Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all 665 articles
Browse latest View live

ስድስት ወራት ያልሞሉት የብስክሌት ፕሮጀክት ሥራ አቆመ

$
0
0
  • ፕሮጀክቱ ከመጀመሩ በፊት የሁለት ሳምንት ጥናት ብቻ ተደርጓል

በዳዊት እንደሻው

በቂ ዝግጅት ሳያደርግ ወደ ሥራ ገብቷል የተባለውና 27 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት የብስክሌት ትራንስፖርት ፕሮጀክት፣ ስድስት ወራት ሳይሞሉት ሥራ አቆመ፡፡

ፕሮጀክቱ በሦስት የአዲስ አበባ የተመረጡ ቦታዎች ተፈጻሚ እንደተደረገ የሚታወስ ሲሆን፣ እነዚህም የቀድሞ ኢምፔሪያል ሆቴል አካባቢ፣ ሰሚትና አያት ጨፌ ናቸው፡፡

ምንም እንኳን ፕሮጀክቱ በአካባቢው ላሉ ነዋሪዎች አማራጭ የትራንስፖርት መገልገያ ይሆናል ተብሎ ታስቦ ተግባራዊ ቢደረግም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግልጋሎት መስጠት አቁሟል፡፡

ይህ ከውጭ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ዕውን የሆነ ፕሮጀክት በዋናነት ለውድቀቱ ተጠያቂ የተደረገው፣ ፕሮጀክቱ ከመጀመሩ በፊት የተደረገው አናሳ ዝግጅት ነው፡፡

‹‹የገንዘብ ድጋፉ ተመላሽ ሊደረግ ነው ስለተባልን ፕሮጀክቱ ሊጀመር ሲል ለሁለት ሳምንታት የፈጀ ጥናት ብቻ አድርገናል፤›› ሲሉ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ኃላፊ ሰለሞን ኪዳኔ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በጊዜው የገንዘብ ዕርዳታው ተፈቅዶ ጥቅም ላይ ሳይውል ለአንድ ዓመት ቆይቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ገንዘቡ ተመላሽ ሊሆን ሁለት ሳምንት ብቻ ሲቀሩት በዋናነት ፕሮጀክቱን ሲያስፈጽም የነበረው የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ጥናቱን በአጭር ጊዜ እንዲያቀርብ እንደታዘዘ ኃላፊው ያስታውሳሉ፡፡ በወቅቱ እሳቸው የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ነበሩ፡፡

ይኼ ሁለት ሳምንት የፈጀ ጥናት በሚገባ ያልተሠራ ስለነበረ፣ አሁን ለተፈጠረው ችግር ምክንያት ሊሆን ችሏል ሲሉ ኃላፊውና ሌሎች ሪፖርተር ያናገራቸው የጽሕፈት ቤቱ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ ጥናቱ ካለቀ በኋላ ጽሕፈት ቤቱ ከአጠቃላይ ፕሮጀክቱ 7.5 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጎ ለብስክሌት ትራንስፖርት ፕሮጀክቱ የሚሆኑ 210 በኤሌክትሪክ ባትሪ የሚሠሩ ብስክሌቶችን ገዝቷል፡፡ ይህም የአንዱን ብስክሌት ዋጋ 33 ሺሕ ብር ያደርሰዋል፡፡

‹‹ይህ ዋጋ በጊዜው የተጋነነና በገበያው ውስጥ ያለውን የብስክሌት ዋጋ ያላማከለ ነበር፤›› ሲሉ ሪፖርተር ያናገራቸው አንድ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ኃላፊ ይናገራሉ፡፡

‹‹በአጠቃላይ በችግሮች የተከበበ ፕሮጀክት ነበር፤›› ሲሉ እኚሁ ኃላፊ ያስታውሳሉ፡፡ ቀሪው አብዛኛው የፕሮጀክቱ ወጪ ለመኪናዎች ተብሎ ከተሠራ መንገድ በተጓዳኝ ለብስክሌት ተጠቃሚዎች መስመሮችን መለየት፣ የእንዲሁም ለብስክሌቶቹ ማስቀመጫ ቤት ለመሥሪያ ውሏል ተብሏል፡፡

ለአብነት ያህል ሁለት ኪሎ ሜትር የሚጠጋው ከኢምፔሪያል አደባባይ ወደ 22 መንገድ የሚወስደው መንገድ በተጓዳኝ የተሠራበት የብስክሌት መሄጃ መስመር ለመለየት የወጣውን ወጪ ሳይጨምር፣ 70 የሚጠጉ ብስክሌቶችን ለመግዛት ወደ 2.3 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉ ታውቋል፡፡ አሥር የአካባቢው ወጣቶች እንዲደራጁ ተደርጎ ብስክሌቶቹ እንደተሰጧቸው ተገልጿል፡፡

ከአሥሩ ወጣቶች ውስጥ አንዱ የሆነው ወጣት ታደለ በዲሾ በአሁኑ ወቅት ከ70 ብስክሌቶች ውስጥ አምስቱ ብቻ እንዲሚሠሩ ይናገራል፡፡

ለመበላሸታቸውም ምክንያቱ የመለዋወጫ ችግር እንደሆነ ወጣቱ ታደለ ይገልጻል፡፡ ‹‹ብስክሌቶቹን ከተረከብን በኋላ መለዋወጫ ማግኘት አልቻልንም፤›› ብሏል፡፡ ብስክሌቶቹን በጨረታ ሲገዙ አቅራቢው ድርጅት አብሮ መለዋወጫም ያቀርባል ተብሎ ቢጠበቅም፣ ነገር ግን ግዢው ከተፈጸመ በኋላ ባልታወቀ ምክንያት ድርጅቱ ማቅረብ እንዳልቻለ፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የማስተባበሪያው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተናግረዋል፡፡

ጨረታው ሲወጣ የተባሉትን ብስክሌቶች ማግኘት አስቸጋሪ እንደነበርና በመጨረሻም አንድ አቅራቢ ብቻ መገኘት እንደቻለ ዶ/ር ሰለሞን ገልጸዋል፡፡

ከብስክሌቶቹ መበላሸት ባለፈ በአሁኑ ወቅት ወጣት ታደለና ጓደኞቹ እንዲሠሩበት የተሰጣቸው መስመር ከመፈራረሱም በላይ፣ የመኪና ማቆሚያ እንደሆነ መመልከት ተችሏል፡፡

ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ ጽሕፈት ቤቱ አጠቃላይ የስትራቴጂ ጥናት ለማስጠናት ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ከአሁን ቀደም የተፈጠሩ ችግሮችን ይቀርፋል ተብሏል፡፡

ይህ ፕሮጀክት ከሞተር አልባ የትራንስፖርት ዘዴዎች አንዱ ሲሆን፣ የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል ነው ተግባራዊ የተደረገው፡፡ የስትራቴጂው ጥናት ካለቀ በኋላ የብስክሌት ትራንስፖርቱ በስፋት በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች ተፈጻሚ ይሆናል ተብሏል፡፡ የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ ለሚደረጉ ሥራዎች፣  የዓለም ባንክ ባለፈው ዓመት 300 ሚሊዮን ዶላር ብድር መስጠቱ ይታወሳል፡፡     

 

Standard (Image)

መድን ድርጅት አራት አዳዲስ የዋስትና አገልግሎቶችን ሊጀምር ነው

$
0
0

በተሽከርካሪ ዋስትና ላይ የዋጋ ክለሳ ሊደረግ ነው

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የሪል ስቴት የመድን ሽፋንን ጨምሮ፣ አራት አዳዲስ የዋስትና አገልግሎቶችን ቀርፆ ገበያ ላይ ለማዋል ዝግጅት ማጠናቀቁ ታወቀ፡፡ እንደ ተሽከርካሪ ያሉ ዋስትናዎች ላይ የዋጋ ክለሳ ሊያደርግ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ከሪል ስቴት ፖሊሲ ሌላ እጀምራቸዋለሁ ያላቸው ቀሪዎቹ ሦስት አዳዲስ ፖሊሲዎች ለቱሪስቶች አጠቃላይ ደኅንነት ዋስትና፣ በአመፆች ሳቢያ ለሚከሰቱ የንብረት ጉዳቶች ዋስትናና ከ30 ዓመታት በላይ ላገለገሉ ተሽከርካሪዎች ዋስትና ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ነፃነት ለሜሳ እንደገለጹት፣ የእነዚህ አዳዲስ አገልግሎቶች የመጨረሻው የዋስትና ቀረፃ ሥራ  በመጠናቀቁ በጥቂት ወራት ውስጥ ወደ ገበያ ይገባል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በቀረፃ ሒደት ላይ ከነበሩ ሰባት አዳዲስ ዋስትናዎች ውስጥ ማክሮ ኢንሹራንስ ተጠናቆ ለገበያ እንደቀረበ ተነግሯል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ የአየር አምቡላንስ ወጪ፣ ጠቅላላ የገጠር ኢንሹራንስ፣ የቱር ኦፕሬተሮች ኃላፊነት፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ የሐኪሞችና የአካውንታንቶች የሙያ ጉዳት ካሳ ኢንሹራንስ ዋስትናዎች ደግሞ ተጠናቀው፣ ለጠለፋ ዋስትና ሰጪዎችና በድርጅቱ ለሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎች ቀርቦ አስተያየት እየሰጠበት እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኩባንያው ወደ ገበያ ለማስገባት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሻለሁ ብሎ ከቀረፃቸው አዳዲስ ዋስትናዎች በተጨማሪ፣ አንዳንድ ነባር ዋስትናዎቹን ለመከለስ እየሠራ ነው ተብሏል፡፡ በገበያ ላይ ከሚገኙ ነባር ዋስትናዎች ውስጥ የተሽከርካሪ ዋስትና አንዱ ነው፡፡ ይህ ዋስትና ጥናትና ክለሳ ሥራ እየተካሄደበት እንደሆነ ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም በረዥም ጊዜ መድን ዘርፍ የትምህርት ዋስትና የፖሊሲው ዝርዝር ድንጋጌዎችና የኢንዶውመንት ዋስትናዎች ላይ፣ የደንበኞችን ወቅታዊ ፍላጎትና የገበያ ሁኔታ መሠረት በማድረግ የመገምገምና አስፈላጊውን የዋስትናና የተመን ማሻሻል ሥራ መጠናቀቁን መረጃው ያመለክታል፡፡ እነዚህ የማሻሻያ ሥራ የተሠራላቸው ነባር ዋስትናዎች አስፈላጊ ግብዓቶች ከተወሰደባቸው በኋላ፣ በአዲሱ ዓመት ተግባራዊ ይሆናሉ ተብለው ይጠበቃሉ፡፡

በ2009 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ መድን ኢንዱስትሪ 7.5 ቢሊዮን ብር የአረቦን ገቢ ያስመዘገበ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ነፃነት፣ ይህም በ2008 ከነበረው በ16.6 በመቶ ዕድገት የተመዘገበበት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ የአረቦን ገቢ ውስጥ 95.2 በመቶ ከጠቅላላ መድን ዘርፍ የተገኘ ሲሆን፣ ቀሪው 4.8 በመቶ ከረጅም ጊዜ መድን ዘርፍ የተገኘ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው በሪፖርታቸው ዓለም አቀፍ የመድን ኢንዱስትሪ ምን እንደሚመስልም አስገንዝበዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 በዓለም አቀፍ ደረጃ በመድን ዘርፉ አጠቃላይ የተመዘገበው አረቦን 4.732 ትሪሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ዕድገቱም እ.ኤ.አ. በ2015 ከነበረው 4.3 በመቶ ወደ 3.1 በመቶ ቀንሷል፡፡ ለዚህ እንደ ዋና ምክንያት የተጠቀሰው በአደጉት አገሮች የመድን ዘርፍ ላይ የታየው ቅናሽ ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2016 በረጅም ጊዜ መድን ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመዘገበው ጠቅላላ አረቦን 2.617 ትሪሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ዕድገቱም እ.ኤ.አ. በ2015 ከነበረው ከ4.4 በመቶ ወደ 2.5 በመቶ እንደቀነሰም ተገልጿል፡፡ በተመሳሳይ በጠቅላላ መድን ዘርፍ የተመዘገበው አጠቃላይ አረቦን 2.115 ትሪሊዮን ዶላር ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2015 ከነበረው ከ4.2 በመቶ ወደ 3.7 በመቶ መቀነሱንና ለዚህም እንደ ዋና ምክንያት የሚቀርበው በአደጉት አገሮች የታየው ቅናሽ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

 

Standard (Image)

የአዲስ ፕሪፋብ ገዥዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አቤቱታ አቀረቡ

$
0
0

 

  • መፍትሔ ካላገኙ ሰላማዊ ሠልፍ እንወጣለን ብለዋል

በዳዊት እንደሻው

የአዲስ ፕሪፋብ ተገጣጣሚ ቤቶች አምራች አክሲዮን ማኅበር ቤት ገዢዎች ላጋጠማቸው ችግር የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጣቸው አቤቱታ አቀረቡ፡፡ እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2009 ዓ.ም.  መፍትሔ የማይሰጣቸው ከሆነ ሰላማዊ ሠልፍ እንወጣለን አሉ፡፡

ቤት ገዢዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት አዲስ ፕሪፋብ በይዞታው ቤቶቹን መገንባት እንዳልቻለ፣ በዚህም ሳቢያ በእንግልት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ነሐሴ 21 2009 ዓ.ም. ቀን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በአዲስ ፕሪፋብ ማኅተም በተጻፈ ደብዳቤ፣ አክሲዮን ማኅበሩ ከገባበት ቀውስ እንዲወጣ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግለት ለተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ጥያቄ ቢያቀርቡም መፍትሔ ማግኘት እንዳልቻሉ አስታውቀዋል፡፡

ለአብነት በተለያዩ ጊዜያት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ ለከተማና ቤቶች ሚኒስቴር፣ ለንግድ ሚኒስቴር፣ ለፌዴራል ሥነ ምግባር ፀረ ሙስና ኮሚሽን የተለያዩ ደብዳቤዎች ጽፈናል ብለዋል፡፡ ነገር ግን አክሲዮን ማኅበሩ አዲስ ቦርድ እንዲያቋቁም ከተደረገለት ድጋፍ ውጪ የረባ ዕገዛ እንዳልተደረገለት አመልክተዋል፡፡

‹‹ነገር ግን ማኅበሩ በተደጋጋሚ ሲያቀርበው የነበረው በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ስሙ ቦሌ በሻሌ በሚባለው አካባቢ የሚገኘው 23,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የማልማት ጥያቄ እስካሁን መፍትሔ አላገኘም፤›› ሲል በደብዳቤው አስፍረዋል፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ በይዞታው ላይ ቤቶቹን ለመገንባት በመስከረም ወር 2009 ዓ.ም ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት አቤቱታ አቅርቧል፡፡ እስካሁን የመጨረሻ ውሳኔ አልተሰጠበትም፡፡ 

‹‹ዛሬ ነገ እየተባለ ጉዳዩ እየተንከባለለ ነው፤›› ሲሉ የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ሥዩም ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ የሆሴዕ ሪል ስቴት ዋና ሥራ አስኪያጅ  አቶ የማነ ገብረ ሥላሴና የአዲስ ፕሪፋብ ሥራ አስኪያጅ በነበሩት አቶ ፍቅረ ማርም ዓለሙ መካከል በ2005 ዓ.ም. በተደረገ የእሽሙር ሽርክና ምክንያት የቦታው ካርታ አዲስ ፕሪፋብ እጅ እያለ፣ አቶ የማነ ካርታው ጠፍቶብኛል በማለት ሌላ ካርታ እንዳወጡና ቦታውም ላይ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ግንባታዎች እንዳካሄዱ በደብዳቤው ተገልጿል፡፡

ስለጉዳዩ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አቶ የማነ ግን፣ ‹‹ጉዳዩ በሕግ የተያዘና በሕግ ማለቅ ያለበት ነው፤›› ብለዋል፡፡  

የሞራል ድቀትና የገንዘብ ኪሳራ በማኅበሩ አባላት እየደረሰ እንደሆነና አብዛኞቹንም ተስፋ እያስቆረጠ ስለሆነ፣ መፍትሔ ሳይዘገይ እንዲሰጥ አክሲዮን ማኀበሩ ጠይቋል፡፡ እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. መልስ ካልተገኘ አባላቱ ሰላማዊ ሠልፍ እንደሚወጡ አክለዋል፡፡

ከስምንት ዓመት በፊት በስድስት መሥራቾቹና በ42 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል የተቋቋመው አዲስ ፕሪፋብ፣ 863 ባለአክሲዮኖች እንደነበሩት ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

Standard (Image)

