Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all 665 articles
Browse latest View live

ሸውራራ ዕቅዶች ዋጋ ማስከፈላቸውን ቀጥለዋል

$
0
0

የአዲስ አበባ (ሰበታ) ጂቡቲ የባቡር ሃዲድ ግንባታ ሲጀመር መስመሩ የገቢና ወጪ ንግድ ማቀላጠፍ የሚያስችል በመሆኑ በርካቶችን ያስደሰተ ፕሮጀክት ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ባለቤትነት በሁለት የቻይና ኩባንያዎች የተገነባው ይህ የባቡር መስመር በጉጉት ሲጠበቅ ቆይቶ፣ ከወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባሉበት ተመርቋል፡፡ የባቡር ፕሮጀክቱ ከመመረቁ በፊት የጀመረውን የሙከራ ጉዞ ወደ ማገባደዱ የቀረበ ቢሆንም፣ ፕሮጀክቱ ያላካተታቸው ማዕቀፎች እየተስተዋሉ በመምጣታቸው ቅሬታ እየፈጠረ መጥቷል፡፡

እነዚህ ጉድለቶች የአሪቱ ፕሮጀክቶች ፕላን የማድረግ አቅም ጥያቄ ውስጥ የከተቱ ሆነዋል፡፡ 656 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኢትዮ ጂቡቲ አዲስ የባቡር መስመር ለምን ተግባር እንደተገነባ እስከመጠየቅ የደረሱ ባለሙያዎች ብቅ እያሉም ይገኛል፡፡ ምክንያቱም አራት ያህል ማዕቀፎች ፕሮጀክቱ ሲጀመር ጀምሮ ተካተው መሄድ ሲገባቸው፣ ጭራሽ ታሳቢ ባለመደረጋቸው ግንባታው ብቻውን ኢኮኖሚውን ሊደግፍ አይችልም ከሚል አስተሳሰብ የመጣ ጥያቄ እንደሆነ እየተስተዋለ ነው፡፡

የባቡር መስመሩ ከአዲስ አበባ ተጉዞ ጂቡቲ ቢደርስም ወደ ወደቦች የሚወስዱ መስመሮች እስካሁን አልተገነቡም፡፡ በዚህ ምክንያት ደረቅ ዕቃዎች የሚራገፉባቸው ወደቦች ውስጥ ሆነ ነዳጅ የሚራገፍበት ሆራይዘን ተርሚናል ውስጥ መግባት አይችሉም፡፡

ባቡሩ በተለመደው የጭነት አሠራር ዕቃ ጭኖ ወደ አገር ውስጥ ቢመጣም፣ ለምሳሌ በአዋሽ በሚገኘው የመጠባበቂያ ነዳጅ ማከማቻ ዲፖ ውስጥ ነዳጅ ያራግፍ ቢባል እንኳ ወደ ቅጥር ጊቢው የሚወስድ ሃዲድ አልተገነባም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአገሪቱ ትልቁ የደረቅ ወደብ ባለበት ሞጆ ደረቅ ወደብ ቅጥር ግቢ የሚገባበት የባቡር መስመርም አልተዘረጋም፡፡

ከዚህ ባሻገር ባቡሮቹ በኤሌክትሪክና በነዳጅ የሚሠሩ ቢሆኑም፣ በታዳሽ ኃይል እንደምትጠቀም ስትገልጽ ለቆየችው ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም ቢሆን የባቡር መስመሩ ቢጠናቀቅም የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት አስፈላጊ የሆኑትን የመሠረት ልማቶች ገና ናቸው፡፡ በቅርብ በሒልተን አዲስ አበባ በተካሄደ ጉባዔ ላይ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የምህንድስና ግዥና ጥገና ኃላፊ አቶ የኑስ ሙሻጋ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ጂቡቲ ዋና የባቡር መስመር ከጂቡቲ የነዳጅ ወደብ ከሆነው ሆራይዘን ተርሚናልና ከአዋሽ ብሔራዊ የመጠባበቂያ ዲፖ ጋር ባለመገናኘቱ በዚህ ዓመት ነዳጅ ማመላለስ አይጀምርም፡፡

አቶ የኑስ በዚህ ጉዳይ ላይ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ ‹‹ይህ የገጠመን ትልቅ ፈተና ስለሆነ ችግሩን መፍታት ይኖርብናል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ነዳጅ ከማመላለስ ይልቅ በባቡር ቢጓጓዝ ወጪን በከፍተኛ መጠን ይቀንሳል፡፡ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ የባቡር መስመሩ ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ስለወጣበት ለግንባታ የወጣውን ብድር በወቅቱ ለመመለስ ነዳጅ በባቡር ማመላለስ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ ስለሆነም ነዳጅ በባቡር አለመማላለስ ኪሳራ የሚሆንበት አጋጣሚም አለ ይላሉ፡፡

የባቡር ሃዲዱ የሚያጓጉዛቸውን ዕቃዎች ሞጆ ደረቅ ወደብ ለማድረስ 3.5 ኪሎ ሜትር አዲስ የሃዲድ ዝርጋታ ለማካሄድ እንቅስቃሴ ገና ተጀምሯል፡፡ ይህ አስፍቶ አለማየትና በጥልቀት አለመታቀዱ ያመጣው ውጤት ነው ይላሉ ባለሙያዎች፡፡ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሕመድ ቱስ ስሞኑን እንደተናገሩት፣ የሞጆ ደረቅ ወደብን ከባቡር መስመሩ ጋር ለማገናኘት 3.5 ኪሎ ሜትር የባቡር ሃዲድ ግንባታ እየተካሄደ ነው፡፡ ‹‹በኮምቦልቻና በመቐለ ደረቅ ወደቦች ግን ተጨማሪ ወጪ ሳይወጣባቸው ከወዲሁ ከዋናው የባቡር መስመር ጋር እንዲተሳሰሩ ተደርጎ ይገነባሉ ሲሉ የኢንተርፕራይዙ የወደብና ተርሚናል ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ደሳለኝ ገብረሕይወት አክለው ተናግረዋል፡፡

በኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶች በኩል ሲታይም ይኸው የፕላን ችግር መኖሩን የሚያመለክቱ ችግሮች ይታያሉ፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከሚያካሂዳቸው ፕሮጀክቶች መካከል ጊቢ ሦስት ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ግንባታው ተጠናቆ በተለይ በ2008 ዓ.ም. አገሪቱን የድርቅ አደጋ ባጋጠማት ወቅት ሌሎች ግድቦች ውኃ መያዝ ባለመቻላቸው በወሳኝ ችግር ወቅት የደረሰ ኃይል ማመንጫ ግድብ ተብሎ ይሞካሻል፡፡

ግድቡ በአሁኑ ወቅት ተጠናቋል ማለት የሚቻልበት ደረጃ ላይ ቢደርስም፣ እያመነጨ የሚገኘው ከማምረት አቅሙ በግማሽ ያነሰ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፓወር ጄኔሬሽን ኤግዚኪዩቲቭ ኦፕሬሽን ኦፊሰር አቶ አንዳርጌ እሸቴ ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው አጭር ቆጥታ እንደገለጹት፣ የግልገል ጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጫ አሥሩም ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት ይችላሉ፡፡

‹‹ነገር ግን እየተመረተ ያለው በአምስት ተርባይኖች ነው፡፡ የተቀሩት በሪዘርቭ ተይዘዋል፤›› ሲሉ አቶ አንዳርጌ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይህ ሊሆን የቻለውም በአገሪቱ የኃይል እጥረት ባለመኖሩ ነው፤›› ሲሉ አቶ አንዳርጌ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በእርግጥ የመረጃ ምንጮች እንደሚጠቁሙት በአገሪቱ የኃይል ፍላጎት ተሟልቶ ሳይሆን የትራንስሜሽንና የሰብስቴሽን ሥራዎች ባለመሠራታቸው ነው፡፡ በርካታ ፋብሪካዎች የኃይል ፍላጎት ቢኖራቸውም ራሱን የቻለ መስመር ስላልተዘረጋላቸው የሚቸገሩም በርካታ ናቸው፡፡ በከተሞች በተለይ የኃይል መቆራረጡ መሻሻል እያሳየ ቢሆንም፣ አሁንም እዚህም እዚያም ችግሩ እንዳለ የሚታይ ነው፡፡ በዋናነት ግን በአዲስ አባ በሰፊው እየተገነቡ ያሉ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ መስተጓጎልም ሆነ፣ ዕጣ የወጣባቸው ቤቶችም ለነዋሪዎች መተላለፍ ያልቻሉት በኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግር መሆኑ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ጭምር ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ በከተማው የሚገኙ አዳዲስ የመኖሪያ ቤቶች ኤሌክትሪክ አልባ ሲሆኑ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለሥልጣናት ግን ችግሩ የእነሱ ሳይሆን ኤሌክትሪክ የሚያሠራጨው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ላይ ጣት መቀሰራቸው አልቀረም፡፡ ያም ሆኖ ግን ኤሌክትሪክ አቅርቦት አለ ቢባልም ማጠንጠኛው ኤሌክትሪኩ አለመድረሱ ነው፡፡

በቅርብ የተቋቋመው የፌዴራል የተቀናጀ የመሠረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ ንጉሤ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ይህ ችግር በሁሉም የመሠረተ ልማት ተቋማት የሚስተዋል ነው፡፡  

አንድ ፕሮጀክት ሲታቀድ ስፋትና ጥልቀት ሊኖረው ይገባል፡፡ ‹‹የባቡር መስመር ለመገንባት ፈልገህ አትነሳም፣ ምንድነው የሚጓጓዘው ብለህ ትነሳለህ እንጂ›› በማለት የሚገልጹት አቶ በቀለ፣ ‹‹ሁሉም የመሠረተ ልማት ተቋማት የተናጠል ዕቅዳቸውን ለማሳካት የሚሯሯጡ በመሆኑ መሰል ችግሮች እየሰፉ መጥተዋል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መንግሥት አዲሱን የፌዴራል የተቀናጀ የመሠረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ አቋቁሟል፡፡ ይህ ኤጀንሲ ባለፈው ቅዳሜ በይፋ ሥራ የጀመረ ሲሆን፣ በተለይ ከዚህ በኋላ የሚሠሩት ግዙፍ የመሠረተ ልማት ተቋማት ወጥ በሆነ መንገድ በሚዘጋጀው ማስተር ፕላን እንዲመሩ ያደርጋል፡፡

እጅግ ችግር ያለባቸው ያልተጣጣሙ ፕሮጀክቶች በሚቋቋሙ ኮሚቴዎች እየተመሩ፣ ችግሩን እንዲያስተካክሉ መመርያ የተላለፈ ሲሆን፣ በግንባታ ሒደት ላይ ያሉት ፕሮጀክቶች ደግሞ ያላካተቱትን ጠቃሚ ግብዓት እያካተቱ ይሄዳሉ ተብሏል፡፡

መንግሥት ከ700 ቢሊዮን ብር በላይ በመመደብ የመንገድ፣ የባቡር ኔትወርክ፣ የቤቶች ልማት፣ የስኳር ልማት፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የውኃ ልማት፣ የኢነርጂ አቅርቦት የመሳሰሉ ግንባታዎችን በሰፊው በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

እነዚህን ፕሮጀክቶች በተለይ የመሠረተ ልማቶችን ዘርፍ አዲስ የተቋቋመው፣ የፌዴራል የተቀናጀ የመሠረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ፣ ሌሎቹ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የሚከናወኑ ቢሆንም፣ በማክሮ ኢኮኖሚ ደረጃ ያሉት ደግሞ በብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን የሚታዩ ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት የፕላን ያለመናበብ፣ ፕሮጀክቶች በተያዙላቸው የጊዜ ገደብ አለመጠናቀቅ፣ በሁለቱም ዘርፎች እየታየ ያለ ችግር ሲሆን፣ የስኳር ልማትና የማዳበሪያው ፋብሪካ ዘርፍ የእነዚሁ ችግሮች ሰለባዎች ሆነዋል፡፡

በስኳር ዘርፉ 2.25 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስኳር ምርት፣ 304 ሺሕ ሜትር ኩብ ኢታኖል፣ 200 ሺሕ ሔክታር ሸንኮራ አገዳ ልማት በፕሮጀክት ውስጥ የተያዙ ናቸው፡፡ ፋብሪካዎቹና የሸንኮራ አገዳ ልማት በታቀደለት ጊዜ ተጣጥሞ መሄድ ባለመቻሉ የደረሱ የሸንኮራ አገዳዎች እየተወገዱም እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ በማዳበሪያ ፋብሪካዎችም እንዲሁ አምስት ዩሪያ፣ ሦስት የዳፕ ፋብሪካዎች፣ አንድ ሰልፈሪክ አሲድ ፋብሪካ፣ አንድ የከሰል ማዕድን ቁፋሮ ግንባታዎች ይገነባሉ ተብሏል፡፡ ነገር ግን የማዳበሪያ ፋብሪካዎቹ ከእነዚሁ ችግሮች ማምለጥ እንዳልቻሉ እየተነገረ ይገኛል፡፡

በአጠቃላይ ፕሮጀክቶች በተያዙላቸው ጊዜ ቢጠናቀቁ፣ በትክክል በተሟላ መንገድ ቢታቀዱና አገሪቱ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የምታስመዘግብ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ግን እየተተገበረ ያለው የዚህ ተቃራኒ በመሆኑ አገሪቱን በሀብት ደረጃ ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ በሚገነቡ የመሠረተ ልማት አውታሮች አጀማመር ደስተኛ ቢሆንም፣ ፕሮጀክቶቹ እንዳማረባቸው የሚጠናቀቁ ባለመሆኑም ደስታ በሐዘን እየተቀየረም ይገኛል፡፡ 

Standard (Image)

የዕድገት ተስፋ የተሰነቀበት የኢትዮጵያና የቱርክ ትብብር

$
0
0

ከሁለት ሳምንታት በፊት በቱርክ ኢስታንቡል ከተማ የቱርክ አፍሪካ ኢኮኖሚክና ቢዝነስ ፎረም ለሁለት ቀናት ተካሂዶ ነበር፡፡ በፎረሙም ከተገኙት በርካታ የአፍሪካ አገሮች ተወካዮች ኢትዮጵያን ጨምሮ ከግማሽ በላይ ያህሉ በሚኒስትሮች ደረጃ የተሳተፉበት ሲሆን፣ ፎረሙንም የቱርክ ፕሬዚዳንት ሪሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን ተገኝተው ከፍተውታል፡፡ ኢትዮጵያም በኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተውና በአገር አቀፍና በክልል የንግድ ምክር ቤቶች ኃላፊዎች ተወክላ ፎረሙን ተሳትፋለች፡፡ ቱርክ በአፍሪካ ካላት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ውስጥ ግማሽ ያህሉን በኢትዮጵያ ያፈሰሰች ሲሆን፣ አሁንም በርካታ የቱርክ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፡፡ በፎረሙ ላይ ከተሳተፉት በቱርክ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ አያሌው ጐበዜን በፎረሙ፣ እንዲሁም በሁለቱ አገሮች የንግድና የሁለትዮች ግንኙነት ዙሪያ ዘካሪያስ ስንታየሁ በኢስታንቡል አግኝቷቸው ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ከቱርክ አፍሪካ ኢኮኖሚክና ቢዝነስ ፎረም ኢትዮጵያ ምን ትጠቀማለች?

አቶ አያሌው፡- በቱርክ አፍሪካ ኢኮኖሚክና ቢዝነስ ፎረም ላይ ከኢትዮጵያ የሚመለከታቸው የንግድ ማኅበረሰብና በኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች፣ እንዲሁም የንግድ ምክር ቤት ኃላፊዎች በኢስታንቡል ተገኝተዋል፡፡ በዚህ ፎረም ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተውም ተሳትፈዋል፡፡ በመሆኑም ይህ ፎረም በቱርክና በአፍሪካ በተለይም በቱርክና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትስስር ያጠናክረዋል፡፡ ፎረሙ በኢንዱስትሪ ልማቶችና በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ከማጠናከሩም ባሻገር የተሞክሮ ልውውጥ በማድረጉ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ የተለያዩ የቢዝነስ ፎረሞች ተካሂደዋል፡፡ ይህንን ግን ለየት የሚያደርገው በርካታ ባለሀብቶችና የአፍሪካ አገሮች የመንግሥት ኃላፊዎች የተገኙበት መሆኑ ነው፡፡     

ሪፖርተር፡- ቱርክ በአፍሪካ ኢንቨስት ካደረገችው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ውስጥ ግማሽ የሚሆነው በኢትዮጵያ ነው፡፡ በአጠቃላይ የሁለቱን አገሮች የንግድ ግንኙነት እንዴት ይገመግሙታል?

አቶ አያሌው፡- ምንም እንኳን የዘገየ ሪፖርት ቢሆንም የሁለቱ አገሮችን የንግድ ልውውጥ ስንመለከት እ.ኤ.አ. በ2014 በቱርክ በኩል ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ ወደ 70 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ነው፡፡ በመሆኑም በንግዱ በኩል ያለው ንፅፅር በጣም የተራራቀ ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ የኢንዱስትሪ ዕድገቱ ሲመጣና አግሮ ፕሮሰሲንግ ስንጀምር፣ ማለትም በግብርናው ምርታችን ላይ እሴት ጨምረን ወደ ውጭ ስንልክ፣ ይህ የንግድ ልውውጥ ይጨምራል የሚል እምነት አለን፡፡

ሪፖርተር፡- ምንም እንኳን በርካታ የቱርክ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ቢኖሩም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እነዚህ ኩባንያዎች የተለያዩ ችግሮች እየገጠሟቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አንዳንዶቹ ኩባንያዎች እንዲያውም ከስረው እስከመውጣት ደርሰዋል፡፡ ስለዚህ ይህ በሁለቱ አገሮች የንግድ ልውውጥ ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ ፈጥሯል?

አቶ አያሌው፡- የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ሽግግር እያደረገ ነው፡፡ የኢንዱስትሪውን ዕድገት ለማምጣት በግብርናው ምርትና ምርታማነትን መጨመር እንዳለበት ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመለወጥ ከምታደርገው ሒደት ጎን ለጎን መሠረተ ልማቶች እየተገነቡ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ የኃይል፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽንና የመንገድ መሠረተ ልማቶች እየተገነቡ ነው፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ አስቀድመው የገቡ የቱርክ ባለሀብቶች በአገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ነገር በሚገባ ያውቃሉ፡፡ ሆኖም ግን በኢትዮጵያ የሚገጥሟቸው ችግሮች በሒደት ሊፈቱ እንደሚችሉ የቱርክ ባለሀብቶች ያውቃሉ፡፡ እንዲያውም በቅርብ ጊዜያት በኢትዮጵያ በነበረው አለመረጋጋት የአንዳንድ የቱርክ ኩባንያዎች ንብረት ወድሟል፡፡ ሆኖም ግን ከቱርክ ባለሀብቶች ጋር በነበረኝ ውይይት ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ በአገሪቱ ያለው ሁኔታ እንደሚሻሻል ተስፋ ነው ያላቸው፡፡   

ሪፖርተር፡- በቅርቡ በአገሪቱ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ የበርካታ ኩባንያዎች ንብረት መውደሙ ይታወሳል፡፡ በዚህም ተቃውሞ የቱርክ ኩባንያዎች ተጠቂ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የቱርክ ኩባንያዎች በአገሪቱ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ምን ዓይነት ሥጋት ገጥሟቸዋል?

አቶ አያሌው፡- በቅርቡ በኢትዮጵያ ተገኝቼ ጉዳት የደረሰባቸውን ኩባንያዎች አይቻለሁ፡፡ ሥጋት አደረብን የሚሉ ባለሀብቶችንም አነጋግሬያለሁ፡፡ ባለሀብቶቹ ያላቸው ስሜት በኢትዮጵያ የተፈጠረው አለመረጋጋት ጊዜያዊ እንደሆነ የሚያመለክት ነው፡፡ ይህንንም ችግር በተለየ አግባብ ሊቀርፉት እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ማለት በኢትዮጵያ መንግሥት፣ በአካባቢው ኅብረተሰብ፣ በራሳቸው ጥረትና ካላቸው የኢንሹራንስ ኩባንያ ጋር በመሆን የጠፋባቸውን ነገር በማስተካከል ወደ ልማት እንደሚገቡና ይህም ተስፋ እንደማያስቆርጣቸው ገልጸውልኛል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት የመልካም አስተዳደር ችግሮች እየፈታን በሄድን ቁጥር ሁኔታዎች እየተስተካከሉ እንደሚሄዱ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ከፍተኛ ሚና ያላትና የሕዝቧ ብዛት ወደ 100 ሚሊዮን የሚደርስ ነው በማለት መንግሥት አንዳንድ ማስተካከያዎች ማድረግ ከቻለ ለቱርክ ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ከየትኛውም አገር የተሻለች ናት የሚል አመለካከት ነው ያላቸው፡፡ በእኛ በኩል የራሳችንን የቤት ሥራ መሥራት ነው የሚጠበቅብን እንጂ፣ በእነሱ በኩል የመንግሥትንና የኅብረተሰቡን ድጋፍ እያገኙ ለመቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን ለማየት ችያለሁ፡፡      

ሪፖርተር፡- የእኛ የቤት ሥራ ሲሉ ምን ማለትዎት ነው?

አቶ አያሌው፡- የእኛ የቤት ሥራ ማለት አሁን ሕዝቡ የተለያዩ ጥያቄዎችን እያነሳ ነው፡፡ መንግሥት ደግሞ በራሱ ግምገማ ተጨባጭ ናቸው ለሚላቸው ጥያቄዎች የማስተካከያ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ ተዘጋጅቷል፡፡ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተገቢው አገልግሎት እንዲገኝ ማድረግ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራውን ማፋጠን፣ ኢንዱስትሪውን ለማስፋፋትና ኢንቨስት ለሚያደርጉ ሰዎች አስፈላጊውን አገልግሎት መስጠት እስከተቻለ ድረስ ይህንን ጊዜያዊ ችግር ልናልፈው እንደምንችል እኛም ባለሀብቶችም እናምናለን፡፡ በቅርቡ የተካሄደው የሥልጣን ሽግሽግ፣ ሕጎችን የማሻሻሉ ሥራና በተከታታይ የሚመጡ ለውጦችን ተከትሎ የግል ባለሀብቱ ተሳትፎ እየጎለበተ እንደሚመጣ እምነት አለን፡፡  

ሪፖርተር፡- የትኛዎቹ ሕጎች ናቸው የሚሻሻሉት?

አቶ አያሌው፡- በፕሬዚዳንቱ መግለጫ ላይ እንደተነገረው ለምሳሌ የምርጫ ሕጉን ማስተካከልና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ማለትም በአገሪቷ ውስጥ በሰላም የሚታገሉት አማራጭ ሐሳቦችን ለሕዝብ እንዲገልጹና ለዴሞክራሲ ሥርዓቱ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ መድረኩ መመቻቸት አለበት፡፡ ከዴሞክራሲው ባሻገርም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለልማቱ ጭምር ጠቃሚ ሐሳቦችን የሚያቀርቡበትን አሠራር መፍጠር ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ በነበረው ተቃውሞ ጉዳት ከደረሰባቸው ኩባንያዎች መካከል ካሳ የጠየቁ የቱርክ ኩባንያዎች አሉ?

አቶ አያሌው፡- እስካሁን ድረስ ካሳ የጠየቁ ኩባንያዎች አላውቅም፡፡

ሪፖርተር፡- በተቃውሞ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት አስበው ሥጋት የገጠማቸው ኩባንያዎች አሉ? በአጠቃላይስ ተቃውሞው የኢንቨስተሮችን እምነት በመሸርሸሩ ረገድ ምን ዓይነት ተፅዕኖ አስከትሏል?

አቶ አያሌው፡- አሁን የተፈጠረውን ሁኔታ ባለሀብቱ ይጠይቀናል፡፡ ‹‹ቅጽበታዊ የሆነ አለመረጋጋት በተወሰኑ አካባቢዎች የተከሰተው ለምንድን ነው?›› ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ኢትዮጵያ ግን 100 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብና ሰፊ ግዛት ያላት መሆኑን ያውቃሉ፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ስለተነሱት ችግሮች ቢጠይቁም፣ መንግሥት ባለፉት 25 ዓመታት ያመጣው ለውጥና ሕዝቡ ውስጥ ገብቶ የመሥራት ትልቅ አቅም እንዳለው ያውቃሉ፡፡ ስለዚህ ተስፋ አንቆርጥም፣ እነዚህም ነገሮች እንደሚሻሻሉ እናምናለን ብለው፣ የንግድ ፎረም ይዘጋጅልን ብለው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ በቅርቡም በርካታ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ ሄደው ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡ በእኛ ኤምባሲ በኩል ቀጠሮ እየተያዘላቸው የሚሄዱ ኩባንያዎችም አሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በኤሌክትሪክና በአግሮ ፕሮሰሲንግ የሚሳተፉ ሲኖሩ፣ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክ በተለይም ባልተጀመሩት ፓርኮች ውስጥ ለመግባት ያቀዱ ኩባንያዎች አሉ፡፡ በአጠቃላይ ችግሩ ምንድን ነው ብለው ይጠይቁና ወደ ኢትዮጵያ ሄደው ግን ሥራችንን መሥራት እንፈልጋለን ይሉናል፡፡ በተለይ በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ገብተው ለመሥራት የተዘጋጁ በርካታ ኩባንያዎች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የቱርክ ኩባንያዎች የኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት ጥያቄ አቅርበዋል? ወይስ መንግሥት በሚገነባቸው ፓርኮች ለመግባት ነው ፍላጎታቸው?

አቶ አያሌው፡- እነሱ በአዲስ አበባና በዙሪያዎቿ ቦታ ለማግኘት ፍላጎት አላቸው፡፡ በእኛ በኩል መሠረተ ልማቱን ለማሟላትና የመንግሥት ድጋፍ ለመስጠት፣ በኃይል፣ በመሬት፣ በግብር አከፋፈል፣ በብድር አሰጣጥና በአጠቃላይ በተለያዩ የመሠረተ ልማቶች እንዲደገፉ ካስፈለገ ወደ ኢንዱስትሪ ልማት መግባት አለባቸው፡፡ ይህንን የቻይና፣ የደቡብ ኮሪያና የሌሎችም አገሮች ኩባንያዎች እንዴት እየተሳተፉ እንደሆነ እየገለጽንላቸው ነው፡፡ መንግሥት ባለማቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ቢገቡ በጣም ተመራጭ ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ፓርኮች የተሟሉ መሠረተ ልማቶች አሏቸው፡፡ ነገር ግን በራሳችን እናልማም ቢሉ ዝግ ነው ማለት አይደለም፡፡ ሆኖም ይኼኛው ግን አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም መሠረተ ልማቱን ለማሟላት ከባድ ነው፡፡ በመሆኑም በመንግሥት አቅጣጫ መሠረት እንዲገቡ የማሳመን ሥራ እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቱርክ ኩባንያ እየተገነባ ያለው የአዋሽ ወልዲያ የባቡር ፕሮጀክት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

አቶ አያሌው፡- ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ የሆነው የአዋሽ ወልዲያ ፕሮጀክት የተጀመረው እ.ኤ.አ. በሚያዚያ ወር 2015 ነበር፡፡ ግንባታውን የሚያካሂደው ያፒ መርከዝ ማሽነሪዎቹን አንቀሳቅሶ ግንባታ በጀመረ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 50 በመቶውን ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ ግንባታውም በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ፕሮጀክቱም 1.7 ቢሊዮን ዶላር ያወጣል፡፡ የፕሮጀክቱ ገንዘብም 300 ሚሊዮን ዶላሩ ከቱርክ ኤግዚም ባንክ የተገኘ ሲሆን፣ ከሌሎች የአውሮፓ አገሮች ባንኮችም ብድር  ተገኝቷል፡፡ መንግሥትም 15 በመቶ የሚሆነውን ይሸፍናል፡፡  

ሪፖርተር፡- በሁለቱ አገሮች መካከል የሚደረጉ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ምን ይመስላሉ?

