Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all 665 articles
Browse latest View live

የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ አራት የመንገድ ግንባታ ስምምነቶች

$
0
0

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በ2009 በጀት ዓመት 69 አዲስ የመንገድ ግንባታ ኮንትራክቶችን ለመፈረምና እነዚህንም መንገዶች ለማስጀመር ዕቅድ መያዙን ይፋ ያደረገው የ2008 በጀት ዓመት መጠናቀቂያ ላይ ነው፡፡ ለ2009 በጀት ዓመት አጠቃላይ ክንውኑም ከ32 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተፈቅዶለታል፡፡

ይሁን እንጂ የበጀት ዓመቱ አምስተኛ ወር እስኪጠናቀቅ ድረስ ምንም ዓይነት ስምምነት ሳያደርግ ቆይቶ፣ ባለፈው ረቡዕ ለበጀት ዓመቱ የመጀመርያ ናቸው የተባሉትን የአራት መንገድ ኮንትራት ስምምነቶችን ፈጽሟል፡፡

አዳዲስ የኮንትራት ስምምነቶችን ለመፈረም ቢገዘገይም፣ ከዚህ በኋላ ተከታታይ የመንገድ ግንባታ ኮንትራክቶችን በመፈራረም ለበጀት ዓመቱ የያዘውን ዕቅድ ሊፈጽም ይችላል ተብሏል፡፡

ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ይጠይቃሉ የተባሉትን የበጀት ዓመቱ የመጀመርያዎቹ የኮንትራት ስምምነቶችን በተመለከተ በተሰጠ መረጃ፣ እነዚህን አራት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶቹን በጨረታ አሸናፊ ሆነው ከባለሥልጣኑ ጋር የተፈራረሙት ደግሞ ሦስት አገር በቀልና አንድ የቻይና ኮንትራክተሮች ናቸው፡፡ ከአራቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ ከ960.1 ሚሊዮን ብር ብላይ ወጪ የሚጠይቀውን የ‹‹የኮንትራት አንድ አበቦ 76 ኪሎ ሜትር›› ስያሜ ያለውን የመንገድ ፕሮጀክት ለመገንባት የኮንትራት ውል የፈጸመው የቻይናው ቻይና ሬል ዌይ ሰቨንዝ ግሩፕ የተባለው ኮንትራክተር ነው፡፡

በጋምቤላ ክልል ውስጥ የሚገኘው ይህ የመንገድ ፕሮጀክት 76 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው ነው፡፡ የዚህ መንገድ የኮንትራት ስምምነት ይዘት እንደሚያሳየው፣ ቻይና ሬል ዌይ ሰቨንዝ ግሩፕ ዲዛይኑንና ግንባታውን በማጣመር የሚሠራው ነው፡፡ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል፡፡ የኮንትራት አንድ አበቦ 76 ኪሎ ሜትር መንገድ፣ በሰባት ሜትር ስፋትና በግራና በቀኝ 1.5 ሜትር ያላቸው የመንገድ ትከሻዎች ኖሮት የሚገነባ ነው፡፡

ቀሪዎቹን ሦስት የመንገድ ፕሮጀክቶች ደግሞ ለመገንባት ዕድል ያገኙት ሦስት አገር በቀል ኮንትራክተሮች፣ በጥቅል ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቁትን ሦስት መንገዶች የሚገነቡ ይሆናል፡፡

በተለይ 36 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለውንና ቤንሻንጉል ክልል ውስጥ የሚገኘውን የአሶሳ-ደለቲ-ባኒዳ ኮንትራት አንድ ፕሮጀክትን ለመገንባት በጨረታ አሸናፊ የሆነው ሰናን የተባለው አገር በቀል ኮንትራክተር፣ በመንገድ ሥራ ሲሳተፍ የመጀመርያው ነው ተብሏል፡፡

ሰናን ኮንስትራክሽን መንገዱን ለመገንባት አሸናፊ የሆነበት ዋጋ 227.4 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ይኽም መንገድ በሰባት ሜትር ስፋትና በግራና በቀኝ 1.5 ሜትር የመንገድ ትከሻ ኖሮት የሚገነባ እንደሆነም የባለሥልጣኑ መረጃ ያስረዳል፡፡ ይህ መንገድ ቀደም ብሎ በጠጠር መንገድ ደረጃ እንደነበር የተጠቀሰ ሲሆን፣ አሁን መንገዱን በአስፓልት ደረጃ ይገነባል፡፡

ባለፈው ረቡዕ የኮንትራት ስምምነት የተደረገበት ሦስተኛው የመንገድ ፕሮጀክት ደግሞ በደቡብ ክልል፤ ከሳይ-ማጂ የሚዘልቀው ኮንትራት ሁለት የመንገድ ግንባታ ነው፡፡ ይህም መንገድ ቀደም ብሎ በጠጠር መንገድ ደረጃ የነበረው ይህንን 29 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመሥራት 773 ሚሊዮን ብር በማቅረብ በጨረታ አሸናፊ የሆነው የንኮማድ የተባለው አገር በቀል ኮንትራክተር ነው፡፡

በዕለቱ የኮንትራት ውል የተፈረመበት ሌላው መንገድ 4.9 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው የመንገድ ፕሮጀክት ነው፡፡ ፕሮጀክቱም በደብረ ማርቆ ከተማ ውስጥ የሚገነባ መንገድ ነው፡፡ 4.9 ኪሎ ሜትሩን የከተማዋን መንገድ ለመገንባት አሸናፊ የሆነው ድሪባ ደፈርሻ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ሲሆን፣ ግንባታውንም በ212.1 ሚሊዮን ብር ለማካሄድ ከባለሥልጣኑ ጋር ተፈራርሟል፡፡

ከሦስቱ ፕሮጀክቶች በተለየ በከተማ ውስጥ የሚካሄደው ይህ መንገድ በሦስት ምድቦች ተከፋፍሎ የሚሠራ ነው፡፡ የመጀመርያው ክፍል 14 ሜትር የመኪና መሄጃ ኖሮት በግራና በቀኝ 2.5 ሜትር ርዝማኔ ያለው የእግረኛ መሄጃና አንድ ሜትር አካፋይ ይኖረዋል ተብሏል፡፡ ሁለተኛው ክፍል ደግሞ 14 ሜትር የመኪና መሄጃ ሲኖረው በግራና በቀኝ 2.5 የእግረኛ መሄጃ እንዲኖረው ተደርጎ ነው፡፡ ሦስተኛውም ክፍል 2.5 ሜትር የእግረኛ መንገድ ያለው 12 ሜትር ስፋት የሚኖረው የተሽከርካሪዎች መሄጃ ይሆናል፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት የተሰጠው ጊዜ 18 ወራት ነው፡፡

በጠጠር መንገድ ደረጃ የነበረው የከተማው መንገድ አሁን ወደ አስፓልት ደረጃ ለማሳደግ የሚካሄደው ግንባታ የዲዛይን ለውጥ ተደርጎለት የሚሠራ ነው፡፡ የከተማውን ደረጃ በጠበቀ መልኩ የዲዛይን ለውጡ የሚሠራ ነው ተብሏል፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት ባለሥልጣኑ እስካሁን የቁጥጥርና የማማከር ሥራውን የሚሠራው አማካሪ ድርጅት አልመረጠም፡፡ 

የቀሪዎቹ የኮንትራት ውል የተፈጸመባቸው ሦስቱ ፕሮጀክቶች ግን አማካሪ የተቀጠረላቸው መሆኑ ታውቋል፡፡ በባለሥልጣኑ መረጃ መሠረት የቻይናው ኮንትራክተር ለሚገነባው መንገድ የቁጥጥርና የማማከር ሥራውን እንዲሠራ የተመረጠው ሲቪል ወርክ አማካሪ ድርጅት ነው፡፡

ሰናን ኮንስትራክሽን የሚገነባውን የአሶ - ባኒዳ ኮንትራት አንድ ፕሮጀክት ለማማከርና ለመቆጣጠር ኢንጂነር ዘውዴ እስክንድ አማካሪ ድርጅት ተመርጧል፡፡ ዶኖ የሚባለው አማካሪ ድርጅት ደግሞ የሳይ-ማጂን ኮንትራት ሁለት መንገድ ፕሮጀክትን እንዲያማክር በባለሥልጣኑ ተመርጧል፡፡

ከአራቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች ከተረከቡት ኮንተራክተሮች ውስጥ የቻይናው ሬል ዌይና ያኮማንድ ከተረከቡዋቸው የመንገድ ግንባታዎች ሌላ በእጃቸው ያላጠናቀቁዋቸው ሌሎች የመንገድ ፕሮጀክቶች አሏቸው፡፡

ሰቨንስ የተባለው የቻይና ኩባንያ አሁን ውል ከፈጸመበት የግንባታ ሥራ ሌላ አራት ፕሮጀክቶችን ይዟል፡፡ እነዚህም ፕሮጀክቶች ከ3.5 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ናቸው፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ቻይና ሬልዌይን ሁለት መንገድ ፕሮጀክቶችን ይዞ እየሠራ ሲሆን፣ ሁለቱ ፕሮጀክቶች ከ2.7 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ናቸው፡፡

 

 

Standard (Image)

ሔሊኮፕተር የሚያሳርፍ ሆቴል ዕውን ለማድረግ የሚንቀሳቀሱት ባለሀብት

$
0
0

በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ደረጃ አንድ አገር በቀል ተቋራጮች መካከል አንዱ ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ነው፡፡ የኮንስትራክሽን ኩባንያው ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ገምሹ በየነ እንደሚገልጹት፣ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ ከ20 ዓመታት በላይ ልምድ አካብቷል፡፡ በመንገድና በሕንፃ ግንባታዎች ላይ በመሳተፍም ይታወቃል፡፡ አሁንም ድረስ በእነዚሁ የግንባታ መስኮች እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ውስጥ በመግባት ከሦስት ዓመት በፊት ሥራ የጀመረውንና ከ760 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የጠየቀውን ኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴልን ገንብተው ለአገልግሎት አብቅተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የኢሊሌ ሆቴል ሁለተኛ ምዕራፍ የሆነው የማስፋፊያ ግንባታን በማካሄድ ላይ ናቸው፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪም በቢሾፍቱ ባቦጋያ ሐይቅ ዳርቻ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቀውን ሆቴልና ሪዞርት፣ በቡራዩ ከተማም ለተመሳሳይ አገልግሎት የሚውል ሪዞርትና ሆቴል እየገነቡ ይገኛሉ፡፡ ‹‹ዶዘርና ሎደር ካልተንቀሳቀሰ ደስ አይለኝም፤›› የሚሉት አቶ ገምሹ፣ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍም ስማቸውን ለመትከል እየሠሩ ነው፡፡ በተለይ ‹‹ኢሊሌ›› የሚለውን ስያሜ ታዋቂ ብራንድ ለማድረግ ውጥን አላቸው፡፡ አዳዲሶቹ ሆቴሎችም ኢሊሌ የሚለውን ስያሜ ይዘው  ወደ ኢንዱስትሪው እንዲገቡ ለማድረግ እንዳቀዱ ይገልጻሉ፡፡ በሆቴልና በቱሪዝም ዘርፍ ኢንቨስትመንታቸውን እያሰፉ ቢሆንም፣ የኮንስትራክሽኑን ሥራ ግን መቼም አልተውም ይላሉ፡፡ በቅርቡ ከሆቴልና ቱሪዝም ሥራው ጋር የተያያዘ አዲስ ነገር ለአዲስ አበባ ከተማ ለማስተዋወቅ ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡ ለከተማዋ እንግዳ እንደሆነ የሚነገርለት አገልግሎት ከኤሊሌ ሆቴል የማስፋፊያ ግንባታ ጋር የተያያዘ ፕሮጀክት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ራሱን ችሎ ሲገነባ አዲስ ይሆናል የተባለው ባለ ስምንት ወለል ያለው ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) ሕንፃ ነው፡፡ በአንድ ጊዜ ከ320 ያላነሱ ተሽከርካሪዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው የተሽከርካሪዎች ማቆሚያ፣ ዘመናዊ ተደርጎ የተገነባና በኮምፒውተር የሚታጋዝ ሥርዓት ያለው ነው፡፡ ይህ የፓርኪንግ ሕንፃ ከኢሊሌ ሆቴል የማስፋፊያ ፕሮጀክት ጋር ቢያያዝም፣ አገልግሎቱ ከአንድ ወር በኋላ ሥራ ይጀምራል፡፡ በዚህ አገልግሎትና በሌሎች ፕሮጀክቶቻቸው ዙሪያ ዳዊት ታዬ አቶ ገምሹ በየነን አነጋግሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ከአንድ ወር በኋላ ሥራ እናስጀምራለን ባላችሁት ዘመናዊ የመኪና ማቆያ ሕንፃና ከዚህ አብሮ እየተገነባ ስላለው የኢሊሌ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ይዘት ቢያብራሩልኝ?

አቶ ገምሹ፡- ከአንድ ወር በኋላ ለአገልግሎት የምናበቃው ፓርኪንግ ቴክኖሎጂ በአገራችን ብቻ ሳይሆን፣ በአፍሪካ ደረጃም ተጠቃሽ የሚሆን ነው፡፡ የፓርኪንግ ስፍራው ስምንት ወለሎች ያሉት ሕንፃ ነው፡፡ ሁለቱ ከምድር በታች፣ ስድስቱ ወለሎች ደግሞ ከምድር በላይ የተገነቡ ናቸው፡፡ በአንድ ጊዜ 320 ተሽከርካሪዎችን የማስተናገድ አቅም አለው፡፡ የመኪና ማቆሚያው አጠቃላይ አወቃቀርና ሥርዓቱ የተለየ ነው፡፡ ለምሳሌ ለፓርኪንግ አገልግሎት የተገጠመለት አሠራር በኮምፒውተር የተደራጀ ሥርዓት ነው፡፡ መኪናው ወደ ሕንፃው ሲገባ በተገጠመው መቆጣጠሪያ መሠረት አስፈላጊውን መረጃ ለአሽከርካሪው የሚሰጥ ነው፡፡ በየትኛው ሕንፃ ክፍል፣ የትኛው ቦታ ላይ ያልተያዘ ክፍት ማቆሚያ ቦታ እንዳለ መረጃውን በማየት ለመገልገል ያስችላል፡፡ ሰዎች መኪናቸውን መረጃውን ከሚያቀርበው ስክሪን ላይ በመመልከት ያልተያዘው የመኪና ቦታ ቀድመው በማወቅ በቀላሉ ለመጠቀም የሚያስችላቸው ነው፡፡ የፓርኪንግ ቴክኖሎጂው አጠቃላይ አወቃቀር አዲስ በመሆኑ የውጭ ኩባንያዎችን ቀጥረን ያሠራነው ነው፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ በዚህ ደረጃ ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱ በአካባቢው ከፓርኪንግ ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመቅረፍ ያስችላል፡፡ ለአገራችንም ዘመናዊ የፓርኪንግ አገልግሎትን የሚያስተዋውቅ እንደሚሆን እናምናለን፡፡ ዘመናዊው ፓርኪንግ የኢሊሌ ሆቴል የማስፋፊያ ፕሮጀክት አካል ቢሆንም፣ የፓርኪንግ አገልግሎቱ ለብቻው ከአንድ ወር በኋላ ሥራ እንዲጀምር እናደርጋለን፡፡ ፓርኪንጉ ጨምሮ አጠቃላይ የኢሊሌ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ ሕንፃዎች አሉት፡፡ ፕሮጀክቱ 22 ወለሎች ያሉት ሕንፃ ግንባታን ያካተተ ነው፡፡ ፓርኪንጉ የሚገኝበት ክፍል ባለአሥር ወለል ሕንፃ አለው፡፡ ሕንፃዎቹ ከሚያካትቷቸው መካከል 2,500 ሰዎችን መያዝ የሚችለው የስብሰባ አዳራሽ አንዱ ነው፡፡ የሕንፃው የላይኛው ክፍል ደግሞ 100 ያህል የሌግዥሪ ሆቴል አፓርትመንት ደረጃ ያላቸው ክፍሎች ይኖሩታል፡፡ ስድስት ወለል የሚይዙት የሕንፃው ክፍሎች ደግሞ ለተለያዩ ግብይቶች የሚውሉ መደብሮች ታስበው የሚገነቡበትን ቦታ የሚሸፍኑ ናቸው፡፡ ይህንን ግንባታ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየሠራን ነው፡፡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የምንጠቀምበት፣ ቱሪስቶች እንደ አማራጭ ሊጠቀሙባቸው የሚያስችሉ መገልገያዎችን በየአፓርትመንቶቹ የምንገጥምበት ነው፡፡     

ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ ከተማ ሰፊ የመኪና ማቆሚያ ችግር አለ፡፡ ካለው ችግር አንፃር የፕሮጀክቱ አስፈላጊነት ባያጠያይቅም፣ በዚህ ኢንቨስትመንት ውስጥ ለመግባት ፍላጎት ያላቸው አካላት ብዙም የሉም፡፡ እርስዎ በዚህ ቢዝነስ ዘርፍ ውስጥ ለመግባት እንዴት አሰቡ?  አዋጭስ ነው? የአገልግሎት አሰጣጡስ እንዴት ነው?

አቶ ገምሹ፡- በአገራችን የሚሠሩ ሕንፃዎች በቂ ፓርኪንግ የላቸውም፡፡ ብዙ ጊዜ እንደምታየው መኪና ለማቆም ጭቅጭቅ ነው፡፡ ከመጀመሪያው ሕንፃዎች ሲታነጹ ጀምሮ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ታሳቢ መደረግ ነበረበት፡፡ ነገር ግን ብዙ ትኩረት ስለማይሰጠው መኪና ለማቆም ያለው ችግር በግልጽ ይታያል፡፡ ባለሀብቱም ከመሬት ጥበት ጋር በተያያዘ ለመኪና መቆሚያ ግንባታ ብዙ ትኩረት አይሰጥም፡፡ ይህ በመሆኑ ደግሞ ከጊዜ በኋላ እየመጣ ያለውን ችግር እየተመለከትን ነው፡፡ ሌላው ዘመናዊ  የፓርኪንግ  አገልግሎት ስላልተለመደ ተገቢውን የአገልግሎት ዋጋ ከፍሎ ለመጠቀም ደስተኛ ያለመሆን ነገር ይታይል፡፡ የፓርኪንግ አገልግሎት ግን በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ዘርፍ የተሰማራ የለም፡፡ ባለሀብቱም ለፓርኪንግ አገልግሎት ሕንፃ ሠርቶ አገልግሎት መስጠት ቢጀምር ወጪዬን እመልሳለሁ ወይ የሚለው ጥያቄ ሊያሰጋው ይችላል፡፡ አዋጭ አይደለም የሚለው ሥጋት ስላለም የፓርኪንግ ቦታዎችን  ገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃት እንደ ቢዝነስ ታይቶ እየተገባበት አይደለም፡፡ በትክክልም ያወጣኸውን ወጪ በቶሎ የምትመልስበት ቢዝነስ አይደለም፡፡ ይህም ቢሆን ግን እኛ ካለው ችግር አንፃር የመፍትሔ አካል ለመሆን በማሰብና የሚመጣው ደንበኛም በምንሰጠው አገልግሎት እንዲደሰት ለማድረግ ነው እንጂ ቢዝነሱ ይህንን ያህል አዋጪ ሆኖ አይደለም፡፡ ገና ልምድ ይጠይቃል፡፡ ይህ ሁሉ ቴክኖሎጂ ፈሶበት አገልግሎቱን ስንጀምር ለአገልግሎቱ እናስከፍላለን ብለን በክፍያ ማስተናገጃ ኮምፒውተሩ እንዲሞላ ያደረግነው ዋጋ በሰዓት 10 ብር ነው፡፡ አንድ ተገልጋይ ለአንድ ሰዓት መኪውን ካቆመ 10 ብር እንዲከፍል ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ ዋጋ አንፃር የምትሰጠው አገልግሎት ተጠረቃቅሞ ሲታሰብ ለግንባታውና ቴክኖሎጂውን ለመግዛት ከወጣው ወጪ ጋር አይገናኝም፡፡ ወጪውን ለመመለስ ረዥም ጊዜ ይወስዳል፡፡ ይህም ሆኖ አገልግሎቱ መኖር አለበት በማለት ወስነን የገባንበት ነው፡፡ ይህ መደረጉ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚዎች እንዲኖሩን መንገድ ይከፍታል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ፓርኪንግ አገልግሎት የሚሰጠው ለኢሊሌ ሆቴልና ከእሱ ጋር በተያያዥነት ለሚጠቀሙ ደንበኞች ብቻ ነው ወይስ ለሌሎች ተጠቃሚዎችም ክፍት ይሆናል? 

አቶ ገምሹ፡- በአጠቃላይ ፓርኪንጉ ሁለት የተለያዩ ክፍሎች አሉት፡፡ ከስምንቱ የፓርኪንግ ሕንፃዎች ሁለቱ ምድር ቤቶች ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው እንግዶች ሲመጡ ያለምንም ክፍያ የሚጠቀሙበት ነው፡፡ ቀሪዎቹ ስድስቱ ወለሎች ላይ ያሉት ማቆሚያዎች ግን ለማንኛውም ደንበኛ በክፍያ አገልግሎቱ የሚሰጥባቸው ናቸው፡፡ በአካባቢው የሚገኙ የተለያዩ ተቋማት ደንበኞች ጭምር ሊገለገሉባቸው የሚችሉ ናቸው፡፡     

ሪፖርተር፡- በአጠቃላይ የመኪና ማቆሚያዎችን ሕንፃ ጨምሮ የኢሊሌ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ምን ያህል ወጪ ይጠይቃል?

አቶ ገምሹ፡- ለፓርኪንግ አገልግሎት የሚውል ሕንፃ መገንባት ድልድይ እንደመገንባት የሚከብድ ነው፡፡ እንደ ማንኛውም ተራ ሕንፃ የሚገነባ አይደለም፡፡ ለሌሎች አገልግሎቶች ታስበው ተመሳሳይ መጠን ያላቸው ሕንፃዎች የግንባታ ወጪ ጋር ስታነፃፅረውም ለፓርኪንግ ብለህ የምትሠራው ሕንፃ ከሌሎቹ ይልቅ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል፡፡ ለፓርኪንግ ተብሎ የሚሠራ ሕንፃ የበለጠ ጠንካራ ሆኖ መሠራት አለበት፡፡ ለምሳሌ ድልድይ ስትገነባ መኪና የሚሄድበት ስለሆነ የሕንፃው መዋቅር የተረጋጋና ንቅናቄን የመቋቋም ጥንካሬውን መጠበቅ አለበት፡፡ የደኅንነት ማስጠበቂያ ልዩ ልዩ መዋቅሮች በደንብ መግባት ይኖርባቸዋል፡፡ የሕንፃው ክፍል መኪና የሚሄድበት ነውና ጭነት የሚቀመጥበት ሕንፃ መገንባት ያለብህ ከሌላው የሕንፃ አገነባብ በተለየ መንገድ ነው፡፡ የምትጠቀምባቸው የኮንስትራክሽን ግብዓቶችም ቢሆኑ ተመሳሳይ ሕንፃዎች ለመገንባት ከምንጠቀምባቸው ግብዓቶች ክፍተኛ ደረጃ ያላቸው ናቸው፡፡ ዲዛይኑም የተለየ ነው፡፡ ለምሳሌ ትልልቅ ሕንፃዎች ላይ ልትጠቀምበት ከምትችለው የአርማታ ብረት የበለጠ መጠን ያለው ብረት መጠቀም አለብህ፡፡ በዚህን ያህል ደረጃ ግንባታው መካሄድ ያለበት መኪና የሚሄድበት በመሆኑ፣ እንደ ድልድይ ግንባታ የምትጠቀምበት የብረት መጠንም በዚያው ልክ ይጨምራል፡፡ ከዚያም በላይ ደግሞ የመሬት መንቀጥቀጥ ቢከሰትስ ብለህ በማሰብ ከመደበኛው የሕንፃ ግንባታ ወጣ በማለት ከመንገድ ግንባታ ጋር ተመሳሳይ ባህሪይ ያለው የአገነባብ ስልት መከተልህ ደግሞ ወጪህን ይጨምረዋል፡፡ ሕንፃው የግልህም ቢሆን የአገር ሀብት ነው፡፡ እንዲህ ያለው የአገር ሀብት ደግሞ ለቀጣዩ ትውልድ የሚያልፍ መሆን አለበት፡፡ ከዚህ አንፃር የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ አጠቃላይ ግንባታ ገና ባለመጠናቀቁ ወጪው ይህንን ያህል ነው ልል አልችልም፡፡ ከወዲሁ ማየት እንደሚቻለው ግን ከፍተኛ መሆኑን ነው፡፡ የፕሮጀክቱን አጠቃላይ ወጪ ለማወቅ ሥራው የግድ መጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡

ሪፖርተር፡- በቢሾፍቱ ባቦጋያ ሐይቅ አካባቢና በቡራዩ ከተማ ውስጥ በሆቴልና ሪዞርት ግንባታዎች ውስጥ ገብታችኋል፡፡ ስለእነዚህ ፕሮጀክቶች ቢገልጹልኝ?

አቶ ገምሹ፡- ኩባንያችን በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ከሌሎች ተቋማት በተለየ የራሳችንን ብራንድ ይዘን እንሠራለን፡፡ በአሁኑ ወቅት ብራንድ የሚባለው ነገር በአብዛኛው ከሰዎች ስም ጋር በተያያዘ የሚጠራ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በደህና ጊዜ ስማቸውን ገንብተውና ማኔጅመንቱን አስቀምጠው ከሚንቀሳቀሱበት ዓለም ሁሉ ገንዘብ እየሰበሰቡበት ነው፡፡ እኛም በራሳችን ማኔጅመንት የራሳችንን ሕንፃ ሠርተን ብዙ በማስተዋወቅ ራሳችንን ብራንድ እናደርጋለን የሚል ራዕይ አለን፡፡ ይህም ይሳካልናል ብለን እናስባለን፡፡ አሁን የምንገነባቸውን ሆቴሎችም በራሳችን ብራንድ ለመጠቀም አስበን የምንሠራቸው ለሌሎችም በማሰብ ነው፡፡    

በባቦጋያ ውስጥ የምንሠራው ሆቴል በአጠቃላይ የሚሸፍነው ቦታ ሰባት ሺሕ ካሬ ሜትር ነው፡፡ ግንባታውን ጀምረናል፡፡ ባለአምስት ኮከብ ሪዞርት ሆቴል ደረጃ የሚገነባ ነው፡፡ ስድስት ወለል ያለው ሕንፃ ነው፡፡ 94 የመኝታ ክፍሎችና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ በሕንፃው አናት ላይ የሔሊኮፕተር ማሳረፊያ አለው፡፡ ሆቴሉ በሐይቅ ዳርቻ የሚገነባ በመሆኑም ሐይቁ ላይ የጀልባ አገልግሎት ለመስጠት ታሳቢ ተደርጎ ዲዛይኑ የተደፈ ዘመናዊ ሆቴልና ሪዞርት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሆቴሉ ግንባታ ምን ያህል ወጪ ይጠይቃል?

አቶ ገምሹ፡-የፕሮጀክት ዲዛይን ግምቱ እንደሚያሳየው አጠቃላይ ወጪው ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅ ነው፡፡ ግንባታው ሲጠናቀቅ የሚፈጀው ምን ያህል እንደሚሆን ወደፊት የሚታወቅ ነው፡፡ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉን በማሳደጉ ረገድ ድርሻችን ከፍ እንዲል በቡራዩ ከተማም ለየት ያለ ሪዞርት እየገነባን ነው፡፡ በቡራዩ ያለው ከላይ ወደ ታች ከተማውን ለመመልከት የሚያስችል ቦታ ላይ የምንገነባው ሆቴል ጅምር ግንባታውን ወይም የአጽመ ሕንፃ ግንባታውን ጨርሰናል፡፡ በቡራዩ ከተማ የሚገነባው ሪዞርት ልዩ ሊባል የሚችል አገልግሎት የሚሰጥበት ነው፡፡ ይህም ሪዞርቱ የጎልፍ መጫወቻ እንዲኖረውና ከሆቴሉ ጋር የሚገናኙ አዳዲስ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችል ግንባታዎችን ለማካሄድና ለማስፋት እንዲሁም ለተጨማሪ የማስፋፊያ ግንባታ የሚሆን ቦታ ከጎን እንዲሰጠን ጠይቀን ምላሽ እየጠበቅን ነው፡፡ አሁን ባለው ደረጃ ግን የቡራዩ ሪዞርት 80 ልዩ መኝታ ክፍሎች ያሉት ሆቴል ነው፡፡ ለተለያዩ ቢዝነሶች የሚውሉ ሞሎችም አሉት፡፡ በነገራችን ላይ የሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪውን የበለጠ ለማሳደግ ከተፈለገ ቱሪስቶች በአማራጭነት ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ የተለያዩ አገልግሎቶችን ማቅረብ ይጠበቅብናል፡፡ ሆቴሎቻችን በሕንፃ ብቻ የተከለሉ መሆን የለባቸውም፡፡ የተሻለ ነገር ለመሥራት ደግሞ በቂ የግንባታ ቦታ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥትም ለዚህ ኢንዱስትሪ ሰፋ ያለ ቦታ መስጠት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም ሆቴል ከተባለ ሰፋ ባለ ቦታ የሚያካልሉ፣ አረንጓዴ ስፍራ ያላቸው፣ በተለያዩ ዕፅዋትና አበቦች የታዋቡ መሆን ይገባቸዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ሆቴሎችን በመሻት የሚመጡ ቱሪስቶችም ሆኑ የአገር ውስጥ ተጠቃሚዎች ከሕንፃ ወጣ ያለ ተፈጥሯዊ ሥፍራ የሚሹም ናቸው፡፡ የሆቴል አገልግሎት ግንብ ብቻ የምትመለከትበት መሆን የለበትም፡፡ የትኛውም ዓለም ላይ ስታይ ሆቴሎች የራሳቸው የሆነ አረንጓዴ ስፍራ ኖሯቸው መስህበነት በተላበሰ ሥፍራ ላይ የሚገኙ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር እንዲህ ያሉ ሆቴሎች እንዲኖሩን ማሰብ ይኖርብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ለሆቴል ግንባታ የሚሰጠው ቦታ ስፋት እንዲኖረው በማድረግ አማራጭ  የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች እንዲፈጠሩ የመንግሥት እገዛ ያሻል፡፡ ኢንዱስትሪው ላይ መሠራት ያለበት ሌላ ትልቅ ጉዳይ ይሩር ከተባለ ዋናው ይህ ነው፡፡ እንዲህ በማድረግ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ማሳደግ ይቻላል፡፡ ተጨማሪ ቱሪስቶችን መሳብ እንችላለን፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ በአሁኑ ወቅት በሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ውስጥ በሰፊው እየገቡ ነው፡፡ ዘመናዊ የፓርኪንግ ግንባታም አካሂደዋል፡፡ ከሚታወቁበት የኮንስትራክሽን  ዘርፍ በመውጣት ወደ ሆቴልና ቱሪዝም እየገቡ ነው ማለት ነው?

አቶ ገምሹ፡- እንግዲህ ኮንስትራሽን በጣም የምወደው ሙያዬና ሥራዬ ነው፡፡ መንገድ ላይ ዶዘሮችና ግሬደሮች ሲቆፍሩ ካላየሁ የሠራሁ አይመስለኝም፡፡ ከኮንስትራክሽን መቼም የምወጣ አይመስለኝም፡፡ እሠራበለታለሁ፡፡ ወደ አዳዲስ ቢዝነሶች ብንገባም በኮንስትራክሽን ሥራ እስከ መጨረሻው እቀጥላለሁ፡፡   

Standard (Image)

በጅማሮው ኪሳራ የገጠመው ራያ ቢራ በሁለተኛው ዓመት ​በአትራፊነት መጓዝ እንደጀመረ ገለጸ

$
0
0

-  ዓምና 104 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አስመዝግቧል

ራያ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ምርቱን ለገበያ ማቅረብ የጀመረበትን የመጀመሪያ ዓመት በኪሳራ አጠናቅቆ አዲሱን በጀት ዓመት ግን በአትራፊነት ጉዞ መጀመሩን ገለጸ፡፡

አክሲዮን ኩባንያው የ2008 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን ለባለአክሲዮኖቹ ቅዳሜ ታኅሳስ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ባስታወቀበት ሪፖርቱ 104.9 ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንዳስመዘገበ ይፋ አድርጓል፡፡

የአክሲዮን ማኅበሩ ቦርድ ሊቀመንበር ሌተና ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሣይ ባቀረቡት ሪፖርት መሠረት በበጀት ዓመቱ በዕቅድ ተይዞ የነበረው የትርፍ መጠን 102.6 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ሆኖም 104.9 ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንደተመዘገበ የኩባንያው የሒሳብ መዝገብ እንደሚያሳይ ጠቅሰው፣ በበጀት ዓመቱ ለተመዘገበው ኪሳራ ዋናው ምክንያት የሽያጭ መጠኑ ከታቀደው እጅግ በማሽቆልቆሉና ሥራ ላይ የዋለው የፋብሪካው የማምረት አቅም በ38 ከመቶ ብቻ በመወሰኑ ነው ብለዋል፡፡

የዓመቱ የሽያጭ መጠን ዝቅተኛ በመሆኑና ሥራ ላይ የዋለው የማምረት አቅም ዝቅተኛ መሆን በበጀት ዓመቱ ትርፍ ሊያስገኝ ባለመቻሉ ኩባንያው ለባለአክሲዮኖች የሚያከፋፍለው የትርፍ ድርሻ እንደማይኖር ተነግሯል፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ በበጀት ዓመቱ ላጋጠመው ኪሳራ ብሎም በዕቅድ ያስቀመጠውን ግብ ሊያሳካ ካልቻለባቸው ምክንያቶች አንዱ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ በቢራ ጥራት ላይ የተከሰተ መዋዠቅ ትልቁን ድርሻ ይይዛል ተብሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በመስከረም ወር 2008 ዓ.ም. ይጀምራል ተብሎ የነበረው የድራፍት ምርት ሽያጭ በተለያዩ ቴክኒካዊ ምክንያቶች ዘግይቶ ጥር ላይ መጀመሩ የታቀደው ስላለመሳካቱ ሌላው ምክንያት ነው፡፡ የምርቱ ዋነኛ የገበያ መዳረሻ ይሆናል ከተባለው ከሰሜን ኢትዮጵያ ውጭ ወደ ሌሎች አካባቢዎች የተደረገው እንቅስቃሴ ውስን መሆንም፣ ፋብሪካው የመጀመሪያውን ዓመት በኪሳራ እንዲያሳልፍ ማስገደዱን ከቀረበው ሪፖርት መረዳት ተችሏል፡፡

በ2008 በጀት ዓመት ኩባንያው 6.1 ሚሊዮን ሳጥን የጠርሙስ ቢራና 219,730 የድራፍት ቢራ ለማምረት አቅዶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ማምረት የቻለው 2.7 ሚሊዮን ሳጥን የጠርሙስ ቢራና 33,010 ድራፍት ቢራ ነበር፡፡ የጠርሙስ ቢራ ምርቱ የዕቅዱን 45 በመቶ፣ የድራፍት ምርቱም የዕቅዱን 15 በመቶ ብቻ ሊሆን ችሏል፡፡ በበጀት ዓመቱ በጠቅላላው ሊመረት ይችላል ከተባለውና በዕቅድ ከተያዘው ውስጥ ማሳካት የተቻለው 41 በመቶ ብቻ እንደሆነ ሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

600 ሺሕ ሔክቶ ሊትር የማምረት አቅም ያለው የራያ ቢራ ፋብሪካ፣ በ2008 በጀት ዓመት ያመረተው 229,38 ሔክቶ ሊትር ብቻ እንደሆነም ታውቋል፡፡ ይህም ኩባንያው በበጀት ዓመቱ አከናውናለሁ ብሎ በዕቅድ ይዞት የነበረው የ1.08 ቢሊዮን ብር ሽያጭ እንዳያሳካ አድርጎታል፡፡ በበጀት ዓመቱ ከሽያጭ ያገኘው ገቢ 449.7 ሚሊዮን ብር ወይም የዕቅዱን 41.5 በመቶ ብቻ ሊሆን ችሏል፡፡ ከዚህ ባሻገር በአክሲዮን ማኅበሩ የዓምናው የሒሳብ ሪፖርት ላይ ኪሳራ ሊመዘገብ ከቻለባቸው ሌሎች ምክንያቶች ውስጥ በበጀት ዓመቱ ኩባንያው ያወጣው ከፍተኛ ወጪ ነው፡፡

የባንክ ዕዳና ወለድ፣ የማኅበራዊ ልማት ድጋፎች፣ የፕሮሞሽን ወጪዎች፣ ለሲቪል ሥራ ተከፋይ ለሆኑ ሒሳቦች በከፊል ለቢራ ሳጥንና ለጠርሙስ መግዣ የዋለው ገንዘብ እነዚህ ከኦፕሬሽን የተገኘ መሆኑን ባለአክሲዮኖቹ እንዲገነዘቡ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ ከፍተኛ ወጪዎች በኩባንያው ለተመዘገበው ትርፍና ኪሳራ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የነበራቸው ተፅዕኖ ከፍተኛ እንደነበር ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ ሆኖም በወደፊት የኩባንያው ሥራ መቃናት ላይ የሚኖራቸው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ኩባንያው አትራፊ አልነበረም ሊባል እንደማይችል የሚጠቁም ነው ተብሏል፡፡ እንደ ሪፖርቱ ከሆነ በኩባንያው ላይ በ2008 በጀት ዓመት ከፍተኛ ወጪ ካስከተሉት መካከል ለባንክ ወለድ የተከፈለ 90.6 ሚሊዮን ብር፣ ለማኅበራዊ ልማት ድጋፍ ጨምሮ ለተለያዩ የምርት ማስተዋወቂያ ወጪዎች 28.3 ሚሊዮን ብር፣ ለአዲስና ነባር የሲቪል ሥራዎች ተከፋይ የሆነ 22.9 ሚሊዮን ብር፣ ለቢራ ጠርሙስ፣ ለካሳና ለመሳሰሉት የዋለው 56.7 ሚሊዮን ብር ወጪ ለአብነት ተጠቅሰዋል፡፡

ኩባንያው ገና በመጀመሪያ ዓመቱ ያወጣው ከፍተኛ ወጪ በሚያገኘው የሽያጭ ገቢ መሸፈን መቻሉ፣ የኩባንያው የወደፊት ተስፋ ብሩህነት የሚያመለክት ነው በማለት በቦርድ ሰብሳቢው የቀረበው ሪፖርት ጠቅሶ፣ ምንጊዜም ቢሆን ለጀማሪ ድርጅት እንዲህ ያሉ ወጪዎች ቀላል እንደማይሆኑ አስፍሯል፡፡ በትርፍና ኪሳራ ላይ ቀላል የማይባል ጫና ሊያሳድር እንደሚችልም ጠቅሰዋል፡፡ ኩባንያው ያስመዘገበው የኪሳራ መጠን ብዙ ጫናዎችን ተቋቁሞ የተመዘገበ በመሆኑና ኩባንያው ለቢራ ገበያው አዲስ ከመሆኑ አንፃርም በገበያው የነበረው የፉክክር ጫና ተዳምረው ከኪሳራው ባሻገር የበጀት ዓመቱ እንቅስቃሴ በጎ ምልክቶች ታይተውበታል ብለውለታል፡፡ የፋብሪካውን አቅም በመጀመሪያው ዓመት 50 በመቶ ለማድረስ በአዋጭነት ጥናቱ የተቀመጠው ከዚህ የመነጨ እንደሆነ የቦርድ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከዕቅድ በታች ለሆነ አፈጻጸሙ ምክንያት የሆኑትን ክፍተቶች በመሙላት በተለይ ከጥራት አኳያ ለተከሰተው ችግር መፍትሔ ሊበጅ በመቻሉ፣ በ2008 ዓ.ም. የመጨረሻ ወራቶች ምርትና ሽያጩ እየጨመረ ሊመጣ መቻሉን አብራርተዋል፡፡ በ2009 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ኩባንያው አትራፊ መሆን እንደጀመረ ተገልጿል፡፡

የቦርድ ሰብሳቢው ይህን በተመለከተ እንደገለጹት፣ በ2008 በጀት ዓመት በተሠሩ ሥራዎች ምክንያት በዓመቱ የመጨረሻዎቹ ወራትና በ2009 የመጀመሪያዎች አራት ወራት ውስጥ ኩባንያው በትክክለኛ የስኬት ጎዳና ላይ መራመድ ለመጀመሩ አመላካች ውጤቶች እየተገኙ ለመሆኑ አስረጂ ያሏቸውን አኃዛዊ መረጃዎችን አቅርበዋል፡፡

ፋብሪካው ወደ አትራፊነት መሸጋገሩን ያመለክታሉ ከተባሉ አኃዛዊ መረጃዎች ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለው የፋብሪካው የማምረት አቅም ደረጃ በደረጃ ዕድገት እያሳየ መጥቶ በ2009 የመጀመሪያዎቹ ወራት ላይ 85 በመቶ መድረሱ አንዱ ነው፡፡ የአራት ወራት ጠቅላላ የሽያጭ መጠን 170.5 ሺሕ ሔክቶ ሊትር መድረሱና የጠቅላላ የሽያጭ መጠን በገንዘብ ሲተመን 338.9 ሚሊዮን ብር ማስመዝገቡ፣ የፋብሪካውን ዕድገት ያሳያል ብለዋል፡፡ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ብቻ የተገኘው የተጣራ ትርፍ 29.47 ሚሊዮን ብር እንደደረሰ የድርጅቱ የሒሳብ መዝገብ ማሳየቱ ትልቅ ተስፋ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ በጥቅምት ወር መጨረሻ የነበረው የጥሬ ገንዘብ መጠን 107 ሚሊዮን ብር እንደሆነ፣ የባንክ ዕዳዎች ዋናውና ወለዱን ጭምር ባወጣው የጊዜ መርሃ ግብር መሠረት እየከፈለ መሆኑ፣ በመቀሌ፣ በሽሬና በማይጭው ከተሞች የሚገኘውን የቢራ ገበያ በአብዛኛው መቆጣጠር መቻሉና፣ የጠርሙስ ቢራ ወደ ውጭ አገር መላክ መጀመሩ ኩባንያው አዲሱን ዓመት በአትራፊነት እንዲጀምር አስችለውታል ተብሏል፡፡ ኩባንያው ምርቱን የላከው በአብዛኛው ወደ እሥራኤል ሲሆን፣ ከዚህ ሽያጭ የተገኘው ገቢ የውጭ ምንዛሪ በመጠኑም ቢሆን የግብዓት አቅርቦቱን ለማሟላት እንዳስቻለው ከቀረበው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡

ፋብሪካው በ2008 በጀት ዓመት መጨረሻ ወራት የነበረው አፈጻጸም እየተሻሻለ በመምጣቱ፣ በ2009 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት የፋብሪካውን 85 በመቶ የማምረት አቅሙን በመጠቀም ምርቱን ለገበያ እያቀረበ በመሆኑ የተመዘገበው ውጤት አበረታች እንደሆነ ተንፀባርቋል፡፡   

ከዚህ ባሻገር የፋብሪካውን ምርት በእጥፍ ለማሳደግ እየተሠራ ያለውን ሥራ በበጀት ዓመቱ ለማጠናቀቅ ዕቅድ መያዙ ተነግሯል፡፡ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱን ሲያጠናቅቅ ምርቱን በስፋት የመሸጥ አቅሙን ሙሉ ለሙሉ አሟጥጦ ለመጠቀምና ወደ በለጠ ትርፋማነት ለማሸጋገር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱን ደረጃ በደረጃ ለማስፈጸም የሚውለው ገንዘብ ከኦፕሬሽን ከሚገኝ ገቢ መሆኑን የሚጠቁመው ሪፖርቱ፣ የመጀመሪያውን የማስፋፊያ ሥራ ጠቅላላ የፋብሪካውን የማምረት አቅም በ25 በመቶ የማሳደግ ሥራ በተያዘው በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ አቅዷል፡፡ ይህ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የማምረት አቅሙን በ150 ሺሕ ሔክቶ ሊትር አሳድጎ 750 ሺሕ ሔክቶ ሊትር እንደሚያደርሰውና ለማስፋፊያ ፕሮጀክቱም እስከ 30 ሚሊዮን ብር ካፒታል እንደሚያስፈልገው በጥናት መረጋገጡን ራያ ቢራ አስታውቋል፡፡

በ2008 ዓ.ም. የታየውን ኪሳራ በተመለከተ ያነጋገርናቸው የኩባንያው ከፍተኛ ባለአክሲዮኖች የራያ ስኬት ሒደት ነው ብለውታል፡፡ ኩባንያው በበጀት ዓመቱ ያወጣው ከፍተኛ ወጪ በተከታዩ ጊዜ ስለማይኖር መጪው ዓመት ጥሩ ትርፍ እንደሚያስመዘግብ በግለሰብ ደረጃ ከፍተኛ ባለአክሲዮን የሆኑት አቶ ዳዊት ገብረ እግዚአብሔር ገልጸዋል፡፡ ‹‹የሒሳብ ሪፖርት ስለሆነ ኪሳራ ተብሏል፡፡ ነገር ግን ኪሳራ ሊባል አይችልም፡፡ ምክንያቱም ብዙ ወጪ አውጥተናል፡፡ የማስፋፊያ ሥራውን ለመጀመር ተጨማሪ መሣሪያዎች እያስገባን ነው፡፡ ስለዚህ ሀብታችንን ለማሳደግ የወጣው ወጪ በመብዛቱ የተከሰተ ነው፡፡ አሁን ግን አትራፊ ሆኗል፤›› ብለዋል፡፡ ፋብሪካው በተከፈተ በ15 ወራት ውስጥ ለመንግሥት ከፍተኛ ገቢ አስገብቷል፡፡ ይህ ትልቅ ነገር ነው በማለት አቶ ዳዊት የራያ ቢራ ተስፋን ገልጸዋል፡፡

የፋብሪካው መቋቋም ያስገኘው ጥቅም መታየት አለበት የሚሉት አቶ ዳዊት፣ ‹‹በ15 ወራት ብቻ በተለያዩ የግብር ዓይነቶች ለትግራይ ክልል ከ251 ሚሊዮን ብር በላይ ማስገባት መቻሉ ለእኔ ትልቅ ትርጉም አለው፤›› ይላሉ፡፡

ራያ ቢራ ከ2400 በላይ ባለአክሲዮኖችን አቅፎ ተቋቋመ ሲሆን፣ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ከባለአክሲዮኖች አሰባስቦ ቀሪውን ከባንክ ብድር በመሸፈን ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በታሪካዊቷ የማይጨው ከተማ ፋብሪካ ገንብቷል፡፡ ከአክሲዮን ኩባንያው ባለድርሻዎች መካከል 42 በመቶውን ቢጂአይ ኢትዮጵያ፣ 25 በመቶውን ደግሞ አቶ ዳዊት ገብረ እግዚአብሔር ይዘውታል፡፡ ከጠቅላላ ጉባዔው ጎን ለጎን በተደረገው ምርጫ እስካሁን ያለው ቦርድ በኃላፊነቱ እንዲቀጥል ተመርጧል፡፡

  

 

Standard (Image)

ዘመን ባንክ ከ200 ሚሊዮን በላይ የተጣራ ትርፍ አስመዘገበ

$
0
0

- የተበላሸ ብድር መጠኑ ከፍተኛ ሆኗል

የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት የ2008 በጀት ዓመት የሥራ ክንውናቸውን የሚያሳይ ሪፖርት ይፋ እያደረጉ ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹም ባለፉት ሦስት ወራት በተከታታይ ይህንኑ ሪፖርታቸው በጠቅላላ ጉባዔ ወቅት በማቅረብ እያሳወቁ ይገኛሉ፡፡ ዘመን ባንክም ቅዳሜ፣ ታኅሳስ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል በጠራው ጠቅላላው ጉባዔ የዓመቱን ክንውን ይፋ አድርጓል፡፡ ነገር ግን ባንኩ ከሌሎች ፋይናንስ ተቋማት በተለየ ጠቅላላ ጉባዔውን ለጋዜጠኞች ዝግ አድርጓል፡፡

‹‹የጠቅላላ ጉባዔው ጋዜጠኞች የሚሳተፉበት አይደለም፤ ጋዜጠኞች ወደ ጠቅላላው ጉባዔው እንዳይገቡ ትዕዛዝ ስለተሰጠ መግባት አይቻልም፤›› በመባሉ የዚህ ጽሑፍ ዘጋቢ ከበር ተመልሷል፡፡

ጠቅላላ ጉባዔው ለጋዜጠኞች ዝግ የተደረገበት ምክንያት ምን እንደሆነ ቢገለጽ? የሚል ጥያቄ ቢቀርብም፣ ትዕዛዝ ነው በመባሉ የጠቅላላ ጉባዔውን ተሳታፊዎች የሚያስተናግዱ ሠራተኞች ጋዜጠኞች ገብተው የጉባዔውን ሒደት እንዳይከታተሉ ከልክለዋል፡፡ ይህንን ዓይነት ዕርምጃ ባንኩ ለምን እንደወሰደ ግልጽ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ በዕለቱ ለባለአክሲዮኖች ከተሰራጨው ዓመታዊ የሒሳብ ሪፖርት መረዳት እንደተቻለው፣ በ2008 የበጀት ዓመት የባንኩ ክንውን ከቀዳሚው ዓመት የተሻለ መሆኑን ነው፡፡

በሒሳብ ሪፖርቱ እንደተመለከተው፣ ባንኩ በ2008 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት 270 ሚሊዮን ብር ከታክስ በኋላ ደግሞ 203 ሚሊዮን ብር ትርፍ አስመዝግቧል፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ከ2007 ዓ.ም. በ33 ከመቶ ብልጫ አለው፡፡

በንጽጽር ሲታይም ባንኩ ዕድገት አሳይቼባቸዋለሁ ብሎ ካስቀመጣቸው ክንውኖቹ መካከል የባንኩ ጠቅላላ ገቢ 40 በመቶ፣ ተቀማጭ ገንዘብ 44 በመቶና ዓመታዊ የብድር መጠኑ 52 በመቶ፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱም በ27 ከመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ይጠቀሳሉ፡፡

ባንኩ የ52 በመቶ ዕድገት እንዳሳየበት በሪፖርቱ የተጠቀሰው በዓመቱ የሰጠው የብድር መጠን ነው፡፡ በ2007 ዓ.ም. ከነበረበት 2.1 ቢሊዮን ብር በ2008 ዓ.ም. 3.2 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ከዚህ በበጀት ዓመቱ ለብድር ከዋለ ገንዘብ ውስጥ 22 በመቶ ድርሻ የሚይዘው ለኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰጠው ብድር ነው፡፡ ለገቢ ዕቃዎች ብድር 21 በመቶ፣ ለውጭ ደግሞ 15 በመቶ ድርሻ የያዘ ገንዘብ ለተበዳሪዎች ተሰጥቷል፡፡ ይሁን እንጂ የባንኩ የተበላሸ የብድር መጠን ከሌሎች ባንኮች ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ከሚባለው ተርታ ተመድቧል፡፡  

በ2008 መጨረሻ ላይ የተበሻለ ብድር መጠኑ 4.76 በመቶ ደርሷል፡፡ ይህ የተበላሸ የብድር መጠን ብሔራዊ ባንክ የባንኮች የተበላሸ የብድር መጠን ከአምስት በመቶ መብለጥ የለበትም ብሎ ካስቀመጠው ጣሪያ ጋር ሲነፃፀር የዘመን ባንክ ከፍተኛ ሆኖ መገኘቱን ያሳያል፡፡

የባንኮች ወቅታዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የ16ቱ የግል ባንኮች አማካይ የተበላሸ የብድር መጠን ከሦስት በመቶ ያነሰ ሲሆን፣ ዘመን ባንክ በአማካይ ሲታይ 4.76 ሆኗል፡፡ ከሰሞኑ የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት አብዛኛዎቹ ባንኮች የተበላሸ የብድር መጠናቸውን ከሦስት በመቶ በታች አውርደዋል፡፡

በ2008 መጨረሻ ላይ የተበላሸ ብድር መጠናቸው የደረሰበትን ካሳወቁት መካከል ኅብረት ባንክ 1.6 በመቶ፣ እናት ባንክ 0.56 በመቶ፣ አቢሲኒያ ባንክ ሁለት በመቶ፣ ብርሃን ባንክ 2.5 በመቶና አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ 1.8 በመቶ ማድረሳቸውን ማሳወቃቸው ይታወሳል፡፡ የቡና ባንክ  የተበሻለ ብድር መጠኑ 3.5 በመቶ በመሆኑ ከዘመን ባንክ ቀጥሎ የሚቀመጥ ከፍተኛው መጠን ነው፡፡

በዘመናዊ ባንክ አገልግሎት ረገድ እመርታ ያሳዩ ውጤቶች እንደታዩ የሚጠቀመው የባንኩ ሪፖርት በኤቲኤም ማሽን ተጠቃሚ ደንበኞቹ በቀን በአማካይ 1.66 ሚሊዮን ብር ገንዘብ ማንቀሳቀሳቸውን፣ በዓመትም ሲሰላም ከ606 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በባንኩ ኤቲኤም ወጪ መደረጉ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ከ1.6 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎት ማንቀሳቀሱም ተጠቃሽ ነው፡፡

በዘመን ባንክ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ለባለአክሲዮኖች በተሰራጨው ሪፖርት መጽሔት ውስጥ የባንኩን የዳይሬክተሮች ቦርድና የማኔጅመንት አባላት ማንነት በሚያሳየው ምስልና ስም ውስጥ የባንኩ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ህላዊ ታደሰና የፋይናንስ ዓለም አቀፍ ባንኪንግ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ስብሐት በላይነህ ናቸው፡፡ ሁለቱ ከፍተኛ የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች ግን በብሔራዊ ባንክ ታግደው በምትካቸው ሌሎች የተሾሙ ቢሆንም፣ መጽሔቱ ላይ የሚታየው ምስል ግን የተነሱት ኃላፊዎች መሆኑ ብዥታ ፈጥሯል ተብሏል፡፡

 

Standard (Image)

ኢትዮጵያ በአሥር ዓመት ውስጥ ወደ መካከለኛ ገቢ ተርታ እንደማትገባ ተመድ ይፋ አደረገ

$
0
0

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድና የልማት ጉባዔ (ዩናይትድ ኔሽንስ ኮንፈረንስ ኦን ትሬድ ኤንድ ዲቨሎፕመንት- አንክታድ) በዝቅተኛ ደረጃ ያደረጉ አገሮች ላይ ያወጣው የዘንድሮ ሪፖርቱ፣ እ.ኤ.አ. ከ2017 ጀምሮ እስከ 2024 ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ መካከለኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ወይም ከዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ይወጣሉ ብሎ ካስቀመጣቸው 16 አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ ሳትካተት ቀርታለች፡፡

የተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ ሪፖርት በአዲስ አበባ ይፋ በተደረገበት ወቅት በኢትዮጵያ የሚገኘው የተቋሙ የአፍሪካ ቀጣና ጽሕፈት ቤት ኃላፊዋ ዶ/ር ጆይ ካቲጌክዋ እንደገለጹት፣ በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ያላደጉ ተብለው ከተፈረጁ 48 የዓለም አገሮች ውስጥ ሦስቱ ማለትም አንጎላ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ እንዲሁም የፓስፊካዊቷ አገር  ቫናቱ ካላደጉ አገሮች ተርታ ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ይሰለፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ቀሪዎቹ 13 አገሮች እ.ኤ.አ. ከ2021 እስከ 2024 ባሉት ዓመታት ውስጥ ከዝቅተኛ ደረጃ ወይም ካላደጉ አገሮች ተርታ በመውጣት መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡

በተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ ትንበያ መሠረት እ.ኤ.አ. ከ2021 እስከ 2024 ባለው ጊዜ ውስጥ ካላደጉት አገሮች ተርታ ይወጣሉ ተብለው የሚጠበቁት አፍጋኒስታን፣ ባንግላዴሽ፣ ቡታን፣ ጂቡቲ፣ ኪሪባቲ፣ የላዖስ ሕዝቦች ዴሞክሲያዊ ሪፐብሊክ፣ ማይናማር (በርማ) ፣ ኔፓል፣ ሳዖተ ቶሜና ፕሪንቺፕ፣ የሰሎሞን ደሴቶች፣ ቲሞር፣ ቱቫሉ እንዲሁም የመን ተካተዋል፡፡ 

እነዚህ አገሮች ከታችኛው ድልድል ወደ መካከለኛው እንደሚሸጋገሩ የሚጠበቁት የተመድ ንግድና ልማት ጉባዔ ከ46 ዓመታት በፊት ባወጣቸው ሦስት መስፈርቶች ቢያንስ ሁለቱን ሲያሟሉ ነው፡፡ ከመሥፈርቶቹ አንደኛው የነፍስ ወከፍ የካፒታል ገቢ ይገኝበታል፡፡

በዚህ መሥፈርት መሠረት በሦስት ዓመታት አማካይ ገቢ ስሌት የአገሮች ግምታዊ አጠቃላይ ብሔራዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ 1035 ዶላር ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ከዝቅተኛ ታዳጊ አገሮች ተርታ ለመውጣት 1242 ዶላር ብሔራዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ማሳመዝገብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህንን መሥፈርት ኢትዮጵያ ማሟላቷ አጠራጣሪ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ዶ/ር ጆይ እንዳብራሩትም ኢትዮጵያ ይህንን መሥፈርት አታሟላም፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የሚቀመጠው የሰው ሀብት መሥፈርት ነው፡፡ የሰው ሀብት ጠቋሚ መለኪያዎች ተብለው ለዚህ መሥፈርት ከተቀመጡት መካከል የተመጣጠነ ሥነ ምግብ ይገኝበታል፡፡ ከጠቅላላው የሕዝብ ቁጥር ውስጥ ምን ያህሉ የተመጣጠነ ምግብ ያገኛል የሚል ንዑስ መጠይቅ ሲኖረው፣ ጤና በተለይም የሕፃናት ሞት ቁጥር በትምህርት ቤት የሚገኙ ተማሪዎች ቁጥር ማለትም የተማሪዎች ጥመርታ ሬሾ እንዲሁም የተማረው ሕዝብ ብዛት (የተማሩ አዋቂዎች ቁጥር) አንፃር የአገሮች የሰው ሀብት መጠን በሚለካበት መሥፈርትም ኢትዮጵያ የለችበትም ተብሏል፡፡

በሦስተኛነት የሰፈረው የኢኮኖሚ ተጋላጭነት የሚለካበት መሥፈርት ነው፡፡ በዚህ መሥፈርት ውስጥ መለኪያ ሆነው የቀረቡት ጠቋሚ ነጥቦች የተፈጥሮ አደጋ (በአደጋው ወቅት የግብርና ዘርፍ የተረጋጋ ምርታማነትና በአደጋው ተጋላጭ የሆነው ሕዝብ ብዛት ይመዘናሉ)፣ ከንግድ ጋር ተያያዥ የሆኑ አሉታዊ ክስተቶች (ማለትም የዕቃዎችና የአገልግሎቶች የተረጋጋ ኤክስፖርት አፈጻጸም ጠቃሚ አኃዞች) የመሳሰሉት ይካተታሉ፡፡ በዚህ መስክ የተቀመጡትን የመስፈርቱን መለኪያዎች በማሟላት ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ብትካተትም፣ በተመድ ሪፖርት መሠረት ግን ከ16 አገሮች ተርታ በመሰለፍ ከዝቅተኛው የድሃ አገሮች ተርታ ለመውጣት ተስፋ ከሚደረጉ አገሮች ዝርዝር ውስጥ መግባት ግን አልቻለችም፡፡ 

አገሮችን ያደጉና ያላደጉ ወይም በዝቅተኛ ደረጃ ያደጉ በሚል መሥፈርት ለሁለት የሚከፍለው የተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ መሥፈርት ከወጣ 45 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ውስጥ ግን ካላደጉ 48 አገሮች ተርታ መውጣት የቻሉት አራት ብቻ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ወደ ላይኛው ዕርከን ያድጋሉ ተብለው ከሚጠበቁት አገሮች መካከል እንደ አንጎላ ያሉት ባስመዘገቡት ብሔራዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ተመዝነው እንደሆነ ያብራሩት ዶ/ር ጆይ ይሁንና በነዳጅና በሌሎች ሸቀጦች ላይ የተመሠረተ ገቢ ያላቸው አገሮች ግን በዓለም የነዳጅ ገበያ ላይ በታየው ዝቅተኛ ዋጋ ምክንያት ውሳኔያቸውን ለማጤንና ካላደጉ አገሮች ተርታ የመውጣት ውሳኔያቸውን ለማዘግየት እያስገደዳቸው ይገኛል፡፡

አንጎላ በነዳጅ ገቢ ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ገንብታለች፡፡ ይሁንና ላለፉት ሁለት ዓመታት በታየው ዓለም አቀፍ መቀዛቀዝ ምክንያት ክፉኛ ከተጎዱ አገሮች መካከል ጎልታ የምትጠቀስ ሆናለች፡፡ በአንፃሩ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ከዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ወደ መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ተርታ ለመግባት እየተሰናዳች አንደምትገኝ መንግሥት እያስታወቀ በሚገኝበት ወቅት፣ ተመድ ግን ይህ ቢያንስ በመጪው አሥር ዓመት ውስጥ ሊሆን እንደማይችል ይፋ አድርጓል፡፡ 

Standard (Image)

ካስቴል ወይን 50 ከመቶ ምርቱን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ማስፋፊያ ማካሄድ ጀመረ

$
0
0

ካስቴል ወይን ከ12 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ሊጠይቅ እንደሚችል የሚጠበቀውን የማስፋፊያ ግንባታ ማካሄድ ጀመረ፡፡ የወይን ምርቶቹን በካርቶን በማሸግ ለገበያ ማቅረብ ጀምሯል፡፡

የካስቴል ወይን ሽያጭ ኃላፊ ወ/ት ዓለምፀሐይ በቀለ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ካስቴል ወይን ዓመታዊ የምርት መጠኑን ከ30 በመቶ በላይ ለማሳደግ የሚያስችለውን የማስፋፊያ ሥራ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ያጠናቅቃል፡፡

በዓመት 1.4 ሚሊዮን ጠርሙስ ወይን የማምረት አቅም ያለው ካስቴል ወይን፣ ምርቱን ለማሳደግ የሚያስችለውን ሥራ የጀመረው ተጨማሪ የወይን እርሻ ቦታ ተረክቦ ተከላ በማካሄድ ነው፡፡

ለምርት ማስፋፊያ የሚሆነውን የወይን እርሻ ማካሄጃ 85 ሔክታር መሬት መረከቡን የገለጹት ወ/ት ዓለምፀሐይ፣ እስካሁን 1.4 ሚሊዮን ጠርሙስ የሚያመርትበትን የወይን ፍሬ ያገኝ የነበረው በ162 ሔክታር መሬት ላይ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ከተጨማሪው የወይን እርሻ በኋላ አጠቃላይ ወይን ምርት የሚያውለው መሬት ወደ 247 ሔክታር በማሳደጉ፣ የወይን ፍሬ ምርቱን በማስፋፋት ከሁለት ዓመት በኋላ ሁለት ሚሊዮን ሊትር በላይ የወይን ጠጅ እንደሚያመርት ይጠበቃል፡፡

ከኢንቨስትመንቱ ባህርይ አንፃር ከሁለት ዓመት በኋላ ምርቱን ለመጨመር ቀድሞ ወይኑ መተከል ስላለበት የወይን ተከላው መጀመሩንና ፋብሪካውም ለምርት ማሳደጊያ የሚሆኑ ማሽነሪዎች ተከላ አብሮ እንደሚከናወን ተብራርቷል፡፡

ወይን የመጠጣት ልማድ እያደገ በመምጣቱ ተጨማሪ ምርት ማምረት ግድ ማለቱን የሚጠቅሱት ወ/ሪት ዓለምፀሐይ፣ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በተከታታይ አዳዲስ ምርቶችን በማቅረብ በደንበኞች ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡

ከውጭ የሚገባውን ምርት ለመቀነስና ወደ ውጭ የሚላከውን ምርት ለማፋፋት በተደረገ ጥናትም ሰሞኑን በጠርሙስ ታሽጎ ከሚቀርበው ወይን በተጨማሪ በካርቶን የታሸገ ወይን ለገበያ ማቅረብ እንደጀመረ አብራርተዋል፡፡

በካርቶን ታሽገው ለገበያ መቅረብ የጀመሩትን ምርቶች በተመለከተ በተሰጠው ማብራሪያ መሠረት በተመሳሳይ ይዘት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት ያስችላል፡፡ በካስቴል ዕቅድ መሠረት አሁን ሁለት ሊትር ተኩል በሚይዙ ካርቶኖች ታሸገው የሚቀርቡት የወይን ምርቶች በቅርቡ ደግሞ በባለሦስትና በባለአምስት ሊትር መጠን ታሽገው ለገበያ መቅረብ እንደሚጀምሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከዓመታዊ ምርቱ ውስጥ 25 በመቶ የሚሆነውን ወይን በካርቶን በማሸግ ለገበያ የማቅረብ ዕቅድ የያዘው ካስቴል፣ የማስፋፊያ ግንባታው ሲጠናቀቅም በካርቶን የታሸጉ ምርቶቹን መጠን እንደሚጨምር ይጠበቃል፡፡

ከ25 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ተደርጎበት ወደ ሥራ የገባው ካስቴል ወይን፣ ገበያውን ሲቀላቀል ከዓመታዊ ምርቱ 50 በመቶውን ለውጭ ገበያ አቀርባለሁ ብሎ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን በውጥኑ መሠረት ግማሽ ምርቱን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ባይችልም ዕቅዱን ለማሳካት እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ እንደ ወ/ሪት ዓለምፀሐይ ገለጻ፣ በአሁኑ ወቅት ከጠቅላላ ምርቱ ከ25 በመቶ በላይ ለውጭ ገበያ እየቀረበ ይገኛል፡፡

በያመቱ የምርት መዳረሻ ቦታዎችን በማሳደግ የካስቴል ወይን ከ15 በላይ አገሮች ማዳረስ ጀምሯል፡፡ የካስቴል ወይን ዋነኛ ገዥዎች ቻይናና አሜሪካ ሲሆኑ፣ ከአውሮፓም   ጀርመን፣ ፈረንሣይ፣ ሆላንድ፣ እንግሊዝና ቤልጂየም ተጠቅሰዋል፡፡ ምርቶቹ ወደ አፍሪካ አገሮች እየተላኩ ሲሆን፣ ጂቡቲና ኡጋንዳም ምርቱን በመቀበል ላይ ይገኛሉ ተብሏል፡፡ ባለፈው በጀትም ዓመት ወደ ደቡብ ሱዳን መላክ እንደጀመረም ተገልጿል፡፡

           

Standard (Image)

ታሪካዊው የፋይናንስ ባለሟሎች ምሽት

$
0
0

የአገሪቱን የፋይናንስ ተቋማት የመቆጣጠር ሥልጣን የተሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ የፋይናንስ ተቋማት በሚያዘጋጇቸው ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች ላይ እምብዛም ሲታደሙ አይታዩም፡፡ ለዓመታት የፋይናንስ ተቋማት በተናጠልም ሆነ በጋራ ሲያዘጋጇቸው በቆዩት መድረኮች ላይ የመገኘት ልምድም የላቸውም፡፡

እንዲህ ባሉት ዝግጅቶች ወቅት ብሔራዊ ባንክን ወክለው በመገኘት የሚታወቁት ከሦስት ሳምንታት በፊት የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው የተሰየሙት የቀድሞው የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ጌታሁን ናና ናቸው፡፡

የግል ባንኮች ከሥራቸው ጋር በተገናኘ ችግር ሲገጥማቸው አቤት ማለት የሚያዘወትሩትና ስለጉዳያቸው ቀድመው የሚያመለከቱት ለምክትል ገዥው ለአቶ ጌታሁን ናና ነበር፡፡ ሐሙስ ታኅሳስ 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ማምሻውን የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ባዘጋጀው መድረክ ላይ የሁሉንም ባንኮች ኃላፊዎች ጨምሮ የብሔራዊ ባንክ አመራሮችን በአንድ ያሰባሰበው ፕሮግራም ላይ ያለወትሯቸው አቶ ተክለወልድ ከተፍ ብለዋል፡፡ የሰውየው መገኘት ለአብዛኛዎቹ የባንክ ሰዎች እንግዳ ነገር እንደነበር መገመት አያዳግትም፡፡

በባንክ ኢንዱስትሪው ጉምቱ ከሚባሉት ጥቂት ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆኑት የቀድሞው የብሔራዊ ባንክ ገዥ፣ የቀድሞው የንግድ ባንክ ሥራ አስኪያጅና የቀድሞው የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ለይኩን ብርሃኑ ዘግየት ብለው ወደ ዝግጅቱ አዳራሽ ሲደርሱ፣ ከአንደበታቸው ያወጡት ቃል የአባባሉን እውነታነት ያረጋግጣል፡፡ አቶ ተክለወልድ መኖራቸውን ሲያውቁም ‹‹የማይታመን ነው፡፡ በጣም ደስ ይላል፤›› ነበር ያሉት፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዥው ምክትሎቻቸውን አስከትለው በተገኙበት የሐሙስ ምሽቱ ፕሮግራም፣ ከቀድሞ የባንክ መሪዎች መካከል እንደ አቶ ጥላሁን ዓባይ ያሉትን ጨምሮ የቀድሞ የባንኮች ማኅበርና የሕብረት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ጌታነህንና ሌሎችንም ያሰባሰበ መድረክ ነበር፡፡ የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ባልተለመደ ሁኔታ ተሰባስበው በነፃነት ያወጉበት ጊዜ እንዳልነበር በመግለጽ የዕለቱ ስብስባ እንዳስደመማቸው የገለጹም ነበሩ፡፡

የገዥው ባንክ ቁንጮ ባለሥልጣናት ተሰባስበው የታደሙበትና ሁሉንም የባንኮች መሪዎች በአንድ ቦታ ያገናኘው መድረክ፣ በአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት እንቅስቃሴ ዙሪያ ስላለ ብርቱ ጉዳይ ለመምከር የተጠራ አስቸኳይ ስብሰባ አስመስሎታል፡፡ በአራቱም አቅጣጫ የአገሪቱን የገንዘብ እንቅስቃሴ የሚመሩ ባንኮች ኃላፊዎችና ባንኮችን የሚቆጣጠረው የብሔራዊ ባንክ መሪዎች በአንድ ላይ የተሰባሰቡበት የተለየ አጀንዳ ነበረው፡፡ ብሔራዊ ባንክ እስከዛሬ ካወጣቸው መመርያዎቹ በተጨማሪ አዲስ መመርያ ስለማውጣቱ የሚመክር ስብሰባ አልነበረም፡፡ የግል ባንኮች ከሚሰጡት እያንዳንዱ ብድር ላይ 27 በመቶ ለቦንድ ግዥ የሚለውን መመርያ ብሔራዊ ባንክ እንዲያነሳ የሚጠይቅም አይደለም፡፡ ዜግነታቸውን የቀየሩ ባለአክሲዮኖች ጉዳይ ከአቅማችን በላይ ስለሆነ ብሔራዊ ባንክ በዚህ ጉዳይ ያወጣውን መመርያ ያንሳልን ለማለት የተገናኙበትም አልነበረም፡፡ ይልቁንም ለአንድ ባለሟል ዕውቅና ለመስጠት ታስቦ የተጠራ እንጂ፡፡

በቅርቡ ከብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥነታቸው በመልቀቅ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክን እንዲመሩ የተሾሙትንና የባንኮች ማኅበር አባል መሆን ግድ የሚላቸውን አቶ ጌታሁን ናናን ለማመስገን፣ ለኢንዱስትሪው ዕድገት ላበረከቷቸው ሥራዎች ዕውቅና ለመስጠት የተሰናዳ ምሽት ነበር፡፡ በኢንዱስትሪው ውስጥ ስለ ሥራው በዚህ ደረጃ ዕውቅና የተሰጠው ሰው ከዚህ ቀደም አለመኖሩ የዕለቱን ዝግጅት ለየት አድርጎታል፡፡ እንዲህ ላለው ዓላማ ሁሉም የዘርፉ ተወናይ መሰባሰቡና በፕሮግራሙ ላይ በግልጽ ሲደረጉ የነበሩ ምክክሮች በራሳቸው ላለፉት 20 ዓመታት ያልታዩ በተቆጣጣሪውና በባንኮች መካከል ከዚህ ቀደም ከነበረው ይልቅ ጥሩ ግንኙነት እንዲፈጠር መንገድ የጠረገ ምሽት ስለመሆኑ በምሽቱ ከተሰጡ አስተያየቶች ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

ለዓመታት በገዥ ሕጎችና በተገዥ ሕግ ተቀባይነት መካከል ሲታዩ ከነበሩ ክርክሮችና ሙግቶች ይልቅ ሲጓዙበት የነበረውን የቀደመ መንገድ በምልሰት እያዩ በነፃነት ሐሳብ ሲለዋወጡ መታየታቸውም አዲስ ነገር ተብሏል፡፡ በተቆጣጣሪውና በሚቆጣጠራቸው ባንኮች መካከል የነበረው ፍትጊያ ሁልጊዜም ጠጣር ቢሆንም፣ የአቶ ጌታሁን ናና ስንብት ግን በዝምታ አይታለፍም በማለት አክብሮት ዕውቅና መሰጠቱ በአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ክሰተት ተብሏል፡፡

የዕለቱን ፕሮግራም ማዘጋጀት ያስፈለገበትን ምክንያት ለታዳሚዎቹ ያስተዋወቁት የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ ሃባ፣ ከባንኮች ጋር የቅርብ ትስስር የነበራቸው አቶ ጌታሁንን ልናመሰግን ይገባል በማለት ከተለየዩ ባንኮች የቀረቡትን ሐሳቦች መነሻ በማድረግ ማኅበሩ የዕለቱን ፕሮግራም እንዳዘጋጀ ጠቅሰዋል፡፡ አቶ ጌታሁን ለአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ዕድገት ቦታ ያላቸው ሰው ስለመሆናቸው የተለያዩ አስረጂዎችን በማቅረብ አቶ አዲሱ መስክረዋል፡፡ ባንኮች አሁን ላሉበት ደረጃ መድረስ የአቶ ጌታሁን አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ያስረዱት አቶ አዲሱ፣ ዕውቅና እንስጣቸው የሚለው ሐሳብ የመነጨው ከሁሉም ባንኮች መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡

የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ተክለወለድ አጥናፉም ‹‹የባንኮች ኃላፊዎች አቶ ጌታሁንን ለማመስገን እንዲህ ያለ ደመቅ ያለ ነገር በማዘጋጀታችሁ አመሰግናለሁ፤›› በማለት ስለ አቶ ጌታሁን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ከአቶ ጌታሁን ጋር ለ27 ዓመታት አብረው እንደሠሩ፣ እንደ ሥራ ባልደረባና እንደ ጓደኛም በደንብ እንደሚተዋወቁ ተናግረዋል፡፡ ‹‹አቶ ጌታሁን በቅንነትና በታማኝነት የፋይናንስ ዘርፉና የአገር ኢኮኖሚ እንዲያድግ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደረገ ትልቅ ሰው ነው፤›› በማለት ገልጸዋቸዋል፡፡ ‹‹በእኔ ዕምነት ከዚህ የበለጠ የሚገባው ሰው ነው፤›› ሲሉም ባንኮች ሲቋቋሙ  የሚገዙበትን ሕግ ከማርቀቅ ጀምሮ የሠሩ፣ ከዚያም ባሻገር የፋይናንስ ኢንዱስትሪው አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዲበቃ የተጫወቱትን ሚና አስረድተዋል፡፡ በብሔራዊ ባንክ ቆይታቸው የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዲፈጠር ጭምር በማድረግ አቶ ጌታሁን የተሳካ ሥራ መሥራታቸውን ገዥው አቶ ተክለወልድ ተናግረዋል፡፡

በማሳረጊያቸውም ‹‹ከአቶ ጌታሁን ጋር ተባብራችሁ እንደሠራችሁት ሁሉ ከአዲሱ ምክትል ገዥ ጋርም የበለጠ ተባብራችሁ እንደምትሠሩ ዕምነት አለኝ፤›› ብለዋል፡፡ የተሰጣቸው ዕውቅና የሚገባቸው መሆኑን በመግለጽም አወድሰዋቸዋል፡፡  የባንኮች መሪዎች አስተያየትም ተመሳሳይ ሲሆን፣ የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ፀሐይ ሽፈራው የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ አሻራቸውን ያሳረፉ ሲሏቸው፣ አቶ ብርሃኑ ጌታነህ በበኩላቸው ዘርፉን ለማሳደግ የደከሙ በማለት ለመመካከርና ለመነጋገር ሁሌም በራቸው ክፍት እንደነበር ጠቅሰውላቸዋል፡፡

በሁሉም ዘንድ እንዲህ ያሉ ሰው ናቸው ለተባሉት አቶ ጌታሁን፣ ዕውቅና አሰጣጡ እናመሰግናለን በሚሉ ቃላት ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ የጣት ቀለበትና የገንዘብ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡ ይሁንና የባንኮች ማኅበር ለአቶ ጌታሁን የሰጠውን የገንዘብ መጠን ምን ያህል እንደሆነ ለመግለጽ አልፈቀደም፡፡

አቶ ጌታሁን በዕውቅና አሰጣጡ ወቅት ንግግራቸውን የጀመሩት ‹‹እጅግ በጣም ከተደሰትኩባቸው ቀኖች አንዱ ነው ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ እጅግ በጣም ነው የተደሰትኩት፡፡ ለዚህም የባንኩን ማኅበረሰብ በሙሉ በጣም አመሰግናለሁ፤›› በማለት ነበር፡፡

የግል ባንኮች ሲቋቋሙና የመንግሥት ባንኮች እንደ አዲስ ሲዋቀሩ፣ ከሱፐርቪዥን ጀምሮ በልዩ ልዩ ሥራዎች ተሳትፎ እንደነበራቸው በማስታወስ ‹‹የግል ባንኮች ተቋቁመው ድክ ድክ ከማለት አልፈው እያደጉ ለዛሬ መድረሳቸው የተለየ ስሜት ይፈጥራል፡፡ ዕድገታቸው ሲያስደስተኝ አንዳንዴ የሚፈጠረው ፍትጊያ ሲያመኝ ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜም በፍትጊያው መካከል እንዳይጎዱብኝ አቅፌ ለመከላከል እየሞከርኩ ቆይቻለሁ፤›› በማለት ለባንኮች የነበራቸውን ድጋፍ አውስተዋል፡፡

‹‹በ20 ዓመት ጊዜ ውስጥ ምንም ዓይነት የባንክ ውድቀት ወይም ችግር አለማጋጠሙ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ይህ ለብሔራዊ ባንክ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ በተለያዩ አገሮች ባንኮች ይወድቃሉ፣ ይነሳሉ፡፡ በእኛ አገር ውስጥ ግን ይህ አለመከሰቱ እጅግ አስደሳች ነው፤›› ነው በማለት የገለጹት አቶ ጌታሁን፣ ወደፊትም የአገሪቱ ባንኮች ዕድገት ቀጣይነት ላይ ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል፡፡

ቀጣዩ ውጥን

የዕለቱ ፕሮግራም በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ጉልህ ሚና አላቸው ለተባሉት ሰው ዕውቅና ከመስጠት ባሻገር ለዘርፉ ዕድገት አስተዋጽኦ ያበረከቱ ባለሙያዎች የሚታወሱበትና ዕውቅና መሰጠት ይኖርበታል የሚል ሐሳብ እንዲፈልቅ ያስቻለ ነበር፡፡

ከዚህ ቀደም በተለያዩ ምክንቶች ለዘርፉ ይደክሙ ለነበሩ ባለሙያዎች ምስጋና ለማቅረብ ያልተቻለ ቢሆንም የሐሙስ ምሽቱ ፕሮግራም ግን ይህ ዕድል እንዲፈጠር፣ ይህንንም ለማመቻቸት ኃላፊነቱን የባንኮች ማኅበር እንዲወስድ የቤት ሥራ የወሰደበት ሆኖ አልፏል፡፡

የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ በቀረበው ሐሳብ መሠረት የሚመሩት ቦርድ በሐሳቡ መክሮ በጥንቃቄ ለመተግበር ምን ማድረግ እንዳለበት ወደፊት ምላሽ እንሰጥበታለን ብለዋል፡፡ የብሔራዊ ባንክ አመራሮችም እንዲህ ያለው የተፍታታና የተዝናና ፕሮግራም በቋሚነት እንዲኖር የበኩላቸውን ለማበርከት ቃል ገብተዋል፡፡

 

 

Standard (Image)

ክልሎች በብሔር ብሔረሰቦች በዓል አዘጋጅነት ሰበብ ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን እየሳዩ ነው

$
0
0

ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት የጸደቀበት ቀን ነው፡፡ ይህንን ቀን መነሻ በማድረግ በያመቱ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል መከበር ከጀመረ 11 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ የመጀመሪያው በዓል በፌደሬሽን ምክር ቤት አሰባሳቢነት ከተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች በተወከሉ የባህል ቡድኖች አማካይነት በአዲስ አበባ ስብሰባ ማዕከል ባህሎቻቸውን በማሳየትና ስለፌደራሊዝም ሲሞፕዝየም በማካሄድ የተጀመረው አከባበር በተከታታይ በተለያዩ ክልሎች እየተካሄደ አሁን ላይ ደርሷል፡፡

ይህ የበዓሉ መሠረታዊ ፓለቲካዊና ማኅበራዊ መገለጫው ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደሚታየው ከሆነ በዙር እንዲከበር መደረጉ በአዘጋጆቹ ክልሎች ላይ የሚፈጥረው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ሌላኛው መገለጫው እየሆነ መጥቷል፡፡

ከሦስት እስከ አራት ሺሕ የሚገመት ቁጥር ያለው የበዓሉ ታዳሚ ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው ይጓጓዛል፡፡ ከተነሰቡት ጀምሮ በዓሉ እስከሚከበርበት ክልል ድረስ ባለው ጉዟቸው መካከል የሚገኙ ሆቴሎችና የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች  የሚያገኙት ኢኖሚያዊ ጠቀሜታ እያደገ መምጣቱ እየታየ ነው፡፡ በዓሉን በሚያዘጋጀው ክልል የሚካሄደው ዝግጅትና የሚያስገኘው የኢኮኖሚ ጥቅምም እየተበራከተ መጥቷል፡፡ ከወትሮው በተለየ መልኩ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችና አዳዲስ ግንባታዎችም በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቁበት አኳኋን እየታየ ነው፡፡  እንግዶችን ያለምንም እንከን በመጡበት አኳኋን ለመሸኘት አዘጋጁ ክልል ከሚያከናውናቸው ሥራዎች በተጨማሪ፣ በግል ባለሀብት የሚገነቡ ሆቴሎች ከወትሮው በተለየ ፍጥነት በመጠናቀቅ ለአገልግሎት መብቃት ጀምረዋል፡፡ ቀደም ሲል የተገነቡትም አቅማቸውን በማሳደግና ተጨማሪ የሰው ኃይል በመቅጠር ሰፊ የሥራ መስክ እየፈጠሩ መጥተዋል፡፡  በብሔር ብሔረሰቦች በዓል ዝግጅት ተጠቃሚ እየሆኑ ከመጡት መካከል የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል፣ የጋምቤላና የቤንሻንጉል እንዲሁም የዘንድሮውን በዓል ያዘጋጀው የሐረሪ ክልል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ ክልሎች በረዥም ጊዜ ሒደት አቅደው ለመሥራት ያልተሳካላቸውን መሠረተ ልማቶች፣ በዓሉ በፈጠረው አጋጣሚ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ያሟሉ ስታዲየሞችና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን መገንባት ችለዋል፡፡ እንዲሁም በግል ባለሀብቶች የባለኮከብ ሆቴል ባለቤት ለመሆንም በቅተዋል፡፡

አቶ አብዱልመሊክ በከር የሐረሪ ክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔና የብሔር ብሔሰረቦች በዓል ዝግጅት ዓብይ አስተባባሪ ናቸው፡፡ 11ኛው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል በክልላቸው መዘጋጀቱ ምን ዓይነት የኢኮኖሚ መነቃቃት እንደተፈጠረ በሪፖርተር ተጠይቀው ሲመልሱ እንዲህ ብለዋል፡፡

‹‹በመጀመሪያ ራስን ችሎ ለማስተዳደር የሚያዙ ዕቅዶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ሐረሪን የሚያስቸግራት የንፁህ ውኃ መጠጥ አቅርቦት፣ የመንገድ ግንባታ፣ ብዙ ጊዜ ፈጅቶ የነበረው የባህል ማዕከል ሥራዎች ነበሩ፤›› ያሉት አቶ አብዱልመሊክ፣ በበዓሉ ምክንያት ለ150 ሺሕ ሰዎች የሚውል ንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ የ3.4 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ግንባታ፣ ከ2500 በላይ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ዘመናዊ የስብሰባ አዳራሽን ያካተተ የባህል ማዕከል ግንባታ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በጠቅላላው በሚሊዮኖች የሚቆጠር በጀት በመመደብ ሥራዎቹ እንዲጠናቀቁ መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ በእነዚህ ግንባታዎች ሰበብ የተንቀሳቀሰው የኢኮኖሚ ዘርፍ እስከዛሬ ከነበረው እንደሚበልጥ አብራርተዋል፡፡

 አቶ አብዱልመሊክ እንደገለጹት፣ በክልሉ በ1.8 ቢሊዮን ብር በጀት በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ታቅዶ የነበረው የስታዲየም ግንባታ ነው፡፡ ይሁንና በዓሉ እንዲከበርበት በማሰብ 680 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎ በ10 ወራት ውስጥ የስታዲየሙ የመጀመሪያ ደረጃና የሜዳ ማልበስ ሥራ እንዲጠናቀቅ በማድረግ፣ ለበዓሉ እንዲደርስ መደረጉን አቶ አብዱልመሊክ አብራርተዋል፡፡ በሐረሪ ክልል ለብዙ ጊዜ ችግር ሆኖ የቆየውን የሆቴል አገልግሎት ዕጥረት ለመቅረፍም በአጭር ጊዜ ውስጥ 43 ክፍሎች ያሉት የእንግዳ ማረፊያ በመንግሥት ወጪ ሊገነባ መቻሉን አፈ ጉባዔው ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹እነዚህ ፕሮጀክቶች በዓሉን ለማዘጋጀት ከተቀበልን በኋላ ታቅደው የተሠሩ ናቸው፡፡ በእነዚህ የሥራ ጊዜያት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል አግኝተዋል፤›› ያሉት አቶ አብዱልመሊክ፣ በበዓሉ ምክንያት ኢኮኖሚው ትልቅ ለውጥ ለማምጣቱ ማሳያ እንደሆነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በሐረሪ ክልል በግል ባለሀብቶች እየተገነቡ ከነበሩ ባለአራት ኮከብ ደረጃ ሊያገኙ እንደሚችሉ ከሚጠበቁ ሦስት ሆቴሎች ውስጥ፣ በዓሉ ከመድረሱ ቀደም ብሎ የተጠናቀቀው ወንደር ላንድ ሆቴል ተጠቃሽ ነው፡፡ የሆቴሉ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ መሐመድ ኢብራሂም እንደገለጹት፣ በሦስት ዓመት ውስጥ በ70 ሚሊዮን ብር ወጪ እንዲገነባ ዕቅድ በማውጣት ሥራውን የጀመሩት ቢሆንም፣ በዓሉ እየደረሰ በመምጣቱ ምክንት ተጨማሪ አንድ ሚሊዮን ብር በመመደብ ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ እንዲጠናቀቀቅ በማድረግ ለበዓሉ ሲባል ሥራ መጀመሩንና በአሁኑ ወቅትም ለአንድ መቶ ሰዎች የሥራ ዕድል እንደፈጠሩ ገልጸዋል፡፡

ክልሎች የስታዲዮም ግንባታዎችን በማካሄድ ለበዓሉ ዝግጅት ማድረግ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ በመሆኑም በሐረሪ ክልል ከዲዛይኑ ጀምሮ እስከ ግንባታው ሥራ ድረስ በአገር በቀል ተቋራጮች የተገነባው የክልሉ ዓለም አቀፍ ሲታዲየም ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ 360 አልጋዎች ያሉት ሆቴልና ስታዲየምን በአንድ አጣምሮ የያዘ ግንባታ ነው፡፡

አዋ አባድር ሁለገብ ስታዲዮም የሚል ስያሜ የተሰጠውን ስታዲየም ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንዲገነባ ለማስቻል በተደረገው እንቅስቃሴ፣ የመጀመሪያው ዙር ግንባታ ተገባዶ ለበዓሉ እንዲደርስ ተደርጓል፡፡ ግንባታው ሲጀመር በቀን ከአንድ ሺሕ  እስከ 2500 የሚደርሱ ሠራተኞችን በመቅጠር ለታሰበለት ቀን አድርሰነዋል ያሉት፣ በአፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን የአዋ አባድር ሁለገብ ስታዲዮም ግንባታ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ፍሰሐ ገብረ ሚካኤል ናቸው፡፡ ‹‹ሥራው ሲካሄድ በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁ በርካታ ወጣቶች የሰብ ኮንትራት ሥራ በመስጠት ከመደገፍ ባሻገር፣ የቀሰሙት ልምድ ራሳቸውን ችለው የተቋራጭ ሥራዎችን እንዲሠሩ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡

በበዓሉ ወቅት የሚቀርቡ የንግድ ትርዒቶች፣ የመዝናኛ ኮንሰርቶች፣ የክልሉን ባህላዊ አልባሳት የሚሸጡ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ፣ ካፍቴሪያዎችና ሬስቶራንቶች በሐረሪና በሌሎችም ክልሎች የሚያስገኙት ኢኮኖሚ ጠቀሜታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችን ዓመታዊ በዓል በበላይነት የሚመራውና የሚቆጣጠረው የፌደሬሽን ምክር ቤት ሲሆን፣ ምክር ቤቱ ተራው ለደረሰው አዘጋጅ ክልል ምን ዓይነት ድጋፍ እንደሚያደርግ ያብራሩት፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገብሩ ገብረ ሥላሴ ናቸው፡፡

ምክር ቤቱ የማስተባበሩን ሥራ በማከወናን በክልሎች ለሚያከናውኗቸው የግንባታ ሥራዎች ከፌዴራል መንግሥት የማማከር ድጋፍ ይሰጣል ያሉት አቶ ገብሩ፣  በግንባታቸው ወቅት ችግር ካጋጠማቸውም በአፋጣኝ ለመፍታት የሚያስችሉ መትፍሔዎችን በማፈላለግ ዕገዛ ያድጋል ብለዋል፡፡ 

Standard (Image)

የጁፒተር እህት ኩባንያ ከቻይና ኩባንያ ጋር የኤሌክትሪክ ቆጣሪዎችን ሊገጣጥም ነው

$
0
0

-  የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎችን ገጣጥሞ ለገበያ ለማቅረብ ተዘጋጅቷል 

የጁፒተር ኩባንያዎች እህት ኩባንያ የሆነው ማይባብ ኤሌክትሮኒክስ ማኑፋክቸሪንግ ኩባንያ፣ ከቻይና ኩባንያ ጋር በመሆን የኤሌክትሪክ ቆጣሪዎችን በአገር ውስጥ ለመገጣጠም መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡ ኩባንያውን በእሽሙር ሽርክና ለመሥራት ተዋውሏል፡፡

ማይባብ ኩባንያ ከቻይናው ሼንዘን ክሎዉ ማኑፋክቸሪንግ ኩባንያ ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት ሁሉንም ዓይነት የኤሌክትሪክ ቆጣሪዎች በአገር ውስጥ ለመገጣጠም የሚያስችል ፋብሪካ ገንብተው አጠናቀዋል፡፡ የማይባብ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ መላኩ ብሥራት እንዳብራሩት ከሆነ፣ መገጣጠሚያ ፋብሪካው በመጪዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ከ300 ሺሕ ያላነሱ ቆጣሪዎችን ማምረት ይጀምራል፡፡ በመጪው ዓመትም ይህንን አቅሙን ወደ 900 ሺሕ ቆጣሪዎችን በማምረት ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማቅረብ ተስፋ መሰንደቁን አቶ መላኩ አብራርተዋል፡፡

በሼንዘን ክሎው ኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ የአፍሪካ ሽያጭ ዳይሬክተር ሁ አን እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ መገጣጠም የሚጀምረው ፋብሪካ፣ ከግብፅ፣ ከናይጄሪያና ከጋና በመቀጠል አራተኛው ኩባንያ ይሆናል፡፡ 

የኤሌክትሪክ ቆጣሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካው ሥራ መጀመር በቅርቡ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋሙ በሁለት ዓመታት ውስጥ እንዲቀርቡለት ካወጣው የ1.2 ሚሊዮን ቆጣሪዎች ጨረታ ጋር መገጣጠሙ ጥሩ አጋጣሚ እንደተፈጠረለት አቶ መላኩም ሆኑ ሚስተር ሁ አን ጠቅሰዋል፡፡ ማይባብ ጨረታውን ቢያሸንፍ የመጀመሪያውን ምዕራፍ ከቻይና በማስመጣት፣ ቀሪዎቹንም እዚሁ ከሚገጣጥማቸው ውስጥ ለማቅረብ ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ማይባብ ኤሌክትሮኒክስ የ70 ከመቶ የባለቤትነት ድርሻ ሲኖረው፣ ሼንዘን ክሎዉ በበኩሉ ቀሪውን 30 በመቶ እንደሚጋራ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል ማይባብ ኤሌክትሮኒክስ ከሰርቢያው ጋሌብ ግሩፕ የሚያስመጣቸውን የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪዎች በአገር ውስጥ ለመገጣጠም የሚያስችለውን ፋብሪካ መገንባቱንና በአጭር ጊዜ ውስጥም ከስምንት እስከ 10 ሺሕ መሣሪዎችን ለገበያ ለማቅረብ መዘጋጀቱን አቶ መላኩ ገልጸዋል፡፡ በዚህ መሠረት ጋለብ ግሩፕ ለማይባብ የሚገጣጠሙትን ሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪዎች ከማቅረብ ባሻገር ለ20 ቴክኒሻኖች ሥልጠና እንደሚሰጥ ተነግሯል፡፡

አቶ መላኩ እንዳብራሩት ለሁለቱ ፋብሪካዎች ተከላና ለማሽነሪዎች በጠቅላላው 5.5 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ውስጥ አራት ሚሊዮኑ ለቆጣሪ መገጣጠሚያው የዋለ ሲሆን፣ 1.5 ሚሊዮኑ ደግሞ ለሽያጭ መመዝገቢያ ፋብሪካ የዋለ ነው፡፡ ማይባብ ኤሌክትሮኒክስ ማኑፋክቸሪንግ በአዲስ አበባ ገርጂ አካባቢ በሁለት ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ሁለቱን ፋብሪካዎች ጎን ለጎን እንደገነባ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ማይባብ ኩባንያ የጂፒተር ትሬዲንግ፣ የጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል እንዲሁም ጄቢ ኮንስትራክሽን እህት ኩባንያ ነው፡፡

 

Standard (Image)

አንበሳ ኢንሹራንስ ከዓምናው ያነሰ ትርፍ አስመዘገበ

$
0
0

- በ2009 ትርፉን ከሁለት እጅ በላይ ለማድረስ ማቀዱን አስታውቋል

በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ካሉ የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው አንበሳ ኢንሹራንስ በ2008 በጀት ዓመት ያስመዘገበው የትርፍ መጠን በበጀት ዓመቱ በዕቅድ ከያዘውም ሆነ ከቀዳሚው ዓመት የትርፍ መጠን ያነሰ ሆኗል፡፡

ታኅሳስ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አንበሳ ኢንሹራንስ ኩባንያ ይፋ ባደረገው ዓመታዊ ሪፖርት መሠረት፣ ዓምና ኩባንያው ከታክስ በፊት ያስመዘገበው ትርፍ 16.9 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ግን ከካቻምናው አኳያ የ23 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ለዘመኑ ከተያዘው ዕቅድ ጋር ሲነፃፀርም በ27 በመቶ ያነሰ ነበር፡፡

የትርፍ መጠኑ ማነስም ለአንድ አክሲዮን በአማካይ የሚከፈለውን የትርፍ ድርሻ እንዲቀንስ አስገድዷል፡፡ እንደ ኩባንያው መረጃ በ2007 ዓ.ም. 28 በመቶ የነበረው የአንድ አክሲዮን የትርፍ ድርሻ በ2008 ወደ 20 በመቶ ሊቀንስ ችሏል፡፡ ለቅናሽ ምክንያት ከተደረጉ መካከለም የካሳ ክፍያ መጨመር፣ አጠቃላይ ወጪ መጨመርና ለኢንሹራንስ የሽያጭ ወኪሎችና ደላሎች የኮሚሽን ክፍያ መጨመራቸው እንደሆነ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

ኩባንያው በበጀት ዓመቱ ከውል ሥራ የመነጨ 29.4 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማግኘት ቢችልም፣ ከታቀደው አኳያ የ21 በመቶ፣ ካለፈው ተመሳሳይ ዓመት ውጤት ጋር ሲነጻጸርም የ17 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡

በ2008 በጀት ዓመት የካሳ ክፍያ አፈጻጸምን የተመለከተው የኩባንያው ሪፖርት እንደሚያሳየው በአጠቃላይ የተከፈለው ካሳ 135.9 ሚሊዮን ብር እንደነበር ነው፡፡ በእንጥልጥል ላይ ያለ 77.9 ሚሊዮን ብር የካሳ ጥያቄም ወደ 2009 በጀት ዓመት መተላለፉን ያሳያል፡፡ 20.9 ሚሊዮን ብር ደግሞ ላልተመዘገቡ የካሳ ክፍያዎች መጠባበቂያ የተያዘ በጀት ነው ተብሏል፡፡

ለካሳ ክፍያ ጥያቄዎች መናር ምክንያት የነበሩት የሥራ አድማስ መስፋትና የተለያዩ የቦንድ ካሳ ክፍያዎች ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸሩ ከፍተኛ መሆናቸው፣ በተሽከርካሪዎች ላይ የሚደርሰው አደጋ በብዛትና በመጠን ማሻቀቡና የመለዋወጫ ዕቃዎችና የጉልበት ዋጋ መጨመር ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የትርፍ መጠኑ ቢቀንስም የተሻለ ሥራ ስለመሠራቱ የሚገልጸው ሪፖርቱ፣ የኦፕሬሽን ዕቅድ አፈጻጸም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 282.1 ሚሊዮን ብር የአረቦን ገቢ ያስመዘገበ ሲሆን፣ ይህም በ2007 ዓ.ም. ከተመዘገበው ጋር ሲነጻጸር የ25 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ከተያዘው ዕቅድ ጋር ሲነጻጸር በ13 በመቶ ማለትም 31.7 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንደነበረው ጠቅሷል፡፡

በበጀት ዓመቱ ለሞተር ከሚሰጥ የመድን ሽፋን 62.5 በመቶ አረቦን ገቢ ለመሰብሰብና ቀሪውን 37.5 በመቶ ደግሞ ሞተር ነክ ካልሆኑት ለማሟላት አቅዶ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ቢያስታውቅም፣ በዕቅዱ መሠረት ግን ሊከናወን አልቻለም፡፡ ለዚህም የቀረበው ምክንያት በአገሪቱ ውስጥ ያለው የገበያ አማራጭና ውድድር ነው፡፡ በመሆኑም 70.4 በመቶውን ድርሻ ከሞተር ሲሰበስብ ቀሪውን 29.6 በመቶ ደግሞ ሞተር ነክ ካልሆኑ መስኮች መሰብሰቡ ለአብነት ተጠቅሷል፡፡ የገንዘብ ነክ የዋስትና ዓይነት 11.2 በመቶ ሲይዝ የባህር ላይ ጉዞ 4.5 በመቶ፣ የእሳትና መብረቅ 3.9 በመቶ፣ ኢንጂነሪንግ 3.5 በመቶ እንዲሁም ለኃላፊነት የሚሰጠው የመድን ሽፋን 3.4 በመቶ ድርሻ ይዘዋል፡፡ ከገንዘብ ነክ የዋስትና ዓይነት በስተቀር ሌሎቹ ሞተር ነክ ያልሆኑት የዋስትና ዓይነቶች ከዕቅድ በታች አፈጻጸም አሳይተዋል፡፡

በሌላ በኩል የኩባንው ዕዳ በ2008 ዓ.ም. የነበረው አፈጻጸም ከ2007 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ61.7 ሚሊዮን ብር ወይም የ34 በመቶ ብልጫ በማሳየት ወደ 245 ሚሊዮን ብር ሊያድግ ችሏል፡፡ ለዚህም ውጤት የኩባንያው የአረቦን መጠባበቂያ መጠን መጨመር በዋናነት ተጠቃሽ ሆኗል፡፡

አጠቃላይ የአረቦን ገቢው (እ.ኤ.አ. ከ2007/08 እስከ 2015/16 በነበረው ጊዜ ውስጥ) በአማካይ 20.5 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ያስታወሰው ሪፖርቱ፣ በ2008 በጀት ዓመት በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ6.1 ቢሊዮን ብር በላይ አረቦን ከመድን ሽፋን እንደተሰበሰበ መረጃው ይጠቁማል፡፡ ከዚህ አጠቃላይ አረቦን ውስጥ የአንበሳ ኢንሹራንስ ኩባንያ ድርሻ 4.6 በመቶ ወይም 282.1 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡ የግል የመድን ኩባንያዎች ከሰበሰቡት 3.9 ቢሊዮን ብር አረቦን አንፃር ሲታይ የኩባንያው የገበያ ድርሻ 7.2 በመቶ መሆኑንም የአንበሳ ኢንሹራንስ ሪፖርት አመልክቷል፡፡

በ2008 ዓ.ም. በሁሉም የሥራ ክንውኖች በተወሰነ መልኩ የተሻለ አፈጻጸም ያሳየበት እንቅስቃሴ ቢኖርም፣ በትርፍና በተከፋይ የትርፍ ድረሻዎች ላይ መቀነስ ታይቷል የሚለው የአንበሳ ኢንሹራንሽ ሪፖርት፣ ወደፊት እደርስበታለሁ ያለውን ግብም አስቀምጧል፡፡

እንደ ኩባንያው ሪፖርት በዚህ በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ እንደሚንቀሳቀስና በሦስት እጅ ጭማሪ የሚያሳይ ትርፍ እንደሚያስመዝግብ ይጠበቃል፡፡ ለዚህም በ2009 ዓ.ም. የሚሰበሰበው ጠቅላላ የውል ሥራ ገቢ በ2008 በጀት ዓመት ከተሰበሰበው በ31 መቶ ብልጫ በማሳደግ 350 ሚሊዮን ብር ለማድረስ ማቀዱ አንዱ ነው፡፡ ከውል ሥራ 55.4 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ከጥቅል ትርፍ 27.5 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ማቀዱን አስታውቋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የተገኘው የኩባንያው ትርፍ ከግብር በኋላ 15 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ የኩባንያው የዲሬክተሮች ቦርድ 13.1 ሚሊዮን ብር ሙሉ በሙሉ ለባለአክሲዮኖች እንዲከፋፈል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

እንደ ኩባንያው ሪፖርት ከበጀት ዓመቱ ዓበይት ተግባራት ውስጥ አንዱና ግንባር ቀደም አድርጎ ያስቀመጠው ለዋና መሥሪያ ቤትና ለሁለገብ አገልግሎት የሚውል ባለ ሕንፃ ግንባታን ነው፡፡ የግንባታ ሥራው ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቃው ሕንፃ ሥራ ጀምሯል፡፡

የአንበሳ ኢንሹራንስ አጠቃላይ ሀብት 335 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት አኳያ የ24 በመቶ ወይም 64.4 ሚሊዮን ብር ዕድገት አስመዝግቧል፡፡ የተከፈለ ካፒታሉ 66.4 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ 

Standard (Image)

የወጪ ንግዱ መዳከም በፋይናንስ ዘርፉ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው

$
0
0

የወጪ ንግዱ በሚፈለገው ደረጃ አለመራመድ አገሪቱ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከማሳነሱም በላይ የተለያዩ የንግድ፣ የአገልግሎትና የኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያሳርፍ ይታያል፡፡ የወጪ ንግዱ በሚጠበቀው ደረጃ አለመከናወኑ በቀጥታ ከሚነካቸው ወይም አሉታዊ ተፅዕኖዎችን ከሚያሳርፍባቸው ዘርፎች ውስጥ የፋይናንስ ዘርፉ አንዱ ነው፡፡

የወጪ ንግዱ ሞቅ ሲል በዚያው ልክ ተጠቃሚ የሚሆኑት ባንኮች፣ ንግዱ ሲቀዛቀዝም የምንዛሪ አቅርቦታቸውንና የሚያገኙትን ጥቅም ይጎዳዋል፡፡ ችግሩ በዚህ ሳይወሰን ባንኮች እርስ በርስ የሚያካሂዱትን ውድድር እንዲጦዝ ሲያደርግና በወጪ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ደንበኞቻቸውም የሚያስገኙላቸውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንዲጨምር ለማድረግ ሲራወጡ እንዲታዩ ያስገድዳቸዋል፡፡

በተከታታይ ዓመታት እየታየ ያለው የወጪ ንግድ ገቢ መቀነስና መቀዛቀዝ ፈተና ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡ ቅዳሜ፣ ታኅሳስ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. የወጪ ንግድ ደንበኞች ቀንን ያከበረው የሕብረት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ታዬ ዲበኩሉ ይህንኑ ሥጋታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ ‹‹በወጪ ንግድ ዘርፍ በአገር አቀፍ ደረጃ ኢንቨስትመንት በማሳደግ፣ ለወጪ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶቻችንን በጥራት፣ በተወዳዳሪ ዋጋና በሚፈለገው መጠን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ የሚደረገው ጥረት አሁንም ዘርፈ ብዙ በሆኑ ችግሮች ሳቢያ ፈታኝነቱ እንደቀጠለ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡

በዘርፉ እየታዩ ካሉት ዋና ዋና ችግሮች ብለው ከጠቀሷቸው ውስጥ ለወጪ ንግድ ሸቀጦች ያለው ዓለም አቀፍ የገበያ ፍላጎት መቀዛቀዝ፣ የምርት ግብዓትና የጥራት ሁኔታ መጓደል፣ የቴክኖሎጂ አቅም ውሱንነት ይገኙበታል፡፡ ከዚህም ባሻገር ብቁና የሠለጠነ የሰው ኃይል እንደልብ ያለመገኘቱ፣ በዘርፉ የሚታየው ሕገወጥ ንግድ ሊገታ አለመቻሉ የወጪ ንግዱን እየፈተኑት ከሚገኙ ችግሮች መካከል በግንባር ቀደምነት እንደሚጠቀሱ አስታውሰዋል፡፡

በ2008 በጀት ዓመትም በአገር አቀፍ ደረጃ በወጪ ንግድ ላይ የታየው አፈጻጸም ደካማ እንደነበር የገለጹት አቶ ታዬ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ 4.22 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ከወጪ ንግድ ዘርፍ ለማግኘት ታቅዶ በአፈጻጸም የተመዘገበው ግን 2.86 ቢሊዮን ዶላር ብቻ እንደነበር አስታውዋል፡፡ በወቅቱ በአገር ደረጃ ለወጪ ንግድ ከቀረቡ የምርት ዓይነቶች መካከል ከዕቅድ በላይ አፈጻጸም የተመዘገበው በሻይ ቅጠል ምርት ብቻ ሲሆን፣ በተቀሩት ሁሉም ዓይነት ሸቀጦች የታየው አፈጻጸም ከዕቅድ በታች ሆኖ መመዝገቡ በዘርፉ ላይ ያለውን ክፍተት ያሳያል ብለዋል፡፡

ሆኖም በእነዚህና በሌሎች ተያያዥ ችግሮችና ፈተናዎች ሳይረቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት ብሎም ለስኬት መብቃት ብርቱ ጥረትን የሚጠይቅ ነው ያሉት አቶ ታዬ፣ አገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ እንድታሳድግ በማገዝ ረገድ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ላሉት ላኪ ደንበኞቻቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እየታየ ያለውን ሥር የሰደደ የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ባንካቸው በወጪ ንግድ ላይ ለተሰማሩ ደንበኞቹ ተወዳዳሪ የአገልግሎት ዓይነቶችን በማቅረብ በኩል ብርቱ ጥረት እያደረገ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡ በቀጥታ ከወጪ ንግድ ጋር የተያዙ የአጭር ጊዜ ብድሮችን ጨምሮ የኦቨር ድራፍት፣ የቅድመ ጭነት ፋይናንስና ሌሎች ተዛማጅ የባንክ አገልግሎቶችን እየሰጠ ሲሆን፣ በ2008 የበጀት ዓመት ባንኩ ከአጠቃላይ ብድር ውስጥ የወጪ ንግድ ዘርፍ 20.74 በመቶ ድርሻ መያዙንም አስታውሰዋል፡፡ ከ204 በላይ ዓለም አቀፍ ባንኮች ጋር ግንኙነት በመፍጠር በወጪ ንግድ ላይ ለተሰማሩ ደንበኞች አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ የሕብረት ባንክ ፕሬዚዳንት ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የውድድር ግለት በሚታይበት የአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ሕብረት ባንክ ደንበኛ በመሆን ወደ ውጭ ሲልኩ ለነበሩ ደንበኞች ዕውቅና የሰጠ ሲሆን፣ በተለያየ ዘርፍ ለባንኩ ከፍተኛ ገቢ ላስገቡ 15 ደንበኞች የዋንጫና የሠርተፍኬት ሽልማት ሰጥቷል፡፡

የሕብረት ባንክ ጠቅላላ ሀብት ብር 17.3 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ የባንኩ ጠቅላላ ካፒታልም 2.07 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

 

Standard (Image)

የደቡብ ግሎባል ባንክ ባለአክሲዮኖች የአክሲዮን ድርሻቸውን በእጥፍ ለማሳደግ ወሰኑ

$
0
0

የተከፈለ ካፒታሉ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. 500 ሚሊዮን ብር ማድረስ የሚጠበቅበት የደቡብ ግሎባል ባንክ ባለአክሲዮኖች የአክሲዮን ድርሻቸውን በእጥፍ ለማሳደግና ዓመታዊ ትርፋቸውን ለካፒታል ማሳደጊያነት ለማዋል ውሳኔ አሳለፉ፡፡

የባንኩ ባለአክሲዮኖች ባለፈው ቅዳሜ ባካሄዱት ጠቅላላ ጉባዔ ባሳለፉት ውሳኔያቸው መሠረት፣ በርካታ የባንኩ ባለአክሲዮኖች እስካሁን ያላቸውን የአክሲዮን ድርሻ በእጥፍ ለማሳደግ የተስማሙበትን ቅጽ በዕለቱ እስከመሙላት ደርሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት ባንኩ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ የተከፈለ ካፒታሉን 500 ሚሊዮን ብር ማድረስ የሚገባው በመሆኑ፣ ባለአክሲዮኖቹ ትርፋቸውን ለካፒታል ማሳደጊያ ከማዋል ባሻገር የጊዜ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት ካፒታሉን ለመሙላት የሚያስችሉ ሌሎች ተግባራትን ለመከወን ተስማምተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው የጊዜ ገደብ በፊት የተከፈለ ካፒታሉን መሙላት የሞት ሽረት ጉዳይ ስለሆነ፣ ባለአክሲዮኖች ከባንኩ ጋር ተባብረው በመሥራት የባንኩን ዕድገት ማስቀጠል የግድ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ሌሎች አዳዲስ አክሲዮን ገዥዎችን በማምጣት ጭምር ባንካቸውን ለማገዝ እንደሚጥሩም ባለአክሲዮኖቹ የገለጹ ሲሆን፣ ገንዘባቸውን በባንኩ ከማስቀመጥ ጀምሮ ሌሎች ሥራዎቻቸውን ከባንኩ ጋር በማስተሳሰር ከተቻለ የሚፈለገውን ውጤት በአጭር ጊዜ ማምጣት ይቻላል እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

ባንኩ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ካፒታሉ 322.1 ሚሊዮን ብር እንደሆነ የገለጹት የባንኩ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኑረዲን አወል፣ በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ከነበረው በ103.2 ሚሊዮን ብር ወይም በ47 በመቶ ጭማሪ የታየበት ነው፡፡

የተከፈለ ካፒታሉ ደግሞ በ322 ሚሊዮን ብር የደረሰ ቢሆንም፣ ባንኩ የተከፈለ ካፒታሉን 500 ሚሊዮን ብር ለማድረስ ከ175 ሚሊዮን ብር በላይ ማሰባሰብ ይጠበቅበታል፡፡

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ ሃባ በበኩላቸው ባንኩ በተያዘው በጀት ዓመት ዋነኛ ክንዋኔ ካፒታሉን ማሳደግ በመሆኑ፣ ለዚህ የሚያግዙ ስትራቴጂዎችን ነድፎ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ የተከፈለ ካፒታሉን ሞልቶ በቀጣዩ ዓመት የተሻለ ትርፍና ዕድገት ይኖራል የሚል እምነታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡

በቅዳሜው ጠቅላላ ጉባዔ የባንኩ የ2008 በጀት ዓመት ሪፖርት በባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኑረዲን የቀረበ ሲሆን፣ የ2008 በጀት ዓመት ትርፉን በሁለት እጅ በማሳደግ 68 ሚሊዮን ብር መድረሱን ለባለአክሲዮኖቹ አሳውቀዋል፡፡  

ከዚህም ሌላ ዓመታዊ ገቢ 74.5 በመቶ እንዳደገና በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ 194.1 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱ ተገልጿል፡፡

በ2008 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ 871.8 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ የአስቀማጮች ቁጥር ደግሞ ከ25,351 ወደ 36,615 ወይም የ44 በመቶ ዕድገት እንዳሳየ አቶ ኑረዲን ገልጸዋል፡፡

እንደ ባንኩ ሪፖርት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተሰጠው ብድር በ76.8 በመቶ አድጎ 599.3 ሚሊዮን ብር ሲደርስ፣ የባንኩ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ደግሞ በ142 በመቶ በማሳደግ 939 ሚሊዮን ብር መድረሱ ተመልክቷል፡፡

የደቡብ ግሎባል ባንክ አሴት 1.3 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ የሚያመለክተው የባንኩ ሪፖርት፣ በ2009 ዓ.ም. ሌሎች አዳዲስ ዘመናዊ የባንክ አሠራሮችን በመተግበር ተወዳዳሪ ባንክ ሆኖ ለመውጣት ይሠራል ተብሏል፡፡ ባንኩ ከ7,000 በላይ ባለአክሲዮኖች አሉት፡፡

 

Standard (Image)

የህንዱ ግዙፍ ሥጋ አምራች ከየካቲት ጀምሮ ወደ ውጭ መላክ እንደሚጀምር ይፋ አደረገ

$
0
0

- በቀን አንድ ሚሊዮን ዶላር ማስገኘት የሚችል አቅም እንዳለው ተገልጿል

የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በዝዋይ ከተማ፣ አዳሚ ቱሉ፣ ሞጆና ዱከም የሚገኙ ስድስት የበግ፣ የፍየልና የዳልጋ ከብት ማደለቢያና ቄራዎች እንዲሁም የተረፈ ምርት ማቀነባበሪያዎችን ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙኃን አስጎብኝቶ ነበር፡፡ ከተጎበኙት መካከል በህንዳውያን ባለሀብቶች የተገነባውና የአላና ግሩፕ ኩባንያ አካል የሆነው ዘመናዊ ቄራና የተረፈ ምርቶች ማቀነባበሪያ አንዱ ነው፡፡

አቶ ግደይ ገብረ መድኅን፣ የአላና ፍሪጎሪፊኮ ቦራን ፉድስ ኩባንያ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ስለ ኤክስፖርት ቄራው ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹ይህ ኤክስፖርት ቄራ መሠረቱን ህንድ ያደረገና በዓለም ከ80 በሚበልጡ አገሮች ኤክስፖርት በማድረግ 2.2 ቢሊዮን ዶላር በዓመት የሚያንቀሳቅስ ሲሆን፣ በአፍሪካ የመጀመሪያውን ኤክስፖርት ቄራ በኢትዮጵያ ዕውን ለማድረግ ግንባታውን አጠናቆ በቅርቡ ሥራ ይጀምራል፤›› ብለዋል፡፡

አላና ግሩፕ በኢትዮጵያ የገነባው ፋብሪካ ሙሉ ለሙሉ በህንድ ከሚገኘው ጋር ተመሳሳይ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ግንባታውን የጀመረው እ.ኤ.አ. በ2015 ጥር ወር ነበር፡፡ በ75 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል ኢንቨስትመንቱን የጀመረው ይኸው ኩባንያ፣ በዝዋይ አዳሚ ቱሉ አካባቢ በ75 ሔክታር መሬት በመረከብ ፋብሪካውን ገንብቷል፡፡ ኤክስፖርት ቄራው በቀን 3000 ሺሕ ዳልጋ ከብቶችን፣ ከአምስት እስከ ስድስት ሺሕ የሚደርሱ በግና ፍየሎችን ለእርድ እንደሚያውል ታውቋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ፋብሪካው ከራሱ ባሻገር የሌሎች ፋብሪካዎችን ምርቶች በመቀበል በተከላቸው የደምና የአጥንት ተረፈ ምርቶች ማቀነባበሪያዎች አማካይነት 80 ኩንታል አጥንት እንዲሁም 40 ኩንታል የደም ተረፈ ምርት የሚያቀነባብር ማሽን የተገጠመለት ሲሆን፣ የተቀነባበሩት ተረፈ ምርቶችም ለዶሮ መኖነትና ለዓሣ ምግብነት ይውላሉ ተብሏል፡፡

በፋብሪካው ከተተከሉት መሣሪያዎች አንዱ ከእንስሳቱ የሚወጣውን ፈርስ በማድረቅ ለኢነርጂ ምንጭነት እንዲውል የሚያስችል ምርት የሚያስገኘው ነው፡፡ ይህም ተረፈ ምርት ለኤክስፖርት ገበያ የሚውል ነው፡፡ በአንድ ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተሠራው ፍሳሽ ማስወገጃ ፋብሪካው ጥቅም ላይ ያዋለውን ውኃ አጣርቶ መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል ከማድረግ ባሻገር፣ ምንም ዓይነት የአካባቢ ብክለት እንዳይፈጠር ለመከለከል የሚያስችል ሥርዓት መሆኑን ኃላፊዎቹ ጠቁመዋል፡፡

አቶ ኃይለ ሥላሴ ወረስ የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንዱስትሪውን በሚመለከት ለሪፖርተር በሰጡት መግለጫ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን 11 ቄራዎች ለውጭ ገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ ቄራዎቹ ባለፈው ዓመት ኤክስፖርት ካደረጉት ምርት 102 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ ይህም ከዘርፉ እንዲገኝ ከታቀደው ውስጥ 70 በመቶ የተከናወነበት ነው፡፡ ‹‹ዘንድሮ 157 ሚሊዮን ዶላር ለማስገባት ያቀድን ሲሆን፣ ባለፉት በአምስት ወራት 39.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ ቀሪውን አላናን ጨምሮ ሦስት የኤክስፖርት ቄራዎች በቅርቡ ወደ ሥራ ስለሚገቡና ወደ ሳዑዲም መላክ ስለምንጀምር ዕቅዱ ሙሉ ለሙሉ ይሳካል ብለን እንገምታለን፤›› በማለት የገለጹ ሲሆን፣ ‹‹አላናን ብቻውን ብንመለከት እንኳ ለግንባታ የሚውለውን 75 ሚሊዮን ዶላር ከራሱ ምንጮች ነው ያመጣው፡፡ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በቀን እስከ አንድ ሚሊዮን ዶላር ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሆኖም ከዶላሩ በላይ በቀንድ ከብት ብዛት ከአፍሪካ አንደኛ የሚለው አገላለጽ በሥጋ ምርት ኤክፖርት አንደኛ በሚለው ይቀይርልናል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ‹‹በመንግሥት በኩል መሬት በሊዝ  ከማቅረብ ጀምሮ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንዲያገኝ፣ 194 ኮንቴይነር ሙሉ ማሽነሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገባ እገዛ ተደርጎለታል፡፡ በቅርቡም አካባቢው ምንም ዓይነት የኢንተርኔት አገልግሎት የሌለው በመሆኑ ሥራ ከመጀመሩ በፊት እንዲገባለትና የንፁህ ውኃ አቅርቦት እንዲያገኝ ኢንስቲትዩቱ ከኦሮሚያ ክልል ጋር እየተነጋገረ እንደሚገኝ ያብራሩት አቶ ኃይለ ሥላሴ፣  አላና ቄራ ሥራ ሲጀምር የቁም እንስሳት ንግዱንና የእርድ አገልግሎቱን እንዲሁም በሌሎች ቄራዎች የሚታየውን የተረፈ ምርት አወጋገድ ሥርዓትን ከመሠረቱ ይቀይረዋል በማለት ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡

አቶ ግደይ የምርት አቅርቦቱን ከየት እንደሚያኙት ለሪፖርተር ሲያብራሩም፣ ፋብሪካው 90 በመቶ የተቀነባበረና አሥር በመቶ ጥሬ ሥጋ ለ80 አገሮች እያቀረበ እንደሚገኝ ገልጸው፣ ይህም የተገነባው ፋብሪካ የአገሮቹን የጤና ጥበቃዎችና ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን በማሟላት እየሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ ‹‹የጤና ችግር ከሌለባቸው በስተቀር በአሁን ወቅት እየሰበሰብን የምንገኘው ከአፋርና ከሶማሌ ክልል እንዲሁም ከቦረና አካባቢ ነው፡፡ እርግጥ እነዚህ አካባቢዎች ብዛት እንጂ ጥራት ላይ ትኩረት ስለማያደርጉ ወደፊት ሥልጠናና ምክር በመስጠት ከአቅራቢዎች ጋር ለመሥራት ዕቅድ ተይዟል፡፡ የመሬት ጥያቄው ከተመለሰልን ደግሞ በአቅራቢያችን ነጋዴዎች እያመጡልን እንረከባለን ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡ በፋብሪካው ከከብት ማስገቢያው ጀምሮ ፕሮሰስ ተደርጎ በካርቶን ታሽጎ ከግቢው እስከሚወጣ ያለው ሒደትና የንፅህና ሁኔታ በዶክተሮች የሚመራ ጥብቅ ክትትል ይደረግበታል፡፡  ለዚሁ ጉዳይ ብቻ የሚውል ላቦራቶሪ ተገንብቷል፡፡ ፋብሪካው ሙሉ ለሙሉ ኮምፒውተራይዝድ ማቀዝቀዣ ተገጥሞለታል፡፡ ፍሳሽ በምንም መልኩ ከግቢው አይለቀቅም፡፡ እዛው ይጣራል፡፡ የሠራተኛ አያያዝና ለአካባቢው ኅብረተሰብ የሚሰጠው ተጠቃሚነትም ተጠቃሽ ነው፡፡ ፋብሪካው በጊዜያዊነት 1500 ሠራተኞች ያሉ ሲሆን፣ ሙሉ በሙሉ ሥራ ሲጀምር 300 ሺሕ ሠራተኞች ይኖሩታል ተብሏል፡፡ ለእነዚህ ሠራተኞች የጤናና የሥራ ላይ ደኅንነትን ማረጋገጥ ግዴታችን ነው ያሉት የፋብሪካው ኃላፊ፣ ለአካባቢው ኅብረተሰብም ህንድ ላይ እንዳለው ፋብሪካ ሁሉ ደም ፕሮሰስ በማድረግ የሚገኘውን ሽያጭ ሙሉ በሙሉ ኅብረተሰቡ እንዲጠቀምበት ይደረጋል ብለዋል፡፡ ለአካባቢው ነዋሪዎች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እየገነባ እንደሚገኝም አክለው ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቁም እንስሳት አቅርቦት ችግር እንደሌለ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ በአንፃሩ የኤክስፖርት ቄራዎች የግብዓት ዕጥረት እንዳለባቸው ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ኃይለ ሥላሴ ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት ችግሩ እንዳለ አምነው፣ የአቅርቦት እጥረቱን ለመቅረፍ በቅርቡ የወጣው የቁም እንስሰት ንግድ አዋጅ ከፌዴራል እስከ ክልል ድረስ እንደሚተገበርና አሁን እየተካሄደ ያለው ሕገወጥ ንግድን ጨምሮ በዘርፉ ያሉ ሌሎች በርካታ ችግሮች እንደሚቀረፉ ጠቅሰዋል፡፡ ሆኖም ፋብሪካዎቹ የግብዓት ዕጥረት ካጋጠማቸው ወደ ውጭ የሚላከውን የቁም እንስሳት ንግድ እስከ ማስቆም ልንሄድ እንችላለን ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ከጥቂት ቀናት በኋላ ሥራ እንደሚጀምርና ወደ ኤክስፖርት እንደሚገባ የሚጠበቀው ጂግጂጋ ኤክስፖርት ቄራ ፋብሪካም በ200 ሚሊዮን ብር ሲያካሂድ የቆየውን ግንባታ ማጠናቀቁን ይፋ አድርጓል፡፡ በ35 ሔክታር መሬት ላይ የተንሠራፋውና በሶማሌ ክልል የተገነባው ይህ የኤክስፖርት ቄራ፣ ምርቱን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች እንደሚልክ ይጠበቃል፡፡ 

Standard (Image)

ለሦስት ወራት የተስተጓጎለው የጂፒኤስ አገልግሎት ተለቀቀ

$
0
0

የተሽከርካሪዎችን ሥምሪት ለመቆጣጠርና ተያያዥ ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችለውንና በአገሪቱ ሲተገበር የቆየው የጂፒኤስ ቴክኖሎጂ ከሦስት ወራት በላይ ሲስተጓጎል ቆይቶ ባለፈው ሳምንት በድጋሚ ሥራ መጀመሩ ተገለጸ፡፡

የተሽከርካሪዎችን ሥምሪት በዘመናዊ መንገድ ለማስተናበር የሚያስችለው ይህ አገልግሎት ተቋርጦ የነበረው በአስቸኳይ ጊዜ  አዋጁ ምክንያት ተሽከርሪካዎቹ ላይ የተገጠሙ ጂፒኤሶች የሚጠቀሙባቸው ሲምካርዶች በመዘጋታቸው ነበር፡፡

ተሽከርካሪዎቹ ላይ የተገጠሙት መሣሪያዎች መረጃዎችን የሚያስተላልፉት ከኢትዮ ቴሌኮም በሚያገኙት ሲም ካርድ ታግዘው ሲሆን፣ የጂፒኤስ ኔትወርክ አገልግሎት በመቋረጡ ሳቢያ ለሦስት ወራት እክል ተፈጥሮ ቆይቷል፡፡ አገልግሎቱ ኪሳራ ውስጥ እንደከተታቸውና ህልውናቸውን እንደተፈታተነው ቴክኖሎጂዎቹን የሚያቀርቡት ኩባንያዎች መግለጻቸውን መዘገባቸውን ይታወሳል፡፡

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ግን ተሽከርካሪዎች ላይ የተገጠሙት መሣሪያዎች ዳታ የሚያስተላልፉበት ሲም ካርድና የጂፒኤስ ኔትወርክ አገልግሎት ማግኘት በመቻላቸው የተስተጓጎለው አገልግሎት እየተስተካከለ መምጣቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይህንን ቴክኖሎጂ ከሚያቀርቡ ኩባንያዎች ያገኘነው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ በአሁኑ ወቅት ኢትዮ ቴሌኮም አቋርጦት የነበረውን የጂፒኤስ ኔትወርክ በመልቀቁ አገልግሎቱን ገዝተው ይጠቀሙ የነበሩ ኩባንያዎችና ግለሰቦች የተሽከርካሪዎቻቸውን ሥምሪት ዳግመኛ ለመከታተል አስችሏቸዋል፡፡

ከአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች በስተቀር ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ላይ የተገጠሙ መቆጣጠሪያና አቅጣጫ አመላካች መሣሪያዎች ዳታዎችን እያስተላለፉ እንደሚገኙም ተገልጿል፡፡ ከሦስት ወራት በፊት አገልግሎቱን ገዝተው ሲጠቀሙ የቆዩ ኩባንያዎች ተሽከርካሪዎቻቸው የት እንዳሉ ማወቅ ሳያስችላቸው በመቅረቱ፣ በሥራቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ከመፍጠሩም በላይ የቴክኖሎጂ አቅራቢ ኩባንያዎች ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሮ ነበር፡፡

የካሳ ኢንጅነሪንግ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሳ ሰለሞን እንደሚሉት፣ የአገልግሎቱ መስተጓጎል ቴክኖሎጂውን በሚያቀርቡት ኩባንያዎችና ቴክኖሎጂውን ሲጠቀሙ በነበሩት መካከል አለመግባባትን አስከትሎ ነበር፡፡

ለ28 አዲስ ተገልጋዮች ዘመናዊ አገልግሎት ለማስገባት የተደረጉ ስምምነቶች በእንጥልጥል እንዲቆዩና የአገልግሎት ክፍያዎችም እስከመቋረጥ በመድረሳቸው ችግሩን ለኢትዮ ቴሌኮምና ለመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለማሳወቅና መፍትሔ እንዲሰጣቸው እስከመማጸን ደርሰው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የኩባንያዎቹ ገቢ መቀዛቀዝ እሳቸው የሚያስተዳድሩት ኩባንያ ገቢ ላይ ተፅዕኖ በማሳደሩ፣ ሠራተኞች እስከመቀነስ የደረሰ ዕርምጃ በመውሰድ ድርጅቱን ለመታደግ ተገደው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

አሁን ግን ኢትዮ ቴሌኮም የኔትወርክ ስርጭቱን በመልቀቁ ኩባንያቸው ላለፉት ሦስት ወራት የተስተጓጎለበትን ሥራ በመቀጠል የቴክኖሎጂው ተጠቃሚዎች ወደ ሥራ የሚገቡበትን መንገድ አደላድሏል፡፡

አገልግሎቱ የተሽከርካሪዎችን ሥምሪት በቀላሉ ለማቀጣለፍ ከማስቻሉም በላይ ከፍጥነት ወሰን በላይ እንዳያሽከረክሩ፣ ባልተገባና ባልተፈቀደ ቦታ እንዳይቆሙ፣ በነዳጅ አጠቃቀምንና በመሳሰሉ ላይ የቁጥጥር ሥራዎች እንዲካሄዱ የሚያግዝ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ የተሽከርካሪዎች ባለቤቶችና ኩባንያዎች በሞባይል ስልኮችና በኮምፒውተር አማካይነት በቀላሉ ለመቆጣጠር የሚያስችላቸው ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በዚህ ዓይነቱ ቴክኖሎጂ ከ5,000 በላይ ተሽከርካሪዎች ጂፒኤስ ተገጥሞላቸው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

 

Standard (Image)

የሆላንዱ ሎቨር ግሩፕ ግማሽ ቢሊዮን ብር ኢንቨስት የተደረገበትን ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ሊያስተዳድር ነው

$
0
0

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁ የሆቴል ብራንዶች መካከል ወደ ኢትዮጵያ  በመምጣት አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ሆቴሎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶችም ለአገልግሎት የሚያውሏቸውን ሆቴሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ብራንድ ሆቴሎችን ከሚያስተዳድሩ ኩባንያዎች ጋር በመደራደርና ኩባንያዎቹ በሚጠይቁት መሥፈርት የሕንፃ ግንባታዎችንና ውስጣዊ ዲዛይኖችን አሟልተው እያደራጁ በጋራ መሥራት እየተለመደ መጥቷል፡፡

እንዲህ ያለውን መንገድ በመከተል ወደ ግንባታ የገቡና አገልግሎት እየሰጡ ካሉት ውስጥ ሒልተን፣ ጎልደን ቱሊፕ፣ ራዲሰን ብሉ፣ ራማዳ፣ ቦን፣ ማሪዮት፣ ዊንድሃምና ሌሎችም ሆቴሎች ይጠቀሳሉ፡፡ ከእነዚህ ባሻገርም ዓለም ላይ የሚታወቁበትን ስያሜ የያዙ ሆቴሎች እየተበራከቱ እንደሚመጡ ይታመናል፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአሁኑ ወቅት በተመሳሳይ መንገድ ኢንዱስትሪውን ለመቀላቀል ድርድር በማድረግ ላይ ያሉና ድርድራቸውን ወደ መገባደድ ላይ የተቃረቡ ከ60 ያላነሱ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ስማቸውን በዓለም የተከሉ ሆቴሎች ከአገር በቀል ባለሀብቶች ጋር እንዲሠሩና የማማከር ሥራ በመስጠት ከሚታወቁ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው ኦዚ ቢዝነስና ሆስፒታሊቲ ማኔጅመንት ግሩፕ ብቻ፣ ወደ 17 የሚደርሱ ሆቴሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ጋር በመደራደር ላይ መሆኑ አንድ ማሳያ ይሆናል፡፡  ከዚህ ቀደም በካሊብራ ሆስፒታሊቲ ኮንሰልታንሲና ቢዝነስ ኩባንያ አማካይነት ድርድሮችን አጠናቀውና ሆቴሎችን ገንብተው ሥራ ከጀመሩ መካከል ካፒታል ሆቴልና ስፓና ራማዳ አዲስ ይጠቀሳሉ፡፡ ካሊብራም እንደ ኦዚ ሁሉ በርካታ ፕሮጀክቶችን ወደ ተግባር ለማምጣት በማደራደር ላይ እንደሚገኝና ዱባይ ከሚገኘው አሌፍ የሆቴል አማካሪ ድርጅት ጋር በሽርክና መሥራት መጀመሩ የሚታወስ ነው፡፡

ሰሞኑን በኦዚ አማካሪነት ሎቨር የተባለው የኔዘርላንድስ ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለተኛው እንደሚሆን የሚጠበቀውን የሆቴል ፕሮጀክት ለማስተዳደር በጊዜ ቢዝነስ ግሩፕ ከተባለው አገር በቀል ኩባንያ ጋር ስምምነት አድርጓል፡፡ ሎቨር ኩባንያ ከሚያስተዳድራቸው ሆቴሎች መካከል ባለአምስት ኮከብ ደረጃ እንደሚኖረው የሚጠበቀው ‹‹ሮያል ቱሊፕ ፕላዛ አዲስ አበባ ሆቴል ሌግዤሪ ስታይል ኮሌክሽን›› የሚል መጠሪያ የተጠሰው ሆቴል ነው፡፡

የበጊዜ ቢዝነስ ግሩፕ ንብረት የሆነው ይህ ሆቴል፣ ከአውሮፓ ኅብረት ጽሐፈት ቤት ፊት ለፊት ደሳለኝ ሆቴል አካባቢ የሚገነባ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የግንባታ ሥራው ተገባዶ የማጠናቀቂያና የውስጥ ዲዛይንና ዲኮር ሥራዎች እየተከናወኑለት ይገኛል፡፡

ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ይጠይቃል የተባለው ይህ ሆቴል ከሎቨር ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት የሎቨርን የአምስት ኮከብ ደረጃ ሊይዝ ከቻለባቸው ምክንያቶች አንዱ ውስጣዊ የዲዛይን ሥራው ነው ተብሏል፡፡ ይህ የዲዛይን ሥራ ንጎያማ ኦክፓኔምና አጋሮቹ በተባለ ታዋቂ የደቡብ አፍሪካ ኩባንያ እየተካሄደ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

88 መኝታዎች የሚኖሩት ይህ ሆቴል ባለስምንት ወለል ሲሆን፣ የስብሰባ አዳራሽ፣ ስፓ፣ ሬስቶራንት፣ ባርና የመሳሰሉትን እንደሚያካትት በሁለቱ ተሻራኪዎች መካከል ስምምነት በተደረሰበት ወቅት ተገልጿል፡፡ በመጪው ዓመት ሥራው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ አገለግሎት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሎቨር ሆቴል ግሩፕ ሮያል ቱሊፕ ሌግዤሪ ኮሌክሽን ወይም ሮያል ቱ ሊፕ በሚል ብራንድ የሚጠሩ ባለአምስት ኮከብ ደረጃ ያላቸውን ሆቴሎች የሚያስተዳድር ነው፡፡ ጎልደን ቱ ሊፕ በሚል ስያሜ የሚጠሩ ሆቴሎች ባለአራትና አምስት ኮከብ ደረጃ ያላቸው ሲሆኑ፣ በሦስተኛ ደረጃ የሚቀመጡት ደግሞ ቱሊፕ ኢን በመባል የሚታወቁት ናቸው፡፡ ቱሊፕ ኢን ሆቴሎች ባለሦስት ኮከብ ያላቸው እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሎቨር ሆቴል ግሩፕ ሦስት ብራንዶችን በመያዝ በ45 አገሮች 240 ሆቴሎችን በማስተዳደር ላይ የሚገኝ ኩባንያ ነው፡፡

Standard (Image)

የአወዛጋቢው ጊቤ ሦስት አንደምታዎች

$
0
0

በደቡብ ክልል ከሚገኙ 14 አስተዳደራዊ ዞኖች መካከል የዳውሮ ዞን አንዱ ነው፡፡ የዳውሮ ዞን ከጂማ ዞን ጋር በጎጀብ ወንዝ፣ ከወላይታ ዞን ደግሞ በጊቤ (ኦሞ) ወንዞች ይዋሰናል፡፡

እነዚህ ሁለት ትላልቅ ወንዞች በዳውሮ ምድር ላይ ተቀላቅለውና ኦሞ ወንዝ የሚል ስያሜ አግኝተው በኢትዮጵያና በኬንያ ድንበር ላይ ወደሚገኘው ቱርካና (ሩዶልፍ) ኃይቅ ይፈሳሉ፡፡

በእነዚህ ሁለት ትላልቅ ወንዞች ላይ ተሽከርካሪዎችን የሚያስተላልፉ ድልድዮች ቀደም ባሉት ጊዜያት ባለመገንባታቸው ዞኑ ለበርካታ ዓመታት ከሌሎች አጎራባች አካባቢዎች ተገልሎ እንደቆየ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ዘግይቶም ቢሆን በሁለቱ ወንዞች ላይ ተሽከርካሪዎችን የሚያስተላልፉ ድልድዮች ቢገነቡም፣ የዳውሮ ዞንን ከጂማም ሆነ ከወላይታ ዞኖች ጋር የሚያገናኙ መንገዶች ባለመገንባታቸው ዞኑ ከአጎራባች አካባቢዎች ጋር የሚገናኘው በጋማ ከብቶች፣ በእግር ጉዞና በአውሮፕላን ነበር፡፡

ወታደራዊው ደርግ ከመውደቁ ሁለት ዓመት ቀደም ብሎ በ1981 ዓ.ም. የዞኑ ተወላጅ የሆኑት አቶ በለጠ ባሹ የዳውሮ ገዥ ሆነው ተሾሙ፡፡ በአሁኑ ወቅት የ64 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋና የአገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ በለጠ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በብዙ ውጣ ውረድ በወቅቱ ከነበረው የሰሜን ኦሞ አስተዳደር ዶዘርና ግሬደር በውሰት በመውሰድ ወላይታን ከዳውሮ የሚያገናኝ መንገድ አስጠርገዋል፡፡ ይህ መንገድ በ1982 ዓ.ም. ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡

በተመሳሳይም በምዕራብ አቅጣጫ ዳውሮን ከጂማ የሚያገናኝ መንገድም ጠረጋ ተካሂዷል፡፡ አቶ በለጠ እንደሚናገሩት እነዚህ መንገዶች በብዙ ድካም ከተከፈቱ በኋላ በወቅቱ ዳውሮ ውስጥ ተሽከርካሪ ያለው አንድም ሰው ባለመኖሩ ሌላ ችግር ነበር፡፡

‹‹የዳውሮ ዞን ተወላጅ የሆኑ አራት ባለሀብቶችን አስተባብሬ አንድ ላንድሮቨር ተሽከርካሪ አስገዝቼ ወደ መስመር አስገባሁ፤›› ሲሉ አቶ በለጠ ከ20 ዓመት በፊት የዳውሮ ዞን የነበረበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ያስታውሳሉ፡፡

በዓባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ እስኪጠናቀቅ ድረስ በኢትዮጵያ ትልቁ ሆኖ የሚቆየው የግልገል ጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በተለይ ለዳውሮና ለወላይታ ዞኖች ብዙ ለውጥ አምጥቷል፡፡ ይህ ፕሮጀክት 220 ኪሎ ሜትር መንገድ በሁለቱ ዞኖች ውስጥ ባሉ ወረዳዎች እንዲዘረጋ አድርጓል፡፡ በወላይታ ዞን መቀመጫ ሶዶ ከተማ እስከ ዳውሮ ዞን መቀመጫ ተርጫ ከተማ የአስፓልት መንገድ እንዲዘረጋ ምክንያት ሆኗል፡፡

ከ20 ዓመታት በፊት በመንገድ ጠረጋ ውጣ ውረድ ውስጥ ያለፉት አቶ በለጠ አሁን ያለው ለውጥ ተዓምር ሆኖባቸዋል፡፡ ‹‹በሕይወት እያለሁ ከሁሉም አካባቢዎች ኋላ ቀርቶ የቆየው ዳውሮ ዞን ብርሃን ሲፈነጥቅለት በመመልከቴ ፈጣሪን አመሰግናለሁ፤›› ይላሉ የዕድሜ ባለፀጋው አቶ በለጠ፡፡

ቅዳሜ ታኅሳስ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. በይፋ ተመርቆ ሥራ የጀመረው የጊቤ ሦስት ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ፣ ሐምሌ 1998 ዓ.ም. በወላይታና በዳውሮ ዞኖች ድንበር ላይ ነበር ግንባታው የተጀመረው፡፡ ከአዲስ አበባ በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ 450 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ይህ ፕሮጀክት መጀመሩ ከዚህ ቀደም በጎጀብ ወንዝ ላይ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ይገነባል ተብሎ፣ ነገር ግን ይህ ዕቅዱ በመታጠፉ ለተቆጩ የዳውሮ ሕዝቦች ትልቅ የምሥራች ነበር፡፡

ይህ ግድብ 246 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን፣ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ቁመት ካላቸው ኃይል ማመንጫ ግድቦች ተርታ ይሰለፋል፡፡

‹‹በኮንክሪት ሙሌት (RCC) ቴክኖሎጂን በመጠቀም በዘመናዊ የምህንድስና ጥበብ የተገነባ ነው፤›› ሲሉ የግልገል ጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ በምርቃቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡

ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በአጠቃላይ አሥር ኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ያሉት ሲሆን፣ እያንዳንዳቸው 187 ሜጋዋት፣ በድምሩ 1,870 ሜጋዋት ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም አለው፡፡

ይህንን ግዙፍ ፕሮጀክት የሲቪል ሥራዎቹን የጣሊያኑ ሳሊኒ ኢምፕሬጂሎ አካሂዷል፡፡ በኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት አሥርት ዓመታት በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ያካሄደው ሳሊኒ፣ የጊቤ ሦስትን ፕሮጀክት በስኬት አጠናቋል፡፡

የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎችን የቻይናው ግዙፍ ኩባንያ ዶንግ ፉንግ ግሩፕ አክናውኖታል፡፡ የማማከር አገልግሎት የሰጡት የጣልያንና የፈረንሣይ ጥምር ኩባንያዎች የሆኑት ኢኤልሲ፣ ኤሌክትሮ፣ ኮንሰልትና ትራክተብል ኢንጂነሪንግ ናቸው፡፡ ከጊቤ ሦስት የሚመነጨው ኃይል የሚያስተላልፉና የሚያከፋፍሉ ፕሮጀክቶችን ደግሞ ቲቢኢኤ እና ሻንጋይ ኤሌክትሪክ ኩባንያዎች አካሂደዋል፡፡

ለኃይል ማመንጫ ግንባታው 1.5 ቢሊዮን ዩሮ ወጪ የተደረገ ሲሆን፣ ይህ ገንዘብ 60 በመቶ ከቻይና መንግሥት በተገኘ ብድር፣ 40 በመቶ ደግሞ በኢትዮጵያ መንግሥት ተሸፍኗል፡፡ የጊቤ ሦስት ፕሮጀክት በዳውሮና በወላይታ ዞን ውስጥ በርካታ መንገዶች እንዲገነቡ አድርጓል፡፡ በአጠቃላይም ከወላይታ ሶዶ ከተማ እስከ ኦሞ ድልድይ፣ ከኦሞ ድልድይ እስከ ዳውሮ ዞን ተርጫ ከተማ ድረስ ያለው መንገድ ግንባታ ተጀምሯል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ይህ መንገድ በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ በአስፓልት ደረጃ እየተገነባ ነው፡፡ ግንባታውን ሁናን ሁንድ እና ቻይና ሬልዌይ ግሩፕ እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ከዋናው የፌዴራል መንግሥት መንገድ ፕሮጀክት በተጨማሪ የሁለቱን ዞኖች ወረዳዎች የሚያገናኙ ከ220 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው መንገዶች መገንባታቸው በወቅቱ ተገልጿል፡፡

በዳውሮ ዞን አምስት ወረዳዎችና አንድ የከተማ አስተዳደር ይገኛል፡፡ ግድቡ በፈጠረው ሐይቅ በተለይ በሁለቱ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ 19 ቀበሌዎችን ይነካል፡፡

በወላይታ ዞን ደግሞ 12 ወረዳዎችና ሦስት የከተማ አስተዳደሮች ይገኛሉ፡፡ ሦስቱን ወረዳዎች ግድቡ የፈጠረው ሐይቅ ይነካል፡፡ በአጠቃላይ የጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጫ ግድብና ግድቡ የፈጠረው ኃይልና አጠቃላይ ተፋሰስ (ካችመንት) 34,150 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡

የዳውሮ ዞን ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዳለቾ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የጊቤ ሦስት ፕሮጀክት በመንገድ አውታር ዝርጋታ ለዞኑ ተወላጆች የሥራ ዕድል፣ የዓሣ ሀብትና ነፋሻ አየር አምጥቷል፡፡

‹‹ይህ ክስተት ትልቅ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች አሉት፤›› ሲሉ ፕሮጀክቱ ያስገኘውን ጥቅም ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ይህ የኦሞ ሸለቆ በጣም ሞቃታማ ነበር፡፡ በሌሎች ዓመታት በተለይ ከኅዳርና ታኅሳስ ወር ጀምሮ ከብቶች የመኖ እጥረት ይገጥማቸዋል፡፡ ከዚህ በዘለለም በአካባቢው ምርታማነት የቀነሰ በመሆኑ፣ በሴፍቲኔት ፕሮግራም የታቀፈ አካባቢ ነው፡፡

አቶ ብርሃኑ እንደሚናገሩት የሐይቁ መፈጠር አካባቢው ነፋሻ አየር እንዲኖረው በማድረጉና መሬቱም እርጥበት እያገኘ በመሆኑ፣ ለግብርና ሥራ አመቺ ሁኔታ እየፈጠረ ነው፡፡ የዓሣ ሀብትም እንዲሁ ጥቅም ላይ መዋል ጀምሯል፡፡ ፕሮጀክቱ በርካታ ጀልባዎችንና የውኃ መሳቢያ ፓምፖችንም ለአካባቢው ማኅበረሰብ በማበርከቱ የተለያዩ ለውጦች እየመጡ መሆናቸውን አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡

አቶ መስፍን ኩማ የወላይታ ዞን ዳሞት ሶሬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ናቸው፡፡ አቶ መስፍንም የአቶ ብርኑን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ አቶ መስፍን ለሪፖርተር እንደገለጹት ከዳውሮ ዞን ጋር በርካታ የሚጋሯቸውን ዕሴቶች ቢኖሩም፣ የመንገድ አውታር ባለመኖሩ ግንኙነታቸው ተገድቦ ቆይቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ግን በየብስ ብቻ ሳይሆን በጀልባ ጭምር መገናኘትና መገበያየት ጀምረዋል፡፡ ግድቡ የፈጠረው ሐይቅ ነፋሻ አየርና እርጥበት ይዞ በመምጣቱም በግብርና ሥራ ላይ መነቃቃት መፈጠሩን አቶ መስፍን ተናግረዋል፡፡

ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በመንገድ አውታር፣ በአየር ፀባይ ለውጥ፣ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ፣ ለሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ቢያበረክትም፣ አሁንም ግን በሁለቱም ዞኖች በርካታ አካባቢዎች ኤሌክትሪክ አቅርቦት እያገኙ አለመሆኑ ታይቷል፡፡ ጊቤ ሦስት በሙሉ አቅሙ ኢኮኖሚውን እየረዳ አለመሆኑም ታውቋል፡፡ ጊቤ ሦስት ኤሌክትሪክ ኃይል ግድቡ በተለይም ሁለቱ (ጊቤና ጎጀብን) ከምዕራብ ኢትዮጵያ ተራሮች የሚመነጩ ወንዞች በማግኘቱ ይህን አካባቢ የ2008 ድርቅ ያልነካው በመሆኑ በክረምቱ ወራትም በቂ ዝናብ በመኖሩ ግድቡ በቂ ውኃ ይዟል፡፡

እያንዳንዳቸው 187 ሜጋዋት የሚያመነጩት አሥሩ ተርባይኖች በሙሉ እንደሚሠሩ ተረጋግጧል፡፡ ነገር ግን ማመንጫ ጣቢያው በማመንጨት ላይ ያለው ኃይል ማመንጨት ከሚችለው በግማሽ ያነሰ (900 ሜጋዋት) ነው፡፡

የጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጫ ኦፕሬሽን ኦፊሰር ቡድን መሪ አቶ ንጉሤ ማሙሻ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አሥሩም ተርባይኖች ይሠራሉ፣ እያመነጨን የምንገኘው ግን 900 ሜጋዋት ኤሌክትሪክ ነው፡፡ ‹‹ይህንን ኤሌክትሪክ ተርባይኖቹን እየቀያየርን እናመርታለን፤›› ሲሉ አቶ ንጉሤ ተናግረዋል፡፡

‹‹የመሠረተ ልማቶች ተገንብተው ባለማለቃቸው ጣቢያው ማመንጨት የሚቻለውን በሙሉ ማመንጨት አልቻልንም፤›› ሲሉ አቶ ንጉሤ ገልጸዋል፡፡ የጊቤ ሦስት ኃይል መንጫ ጣቢያ የሚያመነጨውን ኃይል ለማስተላለፍና ለማሠራጨት የሚያስችሉ አውታሮች ተገንብተዋል፡፡ ከማመንጫ ጣቢያው እስከ ሶዶ ከተማ ከዚያም እስከ አዲስ አበባ ከተማ ድረስ 401 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍን ባለ 400 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተዘርግቷል፡፡ ከዚሁ ጋርም በሶዶና በአዲስ አበባ ከተማ 11 አዳዲስ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ተገንብተዋል፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ግን የኤሌክትሪክ ፍላጎት ላላቸው ኢንዱስትሪዎች የእርሻ ፕሮጀክቶችና ወደመሳሰሉ ፕሮጀክቶች መስመሮችና ማከፋፈያዎች ባለመዘርጋታቸው ጊቤ ሦስት ማመንጨት ያለበትን ያህል እንዲያመነጭ አድርጎታል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ ኃይል የማመንጨት አቅም አደገ ማለት ኤሌክትሪክ ለተጠቃሚው ማድረስ ተቻለ ማለት አይደለም፡፡

‹‹በመሀል ብዙ ነገሮች አሉ፤ ኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮች፣ ማሠራጫ ጣቢያዎች መኖር አለባቸው፡፡ እዚህ ጋ ጉድለት ካለ ማሠራጨት አይቻልም፡፡ እነዚህን መሠረተ ልማቶች ለማሟላት ጎን ለጎን እየሠራን ነው፤›› ሲሉ ኢንጂነር አዜብ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያን በታሪኳ ገጥሟት በማያውቅ ደረጃ ባለፈው 2008 ዓ.ም. ሰፊ ቦታ የሚሸፍን ድርቅ አጋጥሟት ነበር፡፡ ድርቁ የ10.2 ሚሊዮን ዜጎችን የምግብ ዋስትና ከማናጋቱ በላይ የኃይል ማመንጫ ግድቦች በቂ ውኃ መያዝ ባለመቻላቸው የኤሌክትሪክ አቅርቦት ጥያቄ ውስጥ ወድቆ ነበር፡፡

ነገር ግን ጊቤ ሦስት በወሳኝ ወቅት በመድረሱ ሊፈጠር የነበረውን የኤሌክትሪክ እጥረት የሸፈነ የቁርጥ ቀን ፕሮጀክት ሆኗል፡፡

ጊቤ ሦስት ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የግንባታ ሒደት ግን አልጋ ባልጋ አልነበረም፡፡ ፕሮጀክቱ ከጥንስሱ ጀምሮ በርካታ ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን፣ ተቃውሞው ጠንካራና ያልተቋረጠ ስለነበር ፕሮጀክቱን ፋይናንስ ለማድረግ ይሁንታ አሳይተው የነበሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር ቃላቸውን አጥፈዋል፡፡

ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ሐምሌ 1998 ዓ.ም. አፈር ቆረጣ ሲጀምር በተለይ ኢንተርናሽናል ሪቨርስ ግሩፕና ኦክላንድ ኢንስቲትዩት ጊቤ ሦስት የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ያልተደረገለት ነው በሚል የታችኛው ተፋሰስ ሕዝቦችን እንደሚጎዳና አኗኗራቸውንም እንደሚቀይር፣ በኢትዮጵያና በኬንያ ድንበር ለሚገኘው ቱርካና ኃይቅ ዋነኛ ገባር ወንዝ እንደመሆኑ ሐይቁ ላይ ኑሯቸውን ለመሠረቱ ኬንያውያን ጉዳት የሚያደርስ መሆኑን በመጥቀስ ዘመቻ ከፍተው ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በዳውሮ የሚገኘውን የጥቃት መከላከያ ግንብ ቅርስ በመሆኑ ፕሮጀክቱ ይህንን ቅርስ ያጠፋል የሚል ተቃውሞም ቀርቦ ነበር፡፡

ዘመቻው የተቀናጀና ተከታታይ ስለነበር ይህንን ፕሮጀክት ