሉ መቸገራቸውን አስታውቀዋል፡፡

አቶ ዮናስ ይህን ይበሉ እንጂ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በሕጉ መሠረት የቱሪስት አገልግሎት እንዲሰጡ ፈቃድ የተሰጣቸው፣ የቦሌዎቹ ቢጫዎቹ ታክሲዎች በመሆናቸው ከእነዚህ ውጭ ላሉት የቱሪስት አገልግሎት እንዲሰጡ የሚፈቅድ የብቃት ማረጋገጫ ከመስጠት እንደሚቆጠብ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

በባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪስት አገልግሎት ፈቃድ የሚሰጠውን ክፍል የሚመሩት አቶ መሳይ ደምሴ ለሪፖርተር እንዳብራሩት ከሆኑ በመመሪያ ቁጥር 8/2007ም ሆነ በአዲሱ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን መመሪያ 1/2009 መሠረት የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ሆነው በትርጉም የተሰጠቀሱት ቢጫዎቹ የቦሌ ታክሲዎች በመሆናቸው ከዚህ ውጭ ላሉት የብቃት ማረጋገጫ እንደማይሰጥ ግልጽ አድርገዋል፡፡

‹‹መመሪያው እነሱን [ሜትር ታክሲዎችን] አያካትትም፡፡ ሁሉም ታክሲዎችም ቦሌ ኤርፖርት ገብተው መሥራት አይችሉም፡፡ በከተማው እየዞራችሁ አገልግሎት ስጡ ስለተባሉ እኛ ፈቃድ አንሰጥም፤›› ብልዋል፡፡ አክለውም ‹‹ችግሩ እኛ ሳይሆን ባለሥልጣኑ ጋ ነው፤›› የሚሉት አቶ መሳይ፣ በቱሪስት ንግድ ሥራ ፈቃድ ለማውጣት ፍላጎት ላላቸው ሁሉ የብቃት ማረጋገጫ ቢሮው እንደሚሰጥ አስታውሰው፣ ሆኖም ፈቃድ የሚሰጣቸው ሁሉ በመመሪያው መሠረት በቦሌ ኤርፖርትና በሆቴሎች አካባቢ በመቆም አገልግሎት መስጠት እንጂ እንደሌሎች ታክሲዎች በከተማው እየተዘዋወሩ መሥራቱ እንደማይፈቀድላቸው አሳስበዋል፡፡

የቦሌዎቹም ሆኑ የአቫንዛ ታክሲ ባልንብረቶች በአንድ ነገር ይስማማሉ፡፡ ኤርፖርት ውስጥ መሥራት የሚገባቸው ከድኅንነት አኳያ የሚጠበቅባቸውን የሚያሟሉ፣ ብቃትና ፈቃድ ያላቸው ታክሲዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም እንደ አቶ ዮናስም ሆነ አቶ ፍቃዱ አስተያየት ሊፋን 530 ሞዴል የሆኑት ሜትር ታክሲዎች ቦሌ ኤርፖርት ገብተው መሥራት አይገባቸውም ይላሉ፡፡ ይኸውም ከዚህ ቀደም ነጭ በሰማያዊ ቀለም የሚቀቡና በተለምዶ ላዳ ታክሲ የሚባሉትን በመተካት የመጡት ሜትር ታክሲዎች ዱሮውንም የሥራ ክልላቸው በከተማው ተዘዋውረው መሥራት በመሆኑ ኤርፖርት ውስጥ የሚሠሩበት ሥምሪት ሊፈቅዳላቸው አይገባም ይላሉ፡፡

የዘ ሉሲ ሜትር ታክሲዎች ማኅበር ኃላፊ አቶ አንተነህ ትሪሎ ይህንን ይቃወማሉ፡፡ ሁሉም በሚገባው ልክ እኩል በመሥራት እኩል ተጠቃሚ መሆን እንዳለበት የሚገልጹት አቶ አንተነህ፣ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣንን አቋም በመደገፍ ሁላችንም በእኩል እንድንሠራ የሚያደርግ አሠራር ለመከተል መነሳቱ ተገቢ ነው ይላሉ፡፡ ይሁንና የካቲት 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ተግባራዊ ሊደረግ የነበረውን የኤርፖርት ስምሪትም ሆነ የኤርፖርት ታክሲዎችም ወደ ከተማው እየዞሩ ይሥሩ የሚለውን የባለሥልኑን አቋም በመቃወም ወደ ፍርድ ቤት ያቀኑት ቢጫዎቹ የቦሌ ታክሲዎች፣ ሥምሪቱን ማሳገዳቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ ሳቢያም ለተፈጠረው ችግር የዘ ሉሲ ታክሲዎች ማኅበርን ይቅርታ መጠየቁን እንደገለጹ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በወጣው የሥምሪት ዕግድ ሳቢያ ለደረሰባቸው ኪሳራም ካሳ እንደሚጠይቁ መገልጻቸውን ሪፖርተር ዘግቦ ነበር፡፡

በአራት ወገን የተከፋፈውን አለመግባባት በማስመልከት በተለይም በ2007 በወጣውና በዚህ ዓመት በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን በወጣው መመሪያ ላይ የባለሥልጣኑን አስተያየት ለማካተት ተሞክሮ ነበር፡፡ ከተደጋጋሚ ጥረት በኋላ ከባለሥልጣኑ ሥምሪት ክፍል ለመረዳት የተቻለው ጉዳዩ በፍርድ ቤት የተያዘ በመሆኑ ምክንያት ምላሽና አስተያየት ለመስጠት እንደሚያስቸግር ነው፡፡ በመሆኑም ጉዳዩ እልባት እስኪሰጠው ድረስ ባለሥልጣኑ አስተያየት ለመስጠት እንደሚቸግረው አስታውቋል፡፡

በአዲሱ የባለሥጣኑ መመሪያ መሠረት የብቃት ማረጋገጫ ሰጪነት ሚናው የተቀነሰበት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ቅሬታውን አስታውቆ እኛን ከሥርዓቱ ውጭ ማድረግ ተገቢ አልነበረም ሲል በአቶ መሳይ በኩል ገልጿል፡፡ ይህ ተገቢ አይደለም ያሉት አቶ መሳይ ዘርፉን የተመለከተ ጥናት በቢሮው እየተካሄደ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ጥናት አሁን ለተነሱት አለመግባባቶች መፍትሄ እንደሚያመላክት ተስፋ አላቸው፡፡

በአራቱም አቅጣጫ የሚነሱት ቅሬታዎች ማጠንጠኛቸው ግን የመንግሥት አሠራር ላይ ይሽከረከራሉ፡፡ በፌደራልና በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን መካከል ስላለው የአሠራር ክፍተትና አለመናበብ ትልቅ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ ከላይ ያለው አካል ያወጣውን መመሪያ የታች ተጠሪው መሥሪያ ቤት በምን መልኩ እንደሚተገብረውና የራሱን አካሄድ እንዴት እንደሚያራምድ ያሳየ አለመግባባት ተፈጥሯል፡፡ ወደላይም ወደ ጎንም በማይነጋገሩ መሥሪያ ቤቶች አማካይነት በተፈጠረው አመግባባት በርካቶች ባለንብረቶች ስጋት ውስጥ እንዲወድቁና፣ በመንግሥት አሠራር ላይ እምነት እንዲያጡ እያደረጋቸው እንደሚገኝ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የታክሲ ባለንብረቶች ምሳሌ ዋቢ ናቸው፡፡

ከዚህ ባሻገር ግን በከተማው ከሚታየው ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር ይልቅ በቦሌ ኤርፖርት ውስጥ ለመሥራት የሚታየው ግብግብ ሌላም ለጥያቄ የሚጋብዝ ትልቅ ጉዳይ ሆኖ ይገኛል፡፡ የፌደራሉም ሆነ ውክልና የሰጠው የከተማው ትራንስፖርት ባለሥልጣን ለአብነት ያህል በየካቲት ወር መጀመሪያ አስገዳጅ እንደሆነ መግለጫ ሰጥተው በሜትር ታክሲዎች ላይ የጣሉትን የአገልግሎት ታሪፍ በአግባቡ መተግበር አልቻሉም፡፡ በቀረበባቸው ተደጋጋሚ አቤቱታ ሳቢያም ማሻሻያ ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ነገር ግን አንዱን ችግር በቅጡ ከመፍታት ይልቅ ሌላውንም እየደረራረቡ እንደሚገኙ ስሞታ እየቀረበባቸው ይገኛሉ፡፡  

 

Standard (Image)

የአማራ ንግድ ምክር ቤት እንደ አዲስ ተመሠረተ

$
0
0
  • የኢትዮጵያ የዘርፍ ምክር ቤት ምርጫ ቀን ተቆርጦለታል

ከስምንት ወራት በላይ ሲያወዛግብ ከመቆየቱም ባሻገር ለአገር አቀፉ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ መዘግየት ምክንያት እንደሆነ ሲጠቀስ የቆየው የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፈርሶ እንደ አዲስ ተመሠረተ፡፡ ምክር ቤቱን የሚመሩ አዲስ ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንትና የቦርድ አባላት ተመርጠዋል፡፡

የንግድ ምክር ቤቱን የቀድሞ አመራሮች ታግደገው፣ የዕውቅና ሠርተፊኬቱም ተሰርዞ መቆየቱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በመሆኑም እንደ አዲስ ምክር ቤቱን ለመመሥረት በተጠራው መሥራች ጉባዔ ወቅት በተደረገ የቦርድ አባላት ምርጫ፣ የጎንደር ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ መላኩ አዘዘው (ኢንጂነር)፣ የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅራት ምክር ቤትን በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ ተመርጠዋል፡፡ አቶ መላኩ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት 118 ድምፅ በማግኘት እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ዓርብ፣ ሚያዝያ 20 ቀን 2008 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው በዚሁ መሥራች ጉባዔ ወቅት በምክትል ፕሬዚዳንትነት እንዲያገለግሉ በአብላጫ ድምፅ የተመረጡት ከደሴ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተወከሉት አቶ እንግዳወርቅ ኪዳኔ ናቸው፡፡

ንግድ ምክር ቤቱን በቦርድ አባልነት እንዲያገለግሉ በጉባዔተኛው የተመረጡት አዳዲሶቹ የቦርድ አባላት ወ/ሮ ተምኔት ሰለሞን (ከደቡብ ጎንደር)፣ አቶ ሰለሞን ተስፋሁን (ከሰሜን ጎንደር)፣ አቶ አማረ ገብረ ዮሐንስ (ከሰሜን ሸዋ)፣ ወ/ሮ አስረበብ አሰፋ (ከደቡብ ወሎ)፣ አቶ አበበ ደርሰህ (ከጎንደር ከተማ)፤ አቶ ኢስማኤል አሊ (ከደሴ ከተማ)፣ አቶ አዋይ አበራ (ከሰሜን ወሎ)፣ አቶ አማረ ሰለሞን (ከዘርፍ ምክር ቤት) አቶ ያረጋል አይቼው (ከምሥራቅ ጎጃም) እንደተወከሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በዚህ ምርጫ ሒደት ፕሬዚዳንቱንና ምክትል ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ 12 አባላትን ካካተው ቦርድ ውስጥ፣ የባህር ዳር ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በቦርዱ ውስጥ የሚወክለውን ወኪል አባል እንዳላስመረጠ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በመሥራች ጉባዔው ወቅት ከቀድሞው የንግድ ምክር ቤቱ አመራሮች መካከል አቶ ጌታቸው አየነውና (የቀድሞ ፕሬዚዳንት) እና ሌላ የቦርድ አባል የድምፅ ተሳትፎ ሳይኖራቸው በአስረጅነት እንደቀረቡም ታውቋል፡፡

ለወራት ከዘለቀው ውዝግብ እንዲሁም በሚያዝያ 20 ቀን እስከተካሄው ጠቅላላ ጉባዔ ድረስ የነበሩት ሒደቶች ምን ይመስሉ እንደነበር የሚያመላክት ሪፖርት በአማራ ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተዋቸው ወርቁ በኩል ቀርቧል፡፡ በተሰናባቹ ቦርድ ላይ የነበሩትን ቅሬታዎች በተመለከተ፣ አቤቱታውን ማን እንዳቀረበው፣ አቤቱታ አቅራቢዎች ከክልሉ ባሻገር ለፌዴራል መንግሥት ጭምር አቤት ማለታቸውን አቶ ተዋቸው በሪፖርታቸው አቅርበዋል፡፡ ለሕግ መከበር የሚታገል አካል መኖሩ በመልካም ጎኑ በተጠቀሰው ሪፖርት ተመልክቶ ጉዳዩን እንዲፈታና እልባት እንዲሰጥበት የተመረጠው ቦርድ፣ ከሳሾችና ከባህር ዳር ነጋዴዎች ጋር ውይይት ተጠርቶ ከሳሾቹ አለመገኘታቸው አግባብ እንዳልነበር ተጠቅሷል፡፡ በምክር ቤቱ ውስጥ ስላለው ችግር የሕግ ባለሙያ ምክር እንደሚጠየቅበት የቢሮው ምክትል ኃላፊ ባቀረቡት ሪፖርት አመልክተዋል፡፡ የቀድሞው ቦርድ ላይ ከቀረቡት አምስት አቤቱታዎች በአንደኛው ብቻ የሕግ ክፍተት መገኘቱን፣ ይህንንም የቢሮው የሕግ አማካሪና የክልሉ ፕሬዚዳንት የሕግ አማካሪ በማረጋገጣቸው መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. የተካሄደው ጉባዔ የሕግ ጥሰት እንዳለበት መረጋገጡን ሪፖርት አቅራቢው ገልጸዋል፡፡ በዚህ መሠረት መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. የተካሄደው ምርጫ ተሽሮ ዳግመኛ ምርጫ እንዲደረግ ቢሮው መወሰኑንም አስረድተዋል፡፡

ይህንን ውሳኔ ተከትሎ ጥሪውን ማስተላለፍ ያለበት ማን ነው ተብሎ ቢሮው በቀረበበት ጥያቄ የድሮው ቦርድ እንደገና ተሰብስቦ መጥራት ይችላል ተብሎ በደብዳቤ ተገልጾላቸው እንደበር በዕለቱ ከቀረበው ሪፖርት መገንዘብ ተችሏል፡፡

ቢሮው በዚህ መንገድ ያደረገው ጣልቃገብነት የክልሉን ንግድ ምክር ቤት ያግዛል ብሎ ቢያምንም፣ የወቅቱ የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንቱ አቶ ጌታቸው፣ የቦርድ አባላቱን በመጥራት ፈንታ አዲሱን ቦርድ ጠርተው በማወያየት፣ ለመጋቢት 20 ቀን 2009 የጠቅላላ ጉባዔ ጥሪ ማስተላለፋቸው ስህተት ነበር ተብሏል፡፡

የጠቅላላ ጉባዔው ጥሪ ደብዳቤ ከተላለፈ በኋላ የደብዳቤው ይዘት ችግር እንዳለበት ከአባል ምክር ቤቶች በስልክ እንደደርሳቸው፣ ለቢሮው የተጻፈለት ደብዳቤና ለአባል ምክር ቤቶች የተጻፈላቸው ደብዳቤ የይዘት ልዩነት እንዳለበት መረጋገጡንም በሪፖርታቸው አካትተዋል፡፡ ‹‹አንድን ግለሰብ ለማግለል በማሰብ የተጻፈ ነው፤›› ያሉት የቢሮው ኃላፊ፣ ተሰናባቹ ፕሬዘዳንት የቀድሞውን ቦርድ ሳያሰባስቡ በአዲሱ ቦርድ በኩል ጥሪው እንደተላለፈ በማረጋገጡ ቢሮው ወደ ዕርምጃ ሊገባ መቻሉን ለጠቅላላ ጉባዔው አስታውቋል፡፡

ሪፖርቱ ከቀረበ በኋላ በዕለቱ አነጋጋሪ ከነበሩ ጉዳዮች አንዱ ለምን መሥራች ጉባዔ ይባላል የሚለው ነጥብ እንደነበር ታውቋል፡፡ በመሆኑም መሥራች ጉባዔ ለምን እንደተባለ በዕለቱ የተገኙት የቢሮ ኃላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተውበታል፡፡

የክልሉ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና የገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጌታቸው፣ መሥራች ጉባዔ ከሚባል ይልቅ አስቸኳይ ጉባዔ ተብሎ እንዲጠራና ምርጫው በዚሁ አግባብ እንዲካሄድ የቢሮው ፍላጎት እንደሆነ ቢጠቅሱም፣ የቀድሞው የንግድ ምክር ቤቱ አመራር በቢሮው የተላለፈውን ውሳኔ ያለመቀበልና ያለማክበር ብሎም በተዛባ ደብዳቤ ጥሪ በማስተላለፉ ምክንያት፣ ቢሮው ሳይፈልግ መሥራች ጉባዔ ተብሎ እንዲጠራ አስገድቶታል ብለዋል፡፡ ‹‹በእኛ ምክንያት የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ምርጫ በመዘግየቱ አስቸኳይ መፍትሔ መስጠት ስለነበረብን የተወሰደ ዕርምጃ ነው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡  

ይህ ሁሉ በውይይት ወቅት ከተደመጠ በኋላ በቢሮው የቀረበው ሪፖርት፣ በማጠቃለያው በ14 ተቃውሞ በሦስት ድምፀ ተአቅቦ እንደፀደቀ የሪፖርተር መረጃ ያስረዳል፡፡

የምርጫውን ሒደት ለመከታተል በቦታው የተገኙት የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰሎሞን አፈወርቅ ማብራሪያ እንደሰጡበት ለማወቅ ተችሏል፡፡  

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔና የቦርድ አባላት ምርጫ መጓተት ምክንያት ሆኖ የቆየውና በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዕገዳ የተጣለበት የኢትዮጵያ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አዲስ ምርጫ እንዲያካሂድ መወሰኑ ታውቋል፡፡

እንደ አማራ ንግድ ምክር ቤት ተሰናባች አመራሮች ሁሉ የኢትዮጵያ የዘርፍ ምክር ቤት አመራሮችም ከሕግ ውጭ ምርጫ አካሂደዋል ተብለው የሚመሩት ቦርድ ዕግድ እንደወጣበት ይታወሳል፡፡ ያለአግባብ ከሁለት ምርጫ ዘመን በላይ በአመራርነት ቦታው ላይ ቆይተዋል ተብለው በአመራሮቹ ላይ በቀረበባቸው ክስ መሠረት፣ በሐምሌ ወር 2008 ዓ.ም. የተካሄው ምርጫ ተሽሮ በምትኩ አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ በተወሰነው መሠረት ምርጫው ግንቦት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ሊካሄድ ቀጠሮ እንደተያዘለት ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

Standard (Image)

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሩዋንዳ ጉብኝታቸው ከቱሪዝም እስከ ወንጀለኛ ልውውጥ የሚካትቱ 11 ስምምነቶችን ፈርመው ተመለሱ

$
0
0
  • የዓለም ባንክ የንግድ አሠራር መለኪዎችን ለማሻሻል ሩዋንዳ ሞዴል ተደርጋለች

ካቻምና በሩዋንዳ ኪጋሊ ከተማ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊን ለመዘከር የሩዋንዳ መንግሥት በመሠረተው ፋውንዴሽን ሲምፖዚየም ላይ ለመታደም ቢሆንም ከሰሞኑ ግን በ11 መስኮች ላይ የተደረጉ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ለመፈራረም ነበር ወደ ኪጋሊ ያቀኑት፡፡

ከሩዋንዳ መንግሥት የመረጃ አውታሮች ለሪፖርተር በተላከው ኮሚዩኒኬ መሠረት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ጋር ባደረጓቸው የሁለትዮሽ ስምምነቶችና ከፈረሟቸው የመግባቢያ ሰነዶች መካከል በሁለቱ አገሮች መካከል በባህልና በቱሪዝም መስክ የተደረጉትን ጨምሮ ወንጀለኞችን አሳልፎ ለመስጠት፣ የማረሚያ ቤቶች አያያዝ አስተዳደር፣ በሁለቱ መንግሥታት መካከል የሚደረጉ የሕግ ድጋፍ ልውውጦች፣ በመረጃና ተግባቦት መስክ እንዲሁም በመገናኛ ብዙኃን መስክ፣ በወጣቶችና በስፖርት እንዲሁም በጤና ዙሪያ የተደረጉት የመግባቢያና የሁለትዮሽ ስምምነቶች ጠቃሽ ሆነዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር በሕፃናትና ሴቶች መስክ የሁለትዮሽ ትብብር በመመሥረት አብረው ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡

ከሚያዝያ 19 ቀን እስከ ሚያዝያ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. በዘለቀው የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የሩዋንዳ ጉብኝት ወቅት አንዱ ከሩዋንዳ መንግሥት ጋር አብሮ ለመሥራት መንግሥታቸው ፍላጎት እንዳለው የገለጹበት መስክ ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መስክ በተለይ በንግድ አሠራር ሒደት የሚታዩ እንቅፋቶችን በመቀነስ፣ የዓለም ባንክ በየዓመቱ በሚያወጣው ለንግድና ኢንቨስትመንት ቀልጣፋ አሠራርን በሚለካው ‹‹ኤዝ ኦፍ ዱዊንግ ቢዝነስ›› ሪፖርት ላይ ኢትዮጵያ የሪፎርም ፕሮግራም መተግር መጀመሯን አቶ ኃይለ ማርያም ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለጀመረችው የንግድ አሠራር ሪፎርም ሩዋንዳን ተምሳሌት እንደምታደርግም አስውቀዋል፡፡ በአፍሪካ እያስመዘገበች ከምትገኘው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ባሻገር፣ ለንግድና ለኢንቨስትመንት ባላት ምቹነት ሩዋንዳ በዓለም ባንክ መለኪያ ጥሩ ደረጃ ይዛ ትገኛለች፡፡ የሩዋንዳን ፈለግ በመከተል ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መስክ መስህ እንዲኖራት ለማድረግ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሪፎርም ሥራዎችን እያካሄደ እንደሚገኝ ለሩዋንዳው ፕሬዚዳንት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ሩዋንዳን ውጤታማ ካደረጉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ለመማር መንግሥታቸው ፍላጎት እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡

ባለፈው ዓመት መካተቻ ወቅት የተጀመረው የሪፎርም ፕሮግራም፣ የዓለም ባንክን ዓመታዊ ሪፖርት መነሻ በማድረግ፣ በኢንቨስትመንት ኮሚሽን አማካይነት መተግበር የጀመረውም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅርብ ክትትል እንደሆነ ይታወቃል፡፡

የዓለም ባንክ በዋና ዋና መመዘኛ መሥፈርትነት የሚጠቅሳቸው የሚከተሉት አሥር መለኪያዎች ናቸው፡፡ የንግድ ሥራ ለመጀመር የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች፣ የግንባታ ፈቃድ በቀላሉ ለማግኘት መቻል፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት፣ ንብረት ማስመዝገብ፣ ብድር በቀላሉ ማግኘት መቻል፣ ለአነስተኛ ኢንቨስተሮች ከለላ መስጠት፣ ታክስ መክፈል፣ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ ማካሄድ፣ የውል ስምምነቶችን መተግበር እንዲሁም የኪሳራ እወጃን ያለ ውጣ ውረድ መፍታት የሚሉት ዋና ዋና መለኪያዎች ኢትዮጵያን ጨምሮ 190 ያህል አገሮች በማካተት ደረጃ ይወጣላቸዋል፡፡

ሪፖርቱ ዓለም አቀፍ ተደራሽነትና ተቀባይነትን ያተረፈ፣ በርካታ የውጭ ኩባንያዎችም ለእንቅስቃሴያቸው መመዘኛ ከሚያደርጓቸው ነጥቦች መካከል አንዱ በማድረግ የሚጠቅሱት ይኼንኑ የዓለም ባንክ ሪፖርት ነው፡፡ የዚህ ዓመቱን የአገሮችን ደረጃ ይፋ ያደረገው የባንኩ ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ በ159ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል፡፡ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ አገሮችም 31ኛዋ ሆናለች ያለው የዓለም ባንክ፣ አገሪቱ ከወትሮው ይልቅ 12 ነጥቦችን ወደ ታች በማሽቆልቆል ይብሱን ወደታች እንደወረደች አስፍሯል፡፡ በመሆኑም አገሪቱ በኢንቨስትመንት መስህብነት ከሌሎች አገሮች ጋር ለመወዳደር ካሻት ከታች እስከ ላይ መሠረታዊ የለውጥ ሪፎርሞችን መተግበር እንደሚጠበቅባት አሳስቧል፡፡ ከሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት ይልቅ ለየት ባለ አደረጃጀትና የአመራር ኃይል መንቀሳቀስ የጀመረው ኮሚሽኑ፣ የተመቻቸ የንግድና የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታ ለመፍጠር የሚረዱትን የዓለም ባንክ መመዘኛዎችን በጥሩ ውጤት መተግበር የሚያስችሉ ማሻሻያዎችን ማድረግ ከጀመረ አንድ ዓመት አስቆጥሯል፡፡

በዚህ ምክንያት በኢትዮጵያ ለውጥ እንዲመጣ መንቀሳቀስ የጀመረው ኮሚሽኑ በአራት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ከዓለም 50 አገሮች ምርጧ አገር እንድትሆን የሚያስችል ‹‹ራዕይ 2020›› የተባለ እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመሩን አስታውቋል፡፡ ይኼ እንዲሳካም በየአመቱ የ40 ከመቶ ለውጥ ማስመዝገብን መሠረት ያደረገ ውጤት እንዲመዘገብና የአገሪቱ አጠቃላይ ውጤትም አሁን ካለበት 159ኛ ወደ 34ኛ እንዲመጣ ማቀዱን ይፋ ካደረገ ሰነባብቷል፡፡

እንዲህ ያሉ ትልልቅ ለውጦችን ለማስመዝገብ ምሳሌ እንደምትሆን የተጠቀሰችው ሩዋንዳ ከኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን፣ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ይልቅ የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ላይ ትገኛለች፡፡ እንዲህ ያሉ ልውውጦችን በሁለቱ አገሮች መካከል ለማካሄድ በመንግሥታቱ መካከል የተቋቋመ ቋሚ የጋራ ኮሚሽን ተሰይሟል፡፡ 

Standard (Image)

ሐበሻ ቢራ ካፒታሉን ወደ 2.2 ቢሊዮን ብር እንደሚያሳድግ አስታወቀ

$
0
0
  • ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ የተጣራ ትርፍ አስመዘገበ

የአገሪቱን የቢራ ገበያ ከተቀላቀለ አንድ ዓመት ከዘጠኝ ወራት ያስቆጠረው ሐበሻ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ካፒታሉን ለማሳደግ በተጠራው ስብሰባ ወቅት፣ ባለአክሲዮኖች የድርጅቱ ካፒታል ወደ 2.2 ቢሊዮን ብር ከፍ እንዲል መወሰናቸው ተገለጸ፡፡ የመጀመሪያውን የሥራ ዘመኑን በኪሳራ ያሳለፈው ሐበሻ በሁለተኛው ዓመት የተጣራ 32 ሚሊዮን ብር ማትረፉን ይፋ አድርጓል፡፡

የአክሲዮን ኩባንያው እሑድ፣ ሚያዝያ 22 ቀን 2009 ዓ.ም. 5ኛ እና 6ኛውን ጠቅላላ ጉባዔ እንዲሁም 11ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በአንድ አጣምሮ ባካሄደበት ወቅት፣ በተለይ በ11ኛው ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔ አጀንዳው የኩባንያውን ካፒታል ለማሳደግ ሐሳብ አቅርቦ በዚያው መሠረት በአሁኑ ወቅት ያስመዘገበው የ1.1 ቢሊዮን ብር ካፒታል ወደ 2.2 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ አስወስኗል፡፡ ዓምና ያስመዘገበው 32.7 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍም ለካፒታል ማሳደጊያ እንዲውል ተወስኗል፡፡ 

ከካፒታል ማሳደጉ ጎን ለጎን አዲስ የአክሲዮን ሽያጭ እንዲካሄድ የተወሰነ ሲሆን፣ የኩባንያው የዳይሬክተሮች ቦርድም የአክሲዮን ሽያጭ የማካሄድ፣ ሽያጩን የማስመዝገብና አዳዲስ ባለአክሲዮኖችን የመቀበል ሥልጣን የሚሰጥ ውሳኔም ተላልፏል፡፡

ኩባንያው የአክሲዮን መጠኑን ለማሳደግ የወሰነው የምርት አቅሙን ለመጨመር የሚያስችል የማስፋፊያ ግንባታ ለማካሄድ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ ሐበሻ ቢራ ሥራ የጀመረው 300 ሺሕ ሔክቶ ሊትር የማምረት አቅም ይዞ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ይህንን አቅሙን ወደ አራት መቶ ሺሕ ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡ ቀስ በቀስ 700 ሺሕ ሔክቶ ሌትር ማምረት የሚችልበት አቅም ላይ በመድረስ በአጭር ጊዜ ውስጥ የገበያ ድርሻውን ከፍ ለማድረግ እንደቻለ አሳይቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከሚገኝበት የ700 ሺሕ ሔክቶ ሊትር የምርት አቅም በመጪው ዓመት ደግሞ ወደ 1.5 ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር ለማድረስ የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩን የሚገልጸው የኩባንያው ሪፖርት፣ ይህንን ለማሳካት ካፒታል ማሳደጉ አንዱ ዕርምጃ በመሆኑ ይህንኑ ለማሳደግ የሚያስችል ስምምነት በባለአክሲዮኖች ዘንድ ተደርሷል፡፡

የሁለተኛውን የማስፋፊያ ምዕራፍ በመተግበር፣ በዚህ ዓመት እስከ ሰኔ ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ማለትም እ.ኤ.አ. በ2017 ሁለተኛው ሩብ ዓመት፣ ከያዘው የ950 ሚሊዮን ብር የኢንቨስትመንት ፋይናንስ በተጨማሪ የባንክ ብድር ለማግኘት ስለመታቀዱ የኩባንያው ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

የሒሳብ ሪፖርቱና ዓመታዊ የሥራ ክንውኑ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር መሠረት ተሠርቶ የቀረበ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. የ2015 እና የ2016 የሥራ ክንውን ሪፖርቶች በተናጠል በቀረቡበት ከእሑዱ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ መገንዘብ እንደተቻለው፣ በ2015 ኩባንያው የ20.3 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አስመዝግቦ ነበር፡፡ በተናጠል በቀረበው የ2015 ሪፖርቱ ላይ እንደተጠቀሰውም ሥራ በጀመረበት በዚያው ዓመት (ካቻምና) የ73 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ሊያስመዘግብ እንደሚችል ግምቱን አስቀምጦ እንደነበረ አመልክቷል፡፡ ሆኖም የተገመተውን ኪሳራ ለመቀነስ የሚያስችል ሥራ በመሥራቱና ወደ አትራፊነት እንዲሸጋገር በተወሰዱ ዕርምጃዎች ምክንያት ዓምና፣ በ2016 32.7 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ሊያስዘግብ ችሏል፡፡

‹‹የሐበሻ ቢራ ምርትና ብራንድ በገበያው ዘንድ ያገኘው ከፍተኛ ተቀባይነት፣ እነሆ በድጋሚ ከታቀደው በላይ ሽያጭ በማስመዝገብና የትርፍ ህዳጋችንን በማሻሻል ወደ ተጨባጭ የፋይናንስ አፈጻጸምና ውጤት ለመተርጎም ተችሏል፤›› በማለት ኩባንያው ያገኘውን ውጤት ገልጾታል፡፡

የኩባንያው የ2016 የተጣራ የሽያጭ ገቢ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ እንዳስመዘገበ የሚያመላክተው የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት፣ የሽያጭ ወጪውም በአንፃሩ 546 ሚሊዮን ብር እንደነበር አመላክቷል፡፡ የሽያጭ ወጪው ከተጣራ የሽያጭ ገቢው አንፃር ያለው ድርሻ 53 በመቶ መሆኑን ያሳያል፡፡ በአፈጻጸሙም ካቻምና ከነበረው የ62.4 በመቶ የወጪ ድርሻ ጋር ሲነጻጸር በ15 በመቶ የተሻለ ነው ተብሏል፡፡

ከሽያጭ፣ ከምርት ሥርጭትና ከግብይት ወጪዎች ጋር በተያያዘ በበጀት ዓመቱ ከተጣራ ሽያጭ ላይ 10.5 በመቶውን፣ ቢራው ወደ ገበያው እንዲሰርጽ ለማድረግ በሚያስችሉ የብራንድ ማስተዋወቂያ ሥራዎች ላይ ወጪ አድርጓል፡፡ ለሽያጭና ለምርት ሥርጭትም 166 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ የኩባንያው የጠቅላላ አገልግሎትና አስተዳደር ወጪዎች 128 ሚሊዮን ብር ማስመዝገባቸውን የሚገልጸው የፋይናንስ ሪፖርቱ፣ በ2016 ከወለድና ከታክስ በፊት የተገኘው ገቢ 85.4 ሚሊዮን ብር ትርፍ መመዝገቡን አስፍሯል፡፡ ከካቻምናው የ20.9 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አንፃር ሲታይ ኩባንያው በትርፋማነቱ ረገድ ከፍተኛ መሻሻል እንዳስመዘገበ አመላካች መሆኑም ተነግሯል፡፡

ሐበሻ ቢራ ለሚጠቅሳቸው መሻሻሎች ጉልህ አስተዋጽኦ ካበረከቱት መካከል የሽያጭና የምርት ሥርጭት ሰንሰለቶችን ውጤታማ ማድረግ መቻሉ አንዱ ሆኗል፡፡ የኩባንያው የተጣራ ቋሚ ንብረትም ከ933.3 ሚሊዮን ብር ወደ 1.35 ቢሊዮን ብር ማደጉን የሚያመላክተው የኩባያው ሪፖርት፣ ለዚህ ዕድገት ትልቁን አስተዋጽኦ ካበረከቱት ውስጥ የመጀመሪያው በምዕራፍ አንድ የማስፋፊያ ግንባታ ሥራዎች ላይ የታየው የተፋጠነ ዕድገት እንደሆነ አስታውቋል፡፡

ኩባንያው የማስፋፊያ ሥራዎችን ለማከናወን ከፍተኛ ባለአክሲዮን ከሆነው ከባቫሪያ ኦቨርሲስ ኩባንያ መበደሩንም ይፋ አድርጓል፡፡ በሪፖርቱ ውስጥ ‹‹ኩባንያችን በ2015 እና በ2016 ከባቫሪያ ኦቨርሲስ የቢራ አምራች ኩባንያ ጋር ባደረገው የብድር ስምምነት ሦስት ብድሮችን አግኝቷል፡፡ ሁለቱ ብድሮች እያንዳንዳቸው 2.5 ሚሊዮን ዶላር፣ ሦስተኛው ደግሞ 9.8 ሚሊዮን ዶላር) በድምሩ 14.80 ሚሊዮን ዶላር አስገኝተዋል፤›› በማለት ከኩባንያው የተገኘውን ጠቅላላ የብድር መጠን አስታውቋል፡፡ ሁሉም ብድሮች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይሁንታ ተሰጥቶባቸው እንደተገኙ ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡

የወደፊቱን የመጠጥ ኢንዱስትሪውን አቅጣጫና ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ የሚገመቱ ሥጋቶችም በሪፖርቱ ተካተዋል፡፡ ኢንዱስትሪው የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት የተጋረጡበት በመሆኑ፣ ለምርት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለማሟላት አስቸጋሪ ሆኖ መቆየቱ ተጠቅሶ ይኸው ችግር ሊቀጥል እንደሚችል ተገምቷል፡፡ የቢራ ገብስ ምርጥ ዘር በዓይነትና በጥራት እንደሚፈለገው መጠን አገር ውስጥ አለመኖሩ፣ ጥራት ላይ የተመሠረተ የቢራ ገብስ የግብይት ሥርዓት ለመፍጠር የሚከናወነው ሥራ ደካማ መሆኑ፣ የአገር ውስጥ ምርትን ለማሳደግ የማበረታቻ ስልቶችን የመንደፍና የመተግበር ጥረት አለመኖሩና ሌሎችም ችግሮች በኢትዮጵያ የቢራ ገብስ ንግድ ሥራ ውስጥ የሚታዩ ተጠቃሽ እክሎች ስለመሆናቸው አትቷል፡፡

የአገር ውስጥ ገበያው በየዓመቱ ከ15 እስከ 20 በመቶ እያደገ፣ የቢራ ፍጆታም በመጪዎቹ ሦስትና አራት ዓመታት ውስጥ ወደ 20 ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር እንደሚያድግ ተገልጿል፡፡ ከቢራ ፍላጎትና ፍጆታ ጎን ለጎን በርካታ የቢራ ፋብሪካዎች በሚያካሂዱት የማስፋፊያ ሥራዎች አማካይነት የምርት መጠንም በየጊዜው እያደገ መጥቷል፡፡ ከዓምና አሐዞች በመነሳት፣ የአገሪቱ ጠቅላላ የቢራ ፋብሪካዎች አጠቃላይ አቅርቦት ከ11 ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር በላይ እንደደረሰ ግምቶች መኖራቸውን ሪፖርቱ አስፍሯል፡፡

የቢራ ገብስ አቅርቦት ዕጥረት የቢራ ፋብሪካዎችን የሚገዳደራቸው ፈታኙ ችግር ሲሆን፣ በዚሁ ዘርፍ አዲስ አቅም መፍጠር፣ ያለውንም ማሳደግ ግድ እንደሚል የሚጠቅሰው ሐበሻ ቢራ፣ አዳዲስ አምራቾችና የምርት ዓይነቶች ወደ ገበያው መጉረፍ የሚችሉበት ዕድል በርካታ መሆኑንም ይገልጻል፡፡  

ኩባንያው የውጭ ገበያ በትኩረት ከተሠራበት ለኢንዱስትሪው ዕድገት የበለጠ ዕድል ይከፍታል የሚል እምነት አለው፡፡ በዚህ መስክ እስካሁን ዓይነ ግቡዕ እንቅስቃሴ ባይታይም ወደፊት፣ ብዙ ርብርብ የሚደረግበት ስለመሆኑ የሚያመላክቱ ሁነኛ ምልክቶች መታየት እንደጀመሩ ተጠቅሷል፡፡ ሐበሻ ቢራም ለውጭ ገበያ ትኩረት ከሚሰጥቸው ምክንያቶች ውስጥ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግርን ለማስተንፈስ የሚረዳና ለዘለቄታውም አጋዥ መላ እንደሆነ ይገልጻል፡፡  

ሐበሻ ቢራ በመጪው ዓመት ስለሚኖረው ክውንውን በሰጠው ማብራሪያ እንዳስታወቀው ከሆነ፣ ዓምና ካስመዘገበው ይልቅ በ54 በመቶ ብልጫ ያለው የሽያጭ መጠን ይጠብቃል፡፡ ከዚህ ባሻገር ዓምና ካስመዘገበው ትርፍ በ200 በመቶ ብልጫ የሚኖረው የትርፍ ዕድገት እንደሚያስዘግብም አስታውቋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2021 ከአገሪቱ ቀዳሚ የቢራ አምራች ኩባንያዎች መካከል አንዱ እንደሚሆን የሚገልጸው ሐበሻ ቢራ፣ ዓምና የነበረው የገበያ ድርሻ 13 በመቶ እንደነበርም አስታውቋል፡፡     

ከ8,800 በላይ ባለአክሲዮኖችን ያሰባሰበው ሐበሻ ቢራ፣ 70 በመቶ የአክሲዮን ድርሻው የባቫሪያ ኩባንያ ነው፡፡ በጠቅላላ ጉባዔው ወቅት በተደረገ ውይይትም የሐበሻ ቢራን አብላጫ ድርሻ ባቫሪያ መውሰዱ አከራክሮ ነበር፡፡ 70 በመቶው የባቫሪያ ድርሻ መሆኑ ከፍተኛ ድምፅ እንዲኖረው አስችሎታል፡፡ ወደፊት ሊካሄድ በታሰበው የአክሲዮን ሽያጭም ይኸው የኔዘርላንድስ ኩባንያ ከያዘው የበለጠ ድርሻ መቆናጠጥ የሚችልበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል በማለት ሥጋታቸውን የገለጹ ባለአክሲዮኖች ድምጻቸውን ቢያሰሙም የባቫሪያ ኃላፊዎች ግን ካላቸው የ70 በመቶ በላይ የአክሲዮን ድርሻቸውን እንደማያሳድጉ ቃል መግባታቸው ታውቋል፡፡

 

 

Standard (Image)

አዲስ ቻምበር የግብርና ንግድ ትርዒት 75 ኩባንያዎችን ያሳትፋል

$
0
0

 

የአዲስ አበባ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ በዓመት ሦስት ጊዜ በቋሚነት ከሚያዘጋጃቸው የንግድ ትርዒቶች አንዱ የሆነው ‹‹አዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ ልዩ የግብርና እና የምግብ ንግድ ትርዒት›› ከ75 በላይ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉበት ተገለጸ፡፡

በንግድ ምክር ቤቱ የንግድ ትርዒቶች ሥራ አስኪያጅ አቶ ጋሻው አባተ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከተሳታፊ ኩባንያዎች ውስጥ 35ቱ ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ፣ በግብርና ዘርፍ ኢንቨስትመንት ያላቸው፣ ምግብና የምግብ ነክ ሸቀጦች አምራቾች፣ የማምረቻ ዕቃዎች አቅራቢዎችና አገልግሎት ሰጪዎች ናቸው፡፡

ከግንቦት 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው የንግድ ትርዒት ወቅት፣ ከውጭ ከሚመጡ ተሳታፊ ኩባንያዎች ውስጥ የአልጄሪያ፣ የቻይና፣ የሱዳን፣ የግብፅ፣ የህንድ፣ የፓኪስታንና የጣልያን ኩባንያዎች እንደሚገኙበት ተጠቅሷል፡፡

እንዲህ ባለው የንግድ ትርዒት ላይ ለመጀመርያ ጊዜ ተሳታፊ ለመሆን የሚመጡት የአልጄሪያ ኩባንያዎች ሲሆኑ፣ አምስት ያህል ኩባንያዎች በ13 የንግድ ልዑካን ተወክለው እንደሚታደሙ ይጠበቃል፡፡

የአዲስ አበባ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ ዓለም አቀፉን የግብርና እና የምግብ ንግድ ትርዒት ሲያዘጋጅ የዘንድሮው ለአሥረኛ ጊዜ ሲሆን፣ እስካሁን ከተካሄደው የንግድ ትርዒቶች ሁሉ ብልጫ የውጭ ኩባንያዎች የተሳተፉበት የዘንድሮው ስለመሆኑም ለማወቅ ተችሏል፡፡

የግብርና እና የምግብ ነክ ምርቶችና አገልግሎቶችን ለማስተዋወቅ እንደሚረዳ በሚነገርለት በዚህ ዓውደ ርዕይ ለመሳተፍ ዓምና ለመሳተፍ የመጡት የውጭ ኩባንያዎች ብዛት 10 ብቻ ነበር፡፡ የአገር ውስጥ ተሳታፊዎችም ከ25 እንደማይበልጡ የምክር ቤቱ መረጃ ያስረዳል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ ከዚህ የንግድ ትርዒት ባሻገር በቋሚነት የሚያሰናዳቸው ዓመታዊ የንግድ ትርዒቶች፣ አዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት፣ የቱሪዝም፣ የአስጎብኝና የጉብኝት ዘርፍ ላይ ያተኮሩ የንግድ ትርዒቶች ናቸው፡፡

 

Standard (Image)

መንግሥት የአላና ፖታሽ የማዕድን ማውጫንና ንብረቶቹን ተረከበ

$
0
0

 

በፖታሽ ማዕድን ኢንቨስትመንት ዘርፍ ውስጥ ለመሰማራት አላና ፖታሽ ከተባለው ኩባንያ ሙሉ አክሲዮኖችን በመግዛት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረው የእሥራኤሉን አይሲኤል ኩባንያ፣ የፓታሽ ማምረቻ ይዞታውንና ንብረቱን መንግሥት ተረከበ፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ የእስራኤሉ ኩባንያ በአፋር ክልል ደንከል አካባቢ ለፖታሽ ማዕድን ማምረቻ የተከለው ንብረት፣ ከአላና ፓታሽ ተላልፎለት የነበረውን ይዞታና ሌሎችም ቁሳቁሶቹን መንግሥት ለመረከብ ሲያደርግ የነበረውን እንቅስቃሴ ያጠናቀቀው ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ነው፡፡

ርክክቡም አይሲኤል በኢትዮጵያ ሊያካሄድ የነበረውን ፖታሽ የማምረት ሥራ ማቋረጡን ካስታወቀ በኋላ የማምረቻ ቦታውን መንግሥት እንዲረከበው ባቀረበው ጥያቄ መሠረት እንደተፈጸመ ታውቋል፡፡

ኩባንያው በኢትየጵያ የነበረውን ሥራ በማቋረጡና ሠራተኞችንም በማሰናበቱ ለፓታሽ ማዕድን ማምረቻው ሥራ የተዘጋጁ ንብረቶች እንዳይበላሹና እንዳይባክኑ ለማድረግ በቦታው ተገኝተው በመንግሥት ወገን ንብረቱን የተረከቡበት ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን እንዲሁም ከማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የተወከሉ ባለሙያዎች መሆናቸውም ተገልጿል፡፡ ከንብረት ርክክቡ በኋላ ግን አይሲኤል የተሰጠው ፈቃድ ስለመሰረዙ የሚገልጽ ሠርተፍኬት ይሰጠኝ በማለት ጥያቄ ማቅረቡም ታውቋል፡፡ አይሲኤል ብዙ ተስፋ የተጣለትን የፓታሽ ማዕድን አምርቶ ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብ ሲጠበቅበት የነበረውን ፕሮጀክት አቅርጦ የወጣው፣ የቀድሞው ባለይዞታ አላና ፓታሽ መክፈል የሚጠበቅበትን ታክስ ባለመክፈሉ ምክንያት በተፈጠረ አለመግባባት ነው፡፡ ያልታሰበውና መንግሥት ዕውቅና የነፈገው የሽያጭ ስምምነት በአላና ፖታሽና በአይሲኤል ኩባንያዎች መካከል ውለታ የደረገበው መጋቢት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ውጭ በተፈጸመ ሲሆን፣ በወቅቱ በሁለቱ ኩባንያዎች መካከል የተደረገውን ስምምነት የማዕድን ሚኒስቴር በሕጋዊ መንገድ የቀረበልኝ ጥያቄ የለም በማለት እንደማይቀበለው መግለጹ ይታወሳል፡፡ አላና ፓታሽ ግን የኩባንያውን አክስዮኖች ለአይሲኤል መሸጡን ይናገራል፡፡ ትክክለኛው አካሄድ ግን የአክሲዮን ሽያጩ ከመፈጸሙ በፊት ለፈቃድ ሰጪው አካል (በወቅቱ ለማዕድን ሚኒስቴር) ቀርቦ ሒደቱ ታውቆ፣ ማረጋገጫም ሊሰጥበት ይገባ እንደነበር መገለጹም ይታወሳል፡፡ የሽያጭ ዝውውሩ እንዲህ ያሉ አነጋጋሪ ጉዳዮች ቢታዩበትም፣ መንግሥት የእስራኤሉ ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ እንዲሠራ ፈቅዶለት ሲሠራ ቆይቷል፡፡

ሥራው እንዳይቋረጥም በአላና ፖታሽ ፈቃድ አንድ ዓመት ሙሉ ወደ ፖታሽ ማዕድም አምራችነት በመግባት ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ቢሆንም በአላና ፖታሽ ያልተሠሩ ጥልቅ የምርመራ፣ የንፁህ ውኃ ቁፋሮና የአሰሳ ሥራዎችን ሲያካሄድ ስለመቆየቱ የሚጠቁሙ መረጃዎች ይደመጣሉ፡፡ በአንድ ዓመት ቆይታው ለእንዲህ ያሉት ሥራዎች ኩባንያው ከ48 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ማድረጉም ይነገራል፡፡ ይህ ቢባልም በፕሮጀክቱ ቦታ ላይ የሚገኙ ንብረቶች ግምት ምን ያህል እንደሆነ እስካሁን ይፋ አልወጣም፡፡

በመጋቢት ወር 2007 ዓ.ም. በአላናና በአይሲኤል መካከል የተደረገው የሽያጭ ስምምነት አጠያያቂ ቢሆንም፣ አይሲኤል ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሠራ ተፈቅዶለት ከቆየ በኋላ ከ150 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ያደረገበትን ኢንቨስትመንት አላና ፓታሽ በራሱ ስም ሳያስመዘግብ ቆይቷል፡፡ አላና የሚለውን ስያሜ ወደ አይሲኤል ለመቀየር ለማዕድን ሚኒስቴር ያቀረበው ጥያቄም ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል፡፡

ማዕድን ሚኒስቴር ይህ ጥያቄ መስተናገድ የሚችለው አላና ፓታሽ መጀመሪያ ያለበትን ግዴታ በመወጣት ከጉምሩክ የዕዳ ነፃ ማስረጃ ሲያቀርብ እንደሆነ አስታውቆታል፡፡ በዚሁ መሠረት ለጉምሩክ ጥያቄውን ሲያቀርብ፣ አላና ፓታሽ 55 ሚሊዮን ዶላር መክፈል ያለበት ታክስ ስላለ ከዕዳ ነፃ ማስረጃውን ማግኘት የሚችለው ዕዳውን ከከፈለ ብቻ እንደሆነ ተገልጾለታል፡፡ አይሲኤል በኢትዮጵያ የነበረውን ኢንቨስትመንት ለመቀጠል ያለው አማራጭ አላና ፓታሽ አለበት የተባለውን ዕዳ ሲከፍል ብቻ መሆኑም ለመቀጠል አስቸጋሪ ከሆኑበት ምክንያቶች ውስጥ ይጠቀሳል፡፡

የአይሲኤል ማኔጅመንት አላና ፓታሽ አለበት የተባለውን ታክስ መርምሮ መክፈል የሚችለው በ20 ሚሊዮን ዶላር የሚገመተውን ብቻ እንደሆነ አስታውቆ ነበር፡፡ ቀሪውን ለመክፈል የኩባንያው አሠራር እንደማይፈቅድለት በማመልከት ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ቢያሳውቅም፣ ጥያቄው ተቀባይነት አላገኘም፡፡ በዚህ ምክንያት የተፈጠረው አለመግባባት እየሠፋ በመሔዱ፣ ለኩባንያው ከኢትዮጵያ መውጣት ምክንያት ሊሆን ችሏል፡፡ በሌላ በኩል ግን አይሲኤል መጀመሪያውኑ አላና ፓታሽ ይህንን ያህል የመንግሥት ዕዳ እንደነበረበት አያውቅም ነበርም ይባላል፡፡ ቢሆንም ግን ብዙ ተስፋ የተጣለበትና ከሰባት ዓመታት በላይ የቆየው ፕሮጀክት ሳይታሰብ መሐል መንገድ ቀርቷል፡፡

አላና ፓታሽ ይዞታውን በሽያጭ ለአይሲኤል ከማስተላለፉ ቀደም ብሎ በዳሎል የተካሄደው የፓታሽ ማዕድን የማምረት ሥራ አጠቃላይ የኢንቨስትመንት ወጪ እስከ 800 ሚሊዮን ዶላር እንደሚደርስ አስታውቆ ነበር፡፡

በአላና ስም የተያዘው እስራኤሉ ኩባንያ ለፓታሽ ማዕድን ማምረቻ የተረከበው ይዞታ፣ 300 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ነው፡፡ ለፓታሽ ማምረቻ ይሆናል ተብሎ የተለየው 200 ካሬ ኪሎ ሜትር ቦታ ሲሆን፣ በወቅቱ በተደረገ ጥናት በዚህ ይዞታ ብቻ 3.2 ቢሊዮን ቶን የሚገመት የፓታሽ ማዕድን ክምችት እንዳለ ተጠቁሟል፡፡

አይሲኤል በፓታሽና ሌሎች ማዕድናት ኢንቨስትመንት ላይ ከተሰማሩ ትልልቅ ኩባንያዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ከ12 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሀብት እንዳለው የሚነገርለት ይህ ኩባንያ፣ በእስራኤልና በእንግሊዝ የፓታሽ ማውጫዎች አሉት፡፡

አላና ፓታሽ በሚል ስያሜ የፓታሽ ማዕድን ለማምረት ፈቃድ የተሰጠውና መቀመጫውን ካናዳ ያደረገው ኩባንያ፣ ባጠናው መሠረት፣ ከሁለት ዓመት በፊት ምርቱን ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደሚችል ይታሰብ ነበር፡፡

ይህንኑ ውጥን ተከትሎም ፓታሹን ለውጭ ገበያ እንዲያቀርብ መንግሥት ድጋፍ ሲሰጠው ቆይቷል፡፡ በተለይ ምርቱን ሲጀምር ከማምረቻ ቦታው ታጁራ ወደብ ድረስ የአዲስ መንገድ ግንባታ እንዲካሄድ መወሰኑ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጉዳዩን በቅርብ ከሚያውቁ ወገኖች ለመረዳት እንደተቻለው፣ ፓታሽ ማውጫው አካባቢ ከሚገኙ ንብረቶች ውስጥ አደገኛ የሆኑ ኬሚካሎችና ጨረር አመንጪ ቁሳቁሶች ስለሚጉባቸው በጥንቃቄ መወገድ እንዳለባቸው እየተነገረ ነው፡፡

ንብረቱን የተረከቡት የመንግሥት ተቋማት፣ አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ ስለተባሉት ንብረቶች ትኩረት በመስጠት በባለሙያ በጥንያቃቄ ማስወገድ እንደሚገባቸው ማሳሰቢያ እየቀረበባቸው ነው፡፡ ባለሥልጣኑ እንዳይንቀሳቀሱ ያገዳቸው ንብረቶችን ተሸጠው ወደ ካዝናው እንደሚያስገባ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ወደፊት ከአላና ጋር የሚኖረው ግንኙነት ወዴት እንደሚያመራ ለማወቅ አዳጋች ሆኗል፡፡

Standard (Image)

አፍላቶክሲን አደገኛው የጤና ጠንቅ

$
0
0

 

የተለያየ የጥራት ደረጃ የሚወጣላቸው ዛላ የበርበሬ ዓይነቶች በየማዳበሪያው ተሞልተው ተደርድረዋል፡፡ አንደኛ የሚባለውና በኪሎ 60 ብር የሚሸጠው፣ ዛለው ረጃጅምና ደማቅ ቀለም ያለው ነው፡፡ ሁለተኛው በኪሎ 50 ብር የሚሸጠው ሲሆን፣ ከአንደኛው መለስ ያለ ደረጃ የሚሰጠው ነው፡፡ ሌሎቹ የበርበሬ ዘሮች የተሰባበሩ፣ ነጫጭ የሚበዛባቸው ከበርበሬነት ይልቅ በቀለማቸው ወደሌላ የምርት ዓይነት የሚያደሉት በኪሎ እስከ 30 ብር የሚሸጡ ናቸው፡፡

በሾላ ገበያ በርበሬና የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን የሚሸጡት ወይዘሮ ዘመናይ ይርጋ (ስማቸው የተቀየረ ነጋዴ) ፀዳሌ፣ ማረቆና ሃላባ የተባሉት የበርበሬ ዓይነቶች ተመራጭ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ በአጠቃላይ ግን ቆዳው ወፍራምና ዛላው ትልልቅ ሆኖ ደማቅ ቀለም ያለው አንደኛ ተብሎ በውድ ዋጋ ይሸጣል፡፡ ልቃሚ የሚበዛውና አመድማ ዛላ ያለው በርበሬ በርካሽ ዋጋ እንደሚሸጥ ይገልጻሉ፡፡

‹‹አንደኛው ቀለሙ በጣም ቀይ ነው፡፡ ወጥ ሲሠራበትም ያጣፍጣል፡፡ የመጨረሻው ግን አፈር የመሰለ ነው ቀለሙም አያምርም፤›› በማለት በሁለቱ የበርበሬ ዓይነቶች መካከል ያለው ልዩነት ከቀለም ያለፈ እንዳልሆነ ያብራራሉ፡፡ ልዩነታቸውም ከአለቃቀምና ከምርት አያያዝ የመነጨ እንደሆነም በልበ ሙሉነት ይናገራሉ፡፡ በሁለቱ በርበሬዎች መካከል ያለው ልዩነት በሻጋታ የተፈጠረ እንደሆነ ግን የገባቸው አይመስሉም፡፡

በቅናሽ ዋጋ የሚሸጠው በርበሬ በአብዛኛው ሻጋታ ይታይበታል፡፡ ሻጋታ የሚፈጠረውም ምርት እርጥበቱ ሳይጠፋ በሚከማችበት ጊዜ እንደሆነ የሥነ ምግብ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ ‹‹ኪሎ እንዲያነሳ በማለት ገበሬውም ነጋዴውም በርበሬ ላይ ውኃ ያርከፈክፋሉ፡፡ በርበሬ ዕርጥብ ሲሆን ከአንድ ኩንታል እስከ አሥር ኪሎ ትርፍ ይገኛል፡፡ ይህ በርበሬ ቶሎ ካልተሸጠ ግን ስለሚሻግት በቅናሽ ዋጋ እንሸጠዋለን፤›› በማለት ኪሎ እንዲያሳ ሲባል ውኃ የሚርከፈከፍበት በርበሬ ሻጋታ እንዲፈጥር መንገዱን እየጠረጉ ስለመሆኑ ነጋዴዋ ይናገራሉ፡፡ በርበሬ ሲሻግት በጤና ላይ የሚፈጥረው ችግር እንደሚኖር ግን አንድም ጊዜ አልጠረጠሩም፡፡ በሻጋታ ውስጥ ካንሰር አማጭ የሆነው አፍላቶክሲን የተባለው ኬሚካል እንደሚፈጠር የሚያውቁት ነገር የለም፡፡

በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በርበሬ፣ በቆሎ፣ ለውዝ እንዲሁም ቦሎቄ ከፍተኛ የአፍላቶክሲን ክምችት ሊገኝባው የሚችሉ የቅባት፣ የቅመማቅመምና የእህል ዝርያዎች ናቸው፡፡ በቅርቡ ወደ እንግሊዝ የተላከ ሁለት ኮንቴነር በርበሬ በአፍላቶክሲን ተጠርጥሮ እንዲጣል መደረጉን ሚዲያዎች መዘገባቸው ይታወሳል፡፡

ሞቃታማና እርጥበት አዘል በሆኑ የዓለም አካባቢዎች በተለይም ከሰሐራ በታች በሚገኙ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ውስጥ በሚመረቱ የእህል ዓይቶች ውስጥ አፍላቶክሲን በብዛት ይከሰታል፡፡ አፍላቶክሲን በሕፃናት ዕድገት እንዲሁም በማስተዋል ችሎታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ከማሳደሩ ባለፈ ብዙዎችን ለካንሠርና ለተለያዩ ከባድ በሽታዎች እየዳረገ ይገኛል፡፡

አፍሪካ ባላት የአየር ጠባይ ሳቢያ 80 በመቶ የሚሆኑ ሕዝቦቿ ለአፍላቶክሲን ጉዳቶች የተጋለጡ ናቸው፡፡ በአኅጉሪቱ በተለያዩ ጊዜያት በመከሰት ብዙዎችን ከሚያረግፉት የወባና የሳንባ ወረርሽኞች የበለጠ አፍላቶክሲን በርካቶችን ለሞት እየዳረገ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

25 በመቶ በዓለም የሚመረተው ሰብል በአፍላቶክሲን የተበከለ መሆኑም ይነገራል፡፡ በአፍሪካም አንድ ሦስተኛው ለምግብነት የሚውለው ሰብል ከሚገባው በላይ በአፍላቶክሲን የተበከለ ነው፡፡

አቶ ዘሪሁን አበበ፣ በኢትዮጵያ ተስማሚነትና ምዘና ድርጅት የኬሚካል ቴስቲንግ ላቦራቶሪ ቡድን መሪ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ቅርፊት ያላቸው እንደ በቆሎና ለውዝ ያሉ የእህል ዘሮች በእርጥበታማ ቦታዎች በሚከማቹበት ጊዜ በቅርፊታቸው እርጥበት የመያዝ ባህሪ ስላላቸው የመሻገት ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ ቅርፊት ያላቸውን ያህል ባይሆንም ሌሎችም የሰብል ዓይነቶች በእርጥበታማ ቦታ ከተቀመጡ መሻገታቸው አይቀሬ ነው፡፡

ሁሉም ሻጋታ የአፍላቶክሲን መንስዔ ባይሆንም፣ በፍጥነት ማስተካከል ካልተቻለ ግን ወደ አፍላቶክሲን መቀየሩ አይቀሬ ነው፡፡ አፍላቶክሲን ‹‹ኤስፐርጊለስ ፍሌቨስ›› እና ‹‹ኤስፐርጊለስ ፓራሲተከስ›› በተባሉ የፈንገስ ዝርያዎች የሚከሰት አደገኛ ኬሚካል ነው፡፡ b1፣ b2፣ G1፣ G2 የሚባሉ ዝርያዎችም አሉት፡፡ እነዚህ በሰብሎች ላይ የሚከሰቱ ናቸው፡፡ m1፣ m2 የተባሉ በእንስሳት ተዋፅኦዎች ውስጥ የሚገኙ ዝርያዎችም አሉ፡፡

እንስሳት በአፍላቶክሲን የተበከሉ መኖዎች በሚመገቡበት ጊዜ ኬሚካሉ ወደ ተዋጽኦዋቸው ይተላለፋል፡፡ ነገር ግን ኬሚካሉን ወደሌላ ዓይነት ይዘት እንዲቀየር (ሜታቦላይዝ) ስለሚያደርጉት በቀጥታ እንስሳቱን አይጎዳም፡፡ እነዚህ የአፍላቶክሲን ዝርያዎች የሚያደርሱት የጉዳት መጠን የተለያየ ነው፡፡ b1 የሚባለው የአፍላቶክሲን ዝርያ ከሌሎቹ በተለየ አደገኛ ነው፡፡ የጨጓራ ካንሰር የሚከሰተው በዚሁ b1 በተባለው የአፍላቶክሲን ኬሚካል አማካይት ነው፡፡ M1 የተባለው በእንስሳት ተዋጽኦ ውስጥ የሚገኘው ኬሚካል እንደ b1 ሁሉ አደገኛ የሚባል ነው፡፡

በአንድ ኪሎ ግራም ምግብ ውስጥ መገኘት የሚገባው ከፍተኛው የአፍላቶክሲን ክምችት እንደየ ዝርያው ዓይነት ይወሰናል፡፡ በኢትዮጵያ ስታንዳርድ መሠረት b1 የሚባለው አደገኛው የአፍላቶክሲን ዝርያ፣ በአንድ ኪሎ ምግብ ውስጥ የሚኖረው ክምችት ከአምስት ማይክሮ ግራም መብለጥ የለበትም፡፡ በሕፃናት ምግብ ውስጥ የሚገኘው መጠንም በአንድ ኪሎ ግራም ውስጥ ከሁለት ማይክሮ ግራም በላይ ከሆነ አደገኛ ነው፡፡ በአዋቂ ምግቦች ውስጥ እስከ 20 ማይክሮ ግራም ከተገኘ አደገኛ የሚያስብለው ደረጃ ላይ የሚመደብ ነው፡፡

ሰብሎች በማሳ ሳሉ ሊሻግቱና በአፍላቶክሲን ሊጠቁ ይችላሉ፡፡ በአፍላቶክሲን የተጠቃ ምርት በማሳ ላይ በሚራግፍበት ወቅትም ኬሚካሉ ወደ አፈር ውስጥ በመግባት ማሳውን ሙሉ ለሙሉ ሊያበላሸው ይችላል፡፡ ‹‹በምርት ወቅት ማሳ ላይ ከተሠራጨ ችግር ነው፡፡ ኬሚካሉ አፈር ውስጥ ስለሚገባ በማሳው የሚበቅል ምንም ነገር በአፍላቶክሲን የተበከለ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ይሁንና ይህ ከብዙ ጊዜ በጥቂቱ የሚከሰት ነው፡፡ ሰብሎች ማሳ ላይ ሻግተው ችግር ለመፍጠር ረዘም ያለ ጊዜ ይፈጃሉ፤›› ለማለት ችግሩ በብዛት እየተከሰተ ያለው ከማሳ ተሰብስቦ በሚከማችበት ወቅት መሆኑን አቶ ዘሪሁን ይናገራሉ፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ምርት ከመታጨዱ ወይም ከመሰብሰቡ በፊት እንዳይረግፍ እየተባለ በተገቢው ደረጃ ሳይደርቅ የሚታጨድበት ሁኔታ የተለመደ ነው፡፡ በወጉ ያልደረቀው ምርት ጎተራ ከመግባቱ በፊት እንዲደርቅ እየተባለ በአንድ ላይ ይከማቻል፡፡ ይህም ሻጋታ እንዲፈጠር የመጀመሪያውን መንገድ ይከፍታል ያሉት አቶ ዘሪሁን፣ ገለባው ከፍሬው ተለይቶና ተወቅቶ ወደ ጎተራ በሚገባበት ጊዜም ተገቢው ጥንቃቄ ስለማይደረግ፣ በወጉ ያልደረቁ ፍሬዎች ተቀላቅለው ይገባሉ፡፡ በመሆኑም በጎተራ ውስጥ ታፍኖ የሚቀመጠው ምርት የመሻገት ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡

‹‹አንዳንዴ ገበያ ላይ ጤፍ እምክ እምክ አለ ይባላል፡፡ ይህ የሚሆነው ጤፉ እርጥበት እንደያዘ ጎተራ ውስጥ ታፍኖ እንዲቆይ ሲደረግ ነው፡፡ ሁሉም ሻጋታ አፍላቶክሲን አይደለም፡፡ ቶሎ ካልተደረሰበት ግን ወደ አፍላቶክሲንነት ይቀየራል›› ይላሉ፡፡

የአፍላቶክሲን ጉዳይ የዓለምን ትኩረት መሳብ የጀመረው እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ ውስጥ በእንግሊዝ የሚገኝ አንድ የዶሮ እርባታ ውስጥ የነበሩ 100,000 ዶሮዎችን እንደ ጤዛ ካረገፋቸው በኋላ ነው፡፡ ይኸው አፍላቶክሲን በኢትዮጵያ መነጋገሪያ ለመሆን የበቃውም ዓለምአቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት የተባለው ተቋም ተመራማሪዎች ያወጡትን ጥናት ተከትሎ ነው፡፡ ከዓመት በፊት ይፋ የተደረገው ጥናቱ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የወተት ላም አርቢዎችን መነሻ ያደረገና በወተት ውስጥ የሚገኘውን የአፍላቶክሲን ክምችት የሚያሳይ ነበር፡፡

በወቅቱ በርካቶችን ያወዛገበና የእንስሳት ተዋጽኦ ገበያን ሥጋት ውስጥ ጥሎ  እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ከዚህ ክስተት ወዲህ ስሙ የገነነው አፍላቶክሲን፣ ከእንስሳት ተዋጽኦ ባሻገር በተለያዩ የምግብ ይዘት ባላቸው ነገሮች ውስጥ ለጤና አስጊ በሆነ የክምችት መጠን እንደሚገኝ የሚያሳዩ ጥናቶች ይፋ እየወጡ መጥተዋል፡፡

 በዚህ መርዛማ ኬሚካል በእጅጉ እየተጠቁ ያሉትም የለውዝና የበርበሬ ምርቶች እንደሆኑ አቶ ዘሪሁን ገልጸዋል፡፡ አገሮች ካስቀመጧቸው መሥፈርቶች የበለጠ የአፍላቶክሲን መጠን የሚታይባቸውና እንዲመለሱ እየተደረጉ ካሉት ምርቶች ግንባር ቀደም ሆነው ተገኝተዋል፡፡

 ከውጭ የሚገቡ ምግብ ነክ ሸቀጦች እየተፈተሹ መሥፈርቱን የሚያሟሉት እንዲገቡ ሲፈቀድላቸው፣ የማያሟሉት ግን ወደየመጡበት እንዲመለሱ ይደረጋሉ፡፡ ወደ ውጭ የሚወጡትም እንደዚሁ እንደየአገራቱ አሠራርና መሥፈርት ተፈትሸው መሥፈርቶቹን ስለማሟላታቸው የማረጋገጫ ሠርተፊኬት እየተሰጣቸው ይላካሉ፡፡

በዚህ መሠረት ለፍተሻ ወደ ተቋሙ ከሚሄዱ የበርበሬና የለውዝ ምርቶች ውስጥ ከፍተኛ የአፍላቶክሲን ክምችት እንደሚያጋጥም አቶ ዘሪሁን የታዘቡትን ጠቅሰዋል፡፡ በኪሎ ግራም ውስጥ እስክ 60 ማይክሮ ግራም የአፍላቶክሲን ክምችት እንደሚያጋጥም አስታውሰዋል፡፡ ሌሎች መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአንድ ኪሎ ግራም ለውዝ ውስጥ እስከ 500 ማይክሮ ግራም የአፍላቶክሲን ክምችት የሚገኝበት ክስተትም ይታያል፡፡ በአውሮፓ ስታንዳርድ መሠረት በአንድ ኪሎ ግራም ለውዝ ውስጥ መገኘት የሚገባው የአፍላቶክሲን ክምችት ከአሥር ማይክሮ ግራም መብለጥ የለበትም፡፡

በኢትዮጵያ በለውዝ ምርት የሚታወቁት በምሥራቅ ሐረርጌ የሚገኙት የባቢሌ፣ የፈዲስና የጉርሱም አካባቢዎች ናቸው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች በሚገኝ የለውዝ ምርት ላይ የተደረገ ጥናት እንደመሚያመለክተው፣ ተከማችተው በሚገኙ የለውዝ ምርቶች ውስጥ 85 በመቶ ያህል የአውሮፓ ኅብረት ካስቀመጠው በላይ ከፍተኛ የአፍላቶክሲን ክምችት የሚገኝባቸው ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ዮሐንስ እንደሚሉት፣ ከመጠን ባለፈ የአፍላቶክሲን ክምችት ምክንያት ወደ ውጭ የሚላከው የለውዝ ምርት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ መጠን እየቀነሰ ይገኛል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2011 ወደ ውጭ ተልኮ የነበረው የለውዝ መጠን 14,424 ቶን ነበረ፡፡ ይሁንና እ.ኤ.አ. ከ2012 እስከ 2016 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የተላከው የለውዝ መጠን በእጅጉ ማሽቆልቆሉን ከማኅበሩ የተገኘው አሃዛዊ መረጃ ያሳያል፡፡ 12,609 ቶን፣ 592 ቶን፣ 124 ቶን እያለ ወርዶ እ.ኤ.አ በ2016 የተላከው የለውዝ መጠን ወደ 79 ቶን ሊያሽቆለቁል ችሏል፡፡

አስፈላጊውን የፍተሻ ሒደትና መሥፈርት ሳያሟሉ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ከመጠን ያለፈ የአፍላቶክሲን ክምችት በሚገኝባቸው ወቅት እንዲወገዱ ሲደረግ፣ ጤናማ የሆኑት ደግሞ በላቦራቶሪ ተፈትሸው ደኅንነታቸውም ተረጋግጦ ወደ ውጭ ይላካሉ፡፡ ይሁንና ስለ ጉዳዩ ብዙም ግንዛቤ የሌላቸው ሸማቾች፣ በየዕለቱ የሚመገቧቸው ነገሮች ምን ያህል ለጤና የሚገባውን መሥፈርት እንደሚያሟሉ አረጋግጠው ስለመጠቀማቸው በእርግጠኝነት መናገሩ አጠያያቂ ነው፡፡ በዓይን የማይታዩ የኬሚካሎችን ዝርያ ከመመገብ መጠንቀቁ ቀርቶ ሻጋታን የመጠየፍ ባህሉ እስከምን ድረስ እንደሆነ ጥያቄ የሚጭሩ ልማዶች ይታያሉ፡፡

‹‹Assessment of Mothers Knowledge towards Aflatoxin Contamination›› በሚል ርዕሥ እ.ኤ.አ. በ2016 የተደረገ ጥናት፣ ማኅበረሰቡ ስለ አደገኛው ኬሚካል ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ በመሆኑ ምክንያት ችግሩ አሳሳቢ እንደሆነ ለማመላከት ሞክሯል፡፡ በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ብሔር ብሐረሰቦች የሚገኙ እናቶች በጥናቱ ተካተው ነበር፡፡

ምርት ከማሳው ጀምሮ ለምግብነት እስኪሚውልበት ድረስ ያሉትን ሒደቶች በሚያሳየው በዚህ ጥናት መሠረት፣ 64 በመቶ እናቶች ምርት ከማሳው ከተሰበሰበ በኋላ በተለያዩ ዘዴዎች አድርቆ የማስቀመጥ ልምድ እንዳላቸው ታይቷል፡፡ 68 በመቶዎቹ ምግባቸውን መሬት በማንጠፍ በፀሐይ ይደርቃሉ፡፡ 94 በመቶዎቹ ደግሞ ምርት በጎተራ ውስጥ ከማከማቸታቸው በፊት ጎተራቸውን በፀረ ባክቴሪያ ኬሚካሎች እንደሚያፀዱ ጥናቱ ያሳያል፡፡

የተሻለ ጥንቃቄ በማያደርጉት በኩል ያለው ምርት በሻጋታ የሚጠቃበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ በሻጋታ የሚከሰት ባክቴሪያንም እሳት ላይ ሞቅ ሞቅ በማድረግ መግደል እንደሚቻል የሚያምኑም አልታጡም፡፡ ከፊሉን ለእንስሳት መኖነት፣ የተቀረውን ደግሞ ለጠላ መጥመቂያነት እንደሚያውሉትም ጥናቱ ያትታል፡፡

የተበላሸ የሻጋታ ጥራጥሬን ለጠላ መጥመቂያነት የማዋሉ ነገር በአገሪቱ ክፍሎች የተለመደ ነወ፡፡ የሻገተ እንጀራን በምጣድ ሞቅ አድርጎ መብላትም አዲስ አይደለም፡፡ እንዲያውም እንጀራ ሻጋታ መያዝ ሲጀምር ድርቆሽ ማድረግና አቆይቶ መብላት ምግብን ከብክነት እንደመጠበቅ ይቆጠራል፡፡ በሻጋታ ምክንያት የተቋጠረ (የጓጐለ) ዱቄትን አሽተው ለመብል ማዘጋጀት፣ የሻገተ የበርበሬ ዛላን በርካሽ ገዝቶ ለምግብነት ማዋል ሊያደርስ ስለሚችለው የጤና ቀውስ የሚጨነቁ በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡

ምርት ከማሳ ላይ ተነስቶ ወደ ጎተራ እስኪገባ ባሉት ሒደቶች የሚፈጠረው አፍላቶክሲን በቀላሉ መከላከል እንደሚቻል አቶ ዘሪሁን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ምርት እስኪደርቅ ጠብቆ ማጨድ፣ ወደ ጎተራ ከመግባቱ በፊትም በፀሐይ ማድረቅ ተገቢ ነው፡፡ በእኛ አገር የአየር ፀባይ ምግብ ያለ ብዙ ልፋት ይደርቃል፡፡ በዚህ የታደልን ነን፤›› በማለት ዋናው ነገር ምርት ጎተራ ውስጥ በሚከማችበት ጊዜ እርጥበት እንዳይነካው ጥንቃቄ ማድረጉ ላይ እንደሆነም ይመክራሉ፡፡

በተፈጥሮ መከላከል የማይቻል ከሆነም ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እርጥበትንና ሻጋታን መከላከል ይቻላል፡፡ አቶ ራሺም ጀማል የሃይቴክ ትሬዲንግ ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ሃይቴክ ኩባንያ የተለያዩ የግብርና የኢንዱስትሪ ማሽገሪዎችና ግብዓቶችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ሥራ ዘርፍ ይንቀሳቀሳል፡፡ ሻጋታን በባህላዊ መንገድ ማለትም በፀሐይ በማድረቅ መከላከል ካልተቻለ፣ የፈንገስን ዕድገት መግታት የሚችሉ አየር ወደ ውጭና ወደ ውስጥ የማያስገቡ ሄርሜቲክና ሜታል ሳይሎ የተባሉ ቴክኖሎጂዎች የተሻሉ አማራጮች መሆናቸውን አቶ ራሺም ይገልጻሉ፡፡ ሜታል ሳይሎ የሚባለው የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት በብዛት የሚያከፋፍለው፣ አየር እንዳያስገባና እንዳያስወጣ ተደርጎ የሚዘጋጅ እንደ በርሜል ያለ ዘመናዊ ጎተራ ነው፡፡

ሄርሜቲክ ቴክኖሎጂ የሚባለው ደግሞ ነቀዝን፣ ተባይን፣ እንዲሁም እርጥበትና ሻጋታን ያለምንም ኬሚካልና ርጭት የተፈጥሮ ዘዴን በመጠቀም ማከማቸት የሚያስችል፣ ድርጅታቸው እንደሚያከፋፍለው ያለ የፕላስቲክ ጎተራ ዓይነት ነው፡፡ ይህ የፕላስቲክ ጎተራ ከ60 እስከ 1,500 ኩንታል የሚደርስ እህል የማከማቸት አቅም አለው፡፡ እንዲህ ቴክኖሎጂዎች ምርትን ከአፍላቶክሲን ከመጠበቅ ባሻገር ከፍተኛ የምርት ብክነትን ማስቀረት እንደሚችሉ ይናገራሉ፡፡ ይሁንና ተደራሽነታቸው ውሱን ነው፡፡

የአፍላቶክሲን ምርመራ የሚካህድበት ቴክኖሎጂ ባለመኖሩ በአንድ ወቅት ከፍተኛ ወጪ እየወጣ ባህር ማዶ እየተላ ምርት ይመረመር ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ከ2007 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ የአፍላቶክሲን ፍተሻ ማድረግ መጀመሩን የሚናገሩት በድርጅቱ የማርኬቲንግና ኮሙዩኒኬሽንስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ ተክኤ ብርሃኑ ናቸው፡፡ ወደ ውጭ የሚወጡና ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምግቦችን እንፈትሻለን ያሉት አቶ ተክኤ፣ ድርጅቱ ወደ አገር ውስጥ ከሚገቡ በቀር ወደ ውጭ የሚላኩትን በሙሉ የመፈተሽ ሥልጣኑ ውሱን ነው፡፡ ‹‹ስንጠየቅ ብቻ ነው የምንፈትሸው፡፡ ሁሉም ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች እኛ ጋር ላይመጡ ይችላሉ፡፡ ወደ ሌሎች ተቋማት በመሔድ ሊያስፈትሹ ይችላሉ፤›› በማለት በድርጅቱ ፍተሻ የሚደረገው ጥያቄ ሲቀርብለት ብቻ መሆኑን ያናገራሉ፡፡

 ድርጅቱ በአገር ውስጥ በስፋት ለምግብነት የሚውሉ እንደ የእንስሳት ተዋጽኦ፣ ሽሮ፣ በርበሬ ያሉትን የመፈተሽ አቅም ቢኖረውም፣ ለአገር ውስጥ የሚውሉ የምግብ ዓይነቶችን ለማስፈተሽ ሥራዬ ብሎ ወደ ተቋሙ የሚያመራ አለመኖሩም ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ከመጠን ያለፈ የአፍላቶክሲን ክምችት ተገኝቶባቸው ተመላሽ የሚደረጉ ምግብና ምግብ ነክ ሸቀጦች አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ ገበያ ውስጥ ይግቡ ወይስ ምን ይደረጉ የሚለው ጉዳይም አጠያያቂ ነው፡፡

አቶ አብነት ወንድሙ፣ በኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒት እና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ የምግብና ጤና ተቋማት የኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ተገቢው ፍተሻ ሳይደረግባቸው ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶች በተለይ በርበሬ በከፍተኛ የአፍላቶክሲን ክምችት ምክንያት በብዛት ተመላሽ እየተደረገ ነው፡፡ ባለሥልጣኑ እንዲመለሱ የሚደረጉ ምርቶች ወደ ሕዝብ ከመድረሳቸው በፊት እንዲወገዱ የሚያደርግበት አሠራር እንዳለው አቶ አብነት ይናገራሉ፡፡

‹‹ትልቁ ሥራ ግብርና ላይ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ አገር ውስጥ የሚመረቱ አፍላቶክሲን ሊገኝባቸው ይችላሉ ብለን የምንገምታቸውን ምርቶች በየሦስት ወሩ እንዲፈተሹ እናደርጋለን፤›› በማለት ለጊዜው ባለሥልጣኑ ትኩረቱን በወተትና በለውዝ ምርት ላይ በማድረግ እየሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

 

Standard (Image)

የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም በአፍሪካ የባንኮች ሽልማት በፋይናንስ ተደራሽነት ዘርፍ ለሽልማት ታጨ

$
0
0

የአገሪቱ የግልም ሆነ የመንግሥት ባንኮች ለውድድሩ ዕጩ መሆን ባልቻሉበት የዓመቱ የአፍሪካ ባንኮች ሽልማት መስክ፣ የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም፣ በፋይናንስ መስክ ዕጩ መሆኑ ታወቀ፡፡

‹‹አፍሪካ ባንከር ሜጋዚን›› የሚባለውና አይሲ ግሩፕ በተባለው የእንግሊዝ ኩባንያ የሚታተመው መጽሔት፣ በየዓመቱ በሚያካሂደው የፋይናንስ ዘርፉ ላይ ያተኮረ ውድድር ዘንድሮ በአሥር ምድቦች በሚካሄደው ሽልማት፣ በፋይናንስ ተደራሽነት ዘርፍ ለሽልማት የታጨው የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም፣ ከዚህ ቀደምም የዓመቱ ምርጥ የብድርና ቀጠባ ተቋም ተብሎ መሸለሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአገሪቱ ከሚገኙ ከ35 የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት መካከል ከቀደምቶቹ አንዱ የሆነው የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም፣ እስከ ካቻምና ድረስ ከ500 በላይ ቅርንጫፎችን በመክፈት በመላው አማራ ክልል የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማስፋፋት መንቀሳቀሱ ለሽልማት እንዲታጭ ካበቁት መካከል ይጠቀሳል፡፡

አነስተኛ ገንዘብ አቅራቢው የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም፣ ዘንድሮ በድጋሚ ለዕጩነት የቀረበው በፋይናንስ ተደራሽነት መስክ ይሁን እንጂ ከጥቂት ዓመታት ቀደም ብሎም የዓመቱ የአነስተኛ ገንዘብ አቅራቢ ሽልማትን ከመቀዳጀት ባሻገር፣ የግራሚን ሽልማትም ያገኘበት ጊዜ እንደነበር ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ይህ ሽልማት የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት መሥራቹ ባንግዳሌሻዊ ዩኑስ መሐመድ (ዶ/ር) አማካይነት ለዓለም በተዋወቀው የግራሚን ባንክ ፋውንዴሽን መታሰቢያነት የሚሰጥ ሽልማት ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ምርጥ ተቋም እንዲሁም ምርጥ የተቋም መሪ የሚሉ ሽልቶችን ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እ.ኤ.አ. በ2012 ማግኘቱም ተጠቅሷል፡፡

በዘንድሮው የአፍሪካ ባንከር መጽሔት የሽልማት ዘርፎች ውስጥ በዕጩነት የተካተተው አማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም በታጨበት የፋይናንስ ተደራሽነት ሽልማት ዘርፍ ማሸነፍ ከቻለ፣ ግንቦት 15 ቀን 2009 ዓ.ም. በህንድ አህመዳባድ ከተማ በሚካሄደው የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ ታዳሚ እንደሚሆን አይሲ ፐብሊኬሽንስ ያውጣው መርሐ ግብር ይጠቁማል፡፡ በዚህ ሥነ ሥርዓት በአፍሪካ ልማት ባንክ ዕውቅና ተሰጥቶት የሚከናወን ሲሆን፣ ሌሎችም በአፍሪካ የሚንቀሳቀሱ የግልና የመንግሥታቱ ባንኮች ድጋፍ የሚሰጡት ሥነ ሥርዓት እንደሆነ ሽልማቱን ያሰናዳው ተቋም ለሪፖርተር ከላከው መግለጫ ለመረዳት ተችሏል፡፡

 

 

 

 

Standard (Image)

የአሜሪካ መንግሥት በበቆሎ ዘር ማሻሻያ ፕሮግራሙ ተጠቃሚ ያደረጋቸው ገበሬዎች በሔክታር 7.5 ቶን ማምረት ችለዋል አለ

$
0
0

በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤኣይዲ)፣ በኢትዮጵያ መንግሥት እንዲሁም ዱፖንት በተባለው የአሜሪካ ኩባንያ ትብብር በተሻሻለ የበቆሎ ዝርያ ፕሮግራም አማካይነት ተጠቃሚ የሆኑ 250 ሺሕ ገበሬዎች፣ በሔክታር 7.5 ሜትሪክ ቶን ምርት መሰብሰብ እንደቻሉ የአሜሪካ ኤምባሲ አስታወቀ፡፡

ኤምባሲው ለሪፖርተር በላከው መግለጫ ይፋ እንዳደረገው ከሆነ፣ እ.ኤ.አ. ከ2015 ጀምሮ እስከ 2018 በሚተገበረውና ‹‹ፊድ ዘ ፊውቸር›› በተሰኘው ዓለም አቀፍ ፕሮግራም ሥር በሚካተተው የበቆሎ ዘር ማሻሻያ ፕሮግራም አማካይነት፣ በ53 የአገሪቱ ወረዳዎች የሚገኙ ገበሬዎች ቀደም ሲል በሔክታር ያመርቱ ከነበረው የ2.2 ሜትሪክ ቶን ምርት ይልቅ በፕሮግራሙ አማካይነት ወደ 7.5 ሜትሪክ ቶን በሔክታር ማምረት መቻላቸው ከፕሮግራሙ ማጠናቀቂያ ጊዜ ቀደም ብሎ የተገኘ ትልቅ ውጤት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ከወዲሁ የ150 በመቶ ስኬታማ ውጤት ያስገኘው የበቆሎ ዘር ማሻሻያ ፕሮግራም፣ ዱፖንት የተባለው ኩባንያ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ያደረገበት፣ ገበሬዎችም ከአራት ዓመታት ወዲህ የ300 በመቶ ውጤት ማስመዝገብ የቻሉበት ፕሮግራም እንደሆነ የአሜሪካ ኤምባሲ አስታውቋል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ገበሬዎች በበቆሎ አምራችነታቸው ባገኙት የቴክኖሎጂና ሌሎች ውጤታማ የምርት ሥርዓቶች አማካይነት፣ በነፍስ ወከፍ በዓመት የ1,500 ዶላር ወይም በወቅቱ ምንዛሪ የ34,500 ብር ተጨማሪ ገቢ ማግኘት የቻሉበት ውጤታማ ፕሮግራም መሆኑም ተገልጿል፡፡

በዩኤስአይዲ ረዳት አስተዳዳር እንደሁም በፊድ ዘ ፊውቸር ምክትል አስተባባሪ የሆኑትን ቤት ደንፎርድን (ዶ/ር) ጠቅሶ፣ ኤምባሲው በላከው መግለጫ ፕሮግራሙ ከመገባደጃ ጊዜው በሁለት ዓመት ቀድሞ ያስቀመጣቸውን የውጤት መለኪያዎች ማሳካት ችሏል፡፡

የሦስትዮሽ ፕሮግራሙ ባስገኘው ውጤት መደሰታቸው የተገለጸው ይህ ውጤት የአሜሪካ ኤጀንሲዎችና ኩባንያዎች በትብብር በመሥራት ካስመዘገቧቸው ስኬታማ ሥራዎች መካከል አመርቂው መሆኑንም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ፊድ ዘ ፊውቸር በአሜሪካ መንግሥት ይፋ የተደረገና በዓለም ላይ የምግብ እጥረትን ብሎም ረሀብን ለማጥፋት የተከፈተ ዘመቻ ነው፡፡ የዚህ ዘመቻ አካል የሆነው የበቆሎ ዘር ማሻሻያ ፕሮግራም፣ ለገበሬዎች ከሥልጠና ጀምሮ የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችን በማቅረብና በመሳሰሉት መስኮች ድጋፍ የሚሰጥ ነው፡፡

 

Standard (Image)

የጂፒኤስ ቴክኖሎጂ ጅምሮች

$
0
0

ከበርካታ የአገልግሎት ዘርፎች መካከል አንዱ የሆነው የትራንስፖርት ዘርፍ ሲሆን በዚህ ዘርፍ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ በርካታ ችግሮች ይታያሉ፡፡ ከችግሮቹ አንዱ በዘመናዊ አሠራሮችን ያልታጠቀ ነው፡፡ አገልግሎት ላይ ያሉ ተሽከርካሪዎችን በአግባቡ የማስተዳደር ልምዱም ቢሆን ገና ከልማዳዊ አሠራር አልተላቀቀም፡፡ ዘርፉ ካሉበት በርካታ ተግዳሮቶች ውስጥ የተሽከርካሪዎችን ስምሪት በዘመናዊ መንገድ ማስተዳደርና መቆጣጠር አለመቻልም ይጠቀሳል፡፡ ዘርፉን ለማዘመን እንደሚያግዙ ከሚታመንባቸው የአሠራር ስልቶች መካከል ተሽከርካሪዎች ላይ አቅጣጫ ተቋሚና አመላካች መሣሪያ ወይም ጂፒኤስ በመግጠም ስምሪታቸውን ከማዕከል በማስተናበር እያንዳንዱን እንቅስቃሴያቸውን መቆጣጠር የሚያስችለው ቴክኖሎጂ ተጠቃሽ ነው፡፡ በተሽከርካሪዎች ላይ ተገጥሞ በሞባይል ስልኮችና በኮምፒውተር መቆጣጠር የሚያስችለውን ይህንን ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ ለማዋል እንቅስቃሴ ከተጀመረ ስምንት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በጂፒኤስ አማካይነት ተሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችለውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋሙ ኩባንያዎች ቁጥርም ተበራክተዋል፡፡ ስምንት ኩባንያዎች እንዳሉም ይታመናል፡፡ ሆኖም በቴክኖሎጂው የሚጠቀሙ ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰብ ባለንብረቶች ቁጥር አነስተኛ መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡ ቴክኖሎጂው በመግጠምና በመከታተል አገልግሎት ከሚሰጡ ኩባንያዎች መካከል ካሳ ሶፍትዌር ትራኪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሲሆን፣ የኩባንያው ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ካሳ፣ ቴክኖሎጂው ከሚሰጠው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አንፃር ተጠቃሚው አነስተኛ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ አቶ ሰለሞን ቴክኖሎጂው ለባለንብረቶች ከሚሰጠው አገልግሎት በላይ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖረው አስተዋጽኦ እንደሚጎላም ይገልጻሉ፡፡ እየተጠቀሙበት የሚገኙ ግለሰቦችና ተቋማት ንብረታቸውን ከየትኛውም ሥፍራ ሆነው ያለገደብ ለመቆጣጠር ከመቻላቸውም በላይ፣ ከአሽከርካሪዎች ጋር የነበሩ አለመግባባቶችን ለማስቀረት እንዳገዛቸውም ይጠቅሳሉ፡፡ ከወራት በፊት በአገሪቱ በተከሰተው ፖለቲካዊ ግርግር ሳቢያ የጂፒኤስ አገልግሎት በመቋረጡ፣ በቴክኖሎጂው ሲጠቀሙ የነበሩ ተቋማትን ምን ያህል እንደተጎዱም አቶ ሰለሞን ያስታውሳሉ፡፡ ዳዊት ታዬ በቴክኖሎጂውና በአገልግሎቶቹ ዙሪያ አቶ ሰሎሞን ካሳን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከጂፒኤስ አገልግሎት ጋር የተሳሰረውን ቢዝነስ እንዴት መረጡ?

አቶ ሰለሞን፡- ይሄንን ቢዝነስ የመረጥንበት ዋነኛ ምክንያት ዜጎች ንብረት ካፈሩ በኋላ ንብረቶቻቸውን በአግባቡ ለመቆጣጠር የሚያስችል ዘመናዊ አሠራር ያልዳበረ መሆኑን በመረዳት፣ በዚህም ዜጎች እንደሚማረሩ በመገንዘባችን ነው፡፡ በተለይ ከተሽከርካሪዎች ስምሪትና አገልግሎት አሰጣጥ አንፃር የሚታዩ ችግሮችን በጥልቀት አስጠንተን፣ የአገራችን የትራንስፖርት ዘርፍ ከዚህ ችግር በመውጣት ወደ ዘመናዊ አሠራር እንዲገባ አንዱ መፍትሔ ተሽከርካሪዎችን በዘመናዊ መንገድ ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር የጂፒኤስ አገልግሎትን ጠቀሜታ በመገንዘባችን ነው፡፡ ባደረግነው ጥናት መሠረት ቴክኖሎጂው በሌላው ዓለም እየተስፋፋና እያደገ የመጣ የቢዝነስ ዘርፍ ነው፡፡ የቴክኖሎጂው ተጠቃሚዎችን፣ እኛንና መንግሥትን በአጠቃላይ አገርን የሚጠቅም በመሆኑ፣ ወደፊት እየተስፋፋ የሚሄድ ቢዝነስ ይሆናል በሚል እምነት የገባንበት ነው፡፡ የዚህ ቴክኖሎጂ ጠቀሜታ በተለያየ መንገድ ሊገለጽ ይችላል፡፡ ጂፒኤስ የተገጠመለት ተሽከርካሪ በፕሮግራም እንዲሠራ ይረዳል፡፡ ሾፌሮችም በጂፒኤስ ቁጥጥር የሚደረግባቸው መሆኑን ስለሚያውቁ በተቀመጠላቸው ጊዜ ውስጥ የተባሉት ቦታ እንዲደርሱ በማገዝ የትራንስፖርት አገልግሎቱ የተቀላጠፈ አሠራር እንዲኖረው ማስቻሉም ሊጠቀስ ይችላል፡፡ የተሽከርካሪዎቹ ባለንብረቶችም በቀላሉ ንብረቶቻቸውን ለመቆጣጠር አቅም ይፈጥርላቸዋል፡፡ የቴክኖሎጂው አገልግሎት ተሽከርካሪዎች የት ቦታ ላይ ናቸው? የተባሉት ቦታ በትክክል ደርሰዋል ወይ? የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ ብቻም ሳይሆን፣ ሌሎች መረጃዎችንም የትራንስፖርት ድርጅቱ ባለቤት እንዲያገኝ የሚያስችለው ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ስለቴክኖሎጂው ጠቀሜታዎች ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ስለ ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ መረጃ ከመስጠት ባሻገር የሚሰጠው ሌላ ጠቀሜታ አለ? ለምሳሌ የነዳጅ ብክነት ይቀንሳል የሚባለው እንዴት ነው?

አቶ ሰለሞን፡- እንደሚታወቀው በትራንስፖርት ዘርፍ ነዳጅ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል፡፡ የዚያኑ ያህል በትራንስፖርት ዘርፍ ውስጥ በተለያየ መንገድ ነዳጅ ይባክናል፡፡ ይሰረቃል፡፡ ስለዚህ ያልተገባ የነዳጅ ወጪ ለማውጣት የሚገደዱ በርካቶች ናቸው፡፡ አሸከርካሪዎችና ባለንብረቶች በዚህ ሳቢያ ይጋጫሉ፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ ለነዳጅ ብክነት መፍትሔ አለው፡፡ በተለመደው አሠራር አንድ ተሽከርካሪ ስምሪት ከወጣ በኋላ እንዲህ ያለውን ነገር ለመቆጣጠር የሚችሉበት ዕድል አልነበረም፡፡ ጂፒኤስ የተገጠመለት ተሽከርካሪ ግን ምን ያህል ነዳጅ እንደተጠቀመ መረጃ ይሰጣል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ጂፒኤስ የገጠመለት ተሽከርካሪ፣ ለአደጋ ተጋላጭነቱ ይቀንሳል፡፡ ምክንያቱም የሾፌሮችን አነዳድ በቀላሉ መቆጣጠር ስለሚያስችል ነው፡፡ ባለንብረቱ ተሽከርካሪዬ ከዚህ በላይ ፍጥነት እንዳይኖረው እፈልጋለሁ ካለ በሚፈልገው የፍጥነት ወሰን መሠረት ሶፍትዌሩ እንዲሠራ በማድረግ አሽከርካሪውን መቆጣጠር ይችላል፡፡

ለምሳሌ አንድ የማሽን አከራይ ዶዘር ሊሆን ይችላል በቀን ምን ያህል ሰዓት እንደሠራ ለማወቅ ይህ ቴክኖሎጂ እገዛ ያደርግለታል፡፡ አንድን መኪና ለማስተዳደር የሚቸገሩ ሰዎች፣ በዚህ ቴክኖሎጂ ከተጠቀሙ 30 መኪኖች ቢኖራቸው እንኳ 30ውንም ካሉበት ሆነው መቆጣጠር ያስችላቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ተጨማሪ ንብረት እንዲያፈሩ መንገድ ይከፍትላቸዋል፡፡ ስለዚህ ለኩባንያዎች ዕድገትም አስተዋጽኦ አለው ማለት ነው፡፡ የእያንዳንዱን አሽከርካሪዎቻቸውን የሥራ አፈጻጸም በመረጃ ማግኘት ይችላሉ፡፡ ተሸከርካሪዎቹ ምን ያህል ደንበኞች ጋር ደረሱ? ምን ያህል ሸጡ? የቱ ጋ ቆሙ? ምን ያህል ሰዓት ፈጁ? ስለሚሉት ጥያቄዎቻቸው ሁሉ መረጃ ስለሚሰጣቸው፣ ቴክኖሎጂው በደንበኞችና በአሠሪዎች መካከል የግንኙነት ድልድይ ይፈጥራል፡፡ በዚህ ድልድይ መሠረት ሁሉንም ነገር በቀላሉ ማከናወን ይቻላል፡፡ ቴክኖሎጂው የሚያበረክተው ሌላው ዕድል ደግሞ የተሽከርካሪዎችን ስምሪትና አጠቃላይ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ድንበር የማይገድበው መሆኑ ነው፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ሆነው እያንዳንዱን የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ያስችላል፡፡   

ሪፖርተር፡- ቴክኖሎጂው ይህንን ያህል ጥቅም ካለው ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል ተቀባይነት አግኝቷል? ከአገራችን የሥራ ባህል በተለይም በትራንስፖርቱ ዘርፍ ውስጥ ከሚታየው የዘልማድ አሠራር፣ አሽከርካሪዎችም ሆኑ ባለንብረቶች እንዴት እየተቀጠሙበት እንደሚገኙ እናንተስ ጥቅሙን አሳውቃችሁ ለውጥ እንደመጣ መናገር የምትችሉበት ደረጃ ላይ ደርሳችኋል?

አቶ ሰለሞን፡- ይህ ቴክኖሎጂ የሰውን የማሰብ ብቃት ጭምር የሚያሳትፍ ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚህ ቀደም የምርት ኃይሎች የሚባሉት፣ የሰው ጉልበት፣ ገንዘብና መሬት ነበሩ፡፡ አሁን የምርት ኃይሎች ከሚባሉት ውስጥ የሰው የማሰብ ችሎታ ተካቷል፡፡ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መስክ አደጉ የምንላቸው አገሮች ከዚህ ቀደም ይጠቀሙበት የነበረው ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ በየጊዜው ተሻሽሎ የመጣው ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ግን ደግሞ አነስተኛ ወጪን የሚጠይቅ ነው፡፡ በዚህ ቴክኖሎጂ አንድ ሰው በኮምፒውተር ወይም በስማርት ስልክ አማካይነት የፈለጋቸውን ነገሮች ማከናወን እየቻለ በመምጣጡ፣ ለዚህ ቴክሎጂ የሚደረገው ኢንቨስትመንትም ብዙ ገንዘብ የሚፈልግ አይደለም፡፡ ስለዚህ ሰዎች እስካመኑበት ድረስ መጠቀም የሚያስችላቸውን ግንዛቤ ሊዳብሩ ይገባቸዋል፡፡ ይህ እንደየሰዎቹ ባህርይና አቅም ይወሰናል፡፡ ስለቴክኖሎጂው ጠቀሜታና አገልግሎት እኛ ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች አካላትም ሊያስተዋውቁት ይገባል፡፡ እኛ የምንችለው እንደ አንድ የቢዝነስ ተቋም ለአገር ሊጠቅም እንደሚችል፣ ኩባንያዎችም ከዚህ ቴክኖሎጂ የሚያገኙት ጠቀሜታ ለዕድገታቸው መሠረት እንደሆነ እንደሚቻለን መጠን ማሳወቅ ነው፡፡ በዚህ አገልግሎት መስፋፋት ኩባንያዎች ብቻ ሳይሆኑ መንግሥትም ሆነ ኅብረተሰቡ እንደሚጠቀሙ ለመግለጽ እንሞክራለን፡፡ በተለይ ደግሞ ዘመናዊ አሠራርን ከማጎልበት አንፃር የሚሰጠውን ዕድል እየገለጽን ነው፡፡ ድጋፍ ግን ያስፈልጋል፡፡ በቴክኖሎጂው የሚጠቀሙ ድርጅቶች አሉ፡፡ ለመጠቀም ገና የሚመጡም አሉ፡፡ ስለቴክኖሎጂው ያልተገነዘቡም አሉ፡፡ ብዙ መሥራትን ይጠይቃል፡፡  

ሪፖርተር፡- ስለቴክኖሎጂው አተገባበር በርካቶች ተገቢው መረጃ እንደሌላቸው ይታመናል፡፡ ለግንዛቤ ያህል ጂፒኤስ ምንድነው? እንዴትስ ነው እናንተ አገልግሎቱን የምትሰጡበት?

አቶ ሰለሞን፡- ጠቅለል ባለ መልኩ ስለጂፒኤስ አመጣጥ ትንሽ ልንገርህ፡፡ ቴክኖሎጂው የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋማት ሲሠሩበት የቆየ ነው፡፡ በአንድ አጋጣሚ ግን ይህንን ቴክኖሎጂ ለወታደራዊ አገልግሎት ብቻ ለምን እንጠቀምበታለን የሚል ሐሳብ ተነስቶ፣ ከአሥር ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ተደርጎበት ለምን ለሲቪል አገልግሎት አይውልም? በሚል መነሻ እ.ኤ.አ. በ1983 ጥቅም መስጠት ጀመረ፡፡ በቀደመው ጊዜ እነ ቫስኮ ደጋማ እነ ክርስቶፎር ኮሎምበስ ለአሰሳ ሲጓዙ፣ ትክክለኛውን ቦታ ለማግኘት ፀሐይን፣ ከዋክብትን ወይም ጨረቃን ምልክት እያደረጉ ነበር በኮምፓስ የሚጠቀሙት፡፡ አሁን ሁሉ ነገር ተለውጧል፡፡ ጂፒኤስ በየትኛውም ቦታ ከአራት ወይም ከዚያም በላይ ሳተላይቶች እያገዙት የሚሠራ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ 24 ሳተላይቶች ዓለምን ይዞራሉ፡፡ 2,200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሆነው 24ቱ ሳተላይቶች በዓለም ዙሪያ በሰዓት 14 ሺሕ ኪሎ ሜትር እየዞሩ፣ በ12 ሰዓት አንድ ጊዜ ዓለምን በመዞር ምድር ላይ የሚፈልጉትን አቅጣጫዎች በማሰስ መረጃ ያቀብላሉ፡፡ ቴክኖሎጂው ተቀባይ መሣሪያ ወይም ሪሲቨር አለው፡፡ ሳተላይቶቹ የሚረጩትን ጨረር ሪሲቨሩ ተቀብሎ ርቀቱ ስንት እንደሆነ ያሰላል፡፡ ሳተላይቶቹ ቦታውን ለይተው መረጃውን ወደ ሲም ካርድ በመላክ በሰርቨር አማካይነት ሰዎች የሚፈልጉትን ቦታ እንዲያገኙ፣ መኪናቸው ያለበትን ቦታ፣ የሚጓዝበትን የፍጥነት ወሰን፣ ወዴትና የት እንደሄደ የሚያመላክቱ መረጃዎችን እንዲያገኙ ይረዳቸዋል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የጂፒኤስ አልግሎትን ያነሳነው ተሽከርካሪዎች ላይ ተገጥሞ በመሥራት ላይ ካለው ቴክኖሎጂ አኳያ ነው፡፡ ከገለጻዎ መረዳት እንደቻልኩት የጂፒኤስ አገልግሎቶች በርካታ እንደሆኑ ነው፡፡ በአገራችን በዚህ ቴክኖሎጂ ልንጠቀምባቸው የምንችላቸው ሌሎች አገልግሎቶች ምንድን ናቸው?

አቶ ሰለሞን፡- ከሁሉም የቢዝነስ ዘርፎች ጋር የተያያዘ አገልግሎት ይሰጥበታል፡፡ ለብዙ ነገር ልትጠቀምበት ትችላለህ፡፡ አሁን የምናወራው ከተሽከርካሪዎት አንፃር ሆነና ሐሳባችንን መሰብሰብ አስፈለገን እንጂ፣ ከዚህ ቢዝነስ ውጪ ያሉ ዘርፎችንም ቴክኖሎጂው ይደግፋል፡፡ በተሽከርካሪዎችም ቢሆን አገልግሎቱ የተለያየ ነው፡፡ ለምሳሌ ከተሽከርካሪዎች ደኅንነት አንፃር ስንመለከተው፣ አጠቃላይ የትራንስፖርቱ ዘርፍ ጂፒኤስ መጠቀም ቢችል ኑሮ የአገሪቱን የተሽከርካሪ አደጋዎች ቁጥር መቀነስ የሚቻልበት ዕድል አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን በደንብ ቢያብራሩት፡፡

አቶ ሰለሞን፡- ለምሳሌ የጂፒኤስ አገልግሎትን ከመገኛ ብዙኃን ሥራ ጋር አገናኝተህ ልትተገብረው ትችላለህ፡፡ ሌሎች መንገዶችም አሉ፡፡ የት አካባቢ የትራፊክ መጨናነቅ እንዳለ በመመልከት መረጃውን ተሽከርካሪዎቹ ቀድመው እንዲያገኙት ማድረግ ትችላለህ፡፡ የቱ ጋር ዝናብ ሊዘንብ ይችላል? የሚለውንና የመሳሰሉትን መረጃዎች አሽከርካሪዎች እንዲያገኙ በማድረግ አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ ለማድረግ ያስችላል፡፡ አመቺ ያልሆኑ ወይም አደጋ የተከሰተባቸው ቦታዎች ሲኖሩም አሽከርካሪው በምን ያህል ፍጥነት መጓዝ እንዳለበትና ጥንቃቄ እንዲያደረግ የሚያሳስቡ መረጃዎችን ታስተላልፍበታለህ፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ፈተና የሆነው የትራፊክ ማኔጅመንት ነው፡፡ የትራፊክ ፍሰቱ የተጨናነቀ ነው፡፡ ይህንን ለማስተካከል ቴክኖሎጂው በምን መልኩ ሊጠቅም ይችላል?

አቶ ሰለሞን፡- ሌሎች አገሮች በዚህ ቴክኖሎጂ ይጠቀሙበታል፡፡ ተሽከርካሪው አደጋ ሲኖር መረጃ ቀድሞ እንዲያገኝ በማድረግ ከአደጋ እንዲጠበቅ ያደርጋሉ፡፡ የተጨናነቀ የትራፊክ ፍሰት ካለ፣ አሽከርካሪዎች በዚያ መስመር እንዳይገቡ ያደርጋል፡፡ አማራጮችን ይሰጣል፡፡ ጂፒኤሱን በመጠቀም ማሳወቅ ይቻላል፡፡ ትልቅ እገዛ ያደርጋል፡፡ እዚህ አገር በጂፒኤስ መጠቀም ካልተቻለ በቀር ለስንቱ መኪና የትራፊክ ፖሊስ አቁመህ ትችላለህ? ሕዝቡ ብዙ ነው፡፡ ተሽከርካሪውም እየበዛ ነው፡፡ የትራፊክ መጨናነቁን ስታየውም ይህንን ማኔጅ ለማድረግ በጂፒኤስ የተደገፈ ሥራ መሠራት እንደሚያስፈልግ ያሳይሃል፡፡

ሪፖርተር፡- የእኛ አገር ተሽከርካሪዎች በዚህ ቴክኖሎጂ መጠቀም የሚችሉበት አመቺ ሁኔታ ተፈጥሯል? መሠረተ ልማቱስ ተዘርግቷል?

አቶ ሰለሞን፡- መሠረተ ልማቱማ አለ፡፡ ይህንን መጠቀም የሚያስችሉ ዕድሎችም አሉ፡፡ ብዙ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅም አይደለም፡፡ ብዙ የሚፈልግ ነገር አይደለም፤ ቢሮ ውስጥ የምታደራጀው ነገር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጂፒኤስ ቴክኖሎጂውን እንዴት እየተጠቀማችሁበት ነው? ከኢትዮቴሌኮም ጋር ያላችሁ ግንኙነትስ እንዴት ነው?

አቶ ሰለሞን፡- የምናስመጣቸው የጂፒኤስ ቴክኖሎጂዎች በኢትዮቴሌኮም ፈቃድ አግኝተን ነው፡፡ የምንጠቀመውም የቴሌን ሲም ካርድ ነው፡፡ ሁሉም ደንበኞች መረጃዎችን የሚያገኙት የቴሌን ሲም ካርድ ተጠቅመው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከወራት በፊት አገሪቱ ውስጥ ተፈጥሮ በነበረ አለመረጋጋት ጂፒኤስ ያስገጠሙ ኩባንያዎች አገልግሎት ተቋርጦባቸው ስለነበር ተሽከርካሪዎቻቸውን መቆጣጠር አልቻሉም ነበር፡፡ እንዲህ ያለው መቆራረጥ አገልግሎቱን በምን መልኩ ይጎዳዋል? ከፀጥታ አኳያ ችግር ቢፈጠርና ኔትወርክ ቢቋረጥ አገልግሎቱን ለማስቀጠል አማራጩ ምንድን ነው?

አቶ ሰለሞን፡- በዚህ አገልግሎት ዙሪያ ሁሉም ባለድርሻ አካላት አጽንኦት ሊሰጡበት ይገባል፡፡ ባለፉት ሦስት ወራት አገልግሎቱ በመቋረጡ እኛን ጎድቶናል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ማግኘት የሚባውን ገንዘብ ማግኘት አልቻለም፡፡ ተገልጋዮችም ንብረታቸውን ለመቆጣጠር አልቻሉም፡፡ ደንበኞች ወጪ ያደረጉበትን አገልግሎት ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ እንዲህ ያለ ነገር ሲፈጠር ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማነጋገር እንዴት ጉዳቱን መቀነስ እንደሚቻል በውይይት ማስተካከያ ማድረግ ይቻላል፡፡ ከዚህ በኋላም እንዳይደገም መመካከሩ ግድ ይላል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ቴክኖሎጂውን ለማስፋፋት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ዘመናዊ አገልግሎትን ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት ላይ እንቅፋት ሊፈጥር ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ቴክኖሎጂው እየተገጠመ ያለው በትላልቅ ተሽከርካሪዎች ላይ ነው፡፡ በታክሲዎችና ሌሎችም ተሽከርካሪዎች ላይ ለምንድን ነው ሲዘወተር የማይታየው?  ምርቶችን በሚያከፋፍሉትስ ረገድ ቴክኖሎጂው ምን ዓይነት ድጋፍ መስጠት ይችላል?

አቶ ሰለሞን፡- ቴክኖሎጂው በመንግሥት መደገፍ አለበት፡፡ በከተማ ታክሲዎችም ሆነ በአውቶብሶች ብሎም በሁሉም ላይ ገጥሞ መሥራቱ ብዙ ጠቀሜታ አለው፡፡ ጂፒኤስ የሚሰጠው መረጃ በርካታ ነገሮችን ያቃልላል፡፡ አንድ ተሽከርካሪ አደጋ ቢያደርስ የአደጋውን መንስዔ ለማወቅ የሚደረጉ ምርመራዎችን ለማፋጠን ይረዳል፡፡ ምክንያቱም ጂፒኤስ የተገጠመለት ተሽከርካሪ በምን ያህል ፍጥነት ይሽከረከር እንደነበር በቀላሉ ታውቃለህ፡፡ መረጃውንም በሰነድ አትሞ ማውጣት ይችላል፡፡ ሁሉንም የጉዞ ታሪክ ያስቀምጣል፡፡ ከሕግ አንፃር ድጋፍ ይሰጣል፡፡ መንግሥትን ይጠቀማል፡፡ ዋናው የእኛ ዓላማም ይኼው ነው፡፡ ጂፒኤስ ሲባል እኮ መኪናውን ብቻ አይደለም የምትቆጣጠረው፡፡ መኪናዎቹ ሲንቀሳቀሱ ይዘውት የማሄዱትንም ምርት ነው፡፡ ለምሳሌ መድኃኒት ስታከፋፍል ለማን ሰጡ፣ እንዴት ሰጡ የሚለውን ሁሉ ታያለህ፡፡ የዕርዳታ ድርጅት ዕርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎቹ በትክክል ለተረጂው ስለማድረሳቸው ለመቆጣጠር የሚቻልበት አንዱ መንገድ እኮ ይህ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ብዙዎች ግን ስለ ቴክኖሎጂው ዕውቀት የላቸውም፡፡ ፍራቻም አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ቴክኖሎጂው ይህንን ያህል ጠቀሜታ ካለውና የትኛውንም ወገን ከጠቀመ ተገልጋዮች ለምን አላፈራም? ለአገልግሎቱ የሚጠየቀው ዋጋ መብዛት ምክንያት ሊሆን ይችላል?

አቶ ሰለሞን፡- ነፃ ገበያ ስለሆነ ሁላችንም ተወዳድረን ነው ዋጋ የምንሰጠው፡፡  ብዙ ግን ከሚሰጠው ጥቅም አንፃር ክፍያው አነስተኛ ነው፡፡ ዋናው ነገር ቴክኖሎጂውን ከሸጥን በኋላ የምንሰጠው ድኅረ አገልግሎት ነው፡፡ ደንበኛህን መጠበቅ መቻል አለብን፡፡ ያለውን በደንብ ስለያዝነው ህልውናችንን ማቆየት ችለናል፡፡ እንደ መሣሪያው ዓይነት ዋጋውም ይለያል፡፡ ለአንድ ተሽከርካሪ የሚገጠሙ ጂፒኤስ ከ5,000 እስከ 8,000 ብር ይጠይቃል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የወጣበትን ተሽከርካሪ በዚህ ዋጋ መጠበቅ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ባለፈው ጊዜ ለሦስት ወር ያህል የጂፒአርስ ኔትወርክ ሲቆም ገቢያችን መቀነሱ ብቻ ሳይሆን፣ ተገልጋዮች ንብረታቸውን ለመቆጣጠር አለመቻላቸው ጎድቷቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በቴሌኮም ኔትወርክ መቋረጥ ብቻም ሳይሆን ከዚህ ውጪ ባሉ ጉዳዮች አገልግሎቱ ሊቋረጥ የሚችልባቸው ሌሎች መንስዔዎች የሉም? የአገልግሎቱ ሽፋንስ ምን ይመስላል?

አቶ ሰለሞን፡- ከቴሌኮም ኔትወርክ ውጭ ከሆነ የተቋረጠው ችግሩ የእኛ ይሆናል፡፡ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል ኔትወርክ አለ፡፡ አሁን እኮ ኦሞ ሸንኮራ ፋብሪካ ላይ ጂፒኤስ ተገጥሞ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በዚያ መስመር መኪኖቻቸው ላይ ጂፒኤስ ያስገጠሙ ድርጅቶች እንደልብ መቆጣጠር ችለዋል፡፡ ኔትዎርኩ ባይኖር ኑሮ ንብረታቸውን መቆጣጠር አይችሉም ነበር፡፡ ይህ መልካም ነገር ነው፡፡ ቴክኖሎጂውን እንዴት እንጠቀምበት የሚለውን ማሰብ አለብን፡፡ ተሽከርካሪዎቻቸውን ሩቅ ቦታ ያሰማሩ ድርጅቶች ንብረታቸውን ያለ ችግር መቆጣጠር ችለዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ መኪኖች ከተከለለላቸው ቦታ ውጭ ሲወጡም ሆነ ሲገቡ ባለንብረቱ ወዲያው መረጃ የሚያገኝበት አገልግሎት ተፈጥሯል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ለአንድ ፕሮጀክት ሥራ የተላከ መኪና ከፕሮጀክቱ አጥር ውጭ ሲወጣ የሚያሳየውን መረጃ ይዘህ ወዲያውኑ ተመለስ ማለት ትችላለህ፡፡ ከዚህ ሥፍራ ውጭ ተሽከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ የሚያደርግ ፕሮግራም ከጫንክ በዚያ መሠረት ስለሚሠራ የሚፈጠር ችግር አይኖርም፡፡ ተሽከርካሪው የመጨረሻው ፍጥነት ወሰን 80 ኪሎ ሜትር መሆን አለበት ካልክና አሽከርካሪው ከ80 ኪሎ ሜትር በላይ በሰዓት እየነዳ ከሆነ፣ ከተቀመጠለት ፍጥነት በላይ መጓዙን የሚገልጽ ሪፖርት ይደርስሃል፡፡ ሌላው ተሽከርካሪን ለመጠገን፣ ጎማ ለመቀየር ስትፈልግ፣ ይህንን መቼ እንደምታደርግ ለሶፍትዌሩ በምትሰጠው መረጃ መሠረት ጊዜው ሲደርስ ይጠቁምሃል ማለት ነው፡፡ አስታዋሽ ነው ማለት ነው፡፡ መኪናህ ለስንት ሰዓት ቆሞ እንደነበር ሁሉ ይነግርሃል፡፡ ኢንሹራንስ ኩባንያዎችም ጂፒኤስ ለተገጠመላቸው ተሽከርካሪዎች የመድን ዋጋ ይቀንሳሉ፡፡ ምክንያቱም ጂፒኤስ የተገመለት ተሽከርካሪ አደጋ የማድረስ ዕድሉ ካልተገጠመለት መኪና ያነሰ በመሆኑ፣ እንዲህ ላሉት ተሽከርካሪዎች የሚያስከፍሉትን ዓረቦን ቅናሽ አለው፡፡  

ሪፖርተር፡- ጂፒኤስ ስለተገጠመለት ብቻ የኢንሹራንስ ክፍያው ይቀንሳል ማለት ነው?

አቶ ሰለሞን፡- አዎ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህንን አሠራር ለመተግር እየተሞከረ ነው፡፡ እነዚህን ተሽከርካሪዎች ኢንሹራንስ ኩባንያዎች መከታተል የሚችሉበት ዕድል አላቸው፡፡ አደጋ ቢደርስ ስለአደጋው ሙሉ መረጃ እንዲኖራቸው ያግዛቸዋል፡፡ አደጋው እንዴት ደረሰ የሚለውን ለማወቅ ይረዳቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የሚሩበት የመረጃ ሥርዓት ክፈትት ነበረበት፡፡ አሁን ግን በማስረጃ የተደገፈ መረጃ ስለሚኖራቸው የተሽከርካሪውን ታሪክ በቀላሉ አግኝተው መረጃውን ያጠናቅራሉ፡፡ ይህንን ሥራ በመድን ድርጅቶች ለመተግበር ሒደቶች ተጀምረዋል፡፡ ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት ጋር የጀመርነው ሥራም አለ፡፡ በነገርህ ላይ ለባንኮችም ይጠቅማቸዋል፡፡ ገንዘባቸውን ሲያንቀሳቅሱ በቀላሉ ሊቆጣጠሩ ይችላሉ፡፡ የገንዘቡን ፍሰት ከማዕከል ሆነው ያለ ችግር መቆጣጠር ይችላሉ፡፡ 

Standard (Image)

መድን ድርጅቶች በሕይወት መድን ሽፋን ዝቅተኛውን ደረጃ ይዘዋል

$
0
0

 

የኢትዮጵያ የመድን ኢንዱስትሪ፣ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያበረከተው አስተዋጽኦ አነስተኛ ከመሆኑ ባሻገር፣ የአገልግሎት ሽፋኑም ከሚጠበቀው ይልቅ አነስተኛ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በኢንዱስትሪው ውስጥ የሚንቀሳቀሱ 17 ኩባንያዎች ዓመታዊ የትርፍ መጠንም አነስተኛ ሆኖ ይገኛል፡፡

የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ዓመታዊ ትርፍ ከባንኮች ዓመታዊ ትርፍ ጋር ማነፃፀር ካስፈለገም፣ የመድን ኩባንያዎች አፈጻጸም አዝጋሚ ጉዞ እንደሚታይበት ያመላክታል፡፡ ሐሙስ ግንቦት 3 ቀን 2009 ዓ.ም. በተደረገ ውይይት፣ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን ጉዞ በዋናነትም በኢንሹራንስ አገልግሎት ደላሎች ዙሪያ በቡና ኢንሹራንስ ኩባንያ አክሲዮን ማኅበር አስተባባሪነት በተሳናደው መድረክ አስተያየት የሰጡ ባለሙያዎችም ይህንኑ ያረጋግጣሉ፡፡   

መድን ኢንዱስትሪው ከሌሎች አገሮች አኳያ

ቡና ኢንሹራንስ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ፣ የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ የሚገኝበትን ደረጃ ለማመላከት፣ በተለይም በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ፋይዳ ምን ያህል እንደሆነ የሚጠቁሙ አኃዛዊ መረጃዎችና አስተያየቶች ተስተናግደዋል፡፡ የቡና ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳኛቸው መሓሪ ኢንዱስትሪውን በተመለከተ ባደረጉት ንግግር፣ የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ዘርፍ ምን ያህል ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማመላከት መንደርደሪያ ያደረጉት፣ ከወራት በፊት የአገሪቱን የፋይናንስ ኢንዱስትሪ በተዘጋጀ ፕሮግራም ወቅት ተከስቶ እንደነበር የጠቀሱትን አጋጣሚ በማስታወስ ነው፡፡  

የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ዕድገት ሲጠቀስ በአብዛኛው ባንኮች ለኢኮኖሚው ዕድገት ያደረጉትን አስተዋጽኦ ባወሳው መድረክ ላይ የመድን ድርጅቶች ድርሻ ሳይጠቀስ መታለፉን የገለጹት አቶ ዳኛቸው፣ የፋይናንስ ተቋማት ሲጠቀሱ ግን የኢንሹራንስ ኩባንያዎችም ተካተው ቢሆንም፣ የኩባንያዎቹ አስትዋጽኦ ኢምነት መሆኑ በየመድረኩ ሳይጠቀሱ እንዲታለፉ እያደረጋቸው መሆኑ የመድን ዘርፉን ተዋናዮች ከንክኗቸዋል፡፡ በመድን ኢንዱስትሪው ‹‹ምን የሚነገር ነገር ሠራችሁና ነው፤›› እንደሚባሉም ጠቅሰዋል፡፡ ይህ አባባል ኢንዱስትሪው ምን ያህል ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና ዝቅተኛ ግምት እንደሚሰጠው ያሳያል ያሉት አቶ ዳኛቸው፣ ኢንዱስትሪው ለኢኮኖሚው ያለው አስተዋጽኦ የ0.5 በመቶ ድርሻ ብቻ መሆኑ ለዚህ አባባል ምክንያት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

‹‹የአገራችን የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ አሁን ባለበት ደረጃ ሲገመገም ከአጠቃላይ የአገሪቱ ጠቅላላ ምርት አኳያ ያለው አስተዋጽኦ 0.5 በመቶ ብቻ ሲሆን፣ ይህ ምጣኔ የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነፃፀር እጅግ ዝቅተኛ ሆኖ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡ በምሳሌ ሲሳዩም፣ የሞሮኮ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ከአገሪቱ ኢኮኖሚ የሦስት በመቶ፣ የናይጄሪያ 0.6 በመቶ፣ የደቡብ አፍሪካ 15.4 በመቶ እንዲሁም የኬንያ 3.5 በመቶ ድርሻ አለው፡፡ ከዓረቦን ገቢ አንፃር የ2007 ዓ.ም. አኃዞችን መሠረት ያደረገው የሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፣ በሞሮኮ የተመዘገው የኢንዱስትሪው ገቢ 3.18 ቢሊዮን ዶላር፣ በናይጄሪያ 1.8 ቢሊዮን፣ በደቡብ አፍሪካ 5.4 ቢሊዮን፣ በኬንያ 1.52 ቢሊዮን ዶላር ሲያስመዘግብ፣ በኢትዮጵያ ግን 219 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ተመዝግቦበታል፡፡

‹‹ከዚህ መረጃ ለመገንዘብ እንደሚቻለው የእኛ ኢንዱስትሪ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መገንዘብ ይቻላል፤›› ያሉት አቶ ዳኛቸው፣ እያንዳንዱ ባለድርሻ ማድረግ ስለሚጠበቅበት አስተዋጽኦ ማሰብ እንደሚጠቅበት አሳስበዋል፡፡ የቡና ኢንሹራንስ የገበያ የንግድ ልማት ሥራ አስኪያጅ አቶ እንዳልካቸው ተስፋዬ ባቀረቡት ጽሑፍ ኢንዱስትሪው የሚገኝበትን ደረጃ አመላክተዋል፡፡

ከሞተር የተዋደደው ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ

ዓምና 17ቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሰበሰቡት ዓረቦን (ፕሪሚየም) 6.4 ቢሊዮን ብር እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ በዚሁ ዓመት የኬንያ 49 ኩባንያዎች ግን ሁለት ቢሊዮን ዶላር የዓረቦን ገቢ ሰብስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ መድን ኩባንያዎች በበጀት ዓመቱ ከሰበሰቡት 6.4 ቢሊዮን ብር ዓረቦን ውስጥ ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ የተገኘው ስድስት ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ቀሪው ከሕይወት ነክ ዘርፍ የተሰበሰበ ነው፡፡ ይህም የኢንሹራንስ ዘርፉ የተመሠረተው ሕይወት ነክ ባልሆኑ የኢንሹራንስ ፖሊሲዎች ላይ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

ከአጠቃላይ የኢንሹራንስ ዘርፍ ከተሰበሰበው ስድስት ቢሊዮን ብር ውስጥ፣ 3.2 ቢሊዮን ብር ከሞተር ኢንሹራንስ የተገኘ ነው፡፡ ያለፉት አሥር ዓመታት የነበረው የሁሉም ኩባንያዎች መረጃ እንደሚያሳየውም፣ በአማካይ ከ60 በመቶ በላይ የኢንዱስትሪው የመድን ሽፋን በሞተር ወይም በተሽከርካሪ የመድን ዋስትና የተመሠረተ እንደሆነ ነው፡፡ ለኢንዱስትሪው ማደግም ሆነ ማሽቆልቆል ለሞተር መድን የሚሰጠው ሽፋን ትልቁን ሚና እንደሚጫወት አንዱ ማሳያም ይኸው አፈጻጸም ነው፡፡

ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ኢንዱስትሪው በአማካይ የአሥር በመቶ ዕድገት እያሳየ ቢመጣም፣ በመካከሉ እስከ ሦስት በመቶ የወረደ ዕድገት የተመዘገበበት ጊዜም ይጠቀሳል፡፡ በ2006 ዓ.ም. ግን ኢንዱስትሪው ሳይታሰብ የ55 በመቶ ዕድገት አሳይቶ ነበር፡፡ ይህም ከአገሪቱ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ጉዞ ከፍተኛው የዕድገት መጠን ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ይህን ያህል ዕድገት በአንድ ዓመት ብቻ ሊመዘገብ የቻለው ግን አስገዳጁ የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን ተግባራዊ የተደረገበት ወቅት በመሆኑ እንደነበር አቶ እንዳልካቸው አስታውሰዋል፡፡ በሌላ ጎኑ ኩባንያዎቹ በሌሎች የመድን ዋስትናዎች ላይ ደካማ መሆናቸውን ያሳየ ክስተትም ተደርጓል፡፡  

እንደ አቶ እንዳልካቸው ገለጻ፣ በአገሪቱ ከተከፈቱ 420 የመድን ኩባንያዎች ቅርንጫፎች ውስጥ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ቅርንጫፍ ያላቸው ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ በአብዛኛው በከተማና ከተማ ነክ በሆኑ ቦታዎች የተወሰኑ ናቸው፡፡ ከተደራሽነት አኳያ መድን ድርጅቶች ደካማ እንደሆኑ ያሳያል፡፡

ከዓለም የተለየው ኢንዱስትሪ

የኢትዮጵያን የመድን ኢንዱስትሪ ከሌሎች አገሮች የሚለየው ዓቢይ ጉዳይ የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋኑ ነው፡፡ በበርካታ አገሮች ውስጥ ከፍተኛው የዓረቦን ገቢ የሚሰበሰበው ከሕይወት ኢንሹራንስ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በኢትዮጵያ ግን ተቃራኒው ነው የሚታየው፡፡  

አቶ እንዳልካቸው እንደጠቀሱት፣ የኢትጵያ የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን ከስድስት በመቶ በታች ነው፡፡ ለዚህ አስረጂ ያደረጉት ዓምና የነበረውን አፈጻጸም ነው፡፡ ከጠቀላላው የመድን ዓረቦን ውስጥ የሕይወት ኢንሹራንስ ድርሻ 5.2 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ይህም ከዓለም አቀፉ አሠራር ጋር በተፃራሪው የሚቀመጥ ነው፡፡ በሌሎች አገሮች የሕይወት ኢንሹራንስ ድርሻ ሕይወት ነክ ካልሆነው አብላጫ አለው፡፡ በኢትዮጵያ ግን ከ95 በመቶ በላይ የኢንሹራንስ ሽፋን ሕይወት ነክ ላልሆነው ቁሳዊ ንብረት የሚውል ነው፡፡

ከጠቅላላው የዓረቦን ገቢም ከ54 በመቶ በላይ ከሞተር ኢንሹራንስ የተሰበሰበ በመሆኑ፣ የኩባንያዎቹ አገልግሎት በአብዛኛው በሞተር ኢንሹራንስ ሥራ ላይ የተንጠለጠለ መሆኑን አመልክቷል፡፡ በሌሎች አገሮች ውስጥ የሞተር ኢንሹራንስ ይህንን ያህል ድርሻ እንደማይዝ የሚጠቀሱት የዘርፉ ባለሙያዎች፣ የኢትዮጵያ መድን ኢንዱስትሪ በዚህ ረገድ ከዓለም የተለየ የገበያ አካሄድ እንደሚታይበት ይስማሙበታል፡፡

በአመዛኙ በሞተር ኢንሹራንስ ሽፋን ላይ የተጠለለው ይህ ኢንዱስትሪ፣ ከፍተኛ ውድድር ይስተናገድበታል፡፡ ሁሉም ኩባንያዎች በሞተር መድን ሽፋን ረገድ የየራሳው የገበያ ድርሻ አላቸው፡፡ በኢንዱስትሪው ውስጥ ከ40 ዓመት በላይ የቆየው መንግሥታዊው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት፣ ከ22 ዓመታት ወዲህ ከተቋቋሙት ከ16ቱ የግል ኩባንያዎች ጋር የሚያደርገው ውድድር እያየለ መምጣቱም እየተስተዋለ ነው፡፡ በብዙ ጊዜ በበላይት የቆየበትን የገበያ ድርሻ ለግሎቹ ማካፈል ግድ ሆኖበታል፡፡ ከአሥር ዓመት ወዲህ ካለው የየኩባንያዎቹ የገበያ ድርሻ መረጃ መረዳት እንደተቻለው፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ድርሻ በ2008 ዓ.ም. እንኳ ወደ 35 በመቶ ወርዷል፡፡

በኢትዮጵያ ሚሊኒየም ማለትም በ2000 ዓ.ም. 42.7 በመቶ የነበረው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የገበያ ድርሻ እስከ 2006 ዓ.ም. ባሉት ዓመታት ውስጥ በአማካይ 42 በመቶ ላይ ቢቆይም በ2006 ዓ.ም. ማገባደጃ ወደ 40 በመቶ ዝቅ ማለት ጀምሯል፡፡ ካቻምና ወደ 37.2 በመቶ ሲቀንስ፣ ዓምና ወደ 35.6 በመቶ ዝቅ በማለት በየጊዜው የገበያ ድርሻው ከበፊቶቹ ዓመታት ይልቅ እያነሰ እንደመጣ አኃዞቹ ይናገራሉ፡፡

እንደ አቶ እንዳልካቸው ማብራሪያ፣ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መድን ድርጅትን ጨምሮ ሰባት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከአጠቃላይ ገበያ ውስጥ የ74 በመቶውን ከፍተኛ ድርሻ ተቀራምተዋል፡፡ የተቀሩት አሥር ኩባንያዎች 26 በመቶውን ይጋራሉ፡፡

የኢንዱስትሪው የፋይናንስ አፈጻጸም

የአቶ እንዳልካቸው ጽሑፍ፣ የኢትዮጵያ የመድን ኢንዱስትሪ አትራፊ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ይሁንና የሚገኘው ትርፍ ግን ከኢንዱስትሪው ሊገኝ ከሚችለው አኳያ ዝቅተኛ የሚባለው ነው፡፡

በ2002 ዓ.ም. የሁሉም ኩባንያዎች የተጣራ ትርፍ 235.18 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ዕድገቱን ጨምሮ፣ በ2006 ዓ.ም. ወደ 823.5 ሚሊዮን ብር ማሻቀብ ችሏል፡፡ ካቻምናም አሥር ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ጭማሪ በማሳየት የ835.3 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ ይህ መጠን ባንኮች ከሚያገኙት አንፃር ሲታይም የመድን ድርጅቶቹ አፈጻጸም ዝቅተኛ ተብሏል፡፡

17ቱ ኩባንያዎች በአንድ ዓመት ያስመዘገቡት 835.3 ሚሊዮን ብር በአሁኑ ወቅት አንድ የግል ባንክ ለብቻው ከሚያገኘው ትርፍ ያነሰ ነው፡፡ ‹‹እንደ አዋሽ ባንክ ያሉት አንድ ቢሊዮን ብር ድረስ ማትረፍ ችለዋል፤›› ያሉት አቶ እንዳልካቸው፣ መድን ድርጅቶች ግን በጠቅላላው ተደምረው እንደ ባንክ ከሚያገኘው ትርፍ በታች ማስመዝገባቸው ምን ያህል ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ አመላካች ሆኗል፡፡

በአንፃሩ በ2008 መጨረሻ የነበረው የ17ቱም ኩባንያዎች ሀብት 11.5 ቢሊዮን ነበር፡፡ ይህ መጠን በ2000 ዓ.ም. ከነበረው ጋር ሲነፃፀር፣ ከሁለት እጥፍ በላይ ማደጉ ተጠቅሷል፡፡ በ2002 ዓ.ም. የተመዘገበው የሀብት መጠናቸው 3.2 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ የሚሰበስቡት ዓረቦን እየጨመረ ቢመጣም ለካሳ ክፍያ የሚያወጡት መጠን እየጨመረ በመምጣቱ፣ ዓምና 6.4 ቢሊዮ ብር ዓረቦን ቢሰበስቡም፣ ለካሳ ክፍያ ግማሹን ማለትም 3.09 ቢሊዮን ብር እንደከፈሉ በዕለቱ ይፋ ከተደረገው መረጃ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት የሁሉም ድርጅቶች ካፒታል መጠን 1.18 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ወደ 3.5 ቢሊዮን ብር እንዳደገ ተገልጿል፡፡

የኢንዱስትሪው ፈተናዎች

ለመድን ኩባንያዎቹ አዝጋሚ ጉዞ ብሎም ዝቅተኛ አፈጻጸም ምክንያቶች የነበሩ ጉዳዮች ቀርበዋል፡፡ የቡና ኢንሹራንስ ሥራ አስፈጻሚ ከሚጠቅሷቸው መካከል፣ የኢንዱስትሪው ተዋናዮች ደካማ የኩባንያና የንግድ አመራር እንዲሁም የባለሙያ ዕጥረት ሚዛን የሚደፉት ችግሮች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ኢንዱስትሪው ስላሉበት ችግሮች ባለድርሻዎችን እየጠራ አለማማከሩ አንዱ ክፍተት ሆኗል፡፡

የደላሎቹ ሚና

የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው በኩባንያዎቹ እንቅስቃሴ ብቻ የሚራመድ ባለመሆኑ፣ ከኩባንያዎቹ ጋር የሚሠሩ የኢንሹራንስ ደላሎች፣ የሽያጭ ሠራተኞችና ሌሎችም ሚና አላቸው፡፡ በተለይም ደላሎች ለመድን ገበያ መስፋፋት ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ እንደ ባንክና መድን ድርጅቶች፣ የኢንሹራንስ ደላሎችም ሥራቸውን የሚያከናውኑት፣ ብሔራዊ ባንክ በሚሰጣቸው ፈቃድና ዕውቅና መሠረት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ደላሎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ውበቱ ወርቅነህ እንደገለጹትም፣ በመድን ኢንዱስትሪው ውስጥ ደላሎች ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ የንግድ ሕጉም የኢንሹራንስ ደላሎችን ሚና ይደነግጋል፡፡

በኢንሹራንሶች አሠራር ሕግ መሠረት፣ እያንዳንዱ ደላላ ለሁሉም ኩባንያዎች መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ የሚያመጣውንም ሥራዎች ለኩባንያዎች የሚሰጠው፣ በሚያቀርቡለት ዋጋ ላይ ብቻ ተመሥርቶ ሳይሆን፣ በኩባንያዎቹ አቅም መሠረት እንደሆነም ተብራርቷል፡፡

ሁሉም ደላሎች ለ17ቱም ድርጅቶች በተገቢው መንገድ መሠራት ሲገባቸው በተወሰኑት ላይ ብቻ አተኩረው እንደሚሠሩ የጠቀሱ ባለሙያዎችም ደላሎቹን ተችተዋል፡፡ የኢንዱስትሪው ተዋናዮች የቡና ኢንሹራንስን ፈለግ በመከተል በቋሚነት የውይይት መድረክ ለማዘጋጀትና በችግሮቻቸው ዙሪያ እየመከሩ መትሔዎችን ለማፈላለግ ተስማምተዋል፡፡ 

 

Standard (Image)

በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ላይ ያተኮረ ዓውደ ርዕይ ሊካሄድ ነው

$
0
0

 

በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ አገልግሎት ሰጭ ኩባንያዎችና የሚመለከታቸው ከ200 በላይ የመስኩ ተዋናዮች የሚሳተፉበት ‹‹ኢትዮ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ›› የተሰኘ ስያሜ የተጠሰው ዓውደ ርዕይ በሚሊኒየም አዳራሽ ሊካሄድ ዝግጅት መጀመሩ ተገለጸ፡፡

በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ መስክ ላይ በማተኮር ሲካሄድ የመጀመሪያው እንደሆነ የተጠቀሰው ይህ ዓውደ ርዕይ ከነሐሴ 12 እስከ ነሐሴ 14 ቀን 2009 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ እንዲካሄድ ዝግጅቱን የሚሰናዳው ኢትዮ ኃይላንድ ማራቶን የተባለና በንግድ ትርዓቶች ማሰናዳት ዘርፍ የተሠማራው ኩባንያ ነው፡፡

የኩባንያው ኃላፊዎች ስለሚዘጋጀው ዓውደ ርዕይ ሐሙስ ግንቦት 3 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ በአገሪቱ በትራንስፖርትና በሎጂስቲክስ መስክ የተሠማሩ ከ200 በላይ ተሳታፊዎችን ጨምሮ ከ15 ሺሕ ያላነሱ ጎብኝዎች በዓውደ ርዕዩ እንደሚታደሙ ይጠበቃል፡፡

የዓውደ ርዕዩ አዘጋጅ ድርጅት የቦርድ አባል አቶ እሥራኤል ተስፋዬ እንዳስታወቁት፣ ከዚህ ዓመት ጀምሮ በቋሚነት በሚሰናዳው ዓውደ ርዕይ፣ ለዘርፉ ተዋናዮች መተዋወቂያና የገበያ ዕድል መፍጠሪያ ከመሆን ባሻገር በዘርፉ ልዩ ልዩ ተሞክሮ ያላቸው አካላት ልምድ የሚለዋወጡበት መድረክ ይሆናል፡፡ በዓውደ ርዕዩ ከሚጠበቁት መካከል የሕዝብና የዕቃ ማጓጓዣ አገልግሎት ሰጭዎች ማለትም፣ በየብስ በአየር፣ በባህር፣ እንዲሁም በባቡር ትራንስፖርት መስክ የሚንቀሳቀሱ አካላት እንደሚታደሙበት ይጠበቃል፡፡

ከእነዚህ በተጨማሪም የወደብ አገልግሎት ሰጪዎች፣ ዕቃ አስተላላፊዎች፣ ዕቃን የማጓጓዝና ለጉዞ የማመቻቸት አገልግሎት የሚሰጡ (በኮንቴይነር የሚያሽጉ)፣ የመጋዘን አገልግሎትና አስተዳደር ሥራዎችን የሚሠሩ፣ የተሽከርካሪ እንዲሁም የመለዋወጫ አምራቾች፣ አስመጪዎችና ላኪዎች፣ ጋራዦች፣ የንግድ ወኪሎች፣ ነዳጅ አቅራቢዎች፣ ባንኮችና መድን ሻጭ ኩባንያዎች ከሚሳተፉት ውስጥ እንደሚጠቀሱ አዘጋጆቹ ገልጸዋል፡፡

በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ግንባታ ሥራዎችን የሚያካሂዱና ቴክኖሎጂ የሚያቀርቡ ኩባንያዎችም እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡ በተጨማሪም የትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ በተዋረድ የሚገኙ የከተሞችና የክልል የትራንስፖርት ተጠሪ መሥሪያ ቤቶችም ተካተዋል፡፡

አቶ እሥራኤል እንደሚጠቅሱት፣ ትራስፖርት ሚኒስቴር ስለ ዝግጅቱ ድጋፍ እንዲሰጥ ባለፈው ዓመት ጥያቄ ቀርቦለት ነበር፡፡ በመሆኑም ሚኒስቴሩ በሰጠው ይሁንታ መሠረት ዝግጅት ሲደረግበት የቆየው ዓውደ ርዕይ በዚህ ዓመት መጨረሻ ወር ሊካሄድ ቀን መቆረጡን ገልጸዋል፡፡  

Standard (Image)

የፖላንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የትራክተርና የሶፍትዌር ገበያዎች ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ነው

$
0
0

 

  • ትራክተር አምራቹ ኡርሱስ 1,500 ትራክተሮቹ በሜቴክ መገጣጠማቸውን ይፋ አድርጓል
  • የፖላንድ ፕሬዚዳንት ለፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነት የአፍሪካን ድጋፍ ጠይቀዋል

በፖላንድ ፕሬዚዳንት አንድሬ ዱዳ የተመሩ ኩባንዎች ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር የንግድ ትስስር ለመፍጠር ፍላጎት እንዳላቸው ሲያስታውቁ፣ በተለይም በትራክተርና በሶፍትዌር አምራችነት የሚታወቁ ሁለት ኩባንያዎች ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲያደርጉ የቆዩትን እንቅስቃሴ እንደሚያጠናክሩ አስታውቀዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2013 ወደ ኢትዮጵያ ከመጡና ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር የንግድ ግንኙነት ከፈጠሩ መካከል ኡርሱስ ኤስ.ኤ. የተባለው ትራክተር አምራች ኩባንያ አንዱ ነው፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊት ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት የ90 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸውን የ3,000 ትራክተሮች አቅርቦት ስምምት ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የሁለቱ ኩባንያዎች ስምምነት ከትራክተር አቅርቦት ባሻገር የአቅም ግንባታና የቴክሎጂ ሽግግርን ያካተተ በመሆኑ በሺሕ የሚቆጠሩ የኮርፖሬሽኑ ባለሙያዎች ፖላንድ በሚገኘው የኡርሱስ ትራክተር ማምረቻ ፋብሪካ ሥልጠና እንደተሰጣቸው፣ በኡርሱስ ኩባንያ የውጭ ገበያዎች ትብብር ምክትል የንግድ ዳይሬክተር ሚካል ኒዮርስኪ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

እንደ ሚስተር ሚካል ማብራሪያ፣ ኡርሱስ ለሜቴክ ባቀረቸው ትራክተሮች ብዛት 1,500 ደርሰዋል፡፡ ቀሪዎቹን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ትራክተሮች አገር ውስጥ እንዲገጣጠሙ ለማቅረብ የሚያስቸለው የገበያ ዕድል እንዳለ አስታውቀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሜቴክ በዓመት 500 ትራክተሮችን የመጋገጠም አቅም እንዳለው ሲታወቅ ይህ ቁጥር ግን እንደገበያው ሁኔታ ከዚህም በላይ ሊጨምር ወይም ዝቅ ሊል የሚችልባቸው አጋጣሚዎች እንደሚኖሩም ተጠቅሷል፡፡

ትራክተር አምራቹ ከሜቴክ ባሻገር ከስኳር ከርፖሬሽን ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረትም እስካሁን እስከ 280 የፈረስ ጉልበት ያላቸው 200 ትራክተሮችን እንዳቀረበ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ለስኳር ልማት ሥራዎች እንዲስማሙ ተደርገው የተፈበረኩት ትራክተሮች ቁጥር ወደ ፊት እንደሚጨምርም ሚካል ጠቅሰዋል፡፡ ከትራክተሮቹ በተጨማሪ ለጭነት ተግባር የሚውሉ 400 የሸንኮራና የስኳር ውጤቶች ማመላሻዎችን ለስኳር ኮርፖሬሽን ማቅረቡን አስታውቀዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1893 በመመሥረት ከ120 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ኡርሱስ፣ በፖላንድ የስቶክ ገበያ ውስጥ ከተመዘገቡ ትላልቅ ኩባንያዎች ውስጥ ይመደባል፡፡ በፖላንድ ብቻ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ትራክተሮችን ለገበያ ማቅረብ እንደቻለና የመለዋወጫ መሣሪዎችንም እንደሚያቀርብ ሲታወቅ፣ በአማካይ እስከ 25 ዓመታት ለማገልገል የሚችሉ ትራክተሮችን በማምረት በአውሮፓ ከሚጠቀሱ ኩባንያዎች መካከል እንደሚመደብ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ከኡርሱስ ባሻገር ከሦስት ዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የሶፍትዌር ምርቶችና አገልግሎቶቹን ለብሔራዊ የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) እያቀረበ የሚገኘው ሌላኛው ኩባንያ አሴኮ ፖላንድ ግሩፕ የተባለው ሶፍትዌር አምራች ነው፡፡ ኩባንያው በአሁኑ ጊዜ ከኢትዮ ቴሌኮምና ከሌሎች መንግሥታዊ ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመሥራት እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ለሪፖርተር ያብራሩት፣ በአሴኮ ፖላንድ ኩባንያ የካፒታል ልማት ዘርፍ የኮርፖሬት ኃላፊው ሲዛሪ ሚክሳ ናቸው፡፡ እንደ ሚስተር ሲዛሪ ገለጻ፣ አሴኮ ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ለመግባት በመዘግየቱ ምክንያት እንደ ኮር ባንኪን ያሉ የባንክና የመድን ድርጅቶች የሚጠቀሙባቸውን ሶፍትዌሮች የማቅረብ ዕድል ለጥቂት አምልጦታል፡፡ ይሁንና በሌሎች የቴክኖሎጂ ዘርፎች አገልግሎት ላይ የሚውሉ ምርቶችን ለማቅረብ በጨረታዎች እየተሳተፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ከፖላንዱ ፕሬዚዳንት ዱዳ ጋር አብረው የመጡ ሌሎችም ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ የንግድ ማኅበረሰብ አባላት ጋር የንግድ ግንኙነት ለመፍጠር የሚረዳቸውን ውይይት አካሂደው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሬዚዳንት ዱዳ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አገሮች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ለፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነት፣ ፖላንድ ለምታደርገው ቅስቀሳ ድጋፍ እንዲሰጡ መጠየቃቸው ታውቋል፡፡ ከፕሬዚንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) እንዲሁም ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ከኢንቨስትመንት ጉዳዮች ባሻገር ኢትዮጵያ ስለምትሰጣቸው ድጋፍ ከመነጋራቸውም ባሻገር፣ በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እንዲሁም ከአፍሪካ ኅብረት ኃላፊዎችም ጋር ስለዚሁ ጉዳይ መነጋገራቸውን ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ፕሬዚዳንት ዱዳ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ያደረጉትን የሦስት ቀናት የሥራ ጉብኝት በሳምንቱ መጀመሪያ ቀናት አጠናቀው ለፖላንድ ድጋፍ ሊሰጡ ወደሚችሉ ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ማቅናታቸው ታውቋል፡፡ 

Standard (Image)
Viewing all 665 articles
Browse latest View live