አቶ አያሌው፡- ከዚህ በፊት በነበሩ ስምምነቶች ከመከላከያ ጋር ስምምነት አሏቸው፡፡ የተሞክሮ ልውውጦችና የቴክኖሎጂ ሽግግር ያደርጋሉ፡፡ ባለፈው ዓመት ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ጋር ስምምነት አድርገዋል፡፡ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር እንዲሁ ነፃ የትምህርት ዕድል ይሰጣሉ፡፡ ለምሳሌ ቱርክ ወደ 200 የሚደርሱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝተው የመጡ አሉ፡፡ ይህ የነፃ የትምህርት ዕድል ከፍ እንዲል እየተነጋገርን ነው፡፡ በአጠቃላይ በባህል ልውውጥ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በመከላከያ እንዲሁም ከትምህርት ጋር በተገናኘ የሚያደርጉትን ድጋፍ ለማጠናከር እየሠራን ነው፡፡

በከተሞች በኩል ከአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ሐዋሳና ባህር ዳር ግንኙነት ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በተለይ አዳማና አዳና የሚሏት የእነሱ ከተማ ስምምነት ፈጥረዋል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከአንካራ ዩኒቨርሲቲ ጋር ስምምነት አለው፡፡ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲም አጋር ዩኒቨርሲቲ ፈልጉልኝ እያለ ነው፡፡ የአንካራ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር ስምምነት አድርጓል፡፡   

Standard (Image)

የአዋሽ ባንክ ድንበር ተሻጋሪ ውጥን

$
0
0

የአዋሽ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ምርጫ ይካሄዳል በተባለ ቁጥር የሚፈጠሩ ውዝግቦች ይታወሳሉ፡፡ የቦርድ ዳይሬክተር ለመሆን የሚደረገው ፉክቻ ለተከታታይ ዓመታት በግልጽ ሲንፀባረቅ ቆይቷል፡፡ ቅዳሜ ኅዳር 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ባንኩ በጠራው ጠቅላላ ጉባዔ አዳዲስ የቦርድ ዳይሬክተሮች ምርጫ ቢያካሂድም፣ በቀደሙ የምርጫ ዘመኖች የታየው ዓይነት ፉክቻ አልተስተናገደም፡፡ ከምርጫው በፊትም ይነሱ የነበሩ ውዝግቦች ሳይከሰቱ በአዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት ምርጫው ሊካሄድ ችሏል፡፡ ይህ ብዙዎችን አስደስቷል፡፡ በቅዳሜው የባንኩ ጠቅላላ ጉባዔ ከምርጫው ቀደም ብሎ የባንኩ የ2008 በጀት ዓመት የሥራ ክንውን ያስደመጠው ሪፖርትም የባንኩን ባለአክሲዮኖች ሳያስደስት አልቀረም፡፡

የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታቦር ዋሚ ለባለአክሲዮኖች ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት፣ የባንኩ የ2008 በጀት አፈጻጸም አርኪና የተመዘገበውም ውጤት በተለያዩ የባንክ አገልግሎት ዘርፎች ሲታይ ቀዳሚ መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ የባንኩ ያልተጣራ ትርፍ ከትርክ ክፍፍል ድርሻና ከታክስ በፊት 1.004 ቢሊዮን ብር መድረሱ ለስኬቱ ቀዳሚ ተምሳሌት ተደርጓል፡፡ በበጀት ዓመቱ የተገኘው ትርፍም ከቀዳሚው ዓመት በ16 ከመቶ ወይም በ134.8 ሚሊዮን ብር ብልጫ አለው፡፡ የተጣራ ትርፉ 743 ሚሊዮን ብር በመድረሱ በግል ባንኮች ታሪክ ከሚመዘገበው ውስጥ ዳሸን ባንክና አዋሽ ባንክን የሚስተካከላቸው አለመገኘቱን የሚያመላክት ሆኗል፡፡ ለባንኩ ከፍተኛው የተጣራ ትርፍ ሆኖም ተመዝግቧል፡፡ ባንኩ ከግል ባንኮች አፈጻጸም ጋር ሲታይ ብልጫ የወሰደበት ማሳያ ተብሎ የተጠቀሰው ሌላው አፈጻጸሙ በሀብት መጠን ባንኩ የደረሰበት ደረጃ ነው፡፡ በ2008 በጀት ዓመት ማጠናቀቂያ ወቅት የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 31.1 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህም ከግል ባንኮች ከፍተኛው መጠን ነው ተብሏል፡፡

አዋሽ ባንክ የሀብት መጠኑን ከ31 ቢሊዮን ብር በላይ እንዲደርስ ካስቻሉት መካከል ከሌሎች ባንኮች ቀደም ብሎ የራሱ ሕንፃዎች ባለቤት ሆኖ መገኘት መቻሉ አንዱ ነጥብ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት አገልግሎት ላይ የዋሉና በግንባታ ሒደት ላይ ያሉ ከ20 በላይ ሕንፃዎች ባለቤት ነው፡፡

በ2008 በጀት ዓመት ብቻ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የወጣባቸውን በአዲስ አበባ ልደታ አካባቢ፣ ባልቻ አባ ነፍሶ የሚል ስያሜ ያለውን ባለ10 ፎቅ ሕንፃ ግንባታ አጠናቆ ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡ በሐዋሳ ከተማም ስምንት ወለል ያለው ሕንፃ አስመርቋል፡፡ በአዳማ ከተማም ተመሳሳይ ሕንፃ በማስገባት ወደ ሥራ ማስገባቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ባንኩ ከግል ባንኮች የራሱን ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ቀድሞ በመገንባትም ይጠቀሳል፡፡

በተቀማጭ ገንዘብ መጠን በኩል (ኤልሲ በመክፈት የሚገኘውን ጨምሮ) ባንኩ ያሰባሰበው የገንዘብ መጠን 24.2 ቢሊዮን ብር ደርሶለታል፡፡ የተቀማጭ ገንዘቡ ዕድገት ከቀዳሚው ዓመት አኳያ በ4.7 ቢሊዮን ብር ጨምሯል፡፡ በዚህ ረገድ ባንኩ ያሳየውን ውጤት አቶ ዋሚ ሲገልጹት ‹‹ይህ የተቀማጭ ገንዘብ ጭማሪ ከሌሎች የግል ባንኮች አንፃር ሲታይ ከፍተኛውን መጠን የያዘ ነው፤›› ብለውታል፡፡ ይህም ባንኩ ለተከታታይ ዓመታት ዕድገቶችን በማስጠበቅ ያስመዘገባቸው ውጤቶች ከግል ባንኮች አኳያ በኢንዱስትሪው ያለውን ድርሻ ማስጠበቅ እንዳስቻለውም አቶ ዋሚ ጠቅሰዋል፡፡ ባንኩ ብልጫ ይዥበታለሁ በማለት በቦርድ አመራሮቹ ይፋ ያደረገው የብድር መጠን ሌላኛው ነጥብ ነው፡፡ ባንኩ በበጀት ዓመቱ ከቀዳሚው ዓመት ይልቅ የ24 በመቶ ወይም የ2.97 ቢሊዮን ብር ጭማሪ የተመዘገበበትን ብድር በመስጠት በአጠቃላይ 15.4 ቢሊዮን ብር ያስመዘገበ ብድር ለኢኮኖሚው ክፍሎች አቅርቧል፡፡ ባንኩ ያስመዘገበውን የብድር መጠን ከሌሎች የግል ባንኮች አኳያ ‹‹አዋሽ ባንክ በብድር መጠን ከግል ባንኮች በመሪነት ደረጃ እንዲቀመጥ አስችሎታል፤›› በማለት የቦርድ ሰብሳቢው ገልጸውታል፡፡

አዋሽ ባንክ በ2008 በጀት ዓመት ጠቅላላ ገቢው 2.8 ቢሊዮን ብር መድረሱን የጠቆሙት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ፀሐይ ሽፈራው፣ ከግል ባንኮች አንፃር ሲታይ በአንድ በጀት ዓመት የተገኘ ከፍተኛው ገቢ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ከቀዳሚው ዓመት የ523 ሚሊዮን ብር ወይም 23 በመቶ ዕድገት የታየበት ሆኗል፡፡  

በአንፃሩም የባንኩ 2008 በጀት ዓመት ጠቅላላ ወጪ በ287.8 ሚሊዮን ብር ወይም በ27 ከመቶ አድጎ 1.8 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ እንደገለጹት፣ ከጠቅላላ ወጪው ለተቀማጭ ሒሳብ ወለድ ክፍያ 43 በመቶ፣ ለሠራተኞች ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም 34 በመቶ ወጭ የተደረጉትን በዓበይትነት ተጠቅሰዋል፡፡

አዋሽ ባንክ በ2008 በጀት ዓመት እንደ ቀድሞ ዓመታት እምብዛም ዕድገት አላስመዘገበትም ተብሎ የተጠቀሰው በውጭ ምንዛሪ ግኝት መስክ የነበረው እንቅንቅስቃሴ ነው፡፡ የባንኩ ኃላፊዎች እንደገለጹት፣ ባንኩ በ2008 በጀት ዓመት ያገኘው የውጭ ምንዛሪ በስድስት ከመቶ ወይም በ26.6 ሚሊዮን ብር ቀንሷል፡፡

ካቻምና 444.6 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ አስመዝግቦ የነበረ ቢሆንም፣ በ2008 ያገኘው የምንዛሪ መጠን ግን ወደ 418 ሚሊዮን ዶላር ወርዷል፡፡ ለውጭ ምንዛሪ ግኝቱ መውረድ ምክንያት ተብለው የጠቀሱት አገሪቱ ከወጪ ንግድ ያገኘችው ገቢ መቀነሱና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በወጪ በገንዘብ አስተላላፊ ወኪል ድርጅቶች በኩል ለወዳጅ ዘመዶቻቸው በባንኩ በኩል የሚልኩት የውጭ ገንዘብ መጠን በመቀነሱ ነው ብለዋል፡፡ ባንኩ በአገር  ወስጥ ብቻ ሳይሆን በምሥራቅ አፍሪካም ቀዳሚ ከሚባሉ ባንኮች አንዱ ለመሆን እየሠራ ስለመሆኑ የገለጹት አቶ ፀሐይ፣ ይህንንም ለማሳካት ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ይናገራሉ፡፡        

ባንኩ በምሥራቅ አፍሪካ ከሚገኙ የግል ባንኮች ከመጀመሪያዎቹ 10 ባንኮች ተርታ ለመሰለፍ የሚያስችለውን ሥራ ለመሥራት KPMG ከተባለ አማካሪ ድርጅት ጋር አጋርነት መፍጠሩን አቶ ፀሐይ ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ትራንስፎርሚንግ AIB ቪዥን 2015›› በሚል ርዕስ የተነደፈው የባንኩ የአሥር ዓመታት ፍኖተ ካርታንም መተግበር ጀምሯል ተብሏል፡፡ ፍኖተ ካርታው የባንኩን አሠራር በመቀየር፣ የደንበኞችን ፍላጎት በማርካትና ባንኩን በማሳደጉ ረገድ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል፡፡ በዚሁ ፍኖተ ካርታ መሠረት በአዲስ መዋቅር የሰው ኃይሉን ማደራጀቱንም ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡ ባንኩ የአምስት ዋና ኦፊሰሮችንና የሦስት ምክትል ዋና ኦፊሰሮችን ምደባ አካሂዷል፡፡ የ22 ዳይሬክተሮችን መዋቅሮች ከፍቶም ቦታ ደልድሎ ምደባ ማካሄዱን አስታውቋል፡፡ 

ምንም እንኳ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ውስጥ ባላቸው አቅምና በሚሰጡት የብድር መጠን የሚጠቀሱ የግል ባንኮች እስካሁን ባይታዩም፣ አዋሽ ባንክ ጨምሮ ጥቂት የማይባሉት ባንኮች በአፍሪካ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ቦታ ለማግኘት ያልማሉ፡፡ በዚህ ረገድ በተወሰነ ደረጃ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተለያዩ መለኪያዎች በምሥራቅ አፍሪካ ካሉ ባንኮች ውስጥ ስሙ ሲጠቀስ፣ ባንኮችን በተለያየ አቅምና መለኪያ የሚያወዳድሩ የፋይናንስ መጽሔቶችም ይህንኑ ባንክ ሲጠቅሱት እንደነበር ይታወሳል፡፡

 

Standard (Image)

ፕሬዚዳንቱን ባሰናበተ ማግሥት ቡና ባንክ ጠቅላላ ጉባዔውን አካሂዷል

$
0
0

ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ከተመሠረተ ሰባተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ የ2008 በጀት ዓመት የሥራ ክንውኑን ይፋ ለማድረግ የባንኩን ባለአክሲዮኖች በመጥራት ጠቅላላ ጉባዔውን እሑድ፣ ኅዳር 11 ቀን 2008 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ አካሂዷል፡፡

ሰኔ 2001 ዓ.ም. የተቋቋመውን ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ለሰባት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት (በዋና ሥራ አስፈጻሚነት) ሲመሩ የቆዩት አቶ እሸቱ ፋንታዬ፣ ታኅሳስ 3 ቀን 2007 ዓ.ም. በተደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት ለመጪው ዓመት በሰላም ያገናኘን ብለው ባለአክሲዮኖችን ቢያሰናብቱም በጠቅላላ ጉባዔ ወቅት ግን አልነበሩም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከሦስት ሳምንት በፊት ‹‹በፈቃዳቸው ኃላፊነታቸውን ለቀዋል፤›› በመባሉ ነው፡፡

በምትካቸው አቶ ታደሰ ጨንክል ተጠባባቂ ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ተሰይመዋል፡፡ አቶ እሸቱ በጠቅላላ ጉባዔው ወቅት ባይገኙም፣ በዕለቱ የጉባዔው ተሳታፊዎች እጅ ውስጥ ግን ነበሩ፡፡ ይኸውም የ2008 በጀት ዓመት የባንኩን ክንውንና የሒሳብ ሪፖርት በሚያመለክተው መጽሔት ላይ የባንኩ ዋና አስፈጻሚነታቸው ተገልጾ በምስላቸው የተደፈገ መረጃ ውስጥ በመታየታቸው ነው፡፡ የ2008 ክንውናችን ይህንን ይመስል ነበር ብለው በፊርማቸው ጭምር ያረጋገጡበት ሪፖርት ለባለአክሲዮኖች የቀረበበት ነበር፡፡

ከባንኩ የተገኘው መረጃ የሚጠቁመው ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ከኃላፊነት የለቀቁት በዓመታዊ መጽሔቱ የቀረበው የሒሳብ ሪፖርት ከተሰናዳ በኋላ መሆኑን ነው፡፡በመጽሔቱ አቶ እሸቱና የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ኢንጂነር ጥበቡ እሸቴ በጋራ ባኖሩት መልዕክት፣ ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ በ2008 በጀት ዓመት ባንኩ ቁልፍ ከሆኑ የፋይናንስ አፈጻጸም መለኪያዎች አንፃር ጥሩ የሚባል ውጤት ያገኘበት ነው ይላል፡፡ የትርፍ መጠኑም ቢሆን በ37 በመቶ የጨመረ ሲሆን፣ ከታክስ በፊት 250 ሚሊዮን ብር ማግኘት ችሏል፡፡ ከዓምናው ትርፍ አኳያም በ68.5 በመቶ በልጦ ተገኝቷል፡፡  

የባንኩ የተጣራ ትርፍ 187 ሚሊዮን ብር ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ይህ የትርፍ መጠን በአንድ መቶ ብር የአክሲዮን ድርሻ ዋጋ ሲሰላም፣ ለባለአክሲየኖች የሚደርሰው የትርፍ ድርሻ 34.3 ብር መድረሱን የሚጠቁም ነው፡፡ ይህ ውጤት በዓመቱ ከታቀደውና በስትራቴጂ ሰነድ ውስጥ ከተቀመጠው ዕቅድ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሆኑን የሚጠቁሙት ተሰናባቹና የባንኩ ቦርድ ሰብሳቢ፣ ከባንኩ ዕድሜ አኳያ ሲታይም ውጤቱ ጉልህ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ከባንኩ ዝርዝር የሒሳብ ሪፖርት መረዳት እንደሚቻለውም፣ አንድ ሺሕ ብር ዋጋ ያለው አክሲዮን 343.2 ብር ያስገኘ መሆኑን ነው፡፡ በ2007 አንዱ አክሲዮን አስገኝቶ የነበረው ትርፍ 286.6 ብር ነበር፡፡

በአቶ እሸቱና በኢንጂነር ጥበቡ የጋራ ሪፖርት መሠረት በ2008 በጀት ዓመት የባንኩ ተቀማጭ የገንዘብ መጠን በ54 በመቶ አድጎ 5.38 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ የብድር መጠኑንም 51 በመቶ ጨምሮ 3.7 ቢሊዮን ብር ሊደርስ መቻሉን ይገልጻል፡፡ የባንኩ የተበላሸ ብድር መጠን ግን 3.5 በመቶ ሆኗል፡፡ ይህ የተበላሸ የብድር መጠን  ከቀዳሚ በጀት ዓመትም የበለጠ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት የባንኩ የተበላሸ የብድር መጠን ሦስት በመቶ ነበር፡፡ በመሆኑም የተበላሸ የብድር መጠናቸው ከጨመረባቸው ጥቂት ባንኮች መካከል አንዱ አድርጐታል፡፡ በውጭ ምንዛሪ በጀት ረገድም 98.5 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቱን የሚጠቅሰው ሪፖርት፣ በመስኩ የ23.1 በመቶ ዕድገት እንዳሳየ አስታውቋል፡፡

የባንኩ የሀብት መጠን 6.82 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ በ2.37 ቢሊዮን ብር ያህል ሀብቱን ማሳደግ ችሏል፡፡ ቡና ባንክ በበጀት ዓመቱ 22 አዳዲስ ቅርንጫፎችን ከፍቶ ጠቅላላ ቅርንጫፎቹን 102 አድርሷል፡፡ እንደ ባንኩ ሪፖርት ከሆነም በቅርቡ በ15 ኤቲኤሞች የክፍያ ካርድ አገልግሎት ይጀምራል፡፡

   

Standard (Image)

ንብ ባንክ ከግል ባንኮች ይልቅ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ አበዳሪ ሆኖ ተገኝቷል

$
0
0

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ ቀዳሚ ከሚባሉት ስድስት የግል ባንኮች ውስጥ አንዱ ሆኖ ዘልቋል፡፡ ባለፉት ስድስት ዓመታት ሲመዘገብ የቆየው የባንኩ የትርፍ ዕድገት ግን የተለየ አካሄድ ይዞ መዝለቁን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በአምስት ዓመታት የባንኩ እንቅስቀቃሴ ወቅት በአማካይ የተመዘገበው የትርፍ ዕድገት 6.1 በመቶ የመሆኑ ጉዳይ ከቀሪዎቹ 15 ባንኮች የትርፍ ዕድገት ጋር ሲተያይ ይለያል፡፡ የባንኩ የ2008 በጀት ዓመት የትርፍ መጠንም ከታክስ በፊት 458 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህ ትርፍ ከፍተኛ የትርፍ መጠን ካስመዘገቡ ከስድስቱ የግል ባንኮች ዝርዝር ውስጥ የሚያሰልፈው ሆኗል፡፡ ይሁን እንጂ የትርፍ ዕድገቱ ከሌሎቹ አንፃር ሲታይ የተመጠነ ነው፡፡ እስካሁን የ2008 በጀት ዓመት ሪፖርታቸውን ካቀረቡ ባንኮች ለመረዳት እንደተቻለው፣ ያስመዘገቡት የትርፍ ዕድገት ባለነጠላ አኃዝ አለመሆኑን ነው፡፡

የንብ ባንክ ዓመታዊ ትርፍ ሳያቋረጥ እያደገ መሆኑን የሚያሳየው የባንኩ የ2008 የበጀት ዓመት የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት፣ ባለፉት አምስት ዓመታት የባንኩ አማካይ የትርፍ ዕድገት 6.1 በመቶ ሆኖ መቆየቱን አስፍሯል፡፡

ባንኩ በተሸኘው በጀት ዓመት ያስመዘገበው ያልተጣራ ትርፍ 458 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህ ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት በ4.1 ከመቶ ብቻ ያደገ ነው፡፡ የተጣራ ትርፉም ከቀዳሚው ዓመት አኳያ በ5.8 በመቶ ማደጉን ባንኩ ይገልጻል፡፡ ይህ የትርፍ ዕድገት ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ተደጋግሞ ሲመዘገብ የቆየ ነው፡፡

በተጣራ ትርፍ ረገድም ባንኩ የ19.6 ሚሊዮን ብር ወይም የ5.8 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ በበጀት ዓመቱ ያልተጣራ ትርፍ ሆኖ መመዝገቡ የተጠቀሰው 356.6 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ የትርፍ ግብርና መጠባበቂያ ከተቀነሰ በኋላ የተጣራ ትርፉ 226.3 ሚሊዮን ብር በመሆኑ፣ አንድ አክሲዮን የሚያስገኘው የትርፍ ክፍፍል ድርሻ 129 ብር ሆኗል፡፡ ይህም በቀዳሚው ዓመት አንድ አክሲዮን አስገኝቶት ከነበረው 137 ብር ጋር ሲነጻጸር የ2008 በጀት ዓመቱ የትርፍ ክፍፍል ድርሻ በቀዳሚው ዓመት ከተገኘው ያነሰ ሆኗል፡፡

ከባንኩ የ2008 በጀት ዓመት ዓመታዊ ሪፖርት መገንዘብ እንደሚቻለው ከሌሎች ባንኮች የተለየ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ውስጥ ያከናወነው ነው፡፡ የግል ባንኮች ብዙም የማይዳፈሩት ዘርፍ ውስጥ ባንኩ የፈቀደው ብድር ከፍተኛ መሆኑ መገኘቱ ነው፡፡ ይህም የአገሪቱ ባንኮች ብዙም ዓይናቸውን የማይጥሉበት ዘርፍ ሲሆን፣ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ላይ ጠበቅ ያለ የፋይናንስ አቅርቦት እየሠራ ስለመሆኑ ያመላከተ ነው፡፡

በዋናነት ከሚጠቀሱትና አሥር ያህል ከሆኑት የብድር መስጫ ዘርፎች ውስጥ ባንኮች ቅድሚያ ከሚሰጡባቸውና አብላጫውን ከሚይዙት የብድር ዓይነቶች ውስጥ  ለአገር ውስጥ ንግድ እንዲሁም ለወጪና ገቢ ንግድ ዘርፎች የሚያደሉ መሆናቸውን የሚታወቅ ነው፡፡ ንብ ባንክ በአንፃሩ በጠቅላላ ከሰጣቸው ብድሮች ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው ለማምረቻ ወይም ለማኑፋክቸሪንግ የሰጠው ብድር ነው፡፡ ይህ ዘርፍ ከባንኩ ጠቅላላ ብድር ውስጥ 17.7 በመቶውን ድርሻ ይዟል፡፡ በበጀት ዓመቱ የተደረሰበት የብድር ክምችት 7.6 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከሁሉም ዘርፎች የበለጠውን ብድር ያገኘው አምራች ኢንዱስትሪው ነው፡፡ ባንኩ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች 1.68 ቢሊዮን ብር አበድሯል፡፡ ይህም ከጠቅላላ ብድር ውስጥ 17.4 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡

ይህ የብድር አሰጣጥ በግል ባንኮች እምብዛም ያልተለመደ ቢሆንም ባንኮች በመጠኑም ቢሆን ለኢንዱስትሪው ዘርፍ፣ በተለይም ለአምራች ንዑስ ዘርፍ ብድር እንደሚሰጡ ግልጽ ነው፡፡ ይሁንና ግን ሰሞኑን ዓመታዊ ሪፖርታቸውን ይፋ ካደረጉ ባንኮች በበጀት ዓመቱ ከሰጡት ጠቅላላ ብድር ውስጥ አብላጫውን ያዋሉት በሌሎች የኢኮኖሚው ዘርፍ ላይ ነው፡፡ ለአብነት ሕብረት ባንክ ከፍተኛውን ወይም 20.7 በመቶ የሚሆነውን ብድር የሰጠው ለወጪ ንግድ ዘርፍ ነው፡፡ አንበሳ ባንክ በበኩሉ 23 በመቶውን ብድር የተሰጠው ለገቢ ንግድ ሲሆን፣ አዋሽ ባንክም ከጠቅላላ ብድሩ 31 በመቶውን ለአገር ውስጥ ንግድ አበድሯል፡፡ አቢሲኒያ ባንክም ብልጫ ያለውን ብድር የሰጠው ለአገር ውስጥ ንግድ ዘርፍ መሆኑ ታይቷል፡፡ አቢሲኒያ ባንክ ከጠቅላላ ብድር ውስጥ 37 በመቶ ያህሉን ለዚሁ ዘርፍ እንዳዋለ ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ ከጠቅላላ ብድሩ ውስጥ አብጫው ለአገር ውስጥ ንግድና አገልግሎት ያዋለው ሌላው ባንክ ቡና ኢንተርናሽናል ሲሆን፣ ለዚህ ዘርፍ የሰጠው ብድር የ23.8 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡

እነዚህ ባንኮች ለኢንዱስትሪው ዘርፍ በጥቅሉ የሰጡት ብድር ከሌላው ዘርፍ አኳያ ሲታይ አነስተኛ ሲሆን፣ አንበሳና አቢሲኒያ ከጠቅላላ ብድራቸው ለኢንዱስትሪ ዘርፍ ያዋሉት ስድስት በመቶ ብቻ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ አዋሽ ባንክ 10.8 በመቶ፣ ሕብረት 16.3 በመቶ ያለውን ድርሻ ይዟል፡፡ ቡና ባንክ በአንፃሩ ለኢንዱስትሪ ዘርፍ የሰጠው ብድር አራት በመቶ ያህል ብቻ በመሆኑ፣ የንብ ባንክ ብድር የተለየ መስመር መያዙን ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከዚህ ክንውን ባሻገር ንብ ባንክ በሌሎች አገልግሎቶች መስኮች ያገኘውን ውጤት በተመለከተ ካቀረበው ሪፖርት መገንዘብ እንደሚቻለው፣ የባንኩ አጠቃላይ የሀብት መጠን 15.8 ቢሊዮን ብር መድረሱን ነው፡፡ የ19.5 በመቶ ዕድገት የታየበት የባንኩ ጠቅላላ ሀብት፣ በ2007 በጀት ዓመት ወቅት 13.3 ቢሊዮን ብር እንደነበር የባንኩ መረጃ ያሳያል፡፡ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑም 12.4 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ ይህ አኃዝ 9.8 ቢሊዮን ብር እንደነበር የሚያስታውሰው የባንኩ ሪፖርት፣ በ2008 በጀት ዓመት በ27 በመቶ መጨመሩን አስፍሯል፡፡ በባንኩ ሒሳብ ያላቸው አስቀማጮች ቁጥር ከ337 ሺሕ ወደ 412,910 አድጓል፡፡ 26 አዳዲስ ቅርንጫፎች በመክፈትም የቅርንጫፍ ባንኮቹን ቁጥር አስፋፍቷል፡፡

ወጪና ገቢውን በተመለከተ በሪፖርቱ እንደተጠቀሰው፣ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በ2008 በጀት ዓመት አጠቃላይ ገቢው 1.4 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ከቀዳሚው በጀት ዓመት በ222.3 ሚሊዮን ብር ወይም በ18.4 በመቶ ጨምሮ መገኘቱ ባንኩ ጠቅሷል፡፡

የባንኩ ወጪም በ26.6 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ ንብ ባንክ በ2008 በጀት ዓመት ያወጣው ጠቅላላ ወጪ 972.3 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ በ2007 መጨረሻ አስመዝግቦት ከነበረው ጠቅላላ ወጪ አኳያ ሲታይ በ204.3 ሚሊዮን ብር በልጦ ተገኝቷል፡፡

በ2008 በጀት ዓመት ካወጣው ጠቅላላ ወጪ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የያዘው በቁጠባና በጊዜ ገደብ ለተቀመጡ ሒሳቦች የከፈለው ወለድ ሲሆን፣ ከጠቅላላ ወጪው 40.3 በመቶ ድርሻ አለው፡፡

በ2008 በጀት ዓመት ባንኩ ዕድገት ያላሳየበት እንዲሁም ከቀደመው በጀት ዓመት ያነሰ ገቢ ያገኘበት የአገልግሎት ዘርፍ፣ ዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ነው፡፡ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ያገኘው ገቢ ከቀደመው በጀት ዓመት ማለትም ከ2007 ዓ.ም. አኳያ በ8.9 በመቶ ያነሰ ሆኗል፡፡ በ2008 ዓ.ም. ከዚህ ዘርፍ 248.8 ሚሊዮን ብር ቢገኝም ከቀዳሚው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ24.1 ሚሊዮን ብር ቀንሷል፡፡

ከባንኩ ሪፖርት መረዳት እንደሚቻለው ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት የተገኘው ገቢ ሊቀንስ የቻለበት ምክንያት ‹‹በዓለም ገበያ ላይ የግብርና ምርቶች ዋጋ መቀነስ እንዲሁም፣ ባንኮች ሲቀራመቱ የነበረው ይህንኑ አነስተኛ ገቢ ስለነበርና በዚሁ የተነሳ የተገኘው ድርሻም አነስተኛ በመሆኑ ነው፤›› በማለት የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት አስፍሯል፡፡ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል በአሁኑ ወቅት 1.5 ቢሊዮን ደርሷል፡፡   

Standard (Image)

የንግድ ምክር ቤቶች ትክክለኛ አባላት ቁጥር ሊጣራ ነው

$
0
0

- የአማራ ንግድ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የጻፈው ደብዳቤ እያነጋገረ ነው

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ስምንተኛውን ጠቅላላ ጉባዔ ለማካሄድ ቦርዱ አጋጥሞኛል ያላቸውን ችግሮች መርምሮ መፍትሔ ለማፈላለግ የተዋቀረውና ወደ ሥራ የገባው ግብረ ኃይል (ኮሚቴ)፣ 18ቱ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች አሉኝ ብለው ያስመዘገቧቸው አባላትን ትክክለኛነት ወደማረጋገጥ ሊገባ ነው፡፡ በንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት ትክክለኛ ነጋዴ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ ካላቀረቡም አባልነታቸውን ወደ መሰረዝ እንደሚገባም አስታውቋል፡፡

ኮሚቴው ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በአንዳንድ ንግድ ምክር ቤቶች የቀረቡት የአባላት ቁጥር የተጋነነ ስለመሆኑ የቀረበለትን መረጃ መሠረት በማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም ትክክለኛ አባላትን መለየት ቀዳሚ ጉዳይ በመሆኑና አጋጠመ የተባለውን ችግር ለመፍታት የአባላት ጉዳይ ማጣራት አንዱ መፍትሔ ይሆናል ተብሎ በመታመኑ ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት ለሁለት ቀን በተደረገ ውይይት ኮሚቴው የደረሰበትን ድምዳሜ የያዘና 18ቱ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች በአስቸኳይ የአባሎቻቸውን ሙሉ መረጃ እንዲያቀርቡ ማሳሰቢያ የተሰጠበት ደብዳቤም ለሁሉም አባል ምክር ቤቶች ተልኳል፡፡

ግብረ ኃይሉ ኅዳር 9 እና 10 ቀን 2009 ዓ.ም. በጉዳዩ ላይ መረጃዎችን መሠረት ያደረገ ጥልቅ ውይይት ካደረገ በኋላ፣ አባል ምክር ቤቶች ምንም ሳይጓደሉ በአዋጁ ላይ በተቀመጡበት ልክ መፈጸም አለባቸው ባላቸው የንግድ ፈቃድ፣ የዘርፍና አገልግሎት መደበላለቅ እንዲሁም በምዝገባ ሰርተፍኬት ዙሪያ ውሳኔዎች ማሳለፉን ይገልጻል፡፡ አያይዞም እነዚህ መረጃዎች ቀደም ሲል በተደጋጋሚ የተጠየቁ ጉዳዮች ቢሆኑም ልዩ ግብረ ኃይሉ ባልተሟሉት ላይ ስረዛ የማድረግ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ የንግድ ምክር ቤቶቹ ትክክለኛ መረጃ እንዲያቀርቡ አሳስቧል፡፡

በ18ቱም ንግድ ምክር ቤቶች በኩል የቀረቡ አባላት የንግድ ፈቃድን አስመልክቶ በንግድና ዘርፍ ማቋቋሚያ አዋጅ 314/95 ክፍል አራት አንቀጽ ሃያ ቁጥር ሁለት መሠረት ቋሚ የንግድ ቦታቸው ምክር ቤቱ ባለበት ከተማ የሆነና ሕጋዊ የንግድ ፈቃድ ያላቸው መሆን እንደሚገባው በተደነገገው መሠረት መረጃዎቹ መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ቀደም ብሎ ንግድ ምክር ቤቶቹ ያቀረቡትን ሰነድ በመመርመር ማስተካከያ መደረግ አለበት ከተባለም በአዋጁ በተቀመጠው መሠረተ አስተካክለው ያቅርቡ ሲል ደብዳቤው ያሳስባል፡፡

በዘርፍ ተመዝግበው መቅረብ ያለባቸው አባላትን በተመለከተም በንግድና ዘርፍ ማቋቋሚያ አዋጁ 314/95 እና ይህንኑ አዋጅ ለማስፈጸም በቀድሞው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚያዚያ 1996 ዓ.ም. በወጣው መመርያ መሠረት በማምረት ላይ የተሰማሩ ብቻ መሆን እንደሚገባቸው አስገንዝቧል፡፡

በንግድና ዘርፍ ማቋቋሚያ አዋጅ 314/95 ክፍል ስድስት አንቀጽ ሃያ ዘጠኝ ቁጥር አራት በክልል፣ በወረዳና በከተማ ደረጃ የተቋቋሙ ምክር ቤቶች ያገኙትን የምዝገባ ሰርተፍኬት ትክክለኛ ኮፒ በኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት መቀመጥ እንደሚገባው ስለሚያዝ፣ ይህንንም ተፈጻሚ እንዲያደርጉ አዟል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የምዝገባ ሰርተፍኬትን በተመለከተ ንግድ ምክር ቤቶቹ ቀደም ሲል ባቀረቡት ሰነድ ውስጥ የአባላት ዝርዝር ቀርቦባቸው ሰርተፍኬት ያልቀረበላቸውን ምክር ቤቶች፤ እንዲሁም ሰርተፍኬታቸው ቀርቦ አባላቶች ያልቀረበላቸው ምክር ቤቶች ሁሉንም መረጃ ያቅርቡ ብሏል፡፡ እንዲህ ያሉ መረጃዎችን በመመርመር የተመሳከረ መሆኑን ለማረጋገጥም እንዲችል አባል ምክር ቤቶቹ በአዋጅና በመመርያ በግልጽ የተደነገጉ ጉዳዮች ዙሪያ ያላቸውን ማስተካከያም እስከ ኅዳር 22 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲያሳውቁ አሳስቧል፡፡ ይህ የግብረ ኃይሉ ውሳኔ በተለይ በርካታ አባላት አለን ያሉ ንግድ ምክር ቤቶች ያሉዋቸውን አባላት ትክክለኛነት ለማረጋገጥና አዋጁን በትክክል ለማስተግበር ያስችላል ተብሎ ታምኗል፡፡ በሌሎች ምርመራ ይደረግባቸዋል ተብለው ከተያዙ ጉዳዮች ውስጥ በተለይ ከሥር ንግድ ምክር ቤቶች ምርጫ ሳያካሂዱ የክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምርጫ አከናውነዋል በተባሉት ላይም ምርመራውን ወደ ማድረግ እንደሚገባ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ባለፈው ዓመት ያወጣውን መተዳደሪያ ደንብ ጋር ተያይዞ ጥሰት ታይቶባቸዋል የተባሉ ጉዳዮችን ይመረምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡  

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ንግድና ኢንዱስትሪ ገበያ ልማት ቢሮ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት መተዳደሪያ ደንብን በተመለከተ አነጋጋሪ የሆነ ደብዳቤ ጽፏል ተባለ፡፡ በቢሮው ኃላፊ ተፈርሞ ወጣ የተባለው ይህ ደብዳቤ የተጻፈው ለንግድ ሚኒስቴር ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ባለፈው ዓመት ተግባራዊ ያደረገው መመርያ ንግድ ምክር ቤቶችን የሚጐዳ ነው የሚል መልዕክት ያዘለ ነው፡፡ ከአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የቀረበለትን አቤቱታ መሠረት በማድረግ የተጻፈው ይህ ደብዳቤ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ያፀደቀው መተዳደሪያ ደንብና መመርያ ላይ ጉባዔው በቅጡ ያልመከረበትና የጠቅላላ ጉባዔውን መብት በጥቂት የዳይሬክተሮች ቦርድ ፍላጎት ሥር እንዲወድቅ ያደረገ፣ አባል ምክር ቤቶች ተጨማሪ አባላት እንዳያፈሩ የሚያደርግ መሆኑን ይገልጻል፡፡ በተለይም አዲስ ለሚመዘገቡ አባላት የመመዝገቢያ ለእያንዳንዱ ሰው ሦስት ብር ለነባር አባላት በእያንዳንዱ ሰው አምስት ብር እና ከተሰጡ ልዩ ልዩ አገልግሎቶች ገቢ 10 በመቶ ለአገራዊ ምክር ቤቱ ፈሰስ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ መሆኑን በመጥቀስ፣ ክልላዊ ምክር ቤቱ ይህ ደንብ የሚተገበር ከሆነ እንደ ክልል ችግር የሚያጋጥመው መሆኑን አሳውቆናል በማለት ከዚህ አንፃር ሊታይ የሚገባው ጉዳይ መኖሩን ይጠቁማል፡፡ በደብዳቤው መቋጫ ላይም ‹‹የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮም ይህ ወጣ የተባለው ደንብ በክልላችን ያለውን የግሉን ዘርፍ የማልማት ሥራ የሚያቀጭጭና ክልላዊ ምክር ቤቱም ራሱን አደራጅቶ ለአባላቱ የተሻለ ድጋፍ እንዳይሰጥ ችግር የሚፈጥር በመሆኑ፣ ቢሮው አጥብቆ የሚቃወመው መሆኑን ይገልጻል፡፡ ወደፊትም አገራዊ ምክር ቤቱ አባል ምክር ቤቶቹን የሚያጠናክር ሁኔታ እንዲሠራ የሚጠይቀው ደብዳቤ፣ ንግድ ሚኒስቴርም ይህን ጉዳይ እንዲከታተል በአክብሮት ይጠይቃል፡፡

በክልሉ ቢሮ የተጻፈው ይህ ደብዳቤ ግን በተለይ የኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን አስቆጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አፈወርቅ ለሪፖርተር እንደገለጹትም፣ በመተዳደርያ ደንቡ በሁሉም አባል ንግድ ምክር ቤቶች ባሉበት ፀድቆ የተተገበረ ሆኖ እያለ ቢሮው መተዳደርያ ደንቡን አጥብቄ እቃወማለሁ ማለቱ አስገራሚ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት መተዳደርያ ደንብ እንዲህ ባለው ደብዳቤ ሊቀየር የማይችል መሆኑንና መተዳደርያ ደንቡ አያሠራም ከተባለ አባል ምክር ቤቶች ሊያሻሽሉት ይችላሉ ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ መመርያው አያሠራም መባሉ ከእውነት የራቀና ሌሎች አባል ምክር ቤቶች ተቀብለው የሚተገብሩት እንደሆነ እየታወቀ ቢሮው ይህንን ደብዳቤ መጻፉ እንዳሳዘናቸው ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

በተለይ በቢሮው ደብዳቤ በግልጽ የተቀመጠው አንድ አባል ምክር ቤት በአንድ አባሉ ሦስትና አምስት ብር በዓመት ለኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ፈሰስ ያድርግ መባሉን እንደ ከፍተኛ መዋጮ ተደርጎ የመወሰዱ ጉዳይ ግልጽ ሊሆንላቸው አለመቻሉን አቶ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡ በአንድ ነጋዴ አምስት ብር ከከፈለ አባል ንግድ ምክር ቤቱ እንዴት ሊጎዳ ይችላል፡፡ በአንድ አባል አምስት ብር ማዋጣት የሚችል አቅም የለም ከተባለ ያሳዝናል ብለዋል፡፡

አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎችም የክልሉ ቢሮ በመተዳደርያ ደንቡ የተጠቀሰው ክፍያ በተመለከተ የቀረበለት መረጃ ሊመረምረው ይገባ እንደነበርና አሁንም ጉዳዩን ቢመለከተው ይሻል ነበር ይላሉ፡፡

ቢሮው የክልሉን ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ባቀረበው ሐሳብ መሠረት የጻፈው ቢሆንም፣ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውን እንደ ኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራትን በማማከር ተጨማሪ መረጃ መቀበል ነበረበትም የሚል አስተያየት ተሰጥቷል፡፡

እነዚህ ክፍያዎችን በተመለከተ ግን በቅርቡ 18ቱ ንግድ ምክር ቤቶች በተሰበሰቡበት መድረክ ላይ የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው አየነው በአዲስ አባል አምስት በነባር አባል ቁጥር ሦስት ብር በዓመት ለብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ ይከፈል የሚለውን አንቀጽ በመቃወም አስተያየት ሰጥተው ነበር፡፡

ይህ ክፍያ ይበዛል በማለትም ተከራክረዋል፡፡ ነገር ግን በዚሁ መድረክ ላይ አስፈላጊ ከሆነ ግን በአዲስና በነባር አባል ምክር ቤታቸው ሊከፍል ይገባል የተባለው ቀሪ ክፍያ 16 ሺሕ ብር አካባቢ በመሆኑ፣ ይህንን ክፍያ አሁኑኑ ቼክ ልፈርም እችላለሁ እስከ ማለት ደርሰው ነበር፡፡

ይህ የክፍያ ጉዳይ እንደ አጀንዳ ለምን እንደተነሳ ግራ የገባቸው ወገኖች ግን በአሁኑ ወቅት የአማራ ክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በቅርቡ ያካሄደው ምርጫ አዋጅን የተከተለ ያለመሆኑ ተጠቅሶ፣ ጉዳዩ እንዲጣራ ውሳኔ ከተላለፈላቸው መካከል አንዱ በመሆኑ ይህንን ጉዳይ አቅጣጫ ለማስቀየር ተጠቅሞበት ይሆናል ይላሉ፡፡

የክልሉ ቢሮም የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምርጫ ሒደትን ይፈትሽ ብለዋል፡፡ የአማራ ንግድ ምክር ቤት ይህንን አቋሙን በግልጽ ከማንፀባረቁ ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት መተዳደሪያና መመርያ ላይ ተቃውሞዬን አቅርቤያለሁ ይላል፡፡

    

 

Standard (Image)

የስድስቱ ባንኮች ጥምረትና የቦርድ ሊቀመንበሩ ስንብት

$
0
0

- በፕሪሚየም ስዊች ሶሉዊሽን 5.4 ቢሊዮን ብር ተንቀሳቅሷል

ፕሪሚየም ስዊች ሶልውሽን አክሲዮን (ፒኤስኤስ) በመባል የሚታወቀውን ስድስት ባንኮች በጥምረት የፈጠሩትን ኩባንያ ላለፉት ስድስት ዓመታት የቦርድ ሊቀመንበር በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት የቀድሞ የኅብረት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ጌታነህ ኃላፊነታቸውን በፈቃደኝነት ለቀቁ፡፡ ኩባንያው ሥራ ከጀመረ ወዲህ ባሉት አራት ዓመታት በአጠቃላይ ከ5.3 ሚሊዮን በላይ የገንዘብ ዝውውር በፕሪሚየም ስዊች በኩል መካሄዳቸው ተገልጿል፡፡

ለኩባንያው መፈጠር ሐሳብ አመንጪና አደራጅ በመሆን የአስተባባሪነት ሥራውን በመውሰድ ጭምር የሚታወቁት አቶ ብርሃኑ፣ ከፕሪሚየር ስዊች የቦርድ ሊቀመንበርነታቸው መልቀቃቸውን ያሳወቁት ባለፈው ሐሙስ የኩባንያው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ነው፡፡ በዕለቱ ኩባንያውን በቦርድ አባልነት በሊቀመንበርነት ለማገልገል ምርጫ ከመደረጉ ቀደም ብሎ ድጋሚ ላለመመረጥ በማሳወቅ አዲስ አመራር እንዲተካቸው በመግለጽ ከመድረክ የወረዱት አቶ ብርሃኑ፣ ድጋሚ እንዲወዳደሩ የቀረበላቸውን ጥያቄ አልተቀበሉትም፡፡ ከዚህ ውሳኔ የደረሱት በአሁኑ ወቅት ኩባንያው በሁለት እግሩ የቆመና በተተኪዎች እንዲመራ በመሻታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ጌታቸው ናና በተገኙበት የምሽት ፕሮግራም ላይም አቶ ብርሃኑ ባደረጉት ንግግር ኩባንያው በአዲስ አሠራር እንዲቀጥል በመፈለጋቸው ጭምር በድጋሚ ላለመመረጥ ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡

ኩባንያው ሥራ ሲጀምር በኅብረት፣ አዋሽና ንብ ባንኮች ጥምረት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ብርሃኑ፣ በአሁኑ ወቅት ግን ብርሃን፣ አዲስ ኢንተርናሽናልና የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንኮች ኩባንያውን በመቀላቀላቸው የተጣማሪ ባንኮቹ ስድስት ደርሰዋል፡፡ እስካሁንም ከ5.3 ቢሊዮን በላይ የገንዘብ ልውውጥ በፕሪሚየም ስዊች ሶልዊሽን አክሲዮን ማኅበር በኩል የተፈጸመ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ብርሃኑ፣ ይህም አሁን ኩባንያው የደረሰበትን ደረጃ የሚያመለክትና መሠረት የያዘ በመሆኑ ቀጣይ ተግባሮቹን አዳዲሶቹ አመራሮች ይወጡታል የሚል እምነታቸውንም ገልጸዋል፡፡

ፒኤስኤስ በስድስት ባንኮች መካከል የሚከናወኑ የገንዘብ ልውውጦችን በማሳለጥ ለእነዚህ አባል ባንኮች ደንበኞች የአገልግሎት እርካታንና ምቶችን የፈጠረ በመሆኑም፣ በቅርቡ ሥራ በጀመረው አገር አቀፋዊ ስዊች (Et-Switch) በሚደረገው እንቅስቃሴ ወሳኝ ሚና በመጫወት በቁጥር በርከት ያሉ የገንዘብ ልውውጦችን በማስተላለፍ ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡

የፒኤስኤስ አባል ባንኮች የአገልግሎት ጥራትና ቅልጥፍና ላይ የተመሠረተ የገበያ ውድድር ለዘለቄታ ስኬት መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ቀድሞ በማገናዘብ የተጀመረ ሥራ ነበርም ተብሏል፡፡ የግል ባንኮቹ በየግላቸው በመጓዝ የፋይናንስና ሌሎች ሀብቶችን ከማባከን ይልቅ ትብብርን በማስቀደም ዘመናዊ የክፍያ ቴክኖሎጂውን ዘርፍ በመገንባት ረገድ አስተዋጽኦ አድርጓል የሚል እምነትታቸውንም አንፀባርቀዋል፡፡

አባል ባንኮቹ በፒኤስኤስ ሲስተም ተጠቅመው ከሚሰጧቸው ዋና ዋና አገልግሎቶች መካከልም በካርድ አማካይነት ለደንበኞች ተደራሽ በሆኑ ቦታዎች በተቀመጡ ኤቲኤም ማሽኖች መገልገል አንዱ ነው፡፡ ነጋዴዎች ክፍያቸውን በፖይንት ኦፍ ሴል እንዲቀበሉ ማድረግ፣ ሲሲተሙ ሃያ አራት ሰዓት ያለማቋረጥ እንዲሠራና የገንዘብ ልውውጦች መልዕክቶችን እንዲያስተላልፍ የማሽኖቹን የመከታተል ኃላፊነት ወስዶ የሚሠራም ነው፡፡ በዚህም አገልግሎቱ የዘመናዊ ክፍያ ሥርዓቱን ሒደት የተቀላጠፈ እንዲሆን የድጋፍ አገልግሎት በመስጠት ባንኮች በመተባበር ተወዳዳሪ መሆን የሚቻልበትን መንገድ የጠረገ ስለመሆኑም ተናግሯል፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ በተጠናቀቀው 2008 የበጀት ዓመትም ከ370 በላይ ከሲስተሙ ጋር በተገናኙ ኤቲኤሞችና ከ620 በላይ ፖይንት ኦፍ ሴል ተርሚናሎች 2.9 ሚሊዮን የኤቲኤሞችና ከዘጠኝ ሺሕ በላይ ፒኦኤስ የገንዘብ ልውውጦች መልዕክቶችን ለአባል ባንኮቹ ያስተላለፈና ያቀነባበረ ስለመሆኑ በዕለቱ የቀረበ ሪፖርት ያስረዳል፡፡ ይህም ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ያስተላለፈውን የገንዘብ ልውውጦች መልዕክቶች ጠቅላላ ብዛት ከ5.3 ሚሊዮን በላይ እንዲሆን እንዳደረገውና ከእነዚህም ውስጥ 37 በመቶ የአንዱ ባንክ ደንበኛ በሌሎች ባንኮች ክፍያ ማሽኖች ላይ ያካሄዷቸው ግብይቶች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ፒኤስኤስ ከዓለም አቀፍ ማኅበራት ጋር በተደረገ ስምምነት አባል ባንኮች የቪዛ፣ የማስተር ካርድና የዩኒየን ፔይ ካርዶችን በኤቲኤሞቻቸው ላይ እንዲቀበሉ ማስቻሉ የኩባንያው ተግባራት የሚገለጽበት ሌላው ማሳያ መሆኑን የኩባንያው ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡ በ2008 የበጀት ዓመት እነዚህ ካርዶች በፖይንት ኦፍ ሴል ተርሚናል ላይ ተቀባይነት እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡ ይህም ባንኮች እነዚህን ካርዶች በመቀበል ሊያገኙ የሚችሉትን የውጭ ምንዛሪ ከፍ እንዲል አስተዋጽኦ እየበረከተላቸው እንደሆነ በዕለቱ ከቀረበው መረጃ ለመረዳት ተችሏል፡፡

እንደኩባንያው መረጃ ፒኤስኤስ በ2008 የበጀት ዓመት ብቻ 173,216 ካርዶችን ለባንኮቹ በማተም አሰራጭቷል፡፡ ይህም በገበያ ላይ የሚገኙትን የፒኤስኤስ መለያ ያላቸውን ካርዶች ብዛት ወደ 400,000 ማድረስ መቻሉን የኩባንያው ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ ከዚህም ባሻገር ፒኤስኤስ የተዘረጋውን ሲስተም በመጠቀም የተወሰኑት ባንኮች ከወለድ ነፃ የሆነ ካርድና ቅድሚያ ክፍያ ካርድ (Pre-paid Card) ለደንበኞቻቸው መስጠት እንዲጀምሩ በማድረግ የካርድ አገልግሎት እንዲስፋፋ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ኩባንያው እንዲህ ያለውን ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶች ሲሰጥ ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን የተለያዩ ዕርምጃዎች ስለመውሰዱ ተብራርቷል፡፡ በዚህም መሠረት ዓለም አቀፍ የክፍያ ሥርዓቱ ያስቀመጠውን ስታንዳርድ በማሟላት ሲሆን፣ የባንኮች ደንበኞችን መረጃ በጥንቃቄ ከመያዝ አንፃር የተቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ በ2007 ዓ.ም. የPCIDSS (Payment Card Industry Data Security Standard) ሰርተፊኬት ወስዷል፡፡ በ2008 በጀት ዓመትም የዕድሳት ፍተሻ አሟልቶ በመገኘቱ ሰርተፊኬቱን ማግኘቱ፣ ደኅንነቱ የጠበቀ አገልግሎት መስጠቱን ያመለክታል፡፡ የደንበኞች መረጃ ሲያስተላልፍ፣ ሲያቀነባብርና ሲያከማች በማንኛውም መልኩ ላልተፈቀደለት ሦስተኛ ወገን እጅ እንደማይወድቅ ማረጋገጫ ነውም ተብሏል፡፡ የ2008 በጀት ዓመት የፋይናንስ እንቅስቃሴውን በተመለከተ የተገኘው መረጃ የኩባንያው ገቢ ወደ 34 ሚሊዮን ብር መድረሱን ያመለክታል፡፡ ይህም ከቀደሚው ዓመት በ23 በመቶ ማደጉን ያሳያል፡፡ ባለፉት አራት ዓመታትም በኩባንያው በኩል የተንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን 5.4 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአራት ዓመት ውስጥ ከተንቀሳቀሰው 5.4 ቢሊዮን ብር ውስጥ በ2008 በጀት ዓመት የተንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን ከፍተኛ መጠን ያለው ሆኗል፡፡ በ2008 በጀት ዓመት ብቻ የተንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን 3.1 ቢሊዮን ብር ነው፡፡

በገንዘብ ዝውውር መጠንም ቢሆን በ2008 በጀት 2.9 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን፣ ይህም በቀደሙት ሦስት ዓመታት በድምር ከተካሄደው የገንዘብ ልውውጥ በ2008 ዓ.ም. የተደረገው ብልጫ ያለው መሆኑን ያሳያል፡፡

ኩባንያው ወደ ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ትርፍ ማግኘቱን የሚጠቁመው መረጃ በ2008 በጀት ዓመት ለታየው ከፍተኛ እንቅስቃሴ ዋነኛው ምክንያት ተጨማሪ ኤቲኤሞች መተከላቸው፣ ደንበኞች በካርድ ባንኪንግ የመጠቀም ልምዳቸው ማዳበራቸውና ተጨማሪ ካርዶች መሠራጨታቸው ዋና ዋናዎቹ ናቸው ተብሏል፡፡

ኩባንያውን በቦርድ አባልና በሊቀመንበርነት ለመምራት በዕለቱ ምርጫ የተደረገ ሲሆን፣ በምርጫው ውጤት መሠረት አራት ባንኮችና የሦስት ባንኮች ፕሬዚዳንቶች ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት የቦርድ አባል ሆነው ተመርጠዋል፡፡ አቶ ብርሃኑን በመተካት የሚሠሩት የቦርዱ ሊቀመንበር የሚመረጡት ግን ሰባቱ የቦርድ አባላት በሚያደርጉት ስብሰባ ይሆናል፡፡

ከሰባቱ የቦርድ አባላት ውስጥ ሦስቱ በግለሰብ ደረጃ በመመረጥ የቦርድ አባል ሲሆኑ፣ የኩባንያው ቦርድ ሊቀመንበርም የሚመረጠው ከሦስቱ ግለሰብ ተመራጮች መካከል አንዱ ነው፡፡

በዚህ ስሌት ቀጣዩ የኩባንያው ፕሬዚዳንት ሊሆኑ የሚችሉት የአዋሽ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው፣ የንብ ባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ክብሩ ፎንጃ ወይም የኅብረት ባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ታዬ ዲበኩሉ ናቸው፡፡

የቦርድ ሊቀመንበርነታቸውን ለአዲሱ ተመራጭ የሚያስረክቡት አቶ ብርሃኑ ጌታነህ ከፕሪሚየም ስዊች የቦርድ ሊቀመንበራቸው ከፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ከማሳወቃቸው በፊት፣ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱ ተቋማት ይዘውት የነበረውን የኃላፊነት ቦታ በተመሳሳይ መንገድ መልቀቃቸው ይታወሳል፡፡ አቶ ብርሃኑ የኅብረት ባንክ ፕሬዝዳንትነታቸውን የለቀቁት በፈቃዳቸው ነው፡፡ ከዚያም ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበርን ለሁለት የምርጫ ዘመን በፕሬዚዳንትነት ካገለገሉ በኋላ ይህንንም ኃላፊነት በፈቃዳቸው ለቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ሁሉም ባንኮች በአባልነት ያቀፈውን ኢትስዊች የተባለውን ኩባንያም በመሥራችነትና የመጀመሪያው ቦርድ ሊቀመንበር በመሆን ያገለገሉት አቶ ብርሃኑ፣ ከዚህም ኩባንያ በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸው ይታወሳል፡፡

ይህም አቶ ብርሃኑ ከፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ የነበራቸውን ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች በሙሉ መልቀቃቸውን አሳይቷል፡፡

‹‹ይህ ለምን?›› የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ብርሃኑ፣ ‹‹እንዲህ ያሉ የኃላፊነት ቦታዎች ለተተኪዎች ወይም ለወጣቶች መለቀቅ ስላለባቸው ነው፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ፕሪሚየም ስዊች ከስድስት ዓመት በፊት በ30 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመ ሲሆን፣ አሁን ካፒታሉን ወደ 160 ሚሊዮን ብር አሳድጓል፡፡ 

Standard (Image)

በጨርቃጨርቅ መስክ የፈነጠቀው አይካ አዲስ

$
0
0

ከቀኑ ሰባት ሰዓት ነው፡፡ በሃምሳዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ቱርካዊው ዩሱፍ አይደኒዝ፣ ዓለም ገና ከተማ ወደ ሚገኘው የአይካ አዲስ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ቢሯቸው ገና መግባታቸው ነበር፡፡ ፋብሪካው ከአዲስ አበባ በ20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዓለም ገና ከተማ ላይ የተንጣለለ ሲሆን፣ ዩሱፍ አይደኒዝም በፋብሪካው ሕንጻ አምስተኛ ፎቅ ላይ ከሚገኘው ቢሯቸው ቁልቁል በሚታየው መንገድ ላይ የሚሆነውን ይቃኛሉ፡፡

ምንም እንኳ ቀኑን ከሌሎቹ የአዘቦት ቀናት የሚለየው ነገር ባይኖርም አንድ እንግዳ ክስተት ግን ሳይታሰብ ከፋብሪካቸው መግቢያ አካባቢ መታየት ጀምሯል፡፡ ሰዎች እየተበራከቱ፣ እንቅስቃሴያቸውም እየበዛ መጥቷል፡፡ ‹‹ወደ አዲስ አበባ የሚያቀናው መንገድ ላይ ሰዎች በብዛት ሆነው ሲመጡ አየሁ፤›› በማለት በቅርቡ የተከሰተውን በትውስታ ይጥቅሳሉ፡፡

እርግጥም ያ ጊዜ በኢትዮጵያ፣ በተለይም በአዲስ አበባ ዙሪያ ፋብሪካዎቻቸውን ለተከሉ ለብዙዎቹ የውጭ ኩባንያዎች በመጥፎ የሚነሳ አስቸጋሪ ቀናትን አስከትሎባቸዋል፡፡ በተለይም በኢሬቻ ግርግር ወቅት የተከሰተውን እልቂት ተንተርሶ በአገሪቱ የታየው ቁጣና ብጥብጥ ለእንደነ አይደኒዝ ያሉ የውጭ ባለሀብቶች የሚታሰብ አልነበረም፡፡ ‹‹ምን እየተካሄደ ነው ብዬ ስጠይቅ፣ ሰዎች ተቃውሞ እያሰሙ ነው ብለው ነገሩኝ፤›› በማለት ትዕይንቱን ለማስታወስ ይሞክራሉ፡፡ ተቃውሞው እየቀለጠ ጎማ ማቃጠልና መንገድ መዝጋት ደረጃ ሲደርስ፣ ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ እየሆኑ መምጣታቸውን ሲመለከቱም ሚስተር አይደኒዝ ከግርግሩ ሠራተኞቻቸውን እንዴት ያለ ችግር ማስመለጥ እንደሚችሉ ማውጠንጠን ጀምረዋል፡፡ ልብ ያላሉት ነገር ግን ከበታቻቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች የዕለት ሥራቸውን በሚወጡበት ወቅት፣ እሳቸውን ጨምሮ 250 ሚሊዮን ዶላር ያወጡበት ፋብሪካ የሚታደጋቸው የጸጥታ ኃይል ሳይመጣላቸው እንዲሁ አውላላ ሜዳ ላይ መቅረታቸውን ነበር፡፡

‹‹አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከሁሉም አቅጣጫ ጭስ ሲትጎለጎል ማየት ጀመርን፡፡ በአካባቢው ወደሚገኙ የውጭ ኩባንያዎች ስደውልም አብዛኞቹ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተረዳሁ፤›› በማለት ሁኔታውን ይገልጹታል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥም የፋብሪካው ማሽኖች ሥራ እንደሚያቆሙ በማዘዝ፣ ሠራተኞችም ጥንቃቄ በተሞላበት አኳኋን ቀስ በቀስ የፋብሪካውን ቅጥር ግቢ ለቀው እንዲወጡ አድርገዋል፡፡ ሁሉም የፋብሪካው ቴክኒሻኖች በዝግታ ከፋብሪካው ከወጡ በኋላና በአካባቢው ስለደረሰው ጉዳት ሪፖርት ከተደረገ በኋላ ነበር መንግሥት ተጨማሪ የጸጥታ አስከባሪዎችን መላክ የቻለው፡፡

እንደ ዕድል ሆኖም አይካ አዲስ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስበት ከትኩሳቱ መትረፉ እንዳስደሰታቸው ሚስተር አይደኒዝ ይናገራሉ፡፡ ይሁንና ሰባት ሺሕ ያህል ድርጅቱ ሠራተኞች ግን ችግር ይፈጥሩብኛል ብለው እንዳልገመቱም ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይህ ቤተሰቤ ነው፡፡ የምተማመነው በሠራተኞቼ ነበር፤›› ሲሉም በአጽንኦት ይናገራሉ፡፡

ለጥቂት ጊዜያት ከሚስተር አይደኒዝ ጋር ቆይታ ያደረገ ሰው ለቢዝነስ በተለይም ለጨርቃጨርቅ ዘርፍ የተለየ አመለካከት ያላቸው ሰው መሆናቸውን ሊገነዘብ ይችላል፡፡ ከ7500 ያላነሱ የአይካ አዲስ ሠራተኞች አብዛኞቹ በፋብሪካው ምክንያት ወደ ሥራ ዓለም የገቡ ናቸው፡፡ ለሥራ የሚመለምሏቸውም ገና ከትምህርት ቤት የወጡትን፣ በብዛትም አሥረኛ ክፍል ያጠናቀቁትን ሲሆን፣ ወዲያውኑ ወደ ሥልጠና ያስገቧቸውና ሲያጠናቅቁ በየሥራ መደቦች ውስጥ ያሰማሯቸዋል፡፡ በአይካ አዲስም ሆነ ምርቱን በሚገዙ የአውሮፓ ኩባንያዎች አማካይነት ለሠራተኞች የሚሰጠው የሥራ ላይ ሥልጠና፣ በጥራት የመሥራትም ሆነ የማምረት ብቃታቸውን በማሻሻል፣ ከሰባት ዓመታት በፈት ፋብሪካው ሥራ ሲጀምር ይተማመንባቸው የነበሩትን 160 የውጭ ሙያተኞች ቁጥር ወደ 52 እንዲቀንስ አብቅተውታል፡፡

ቱርክኛ ከሚጫነው ንግግራቸው ውስጥ በአብዛኛው የአማርኛ ቃላትና ዓረፍተነገሮች ይደመጣሉ፡፡ አማርኛ ለማውራት ብዙም አይቸገሩም፡፡ አመለካከታቸውን ሥራዬ ብሎ ለተከታተለ ባለፋብሪካው ሰውዬ የውጭ ሰውነት ወይም ባይተዋርነት የማይሰማቸው እየሆኑ መምጣታቸውን ሊገነዘብ ይችላል፡፡ ከአንደበታቸው ‹‹አገራችን››፣ ‹‹መንግሥታችን››፣ ‹‹ሕዝባችን›› የሚሉ ቃላትን ለማድመጥ ብዙ ልፋትን አይጠይቅም፡፡ 20 ሔክታር መሬት ላይ በተንጣለለው ፋብሪካቸው ውስጥ ሲዘዋወሩ ለሠራተኞቻቸው ሰላምታ የሚሰጡትም በአማርኛ ነበር፡፡

በቱርክ ኢስታንቡል ከተማ እ.ኤ.አ. በ1988 የተመሠረተው ተርኪ አይካ ቴክታይል ኮርፖሬሽን፣ ለሩብ ክፍለ ዘመን የተካበተ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ልምድ አዳብሯል፡፡ አይካ ለዓመታት ያደላው ምርቶቹን ለአውሮፓ ገበያ በማርቀቡ ላይ ሲሆን፣ ነገሮች የተቀየሩት ግን ሚስተር አይደኒዝ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር በተገናኙበት ወቅት ነበር፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በኢስታንቡል እንዲገናኙ ምክንያት የሆኑት የወቅቱ በቱርክ የኢትዮጵያ አምባሳደር፣ የዛሬው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ነበሩ፡፡ ‹‹መለስን ያገኘኋቸው በኢስታንቡል አርፈውበት በነበረው ሆቴል ውስጥ ነበር፡፡ በጨርቃጨርቅ ዘርፍ ላይ ኢንቨስት ባደረግ እንደሚያስደስታቸው ነግረውኛል፡፡ ይህን ከማድረጌ በፊት ግን ኢትዮጵያን መጎብኘት እንዳለብኝም ገልጸውልኛል፤›› በማለት ወደ ኢትዮጵያ የመጡበትን አጋጣሚ አስታውሰዋል፡፡

አመጣጣቸው ከጥሩ መነሻ ቢመጡም እ.ኤ.አ. በ2007 ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ በጎበኙበት ወቅት ያደረባቸው መልካም ስሜት ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ገፋፍቷቸዋል፡፡ አይካ አዲስ በአይካ ቴክስታይል ኮርፖሬሽን ሥር የሚተዳደር ብቸኛው በውጭ አገር የሚንቀሳቀስ እህት ኩባንያ ሲሆን፣ ለሚስተር አይደኒዝም ቢሆን አይካ አዲስ የመጀመሪያው የውጭ አገር ኢንቨስትመንት ተሞክሯቸው ነው፡፡

አይካ አዲስ በ150 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተንጣለለ፣ ዘመናዊና የተራቀቀ ፋብሪካ ሆኖ ለመገንባትና ሥራ ለመጀመር አራት ዓመታት ፈጅቶበታል፡፡ ከበርካታ ሚሊዮን ዶላሮች ባሻገር መላ ትኩረታቸውን የሰጡበት ፋብሪካ ይኸው አይካ አዲስ ፋብሪካ እንደሆነ ሚስተር አይደኒዝ ይገልጻሉ፡፡

ፋብሪካው ሥራ ከጀመረ ከስድስት ዓመታት በኋም እንኳ የውጭ ጎብኝዎች በሚመጡበት ወቅት ራሳቸው መላ ፋብሪካውን ተዟዙረው ማስጎብኘቱን ሥራዬ ብለውታል፡፡ በዚህ እንደሚደሰቱም ከሁኔታቸው መረዳት ይቻላል፡፡ የፋብሪካውን ጥጋጥግ ሳይቀር ጠንቅቀው የሚያውቁ መሆናቸውም ግርምትን ያጭራል፡፡ ጥቃቅኗ ነገር ሁሉ አታመልጣቸውም፡፡ የሲቪል ሥራዎችና የፋብሪካ ተከላ በሚካሄበት የግንባታ ወቅት ሳይቀር እያንዳንዷን ጥቃቅን ነገር በመከታተል ያስፈጽሙ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ‹‹ትልቅ ፋብሪካ ስገነባ በዘርፉ ያለኝን የ40 ዓመታት ልምድ ማሳየት ነበረብኝ፤›› ይላሉ፡፡ አይካ አዲስ በአውሮፓውያን ዕይታ ሳይቀር ዘመናዊና መጠነ ሰፊ አምራች ተቋም እንደሆነ ያምናሉ፡፡

አይካ አዲስ ሁሉንም የምርት ሒደቶች በአንድ አጣምሮ የያዘና እርስ በርሱ የተሳሰረ ማምረቻ ጣቢያ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከጥጥ ፈትል ጀምሮ፣ ዲዛይን የማውጣት፣ ቅድ የማዘጋጀት፣ የስፌት ሥራ፣ የማቅለም ሒደቶችን አካቶ ያለቀ ምርት የማውጣትና የምርት አርማ የማተም፣ የምርት ማሸጊያዎችና የምርት መግለጫ ወረቀቶችን ጨምሮ ሁሉንም የምርት ሒደቶች የሚያጠቃልል ሥልተ ምርት በአንድ ፋብሪካ ውስጥ አካቶ ይገኛል፡፡ ‹‹በአንድ ተቋም ውስጥ የታቀፉ የተለያዩ ፋብሪካዎች ስብስብ ሲሆን፣ እያንዳንዱን ማምረቻም እንደየ ሥራው ጠባይ እንከታተላለን፤›› በማለት ከአንድ ሰዓት በላይ በሚጀው የፋብሪካው ጉብኝት ወቅት አብራርተዋል፡፡

ሁለት ራሳቸውን የቻሉ የፈትል ማምረቻዎች ያሉት አይካ አዲስ፣ አንደኛውን ክር ለማምረት ሲያውለው ሌላኛውን የተቀለመ የጥጥ ለመፍተል ይጠቀምበታል፡፡ በዚህ መንገድ ፋብሪካው በጠቅላላው በቀን 40 ቶን ክር እንዲያመርት ያስችሉታል፡፡ ልዩ ልዩ ማሽነሪዎችን በመጠቀም ከተፈጥሮ ጥጥ፣ ከፖሊስተር፣ ከኒሎንና ከሌሎችም ክር በማምረት ላይ ይገኛል፡፡

በስፌት ሥራው ወቅት ነገሮች መልካቸውን መያዝ ይጀመራሉ፡፡ ልዩ ልዩ መልክና ብዛት ያላቸው ክሮች ወደ ጨርቅነት መቀየር የሚጀምሩትም በስፌት ፋብሪካ ውስጥ ነው፡፡ በቀን 40 ቶን ጨርቅ ማምረት የሚችልባቸው 116 የስፌት ማሽነሪዎች ያለማቋረጥ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ከሚያመርታቸው መካከልም ፖሊስተር፣ ፎጣዎች፣ ድርብ ስፌት ጨርቆች ይጠቀሳሉ፡፡

ከዚህ ሁሉ ግን ሚስተር አይደኒዝ በኩራት የሚመለከቱት የማቅለሚያ ፋብሪካቸው ነው፡፡ በእንፋሎት የሚሠራው ማቅለሚያ ማሽን በዓለም ላይ አዲስ ቴክኖሎጂ ሲሆን፣ ለማቅለሚያ የሚውሉ ኬሚካሎችን ከማደባለቅ ጀምሮ ለቅመማ የሚውለውን ምጣኔ እስከመለካት ያለውን ሥራ በኮምፒውተር ታግዞ የሚያከናውን መሣሪያ ነው፡፡ በእንፋሎት ማሞቂዎች የሚታገዙት ማቅለሚያ ማሽኖች፣ በቀን 35 ቶን ጨርቅ፣ ዘጠኝ ቶን ክርና የጥጥ ፈትል እንዲሁም 20 ቶን ጨርቅ የመጭመቅና የማጠብ አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ ማቅለሚያ ማሽኑ ለማጠብ፣ ለመጭመቅና ለማድረቅ እንፋሎት ብቻ ይጠቀማል ያሉት ሚስተር አይደኒዝ፣ የማቅለሚያ ክፍሉ በሰዓት 20 ቶን እንፋሎትና ሙቅ ውኃ የሚያመነጭ ሲሆን እስከ 70 ቶን የድንጋይ ከሰል ለኃይል ፍጆታው እንደሚጠቀም አብራርተዋል፡፡ አሁን ባለበት ደረጃ ማለሚያው ጨርቅና ክር ለማቅለም እያገለገለ ሲሆን፣ እንደ ሚስተር አይደኒዝ ከሆነ ይህ ዓይነቱ አሠራር በብዙዎቹ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ያልተለደ ነው፡፡ ዘመናዊው ማቅለሚያ ዘመናዊ የማተሚያ ማሽነሪዎችም ተተክለውለታል፡፡ በቀን እስከ ስድስት ቶን የሚደርሱ ከ12 ያላነሱ ልዩ ልዩ ቀለማትን በአንድ ጊዜ የማተም አቅም አለው፡፡

የአልባሳት ማምረቻ ክፍሉ ትልቁን የሰው ኃይል የሚይዝ ሲሆን፣ በፈረቃ የሚሠሩበት፣ የሚቆርጡ፣ የሚሰፉ፣ የሚተኩሱ የሚያሽጉና ሌላውንም ተጓዳኝ ሥራ የሚያከናውኑ 3000 ሠራተኞች የሚራጡበት የምርት ክፍል ነው፡፡ በቀን 75 ሺሕ አልባሳት ይመረቱበታል፡፡ እስከ 80 ሜትር የሚርዝሙ ጨርቆችን የሚያመርቱ አራት የአልባሳት ማምረቻዎች ያሉት ፋብሪካው በዚህ የምርት መስመር ብቻ 45 ሠራተኞችን አሰማርቶ ያለ ማቋረጥ ምርት ያወጣል፡፡

እርስ በርሱ የተቀናጀና ሙሉ ለሙሉ ራሱን የቻለ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ መትከል በጣም ውድ ቢሆንም አይካ አዲስ ግን ምርጥ የሚባለውን ሥርዓት በመከተል ተወዳዳሪና ኤክስፖርት ተኮር ፋብሪካ ለመሆን እንደበቃ ሚስተር አይደኒዝ ይገልጻሉ፡፡ ኩባንያው የሚቀርቡለትን የሥራ ትዕዛዞች በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ለማቅረብ የሚችልበትን ቀርጠኛ አሠራር የሚከተል በመሆኑም ቺቦን ከመሳሰሉ የጀርመን የአልባሳት ኩባንያ ጋር በመሥራት ምርቶቹን ለማቅረብ አስችሎታል፡፡

ግብዓቶችንና ጥሬ ዕቃዎችን ከውጭ የማስመጣቱ ሒደት በኢትዮጵያ በተለየ መንገድ ጊዜ እንደሚፈጅ የሚጠቅሱት ባለሀብቱ፣ ‹‹ከውጭ ዕቃ አስመጥተን ፋብሪካ ደጃፍ እስኪደርስ ድረስ ሦስት ወር ሊፈጅ ይችላል፡፡ ይህን ያህል ጊዜ መጠበቅ ግን አልችልም፤›› ይላሉ፡፡ በመሆኑም የ30 ሚሊዮን ዶላር ግምት ያላቸው እንደ ኬሚካል፣ ክር፣ አልባሳትና ማቅለሚያ ያሉ ግብዓቶችን በክምችት ለመያዝ መገደዱን አስታውቀዋል፡፡

ከአራት ዓመት በፊት ጀምሮ የአገሪቱን 60 ከመቶ የጨርቃጨርቅ ኤክስፖርት ድርሻ የተቆጣጠረው አይካ አዲስ፣ የ63 ሚሊዮን ዶላር ግምት ያላቸው ልዩ ልዩ ምርቶችን በመላክ አገሪቱ ካስመዘገበችው የ111.45 ሚሊዮን ዶላር ኤክስፖርት አፈጻጸም ውስጥ ከግማሽ እጅ በላይ ድርሻውን በመያዝ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ እርግጥ አይካ የ100 ሚሊዮን ዶላር ምርት የማምረት አቅም ያለው ቢሆንም አሁንም ድረስ ግን በሙሉ አቅሙ ማምረት ሳይቻለው ቆይቷል፡፡

የሚገጥሟቸውን ፈታኝ ችግሮች በተመለከተ ሲገልጹም አገሪቱ ከወጪ ንግድ ከማግኘት ያቀደችውን የገቢ መጠን ለማሳካት፣ መስተካከል አለባቸው የሚሏቸው ነጥቦች በርካታ ናቸው፡፡ ከሎጂስቲክስ አኳያ የወደብ ክፍያ፣ በአገር ውስጥ ለማጓጓዝ የሚጠይቀው የትራንስፖርት ወጪ በጨርቃጨርቅ መስክ ለተሳመሩ ኩባንያዎች ትልቁን ድርሻ የሚይዙ ችግሮች መሆናቸውን ሚስተር አይደኒዝ ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ለምሳሌ ወደ አገር ውስጥ ዕቃዎችን ለማስገባት የወደብ ክፍያው 1150 ዶላር ሲሆን ወደ ውጭ ለመላክ የሚጠይቀው 650 ዶላር ነው፡፡ ይህ ሌሎች ወደቦች ከሚያስከፍሉት 200 ዶላር አኳያ ሲታይ በጣም ውድ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ዕቃዎችን በአገር ውስጥ ለማጓጓዝ የሚጠይቀውን ወጪ በሚመለከትም፣ ባለ 40 ጫማ ኮንቴይነር ዕቃ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት 2175 ዶላር እንደሚወጣ፣ ወደ ውጭ ለመካልም 1400 ዶላር እንደሚያስከፍል ገልጸው፣ በዓለም አቀፍ ዋጋ አንጻር ከ200 እስከ 300 ዶላር የሚፈጀው የማጓጓዣ በኢትዮጵያ ግን ከሚቻለው በላይ የተጋነነ እንደሆነ በምሬት አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን በየአስባቡ የሚከሰተው መጓተትና መጉላላት ለእንደ አይካ አዲ ያሉት ግዙፍ ፋብሪካዎች ከባድ ራስ ምታት ሆኖባቸዋል፡፡

ይህም ይባል እንጂ የሚብሰው ከባድ ችግር ከጥጥ ጥራት ጋር እንደሚያያዝ ሚስተር አይደኒዝ አበክረው ይናገራሉ፡፡ ‹‹60 ከመቶው የሚሸፍነው ምርታችን ከተፈጥሮ ጥጥ እንደምናመርት ይታወቃል፡፡ ይሁንና የቱንም ያህል የተፈጥሮ ጥት ቢያመርቱ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ አምራቾች የጥራት ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት የላቸውም፤›› ያሉት ባለሀብቱ፣ በዚህ ሳቢያ አብዛኛውን የጥጥ ፍጆታ የሚያሟላው ከህንድ በማስመጣት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

የቡታግዝና የከሰል ድንጋይ ዋጋ በኢንዱስትሪው ለሚንቀሳቀሱ አምራቾች እንደ ሬት የሚያስመርሩ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ‹‹ከኢትዮጵያ ጋር ከሚፎካከሩ አገሮች አኳያ የቡታጋዝና የከሰል ድንጋይ ዋጋ ከፍተኛ ሆነው ይገኛሉ፤›› በማለት እስካሁን የተጠቀሱት ማነቆዎች ተደማምረው የአገሪቱን ተወዳዳሪነት ይበልጥ ሊሸረሽሩት እንደሚችሉ ያላቸውን ስጋት ከመግለጽ አልተቆጠቡም፡፡

ይሁንና በአገሪቱ ያለው ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ዋጋ ተስፋቸውን ቢገነባውም ተደጋግሞ የሚከሰተው መቆራረጥ ግን ቀዝቃዛ ውኃ ሲችልስበት ቆይቷል፡፡ በመሆኑም አነስተኛ የኃይል ማሰራጫ ጣቢያ በራሳቸው ወጪ ለመትከል መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡

እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ ሆኖም አይካ አዲስ የማስፋፊያ ግንባታ በአየር ጤና አከባቢ ለማካሄድ መዘጋጀቱን ሚስተር አይደኒዝ አስታውቀዋል፡፡ በአገሪቱ ከሚታየው የጥጥ ምርት አቅርቦትና ጥራት ችግር በመነሳት በኦሞ አካባቢ የፈተጥሮ ጥጥ ለማምረት የሚችሉበት ቦታ ቢረከቡም ፕሮጀክቱ ፈቅ ሊል እንዳልቻለ ታውቋል፡፡

በዓለም የአልባሳት ኢንዱስትሪ ውስጥ በርካታ ፍላጎት ካላቸው ኩባንያዎች ጥያቄ እንደሚቀርብለትና ጥሩ ገበያ እንደገነባም ይናገራሉ፡፡ ‹‹ማሽ አላህ በዚህ ዓመት በቂ ገበያ አግኝቻለሁ፤›› በማለት እ.ኤ.አ. በ2017፣ የ100 ሚሊዮን ዶላር ኤክስፖርት ዕቅዳቸውን እንደሚያሳኩ እርግጠኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

 

 

 

 

Standard (Image)

አፍሪካውያን በአኅጉራዊ የንግድ ቀጣና ላይ ለሳምንት የሚቆይ ምክክር ጀምረዋል

$
0
0

በመላው አኅጉረ አፍሪካ እንደሚተገበር ይጠበቅ የነበረው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት እንደታሰበው መጓዝ ሳይችል ቆይቷል፡፡ 54 አገሮች ስምምነት እንደሚያደርጉበት የሚታሰበው ይህ ስምምነት፣ በበርካታ ምክንያቶች ሁሉንም አገሮች አስማምቶ ወደ ተግባራዊነቱ ለማምጣት አቀበት በሆኑት ጉዳዮች ላይ በአዲስ አበባ ለመምከር የሳምንት ቀጠሮ የያዙ ልዑካን በከተማው ተገኝተዋል፡፡

በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽንና በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ትብብር የተሰናዳውና ለሳምንት የሚዘልቀው ጉባዔ፣ የ54ቱም አገሮች ተወካዮችን በማገናኘት ከዚህ ቀደም ምላሽ ማግኘት ያልቻሉ ጉዳዮች ላይ እልባት ይሰጣሉ ተብለው ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡

አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተጠባባቂ ዋና ጸሐፊ ዴቪድ ሉክ ሰኞ፣ ኅዳር 19 ቀን 2009 ዓ.ም. በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን አዳራሽ መካሄድ የጀመረውን ይህንን ጉባዔ በማስመልከት እንደተናገሩት፣ አፍሪካ እርስ በርስ በመተሳሰር የንግድ ልውውጥ ማድረግ ብትችል፣ በዓመት ከ2.5 ከመቶ ያላነሰ፣ በገንዘብ ሲመነዘርም ከ65 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለመላው የአኅጉሪቱ አገሮች ያስገኛል፡፡

በ54ቱ አገሮች ውስጥ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሕዝብ የሚገኝ ሲሆን፣ የአገሮቹ ጥርቅም የኢኮሚ አቅም (ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ) ከ3.4 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ይገመታል፡፡ አገሮቹ እርስ በርስ ቢገበያዩ፣ ድንበሮቻቸውንና ኬላዎቻቸውን ቢያነሱ፣ በገቢና ወጪ ንግዳቸው ላይ የጣሏቸውን የታሪፍ፣ የኮታ እንዲሁም ሌሎች ታርፍ ነክ ያልሆኑ ከልካይ ሁኔታዎችን እንዲያነሱ ግፊት የሚያደርጉት፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና የአፍሪካ ኅብረት አገሮች አኅጉራዊውን ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥናታዊ መረጃዎችንና ሌሎችም ማስረጃዎችን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡

በተስማሚ ወይም በአኅጉራዊው ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ያደረጉ አገሮች ምላሽ እንዲሰጡባቸው ከሚጠበቁ ነጥቦች መካከል ዴቪድ ሉክ ከጠቃቀሷቸው መካከል፣ አገሮች የነጻ ንግድ ስምምነቶችን ከማጽደቃቸው በፊት የሲቪል ማኅበራትንና ዜጎችን በማሳተፍ ለስምምነቱ ሕዝባዊ ተቀባይነት የማስገኘት ሒደት ላይ ምላሽ መስጠት ይጠብቃቸዋል የሚለው ይጠቀሳል፡፡ ሕዝቡን ማወያየት፣ ስለ ነጻ የንግድ ቀጣናው ስምምነት ጥቅሞችና ሥጋቶች ሰፊ ክርክሮችና ውይይቶች እንዲደረጉ ማድረግ የየአገሮቹ ኃላፊነት ይሆናል ተብሏል፡፡

በአኅጉር ደረጃ አገሮች ለውድድር መክፈት የሚኖርባቸው ዘርፎች የቱን ያህል ክፍት መደረግ አለባቸው፣ በአኅጉራዊው ነጻ የንግድ ስምምነት ምክንያት ከንግድ ሥራቸው ሊፈናቀሉና ተጋላጭ ሊሆኑ የሚችሉ ምን ያህል የኅብረተሰቡ ክፍሎች አሉ እንዲሁም በምን ያህል መጠን ለእነዚህ ክፍሎች ጥበቃ ማድረግ ያስፈልጋል፣ እያንዳንዱ አገርስ የትኛውን የኢኮኖሚ ክፍል ክፍት ማድረግ ይጠበቅበታል የሚሉትን ጨምሮ ምላሽ የሚሹ ጥያቄዎች በርካታ ናቸው፡፡ የስሪት አገር ሕጎች፣ ቴክኒካዊ የንግድ ክልከላዎችን ጨምሮ ሌሎችም ነጥቦች ለሳምንት በሚቆው ጉባዔ ወቅት እንደሚነሱ ይጠበቃል፡፡

ምንም እንኳ አኅጉራዊው ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት በበአብዛኞቹ አገሮች ዘንድ ተቀባይነት ቢያገኝም፣ ተግባራዊ አፈጻጸሙ ግን በበርካታ ምክንያቶች ወደኋላ እያለ ይገኛል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ስምምነቱን ከፈረሙ ቢሰነብቱም የአገሪቱን የንግድ አውታሮችና የኢኮኖሚ መስኮች ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ክፍት ማድረጉ ላይ የሚያነሷቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡

ኢትዮጵያ ለሌሎች አገሮች የንግድ በሯን ክፍት ማድረጓ በጥንቃቄ የሚደረግ እንደሆነ የመንግሥት ባለሥልጣናት ደጋግመው ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ የቀድሞው የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አህመድ ሺዴ በቅርቡ በዚሁ ጉዳይ ላይ ተጠይቀው እንዳብራሩት ከሆነም ቀድሞ ዝግጅት ሊደረግባቸው የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች በመኖራቸው በጥንቃቄ የሚታይ ነው፡፡

የኢኮኖሚ ምሁራን በበኩላቸው አገሪቱ በሯን መክፈት የምትችልበት አቅም ላይ መድረሷንና በሌሎች የአፍሪካ ምርቶች የምትጥለቀለቅበት ሥጋት ብዙም እንደማያሳምን ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድና የልማት ጉባዔ የአፍሪካ፣ ያላደጉ አገሮች ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋቸው ታፈረ ከመንግሥት የተለየ አቋም አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ ያላት የኢንዱስትሪም ሆነ የሕዝብ ብዛት በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ምርቶች የመጥለቅለቅ ሥጋት ውስጥ እንደማይከታት ያምናሉ፡፡ ይልቁንም አገሪቱ በጨርቃጨርቅ፣ በቆዳና በቆዳ ውጤቶች መስክ የሌሎች አገሮችን ገበያ የመጋራት አቅም ላይ እንደምትገኝ በመግለጽ የአፍሪካ ነጻ የገበያ ቀጣና ስምምነትን ተግባራዊ እንድታደርግ ሲመክሩ ይታወሳሉ፡፡

የአፍሪካ የእርስ በርስ የንግድ ግንኙነት እጅግ አነስተኛ በሆነበት ይልቁንም አፍሪካውያን ከሌሎች አኅጉራት ጋር ያላቸው የንግድ ልውውጥ ከፍተኛ በሆነበት፣ እንደ አሜሪካ ያሉ አገሮች ከታሪፍና ከኮታ ነጻ የገበያ ዕድል (አጎዋ) በሰጡበት ወቅት፣ ከሌሎች ለመማርና ግንኙነትን ለማስፋፋት የሚያስችሉ ዕድሎች ባሉበት ወቅት አፍሪካውያኑ ወደ አኅጉራዊው ነጻ የንግድ ስምምነት ትግበራ ለመምጣት የሚያሳዩት ማቅማማት ሲያስተቻቸው ቢቆይም፣ የየአገሮቹ ተደራዳሪዎች የሚያነሷቸው አንኳር ጥያቄዎች ምላሽ ሊያገኙ ባለመቻላቸው ነጻ የገበያ ቀጣና በአፍሪካ ደረጃ ዕውን ሳይሆን እንደቆየ በጉባዔው የሚደመጥ ሐሳብ ነው፡፡ በሳምንቱ መጨረሻ አገሮቹ ሊስማሙባቸው አሊያም ይበልጥ ልዩነቶቻቸውን ሊያሰፉ የሚችሉባቸው ነጥቦችም ከወዲሁ ትኩረትን ስበዋል፡፡

 

 

Standard (Image)

ሥራ ያጣው ሥራ ተቋራጭ

$
0
0

በደረጃ አንድ ተቋራጭነት ከሚንቀሳቀሱ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች መካከል  በተለይ በሕንፃ ግንባታዎች መስክ በአብዛኛው ከሚጠቀሱት ውስጥ አንዱ ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን (ታኮን) ነው፡፡ ከ1,700 በላይ ሠራተኞችን ሲያስተዳድር የቆየው ታኮን፣ አሁን ላይ በግዙፍነቱ የሚጠቀሰውን ያዩ የማዳበሪያ ፋብሪካ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ በትግራይ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ስታዲየም፣ በአዲስ አበባ ከተማ ልደታና መገናኛ አካባቢ የተገነቡትን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕንጻዎች፣ የዳኞች መኖሪያ ቤት (አራት ባለ ጂ+18 ሕንፃዎች) ጨምሮ በመቀሌ፣ በጂማ፣ በሐዋሳ፣ በባህር ዳር፣ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍም ይጠቀሳል፡፡ የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የማሪታይም ሕንፃ ማጠቃለያ፣ የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ሕንፃ ግንባታዎችን አጠናቆ ማስረከቡም ሳይወሳ አይታለፍም፡፡ 650 መጋዘኖችና ሱቆች ያሉትን ትልቅ የገበያ ማዕከል ጨምሮ ከአፍሪካ ኢንሹራንስ ኩባንያ ሕንፃዎች አንዱን ገንብቶ ሲያጠናቅቅ፣ ሁለተኛውን በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ ከጤና ኬላዎች እስከ ትልልቅ ግንባታዎች ላይ ተሳታፊ የሆነው ይህ ኩባንያ በአሁኑ ወቅት የ18 ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራዎች በእጁ ቢኖሩም አብዛኛዎቹን ወደማጠናቀቁ መቃረቡን አስታውቋል፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭም በሶማሊያ የበርበራ ተርሚናል ግንባታ ላይ ተሳትፏል፡፡ ሰሞኑን ግን ከታኮንና ከሌሎች እህት ኩባንያዎችን ከሚያስተዳድረው ታፍ ኮርፖሬት ሥር ከሚገኙ ኩባንያዎች 442 ሠራተኞችን ቀንሷል፡፡ ኩባንያው አትራፊና ውጤታማነቱ እየጎላ በሚነገርበት በዚህ ወቅት ለምን ቅነውን አደረገ? የሚለው ጥያቄ ቀድሞ ያቃጭላል፡፡ ታኮንን ጨምሮ ከሰባት ያላነሱ ኩባንያዎችን የሚያስተዳድረው ታፍ ኮርፖሬት እንዳስታወቀው ከሆነ ለሠራተኞቹ መቀነስ ምክንያታዊና በመግባባት ላይ የተመሠረተ ዕርምጃ ተወስዷል፡፡ ቅዳሜ፣ ኅዳር 17 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሠራተኞቹ በተዘጋጀ የስንብት ፕሮግራም ወቅትም ይኸው ተንፀባርቋል፡፡ በሠራተኞች ቅነሳና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ዳዊት ታዬ የታፍ ኮርፖሬች ሥራ አስፈጻሚ የሆኑትን አቶ ሰይፉ አምባዬን አነጋግሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ከተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ጀምሮ በታፍ ኮርፖሬት ሥር በሚተዳደሩ ኩባንያዎቻችሁ ውስጥ ይሠሩ የነበሩ ሠራተኞች ቅነሳ አድርጋችኋል፡፡ ይህንን ማድረግ ለምን አስፈለገ? የተቀነሱትስ ምን ያህል ናቸው?

አቶ ሰይፉ፡- ከታኮን 324፣ ከይበል ኢንዱስትሪ 102፣ ከታፍ ኮርፖሬት ዋና መሥሪያ ቤት ደግሞ 16 ያህል ሠራተኞችን ቀንሰናል፡፡ ከሦስቱ ድርጅቶች በአጠቃላይ የተቀነሱት 442 ሠራተኞች ናቸው፡፡ ሠራተኞቹን ለመቀነስ የተገደድንባቸው ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች አሉ፡፡ አንዱ በእጃችን ከሚገኙ ፕሮጀክቶች ወደ ሦስት አራተኛ የሚሆኑት ወደ ማጠናቀቂያ ሥራ የገቡ በመሆናቸው ነው፡፡ የግንባታ ፕሮጀክቶች ወደ ማጠናቀቂያ ሥራ ሲደርሱ በርካታ ቁጥር ያለው ትርፍ ሠራተኛ ይኖርሃል ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ወደ ማጠናቀቂያ ሥራ የደረሱ ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠል በመቸገራችን ነው፡፡ ይህም ማለት ለማጠናቀቂያ ሥራው የሚሆኑ ዕቃዎችን ከውጭ ለማስገባት የሚያስፈልገንን የውጭ ምንዛሪ ባለማግኘታችን ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ከዛሬ ነገ እናገኛለን በሚል ተስፋ ከስድስት እስከ ስምንት ወራቶች ይህን ያህል ቁጥር ያለው ሠራተኛ ይዘን ስነጠብቅ ቆይተናል፡፡ ይህንን ተሸክሞ መቀጠል ከባድ እየሆነ መጥቷል፡፡ የውጭ ምንዛሪው ከዛሬ ነገ ይፈቀዳል ይባላል ግን ሊፈቀድልን አልቻለም፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የምንጠቅሰውና ለሠራተኞች መቀነስ ምክንያት የሆነን ትርፍ ቁጥር ያላቸውን ሠራተኞች ይዘን ለመቀጠል የሚያችሉን አዳዲስ ፕሮጀክቶች ማግኘት አለመቻላችን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ታኮን እንደ ቀድሞው አዳዲስ ፕሮጀክቶች ማግኘት ያልቻለበት ምክንያት ምንድን ነው?

አቶ ሰይፉ፡- ለዚህ ምክንያቱ ብዙ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዱ መንግሥት የሚያወጣቸው ጨረታዎች ጋር የሚያያዝ ሊሆንም ይችላል፡፡ ብዙውን ጊዜ ጨረታዎች የሚወጡት በዓመቱ አጋማሽ ወቅት ጥር ወይም ታኅሳስ ላይ ነው፡፡ በዚህ ወቅት አዲስ ሥራ ብናገኝ የቀነስናቸውን ሠራተኞች ልንመልሳቸው እንችላለን፡፡ ስለዚህ በዚህ ምክንያት በጣም ብዙ ሠራተኞች ተሸክመን መሄድ አስቸጋሪ እየሆነብን መጥቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኮርፖሬቱ ዋነኛ ገቢ ታኮን ነው፡፡ በመሆኑም እሱ ሥራ አላገኘም ማለት ነገሩን ሁሉ አስቸጋሪ ያደርገዋል ማለት ነው፡፡ የታኮን ሥራ አለማግኘት በኮርፖሬሽኑም ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ምክንያቱም ዋናው ገቢ ከኮንስትራክሽን ዘርፉ (ከታኮን) የሚገኝ በመሆኑ ነው፡፡ በኮርፖሬቱ ሥር ያለው ሌላው ተቋም ይበል ኢንዱስትሪያል የተባለው ድርጅታችን ሲሆን፣ በኮርፖሬቱ በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠ የገቢ ምንጭ ኩባንያ ነው፡፡ ነገር ግን በጣም በርካታ ሥራዎች በእጁ ይዞ የነበረው ይኸው ይበል ኢንዱስትሪም በተመሳሳይ መንገድ በእጁ የነበሩ ሥራዎችን በአብዛኛው አጠናቆ አስረክቧል፡፡ ይበል ኢንዱስትሪያል በጣም የተቸገረበት ሌላው ነገር ማግኒዚየም ኦክሳይድ ያቀርብለት የነበረ አንድ ተቋም ሥራ ማቆሙ ነው፡፡ ይበል ኢንዱስትሪ ማግኒዥየም ቦርድ ለማምረት የሚጠቀምበት ጥሬ ዕቃ የሚያቀርበው ይህ ኩባንያ በመሆኑ እኛ በማናውቀው ምክንያት ሥራ ማቆሙ ለይበል ሥራ እንቅፋት ሆኗል፡፡ የማግኒዢየም ግብዓት ከሌለ ደግሞ ማግኒዥየም ቦርዱንም ሆነ ሌሎች ምርቶችን ማምረት ስለማይቻል ከይበል ኢንዱስትሪያልም ሠራተኞችን ለመቀነስ ተገደናል፡፡ ወደዚህ ዕርምጃ ከመግባታችን በፊት ለበርካታ ወራት ሥራ እናገኛለን ብለን በተስፋ በመጠባበቅ ሥራ ያልነበራቸውን ሠራተኞች ሳንቀንስ ቆይተናል፡፡ ምናልባት ካለን የሥራ አኳያ መጠን አኳያ እነዚህን ሠራተኞች ከስድስት ወይም ከሰባት ወራት በፊት መቀነስ ነበረብን፡፡ ነገር ግን ከዛሬ ነገ ሥራ ሊመጣ ይችላል የሚል ተስፋ ስለነበረን እንዲቆዩ አድርገናል፡፡ ሠራተኞች እንዳይቀነሱ የነበረን ፍላጎት ብርቱ ነበር፡፡ ሠራተኞቹ ብዙ ሥልጠና ያገኙና ያበቃናቸው፣ በዓመት ብዙ ሥልጠና የወሰዱና በብዙ የሥራ ግምገማ ሒደቶች ውስጥ ያለፉ፣ በየጊዜው ተገምግመውም ብቃታቸው የተመሰረከላቸው አሉ የተባሉ ሠራተኞች ናቸው፡፡ በዚህ ደረጃ ብቃት የነበራቸው ሠራተኞች በመሆናቸው ላለመልቀቅ ስንንገታገት ቆይተናል፡፡ በመጨረሻ ግን በእንዲህ ያለ አካሄድ መጓዙ አስቸጋሪ ሆነብን፡፡ በመሆኑም እነዚህን ሠራተኞች ለጊዜው እንቀንስና ሥራ ማግኘታችን ስለማይቀር ቅድሚያ እንደምነሰጣቸው በማሰብ ጭምር የወሰድነው ዕርምጃ ነው፡፡ ሥራ ስናገኝ እነሱን እንመልሳለን ያልነውም በምንፈልገው ደረጃ ሥለሰለጠኑ ነው፡፡ ከድርጅታችን ጋር ብዙ  ሠርተዋል፡፡ ለሥራውም ለድርጅቱም ፍቅር አላቸው፡፡ ይህንን እናውቃለን፡፡ ስንብቱ በይፋ ከተገለጸ በኋላ ከሠራተኞች ያገኘነው ምላሽም ይህንኑ ነው፡፡ ሥራ መልቀቅ ጥሩ ስሜት ባይፈጥርም በመተማመንና በመግባባት የተፈጸመ ነው፡፡ ይህንን ቃል ገብተን ነው የምንሸኛቸው፡፡ ሌላው ሕጉ በሚፈቅደውና እነሱ ደስ በሚላቸው መንገድ ትክክለኛ ሕጉን ተረድተው ነው እንዲቀነሱ ያደረግነው፡፡ አብዛኛው ሠራተኛ የተቀነሰው ከኮንስትራክሽን ኩባንያው ነው፡፡ በኮንስትራክሽን ሥራ ያለምንም ማስጠንቀቂያ ልታሰናብት ትችላለህ የሚል ሕግ አለ፡፡ እኛ ግን በዚያ መልኩ አልሄድንም፡፡ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት፣ ግን ደግሞ በማያሻማ መንገድ፣ ሠራተኛውንም በማይጐዳ ሁኔታ ነው የምንቀንሳቸው፡፡ ስናሰናብታቸው የአራት ወር ደመወዝና የአገልግሎታቸውን ክፍያ ጨምረን ነው የምንሸኛቸው፡፡     

ሪፖርተር፡- እዚህ ላይ ግን የአራት ወር ደመወዝ ከፍላችሁ በተጨማሪም የአገልግሎት ዘመን ክፍያ አክላችሁ መሸኘታችሁ ግድ ከሆነ አዲስ ሥራ እስኪገኝ ድረስ ቢያንስ ለአራት ወራት ከሥራ ገበታቸው ሳይለቁ ማቆየት አይቻልም ነበር? ምክንያቱም የአራት ወር ደመወዝ ከፍላችኋል፡፡

አቶ ሰይፉ፡- አራት ወር አቆየናቸው ማለት እኮ ለእነሱ አገልግሎት ማቅረብ አለብን ማለት ነው፡፡  እነሱን ማኔጅ ማድረግ አለብህ፡፡ እነሱ ያለሥራ መቀመጣቸው ሥራ እየሠራ ባለው ሠራተኛ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ የብቃት ችግር ነው የሚጨምረው፡፡ ስለዚህ ለእነሱ የአራት ወርና የአገልግሎት ክፍያ ጨምረህ ሸኝተህ ያለውን ሠራተኛ ውጤታማ ማድረግ ስለሚያስፈልግ ነው ያሰናብታናቸው፡፡ ሥራ ሲገኝ ደግሞ የሄዱትን መመለስ ይቻላል፡፡ እናቆያቸው ቢባል እንኳ ለእነሱ የሚሆን ሥራ እኮ የለም፡፡ ያደረግነው የቅነሳ ሒደት ግን ቀሪውንም ሆነ የተቀነሰውን ሠራተኛ ስሜት በማይነካ መልኩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደዚህ ዕርምጃ ከመግባታቸው በፊት ስለሁኔታው ከሠራተኞች ጋር መክራችኋል? ለምሳሌ ቅነሳው በትክክል እርስዎ እንዳሉት ከፕሮጀክት መጠናቀቅና አዳዲስ ሥራ ከመጥፋት ጋር መሆኑን ነግራችኋል? ቅሬታ አልፈጠረም ትላላችሁ?

አቶ ሰይፉ፡- ከሠራተኛው በሚገባ ጋር ተመክሮበታል፡፡ በያንዳንዱ ሳይት ላይ በዚሁ ጉዳይ ውይይቶች አድርገናል፡፡ ለምሳሌ ያዩ የማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክት ድረስ በመሄድ ስለሁኔታው አስረድተናል፡፡ የየኩባንያዎቹ የሥራ ኃላፊዎች ሠራተኞቹን በጋራ አወያይተዋል፡፡ በግል እየጠሩም ጭምር በማነጋገር ስላለው ሁኔታ በማነጋገር በሁኔታው ላይ ተማምነዋል፡፡ ሠራተኞቹ በምላሹ የሰጡት አስተያየትም የሚያስደስት ነው፡፡ አስተያየታቸውም በመግባባት ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ ለስንብት በተዘጋጀው የምሳ ፕሮግራም ወቅት ሠራተኞቹ በፍቅር ነው የተሸኙት፡፡ ስለዚህ ከመጀመሪያው ጀምሮ በተሟላ መግባባት የተሠራ ሥራ ነው፡፡ እንዲያውም ወደ ዕርምጃው ከመግባታችን በፊት ከማኔጅመንቱ ጋር ተማምነን ነው፡፡ የተቀነሱት ሠራተኞች ሕግ በሚፈቅደው መሠረት መሆኑን መግለጻቸው ብቻ ሳይሆን አምነውበትም ነው፡፡ በአጠቃላይ ስናየው ከየኩባንያዎቻችን የሚቀርበው አቤቱታ ከአቅማችን በላይ ሠራተኞች ተሸክመናል ምን እናድርግ የሚሉ ነበሩ፡፡ በዚህ መሠረት መቀነስ አለበት የምትሏቸውብ የሠራተኞች ብዛት አቅርቡና በሕጉ መሠረት ፈጽሙ ነበር ያልነው፡፡ በቅነሳው ዙሪያ አስተዳደሮቻችን እንዳይሳሳቱ አራት የሕግ ባለሙያዎችን በመያዝ በጉዳዩ ላይ ሦስት ወይም አራት ጊዜ ውይይት አድርገናል፡፡ ስለዚህ በሁሉም አቅጣጫ የሕግ ባለሙያዎቹ ያላቸውን ሐሳብ አቅርበው ሐሳቡን ወደ አንድ በማምጣት በዚያ መልኩ ነው ወደ ዕርምጃው የሄድነው፡፡ ሌላ ምንም ችግር የለም፡፡ ሌላው ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ የቆመ ነገር የለም፡፡  

ሪፖርተር፡- ኩባንያችሁ የዚህን ያህል ሠራተኛ ሲቀንስ አብሮ የሚታየው የገቢው መቀነስ ጋር አይያያዝም? የሠራተኛ ቅነሳ ሲባል የድርጅቱ እንቅስቃሴ መቀነሱንም ያመለክታልና፡፡

አቶ ሰይፉ፡- በፍፁም የድርጅቱ ገቢ በመቀነሱ አይደለም፡፡ ድርጅቱ የተሻለ ገቢ አለው፡፡ ካለፈው ዓመትም የበለጠ ገቢ እያገኘ ነው፡፡ ጥያቄው በምንም መልኩ ከዚህ ጋር አይገናኝም፡፡ ዘንድሮ ግን እንሠራዋለን ያልነውን ሥራ ለመሥራት የሚያስችል የሰው ኃይልና ማሽነሪ ነበረን፡፡ አዳዲስ ሥራዎች ስላላገኘን በእጃችን ካሉትም ወደ 18 ፕሮጀክቶች ውስጥ ወደ ሦስት አራተኛው ማጠናቀቁ ላይ ደረስን፡፡ ሥራዎቹ እዚህ ደረጃ ላይ ከደረሱ በኋላ አብዛኛው ሥራ የሚሠራው በሰብ ኮንትራት ነው፡፡ የእኛ ሰው ሥራ እነዚህን ሰብ ኮንትራክተሮች ማስተባበርና መቆጣጠር ነው፡፡ እኛ ፍሬሙን ከጨረስን፣ ኮንክሪቱን ካጠናቀቅን በኋላ የእኛ ሰው የሚሠራው ሌላ ሥራ አይኖረውም፡፡ ከዚህ ወዲያ ያለው በሰብ ኮንትራክተር የሚሠራ ነው፡፡ የአሉሚኒየም፣ የወለል፣ የኤሌክትሪክ ዝርጋታ፣ የሳኒተሪና የመሳሰሉት በሰብ ኮንትራክተሮች የሚሠሩ ሥራዎች በመሆናቸውና እነዚህ ሥራዎችም በፕሮጀክቶቻችን መጠናቀቂያ ላይ በመድረሳቸው ምክንያት ሥራ የፈታውን ሠራተኛ አዲስ ሥራ ካገኘህ ወደዚያ ማዛወር አለብህ፡፡ ካልሆነ ግን ትቀንሳለህ፡፡  

ሪፖርተር፡- በአጠቃላይ ፕሮጀክቶቻችሁ ሦስት አራተኛው የማጠናቀቂያ ሥራዎች ላይ ከደረሱ፣ እርስዎ እንዳሉትም ተጨማሪ አዲስ ሥራ ከሌለ ቀጣዩ ጉዞዋችሁ ምን ሊሆን ነው? በዘርፉስ አሸንፈን ልንረከበው እንችላለን ብላችሁ የምትጠብቁት ሥራ አለ?

አቶ ሰይፉ፡- ለሠራተኞች ቅነሳ ምክንያት የሆነው አንዱ ጉዳይ ጨረታዎችን ለማሸነፍ እየተቸገርን መሆናችን ነው፡፡ ጨረታዎችም በብዛት አልወጡም፡፡ ከውጭ ኮንትራክተሮች ጋር ያለው ፉክክርም በጣም በርትቷል፡፡ ስለዚህ አብዛኛውን ሥራ የውጭ ኮንትራክተሮች እየወሰዱት ስለሆነ ይህ ትልቅ ተግዳሮት ሆኗል፡፡ ይህንን ችግር ከመንግሥት ጋር በመነጋገር መፍታት ያስፈልጋል፡፡ መንግሥትም ያለውን ሁኔታ በመገንዘብ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን የሚደግፉ ሕጎች እያወጣ ነው፡፡ ይህ ተስፋ ሰጪና መልካም ነገር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን የሚደግፉ ሕጎችን እያወጡ ነው ሲሉ ለምሳሌ የትኛው ሊጠቀስ ይችላል?

አቶ ሰይፉ፡- ለምሳሌ በኤሌክትሪክ ኃይል ዙሪያ በሚወጡ ጨረታዎች ወቅት የውጭ ኮንትራክተሮች ሲጫረቱ፣ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች 40 በመቶ የእሽሙር ወይም የጆነት ቬንቸር አጋርነት መፍጠር አለባቸው የሚል አንቀጽ አለ፡፡ እንዲህ ዓይነት ሕጎች ካሉ በሁለት መንገድ ጥቅም ይኖራቸዋል፡፡ አንዱ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ሥራ እንዲያገኙ ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ በጆይንት ቬንቸር መሥራታችን ደግሞ ለዕውቀት ሽግግር ይጠቅመናል፡፡ አሁን ግን ሥራ የማግኘት ከፍተኛ ችግር አለ፡፡ በጨረታው ሥርዓት ውስጥ እንዲህ ያሉ ሕጎች መኖራቸው መልካም ነው፡፡ ሌላው ቁልፍ ጉዳይ ደግሞ እኛው ራሳችን መዘጋጀት ስለሚኖርብን ነው፡፡ በምን መልኩ ነው ሥራ ማግኘት ያለብን? ለሥራችን የምንጠይቀው ዋጋ ከፍ ብሎ ከሆነም ሁኔታውን ማየት ወይም የአቅም ችግር ከሆነም ራሳችንን ማደርጀትና ማብቃት ይጠበቅብናል፡፡ ተወዳዳሪ ለመሆን በሁሉም ረገድ ራሳችንን ማብቃት አለብን፡፡ በሁለቱም ወገን መንግሥት የሚሠራውን ሥራ አጠናክሮ ከቀጠለና በእኛ በኩል ያለውን ክፍተትም ከሞላን አሁን ያሉትን ችግሮች ለዘለቄታው መፍታት እንችላለን፡፡ ይህ መሆን ከሆነ ችግሮቻችን ጊዜያዊ ይመስሉኛል፡፡ እኛም እያየን ያለነው ነገር ስላለ በእኛ በኩል እየተዘጋጀን ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን (ታኮን) በብዛት የሚታወቀው በሕንፃ ግንባታ ነው፡፡ ወደ መንገድ ሥራ የመግባት ዕቅድ የለውም?

አቶ ሰይፉ፡- መንገድ ሥራ ላይ ገብተናል፡፡ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ መሥራት ጀምረናል፡፡ በጣም የምንታወቅበት ባይሆንም መንገድ ላይ ሠርተናል፡፡ እርግጥ የሠራናቸው ትንንሽ ናቸው፡፡ አሁን ግን ጨረታ ውስጥ ገብተን ትንንሽ ቢሆኑም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ልናሸንፍባቸው እንችላለን ብለን የምናስባቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ሆኖም በትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ከመሳተፍ የሚገድበን ነገር አለ፡፡ እኛ ብዙውን ጊዜ በሕንፃ ግንባታ ላይ ስለሆነ ያሳለፍነው ትላልቅ የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ ለመሳተፍ እንደ ቅድመ ሁኔታ እየቀረቡ ያሉት እንደ ተርን ኦቨር ያሉትን መጠይቆችን ለማሟላት እንቸገራለን፡፡ ይህንን ችግር መንግሥት ያጤነው ይመስለኛል፡፡ ለማስተካከልም የተጀመሩ ነገሮች አሉ፡፡ ለእኛ ብቻ ሳይሆን በርካታ የአገር በቀል ኮንትራክተሮች መንገድ ሥራ ላይ ያላቸው ተርን ኦቨር ትንሽ ስለሆነ ይህ እንዲታይልን ለመንግሥት ጥያቄ አቅርበናል፡፡ እንደምንሰማው ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንም ሆነ ከግዥ ኤጀንሲ አወንታዊ ነገር መኖሩን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ለመጫረት የሚጠየቀው ተርን ኦቨር የአገር በቀል ኮንትራክተሮችን አቅም ያገናዘበ እንዲሆን አንዳንድ መሻሻሎች ይደረጋሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡ ይህ ከሆነ ትልልቅ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ እንገባለን፡፡ አሁን ትልቅ ችግር እየሆነ ያስቸገረን የሚጠየቀውን መስፈርት የሚያሟሉ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ጥቂት መሆናቸው ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አብዛኛውን የመንገድ ግንባታ ሥራ የሚወስደው የውጭ ኮንትራክተር ሆኗል፡፡ አንድ ጊዜ ወደ ስምንት ፕሮጀክቶች ጨረታ ወጥተው ሁሉንም የውጭ ከንትራክተሮች ወስደዋቸዋል፡፡ ይህ አሳሳቢ ነው፡፡ እንዲህ መቀጠል አለበት ብለን አናምንም፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙ ጊዜ እንደሚባለው የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች የጨረታ መስፈርት ጠንካራ በመሆኑ ሊያሟሉ የሚችሉት ዓይነት መስፈርት ይቀረጻል ሲባል ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ጉዳይ በተመለከተ በማኅበራችሁ በኩል ያደረጋችሁት እንቅስቃሴ አለ?

አቶ ሰይፉ፡- እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን በማኅበራችን በኩል ነው እያቀርብን ያለነው፡፡ መስፈርቱን በሚመለከት ማኅበሩ ለኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ጉዳዩን አቅርቧል፡፡ ባለሥልጣኑም ለግዥ ኤጀንሲ ጉዳዩን አቅርቧል፡፡ በተወሰነ ደረጃ የተሻሻለ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ከአሁን በኋላ የሚኖሩ ጨረታዎች እንደ ቀድሞው ለአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ላይከብዱ ይችላሉ የሚል ተስፋ ይዘናል፡፡

ሪፖርተር፡- ለአገር ውስጥ ኮንትራክተር ችግር ከነበረው ውስጥ የትኛው መስፈርት ላይ ነው ማሻሻያ ይደረጋል ብላችሁ የምትጠብቁት?

አቶ ሰይፉ፡- በመንገድ ላይ ለመጫረት አቅርቡ የምንባለው ተርን ኦቨር መጠንና ልምድ  ላይ የሚጠየቀው ነው፡፡ አቅርቡ የሚባለው ተርን ኦቨር መጠን ከቀነሰ የሚጠየቀውም ልምድ ከተሻሻለ ብዙውን መስፈርት የሚያሟላ ኮንትራክተር ይኖራል፡፡ ችግሩ የሚነሳው በኮንስትራክሽን ሥራ ውስጥ የቆየው አብዛኛው ተቋራጭ በመንገድ ሥራ ላይ ሳይሆን በሌላ ግንባታ መስክ ስለሆነ ለመንገድ የሚጠየቀውን መሥፈርት ሳናሟላ ይቀራል፡፡

ሪፖርተር፡- ትልልቅ ግንባታዎችን ለማካሄድ ጨረታ የሚያወጡ ኩባንያዎች አገር በቀል ኮንትራክተሮች ሊያሟሉ የማይችሏቸውን መሥፈርቶች ሆነ ብለው እያካተቱ የጨረታ ሠነድ ያዘጋጃሉ ይባላል፡፡ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ሊሠሯቸው የሚችሉ ሥራዎች ሆነው ሳለ የሚጠየቁት መሥፈርት ግን እነሱን የማያሳትፍ እየሆነ ነው ይባላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ነገር እንዲስተካከል ኮንትራክተሮች ይጠይቃሉ፡፡ ማኅበራችሁስ በዚህ ረገድ የሠራው ሥራ አለ? እርስ በርስ ትመካከራላችሁ?

አቶ ሰይፉ፡- ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በማኅበር ተደራጅተን ወደ የመሥሪያ ቤቱ ሄደናል፡፡ አማካሪ ቀጥረን የሌሎች አገሮች ልምድ ምን ይመስላል የሚለውን ሁሉ አስጠንተናል፡፡ የሌሎች አገሮች ልምድ ምን እንደሚመስል አይተናል፡፡ ከዚህ አንፃር በመንግሥት አካላት ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ሠርተናል፡፡ የግል ዘርፉም የራሱ ድርሻ አለው፡፡ መንግሥት የመሪነት ሚናውን ከተጫወተ የምንጠብቀው ነገር ይኖራል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ገበያውን የሚገዛው ውድድር ነው፡፡ የግል ዘርፉ ተዋናዮች በዚያ መልኩ መሄድ መብታቸው ቢሆንም፣ እዚህ አገር ያልተሠራ ነገር፣ የአገር ውስጥ ኮንትራክተር ሠርቶት የማያውቀውን ሥራ እንደ መሥፈርት እየቀረቡ ነው፡፡ ያልተሠራ ሥራ መሥራት አለባችሁ ተብሎ መስፈረት መውጣት የለበትም፡፡ በሌላ መልኩ መካካስ ነበረበት፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ለአገር ውስጥ ኮንትራክተር አደገኛ ነገር ነው፡፡ እንዲህ ባሉ መሥፈርቶች የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ሥራ እንዳያገኙ ማድረግ ኮንትራክተሩን ብቻ የሚጎዳ አድርገን መውሰድ የለብንም፡፡ ነገሩን እንደ አገር ካየኸው የኮንትራክተሩ ጉዳት ትንሽ ነው፡፡ ለውጭ ኮንትራክተር የሚሰጡ ሥራዎች እየበዙ በመጡ ቁጥር በኮንስትራክሽን ዙሪያ ያሉ አገር በቀል ኩባንያዎችን በጠቅላላ ይጐዳል፡፡ ምክንያቱም አንድ ፕሮጀክት በውጭ ኮንትራክተር ተሠራ ማለት ሥራውን የተረከበው የውጭ ኩባንያ የትኛውንም የግንባታ ግብዓት ከውጭ ኩባንያ በመግዛት በብዛት ውደ አገር ውስጥ ያስገባል፡፡ የሰብ ኮንትራክት ሥራዎችንም የሚሰጠው ለውጭ ኮንትራክተር እንዲሆን ዕድል ይሰጠዋል፡፡ ሠራተኛውንም ከውጭ ያስመጣል፡፡ ባለሙያውም ከውጭ ያመጣል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ነገሮች አገር በቀል የኮንስትራክሽን ግብዓት አቅራቢዎች ላይም ተፅዕኖ ስለሚያሳርፉ በመጨረሻው የሚጎዳው የአገሪቷ ሕዝብና በዚያ  የሥራ መስክ የተሠማሩትን ባለድርሻዎች ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ካየነው የአገር ውስጥ ኮንትራክተር ይሳተፍ ሲባል ለራሱ አስቦ ብቻ እንዳልሆነ መታወቅ አለበት፡፡ ጉዳዩን እንደ አገር ጉዳይ ማየት አለብን፡፡ በውጭ ኮንትራክተሮች የሚሠሩ ፕሮጀክቶች የሚፈልጉትን ነገር ከውጭ እንዲመጣ ያደርጋሉ እንጂ እዚሁ ባለ ነገር ላይ እሴት ጨምረው አይሠሩም፡፡ የአገር ውስጥ ኮንትራክተር ሥራውን ቢያገኝ ግን የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን አሠማርቶ ነው የሚሠራው፡፡ ስለዚህ ይህ ሁኔታ ሊያሳስበን ይገባል፡፡    

ሪፖርተር፡- ታኮን ኩባንያ እንደ አዲስ ራሱን ለማደራጀት በማሰብ አዲስ መዋቅር መዘርጋቱን አስታውቆ ነበር፡፡ በዚህ አሠራር ለውጥ አመጣ?

አቶ ሰይፉ፡- ውጤቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ታኮን በአማካይ በዓመት 106 ከመቶ እያደገ ነው፡፡ የለውጥ ሥራውን በአዲስ አሠራር ከጀመርን በኋላ ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል፡፡

ሪፖርተር፡- በምሳሌ ሊገለጽ ይችላል?

አቶ ሰይፉ፡- በገቢ፣ በትርፍና በጥራት ሥራን አጠናቆ በማስረከብና በመሳሰሉት መሻሻሎች አሉ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ትልቅ እመርታ እያየን ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ ለውጥ አንፃር ተመጣጣኝ ሥራዎች አልነበሩንም፡፡ ስለዚህ ሥራ መፍጠሩ ላይ እኛም በራሳችን መሥራት አለብን፡፡   

Standard (Image)

የግብርና ምርት ማቀነባበሪያዎች በውጭ ምንዛሪ እጥረት ማምረት እንዳልቻሉ ገለጹ

$
0
0

የግብርና ውጤቶችን በማቀነባበር ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች የውጭ ምንዛሪ እጥረት ማነቆ እንደፈጠረባቸው ገለጹ፡፡ ለአግሮ ፕሮሰሲንግ ፋብሪካዎቹ የማምረቻ ጥሬ ዕቃዎችን ከውጭ ለማስገባትም ሆነ፣ ያመረቱትን ወደ ውጭ ለመላክ የሚውሉ እንደማሸጊያ ያሉ ግብዓቶችን ከውጭ ለማስገባት እንቅፋት እንደፈጠረባቸውና ሙሉ አቅማቸውን ከመጠቀም እንደገታቸው አስታውቀዋል፡፡

በሥራቸው ላይ እክል የሆነባቸውን ችግር እንደሚፈልጉት መጠን እንዳይሠሩ እንዳገዳቸው ቅሬታቸውን የገለጹት ኩባንያዎች፣ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ከዓመት ላላነሰ ጊዜ ወረፋ የሚጠብቁበት ሁኔታ መኖሩ እንዳማረራቸውና አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

በሞያ ፉድ ኮምፕሌክስ የሽያጭና ግብይት ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ መገርሳ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ድርጅቱ በሙሉ አቅሙ እንዳይሠራ እንዳገደው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ድርጅቱ አራት ዓይነት ጣዕም ያላቸው ብስኩቶችን አምርቶ ለገበያ ያቀርባል፡፡ ማሸጊያና የተለያዩ ቅመሞችን የሚያስመጣውም ከአውሮፓ ነው፡፡ የምርቶቹን ዓይነት ለመጨመር ፍላጎት ቢኖረውም በተጋረጠበት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ የምርት መጠኑን መጨመር ቀርቶ የነበሩትንም የምርት ዓይነቶች ለማስቀጠል እንደተቸገረ ገልጸዋል፡፡

በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ለተለያዩ የምርት ሥራዎች የሚውሉ ኬሚካሎች፣ ማሸጊያዎችና የመሳሰሉትን ጥሬ ዕቃዎች ከውጭ በሚያስመጣው በትንሳዔ ኢንተርናሽናል የቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ኃላፊ አቶ ብሩክ ሞገስም ኩባንያው ስለሚገኝበት ችግር እንዲህ ብለዋል፡፡ ‹‹ድርጅቱ ዕቃዎቹን የሚያስመጣው ከስዊዘርላንድ ነው፡፡ አሁን ባለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ዕቃዎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት እየተቸገርን ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ የምናገኘው ጥያቄ ባቀረብን በዓመቱ ነው፡፡››

እንጀራና ሌሎችም ምግብ ነክ ነገሮችን ወደ ውጭ የሚልኩ ድርጅቶችም ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ለመላክ ደረጃውን የጠበቀ ማሸጊያ እንደሚያስፈልጋቸው፣ ነገር ግን ባለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት የሚፈልጉትን ለማግኘት እየተቸገሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ይህንን ያሉት አራተኛው አዲስ አግሮ ፉድ ዓለም አቀፍ የግብርናና የግብርና ማምረቻ ቁሳቁሶች፣ የምግብና ምግብ ነክ ዕቃዎች እንዲሁም የማሸጊያ ቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን ዓርብ ኅዳር 23 ቀን 2009 ዓ.ም. በኤግዚቢሽን ማዕከል በተከፈተበት ወቅት ነው፡፡

በኤግዚቢሽኑ ላይ ከ60 በላይ የሚሆኑ ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ፣ ከቱርክ፣ ከኤንዶኔዥያ፣ ከቻይና፣ ከህንድና ከአፍሪካና ከሌሎችም አገሮች የመጡ የውጭ ኩባንያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉ የአገር ውስጥ ተቋማትም ተሳታፊ ናቸው፡፡

ኤግዚቢሽኑን ያዘጋጁት ኢትኤል አድቨርታይዚንግ፣ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽኖችና ኮንፈረንሶችን በማዘጋጀት ከሚታወቀው የቱርኩ ላዲን ኢንተርናሽናል ፌር ኤንድ ኮንግረስ ጋር በመተባበር ነው፡፡ የኢትኤል አድቨርታይዚንግ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሪት ሃይማኖት ተስፋዬ እንደምትለው፣ የኤግዚቢሽኑ ዋና ዓላማ በውጭ አገሮች ያሉ በግብርናና በግብርና ምርቶች ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ እንዲሠሩ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲፈጠርና የገበያ ትስስር እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ እስከ ሰኞ ኅዳር 26 ቀን የሚቆየውን ኤግዚቢሽኑን የከፈቱት በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ፋቲህ ኡሎይ ናቸው፡፡ 

Standard (Image)

የህልውና አደጋ ውስጥ የወደቀው የጂፒኤስ ቴክኖሎጂ

$
0
0

የተለያዩ የጭነትና ሌሎች የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ የትራንስፖርት ድርጅቶችና ግለሰቦች የተሽከርካሪዎቻቸውን ሥምሪትና እንቅስቃሴን ካሉበት ሆነው ለመከታተልና ለማወቅ ሲቸገሩ መቆየታቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ደረቅና ፈሳሽ ጭነቶችን የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች ከሚጓዙባቸው አካባቢዎች ሆነው ከኩባንያዎቻቸው ጋር ያደርጉ የነበረው ግንኙነትም የተገደበ ስለነበር ዘርፉ በኋላ ቀር አሠራር ተገድቦ እንዲቆይ አስገድዶታል፡፡ 

የተሽከርካዎቻቸው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? የት አካባቢ ይገኛሉ? ምን እያደረጉ ነው? የሚሉትን ዓይነት ጥያቄዎች ለመመለስ ሳይችሉ መቆየታቸው አገልግሎታቸው እንዲጓተት ብቻም ሳይሆን፣ ጭነቶች ላይ ሰርቆት እንዲፈጸም ምክንያት ሆኖም ቆይቷል፡፡ ካለፉት ስምንት ዓመታት ወዲህ ግን የተሽከርካሪዎቻቸውን ሥምሪት በቀላሉ ለማወቅ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች ሥራ ላይ መዋል ጀምረዋል፡፡ የቴክኖሎጂዎቹን ጠቀሜታ በመገንዘብ በርካታ ግለሰቦችና ኩባንያዎች ተሽከርካሪዎች ላይ በሚገጡ አቅጣጫ ጠቋሚ (ጂፒኤስ) አማካይነት እንቅስቃሴ ላይ የሚገኙ ተሽከርካሪዎቻቸውን ለመቆጣጠር ችለዋል፡፡

ቴክኖሎጂውን በየትኛውም ተሽከርካሪ ላይ ገጥሞ መገልገል የሚቻል ሲሆን፣ የጭነትና የፈሳሽ ተሽከርከሪዎች ብቻም ሳይሆኑ ሌሎችም እንደ አምቡላንስ ያሉ፣ የተጎዱ ተሽከርካሪዎችን የሚያነሱ መኪኖች ሳይቀሩ ጂፒኤስ ተገጥሞላቸው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ እየተለመደ በመምጣቱም አገልግሎቱን የሚሰጡ ኩባንያዎች እንዲጨምሩ አድርጓል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ ይህንን ዘመናዊ የትራንስፖርት መቆጣጠሪያ መሣሪያ በመግጠምና ከዚሁ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን በመሥራት ላይ የሚገኙ ኩባንያዎች ቁጥም ስምንት ደርሷል፡፡

በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ ይህንን አገልግሎት ለማስተዋወቅና ለማለማመድ ብዙ ደክመዋል፡፡ ጠቀሜታውን ለማሳየትና ወደ ገበያ ለመግባትም ውጣውረዶቹ ቀላል አልነበሩም፡፡ በርካታ ልፋት እንደገጠማቸው የሚያወሱት እነዚሁ ባለሙያዎች፣ አሁን ላይ ቴክኖሎጂው ተለምዶ ጥቅሙም ግንዛቤ ስለተያዘበት አገልግሎቱን የሚፈልጉ ኩባንያዎችና ግለሰቦች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡

ይሁንና አንድ አገራዊ ችግር የህልውና ጥያቄ አስነስቷል፡፡ የኔትወርክ መቋረጥ ለኩባንያዎቹ ፈተና ሆኗል፡፡ በጂፒኤስ የታገዘ የመኪና ሥምሪት አገልግሎት ለመስጠት የጂፒአርኤስ ሲም ካርድ (GPRS Network) መጠቀም የግድ ነው፡፡ ሲም ካርዱን ለዳታ አገልግሎት በማዋል በጂፒኤስ የመኪና ስምሪት ለመስጠት የሚያስችል እንስቃሴ እንዲያደርጉ ታስቦ መኪኖቹ ላይ ይገጠማል፡፡ ይህንን መሣሪያ ያስገጠመ ኩባንያ ተሽከርካሪዎችን የትም ቦታ ሆኖ በምባይል ስልክ አለያም በኮምፒውተር መቆጣጠር ይቻላል፡፡

ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው የሚባልለት ይህ ቴክኖሎጂ ጂፒኤስ የተገጠመለት አንድ  ተሽከርካሪ ከተፈለቀደለት ፍጥነት በላይ እንዳያሽከረክር፣ ተሽከርካሪም ፍጥነቱን እንዲመጥን የሚያሳስብ መረጃ ለማቀበል ያስችላል፡፡ ተሽከርካሪው ምን ያህል ነዳጅ እንደተጠቀመ፣ የት ቦታ እንደሚገኝ፣ እንቅስቃሴ ካቆመም ያቆመበትን አካባቢና ሌሎች መረጃዎችን አደራጅቶ የሚያቀብል ነው፡፡

የተሽከርካሪ ባለንብረቶችም እንዲህ ባሉት መረጃዎች ታግዘው የተሽከርካሪዎቹ የእንቅስቀቃሴ ሁኔታ ላይ ለመወሰን ያስችላቸዋል፡፡ የተጫነ ዕቃ በትክክል ለደንበኛው መድረስ አለመድረሱን ለማረጋገጥ ጭምር ቴክኖሎጂው የሚያግዝ በመሆኑ፣ የትራንስፖርት ድርጅቶቹን ሥራ ያቃለለ፣ ብክነትን ያስቀረና ወጪ በመቆጠብ እገዛ ያደረገ ቴክኖሎጂ እንደሆነ ሲነገርለት ቆይቷል፡፡ አገልግሎቱን እየተጠቀሙ ያሉ ኩባንያዎችና ግለሰቦች በቴክኖሎጂው ሳቢያ ውጤታማ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ይህን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ ድርጅቶችና ግለሰቦች በሺዎች የሚቆጠሩ ተሽከርካሪዎቻቸው ላይ አስገጥመዋል፡፡ ሥራቸውንም ከዚህ ቴክኖሎጂ ጋር አያይዘው እየመሩ ይገኛሉ፡፡ ይህንን ቴክኖሎጂ በመጠቀም አገልግሎት እየሰጡ ካሉት ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው የካሳ ሶፍትዌር ትራኪንግ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ካሳ እንደገለጹት፣ ቴክኖሎጂው በኢትዮጵያ ውስጥ መተግበሩ የአገሪቱን የትራንስፖርት ዘርፍ በማዘመን ረገድ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ ልማዳዊ ከሆነ አሠራር ወጥቶ ወደ ዘመናዊ አሠራር እንዲሸጋገር አስችሏል፡፡ እንደ ቀድሞው ጊዜ ለስምሪት የወጣውን ተሽከርካሪ ከሄደበት በደህና እስኪመለስ ስለደኅንነቱ መጨነቅን ያስቀራል፡፡ በዘርፉ ይስተዋሉ የነበሩ የነዳጅ ብክነቶችንና ስርቆቶችን ለማስቀረትም ይጠቅማል፡፡ እንደውም አንድ ሰሞን ‹‹ቅሸባ›› የሚባል ልዩ መጠሪያ ያተረፈ የጭነት ስርቆት ተስፋፍቶ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በቴክኖሎጂው አማካይነት እንዲቀንስ ማድረግ ስለመቻሉም ይነገራል፡፡

ይሁን እንጂ ባለፉት ሦስት ወራት ይህ አገለግሎት ተስተጓጉሏል፡፡ አገልግሎቱን የገዙ ኩባንያዎችም ተሽከርካሪዎቹን እንደ ቀድሞው ከየወጡበት የሥምሪት አካባቢ ለመቆጣጠር፣ የት እንዳሉና እንደዋሉ ወይም ምን እየሠሩ እንደሆነ ለማወቅ የሚያስችላቸው አገልግሎት ተቋርጧል፡፡ ኩባንያዎች ያስገጠሟቸው መሣሪያዎች አገልግሎት እየሰጡ ባለመሆኑ ተሽከርካዎቻቸውን ለመቆጣጠር አልቻሉም፡፡

ለአገልግሎቱ መቋረጥ ምክንያት የሆነው ደግሞ መንግሥት በወጣው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት መሣሪያዎች ዳታ የሚያስተላልፉበት ሲም ካርድ ሙሉ በሙሉ የጂፒአርኤስ ኔትወርክ ማግኘት ባለመቻሉ ነው፡፡ የጂፒኤስ መሣሪያዎች ሲም ካርዶችን ተጠቅመው ዳታ ማስተላለፍ የሚያስችላቸው አገልግሎት መስተጓጎሉ መሣሪያውን ያስገጠሙ ኩባንያዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ መሣሪያውን እየገጠሙ ያሉትንም ኩባንያዎች እንቅስቃሴ አስተጓጉሏል፡፡

ይህ ክስተት ኩባንያዎቹና ግለሰቦቹ ተሽከርካሪዎችን እንደ ቀድሞ ለመቆጣጠር ያላስቻለ ብቻ ሆኖ አልቆመም፡፡ አገልግሎቱ በመቋረጡ መሣሪያውን ባቀረቡት ኩባንያዎችና አገልግሎቱን በገዙት የትራንስፖርት ድርጅቶች መካከል ያለመግባባትን እየፈጠረ ስለመሆኑ አቶ ሰለሞን ይገልጻሉ፡፡ ችግሩ በአዋጁ ምክንያት ከጂፒአርኤስ ኔትወርክ መቋረጥ ጋር የተያያዘ ቢሆንም፣ ‹‹ደንበኞች ግን ችግሩ በእኛ ስህተት የተፈጠረ  አድርገው በመውሰድ ውላቸውን እስከማቋረጥ እየደረሱ ነው፤›› በማለት ስለሁኔታው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ችግሩ የእኛ አለመሆኑን በመግለጽ ደብዳቤ ጽፈን እንዲታገሱን እየጠየቅን ነው፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ሥራ ላይ ከተሰማራውና ፍሊት ማኔጅመንት ሲስተምስ ከተባለው ኩባንያ ያገኘነው መረጃም በተለይ በኦሮሚያ ክልል አብዛኛው አካባቢ አገልግሎቱ ተቋርጧል፡፡ በዚህም የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ መቆጣጠር አልተቻለም፡፡ አገልግሎቱ በመቋረጡ ምክንያት ኩባንያው የገጠመውኝ ችግር ለኢትዮ ቴሌኮም በማሳወቅ ምላሽ እየጠበቀ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

መሣሪያውን ለማስገጠም ኮንትራት የፈረሙ ሳይቀሩ ኔትወርኩ ባለመሥራቱ ምክንያት በውጭ ምንዛሪ ተገዝተው የገቡ መሣሪያዎች ሳይቀር ያለሥራ በመቀመጣቸውን የገለጹጽ አቶ ሰለሞን፣ በተሽከርካሪዎች ላይ ያስገጠሙት አዳዲስ ደንበኞችም ኔትወርኩ ባለመሥራቱ ለተገጠመው መሣሪያ ክፍያ ለመፈጸም ማንገራገራቸው ሥራቸውን እያበላሸባቸው እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

እንዲህ ባለው ሥራ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች የገጠማቸውን ችግር ለኢትዮ ቴሌኮምና ለመገናኛና ኢንፎርሜሽን ኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር በደብዳቤ ጭምር ቢያሳውቁም እስካሁን ድረስ አወንታዊ ምላሽ አለማግኘታቸውን አቶ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡ እስካሁን መፍትሔ የሚሰጥ ዕርምጃ ባለመገኘቱም ከደንበኞቻቸው ጋር እያራራቃቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ለዚህ አገልግሎት የሚውሉትና ከኢትዮ ቴሌኮም የሚገዙት ሲም ካርድ ለዳታ አገልግሎት ብቻ የሚውሉ በመሆኑ አገልግሎታቸው እንዳይቋረጥ ማድረግ ይቻል ነበር ይላሉ፡፡ አቶ ሰለሞን እንደሚሉት ኔትወርኩ እንዲለቀቅ ካልተደረገ በቀር ዘመናዊ የትራንስፖርት ሥምሪት ለመስጠት የተቋቋሙ ድርጀቶች ህልውና አደጋ ላይ መውደቁን አሳስበዋል፡፡

ለመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተጻፈው ደብዳቤ ካሰፈረው ውስጥ ‹‹የኔትወርኩ መቋረጥ ድርጅታችንን ለከፍተኛ ኪሳራ ዳርጓል፡፡ ሠራተኛ ለመበተን ተገደናል፡፡ በደንበኞች ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ተዓማኒነት አጥተናል፡፡ የድርጅታችንም ቀጣይ ህልውና አደጋ ላይ ወድቋል፤›› በማለት መፍትሔ እንዲሰጣቸው ኩባንያዎቹ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ‹‹ለምሳሌ እኔ ባለፉት ሦስት ወራት ለሠራተኞች ደመወዝ ከዚህም ከዚያ ብዬ ከፍያለሁ፡፡ የቤት ኪራይ ለመከፈል ግን እየከበደኝ ነው፡፡ ያሉንን ክፍያዎች ለመሰብሰብ ካለመቻላችን በላይ አዳዲስ ኮንትራት ቢኖረንም ሥራው ሳይኖር ክፍያ ማግኝት ስለተቸገርን መንግሥት ጉዳዩን ቢመለከተው፣›› በማለትም ስለሚገኙበት ሳሳቢ ሁኔታ በመጥቀስ ተማፅኖ የሚያቀርቡት አቶ ሰለሞን፣ ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት ከመቋረጡ ቀድሞ እንዳይቆም ለማድረግ የሚችልበት አማራጭ መንገድ መጠቀም ይችል እንደነበርም ገልጸዋል፡፡

ለወራት የዘለቀው ችግርን ግን እስካሁን አልተቀረፈም፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ያቋረጠውን አገልግሎት ለማስቀጠል ተስፋ መስጠቱን የሚጠቁሙ መረጃዎችም እየወጡ ነው፡፡ ከፍሊት ማኔጅመንት የተገኘው መረጃም ችግሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊፈታ እንደሚችል ኩባንያው ቃል ስለገባ ይህንኑ እንኪፈጽም በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ኩባንያው አስታውቋል፡፡ የኔትወርኩ መቆራረጥ ግን ኩባንያዎችንም ተገልጋዮችንም ጎድቷል፡፡

 

Standard (Image)

ለዘረ መል ጥጥ የታጩ ማሳዎች

$
0
0

በዓለም የግብርና ዘርፍ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ በግዙፉ የሚጠቀሰው የአረንጓዴው አብዮት እየተባለ የሚጠራው ወቅት ነው፡፡ በርካቶች ከረሃብና ቸነፈር ለመዳን የቻሉበትን የሳይንስ ውጤት የተገበረው ይህ አብዮት በግብርና መስክ አዳዲስ ክስተቶችን በማስተናገድም ይታወሳል፡፡

የአረንጓዴው አብዮት ተቋዳሽ ከነበሩ አገሮች መካከል በተለይ በደቡብ አሜሪካና በእስያ የሚገኙ አገሮች በርካታ ሕዝቦቻቸውን ከድርቅ አደጋ ለመታደግ በቅተዋል፡፡ ህንድና ሜክሲኮ በአረንጓዴው አብዮት ብዙ አትርፈዋል፡፡ ለሕዝባቸው የዕለት ቀለብ ለመስፈር ከመቻል ተርፈረው እህል ለመላክ የሚችሉበት አቅም እንዲያገኙ በሩን የከፈተው ይኸው አብዮት በብዙ ፈርጁ ሲወደስ ቆይቷል፡፡

የአረንጓዴው አብዮት አባት እየተባሉ የሚጠቀሱት አሜሪካዊው ምሁር ዶ/ር ኖርማን ቦርሎግም ለቴክኖሎጂው መስፋፋት በብዙ ስማቸው ይነሳል፡፡ ይዘከራል፡፡ ይህ አብዮት ለአብዮትነት እንዲፈረጅ ካበቁት መካከል በግብርናና በእርሻ ሥራዎች ላይ የሚተገበሩ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማስተዋወቁ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በልማድ ይሠራባቸው የነበሩትን ዘደዎች በመቀየር፣ በላቦራቶሩ የተሻሻሉ፣ ከፍተኛ ውጤት የሚሰጡ ልዩ ልዩ የሰበል ዝርያዎችን በማውጣት ለአምራቾች ማዳረስ አንዱ የአብዮቱ ተልዕኮ ነበር፡፡

የተዘራው ዘር አረም እንዳይወርሰው፣ ተባይ እንዳይጨርሰውም ፀረ አረምና ተባይ መከላከያዎችን መርጨት እየተዘወተረ የመጣው በአብዛኛው ከአረንጓዴው አብዮት በኋላ ነበር፡፡ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የዘረ መል ምህንድስናን (ጄኔቲካሊ ሞዲፋይድ ኦርጋኒዝምስ) በመተግበር ሲሠራበት ቆይቷል፡፡

ምንም አንኳ በበርካቶች አገሮች ዘንድ ተቀባይነት በማግኘት ውጤት ቢታይበትም የዚያኑ ያህል ሲተች ቆይቷል፡፡ አረንጓደው አብዮት የጥቅሙን ያህል ጉዳቱም በርካታ ነው ተብሎ ሲወገዝ ኖሯል፡፡ በርካታ ለም መሬቶች መዳበሪያ ከመለዱ በኋላ ያለማዳበሪያ ምርት አልሰጥ ብለዋል ከሚለው ጀምሮ፣ የአፈር አሲዳማነትን አምጥቷል፣ የከባቢ አየርን ጤንነት አዛብቷል፣ መርዛማ ኬሚካሎችን አበራክቷል ወዘተ. የሚሉ ውንጀላዎች ሲቀርቡበት ቆይቷል፡፡ 

ይህም ቢባል ግን እንደ ህንድ ባሉ አገሮች ውስጥ ከስድስት ሚሊዮን ያላነሰ ሕዝብ በረሃብ ከመርገፍ ታድጓል ብለው የሚሞግቱለት ባለሙያዎችም አሉ፡፡ ጠቀሜታው በርካታ ስለመሆኑ ከሚገልጹት መካከል የደቡባዊና ምስራቃዊ አፍሪካ የጋራ ንግድ ተቋም (ኮሜሳ) ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ጌታቸው በላይ አንዱ ናቸው፡፡

አረንጓዴው አብዮት በእስያም ሆነ በደቡብ አሜሪካ ያደረገውን አስተዋጽዖና ያስገኘውን ውጤት ያህል በአፍሪካ  ምንም ሊያስገኝ አልቻለም፣ በአፍሪካ ተሞክሮ ከሽፏል የሚለውን ስሞታ ዶ/ር ጌታቸው አይቀበሉትም እንደውም በተገላቢጦቹ ለቴክኖሎጂው አፍሪካ ዝግጁ አልነበረችም የሚል የመልስ ምት ያቀርባሉ፡፡

ይህ አብዮት በአፍሪካ ተሳካም አልተሳካ ከዓመታት በኋላ ሌላኛውን የቴክኖሎጂ ውጤት አስከትሏል፡፡ መነጋገሪያ ከሆነም ሁለት አሥርት አስቆጥሯል፡፡ ከአረንጓዴው አብዮት በባሰ ሁኔታ ክርክርና ንትርክ አስነስቷል፡፡ የዘረመል ምህንድስና፡፡

አፍሪካውያን ለዘረመል ምህንድስና ፊታቸውን ኡዙረው ቆይተዋል፡፡ እንደውም ጠበቅ ያሉ ሕጎችን በማውጣት ጭምር ቴክኖሎጂው እንዳሻው እንዳይስፋፋ ሲከላከሉ ቆይተዋል፡፡ ነገሮች ግን እንዲህ እንደሆኑ የሚቀጥሉ አይመስሉም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ እንዳለው ከሆነ ሕጎቻቸውን በማሻሻል የዘረ መል ምህንድስናን ለመቀበልና ለመተግበር የፈቀዱ አገሮች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል፡፡

በኢንዱስትሪ መስክ ለማደግ ካላቸው ፍላጎት በመነሳት በግብርና የሚፈልጓቸውን ጥሬ ዕቃዎችን በብዛትም በጥራትም እንደልብ ለማግኘት ከሚቻልባቸው ቴክኖሎጂዎች መካከል የዘረ መል ውጤቶች እንደሆኑ ማመን ከጀመሩ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ሆናለች፡፡ በዘረ መል ምህንድስና የተመረተ ጥጥ ለማልማት እንቅስቃሴ ጀምራለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ቢቲ ኮተን የተሰኘውን ዝርያ ከህንድ በመውሰድ ሙከራ ስታደረግ ቆይታ ለአምራቾች ለማሰራጨት ጫፍ መድረሷን ይፋ አድርጋለች፡፡ በቅርቡ እንደተዘገበው ከሆነም በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የዚህ ጥጥ ዝርያ ለገበያ መቅረብ ይጀምራል፡፡

የዘረ መል ጥጡን በሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ለማልማት እንደሚታሰብ ከመንግሥት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ዕቅድ መረዳት ተችሏል፡፡ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሚመራው የጥጥ ዘርፍ ልማት ስትራቴጂም ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡ አገሪቱ በጠቅላላው ከሰባት ሚሊዮን ሄክታር ያላነሰ ለጥጥ ተስማሚ መሬት እንዳላት ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

ለዘረ መል ጥጥ ምቹ የሆነው ሌላው አጋጣሚ መንግሥት እያስፋፋው የሚገኘው የኢንዱስትሪ ፓርኮ ግንባታ ነው፡፡ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለሚሠማሩ ጨርቃጨርቅና አልባሳት አምራቾች የሚውል የጥጥ ምርት እንደልብ ማምረትና ማቅረብ ግድ የሚልበት ጊዜ መሆኑን፣ ግብዓቱ ያለችግር ለፋብሪካዎች እንዲቀርብ ለማስቻልም ጥጥ አምራቾች የቢቲ ኮተን ዝርያ እንዲጠቀሙ የማድረግ ዕቅድ ተወጥኖ፣ የሙከራ ሥራውም ከላቦራቶሪ ወደ ማሳ ከገባ ሰነባብቷል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት፣ በአሁኑ ወቅትም የኢንዱስትሪ ዘርፍና የፋይናስና ዕቅዶች ውጤማነት ክትትልና ድጋፍ ዘርፍ አስተባባሪ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው የሚነገርላቸው ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ የዘረ መል ጥጥ በስፋት መመረት እንደሚጀምር በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡

የባዮቴክኖሎጂ ምሁራን የዘረ መል ምህንድስና ቴክኖሎጂ በአግባቡ ከተሠራበት ጥቅሙ እንደማያጠራጥር ይከራከራሉ፡፡ በተደጋጋሚ በቴክኖሎጂው ላይ የሚነሱት ዘመቻዎችም ትክክለኛ ሳይንስን መሠረት አድርገው እንደማይነሱ ይሞግታሉ፡፡ ይሁንና ተቃውሞቹ ግን አሁንም ድረስ ቀጥለዋል፡፡ እንደ ጀርመንና ፈረንሳይ ያሉ አገሮች የዘረ መል ምህንድስና ውጤቶች ወደ አገሮቻቸው እንዳይገቡ መከልከላቸው ተሰምቷል፡፡

ከአውሮፓውያኑ ባሻገርም ቡርኪናፋሶ በቅርቡ የዘረ መል ጥጥ ከአገሯ እንዲወጣ ትዕዛዝ ማስላለፏ ይታወቃል፡፡ ለዕርምጃው መንስዔ የሆነው ደግሞ አገሪቱ ከዘረ መል ጥጥ የምታገኘው የምርት ጥራት ደካማ ሆኖ በመገኘቱ ሲሆን፣ በዘረ መል ምህንድስና የተመረተ ጥጥ ያከሰራቸው ገበሬዎችም ዝርያውን ያቀረበላቸውን የአሜሪካውን ታዋቂ የዘረ መል ቴክኖሎጂዎች አቅራቢ ኩባንያ የሆነውን ሞንሳንቶ ላይ ክስ አቅርበዋል፡፡ ኩባንያው የ83 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍላቸውም ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ይህ ሁሉ ቴክኖሎጂው ጉዳት እንዳለው ማሳያ መሆኑን የሚከራከሩ ወገኖች በኢትዮጵያ ሊተገበር ስለታሰበው የጥጥ ዝርያም ስጋታቸውን ሲያስተጋቡ ቆይተዋል፡፡ ጉዳቱ በሳይንስ ተፈትሾ መረጋገጡን፣ በርካታ ጥቅም ያሳተሳሰራቸው የውጭ ኩባንያዎችና ተመራማሪዎች የሚያደርጉት ጫና እያየለ በመምጣት እንዲህ ያለውን ቴክኖሎጂ በግድ የመቀበል ያህል እያደረጉት መምጣጣቸውን ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡

የመልካ ማኅበር ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተርና የአካባቢ ጥበቃ አቀንቃኙ ዶ/ር ሚሊዮን በላይ፣ ቴክኖሎጂው ከሚሰጠው ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ አመዝኖ ስለመገኘቱ በርካታ አስረጂ ማሳያዎች እንዳሉ ይሞግታሉ፡፡

መንግሥት ግን ፀረ ዘረ መል አዋጁን ከማሻሻል ባሻገር ዝርያዎች ተሞክረው ወደ እርሻ ማሳያዎች እንዲገቡ ይሁንታውን ሰጥቷል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ፣ የባዮቴክሎጂ ዘርፍ ተመራመሪዎችና የምርምር ተቋማት ኃላፊዎች፣ ጥጥ አምራቾች የተወከሉበት የሰሞኑ የህንድ ጉበኝት ከኢትዮጵያ ባሻገር ኬንያውያንን፣ ዛምቢያውያንን፣ የስዋዚላንድ ተወካዮችንና የማሊ ሰዎችን ያካተተ ነበር፡፡

የአፍሪካውኑ ጉብኝት ህንድ የምታመርታቸውን የዘረ መል ጥጥ ዝርያዎችን፣ የእርሻ ማሳዎችን፣ በዚህ ቴክኖሎጂ ላይ የሚመራመሩ የምርምር ተቋማትን ያስጎበኘ ነበር፡፡ ህንድ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ገበሬዎችን በዘረ መል ጥጥ አምራችነት ዘሰማርታለች፡፡11 ሚሊዮን ሄክታር መሬትም በዚህ የጥጥ ዝርያ ሸፍናለች፡፡ ከ95 ከመቶ በላይ የህንድን የጥጥ እርሻዎች የሞላውም ሞንሳንቶ ማሂኮ ከተባለው የህንድ ኩባንያ ጋር የሚያቀርበው ቦልጋርድ-II የተባለውና በላቦራቶሪ ምህንድስና የተሠራው ጥጥ ነው፡፡ ይህ ጥጥ ግን በቡርካና ፋሶ ገበሬዎችን ለኪሳራ መዳረጉ የተነገረለት ነው፡፡

ይህም ቢባል ህንድ በጥጥ ምርት ራሷን ችላ፣ ትርፍ አምራች ሆና ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሯን አስታውቃለች፡፡ ላለፉት 15 ዓመታት ስታመርተው በመቆየቷ ይህ ነው የሚባል ችግር እንዳልገጠማት ትገልጻለች፡፡ ይሁንና ግን በርካታ ፀረ ቢቲ ኮተን ዘመቻዎች በህንድ ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡ ገበሬዎች ራሳቸውን ለማጥፋት ተገደዋል፤ ጥጡ በቀላሉ ይቋቋመዋል ተብሎ የሚነገርለትንና እንዲቀንስ እያስቻለው ነው የተባለለትን ቦልዎርም የተባለውን የጥጥ ተባይ በቶሎ ተላምዷል የሚሉ ቅሬታዎች በህንድ ሲስተጋቡ ቆይተዋል፡፡

የቴክኖሎጂው ደጋፊዎች ግን ሁሉንም በሳይንስ አረጋግጠን አብዛኛውን ተቃዋሚ በውጤቱ አሳምነናል በማለት ላይ ናቸው፡፡ የደቡብ እስያ የባዮቴክኖሎጂ ማዕከል መሥራችና ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ባጊራት ኮዳህሪ ለሪፖርተር እንደገለጹት ከሆነ አፍሪካ ከህንድ ጋር ተመሳሳይ የአየር ጠባይ ያላት፣ በትሮፒክ ዞን ውስጥ የምትገኝ በመሆኑ በህንድ የሚሠራውና ውጤታማ የሆነው ነገር በአፍሪካም ውጤታማነት እንሚያሳይ ያምናሉ፡፡

ስለዚህም የህንድን ተሞክሮ ውሰዱ፣ ከታች ጀምራችሁ ከማጥናት ይልቅ በተጠናው ላይ ተመስርታችሁ ወደ ሥራ ግቡ የሚል ምክር ለግሰዋል፡፡ በዚህ አባባል ዶ/ር ጌታቸውም ይስማማሉ፡፡ ዶ/ር ሚሊዮንና መሰሎቻቸው ግን ይህን አይቀበሉትም፡፡ በአንዱ አገር ያለው የሥነ ምህዳር ብዜተ ሀብት፣ ልዩልዩነት፣ የአፈር ጠባይ፣ የሰብል ዓይነትና ሌላውም ሲታይ እንዲህ ያለው አመለካከት ፈጽሞ ተቀባይነት እንደማይኖረው ይሞግታሉ፡፡

በዚህም ተባለ በዚያ መንግሥት የጥጥ ቴክኖሎጂን በዘረ መል በመመሥረት ከፍተኛ ምርት የማግኘት ህልሙን ለመተግበር ከጫፍ ደርሷል፡፡ አምራቾች እስከተቀበሉት ድረስ ቴክኖሎጂው ወደ እርሻ ማሳዎች ለመግባት የሚችልበት ቀነ ቀጠሮ ተቆርጦለታል፡፡

 

Standard (Image)

ከሁለት እጥፍ በላይ የትርፍ ዕድገት ያስመዘገበው ደቡብ ግሎባል ባንክ ካፒታል የማሳደግ ፈተና ይጠብቀዋል

$
0
0

ከ16ቱ የአገሪቱ የግል ባንኮች ኢንዱስትሪውን በመቀላቀል ከመጨረሻዎቹ የግል ባንኮች ሁለተኛው በመሆን ወደ ሥራ የገባው ደቡብ ግሎባል ባንክ አምስተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ቅዳሜ ኅዳር 24 ቀን 2009 ዓ.ም. የላቀ አስተዋጽኦ አደረጉ ላላቸው የባንኩ ደንበኞች ዕውቅና ለመስጠት ባዘጋጀው ‹‹የደንበኞች ቀን›› ፕሮግራም ወቅት የባንኩ ኃላፊዎች እንደገለጹት፣ ባንኩ በአራት ዓመታት ቆይታው ዕድገት እያሳየ መምጣቱን ነው፡፡

ደቡብ ግሎባል በ2008 በጀት ዓመት ያስመዘገበው ውጤት ባለፉት ሦስት ዓመታት ከተገኘው የበለጠ ስለመሆኑ የገለጹት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ሃዲሱ ሃባ፣ ባንኩ በበጀት ዓመቱ በተለይ ከታክስ በፊት ያገኘው ትርፍ የ200 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ በ2008 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት 68 ሚሊዮን ብር ማትረፍ መቻሉ በቀደመው በጀት ዓመት አስመዝግቦት ከነበረው 22.6 ሚሊዮን ብር አኳያ የዘንድሮ ትርፉ ከሁለት እጥፍ በላይ ዕድገት የታየበት ነው፡፡ ይህ የትርፍ ዕድገት በኢንዱስትሪው ውስጥ ከተመዘገበው አንፃር ከፍተኛው ዕድገት ቢሆንም የባንኩ ዓመታዊ ትርፍ ከብዛት አኳያ ከሌሎች ባንኮች አንፃር ሲታይ ግን አነስተኛ መጠን ያለው ነው፡፡ የባንኩ ኃላፊዎች ግን የትርፍ መጠኑ ቢያንስም ከፍተኛ ዕድገት አሳይተናል ይላሉ፡፡ ከባንክ አገልግሎቶች አኳያ ደቡብ ግሎባል ባንክ ካለፉት ዓመት የተሻለ ዕድገት ማሳየቱን የሚያመለክተው የፕሬዚዳንቱ ንግግር፣ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን በ6.4 በመቶ በማሳደግ በ2008 በጀት ዓመት 871.8 ሚሊዮን ብር እንደደረሰ ያትታል፡፡ በባንኩ የደንበኝነት መዝገብ ውስጥ የሰፈሩና ሒሳብ የከፈቱ ደንበኞች ቁጥርም በ44.4 በመቶ ማሳደጉ የባንኩን ተደራሽነት መጨመር ያሳያል ተብሏል፡፡ አጠቃላይ የባንኩ ሀብት በ13 በመቶ በማደግ 1.3 ቢሊዮን ብር ማድረስ መቻሉን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ በ2008 በጀት ዓመት ባንኩ የሰጠው የብድር መጠን በ76.8 በመቶ በማደግ 599.3 ማስመዝገቡ የባንኩን ጤናማ ጉዞ አመላካች እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ የባንኩ ጠቅላላ ገቢ 194.1 ሚሊዮን ብር ነበር ተብሏል፡፡

ባንኩ በኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን የገበያ ድርሻ ለማሳደግ የአምስት ዓመታት ስትራቴጂክ ዕቅድ በማውጣት እየሠራ መሆኑን የገለጹት የባንኩ የዕቅድና ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ብሩ፣ ባንኩ ገና ታዳጊ ቢሆንም ባለፉት አራት ዓመታት ጉዞው ውጤታማ ነበር ይላሉ፡፡ ለዚህ ማሳያ ብለው ያስቀመጡት የባንኩን የአራት ዓመታት ትርፍና ኪሳራ የሚያሳየውን አኃዛዊ መረጃ በመጥቀስ ነው፡፡  

ባንኩ ወደ ሥራ በገባበት በ2005 ዓ.ም. የመጀመሪያው ዓመት አፈጻጸሙ 14.3 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ማስመዝገቡን የሒሳብ ሪፖርቱ አሰናድቷል፡፡ ይሁን እንጂ ከመጀመሪያው ዓመት በኋላ ከኪሳራ ወጥቶ በ2006 ዓ.ም. 18.5 ሚሊዮን ብር፣ በ2007 ደግሞ 22.6 ሚሊዮን ብር በማትረፍ በአሁኑ ወቅት 68 ሚሊዮን ብር ሊደርስ መቻሉ የባንኩን የዕድገት ጉዞ ያሳያል ብለዋል፡፡ በደንበኞች ቀን ፕሮግራም ላይ የባንኩ ኃላፊዎች በሁሉም የባንክ አገልግሎት ዘርፎች ዕድገት መኖሩን ተናግረው፣ በ2008 በጀት ዓመት የተከፈለ ካፒታሉ በ32.3 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየም ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ባንኩ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት የተከፈለ ካፒታሉን 500 ሚሊዮን ብር ለማድረስ 138 ሚሊዮን ብር ማስመዝገብ ይጠበቅበታል፡፡

የባንኩን ካፒታል በሚፈለገው መጠን ማሳደግ ባለመቻሉ በብሔራዊ ባንክ ሕግ መሠረት የተከፈለ ካፒታሉን ግማሽ ቢሊዮን ብር ማድረስ ያልቻለ ብቸኛው ባንክ እንዲሆን አስገድዶታል፡፡ የብሔራዊ ባንክ መመርያ በሚያዘው መሠረት፣ ለካፒታል ማሳደጊያ የተሰጠው የጊዜ ገደብ የሚጠናቀቀው በዚህ ዓመት ነሐሴ ወር ላይ በመሆኑ ባንኩ በቀሩት ወራቶች ቀዳሚ ሥራ አድርጎ የሚወስደው የተከፈለ ካፒታሉን 500 ሚሊዮን ብር ለማድረስ ነው፡፡ በባንኩ በደንበኞች ቀን ፕሮግራም ላይ የተገኙት የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኑረዲን አወል፣ ባንኩ እያገኘ ያለው ውጤት አበረታች ቢሆንም ካፒታሉን በማሳደጉ ረገድ የታየውን ክፍተት ለመድፈንና ቀሪውን የተከፈለ ካፒታል መጠን የሞት ሽረት ጉዳይ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ካፒታሉን ማሟላት ግዴታ በመሆኑም ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡ እስከ መጪው ነሐሴ ወር ይህንን ያህል ካፒታል መሙላት ፈታኝ ሊሆን ይችላል የሚል ሥጋት በባለአክሲዮኖች ዘንድ ቢኖርም፣ የባንኩ ኃላፊዎችን ግን ግማሽ ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል እንደሚመዘገብ ያምናሉ፡፡

በዕለቱ ከባለአክሲዮኖች እንደተገለጸው ባንኩ ካፒታል በማሰባሰብ ላይ ክፍተት ያለበት በመሆኑ የተቀመጠው የጊዜ ገደቡ ከመድረሱ በፊት ይህንን ማሟላት ይቻላል ወይ የሚለው ጉዳይ አሳስቧቸዋል፡፡

ስለዚህ ባንኩ ያተረፈውን ትርፍ ለካፒታል ማሳደጊያ እንዲውል ከማድረግ ባሻገር ባለአክሲዮኖች የአክሲዮን ድርሻቸውን ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸው አስተያየት ተሰጥቷል፡፡ የባንኩ ዋነኛ ሥራ መሆን ያለበት ካፒታሉን ማሳደግ እንደሆነ ያሳሰቡት ባለአክሲዮኖች፣ በዕለቱ የነበራቸውን አክሲዮን በእጥፍ ለማሳደግ ቃል ሲገቡ ታይተዋል፡፡

የባንኩ የግብይት ዘርፍ ኃላፊም የተከፈለ ካፒታሉን የጊዜ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት ለማሟላት የተለያዩ ስትራቴጂዎች መቀረጻቸውን አስታውሰው፣ ለዚህም የባንኩ ደንበኞች ባለአክሲዮኖች አዳዲስ አክሲዮን እንዲገዙ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

የባንኩ ባለአክሲዮኖች በባንኩ አክሲዮን ተጨማሪ አክሲዮኖችን ከመግዛት ጀምሮ አዳዲስ ባለአክሲዮኖችን በማምጣት የባንኩን ዕቅድ እንደሚያሳኩ ገልጸዋል፡፡ አቶ አዲሱም የባንኩን ካፒታል 500 ሚሊዮን ብር ለማድረስና በስትራቴጂክ ዕቅዱ መሠረት በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ውስጥም ካፒታሉን ሁለት ቢሊዮን ብር ለማድረስ ከባንኩ ደንበኞች ብዙ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ 

Standard (Image)

ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ከወለድ አልባ አገልግሎት 1.25 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ሰበሰበ

$
0
0

ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ ዕድገት ማሳየቱንና ከዚህ ዘርፍ ተጠቃሚዎች ያሰባሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 1.25 ቢሊዮን ብር መድረሱን ይፋ አደረገ፡፡

ባንኩ የ2008 በጀት ዓመት የሒሳብ ሪፖርቱን ቅዳሜ፣ ኅዳር 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ይፋ ሲያደርግ እንደገለጸው፣ የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎቱ ከወትሮው በተሻለ እያደገ መምጣቱንና በ2008 መጨረሻ ላይ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥርም 97,530 መድረሱን ገልጿል፡፡ በ2007 ዓ.ም. 55,960 የወለድ አልባ አገልግሎት ተጠቃሚዎች እንደነበሩም አስታውሷል፡፡ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እንዲተገበር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣውን መመርያ መሠረት በማድረግ ከሌሎች ባንኮች ቀድሞ አገልግሎቱን በመጀመር የሚጠቀሰው ኦሮሚያ ባንክ፣ በ2008 በጀት ዓመት ከወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ብቻ ያሰባሰበው ተቀማጭ ገንዘብ በ43 በመቶ እንዳደገ ጠቅሷል፡፡ በ2007 በጀት ዓመት 873.7 ሚሊዮን ብር ከወለድ አልባ አስቀማጮች የተሰባሰበው ተቀማጭ ገንዘብ በ2008 መጨረሻ ላይ 1.25 ቢሊዮን ብር በመድረሱ በዚህ ዘርፍ ከፍተኛ የሚባል ዕድገት መመዝገቡን ያሳያል ተብሏል፡፡

ይህም ከጠቅላላው የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ ከወለድ አልባ ብቻ የተሰባሰበው መጠን 13 በመቶውን እንደሚይዝ ባንኩ አስታውቋል፡፡

ወለድ ከማይታሰብበት ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ 716 ሚሊዮን ብር ዋዲህ፣ 378 ሚሊዮን ብር ደግሞ አማና ተብለው በሚታወቁት የአገልግሎት ዘርፎች አማካይነት በባንኩ የተቀመጠ ገንዘብ ነው፡፡

ከወለድ ነፃ ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ ሥራ ላይ ለማዋል በተደረገው እንቅስቃሴም በወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት አሠራር መሠረት 509 ሚሊዮን ብር ለተለያዩ ቢዝነሶች በብድር ተለቋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ሙረሃባ በተባለው የወለድ አልባ አሠራር መሠረት ፋይናንስ የተደረገበት ብልጫውን የያዘ ሲሆን፣ በሙረሃባ ለአገር ውስጥ ንግድ ፋይናንስ የተደረገው የገንዘብ መጠንም 123 ሚሊዮን ብር እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከዚህም ሌላ በወለድ አልባ አገልግሎት በኩል 23.9 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱንና በዚሁ የአገልግሎት ዘርፍ 57 ሚሊዮን ብር ገቢ እንደተሰበሰበም የባንኩ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ ይህ አገልግሎት አዲስ ቢሆንም ከጅምሩ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ባንኩ ገልጿል፡፡ ከመደበኛው የባንክ አገልግሎት በተለየ ራሱን ችሎ የሚሠራበት ይህ ዘርፍ ፋይናንስ የሚደረግበት መንገድም እንደመደበኛው አገልግሎት ወለድ የሚጠይቅበት ሳይሆን፣ አዋጭ የሆኑ የንግድ መስኮች እየተመረጡ ለአገልግሎቱ በተፈቀዱ አሠራሮች መሠረት ያለ ወለድ ገንዘብ በብድር የሚሰጥባቸውን መንገዶች ይከተላል፡፡

የባንኩን የ2008 በጀት ዓመት አጠቃላይ እንቅስቃሴ በተመለከተ በቀረበው ሪፖርትም ከአጠቃላይ የባንኩ አገልግሎት ከታክስ በፊት 325 ሚሊዮን ብር ትርፍ ተመዝግቧል፡፡ በቀደመው ዓመት ከታክስ በፊት 293.9 ሚሊዮን ብር እንዳተረፈ ይታወሳል፡፡ የ2008 የተመዘገበው የተጣራ ትርፉም 248.3 ሚሊዮን ብር እንደሆነ የሚያመለክተው የባንኩ ሪፖርት፣ ከቀዳሚው ዓመት በ12 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ነው፡፡

የባንኩ አጠቃላይ ሀብትም በቀደመው በጀት ዓመት ከነበረበት 9.53 ቢሊዮን ብር በ18 በመቶ ጨምሮ 11.9 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑም (በወለድ አልባ አገልግሎት የተሰበሰበውን ጨምሮ) 17 በመቶ በማደግ 9.3 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በ2008 ዓ.ም. የሰጠው የብድር መጠን በ2007 በጀት ዓመት ከነበረው አምስት ቢሊዮን ብር ጭማሪ አሳይቶ በ2008 መጨረሻ ላይ 5.7 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ ባንኩ አስታውቋል፡፡ ይህ የብድር መጠንም በወለድ አልባ የባንክ አገልግሎቱ ፋይናንስ የተደረገውንም ያጠቃልላል፡፡

በ2008 በጀት ዓመት የተመዘገበው የገቢ መጠን ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ቢሊዮን ብር መድረሱን የባንኩ ሪፖርት ያሳያል፡፡ በቀደመው ዓመት 849.5 ሚሊዮን ብር እንደነበር የሚያስታውሰው የባንኩ ሪፖርት፣ በ2008 በጀት ዓመት ግን በ37 በመቶ አድጎ 1.2 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይሁን እንጂ የባንኩ ዓመታዊ ወጪ በ51 በመቶ ጨምሯል፡፡ በበጀት ዓመቱ ባንኩ በጠቅላላው 838.5 ሚሊዮን ብር ወጪ አድጓል፡፡ ይህ ወጪ ከቀደመው በጀት ዓመት አኳያ በንፅፅር ሲቀመጥም ከ283 ሚሊዮን ብር በላይ ጨምሯል፡፡

በውጭ ምንዛሪ ግኝት በኩል ባንኩ ከካቻምናው ያነሰ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ ባንኩ በ2007 በጀት ዓመት 225 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቶ የነበረ ሲሆን፣ በ2008 በጀት ዓመት ያገኘው የውጭ ምንዛሪ ግን 223 ሚሊዮን ዶላር ሆኗል፡፡ ይህ ክፍተት በተለይ ከወጪ ንግድ ገቢ መቀዛቀዝ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በአሁኑ ወቅት 200 ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፣ 1.4 ቢሊዮን ብር ካፒታል አስመዝግቧል፡፡

Standard (Image)

አዲስ ባንክ 112 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ

$
0
0

ከሌሎች የግል ባንኮች በተለየ አደረጃጀት የተለያዩ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን፣ የብድርና ቁጠባ ተቋማትን፣ ከ170 በላይ ዕድሮችንና የመሳሰሉትን ተቋማት በአክሲዮን ባለቤትነት ያቀፈው አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ በ2008 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት 112.8 ሚሊዮን ብር ማትረፉን ገለጸ፡፡

ባንኩ ቅዳሜ፣ ኅዳር 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ከታክስ በኋላ 85.4 ሚሊዮን ብር ማግኘቱንና ለመጠባበቂያ የሚያዘው ተቀናሽ ተሰልቶ የተጣራ ትርፉ 64 ሚሊዮን ብር መድረሱን አስታውቋል፡፡ የተጣራ ትርፉ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ45.5 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡

የተመዘገበው ትርፍ በአክሲዮን የትርፍ ድርሻ መጠን ሲሰላ በአንድ አክሲዮን የሚደርሰው የትርፍ መጠን ጭማሪ ካሳዩ ጥቂት ባንኮች መካከል አንዱ አድርጎታል፡፡ ከዚህ አኳያ እያንዳንዱ አክሲዮን ያስገኘው ትርፍ 193 ብር  ወይም 19.3 በመቶ ሆኗል፡፡ በቀደመው ዓመት የአንድ አክሲዮን የትርፍ ድርሻ 187 ብር ወይም 18.7 በመቶ ነበር፡፡ በሌሎች የባንክ አገልግሎቶች የተገኘውን ውጤት የሚያሳየው የባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት፣ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ በ2008 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ 1.7 ቢሊዮን ብር መድረሱን ነው፡፡ የባንኩ አስቀማጮች ቁጥርም በ45.6 በመቶ ዕድገት አሳይቶ 39,945 እንደደረሰ ጠቅሷል፡፡

አስቀማጮችን ለመሳብ በባንኮች መካከል ያለው ውድድር ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር ባንኩ ሊጠቀስ የሚችል ሥራ ቢሠራም፣ ካለው የብድር ፍላጎት አኳያ ሲታይ ግን ተጨማሪ ተቀማጭ ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራ መሥራት እንደሚገባው የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኃይለመለኮት ተክለጊዮርጊስ ባቀረቡት ሪፖርት ጠቅሰዋል፡፡

ባንኩ ለደንበኞች ያቀረበው የብድር መጠን በ37.5 በመቶ እንዳደገ የባንኩ ሪፖርት ጠቅሶ፣ በ2008 መጨረሻ ላይ የሰጠው የብድር መጠን 1.1 ቢሊዮን ብር ማስመዝገቡን አመላክቷል፡፡

ባለፈው በጀት ዓመት ባንኩ በዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ በጠቅላላው 69.3 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ችሏል፡፡ የተገኘው ገቢ ከአጠቃላይ የባንኩ ገቢ ውስጥ 23.5 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡ የተገኘው ገቢ አበረታች ቢሆንም በአጠቃላይ በኢንዱስትሪው የተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ተፅዕኖ እንዳሳደረበት የባንኩ ሪፖርት ሳይጠቅስ አላለፈም፡፡

የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 2.5 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ46.6 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ በዓመቱ መጨረሻ የባንኩ አጠቃላይ ካፒታል (የተከፈለ ካፒታል፣ መጠባበቂያና ያልተከፋፈለ ትርፍ ታክሎበት) 636.5 ሚሊዮን ብር ማስመዝገቡን የሚያሳየው ሪፖርት፣ ይህም ባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 445.1 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ43 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡

ከባንኩ አጠቃላይ ካፒታል ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የተከፈለ ካፒታል ነው፡፡ 516.4 ሚሊዮን ብር በማስመዝገብ ካለፈው ዓመት አኳያ የ41 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡ በተጓዳኝ የባንኩ የባለአክሲዮኖች ቁጥርም በዓመቱ የ16 በመቶ ዕድገት በማሳየት 8,370 ደርሷል፡፡  

በ2008 ዓ.ም. ባንኩ በጠቅላላው 294.8 ሚሊዮን ብር ገቢ አግኝቷል፡፡ ባለፈው ዓመት ከነበረው የገቢ መጠን ጋር ሲነፃፀር 42.1 በመቶ ዕድገት የታየበት እንደሆነም አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ ይፋ አድርጓል፡፡ በበጀት ዓመቱ የሥራ አፈጻጸም ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ የነበረው ድርቅ ያስከተለው ተፅዕኖ፣ በባንኮች መካከል የነበረው ከፍተኛ ፉክክርና የውጭ ምንዛሪ ዕጥረትም ፈታኝ ክስተቶች እንደነበሩ ባንኩ ገልጿል፡፡

 

Standard (Image)

ከተሽከርካሪ የሚመነጭ በካይ ጋዝን ለመቀነስ የሚረዳ አዲስ ቴክኖሎጂ ቀረበ

$
0
0

 

ከተሽከርካሪዎች የሚወጣውን የበካይ ጋዝ ልቀት በ80 በመቶ መቀነስ ይችላል የተባለና ጣልያን ሠራሽ ‹‹ሱፐርቴክ›› የተባለ ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ ሊውል ነው፡፡ ቴክኖሎጂው የበካይ ጋዝ ልቀትን በመቀነስ፣ ብክለትን ከመቆጣጠር ባሻገር እስከ 12 በመቶ የነዳጅ ፍጆታን እንደሚቀንስ ተነግሮታል፡፡ ለአውቶሞቢሎች፣ ለሚሳብ ተሽከርካሪዎች፣ ለጭነት፣ ለአውቶብሶችና ለረዣዥም ተሽከርካሪዎች እንዲሁም በነዳጅ ለሚሠሩ ጀነሬተሮች የሚያገለግል ሲሆን፣ የገበያ ዋጋውም ከ25 እስከ 100 ዩሮ እንደሆነ ታውቋል፡፡ በ30 አገሮች ውስጥ የሚሰጠው አገልግሎት ሱፐርቴክ ቴክኖሎጂን የሚያስመጣው ኢዙኬም ትሬዲንግ የተባለ አገር በቀል ኩባንያ ነው፡፡

በመኪና የነዳጅ መያዣ ቋት (ሳልቫቲዮ) ውስጥ የሚገጠመው ይህ ቴክኖሎጂ፣ ጭስ ማውጫን የማፅዳት ባህሪይ እንዳለው፣ የካርቦን ዝቃጭን እንደሚቀነስ፣ ለሞተር የበለጠ ዕድሜን በመስጠት በየጊዜው የሚደረግን ጥገና እንደሚቀንስ ስለቴክኖሎጂው ገለጻ የሰጡት አቶ ዮሐንስ ወልደገብርኤል አስረድተዋል፡፡

የኩባንው ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ አብዱላዚዝ ከማል፣ ቴክኖሎጂው በተለያዩ የዓለም ክፍሎችና በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ጥቅም ላይ መዋሉን ተናግረዋል፡፡ ቴክኖሎጂውን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ጣልያን አገር ከሚገኘው የምርቱ ባለቤት ኩባንያ ጋር በተናጠል መፈራረማቸውን፣ የገበያ ሽፋኑንም በምሥራቅ አፍሪካ በሚገኙ አገሮች ሁሉ ተደራሽ የማድረግ ዕቅድ መነደፉን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በነዳጅ ለሚሠሩ ጀነሬተሮች ቴክኖሎጂው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሥራ ላይ እንደሚውል ገልጸው፣ ‹‹ቴክኖሎጂውን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ከባንኮች የውጭ ምንዛሪ ጠይቀናል፡፡ ገንዘቡ እጃችን ሲገባ ወደ አገር ውስጥ የማስገባቱን ሥራ እንጀምራለን፡፡ ከቀረጥ ነፃ እንድናስገባ ለመንግሥት ጥያቄ አቅርበናል፤›› ብለዋል፡፡ አቶ አብዱላዚዝ ይህንን የተናገሩት፣ እሑድ ኅዳር 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በመንገድና ትራንስፖርት ባለሥልጣን ጽሕፈት ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ነበር፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲህ ያሉ ቴክኖሎጂዎች ብቅ እያሉ ሲሆን ከዚህ ቀደም የጃፓን ሥሪት ቴክኖሎጂ  በአሁኑ ወቅት በዓለም ትልቅ መነጋገሪያ የሆነውን የበካይ ጋዞች ልቀትን ለመቆጣጠር ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ ከፍተኛ የሆነው የበካይ ጋዝ ልቀት በኢንዱስትሪ ከበለፀጉት አገሮች የሚለቀቅ ሲሆን፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉት ታዳጊ አገሮች የሚለቀቀው የበካይ ጋዝ መጠን ከሌሎቹ አንፃር ሲታይ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ የበካይ ጋዝ ምንጭ ከሆኑት መካከል ትራንስፖርት አንዱ ነው፡፡ በአገሪቱ 30 በመቶ የሚሆነው የበካይ ጋዝ ልቀት ከተሽከርካሪዎች የሚወጣ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2012 የወጣ ሪፖርት እንደሚያሳየው አዲስ አበባ ከተማ 4.8 ሚሊዮን ቶን ካርቦንዳይኦክሳድ ጋዝ ወደ ከባቢ አየር ትለቃለች፡፡ ከዚህ ውስጥ 47 ከመቶ ከተሽከርካሪዎች የሚለቀቅ ነው፡፡ ካለው የሕዝብ ብዛት አኳያ በአገሪቱ ያለው የተሽከርካሪ ቁጥር በእጅጉ አናሳ ነው፡፡

ከ90 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በሚኖርበት አገር ውስጥ የተሽርካሪዎች ብዛት 708,000 ብቻ ነው፡፡ ይህንን ያህል ተሽከርካሪ ባለበት ሁኔታ ከተሽከርካሪዎች የሚለቀቀው የበካይ ጋዝ መጠን ከሚጠበቀው በላይ መሆኑ በአብዛኛው በዕድሜ የገፉና ያረጁ ተሽከርካሪዎች በብዛት መኖራቸው አንዱ መንስዔ ሲሆን፣ የሚነጨው በካይ ጋዝ መጠንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ አሳሳቢ ሆኗል፡፡

ይህም ሆኖ በአገሪቱ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ የጥናት ሰነድ መሠረት ከፍተኛውን የበካይ ጋዝ የሚያመነጩት የግብርናና የደን ምንጣሮ ተግባራት ናቸው፡፡

 

Standard (Image)

ንግድ ሚኒስቴር የንግድ ምክር ቤቶች የምርጫ ሕጋዊነት እንዲረጋገጥ አሳሰበ

$
0
0

ንግድ ሚኒስቴር የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ያካሄዷቸው ምርጫዎች ሕጉን ተከትለው የተካሄዱ መሆናቸው እንዲረጋገጥና የዘገየውም የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር  ቤት ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫም በዚሁ መሠረት እንዲካሄድ አሳሰበ፡፡

      በሚኒስቴሩ የንግድና የአክሲዮኖች ዘርፍ ማኅበራት ጉዳዮች ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በአቶ ኑረዲን መሐመድ ተጽፎ የወጣው ደብዳቤ፣ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና በተዋረድ የሚገኙ ምክር ቤቶች ሕጉን ተከትለው ምርጫ ማከናወናቸውን በቅድሚያ የማረጋገጥ ሥራ ከተሠራ በኋላ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ምርጫና ጉባዔ እንዲካሄድ ጠይቋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በተለያዩ ምክንያቶች መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በማካሄድ ፕሬዚዳንትና የቦርድ አመራር አባላት ምርጫ ያላካሄደ መሆኑ ይታወቃል፤›› በማለት የሚጀምረው ይኸው ደብዳቤ፣ የምርጫ አሠራርና ደንብን ያልተከተሉ የአሳታፊነት ጉድለት የሚስተዋልባቸው ምርጫዎች በየደረጃው ተከናውነዋል ሲል ከዚህ ቀደም የቀረቡ አቤቱታዎችን ዋቢ አድርጓል፡፡

‹‹በተለይም ክልሎችና የከተማ አስተዳድሮች እንዲሁም ሌሎች አባል ምክር ቤቶች ምርጫ ሳያካሂዱ ወደ ቀጣዩ እርከን ነባር አመራር ይዘው የሚቀርቡባቸው ምርጫዎች እየተከናወኑ ነው በማለት የተለያዩ ቅሬታዎችና አቤቱታዎች እየቀረቡ ይገኛሉ፤›› በማለት የሚጠቅሰው የሚኒስቴሩ ደብዳቤ፣ ለቅሬታዎቹ አስፈላጊው መፍትሔ እንዲሰጣቸው በማለት ምክር ቤቶችን ጠይቋል፡፡

በንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 341/1995 እንዲሁም ከምክር ቤቱ መተዳደሪያ ውጭ ከሁለት ጊዜ በላይ የተመረጡ የቦርድ አመራር አባላት አሉ ተብሎ የቀረበው ቅሬታና አቤቱታም አስፈላጊ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ በማሰባሰብ ጉዳዩ እንዲጣራ ንግድ ሚኒስቴር ጽፏል፡፡

ሁሉም አባል ንግድና ምክር ቤቶች በአዋጁና በመተዳደሪያ ደንባቸው መሠረት በየደረጃቸው በሕጋዊ መንገድ ምርጫ ያላከናወኑ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ሌሎች አባል የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ሕጉን ተከትለው ግልጽ፣ ፍትሐዊና አሳታፊ ምርጫ ስለማከናወናቸው የማረጋገጥ ሥራ እንዲሠራም አሳስቧል፡፡

የማጣራቱ ሥራ በየክልሉ ንግድ ቢሮዎች ድጋፍ ከተሠራ በኋላ የአገራዊ ንግድ ምክር ቤቱን መደበኛ ጉባዔና ምርጫ ማካሄድ እንደሚገባ የዳይሬክተሩ ደብዳቤ ጠቅሷል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት መስከረም መጨረሻ ላይ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ ይዞት የነበረውን መርሐ ግብር፣ የቦርድ አመራር አባላት ያጋጠሙኝ ችግሮች አሉ በማለት ምርጫና ጠቅላላ ጉባዔውን ማራዘሙ ይታወሳል፡፡

ተፈጠሩ ከተባሉ ችግሮች ውስጥ ሕግን መሠረት በማድረግ ከሥር ጀምሮ መደረግ የነበረባቸው ምርጫዎች ከሕግ ውጭ መከናወናቸው፣ በተደጋጋሚ በንግድ ምክር ቤቱ አመራር ቦታ ላይ ለመውጣት ሕግን ያልተከሉ ምርጫዎች ተደርገዋል የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ እንቅፋት ሆኑብኝ ያላቸውን እንዲህ ያሉ ችግሮች እንዲፈቱ ለማድረግ አጣሪ ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡  ሰባት አባላት ያሉት ይህ ኮሚቴ ከሕግ ውጭ ተከናወኑ ያላቸውን ጉዳዮች ለማጣራት የሁለት ወራት ጊዜ ተሰጥቶታል፡፡ ኮሚቴው በሕወጥ መንገድ ተመረጡ የተባሉ የምክር ቤቶች አመራሮችን ጉዳይ የሚያይ ሲሆን፣ የደረሰበትን ውጤት ሪፖርት በማድረግ ጠቅላላ ጉባዔው እንዲካሄድ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኮሚቴው በማጣራቱ ሥራ ወቅት አቤቱታ የቀረበባቸው ጉዳዮች እርግጥ ተፈጽመው ከተገኙ ዕርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ሕገወጥ ምርጫ ተከናውኗል በማለት ንግድ ሚኒስቴር ድረስ አቤቱታ ከቀረበባቸው መካከል የኢትዮጵያ ዘርፍ ምክር ቤት፣ የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ይገኙባቸዋል፡፡

ከአቤቱታዎቹ መካከል በሚመሯቸው ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ከተቀመጠው መመርያ ውጭ ከስምንት ዓመታት በላይ በብቸኝነት ፕሬዚዳንት ሆነው የዘለቁ ግለሰቦች መኖራቸው አግባብ አይደለም የሚለው ሚዛን ደፍቷል፡፡

 

 

 

Standard (Image)

የጀርመኑ ቦሽ ኩባንያ የዕደ ጥበብ መሣሪያዎችን በብድር ሊያቀርብ መዘጋጀቱን አስታወቀ

$
0
0

የኢትዮጵያ ዕደ ጥበባትና መሰል ተቋማትን የሥራ ቅልጥፍናና ውጤታማነት የሚያግዝ የቦሽ ፖወር ቦክስ ቴክኖሎጂ በቅርቡ በብድርና በሊዝ ለማቅረብ ማቀዱን የጀርመኑ ቦሽ ኩባንያ አስታወቀ፡፡

እ.ኤ.አ. በጁን 2016 የቦሽ ፖወር ቦክስ ቴክኖሎጂን በጋና ኩማሲ ሶኮባን ልዩ ልዩ የእንጨት ምርቶች መናኸሪ በሆነችው መንደር ውስጥ /Sokoban Wood Village/ በአፍሪቃ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀውና መቀመጫውን በጀርመን ያደረገው ቦሽ ግሩፕ ኩባንያ፣ ይህንን የፈጠራ ውጤት ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች የማዳረስ ዕቅድን እንዳለውም ይፋ አድርጓል፡፡

ኩባንያው ለሪፖርተር በላከው መግለጫ መሠረት ቦሽ ፓወር ቦክስ አነስተኛ የንግድ ተቋማት የሚታገዙበትንና ውጤታማ የሚሆኑበትን ዕድል ለመፍጠር፣ ክህሎታቸውን ለማሳደግ እንዲሁም የሥራ አድማሳቸውን በማስፋት ወደ መደበኛው የኦኮኖሚ ሥርዓት መግባት የሚችሉበትን መንገድ ለማመቻቸት የተነደፈ ጅማሮ እንደሆነ ጠቅሷል፡፡ ይህ ጅማሮው ሥራ ፈጠራን ለማበረታታትና አነስተኛ የንግድ ተቋማትን መደበኛ ካልሆነው የኢኮኖሚ ዘርፍ ለመውጣት የሚያደርጉትን ሽግግር ለማቀላጠፍ ያለመ የረጅም ጊዜ ዕቅድ ነው፡፡ ስለ ቦሽ ፖወር ቦክስ አጠቃቀም ከቦሽ ግሩፕ ተገቢውን ሥልጠና የወሰዱ ሥራ አስኪያጆች፣ የቴክኒክ ባለሙያዎችና አሠልጣኞች በአፍሪካ እንዳሉትና በኢትዮጵያ ይህንኑ ለማስረጽ እንደሚፈልግ ኩባንያው አስታውቋል፡፡

አፍሪካውያን የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች  በዘርፉ መሪ በሆነው ቦሽ ኩባንያ የተፈበረኩ  ዘመናዊ የኃይል ቁሳቁሶችን መግዛት፣ መኮናተር ወይም መከራየት የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረ ያስታወቀው ኩባንያው መሣሪያዎቹን በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ተጠቃሚዎች ማቅረብ እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡ ቦሽ ፓወር ቦክስ ሥራን ከማቀላጠፉ በላይ በዕደ ጥበባት ምርቶች ጥራት ላይ ከፍተኛ መሻሻል እንዲኖር ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ በዚህም የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች የንግድ ሥራቸው እንዲያድግ ያግዛል ብሏል፡፡

የሶኮባን የእንጨት ቴክኖሎጂ አምራቾች መንደር ከተመረጡ የቦሽ ፓወር ቦክስ መቋቋሚያ ቦታዎች የመጀመሪያው ነው፡፡ 

በኩማሲ ክልል ከተጀመረና በተሞክሮ ከታየ ጀምሮ፣ በርካታ የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች የቦሽ ፓወር ቦክስ ቴክኖሎጂን ለመግዛት እንዲሁም በተጓዳኝ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማግኘት የቦሽ ቢሮዎችን እየጎበኙ ሲሆን፣ እስካሁንም 50 ያህሉ ሥልጠና ለማግኘት መመዝገባቸውን ኩባንያው ጠቅሷል፡፡ 

የቦሽ ኩባንያ የአፍሪካ ቅርንጫፍ ፕሬዚዲንት ዶ/ር ማርከስ ቲል ‹‹እያንዳንዱ የቦሽ ፓወር ቦክስ ቴክኖሎጂ ስለ አጠቃቀሙና አያያዙ ማስተማሪያ አለው፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገትን መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳብ ዕድሎችን ስለመፍጠርና በዚህም ግለሰቦች፣ ማኅበረሰብ፣ አገሮች፣ በአጠቃላይ ዓለማችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ የቦሽም ዋና ዓላማው ይህ ነው፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡       

ለኢትዮጵያ ገበያ የሚቀርበው ቦሽ ፓወር ቦክስ ለዕደ ጥበብ ባለሙያዎችና ሌሎች ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት በከፍተኛ ደረጃ የጊዜን፣ የኃይልንና የገንዘብ ብክነትን በመቀነስ እንደሚግዛቸው የኩባንያው ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

Standard (Image)

ኤርፖርቶች ድርጅት በ24 ሚሊዮን ብር በዘመናዊ ሶፍትዌር የታገዘ አሠራር መዘርጋቱን አስታወቀ

$
0
0

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ዘመናዊ የሶፍት ዌር ቴክኖሎጂ በመጠቀም አሠራሩን ለማዘመን የሚያግዘውን ቴክኖሎጂ በ24 ሚሊዮን ብር በመግዛት የፕሮጀክት ትግበራውን አጠናቆ ሥራ ማስጀመሩን አስታወቀ፡፡

ፕሮጀክቱ የድርጅቱን ተወዳዳሪነት ከሚያሳድጉ ሌሎች ሥራዎች ባሻገር እንደተከናወነ ድርጅቱ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

24 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ቴክሎጂ የድርጅቱን አሠራር ዘመናዊ የማድረግ (የኦቶሜሽን ፕሮጀክት) ሒደት አካል ሲሆን፣ Enterprise Resource Planning (ERP) በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ በትላልቅ ተቋማት ተመራጭ ቴክኖሎጂ እየሆነ የመጣ ነው።  

የኦቶሜሽን ሥራው ለባለድርሻ አካላትና ለደንበኞች ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ቀልጣፋ የኤርፖርት አገልግሎት እንዲኖር የሚያግዝ እንደሆነ ያስታወቀው ኤርፖርቶች ድርጅት፣ በድርጅቱ ውስጥ ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራር እንዲኖር ከማስቻል ባለፈ ሁሉንም አገልግሎቶች በማዘመን ለተጠቃሚው ለማቅረብ የሚያስችል ነው ብሏል። የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ሥራውን እንዲያከናውን ለኧርነስት ኤንድ ያንግ ኩባንያ በሰጠው ሥራ መሠረት ፕሮጀክቱ ተጠናቆ በይፋ መተግበር መጀመሩን አስታውቋል። 

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ ዳዊት፣ ቀደምት የአቪዬሽን ታሪክ ያላት ኢትዮጵያን በኤርፖርት አገልግሎት ዘርፍ መሪ ለመሆን እንድትችል ከሚከናወኑ ትላልቅ ፕሮጀክቶች መካከል ተጠቃሽ እንደሆነ ገልጸዋል። ኢንዱስትሪውን ይበልጥ ለማሳደግና ዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ገብቶ ለመወዳደር እንዲቻል በማሰብ የተተገበረ አዲስ አሠራር መሆኑን አመልክተዋል። ይህም በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ሌላ ታሪክ ለመሥራት በር የከፈተ ሒደት ነው ብለዋል። ከአመራሮችና ከመላው ሠራተኛ የሚታይ ለውጥ ማምጣት እንደሚጠበቅ አሳስበዋል። 

የኧርነስት ኤንድ ያንግ ማኔጂንግ ፓርትነር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለውን ዘመናዊ አሠራር መከተሉ ድርጅቱ በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ያለውን ድርሻው በማስፋት የበለጠ ተወዳዳሪና ብቃት ያለው እንዲሆን የሚያስችለውና ወደፊት ሊደርስበት የሰነቀውን ዓላማ ዕውን ለማድረግ መሠረት የሚጥል ሥራ ነው ብለዋል። ድርጅቱ በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ውስጥ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦም ከፍ የሚያደርግለት መሆኑንም ጠቁመዋል። 

ፕሮጀክቱ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ መጠናቀቅ መቻሉ የመጀመሪያ ትልቅ ሥራ መሆኑ፣ የሠራተኞችን ተነሳሽነት የሚያሳይና የሚያኮራ ሥራ እንደሆነም አቶ ዘመዴነህ  ተናግረዋል።   

የፕሮጀክቱ ትግበራ የድርጅቱን ዋና መሥሪያ ቤትን ጨምሮ የአዲስ አበባ ቦሌ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት፣ የድሬዳዋ፣ የባህር ዳር፣ የግንቦት ሃያና የመቀሌ አሉላ አባ ነጋ ዓለም አቀፍ ኤርፖርቶችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በተደገፈ ሥርዓት በመረጃ መረብ በማስተሳሰር ሥራቸውን ለማከናወን የሚያስችል እንደሚሆን ይጠበቃል። 

Standard (Image)
Viewing all 665 articles
Browse latest View live