እያሽቆለቆለ የመጣውን የወርቅ ኤክስፖርት ገቢ ለመታደግ መርሐ ግብር ተነደፈ

$
0
0

ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ የመጣውን የወርቅ ኤክስፖርት ገቢ ለማሻሻል የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የሥራ መርሐ ግብር ነደፈ፡፡

የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ከ2004 በጀት ዓመት ጀምሮ ለብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው የወርቅ ምርት መጠን እየቀነሰ መጥቷል፡፡ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና በባለድርሻ አካላት በተደረጉ ውይይቶች የችግሩ ምንጮች ምን እንደሆኑ መለየታቸውን የገለጹት አቶ ሞቱማ፣ ሕገወጥ የወርቅ ንግድ (ኮንትሮባንድ) ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

‹‹ዋናውና ትልቁ የኮንትሮባንድ ችግር ነው፡፡ የኮንትሮባንድ ችግር በአንድ ደረጃ የሚፈታ አይደለም፡፡ ሁለገብ ወርቅ ከሚመረትበት ቀበሌ ጀምሮ ጥረት መደረግ አለበት፡፡ ወርቅ ከሚመረትበት አካባቢ በኪስ በቀላሉ ተይዞ ሊወጣ የሚችል በመሆኑ፣ ባሉን ረዥም ድንበሮች በሙሉ የፀጥታ ኃይል አቁመን ለማስጠበቅ አንችልም፤›› ያሉት አቶ ሞቱማ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ የአስተሳሰብ ለውጥ የማምጣት ሥራ በስፋት መከናወን አለበት ብለዋል፡፡

ኅብረተሰቡ የኮንትሮባንድ ንግድ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጥረውን ከፍተኛ ጉዳት እንዲረዳ በማድረግ የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጣ ሰፊ የቅስቀሳ ሥራ እንደሚከናወን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ወርቁ በሕገወጥ መንገድ ከአገር ሲወጣ ስለሚያስከትለው ጉዳት ማስገንዘብና ለማዕከላዊ ገበያ ቢቀርብ ግን እኔም በተወሰነ ደረጃ ልጠቀም እችላለሁ የሚል እምነት በኅብረተሰቡ ዘንድ ማስረፅ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

ይህን ለማድረግ ከተለያዩ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ሚኒስቴሩ እየሠራ እንደሚገኝ  ገልጸው፣ አንድ ኮሚቴ መዋቀሩን ተናግረዋል፡፡ ኮሚቴው በ2010 ዓ.ም. የተለያዩ ሥራዎችን እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እያሽቆለቆለ የመጣውን ከማዕድን ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ለመታደግ የነደፈው መርሐ ግብር የሕገወጥ ወርቅ ዝውውርን መቀነስ ሲሆን፣ ሁለተኛው የመርሐ ግብሩ ክፍል ደግሞ ከብሔራዊ ባንክ ጋር በጉዳዩ ላይ በቅርበት መሥራት ነው፡፡

አቶ ሞቱማ እንዳሉት፣ የኮንትሮባንድ ንግድን የሚያባብሰው አንዱ ምክንያት በባንክና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው የውጭ ምንዛሪ ልዩነት መስፋት ነው፡፡ ‹‹በባንክ ያለው የዶላር ምንዛሪና በጥቁር ገበያ ያለው ምንዛሪ ልዩነት እየሰፋ በመጣ ቁጥር፣ በድንበር ወደ ጎረቤት አገሮች የሚሄደው የወርቅ መጠን እየጨመረ ይመጣል፤›› ያሉት አቶ ሞቱማ፣ ብሔራዊ ባንክ በዓለም ካለው የወርቅ ገበያ ዋጋ አምስት በመቶ በመጨመር ከአገር ውስጥ ወርቅ አምራቾችና አቅራቢዎች እንደሚገዛ አስረድተዋል፡፡ የምንዛሪ ልዩነት በሚሰፋበት ወቅት አምራቾቹ ከኮንትሮባንድ ገበያው የበለጠ ገንዘብ የሚያገኙ በመሆኑ ወደ ኮንትሮባንድ ንግዱ እንደሚያዘነብሉ አስረድተዋል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት በገንዘብ ፖሊሲው ላይ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

‹‹በገንዘብ ፖሊሲ አካባቢ የሚሠሩ በርካታ ሥራዎች አሉ፡፡ ችግሮቹ ተለይተዋል፡፡ በችግሮቹ ላይ ሁላችንም ተስማምተናል፡፡ ቀጥሎ ያሉትን ችግሮች በጋራ ሆነን እንፈታለን፤›› ብለዋል፡፡

ሌላው ለኮንትሮባንድ ንግዱ መስፋፋት በምክንያትነት የተጠቀሰው የብሔራዊ ባንክ የወርቅ ግዢ ክፍያ ሥርዓት ለውጥ ነው፡፡ የወርቅ ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ በየዕለቱ የሚለዋወጥ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ወርቅ አምራቾችና ነጋዴዎችን ለማበረታታት ከዓለም አቀፍ ገበያ ዋጋ አምስት በመቶ ጨምሮ የሚገዛ ከመሆኑም በላይ፣ የየዕለቱን የወርቅ ገበያ ዋጋ በመከታተል ትልቁን ዋጋ ተመልክቶ በዚያ ዋጋ ሲገዛ እንደነበር ተገልጿል፡፡

አቶ ሞቱማ እንዳሉት፣ በወር ውስጥ ከተመዘገበው ትልቁን ዋጋ በመውሰድ በዚያ ዋጋ ቆርጦ ተመን በማውጣት ወርቁን ከአቅራቢዎች ሲገዛ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ አሠራር በባንኩ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ በማስከተሉ እንዲቀር በመንግሥት ተወስኗል፡፡

‹‹በማይሸጥበት ዋጋ እየገዛ ባንኩን ለኪሳራ የዳረገው በመሆኑ እንዲቀር ተደርጓል፡፡ ይህ ግን በወርቅ አቅራቢዎች ላይ ቅሬታ ፈጥሮ ወደ ኮንትሮባንድ ንግዱ እንዲሳቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል፤›› ያሉት አቶ ሞቱማ፣ በወርቅ ንግድ ውስጥ በርካታ ችግሮች መታየታቸውን መሥሪያ ቤታቸው ከብሔራዊ ባንክና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የተለያዩ ሥራዎች በማከናወን ላይ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በአንደኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የማዕድን ሚኒስቴር ከማዕድን ኤክስፖርት በየዓመቱ 800 ሚሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ አቅዶ፣ በመጀመርያው ዓመት 600 ሚሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ ችሎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በዓለም አቀፍ ገበያ የወርቅ ዋጋ በመቀነሱና የኮንትሮባንድ ንግድ በመስፋፋቱ ምክንያት ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ከማዕድን ወጪ ንግድ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ እያሽቆለቆለ መጥቶ፣ ባለፈው ዓመት የተገኘው 230 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡   

በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የማዕድን ማውጫዎች እንደለሙ ይታወቃል፡፡ ብቸኛ ከፍተኛ ደረጃ ወርቅ አምራች የሆነው ሚድሮክ ጎልድ በለገደንቢ ወርቅ ማውጫ በዓመት ከ3.5 እስከ አራት ቶን ወርቅ እያመረተ ለውጭ ገበያ ያቀርባል፡፡

ከለገደንቢ ተጨማሪ በሌሎች ቦታዎች የወርቅ ፍለጋ ሥራዎች ያካሄደው ሚድሮክ ጎልድ፣ በመተከል ወርቅ ለማምረት ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

የባህላዊ ወርቅ አምራቾች ከፍተኛ ምርት በማምረት ለብሔራዊ ባንክ በማቅረብ ከዘርፉ ለሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በደቡብ፣ በቤኒሻንጉልና በጋምቤላ ክልሎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ባህላዊ የወርቅ አምራቾች እንዳሉ ይገመታል፡፡ በማኅበራት የተደራጁ ባህላዊ ወርቅ አምራቾች በየዓመቱ እስከ ዘጠኝ ቶን ወርቅ እያመረቱ ለብሔራዊ ባንክ እያቀረቡ እስከ 400 ሚሊዮን ዶላር ያስገኙ ነበር፡፡ በወርቅ ዋጋ መቀነስና በኮንትሮባንድ መስፋፋት ከባህላዊ ወርቅ አምራቾች የሚገኘው የወርቅ መጠንና የውጭ ምንዛሪ እያሽቆለቆለ መጥቷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሦስት ኩባንያዎች ከፍተኛ የወርቅ ማውጫዎች በመገንባት ሒደት ላይ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ አቶ ሞቱማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኒው ሞንት የተሰኘው ግዙፍ የአሜሪካ ኩባንያ በትግራይ ክልል ሰፊ ሥራ እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከፊ ሚነራልስ የተሰኘ የእንግሊዝ ኩባንያ በምዕራብ ወለጋ ቱሉካፒ በተባለ አካባቢ የወርቅ ማምረቻ ለመገንባት በዝግጅት ላይ ነው፡፡ ሚድሮክ ጎልድ በበኩሉ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ከፍተኛ ወርቅ ማዕድን ልማት ስምምነት፣ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር ተፈራርሞ ምርት ለመጀመር በዝግጅት ላይ እንደሆነ ታውቋል፡፡

አቶ ሞቱማ እንዳሉት፣ እነዚህ ሦስት ኩባንያዎች ማምረት ሲጀምሩ አገሪቱ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው ወርቅ በከፍተኛ መጠን ያድጋል፣ ከዘርፉ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ መጠንም ይጨምራል፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማብቂያ ከማዕድን ዘርፍ በዓመት ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱ ይታወሳል፡፡

የተለያዩ ኩባንያዎች በማዕድን ልማት ዘርፍ ለመሰማራት የሚስችላቸውን ስምምነት ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ቢፈራረሙም፣ በአብዛኛው ወደ ልማት ሲገቡ አይታዩም፡፡ አቶ ሞቱማ በሰጡት ማብራሪያ፣ የማዕድን ፍለጋና ልማት ሥራ በባህሪው ውስብስብና ረዥም ጊዜ የሚወስድ የሥራ መስክ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ጥልቅ የሆኑ ጉድጓዶች በሚቆፈሩበት ወቅት የሚፈጠሩ ችግሮች አሉ፡፡ ሥራው ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቅ፣ ውስብስብ የሆነና ረዥም ጊዜ የሚፈጅ ነው፤›› ያሉት አቶ ሞቱማ፣ ኩባንያዎች በማዕድን ዋጋ መውረድ ወይም በሌሎች የራሳቸው ምክንያት ዕቅዳቸውን እንደሚለውጡ ገልጸዋል፡፡

ለማዕድንና ነዳጅ ፍለጋ ሥራ ገብተው ብዙ ሚሊዮን ዶላር ከስረው የሚወጡ ኩባንያዎች እንዳሉም ገልጸዋል፡፡ ከካሳ ክፍያና ከአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ጋር በተያያዘ በሚፈጠሩ ችግሮች የሚዘገዩ ፕሮጀክቶች እንዳሉ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል የሚታዩ ችግሮችም እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ በመሥሪያ ቤቱ በኩል የክትትል ማነስ ችግር እንዳለ አምነዋል፡፡

‹‹የእኛም የክትትል ችግር አለ፡፡ በምርመራ ላይ ያሉትንና የምርት ፈቃድ የወሰዱትን እየተከታተልን መደገፍ የሚገባቸውን እየደገፍን፣ ያላግባብ የቆዩትን እያስወጣን መሄድ አለብን፡፡ በዚህ ላይ ጠንክረን የተሻለ ሥራ ማከናወን ይኖርብናል፤›› ብለዋል፡፡  

አገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ የጀመረችውን የሽግግር ጉዞ ለማገዝ የማዕድን ዘርፍ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ ማዕድናትን በማምረት፣ የአምራች ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡  

 

 

 

Standard (Image)

የአራት ክልሎች የኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽኖች 12 ቢሊዮን ብር ብድር ጠየቁ

$
0
0

 

በአማራ፣ በደቡብ፣ በኦሮሚያና በትግራይ ክልሎች የተቋቋሙ የኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽኖች፣ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አማካይነት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ 12 ቢሊዮን ብር እንዲያሰጣቸው ጥያቄ አቀረቡ፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተሾመ ዓለማየሁ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አራቱ ኮርፖሬሽኖች በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስተባባሪነት ብድር እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

‹‹ኮርፖሬሽኖቹ የአዋጭነት ጥናት አቅርበዋል፡፡ እኛም ጥያቄውን ከመረመርን በኋላ በ20/80 ሥሌት ብድሩን እንፈቅዳለን፤›› ሲሉ አቶ ተሾመ አስረድተዋል፡፡

መንግሥት የግብርና ምርቶችን በስፋት በሚመረትባቸው 17 ቦታዎች የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት አቅዷል፡፡

በመጀመርያ ዙር በአማራ ክልል ቡሬ፣ በደቡብ ክልል ይርጋለም፣ በትግራይ ክልል ሁመራና በኦሮሚያ ክልል ባቱ አካባቢዎች ፓርኮቹን ለመገንባት ታቅዷል፡፡

ለእነዚህ አራት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ 17 ቢሊዮን ብር ካፒታል የሚያስፈልግ ሲሆን፣ አምስት ቢሊዮን ብር የሚሆነውን ኮርፖሬሽኖቹ በመዋጮ መልክ ያወጣሉ፡፡

አቶ ተሾመ እንደገለጹት፣ የኮርፖሬሽኖቹ ካፒታል ሊጨምር ይችላል፡፡ ‹‹ባንኩም ኮርፖሬሽኖቹ ያቀረቡትን የአዋጭነት ጥናት በራሱ መንገድ ከመረመረ በኋላ በቅርቡ ምላሽ ይሰጣል፤›› ብለዋል፡፡ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ በፌዴራል መንግሥት የታቀዱ ሲሆን፣ የፓርኮቹ ባለቤቶች ክልሎች ናቸው፡፡

እነዚህ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በመስከረም 2009 ዓ.ም. እንደሚጀመርና በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ፣ ጥር 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በመሩት ስብሰባ ላይ ተገልጾ ነበር፡፡

ነገር ግን 2009 ዓ.ም. ሊጠናቀቅ ቀናት ብቻ ቢቀሩትም ግንባታው አልተጀመረም፡፡ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ ግንባታው የዘገየው የዲዛይንና የግንባታ ውል መመርያ ዝግጅቶች ረዥም ጊዜ  በመውሰዳቸው ነው፡፡

የእነዚህ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መቋቋም በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ተወስኖ የቆየውን የአግሮ ኢንዱስትሪ ክምችት ወደ ክልሎችም እንደሚወስደው፣ ከዚህም በላይ በአገሪቱ የግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ኤክስፖርት ለማድረግ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡ 

Standard (Image)

ኢትዮጵያ ከአምስት ዓመት ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ስኳር ኤክስፖርት አደረገች

$
0
0
  • በኬንያ አዲስ ገበያ ተፈጥሯል

የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ከተቋቋመ ከ2003 ዓ.ም. ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ስኳር ኤክስፖርት ተደረገ፡፡ መንግሥት ከኬንያ መንግሥት የቀረበለትን ጥያቄ በመቀበል ለስኳር ኮርፖሬሽን በሰጠው መመርያ መሠረት 43 ሺሕ ኩንታል ስኳር ወደ ኬንያ ተልኳል፡፡

ስኳር ኮርፖሬሽን በ2003 ዓ.ም. ከመቋቋሙ በፊት የአውሮፓ ኅብረት ለታዳጊ አገሮች ከጦር መሣሪያ በስተቀር የሚያመርቱትን ምርት ከቀረጥ ነፃ እንዲልኩ በሚሰጠው  ዕድል፣ ኢትዮጵያ ያላለቀለት ስኳር ወደ አውሮፓ ትልክ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ከዚያ ጊዜ በኋላ ኢትዮጵያ ስኳር ወደ ውጭ መላከ ከማቋረጧም በላይ፣ በአገር ውስጥም ከፍተኛ የስኳር እጥረት በመከሰቱ እስከ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ድረስ ከውጭ ስታስገባ ቆይታለች፡፡

የስኳር ኮርፖሬሽን ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጋሻው አይችሉም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ከኬንያ መንግሥት በቀረበላት ጥያቄ መሠረት 43 ሺሕ ኩንታል ስኳር ወደ ውጭ ልካለች፡፡

‹‹የኬንያ መንግሥት ጥያቄ የመጣው ኮርፖሬሽኑ በጥሩ ዋጋ ኤክስፖርት ለማድረግ፣ በአገር ውስጥ እጥረት ከተፈጠረም ኢምፖርት ለማድረግ ባቀደበት ጊዜ ነው፤›› በማለት አቶ ጋሻው ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኬንያ ለኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ሁነኛ መዳረሻ መሆን ጀምራለች፡፡ በተለይ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኬንያን ጨምሮ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በድርቅ ከተመቱ በኋላ ኢትዮጵያ ለኬንያ ገበያ በቆሎ አቅርባለች፡፡ 

የኬንያ ገበያ ከበቆሎ በተጨማሪ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን፣ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርት ለሆነው ስኳር ሁነኛ መዳረሻ መሆኑ እንደታመነበት አቶ ጋሻው ገልጸዋል፡፡

በሚቀጥለው 2010 በጀት ዓመት ነባሮቹን ጨምሮ ስምንት የስኳር ፋብሪካዎች ወደ ምርት ይገባሉ፡፡ በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ 6.5 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ይመረታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ጋሻው ተናግረዋል፡፡

የአገሪቱ የስኳር ፍላጎትም ከዚሁ ምርት ጋር የሚቀራረብ በመሆኑ፣ ስኳር ኮርፖሬሽን ጥሩ ዋጋ በሚገኝበት ወቅት ወደ ውጭ ለመላክ፣ እጥረት በሚፈጠርበት ወቅት ደግሞ ከአራማጭ ገበያዎች ወደ አገር ለማስገባት አቅዷል፡፡

ከ43 ሺሕ ኩንታል በተጨማሪ ስኳር ለመላክ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን፣ የስኳርና የተለያዩ የስኳር ተረፈ ምርቶችን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ የጥራት ሰርተፊኬት  የምርት መለያ (ብራንድ) ዝግጅት እየተደረገ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሁሉም ስኳር ፋብሪካዎች በዕድሳት ላይ በመሆናቸው ሥራ አቁመዋል፡፡ ይሁንና እንደ አቶ ጋሻው ገለጻ በቂ አቅርቦት አለ፡፡

ስኳር እየተከፈፈለ የሚገኘው ንግድ ሚኒስቴር በሚያወጣው ኮታ መሠረት በሸማች ማኅበራት፣ በኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ በኢትፍሩትና በቀድሞ ጅንአድ አማካይነት ነው፡፡

 

 

Standard (Image)

​ሁለት ሥራ ተቋራጮች ከ750 ሚሊዮን ብር በላይ የሚወጣበት መንገድ ለመገንባት ተፈራረሙ

$
0
0

የአዲስ አበባ ከተማ መንገደች ባለሥልጣን ለአዲሱ በጀት ዓመት የመጀመሪያ የሆነውን መንገድ ከ750 ሚሊዮን ብር በላይ ለማስገንባት፣ ከሁለት የአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች ጋር የግንባታ ውል ተፈራረመ፡፡

ማክሰኞ ነሐሴ 23 ቀን 2009 ዓ.ም. የግንባታ ውል የተፈረመለት የመንገድ ፕሮጀክት በሁለት ቦታ ተከፍሎ የሚገነባ ነው፡፡ የመጀመሪያው ከቦሌ ቡልቡላ የግብዓት ማምረቻ መግቢያ ወረዳ 12 መስቀለኛ መንገድ፣ ቡልቡላ 40/60 ኮንዶሚኒየም ድረስ  3.8 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መሆኑ ተገልጿል፡፡ ለዚህ መንገድ አሸናፊ ሆኖ ግንባታውን ለማካሄድ የተዋዋለው ፉል ጄኔራል ኮንትራክተር የተባለ አገር በቀል ኩባንያ ነው፡፡ ይህንን መንገድ ለመገንባት በጨረታ አሸናፊ የሆነበት ዋጋ 381.8 ሚሊዮን ብር እንደሆነ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ገልጿል፡፡ የእግረኛ መንገድን ጨምሮ 30 ሜትር ስፋት እንደሚኖረው፣ የወሰን ማስከበር ሥራውን ጨምሮ በ24 ወራት የጊዜ ገደብ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ከቦሌ ቡልቡላ ወረዳ 12 መስቀለኛ መንገድ መነሻ አድርጎ ቡልቡላ አደባባይ፣ ቡልቡላ 40/60 ኮንዶሚኒየም አቋርጦ ኖቫ ሪል ስቴት የሚዘልቅ ሲሆን፣ ሁለት አገናኝ መንገዶችን የሚያጠቃልል ነው፡፡ 4.1 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ይህ የግንባታ ክፍል እግረኛ መንገዱን ጨምሮ በ30 ሜትርና በ25 ሜትር ስፋት የሚገነባ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህንን መንገድ ለመገንባት አሸናፊ የሆነው ራማ የተባለው አገር በቀል ኮንትራክተር ነው፡፡ ራማ አሸናፊ የሆነበት ዋጋም 374.4 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ተገልጿል፡፡

አጠቃላይ ርዝመታቸው ስምንት ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑት ሁለቱ መንገዶች በአሁኑ ወቅት በጣም የተጎዱና ጠባብ በመሆናቸው፣ ለእግረኛም ሆነ ለአሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ አዳጋች ሆነው እንደቆዩ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም የ40/60 እና የ20/80 የጋራ ቤቶች መገንባታቸውና አዳዲስ የመኖሪያ መንደሮች እየተስፋፋ በመምጣታቸው፣ ከዚህ ቀደም የነበረው መንገድ በበቂ ሁኔታ ተጠቃሚዎችን ሊያስተናግድ ባለመቻሉ ነው መንገዶቹ የሚገነቡት፡፡ የመንገዶቹ ግንባታ ሲጠናቀቅ የሚስተዋለው ችግር በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀረፍና የከተማዋን የመንገድ ሽፋን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ባለሥልጣኑ ገልጿል፡፡

የግንባታ ስምምነቱን በባለሥልጣኑ በኩል የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ተገኝ (ኢንጂነር) በፉል ኮንስትራከሽን በኩል የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ልመነው ፈለቀ፣ በራማ ኮንስትራክሽን በኩል ደግሞ የድርጅቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ፍሬው ተድላ (ኢንጂነር) ፈርመዋል፡፡

ከእነዚህ የመንገድ ግንባታዎች በተጨማሪ ባለሥልጣኑ በ2010 በጀት ዓመት ግንባታ የሚያስጀምርባቸውና በጨረታ ሒደት ላይ የሚገኙ መንገዶች እንዳሉም አስታውቋል፡፡ በቅርቡ የጨረታ ውጤታቸው ታውቆ የግንባታ ስምምነት ይደረግላቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ መንገዶች መካከል ከፋፋ ምግብ ፋብሪካ፣ ዳማ ሆቴል፣ ብሔረ ጽጌ፣ ሰኔ ዘጠኝ ትምህርት ቤት፣ ደብረዘይት መንገድ፣ አያት መሪ ሳይት አራት ኮንዶሚኒየም፣ ቦሌ አያት፣ አያት ኮንዶሚኒየም፣ ኃይሌ ጋርመንት አደባባይ፣ ጀሞ አደባባይ፣ ከ22 ማዞሪያ እስከ እንግሊዝ ኤምባሲ ያሉት መንገዶች ይገኙባቸዋል፡፡ ከራስ ደስታ ሆስፒታል እስከ ቀጨኔ መድኃኔዓለም፣ ከሽሮሜዳ እስከ ቁስቋም፣ ከመገናኛ ውኃ ልማት እስከ ወረዳ 17 ጤና ማዕከል፣ ከሲኤምሲ እስከ አያት፣ ጉርድ ሾላ፣ ሰሚት፣ መሪ፣ ቄራ፣ ሳርቤት፣ ጎፋ መብራት ኃይል ኮንዶሚኒየም ያሉት የመንገድ ፕሮጀክቶችም በተመሳሳይ ይገነባሉ ተብለው ከሚጠበቁት ፕሮጀክቶች ውስጥ ተካተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣንን ለ2010 በጀት ዓመት 6.3 ቢሊዮን ብር በጀት እንደተመደበለት ይታወቃል፡፡

 

 

Standard (Image)

ኢትዮጵያና ጃፓን ከሰሜን ኮሪያ ኑክሌር እስከ አፍሪካ ቀንድ ባሉ ሥጋቶች ተመሳሳይ አቋም እንዳላቸው ተገለጸ

$
0
0

 

  • ጃፓን ለመንገድ ግንባታ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብድር ማቅረብ ትፈልጋለች

እሑድ ነሐሴ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከአገሪቱና ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ባለሥልጣናት ጋር የተወያዩት የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታሮ ኮኖ፣ ከሰሜን ኮሪያ የኑክሌርና የሚሳይል ጥቃት ጀምሮ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በሚታዩት የፀጥታ ሥጋቶች ላይ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር የሚስማማ አቋም እንዳላት አስታወቁ፡፡

የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ፣ እንዲሁም በሚኒስቴሩ የፕሬስና ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጄኔራል ረዳት ሚኒስትር ኖሪዮ ማሩያማ፣ ከአገር ውስጥና ከውጭ መገናኛ ብዙኃን አባላት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳስታወቁት፣ ጃፓን ከሰሜን ኮሪያ ተስፋፊ የኑክሌር፣ የሚሳይልና የጃፓን ዜጎችን ጠልፎ የመውሰድና የማገት ከፍተኛ ሥጋት እንደተጋረጠባት አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት የማያወላዳ ማዕቀብ እንዲጥል የጃፓን ፍላጎት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

 የሰሜን ኮሪያ ጉዳይ ከቁጥጥር ውጪ ከመውጣቱ በፊት ሊገታ ይገባዋል ያሉት ቃል አቀባዩ ማሩያማ፣ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤትም ከባድ ማዕቀብ እንዲጣል ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል የሆነችው ኢትዮጵያም በሰሜን ኮሪያ ላይ ተመሳሳይ አቋም እንደሚኖራት ተናግረዋል፡፡ ይሁንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የድጋፍ ድምፅ እንድትሰጥ ጠይቀዋል ወይ ለሚለው የጋዜጠኞች ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ ምንም እንኳ ጃፓንና አጋሮቿ የፀጥታው ምክር ቤት ከረረ ያለ ዕርምጃ እንደሚወስድ ይናገሩ እንጂ፣ ሩስያና ቻይና ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላቸው የንግድ ግንኙነት እንዲገታ ለማድረግ ከአባል አገሮች ከፍተኛ ግፊት ማድረግ ይጠበቃል ተብሏል፡፡ ሰሜን ኮሪያ ከ90 በመቶ በላይ የወጪ ንግዷ ከቻይና ጋር እንደሚከናወን ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል፡፡

በደቡብ ሱዳን ላለፉት አምስት ዓመታት ሲንቀሳቀስ የቆየው የጃፓን ራስ ተከላካይ ጦር ተልዕኮ በማብቃቱ እንደወጣ ያብራሩት ማሩያማ፣ በእነዚህ ዓመታት 5,000 ያህል የጃፓን ራስ ተከላካይ ጦር አባላት ልዩ ልዩ የመሠረተ ልማትና የምህንድስና ሥራዎችን ሲያከናውኑ ይቆዩ እንጂ በመደበኛ ውጊያ የመሠማራት ዓላማ እንዳልነበራቸውም አብራርተዋል፡፡ ከደቡብ ሱዳን በተጨማሪ ጃፓን በጂቡቲ ስላላት ወታደራዊ ተልዕኮም ጥያቄ ቀርቦላቸው ማብራሪያ የሰጡት ማሩያማ፣ የመርከቦችን ህልውና ከባህር ወንበዴዎች ለመከላከልና በሰላይ አውሮፕላኖች የታገዘ የመረጃ ማሰባሰብ ሥራ እንደሚከናወን አብራርተዋል፡፡ የሚሰበሰበው መረጃም አጋር ለሆኑ አገሮች ጭምር እንደሚሠራጭ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ማንሰራራት ከጀመረው የባህር ላይ ውንድብና እስከ አሸባሪዎች ጥቃት መንግሥታቸው ከአፍሪካ አገሮች ጋር አብሮ የመሥራት ፍላጎት እንዳለው አስታውቀዋል፡፡ በፀረ አክራሪነት ዘመቻ ጃፓን ኢትዮጵያ የምታከናውናቸውን ተግባራት እንደምትደግፍ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህም በላይ የአክራሪነትና የአሸባሪነት መነሻው የልማት መጓደል ስለሆነ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአፍሪካ አገሮች የሚሰጠው ድጋፍ እንደሚጠናከር ማያማ ሲገልጹ፣ በአፍሪካና በጃፓን መካከል እ.ኤ.አ. ከ1993 ጀምሮ ሲካሄድ የቆየውን የአፍሪካ ልማት ላይ ያነጣጠረ ጉባዔ አስታውሰዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቅርቡ በሞዛምቢክ የተካሄደውን የ‹‹ቶኪዮ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ለአፍሪካ ልማት (ቲካድ)›› የሚኒስትሮች ስብሰባ መርተዋል፡፡ እግረ መንገዳቸውን ወደ አዲስ አበባ የመጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ባለፈው ዓመት በናይሮቢ በተካሄደው ስድስተኛው የቲካድ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ወቅት ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮችና የድርጊት መርሐ ግብሮች አተገባበር ላይ መወያየታቸውም ተገልጿል፡፡

በናይሮቢው የቲካድ ስድስት ጉባዔ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ለአፍሪካ ልማት አገራቸው 30 ቢሊዮን ዶላር መመደቧን ይፋ አድርገው ነበር፡፡ ይህ ገንዘብ እ.ኤ.አ. እስከ 2018 ከጃፓን መንግሥትና ከግል ኩባንያዎች በመመንጨት ለአፍሪካ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎች እንደሚውል መገለጹም ይታወሳል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ማሩያማ፣ ከተጠቀሰው ገንዘብ ውስጥ አምስት ቢሊዮን ዶላር መለቀቁን አውስተዋል፡፡ ከዚህ ገንዘብ ውስጥም 3.8 ቢሊዮን ዶላር ለመሠረተ ልማት ሥራዎች መዋሉን አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ኦፊሴላዊ የዕርዳታ ድጋፍ ከመስጠት ባሻገር፣ የጃፓን መንግሥት በአገሪቱ መገበያያ ገንዘብ (የን) ላይ የተመሠረተ ብድር ከ43 ዓመታት በኋላ ለኢትዮጵያ መስጠት መጀመሩ ይታወሳል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ከተፈደቀው የ50 ሚሊዮን ዶላር ብድር በተጨማሪ፣ በቅርቡ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ብድር ለመስጠት መንግሥታቸው ፍላጎት እንዳለው ማሩያማ ይፋ አድርገዋል፡፡

ከጅማ ከተማ እስከ ጭዳ ላለው የመንገድ ዕድሳት የሚውል 100 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ እንደምትሰጥ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ያስታወቀችው ጃፓን፣ ከዚህ ገንዘብ በላይ እንደሚሆን የሚጠበቅ የብድር ስምምነትም በዚሁ አካባቢ ለሚገነባ የመንገድ ፕሮጀክት ለማበደር የሚያስችሉ ሥራዎች መጀመራቸውንና የሰነድ ስምምነት ለማድረግ የሚረዱ ዝግጅቶች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ማሩያማ አስታውቀዋል፡፡

በሞዛምቢኳ ማፑቶ ከተማ የተካሄደው የሚኒስትሮች ስብሰባ አምና በኬንያ የተደረገውን ጉባዔና ውጤቶቹን ከመገምገም ባሻገር፣ ለመጪው ጉባዔ የዝግጅት አጀንዳዎችም የሚደረጉበት እንደሆነ ታውቋል፡፡ የቲካድ ጉባዔ መላው የአፍሪካ አገሮች በከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው የሚታደሙበት ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በየሦስት ዓመቱ መካሄድ ጀምሯል፡፡ ከዚህ ቀደም በየአምስት ዓመቱ በጃፓን ይካሄድ የነበረው የቲካድ ጉባዔ ከእንግዲህ በአፍሪካና በጃፓን ከተሞች መካከል ይዘዋወራል፡፡

የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እሑድ ዕለት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

 

 

 

 

 

Standard (Image)

ሰሊጥም እንደ ቡና

$
0
0

የሰሊጥን አጠቃላይ የግብይት ሥርዓት ለመለወጥ ምክር ተጀምሯል

ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት የሚጠቀሰውን ሰሊጥ አጠቃላይ የግብይት ሥርዓት ለመለወጥ የሚያስችል አደረጃጀትና አሠራር ለመዘርጋት የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ምክር መጀመራቸው ታውቋል፡፡ የአገሪቱን ሰሊጥ ከምርት እስከ ወጪ ንግድ ድረስ ያለውን አጠቃላይ የግብይት ሒደት ለመለወጥ ታስቦ የተጀመረው እንቅስቃሴ ጉዳዩ በሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማትን ጨምሮ የአቅራቢዎችና ላኪዎች ማኅበራት የተወከሉበት ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተመከረበት ነው፡፡

በቅርቡ የቡናን አጠቃላይ የግብይት ሥርዓት ለመለወጥ ከተወሰዱ ዕርምጃዎች ጋር ተመሳሳይ የሆነ አሠራር ለመዘርጋት ያስችላል የተባለ ጥናት ቀርቦ፣ በችግሮችና በመፍትሔ ሐሳቦች ላይ እየተመከረበት እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡  

በዘርፉ የተሰማሩ ላኪዎች፣ አምራቾችና ሌሎች ተዋንያኖች የሰሊጥ የወጪ ንግድ ገበያ መቀዛቀዝና ከግብይት ሥርዓቱ ጋር ተያይዘው የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላትና ከዚህ በኋላ ግብይቱ እንዴት መሄድ አለበት የሚለውን የመፍትሔ ሐሳብ ይህ ኮሚቴ ይቀርፃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የሰሊጥ ምርት በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ግብይቱ እንዲፈጸም ግዴታ የተጣለበት እንደመሆኑ መጠን፣ ለሰሊጥ የውጭ ምንዛሪ ግኝት መቀዛቀዝ አንዱ ከምርት ገበያው አሠራር ጋር የተያያዘ ነው ይባላል፡፡ በመሆኑ ይህም ጉዳይ ታይቶ የተሻለ አሠራር ለመዘርጋት በባለድርሻ አካላቱ መፍትሔ ሊበጅ እንደሚችል ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ በምክክሩ በሰሊጥ ግብይት ዙሪያ እስካሁን ያሉትን ችግሮች በመርመር፣ የአፈጻጸም ስልቶችና ተያያዥ ጉዳዮችን የያዘ ረቂቅ በማሰናዳት በቅርቡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቀርባልም ተብሏል፡፡

በረቂቁም ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመሩትና በዘርፉ ያሉ ተዋንያን ሁሉ በሚገኙበት ከተመከረ በኋላ፣ የራሱ የሆኑ መመርያዎች ተዘጋጅተውለት ሥራ ላይ ለማዋል እንደታሰበም ለማወቅ ተችሏል፡፡ አሁን በሰሊጥ ዘርፍ የተሰማሩ ማኅበራት  የተወከሉበት፣ ንግድ ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ተወካዮችን ይዞ የሰሊጥ ጉዳይን እየተመለከተ ያለው ኮሚቴ የሚመራው፣ በእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የሰሊጥን ምርት ለዓለም ገበያ ከሚያቀርቡ ጥቂት አገሮች አንዷ ብትሆንም በበቂ እየተጠቀመችበት አይደለም፡፡ የሰሊጥ ምርት ግብይትን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በተለይ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ የሰሊጥ ምርት እየተሸጠበት ያለው አማካይ ዋጋ በኩንታል ከ1,600 እስከ 2,000 ብር ነው፡፡

ነገር ግን ከአራት ዓመት በፊት የአንድ ኩንታል ሰሊጥ እስከ 4,400 ብር ይደርስ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ የሰሊጥ ዋጋ በዚያን ያህል መውረድ የዓለም አቀፉ ገበያ ዋጋ በመውረዱ ብቻ ሳይሆን የምርት ጥራት እንደ ዋነኛ ችግር ይታያል፡፡ ዘርፉን ለመለወጥ ይወሰዳሉ ተብለው ከሚጠበቁ ውሳኔዎች መካከል የምርት ጥራትን ማሻሻል ከዚህ ምክክር እንደሚጠበቅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በቅርቡ ይፋ የሆነው የንግድ ሚኒስቴር መረጃም ከቅባት እህሎች የተገኘው ገቢ መውረዱን ይጠቁማል፡፡ ሆኖም ይህም ዘርፍ እንደሌሎች ምርቶች የወጪ ንግድ ገቢው እየወረደ ከመምጣቱ አንፃር አለበት የተባሉ ችግሮች ተቀርፈው ገቢውን ማሳደግ እንደሚገባ የባለድርሻ አካላቱ ከስምምነት ደርሰዋል፡፡ በሚኒስትር ዴኤታው እየተደረገ ያለው ውይይት ከአንድ ወር ተኩል በላይ ጊዜ ተወስዶ እየተመከረበት ነው፡፡

በየዓመቱ ለውጭ ገበያ ከሚቀርበው የሰሊጥ ምርት ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ምርት በመሸመት ቻይና ቀዳሚ መሆኗ ይታወቃል፡፡

 

 

Standard (Image)

የአንድ ቢሊዮን ዶላር የቡና ዕድሎች

$
0
0

 

በኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ገቢ ሰንጠረዥ ውስጥ ከሁሉም የወጪ ንግድ ምርቶች  ከፍተኛ ገቢ በማስገኘት ቡና በመሪነቱ ዓመታትን ተሻግሯል፡፡ የአገሪቱ የወጪና ገቢ ንግድ መረጃዎች በተደራጀ መልክ መተንተን ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ዋና ዋና የወጪ ምንዛሪ ምንጭ ከሆኑ ምርቶች ሁሉ በመላቅ በአንደኛነት ደረጃ እንደሚገኝ መዛግብቱ ያሳያሉ፡፡ በአገሪቱ ቡናን በመቅደም የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ሊያስገኝ የሚችል ምርት እስካሁን ሊመጣ አልቻለም፡፡

የኢትዮጵያ ቡና አቅራቢዎች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ቃሚሶ እንደሚገልጹትም፣ እስካሁን ቡናን የሚተካ ተወዳዳሪ ምርት አልመጣም፡፡ ወደፊትም ቡና የአገሪቱ የጀርባ አጥንት በመሆን እንደሚቀጥል ያምናሉ፡፡

ሆኖም ግን ከጠቅላላው የወጪ ንግድ ገቢ አኳያ፣ ቡና ይዞት የቆየው ድርሻ ቀስ በቀስ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ከዛሬ 30 ዓመታት በፊት እንደነበረው ከጠቅላላው የወጪ ንግድ ገቢ ውስጥ ከ60 ወይም ከ70 በመቶ የሚደርስ የገቢ ድርሻ የለውም፡፡ የገቢ ድርሻው እየቀነሰ መጥቶ ወደ 20 በመቶ ገደማ ከገባ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የአገሪቱን የወጪ ንግድ የገቢ መጠንና የእያንዳንዱን ምርት የንግድ ድርሻ የሚያመላክቱ ጥናቶች፣ የቡና ድርሻ በየዓመቱ እየቀነሰ መምጣቱን ያሳያሉ፡፡ ከ1973 ዓ.ም. እስከ 1976 በነበሩት ዓመታት የአገሪቱ ዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ ገቢ በአማካይ 397.43 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ በዚህ ወቅት የቡና ዓመታዊ ገቢ 247.07 ሚሊዮን ዶላር ስለነበር፣ ከጠቅላላው የወጪ ንግድ ድርሻው 62.14 በመቶ ይሸፍን ነበር፡፡

ከ1978 እስከ 1981 ዓ.ም. አገሪቱ ዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ ገቢ በአማካይ 399.2 ሚሊዮን በሆነበት ዓመታት ከጠቅላላ የወጪ ንግድ ገቢ የቡና ድርሻ 63.8 በመቶውን በመያዝ ዋነኛ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከ1982 እስከ 1985 ዓ.ም. ድረስ በየዓመቱ ሲመዘገብ የነበረው ዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ ገቢ 274.6 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ባሽቆለቆለበት ጊዜም ቢሆን፣ የቡና ድርሻ 53.4 በመቶ እንደነበር የተሰባሰቡት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ከ1986 ዓ.ም. በኋላም የቡና የበላይነት ዘልቋል፡፡ እስከ 1992 ዓ.ም. ድረስ የአገሪቱ የወጪ ንግድ አማካይ ገቢ ወደ 517 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ሲል፣ የቡና ድርሻም ወደ 61.4 በመቶ አሻቅቧል፡፡ በወጪ ንግድ ገበያ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ይይዝ የነበረው የቡና ድርሻ ካለፉት 20 ዓመታት ወዲህ ግን እየቀነሰ መጥቷል፡፡

በተለይ ካለፉት አሥርታት ወዲህ መረጃዎች የድርሻው ቅናሽ እየጎላ መምጣቱን አኃዞቹ አመላክተዋል፡፡ በ2003 ዓ.ም. አገሪቱ ከጠቅላላ የወጪ ንግድ 2.74 ቢሊዮን ዶላር ስታገኝ፣ ከቡና የተገኘው ደግሞ 841.8 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ይሁንና ከጠቅላላ የወጪ ንግድ ገቢ አንፃር ሲመዘን ድርሻው 30.6 በመቶ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ካስመዘገበችባቸው ዓመታት አንዱ 2004 ዓ.ም.  ነው፡፡ በወቅቱ ከጠቅላላ የወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ 3.15 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ የቡና ገቢ 833.1 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ድርሻውም 26 በመቶ ነበር፡፡ ሆኖም የቡና ድርሻ ከዚህ በኋላ እየቀነሰ መምጣቱን ሳይገታ በ2005 ለአገሪቱ ያስገኘው የውጭ ምንዛሪ ከቀደሙት ዓመታት ይባሱን ቀንሶ 746.6 ሚሊዮን ዶላር ሆኖ ነበር፡፡ ከጠቅላላ የወጪ ንግድ ገቢ ድርሻውም ወደ 24 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡ በ2006 ዓ.ም. ወደ 21.6 በመቶ በመቀነስ ባለፉት 15 ዓመታት ከነበረው ድርሻ በታች እያሽቆለቆለ ቀጠለ፡፡

የቡና ገቢ እንዲህ እየዋለለ ለመቀጠሉ የሚቀርቡት ምክንያቶች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ የዓለም የቡና ዋጋ መውደቅ፣ ለዓለም ገበያ የሚቀርበው ቡና መጠን መቀነስ ደጋግመው ይጠቀሳሉ፡፡ ከሁለት ዓመታት ወዲህም ቢሆን እነዚህ ምክንያቶች አሁንም የሚደመጡ የተለመዱ ሰበቦች ቢሆኑም፣ አገሪቱ ወደ ውጭ የምትልካቸው ምርቶች እየጨመሩ በመምጣታቸውና እንደ አበባ ያሉ ለአገሪቱ የወጪ ንግድ ዘርፍ እንግዳ  ምርቶች የወጪ ንግዱን መቀላቀላቸው ምንም እንኳ ዋነኛ የአገሪቱ የወጪ ንግድ ገቢ ቁንጮነቱን፣ የቡናን ከፍተኛ የበላይነት ድርሻ ግን ሸርሽሮታል፡፡

ከጠቅላላው የአገር ውስጥ ምርት ዕድገት አኳያ፣ በኢኮኖሚው ውስጥ ይዞት የቆው ድርሻም ቢሆን እየቀነሰ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህ ሲባል የቡና ጠቀሜታ መቀነስን ወይም የቡና ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚቀንስ ምክንያት ሆኖ ሳይሆን፣ በስታስቲካዊ አገላለጽ፣ ቡና ባደገና በያዘው ድርሻ መጠን በዚያው አግባብ ሌሎች ምርቶችም ለውጭ ገበያ እየቀረቡ በመምጣታቸው በቡና የተያዘውን የአንድ ምርት የበላይነት ድርሻ የሚጋሩ ሸቀጦች ለውጭ ገበያ መቅረብ መጀመራቸውን የሚያመላክት አካሄድ ነው፡፡ 

ይህም ቢባል የ2009 በጀት ዓመት መረጃ እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያ ከቡና ከፍተኛውን የውጭ ምንዛሪ ያስመዘገበችበት ዓመት ተብሎ መጠቀሱን ነው፡፡ ከፍተኛ መጠን ያስመዘገበ የ882.7 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ 2009 ዓ.ም. ከሌሎቹ ጊዜያት ለየት እንዲል አድርጎታል፡፡ ይህም ሆኖ ከዘንድሮ የወጪ ንግድ ምርቶች አኳያ የቡና ድርሻ 24 በመቶ ነው፡፡

አገሪቱ ካላት የቡና ማሳና ልታመርት ከምትችለው መጠን አንፃር፣ ከፍተኛነቱ የተነገረለት የቡና ገቢ፣ ያን ያህል ብዙ እንደማያኩራራ አቶ ዘሪሁን ይገልጻሉ፡፡ ነገር ግን የቡና የወጪ ንግድ መጠን ወደፊት የተሻለ መሆኑ እንደማይቀር ያምናሉ፡፡ ለዚህም ከምርት ጀምሮ አጠቃላይ የቡና ግብይት ሒደት ላይ አዳዲስ አሠራሮች እየተተገበሩና ነባሮቹ እየተለወጡ መምጣታቸው፣ የቡና ገቢ እያደገ ይመጣል የሚል እንዲሉ አድርጓቸዋል፡፡

ዘንድሮ ከቡና የተገኘው ገቢ ለመጨመሩ እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው፣ በዓለም ገበያ የተወሰነ የዋጋ ለውጥ መታየቱና በበጀት ዓመቱ መጠናቀቂያ ወቅት በቡና ላይ መተግበር የተጀመረው ለውጥ አስተዋጽኦ እንደነበረው የኢትዮጵያ ቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ግብይትና ልማት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳኒ ረዲ ይስማሙበታል፡፡

ሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በተጀመረው የ2010 በጀት ዓመት መጨረሻ፣ አገሪቱ ከዘንድሮውም በላይ ከፍተኛ የወጪ ንግድ ገቢ በቡና ታስመዘግባለች ተብሎ የሚታመንበት አንዱ ምክንያትም የለውጥ እንቅስቃሴው መጀመር እንደሆነ የሚያመላክቱ ጠቋሚ መረጃዎች ይጠቀሳሉ፡፡

ሪፎርሙ ገና ከጅምሩ ተስፋ እየታየበት ስለመሆኑም በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሐምሌ 2009 ዓ.ም. የቡና ግብይት ላይ የተመዘገበው መረጃ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ምርት ገበያው በሐምሌ 2009 ዓ.ም. ያገበያየው የቡና መጠንና የግብይቱ ዋጋ ከቀደመው ዓመት ብልጫ ይዞ መገኘቱ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከንግዱ ማኅብረሰብ ጋር በተነጋገሩበት መድረክ፣ ብዙ ቡና በማይላክበት የሐምሌ ወር እንኳ ከቡና የተገኘው ገቢ ከፍተኛ ሆኖ መገኘቱ በቅርቡ መተግበር የጀመረው የቡና ሪፎርም ውጤት እንደሆነ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ 

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ የታየው የለውጥ አዝማሚያ በ2010 በጀት ዓመት የቡናን የወጪ ንግድ ገቢ ከ20 እስከ 30 በመቶ እንደሚያሳድገው ተስፋ አሳድሮባቸዋል፡፡

በእርግጥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምኞት በተግባር ከታየ፣ ቡና አዲስ ታሪክ ማስመዝገቡ አይቀሬ ነው፡፡ ይኸውም በ2009 ዓ.ም. የተመዘገበው 882.7 ሚሊዮን ዶላር ገቢ፣ በትንበያዎች መሠረት በአማካይ በ25 በመቶ መጨመር ከቻለ፣ ከቡና የሚገኘው ገቢ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት አዲስ ታሪክ ሆኖ በአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ውስጥ ከምንጊዜው ይልቅ ከፍተኛውን ድርሻ ያስገኝለታል ማለት ነው፡፡

 ለአገሪቱ የቡና ወጪ ንግድ ወርቃማ ዕድል እንደሆነ የሚቆጠረው ሌላው ምክንያት፣ የዓለም ቡና ዋጋን በማስመልከት ከሰሞኑ ይፋ የወጡ መረጃዎች ናቸው፡፡ የዓለም የቡና ዋጋ እያንሰራራ መምጣቱ ብቻም ሳይሆን፣ ቀዳሚዋ የቡና አምራችና ላኪ ብራዚል፣ የቡና ምርቷ ችግር ውስጥ መግባቱ በመሰማቱ ነው፡፡ እንደ ዓለም ቡና ድርጅት መረጃ ከሆነ፣ ባለፈው ሐምሌ ወር የቡና ዋጋ የአራት በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ዋጋው አሁንም በመጨመር ላይ እንደሚገኝ የገበያ መረጃው ያሳያል፡፡

ካለፈው ሚያዝያ ወዲህ የቡና ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱ ተመዝግቧል፡፡ ጭማሪው በየወሩ እየታየ መቀጠሉም ድርጅቱ አስፍሯል፡፡ የቡና ዋጋ መጨመር ብቻ ሳይሆን፣ በሐምሌ ወር ለገበያ የቀረበው ከሰኔ ወር ይልቅ በመጠን ረገድ ብልጫ እንዳሳየ ታውቋል፡፡

የቡና የወጪ ንግድ እያደገ የመጣው ከገዥዎች በመጣ ከፍተኛ ፍላጎት እንደሆነ የሚጠቁመው ይህ መረጃ፣ የቡና ገዥዎች ፍላጎት መጨመር የቡና ዋጋ ከፍ እንዲል በማድረጉ፣ የዓለም ቡና ገበያ መነቃቃት እንዲታይበት አስችሏል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ላኪዎች፣ በተሻለ ዋጋ ቡናቸውን መሸጥ የሚችሉበት ዕድል በመከሰቱ፣ በ2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የቡና የወጪ ንግድ የተሻለ አፈጻጸም ሊያስመዘግብ እንደሚችል ይገመታል፡፡ አቶ ሳኒ እንደሚጠቅሱት፣ የዓለም ቡና ዋጋ መጨመሩ እርግጥ ቢሆንም፣ ጭማሪው ቀድሞ ወርዶ የነበረውን የቡና ዋጋ ወደ ቀድሞ ቦታው ለመመለስ እንደሚያስችለው አመላካች መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ከእነዚህ ሁለት ዕድሎች ባሻገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቋቋሙት ‹‹ጠንካራ ፀረ ኮንትሮባንድ ግብረ ኃይል›› በሕገወጥ መንገድ የሚወጣውን ቡና መጠን በመቀነስ ለዓለም ገበያ የሚቀርበውን መጠን ለማሳደግ ይረዳል ተብሏል፡፡ አቶ ሳኒ እንደገለጹት፣ ‹‹በመረጃ ላይ የተመሠረተ ገበያ ማራመድ ከተቻለ በቡና ላይ የተጀመሩት አዳዲስ አሠራሮች በደንብ ሲተገበሩና ሕገወጥ ተግባራትን መቆጣጠር ሲቻል የቡና ገቢም ያድጋል፤›› ብለዋል፡፡

 

Standard (Image)

በኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚታየው የዋስትና ውስንነት የተቋራጩ ችግር ነው ተባለ

$
0
0

በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ የሚስተዋለው የውልና የዋስትና አፈጻጸም ውስንነት የሚታየው በአብዛኛው በሥራ ተቋራጩ አማካይነት በሚከሰት ክፍተት ሳቢያ መሆኑ ተገለጸ፡፡ በኢትዮጵያ ከኮንስትራክሽን ሕግና ደንብ ባሻገር፣ በሁለት ሥራ ተቋራጮች መካከል የሚደረግ ስምምነት በዘርፉ ለሚከናወኑ የውልና የዋስትና ጉዳዮች የጎላ ድርሻ እንዳላቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

 ነሐሴ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. በካፒታል ሆቴል በተዘጋጀው ‹‹ወሰኑ ያለየለት የኮንስትራክሽን ዋስትና ምንነትና ተግባር ላይ የሚስተዋሉ የሕግ ክፍተቶች›› በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ነበር፡፡ የኮንስትራክሽን ዘርፉ የሕግ ማዕቀፍ አተገባበር ሲቃኝም በሥራ ተቋራጮች መካከል የሚከናወነው ስምምነት ግልጽነት የጎደለው ነው ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ መንግሥት ከሚመድበው ጠቅላላ በጀት 60 በመቶውን የሚወስደው ይኸው ዘርፍ ነው፡፡ በተቋራጮች፣ በአማካሪዎችና በአስገንቢዎች እንዲሁም በፋይናንስ ተቋማት መካከል ያለው ግንኙነት የተያያዘ በመሆኑ፣ አንዱ ከሌላው በግልጽ የተለያየ የሥራ ድርሻ እንዳላቸውና ይኼንንም የሚገዛ አሠራር ባለመዘውተሩ ምክንያት በዋስትና ላይ ችግሮች እንዲፈጠሩ መንስዔ መሆኑንም ተገልጿል፡፡

ዋስትናው በውል አፈጻጸም ወቅት እንደተጨማሪ ግዴታ የሚቆጠርና በሕግ ፊት የፀና እንደሆነ፣ የኮንስትራክሽን አደጋዎችን ከመቀነስ አንፃር በተለይም ከሕንፃ አዋጅ መውጣት በኋላ ማንኛውም ሥራ ተቋራጭ በሚሠራው ሥራ ምክንያት ለሚደርስ ጉዳት ከታወቀ የመድን ድርጅት ዋስትና ማቅረብ እንዳለበት ያስቀምጣል፡፡

‹‹በሁለት ሥራ ተቋራጮች መካከል የሚከናወን የውል ስምምነት በኢትዮጵያ ከተቀመጠው የኮንስትራክሽን ሕግ በተጨማሪ፣ በግላቸው የካሳ ውል ማሠር ይኖርባቸዋል፤›› ያሉት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አማካሪና የአየር ንብረት ለውጥ ዳይሬክተር ሙሉጌታ መንግሥቴ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

በውል አፈጻጸም ወቅት የተለያዩ ዋስትናዎች የሚተገበሩ ሲሆን፣ ዋስትና አብዛኛውን ጊዜ በገንዘብ አበዳሪ ተቋማት ማለትም እንደ ባንክና ማይክሮ ፋይናንስ ባሉት አካላት ሽፋን ይሰጠዋል ተብሏል፡፡ በዚህም መሠረት የሰው ዋስትና፣ የንብረት፣ የፋይናንስ ዋስትናና የኮንስትራክሽን ዋስትናን ያካተተ ነው፡፡

በመድረኩ የተለያዩ የስምምነት ክፍተቶች የተነሱ ሲሆን፣ በተለይ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የመንግሥት ግንባታዎች ቁጥር ላቅ ያለ መሆኑ ተጠቅሶ፣ በተለምዶ የመንግሥት ኪስ እርጥብ (Solvent) ነው ቢባልም በወጭ አስተዳዳር ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች የክፍያ መዘግየት እንደሚያጋጥም ተጠቅሷል፡፡

በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ የታወቁ የዋስትና ዓይነቶችም ቀርበዋል፡፡ በዋነኛነት የውል ማስከበሪያ፣ የጨረታ ማስከበሪያና ቅድሚያ ክፍያ፣ የዋናው ገንዘብ መያዣና የጥገና ብልሽት ዋስትናዎች ክፍተቶች የሚታዩባቸው መስኮች ናቸው፡፡

የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ውል ከመጠንሰሱ ቀደም ብሎና ሥራ ከጀመረ በኋላ  እስከመጠናቀቂያው ድረስ ባለው ሒደት ላይ ዋስትናዎቹን ዓለም አቀፍ የማድረግ ጉዳይ ሌላኛው በፕሮጀክቶች ላይ የሚታይ የችግር መነሻ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

በ52 ፕሮጀክቶች ማለትም አሥሩ በሕንፃ፣ አሥሩ በውኃ ሥራና 32 በመንገድ ግንባታ ሥራዎች ላይ ጥናት ተደርጎ እንደተገኘው ከሆነ፣ የፕሮጀክቱ ቀረፃ ላይ የሚታየው ክፍተት ዋነኛ ችግር እንደሆነ አረጋግጠናል ያሉት አቶ አረጋ ዋሻ፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡

‹‹በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ ወጥነት ያለው የአሠራር ሥርዓት ባለመኖሩ፣ ዘርፉ ለሙስና የተጋለጠ ነው፤›› በማለት አቶ አረጋ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በኢትዮጵያ ያለው የዋስትና ገበያ ላይ የመንግሥት ክትትል አናሳ በመሆኑ፣ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሥራ ተቋራጭ በርካታ ሠራተኞችን በሥሩ ቀጥሮ ሊያሠራ ቢችልም፣ በሠራተኞች ማጭበርበር ለሚደርስበት ጉዳት ማካካሻ የሚሆን የመተማመኛ ዋስትና (Fidelity Bond) አለመኖሩም በጥናቱ ቀርቧል፡፡

በኮንስትራክሽን ዋስትና አፈጻጸም ወቅት በተግባር ከሚስተዋሉ ተግዳሮቶች አንዱ በመንግሥት የጋራ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ የዋናው ገንዘብ መያዣ (Retention) የፕሮጀክቱ ግንባታ ተጠናቆ የጊዜያዊና የመጨረሻ ርክክብ ከተፈጸመ በኋላ ሳይከፈል የሚቀየረው አምስት በመቶ ገንዘብ አብዛኛውን ጊዜ ተመላሽ ስለማይደረግ፣ ተቋራጮች ለሌላ ወጪ እየተዳረጉ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በፍርድ ቤቶች ዘንድ የሚታዩ የአተረጓጎም ክፍተቶችም ተነስተዋል፡፡ በኮንስትራክሽን ፕሮጀክት የመልካም ሥራ አፈጻጸም ዋስትናን በተመለከተ በንግድ ሕግ ይታይ ወይስ በፍትሐ ብሔር ሕግ ይገዛ? የሚለው ነጥብም በጥናቱ ተካቷል፡፡

የመንግሥት የጨረታ ሰነድን በተመለከተ የሰብዓዊ መብት ድርድር በውስጡ ማካተት እንዳለበትና በኢትዮጵያ በሥራ ወቅት ሠራተኞች ላይ የሚደርሰውን አደጋ አሠሪው ሙሉ በሙሉ ኃላፊነቱን መውሰድ እንዳለበት በሕግ ከማስቀመጥ ባሻገር አፈጻጸሙ ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል፡፡

የዋስትና ሕግ ውስብስብነትን ተከትሎ የሥራ ተቋራጮች ከአገር ውስጥ ሕግ በተጨማሪ በውጭ ሕግ በመጠቀም ችግሩን ለመፍታት ሲሞከሩ መስተዋሉም ተገልጿል፡፡

በፌዴራል የመንግሥት የግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 649/2001 አንቀጽ 47 በተቀመጠው መሠረት፣ የመንግሥት ግንባታ ውሎች ላይ አቅራቢ (ውል ተቀባይ) ሆኖ የሚቀርብ ወገን፣ ግዴታውን ባለመፈጸሙ ምክንያት በመንግሥት መሥሪያ ቤት ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ማካካሻ የሚውል የውል ማስከበሪያ ማቅረብ እንደሚጠበቅበት ይጠቀሳል፡፡ ይሁንና ይኼ ሕግ እንደሚጠበቀው መጠን ዋስትና እያረጋገጠ ባለመሆኑ ማሻሻያ እንደሚያስፈልገውና የሥራ ተቋራጮችም ሕጉ ላይ ከተቀመጠው ባሻገር ተጨማሪ የውል ስምምነቶችን ማካተት እንደሚገባቸው በስብሰባው ወቅት ተነስቷል፡፡

 

Standard (Image)

ኢትዮጵያ የጉምሩክ ታሪፏን በአራት ዓመት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ልታነሳ እንደምትችል ኮሜሳ አስታወቀ

$
0
0

-የቀጣናውን የንግድ ስምምነት ቀስ በቀስ ለመቀላቀል መወሰኗን እንደማይቃወም ገልጿል

በብርሃኑ ፈቃደ፣ ማሔ ደሴት ሲሼልስ

የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) በመጪዎቹ አራት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ የጉምሩክ ታሪፏን ሙሉ በሙሉ ልታነሳ እንደምትችል አስታወቀ፡፡

በሲሼልስ አስተናጋጅነት በተካሔደው የኮሜሳ ንግድና ልማት ባንክ 33 ጠቅላላ ጉባዔ የተገኙት የኮሜሳ ዋና ጸሐፊ ሲዲሶ ንዴማ ንግዌና፣ በመጪዎቹ አራት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ የጉምሩክ ታሪፍ አሁን ከሚገኝበት የ40 በመቶ ምጣኔ ወደ ዜሮ እንደሚወርድ ተናግረዋል፡፡ አገሪቱ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ውስጥ ቀስ በቀስ ለመታቀፍ ካላት ፍላጎት አኳያ የታሪፍ ለውጡን እንደምታደርግ ዋና ጸሐፊው ገልጸዋል፡፡ 

በኮሜሳ አባል አገሮች መካከል የንግድና የኢኮኖሚ ትስስርን ለመፍጠር አንዱ መሠረታዊ መስፈርት የጉምሩክ ቀረጥ ማስከፈያ ታሪፍን ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት አሊያም ዝቅተኛ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ በአባል አገሮች መካከል ያለው የንግድ ግንኙነት፣ አባል ካልሆኑ አገሮች ይልቅ ተጠቃሚ እንዲያደርጋቸው በተደረሰው ስምምነት መሠረት፣ የታሪፍ ምጣኔው ብቻም ሳይሆን ሌሎችም ታሳቢ የሚደረጉ የንግድ ልውውጦችን ለማቀላጠፍ ይታሰባል፡፡

ከኮሜሳ ባሻገር በአፍሪካ አገሮች መካከል ለሚጠበቀው ነፃ የንግድ ስምምነት በኮሜሳ፣ በደቡባዊ የአፍሪካ አገሮች የልማት ማኅበረሰብ እንዲሁም የምዕራብ አፍሪካ አገሮች አኮኖሚያዊ ማኅበረሰብ የተሰኙት ሦስት ተቋማት፣ ከወራት በፊት በግብፅ ባደረጉት ስምምት መሠረት የሦስትዮሽ ነፃ የንግድ ስምምነት ማዕቀፍ ለመመሥረት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡

ይሁንና እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ባላቸው ዝቅተኛ የአምራች ኢንዱስትሪ አቅም፣ ባላቸው የሥራ አጥ ቁጥር ወይም በጠቅላላው ባላቸው የተወዳዳሪነት አቅም ሳቢያ የኮሜሳን ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት አለያም የአኅጉራዊው የንግድ ቀጣና ስምምነትን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቀላቀል ከባድ እንደሚያደርግባቸው ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ቀስ በቀስ የቀጣናው ነፃ የንግድ ስምምነት ለመቀላቀል ማሰቧ ምክንያታዊ እንደሆነም ይገለጻል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን፣ አገሪቱ ከምትሰበስበው የገቢ መጠን ውስጥ ከጉምሩክ የሚገኘው ገቢ ከፍተኛ ድርሻ ያለው በመሆኑም ጭምር ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከጉምሩክ የምትሰበስበውን ቀረጥ በማስቀረት የነፃ ገበያውን ትቀላቀላለች ተብሎ አይጠበቅም፡፡ 

በአንፃሩ በኢትዮጵያ እየተገነቡ የሚገኙ የመሠረተ ልማት አውታሮች የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር እንደሚያስችሉ ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡ ለአብነት ኢትዮጵያ ከኬንያ፣ ከጂቡቲ፣ ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከታንዛንያና ከመሳሰሉት አገሮች ጋር በመንገድ፣ በባቡርና በአየር ትራንስፖርት፣ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አማካይነት የምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ቀስ በቀስ የንግድና የኢኮኖሚ ትስስርን ለማስፈን መነሻዎች ይደረጋሉ፡፡

የኮሜሳ ዋና ጸሐፊው እንደሚያምኑት ኢትዮጵያ በቆዳና በቆዳ ውጤቶች ዘርፍ፣ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራችነት የምታደርገው እንቅስቃሴ ወደ አጎራባች አገሮች ብሎም ወደ ሌሎች የአኅጉሪቱ መዳረሻዎች ምርቶቿን የማስፋፋት ዕድል አላት፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚመረቱ ቆዳ ነክ ምርቶች የአውሮፓ ምርቶችን የመወዳደር አቅም እንዳላቸው ሲጠቅሱም የቆዳ ጃኬቶችን ምሳሌ አድርገዋል፡፡

በኢትዮጵያ በአማካይ 25 ዶላር የሚያወጣ ቆዳ ጃኬት፣ በአውሮፓ 200 ዶላር ከሚያወጣው ጋር ያለው ተወዳዳሪነት እኩል እየሆነ በመምጣቱ ምክንያት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች ባሻገር በምዕራቡ ዓለም ተፈላጊነት ያላቸው ምርቶችን የማምረት አቅም እየገነባች መሆኗ፣ ለቀጣናው ትስስር ያላትን አቅም እንደሚያመላክት ጠቅሰዋል፡፡

በአገሪቱ ከተገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞንን ጨምሮ የቦሌ ለሚን፣ የሐዋሳና የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን መጎብኘታቸውን የገለጹት ንግዌና፣ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአፍሪካ የነፃ ንግድ ስምምነትን ለመቀላቀል የሚያበቋት ምልክቶች እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡

በአንፃሩ በተባበሩት መንግሥታት የንግድና የልማት ጉባዔ (UNCTAD) ከፍተኛ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ከሆኑት መካከል ታፈረ ተስፋቸው (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካን የነፃ የንግድ ስምምነት ለመቀላቀል የሚያስችላት አቅም ላይ እንደምትገኝ ያምናሉ፡፡ የቀጣውን የንግድ ስምምነት ለመቀላቀል መዘግየቷም ተቀባይነት እንደሌለው ሲገልጹ ይታወቃሉ፡፡ አገሪቱ ካላት የሕዝብ ብዛትና እያመረተች ከምትገኘው ሸቀጥ አኳያ በሌሎች አገሮች የበላይነት ተወስዶባት፣ የሌሎች አገሮች ሸቀጥ ማራጋፊያ ትሆናለች፣ የሥራ አጥ ቁጥር ይባባሰል የሚለው ሥጋት አያሳምናቸውም፡፡ ይልቁንም የአገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ አቅም ያለው በመሆኑ በሌሎች አገሮች ሰፊ የገበያ ዕድል የማግኘት ብቃት እንዳለው የሚያጣቅሱት፣ የሲሚንቶ፣ የመጠጥ እንዲሁም የቆዳ ኢንዱስትሪውን እንቅስቃሴ በማጣቀስ ነው፡፡

 

 

 

Standard (Image)

በአዲስ አበባ የሥራ ላይ አደጋዎች መብዛታቸው ተገለጸ

$
0
0

 

 

በአዲስ አበባ ከተማ በተለይ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ የሥራ ላይ አደጋዎች እያጋጠሙ እንደሆነ ተገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና የማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሰላማዊ ኢንዱስትሪ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ፍቅሩ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በ2009 ዓ.ም. ብቻ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሥራ ላይ አደጋ የ11 ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡

‹‹ይህ አኃዝ ለሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሪፖርት የተደረገ ብቻ ነው፡፡ በድርድር የሚያልቁ ጉዳዮችን ደግሞ ቤቱ ይቁጠረው፤›› በማለት አቶ ደረጀ የሥራ ላይ አደጋዎች ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አቶ ደረጀ ጨምረው እንደገለጹት፣ ቢሮው መረጃ የሚያጠናቅረው ፖሊስ አጣሩልን ብሎ ሲጠይቅ በሚገኝ ሪፖርት ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ በየሳይቱ በሚደረግ ድርድር ተጎጂዎች ትክክለኛ ጥቅማቸውን ሳያገኙ እየቀሩ፣ ለማኅበራዊ ቀውስ እየተደረጉ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ለአብነት በቅርቡ ያጋጠማቸውን ክስተት አቶ ደረጀ ያብራራሉ፡፡ ስሙን መናገር ያልፈለጉት አንድ የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጭ ውስጥ የሚሠራ ባለሙያ በማሽን እጁ ተቆረጠ፡፡ የድርጅቱ ባለቤት አደጋ የደረሰበትን ተጎጂ ካሳከመ በኋላ አምስት ሺሕ ብር ብቻ ሰጥቶ ጉዳዩ እንዲያበቃ አደረገ፡፡ አቶ ደረጀ ጉዳዩን ጨምረው ሲገልጹ፣ በሕጉ መሠረት ቢኬድ ግን ተጎጂው ሕክምና ከተደረገለት በኋላ የሐኪሞች ቦርድ የጉዳቱን ደረጃ ያሳውቃል፡፡ ሠራተኛው በጉዳቱ መጠን መሠረት ለመጨረሻ ጊዜ ያገኘው ደመወዝ ለአምስት ዓመት ተባዝቶ ይከፈለዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ተግባዊ እንዳልሆነ አቶ ደረጀ  ይናገራሉ፡፡

በግንባታዎች ወቅት ደረጃውን የጠበቀ መወጣጫ (ስካፎልዲንግ) የማይጠቀሙ፣ ይልቁንም ለአደጋ የተጋለጠ የእንጨት መወጣጫ የሚገለገሉ፣ ለአሳንሳር የተተው ቦታዎች መከላከያ እንዳይኖራቸው በሚያደርጉ ኮንትራክተሮች ምክንያት የሰው ልጆች ሕይወት እየተቀጠፈ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ 377/1996 አንቀጽ 92 በሥራ ቦታዎች ላይ መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች በግልጽ ቢደነገግም፣ አዋጁ ተግባራዊ አለመደረጉን አቶ ደረጀ ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ኮንስትራክሽን ቢሮ አዘጋጅነት በተጀመረው የኮንስትራክሽን ሳምንት የውይይት መድረክ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተቋማት ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር አበበ ድንቁ እንደገለጹት፣ የሙያ ሥነ ምግባር በሌላቸው ወገኖች የሚካሄዱ ግንባታዎች ጥራት የጎደላቸው፣ ተጠያቂነት የሌለባቸውና እንደተገነቡ የሚፈርሱ ናቸው፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት ግንባታዎች በሰው ልጆች ሕይወትና አካል ላይ፣ እንዲሁም በሕዝብ ሀብት ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት የሚያደርሱ ሆነዋል፤›› በማለት ፕሮፌሰር አበበ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን የግንባታ ፈቃድ የመስጠት፣ በሰጠው ፈቃድ መሠረት ግንባታ መካሄዱን መቆጣጠር፣ ግንባታው ተካሂዶ ሲጠናቀቅም የመጠቀሚያ ፈቃድ የመስጠት ሥልጣንና ኃላፊነት አለው፡፡

ነገር ግን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ ባለሥልጣኑ የተሰጠውን ሥልጣን ተጠቅሞ ኃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም፡፡

ለዚህም እንደ ማስረጃ እየቀረበ የሚገኘው በከተማው ውስጥ በግንባታ ላይ ያሉ ሕንፃዎች በተለይ የመጀመሪያው ወለል ላይ ለባንኮች ተከራይተው አገልግሎት ሲሰጡ መመልከት የተለመደ   መሆኑ ነው፡፡

 

 

Standard (Image)

ስኳር ኮርፖሬሽን በአገሪቱ የስኳር እጥረት የለም አለ

$
0
0

 

  • የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አዲስ የሥርጭት ካርድ ማደል ጀመረ

ንግድ ሚኒስቴርን ጨምሮ ሁሉም የከተማና የክልል ንግድ ቢሮዎች ስኳር በኮታ እያደሉ ቢሆንም፣ ስኳር ኮርፖሬሽን በየወሩ 569 ሺሕ ኩንታል እያቀረበ መሆኑንና የክምችት ችግር እንደሌለበት አስታወቀ፡፡

      ስኳር ኮርፖሬሽን 200 ለሚጠጉ የቢራ፣ የለስላሳ፣ የምግብ፣ የከረሜላና እንዲሁም ለምርቶቻቸው ስኳር ለሚፈልጉ ኢንዱስትሪዎች በየወሩ 170 ሺሕ ኩንታል ያቀርባል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ አሥር ክፍላተ ከተሞች 112 ሺሕ ኩንታል ስኳር፣ ለክልሎች ደግሞ 287 ሺሕ ኩንታል ያቀርባል፡፡

      በንግድ ሚኒስቴር አማካይነት በወጣው ኮታ መሠረት የክልል ቢሮዎች በኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ በሸማቾች ማኅበራት፣ በቀድሞዎቹ ኢትፍሩትና ጅንአድ አማካይነት ለተጠቀሚዎቹ ያከፋፍላሉ፡፡

የስኳር ኮርፖሬሽን ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጋሻው አይችሉም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እስካሁን ኮርፖሬሽኑ የስኳር እጥረትን በተመለከተ የቀረበለት ሪፖርት የለም፡፡

‹‹የአቅርቦትም የክምችትም ችግር የለብንም፡፡ ፍላጎት ማርካት ካልተቻለ እንኳ ከውጭ እናስገባለን፤›› ሲሉ አቶ ጋሻው ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በሚገኙ የስኳር ፋብሪካዎች ከ3.5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ያመርታሉ፡፡ ፍላጎቱን ለማሟላት ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ወደ አገር ውስጥ ይገባል፡፡ ይህ መጠን በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ክፍተት እንዳይኖር ያደርጋል ተብሏል፡፡

በሚቀጥለው 2010 በጀት ዓመት ደግሞ ነባሮቹን ጨምሮ ስምንት ስኳር ፋብሪካዎች ወደ ምርት እንደሚገቡ፣ የአገሪቱ የማምረት አቅምም ሰባት ሚሊዮን ኩንታል እንደሚደርስ ተገልጿል፡፡

ነገር ግን ስኳር በበቂ ሁኔታ እየደረሰ አለመሆኑን የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየገለጹ ነው፡፡ በተለይ ሰሞኑን በኬንያ መንግሥት ጥያቄ መሠረት ከኢትዮጵያ 44 ሺሕ ኩንታል ስኳር ወደ ጂቡቲ መላኩ በብዙዎች ዘንድ አግራሞትን ፈጥሯል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ፣ ከተለያዩ ክፍላተ ከተሞች በተለይ የስኳርና የዘይት እጥረት እየገጠመ መሆኑ ሪፖርት እየቀረበለት ነው፡፡

ይህንን ችግር ለመፍታት ቢሮው የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውን ቢቆይም፣ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ‹‹የመሠረታዊ ሸቀጣ ሸቀጥ አባወራና እማወራ ከቸርቻሪ ሱቆች ጋር ለማስተሳሰር የተዘጋጀ የሥርጭት ካርድ›› የሚል የግብይት ካርድ ማደል ጀምሯል፡፡

የሥርጭት ካርዱ እንደሚያብራራው አንድ አባወራ/እማወራ ወርኃዊ የስኳር ኮታ አምስት ኪሎ ግራም፣ የዘይት ኮታ ደግሞ እስከ አምስት ሊትር ድረስ ነው፡፡ የዘይት መጠኑ እንደየአቅርቦቱ የሚለያይ ይሆናል ይላል፡፡

‹‹የሥርጭቱ ካርድ በየ15 ቀናት ወይም በወር ለአንድ ጊዜ ግብይት የሚያገለግል ነው፤›› ይላል አዲሱ የግብይት ካርድ፡፡ ይህ አዲስ የመገበያያ ካርድ የተዘጋጀው ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ካለ መደብር እንዲገበዩ ለማድረግና ክልከላን ለማስቀረት የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይህ አሠራር በቅርቦትና በፍላጎት መካከል አለመጣጣም መኖሩን ያሳያል ብለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ምንጮች ለሪፖርተር እንደሚገልጹት ግን፣ በዚህ ንግድ ዘርፍ የአየር በአየር ንግድ በመኖሩና በኮንትሮባንድ ስኳር ከአገር የሚወጣ በመሆኑ ለነዋሪዎች ተደራሽ ለማድረግ ጠቃሚ እንደሆነ ይሞግታሉ፡፡

ኤክስፖርቱን በተመለከተ አቶ ጋሻው ሲያስረዱ፣ በዓለም ብራዚልና ታይላንድ ብቻ ስኳር ወደ አገራቸው አያስገቡም፡፡ ሌሎች አምራች አገሮች ግን ጥሩ ዋጋ ሲያገኙ ኤክስፖርት ያደርጋሉ፡፡ በአገራቸው እጥረት ሲከሰት ደግሞ ጥሩ ዋጋ ከሚያገኙበት ገበያ ኢምፖርት ያደርጋሉ፡፡ ኮርፖሬሽኑ በዚህ መሠረት በአገሪቱ ካለው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ስትራቴጂ መንደፉን አቶ ጋሻው ገልጸዋል፡፡

‹‹የኬንያ ጥያቄ የመጣው ይህንን ስትራቴጂ በነደፍንበት ወቅት ነው፤›› ሲሉ አቶ ጋሻው የኮርፖሬሽኑን ሐሳብ ገልጸዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ምርቶች አዲስ ገበያ እየሆነች ወደመጣችው ኬንያ ስኳር በ110 ተሽከርካሪዎች እየተጓዘ ባለበት ወቅት ግን ችግር አጋጥሞ ነበር፡፡

ለችግሩ መነሻ የሆነው ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ በሚወስደው መንገድ ላይ አንድ ከባድ ተሽከርካሪ ከ280 ኩንታል በላይ መጫን አለመቻሉ ነው፡፡ ነገር ግን ከወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ የተነሱት ከባድ ተሽከርካሪዎች 400 ኩንታል ጭነው፣ አስፈላጊውን ሰነድ አሟልተው፣ እንዲሁም ተሽከርካሪዎቹ ለቆሙበት ዴሚሬጅ የሚከፍለው አካል ባለመለየቱ ለቀናት ተጉላልተው እንደነበር ታውቋል፡፡

አቶ ጋሻው እንዳሉት ይህ ችግር ተፈትቶ ሐሙስ ነሐሴ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ተሽከርካሪዎቹ ወደ ኬንያ ጉዞ ማድረግ ጀምረዋል፡፡

 

 

Standard (Image)

ተፈናቃይ አርሶ አደሮችን በድጋሚ ለማቋቋም 309 ሚሊዮን ብር በጀት ተያዘ

$
0
0

 

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ክልል ውስጥ በቂ ካሳና ምትክ ቦታ ሳይሰጣቸው ከ1988 ዓ.ም. ጀምሮ የተፈናቀሉ አርሶ አደሮችን በድጋሚ ለማቋቋም 309 ሚሊዮን ብር በጀት ተያዘ፡፡

በአሁኑ ወቅት በችግር ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃይ አርሶ አደሮችና ቤተሰቦቻቸውን ለማቋቋም ኃላፊነት የተሰጠው የልማት ተነሽ አርሶ አደሮች መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት፣ በድጋሚ ሊቋቋሙ ይገባቸዋል ያላቸውን በመለየት ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ከአዲስ አበባ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ መረጃ በመውሰድ፣ የራሱን ባለሙያዎች በማሰማራት ባካሄደው ቆጠራ 7,072 አባወራና እማወራዎች ተፈናቅለዋል፡፡ በአጠቃላይ ከነቤተሰቦቻቸው የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች ቁጥር 22,209 እንደሚሆን፣ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ታምራት መክት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አቶ ታምራት እንደገለጹት፣ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ በ2009 ዓ.ም. ቢቋቋምም በአብዛኛው ዝግጅትና ድጋፍ ሊደረግላቸው የሚገባ አርሶ አደሮችን በመለየት ቆይቷል፡፡ ነገር ግን በተወሰነ ደረጃም ቢሆንም የአርሶ አደር ልጆችን ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡

አቶ ታምራት እንዳሉት፣ በ2010 በጀት ዓመት ግን ሊደገፉ የሚገባቸውን አርሶ አደሮች የበለጠ በመለየት ለማቋቋም 309 ሚሊዮን ብር በጀት እንደተያዘ ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ከ1988 ዓ.ም. ጀምሮ በተካሄዱ ሰፋፊ ግንባታዎች አርሶ አደሮች ሲያፈናቀሉ ቆይተዋል፡፡ በተለይ የኢንዱስትሪ ዞኖች፣ የመኖሪያ ቤቶች፣  የአትሌቲክስ ማዘውተሪያና በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ የሚካሄዱ በርካታ ግንባታዎች አርሶ አደሮችን አፈናቅለዋል፡፡

በልማት ምክንያት ነባር ነዋሪዎችን የማፈናቀል ጉዳይ አሁንም ቢሆን በአስተዳደሩ የሚቀጥል ቢሆንም፣ ቀደም ሲል በልማት ምክንያት የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች በድጋሚ ለማቋቋም ከዚህ በኋላ የሚፈናቀሉ የተሟላ ድጋፍ ተሰጥቷቸው እንዲነሱ ለማድረግ ታስቧል፡፡ በቂ ምትክ ቦታና በቂ ካሳ ያልተሰጣቸው፣ ምትክ ቦታ የተሰጣቸውም ቢሆኑ ለመኖሪያ አመቺ ባልሆኑ ወንዝ ዳር ቦታዎችና ተዳፋት ሥፍራዎች ላይ በመሆኑ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ንፁህ የመጠጥ ውኃና መንገድ ስለሌሉ ጭምር ኑሯቸውን የከፋ እንዳደረገው ተፈናቃይ አርሶ አደሮቹ በየካቲት 2009 ዓ.ም. በተካሄዱ ስብሳባዎች መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

ዘግይቶም ቢሆን የፌዴራል መንግሥትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በልማት ምክንያት ለጉዳት የተዳረጉ አርሶ አደሮችን በድጋሚ ማቋቋም እንደሚያስፈልግ አምነዋል፡፡ በዚህ መሠረትም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የልማት ተነሽ አርሶ አደሮች መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት እንዲቋቋም መደረጉ ይታወሳል፡፡

 

 

 

Standard (Image)

የኮሜሳ የንግድና የልማት ባንክ ለሦስት የኢትዮጵያ ኩባንያዎች የ60 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለቀቀ

$
0
0

በብርሃኑ ፈቃደ፣ ማሔ ደሴት ሲሼልስ

ራሱን በምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) የንግድና የልማት ባንክ በማለት ስያሜውን ያሻሻለው የቀድሞው ፒቲኤ (Preferential Trade Agreement- PTA Bank)፣ በዚህ ዓመት ጥር ወር ይፋ ባደረገው መሠረት ለሦስት ኩባንያዎች በአጠቃላይ የ60 ሚሊዮን ዶላር ብድር ጥያቄ ቀርቦት ሲመለከት ቆይቶ ፈቀደ፡፡

የባንኩ 33ኛ ጠቅላላ መደበኛ ጉባዔ በሲሼልስ በተካሄደበት ወቅት የባንኩ ፕሬዚዳንት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ጋቴፕሮ የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኩባንያ፣ እንዲሁም እንይ ጄኔራል ቢዝነስ በጠቅላላው የ60 ሚሊዮን ዶላር ብድር ጥያቄያቸው ተቀባይነት በማግኘቱ ባንኩ ብድሩን ለቆላቸዋል፡፡

አዲሱን ስያሜውን በአዲስ አበባ ይፋ ባደረገበት ወቅት የባንኩ ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ይልማ ታደሰ እንዳስታወቁት የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ እንይ ጄኔራል ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ፣ እንዲሁም ጋቴፕሮ የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኩባንያ እያንዳንዳቸው የ20 ሚሊዮን ዶላር ብድር ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ከሦስቱ ኩባንያዎች በተጨማሪ ሌሎችም በድርድር ሒደት ላይ የሚገኙ እንዳሉና በቅርቡ ይፋ እንደሚደረጉም ጠቁመዋል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ዓለም አቀፍ ብራንድ ሆቴል ለመክፈት በካሊብራ አማካሪ ኩባንያ አማካይነት ከፈረንሣዩ አኮር ግሩፕ ጋር ስምምነት ያደረገው እንይ ኩባንያ፣ አኮር ከሚያስተዳድራቸው ውስጥ ፑልማን የተባለውን ብራንድ ሆቴል በኢትዮጵያ ለመክፈት የ20 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገውና ከፈረንሣይ አበዳሪ ተቋማት ብድሩን ለማግኘት እንቅስቃሴ ሲያደርግ እንደቆየ ይታወሳል፡፡ ይሁንና የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ አገሮች የጋራ ገበያ ተቋም (ኮሜሳ) ባንክ ከሆነው የንግድና የልማት ባንክ ብድሩ ስለተለቀቀለት፣ የሆቴል ፕሮጀክቱን በቅርቡ ዕውን እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡ ጋቴፕሮ የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኩባንያም ያቀረበው የ20 ሚሊዮን ዶላር ብድር በመለቀቁ፣ የብረታ ብረት ፋብሪካውን ዕውን ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡  

አቶ አድማሱ በሲሼልሱ ጉባዔ ወቅት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ለሚንቀሳቀሱ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች የሚውል 600 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለመልቀቅ ባንካቸው ዝግጁ ነው፡፡ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥም በአንድ ጊዜ እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ብድር ለኢትዮጵያ ለመስጠት ባንኩ ፍላጎት እንዳለው ይፋ አድርገዋል፡፡ ለዚህም በአገሪቱ በስኳር ልማት፣ በኢነርጂ፣ በቱሪዝም፣ በማኑፋቸክሪንግና ለሌሎች ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ለሚያመርቱ ዘርፎች ማበደር የሚቻልበት ሰፊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በመኖሩ እንደሆነ አቶ አድማሱ ጠቁመዋል፡፡

የአሁኑ የንግድና የኢንቨስትመንት ባንክ ከዚህ ቀደም ለሐበሻ ሲሚንቶ የ50 ሚሊዮን ዶላር ብድር መልቀቁን አቶ አድማሱ አስታውሰዋል፡፡ ከሐበሻ ሲሚንቶ በተጨማሪ የኢትዮጵያ አየር መንገድም 40 ሚሊዮን ዶላር ብድር ማግኘቱ አይዘነጋም፡፡ ከእነዚህ ተቋማት በተጨማሪ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ከ200 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ብድር እንደሚለቀቅለት መዘገባችን አይዘነጋም፡፡ ይሁንና የብድሩ ዓይነት በአብዛኛው የአጭር ጊዜ በመሆኑ ለተበዳሪ ተቋማት በተለይም ለንግድ ባንክና ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚሰጠው ብድር በየጊዜው እንደሚለዋወጥ ገልጸው፣ በተለይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብድር ባስፈለገው ጊዜ ሁሉ እንደሚቀርብለት አስታውቀዋል፡፡

ከወራት በፊት ባንኩ በታሪኩ በአንድ ጊዜ ሲፈቅድ የመጀመርያው የሆነውን የ250 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለኬንያ ማፅደቁ ይታወሳል፡፡ የባንኩን ስያሜ መቀየር ካስፈለገባቸው ምክንያቶች መካከል በየጊዜው እያደገና ለውጥ እያሳየ ከመምጣቱ ጋር እንደሚያያዝ፣ ከዚህም በተጨማሪ የኮሜሳ አባል ያልሆኑ አገሮችንም ለማካተት ታስቦ እንደሆነ ያወሱት አቶ አድማሱ በዚህም እንደ ሞዛምቢክ፣ ደቡብ ሱዳንና ታንዛኒያ ያሉ አገሮች በቅርቡ ወደ አባልነት መቀላቀላቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ ማዳጋስካር ያሉ በህንድ ውቅያኖስ ዳርቻ የሚገኙ ደሴቶችም ባንኩን ለመቀላቀል እየተቃረቡ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ በአሁኑ ወቅት የባንኩ 21 አባል አገሮችን ጨምሮ አሥር ተቋማት አክሲዮን በመግዛት የባንኩ ባለድርሻ መሆናቸው ታውቋል፡፡

እንደ አፍሪካ ልማት ባንክ ያሉ ተቋማትን በባለድርሻነት ያቀፈው ይህ ባንክ፣ በአቶ አድማሱ መመራት ከጀመረ ወዲህ የነበረውን አንድ ቢሊዮን ዶላር ሀብት ወደ አምስት ቢሊዮን ዶላር ማሳደግ ችሏል፡፡ ለዚህ ለውጥ ትልቁን ሚና የተጫወቱት አቶ አድማሱ በአባል የቦርድ ገዥ አገሮች ዘንድ ተሞካሽተዋል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2018 እስከ 2022 ባለው ጊዜ ውስጥ ባንኩን ለመጪዎቹ አምስት ዓመታት ሲመሩም የባንኩን ጠቅላላ ሀብት በእጥፍ በማሳደግ ወደ አሥር ቢሊዮን ዶላር የሚያደርሱበት፣ የባንኩ የተከፈለ ካፒታልም ከእጥፍ በላይ በማደግ ተጨማሪ 100 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስበት፣ የባንኩ የተጣራ ትርፍ አሁን ካለው 101 ሚሊዮን ዶላር ወደ በ180 ሚሊዮን ዶላር ከፍ የሚልበትን የኮርፖሬት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ የቦርድ አባላት አፅድቀውላቸዋል፡፡

 

 

Standard (Image)

የምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሥራ መልቀቂያ አስገቡ

$
0
0

 

በለውጥ ሒደት ላይ መሆኑና አዳዲስ አሠራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሆነ የተገለጸው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኤርሚያስ እሸቱ፣ ያልተጠበቀ ነው የተባለ የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸው ታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ለመምራት ሦስተኛው ሰው የነበሩት አቶ ኤርሚያስ ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ ምክንያት የሆናቸው ጉዳይ አልታወቀም፡፡ የምርት ገበያው የዳይሬክተሮች ቦርድ ግን የሥራ መለቀቂያ ጥያቄያቸውን ተቀብሎ፣ አዎንታዊ መልስ እንደሰጣቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ሆኖም አቶ ኤርሚያስን የሚተካ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እስኪገኝ ድረስ፣ በኃላፊነታቸው እንዲቆዩ መደረጉን ምንጮች አመልክተዋል፡፡

ምርት ገበያው አዳዲስ አሠራሮች ተግባራዊ እያደረገ መሆኑ እየተገለጸና እሳቸውም በተለይም ለውጡን ለመምራት ያሏቸውን ዕቅዶች እያሳወቁ ባሉበት ወቅት፣ ሳይታሰብ የሥራ መልቀቂያ አስገብተዋል መባሉ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

አንደ ምንጮች ገለጻ፣ ምርት ገበያው ለውጥ ለማድረግ ቦርዱ ሥር ነቀል ግምገማ እያካሄደ ነው፡፡ አቶ ኤርሚያስንም ጠንከር ብሎ ገምግሟል፡፡ የሥራ መልቀቂያ ጥያቄ ቀረበ የተባለውም ከዚህ ግምገማ በኋላ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሥራ አመራር ቦርድ የምርት ገበያውን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችም በጥብቅ መገምገሙ ተገልጿል፡፡ እስከ ምሽት አምስት ሰዓት ድረስ እየተቆየ የተካሄደው ግምገማ አቶ ኤርምያስን ያካተተ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከግምገማው የሚገኘው ውጤትም የተቋሙ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በቦታቸው ላይ መቆየት አለመቆየታቸው ሊወሰን የሚችል ሊሆን እንደሚችል፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ጠቁመዋል፡፡

በምርት ገበያው ለውጥ ለማምጣት ጠንካራ ጎኖቹንና ድክመቶቹን ለመለየት ግምገማው እየተካሄደ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ ይህ የምርት ገበያው ሰሞነኛ ግምገማ ከአሁን በፊት በተቋሙ ያልታየ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ላይ ከተደረገው ግምገማ በኋላ ሁሉንም ሠራተኞች የያዘ ውይይት ይደረጋል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡

በአቶ ኤርሚያስ የሥራ መልቀቂያ ጥያቄ ላይ የምርት ገበያው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ለጊዜው አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ አቶ ኤርሚያስን ለማነጋገር ሪፖርተር ለቀናት በተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም አልተሳካም፡፡ በሥራ ገበታቸው ላይ እንዳሉ ግን ታውቋል፡፡

የ42 ዓመቱ ጎልማሳ አቶ ኤርሚያስ ምርት ገበያውን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት እንዲመሩ የተሰየሙት ታኅሳስ 23 ቀን 2007 ዓ.ም. ነበር፡፡ ምርት ገበያውን ከመቀላቀላቸው በፊት የዘመን ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ሲያገለግሉ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከ20 ዓመታት በላይ የእንግሊዝ ቆይታ በኋላ ወደ አገር ቤት ተመልሰው ኑሯቸውን የጀመሩት በ1994 ዓ.ም. ነበር፡፡ በውጭ ቆይታቸውም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚታወቁት አይቢኤምና አልካቴል ማክሮ ስትራቴጂ በተባሉ ኩባንያዎች ውስጥ ሲሠሩ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያን ከምሥረታው ጀምሮ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ያገለገሉት እሌኒ ገብረ መድኅን (ዶ/ር) ኃላፊነታቸውን ሲለቁ፣ በእሳቸው እግር የአቢሲኒያ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ አንተነህ አብርሃም ተክተዋቸው ነበር፡፡ ሆኖም አቶ አንተነህ ከጤና እክል ጋር በተያያዘ ምክንያት ለወራት የያዙትን ኃላፊነታቸውን ሳይታሰብ ከለቀቁ በኋላ በአቶ ኤርሚያስ መተካታቸው አይዘነጋም፡፡

 

Standard (Image)

አቢሲንያ ባንክ ለልዩ ደንበኞቹ ልዩ የቅርንጫፍ አገልግሎት አስተዋወቀ

$
0
0
  • በልዩ ቅርንጫፎቹ የግል ስብሰባዎች ማካሄድን ጨምሮ በየቤታቸው አገልግሎት ያገኛሉ

አቢሲኒያ ባንክ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት በገዛው ሕንፃ ውስጥ ‹‹ተቀዳሚ›› ያላቸውን ደንበኞች የሚያስተናግድበትና ከመደበኛ ቅርንጫፎቹ በተለየ ደንበኞቹን የሚያስተናግድበት ቅርንጫፉን ሥራ አስጀመረ፡፡ አዳዲስ የባንክ አገልግሎቶችንም ይፋ እንደሚያደርግ አስታወቋል፡፡

‹‹ራስ›› የተሰኘው ልዩ ቅርንጫፍ ቅዳሜ፣ ሐምሌ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ሥራ በጀመረበት ወቅት እንደተገለጸው፣ በልዩ አደረጃጀት የተሰናዳው ቅርንጫፍ በዋናነት ለተቀዳሚ ደንበኞቹ የላቀ አገልግሎት እንዲሰጥ ተፈልጎ መሆኑን፣ የአቢሲኒያ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ አስማረ አስታውቀዋል፡፡ በልዩ አደረጃጀት አገልግሎት ለመስጠት የተዋቀረው ቅርንጫፍ፣ በተመሳሳይ መንገድ አገልግሎት መስጠት ከጀመረው ሐበሻ የሚል ስያሜ ከተሰጠው ልዩ ቅርንጫፍ ተከትሎ ሥራ የጀመረ ነው፡፡ በዚሁ አግባብ በቅርቡ ሦስተኛውን ልዩ ቅርንጫፍ እንደሚከፍትም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡

የራስ ልዩ ቅርንጫፍን ውስጣዊ ይዘትና አገልግሎት በተመለከተ በቀረበው ማብራሪያ መሠረት፣ ከ1,000 ካሬ ሜትር በላይ በሚያካልል ሥፍራ ለየት ባለ ውስጣዊ ዲዛይን የተደራጀ ነው፡፡ የቅርንጫፉ አገልግሎት መስጫ ልዩ የእንግዳ መቀበያ፣  የስብሰባ አዳራሾች፣ የእንግዶች መቆያ ክፍልን ጨምሮ የማብሰያና የመመገቢያ ክፍሎችን ያካተተ ነው፡፡ በተቀማጭ ሒሳብ መጠን፣ በብድርና በውጭ ምንዛሪ እንቅስቃሴ ለባንኩ የተሻለ ጥቅም የሚያስገኙ ደንበኞችን በይበልጥ ለማገልገል የተሠራ ቅርንጫፍ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሙሉጌታ፣ ከባንኩ ጋር የረጅም ጊዜ የሥራ ግንኙነት ያላቸውን ደንበኞች፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ በመልካም ምግባራቸው ተቀባይነትና ዕውቅና ያተረፉ ግለሰቦች፣ ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ ያላቸውን ባለአክሲዮኖችና ባለሀብቶችና ሌሎችም ከባንኩ ጋር ባላቸው የሥራ ስፋትና ግንኙነት የተነሳ ልዩ መስተንግዶ የሚገባቸው ደንበኞች የሚገለገሉበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም እንዲህ ያሉት ደንበኞች የቅርንጫፉን የስብሰባ አዳራሽ ለግል የሥራ ውይይት መጠቀም ይችላሉ፡፡ ለዚህ አገልግሎት ደንበኞቹ ምንም ዓይነት ክፍያ እንደማይጠየቁም ባንኩ አስታውቋል፡፡

ቀዳሚ ደንበኞች ለግል የሥራ እንቅስቃሴያቸው የሚያስፈልጋቸውን ነፃ የኢንተርኔት፣ የስልክ፣ የፋክስና የመረጃ አገልግሎት ወደ ቅርንጫፉ ለመገልገል በሚመጡበት በማንኛውም ጊዜ መጠቀም የሚችሉበት ዕድል መፈጠሩንም የባንኩ ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡ ባንኩ ተቀዳሚ ላላቸው ደንበኞቹ ሌሎችም ተጨማሪ አገልግሎቶችን አመቻችቷል፡፡

የገንዘብ እንቅስቃሴያቸውን ደንበኞቹ ያሉበት ድረስ በመሄድ ያስተናግዳል፡፡ ይህንን አገልግሎት በተመለከተ አቶ ሙሉጌታ ሲያብራሩም፣ ‹‹ባንኩ ከቅርንጫፉ ውጪ ለተቀዳሚ ደንበኞቹ የሚሰጠውን አገልግሎት በማስፋት በሥራ ቦታቸው ወይም በመኖሪያ ቤታቸው በመገኘት የተለያዩ የባንክ አገልግሎቶችን ያቀርባል፤›› ብለዋል፡፡ ይሁንና የዚህ አገልግሎት አሰጣጥም እንደሌሎቹ መደበኛ ገንዘብ የመሰብሰብ ወይም የመክፈል አገልግሎቶች ጥንቃቄና ደኅንነቱ በተጠበቀ መንገድ እንደሚሰጥ ጠቅሰዋል፡፡  

ደንበኞቹ ከባንኩ ጋር የሚኖራቸውን ጉዳዮች የሚከታተልና የሚያስፈጽም የደንበኞች ግንኙነት ሥራ አስኪያጅ የሚመደብ በመሆኑ፣ ልዩ ቅርንጫፉን ከዋናው መሥሪያ ቤትም ሆነ ከሌሎች ቅርንጫፎቹ የተለየ ያደርገዋል ተብሏል፡፡ ደንበኞች ከቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጁ፣ ከደንበኞች ግንኙነት ሥራ አስኪያጁና ከአገልግሎት ሰጪ መኮንኑ ጋር ባስፈለጋቸው ጊዜ ውይይት ማድረግ የሚያስችሉት የግል መሰብሰቢያ ቢሮዎች የተዋቀሩ ሲሆን፣ ባንኩ ራስ በማለት በሰየመው ቅርንጫፉ በልምዳቸውና በደንበኛ ተኮር አገልግሎታቸው የተመረጡ 40 ሠራተኞች አገልግሎት እንዲሰጡ መመደቡንም አስታውቋል፡፡   

አቢሲኒያ ባንክ የኢንተርኔት ባንክ አገልግሎትን ተግባራዊ ያደረገ ሲሆን፣ በአዲሱ በጀት ዓመትም የወኪል ባንክና ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን ለመጀመር ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡ አቢሲንያ ባንክ ሌሎችም አዳዲስ የባንክ አገልግሎቶችን ለማስጀመር እንደወጠነ አስታውቆ፣ በቅርቡ እተገብራቸዋለሁ ካላቸው መካከል የሴቶችን፣ የወጣቶችንና የዕድሜ ባለፀጎችን ማዕከል ያደረጉ አዳዲስ አገልግሎቶች እንደሚተገበሩ ጠቅሰዋል፡፡ እነዚህን አገልግሎቶች ለመጀመር የቅድመ ትግበራ ሥራ እንደተጀመረም ተገልጿል፡፡

አቢሲኒያ ባንክ በ2009 ዓ.ም. ከታክስ በፊት ከ801 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታውቆ፣ የተቀማጭ ገንዘቡንም በ2008 ዓ.ም. ከነበረው በ52.2 በመቶ በማሳደግ በ2009 ዓ.ም. መጨረሻ ወደ 20.7 ቢሊዮን ብር አድርሷል፡፡

የባንኩ ደንበኞች ቁጥር ከ750 ሺሕ በላይ እንደደረሰ፣ የሠራተኞቹ ቁጥርም ከአምስት ሺሕ በላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡  አቢሲኒያ ባንክ ከ20 ዓመታት በፊት ሥራ የጀመረው በ50 ሚሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታልና በ17.8 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ሲሆን፣ ባንኩን የመሠረቱት የመጀመርያዎች ባለአክሲዮኖች ቁጥር 131 ነበር፡፡ በወቅቱ ሥራ የጀመረውም በ32 ሠራተኞች እንደነበር ይታወሳል፡፡

በአሁኑ ወቅት የባንኩ የተፈቀደ ካፒታል አራት ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ የተከፈለ ካፒታሉም 1.8 ቢሊዮን ብር ሆኗል፡፡ የባለአክሲዮኖቹ ቁጥር 2,171 እንደሆነና አጠቃላይ የሀብት መጠኑም ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡ አቢሲኒያ ባንክ በአዳዲስ አገልግሎቶች ያስተዋወቃቸውን ልዩ ቅርንጫፎች ጨምሮ የቅርጫፎቹ ቁጥር 237 ደርሷል፡፡

 

Standard (Image)

ለእህል ጥራት ተስፋ የሚደረገው ከረጢት የድኅረ ብክለትን ለመቀነስ እያገዘ ነው

$
0
0

በድኅረ ምርት ከአሥር እስከ 12 በመቶ የሚሆነውን ብክነት ለመቀነስ የሚያግዝ የእህል ማከማቻ ቀረጢት ለአርሶ አደሮች መቅረብ ጀመረ፡፡

ሔርሜቲክ በተሰኘ ቴክኖሎጂ (አየር ወደ ከረጢት ውስጥ እንዳይገባ የሚያግድ) አማካይነት የሚሠራው ቀረጢት፣ የትኛውም የእህል ምርት ከነበረበት የጥራት ደረጃ ሳይጓደልና ሳይበላሽ ለሁለት ዓመታት እንዲቆይ የሚያስችል መሆኑን ቴክኖሎጂውን እያቀረበ የሚገኘው የሻያሾኔ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ ሠርፀ ይናገራሉ፡፡

የግብርና ማማከር፣ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን የማስፋፋትና የማስተዋወቅ ሥራ የሚሠራው ድርጅቱ፣ ቴክኖሎጂውን የሚያስመርተው ከሦስት ፋብሪካዎች ጋር በመተባበር  ነው፡፡ በኢትዮጵያ በ27 ዞኖች ውስጥ ለሚገኙ 6,000 መንደሮች ምርቱን ለማሰራጨት የማስተዋወቅ ሥራ መካሔዱን የሚናገሩት አቶ ያሬድ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት 280,000 ከረጢቶችን ማሠራጨት እንደተቻለም ገልጸዋል፡፡ በመጪው ዓመት  360,000 ቀረጢቶችን ለአርሶ አደሩ የማሠራጨት ዕቅድ እንደተያዘም አስታውቀዋል፡፡

ቴክኖሎጂው ከተሠራጨባቸው የአገሪቱ ክፍሎች መካከል የመራቤቴ ወረዳ አንዱ ሲሆን፣ እሑድ፣ ነሐሴ 27 ቀን 2009 ዓ.ም.  ለወደራ ኅብረት ሥራ ዩኒየን አባል አርሶ አደሮች ቴክኖሎጂውን ለማስተዋወቅ ተሞክሯል፡፡

የኔዘርላንድስ መንግሥት የልማት ድርጅት ድጋፍ በሚሰጠው ማኅበራት ለለውጥ በተሰኘ ፕሮጀክት አማይነት፣ ቴክኖሎጂው በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልሎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች ለማዳረስ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በድርጅቱ የአግሪ ቢዝነስ አማካሪ አቶ መስፍን ወልደሥላሴ እንደጠቀሱት፣ መራቤቴን ጨምሮ በሦስቱ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ ሦስት ዩኒየኖች አማካይነት 4,500 ቀረጢት መሰራጨቱም ታውቋል፡፡ በሚቀጥሉት ወራት 6,000 ከረጢቶችን ለማሰራጨት እንቅስቃሴ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

የአንዱ ከረጢት ዋጋ ከ70 እስከ 100 ብር ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ በሚደረግባቸው የአገሪቱ ክፍሎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች 47 ብር በመክፈል ቀረጢቱን እንዲያገኙ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡ ‹‹280,000 ማሠራጨት ብዙ የሚባል አይደለም፡፡ ነገር ግን እያደገ የመጣበት ፍጥነት ከፍተኛ ነው፡፡ ቴክኖሎጂው ከተዋወቀ ወዲህ ሥርጭቱ በሁለትና በሦስት እጥፍ እያደገ ነው፤›› በማለት የገለጹት አቶ ያሬድ፣ ምርቱን በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ለማድረስ የአቅም ችግር ባይኖርባም የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር ግን ፈተና እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ቴክኖሎጂውን የሚያከፋፍሉ ለአርሶ አደሩ በቅርብ የሚገኙ ወኪሎች አለመኖራቸው የዋጋ ውድነት እንዲፈጠር እንዳደረገና ይህንን አርሶ አደሮች በተደጋጋሚ ጊዜ የሚነሱት ጥያቄ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ ከረጢቱን በመጠቀም ምርት ሳይበላሽ ማትረፍ ከሚችሉት መጠን አኳያ ሲታይ፣ ዋጋው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም የሚሉት አቶ ያሬድ፣ የምርት መጠኑ ሲጨምር የአንዱ ፕላስቲክ ዋጋ ከሁለት እስከ ሦስት ብር ድረስ የዋጋ ቅናሽ ሊያሳይ እንደሚችል ይናገራሉ፡፡

መንግሥት ትኩረት የሚሰጠው ከሆነና የቀረጥ አከፋፈል ሥርዓቱን የሚያሻሽለው ከሆነም አሁን ካለው በታች በቅናሽ ሊሠራጭ እንደሚችል አክለዋል፡፡  የድኅረ ምርት ብክነት በአገሪቱ ትልቅ ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከአሥር እስከ 12 በመቶ የሚሆነው የምርት ብክነትም ምርት በማከማቸት ወቅት የሚከሰት ነው፡፡ ሆኖም ግን በድኅረ ምርት አሰባሰብ የሚታየው አማካይ የአገሪቱ የምርት ብክነት እስከ 30 በመቶ እንደሚገመት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ምርት በነቀዝ፣ በአይጥና በተለያዩ ተባዮች ስለሚበላ፣ በጥራትም ሆነ በመጠን ሲቀንስ ይታያል፡፡ በተለይ ሞቃታማ በሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች የግብርና ምርቶች በከፍተኛ ደረጃ በተባይ ለሚከሰት ብልሽት የተጋለጡ ናቸው፡፡

የወደራ ሁለገብ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ ይርዳው ዓለሙ እንደሚሉት፣ በአካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ከማሳ ከሰበሰቡ በኋላ ሳይበላሽ አከማችተው ለማቆየት ሲቸገሩ ቆይተዋል፡፡ ከሁለት ወራት በላይ ማስቀመጥ እንደማይችሉም ገልጸዋል፡፡

ማሽላ፣ በቆሎና ባቄላ በተለየ ሁኔታ በነቀዝ የሚጠቁ የምርት ዓይነቶች ሲሆኑ፣  አርሶ አደሮች ተስማሚ የማከማቻ ዘዴዎችን በማጣት፣ ዋጋውን በግማሽ ቀንሶ ለገበያ ለማቅረብ እንደሚገደዱ ይናገራሉ፡፡ የኢትዮጵየ ምርት ገበያ አባል የሆነው ይህ ዩኒየን፣ በአካባቢው የሚመረቱ የተለያዩ ጥራጥሬዎችና የሰብል እህሎችን ወደ ውጭ ለመላክ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ይሁንና ባለፈው ዓመት 400 ኩንታል የማሾና ሌሎች ጥራጥሬዎችን ለውጭ ገበያ ቢያቀርቡም፣ በጥራት ጉድለት ምክንያት ምርቱ  እንደተመለሰባቸው አስታውሰዋል፡፡ በመሆኑም አዲሱን ቀረጢት ከእንዲህ ዓይነቱ ሥጋት እንደሚቀረፍ ተስፋ ያደርጉበታል፡፡  

 

Standard (Image)

አዲስ አበባ ሁለተኛውን የሒልተን ሆቴል ልታገኝ ነው

$
0
0

ታፍቢቢ ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከሒልተን ዓለም አቀፍ ግሩፕ ጋር በመስማማት ‹‹ደብልትሪ ባይ ሒልተን›› የተባለውን የሆቴል ብራንድ በኢትዮጵያ ለማስተዳደር ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

በሒልተን በዓለም አቀፍ ሥር ከሚተዳደሩ 15 ታዋቂ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው ደብልትሪ ባይ ሒልተን በሚፈቅደው ከፍተኛ ደረጃ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት አካባቢ፣ ብራስ ሆስፒታል አጠገብ እየተገነባ የሚገኘው ይህ ሆቴል፣ ሒልተን እንዲያስተዳድረው ስምምነት የተደረገው ሰኞ፣ ነሐሴ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ነበር፡፡ ይህን ሆቴል ሒልተን እንዲያስረዳድረው ስምምነት የተደረገው ሰኞ፣ ነሐሴ 29 ቀን 2009 ዓ.ም ነበር፡፡ ይህን ሆቴል ሒልተን እንዲያስተዳድረው ለማድረግ የተደረገው ድርድር ረዘም ያለ ጊዜ መውሰዱም ታውቋል፡፡

በግንባታ ላይ የሚገኘው ባለ 11 ፎቅ ሆቴል፣ በአሁኑ ጊዜ 70 በመቶ የግንባታ ሒደቱ መጠናቀቁን የታፍቢቢ ቢዝነስ ግሩፕ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ተካ አስፋው ገልጸዋል፡፡

ሆቴሉ አውሮፓ ሠራሽ በሆኑ የግንባታ ዕቃዎች እየተገነባ እንደሚገኝ ሲታወቅ፣ ከቦሌ ኤርፖርት በአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መገኘቱና በአዲስ አበባ ከተማ ዋና እምብርት አካባቢ ላይ መገንባቱ፣ ከኤርፖርት በቅርብ ርቀት መቆየት ለሚመርጡ እንግዶች ተፈላጊ እንደሚያደርገውም ኃላፊዎቹ ይገልጻሉ፡፡

የሆቴሉ የ30 በመቶ ቀሪዎቹ ግንባታዎች በስምንት ወራት ውስጥ ተጠናቀው ሆቴሉ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀመር አቶ ተካ ገልጸዋል፡፡ ለሆቴሉ ውጫዊ ግንባታ፣ ውስጣዊ ዲዛይንና ልዩ ልዩ መገልገያ ዕቃዎችን ለማሟላት እስከ 300 ሚሊዮን ብር ድረስ እንደሚጠይቅ ተገምቷል፡፡ በግንባታው ሒደት ከ500 ሰዎች በላይ የተሳተፉ ሲሆን፣ አጠቃላይ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባም ከ400 እስከ 500 ሰዎች የሥራ ዕድል ሊፈጥር እንደሚችል አቶ ተካ ገልጸዋል፡፡

በዓለም ስመ ጥር የሆኑ የሥነ ሕንፃ ኩባንያዎችን በማወዳደር የሆቴል ዲዛይን እንዲሠራ የተመረጠው ኩባንያ ባቀረበው ዲዛይን መሠረት የሆቴሉ ግንባታ መጀመሩንም አቶ ተካ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሆቴላችን በዓለም ካሉ ታዋቂ ሆቴሎች መካከል አንዱ እንዲሆን በነበረን ምኞትና ጥረት፣ አንጋፋና በዓለም ታዋቂነትን ካተረፉት ውስጥ ሒልተን ሆቴልን በመምረጥ ለረዥም ጊዜ በመወያየትና ግንኙነት በማድረግ ዛሬ የተፈራረምነው ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ በዚህ መሠረት ከሒልተን ዓለም አቀፍ ሆቴሎች አንዱና ታዋቂ የሆነውን ‹‹ደብልትሪ›› ብራንድን መርጠናል፤›› ብለዋል፡፡

በደብልትሪ ባይ ሒልተን ብራንዱን በ40 አገሮች ውስጥ 500 ሆቴሎችን የሚያስተዳድረው ሒልተን ዓለም አቀፍ፣ በሥሩ ከሚገኙ 15ቱ ብራንዶች ውስጥ በኢትዮጵያ አዲስ አበባ ሒልተንና በሐዋሳ በሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ እየገነባው የሚገኘው ሆቴል ይጠቀሳሉ፡፡

ሒልተን ሆቴል በአዲስ አበባ ሲያስተዳድረው የቆየው ንብረት ከ50 ዓመታት በላይ በማስቆጠር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁ ብራንድ ሆቴሎች ፈር ቀዳጁ ነው፡፡ ይህንኑ በማስታወስ፣ አዲሱን ሆቴል ለማስተዳደር የተስማማው ሒልተን በአፍሪካም ሆነ በዓለም በርካታ መዳረሻዎች ካሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሥሪያ ቤት አቅራቢያ መገንባቱም አዲሱን ሆቴል ተመራጭ ከሚያደርጉት መካከል እንደሚመደብ፣ የሒልተን ሆቴል የአውሮፓ፣ መካከለኛው ምሥራቅና አፍሪካ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት ፓትሪክ ፊትዝጊበን ተናግረዋል፡፡ በርካታ ትዕይቶች ከሚታደሙበት ከሚሊኒየም አዳራሽ ጀምሮ፣ ለአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ ለአፍሪካ ኅብረትና ለሌሎችም ትልልቅ ተቋማት አማካይ ቦታ ላይ የሚገኝ፣ ከፍተኛ በሚባሉት የሆቴል ደረጃዎች መስክ የሚመደበው ይህ ሆቴል ለኢትዮጵያ የሆቴል ኢንዱስትሪ ትልቅ እሴት እንደሚሆንም ጠቅሰዋል፡፡

 

Standard (Image)
Viewing all 665 articles
Browse latest View live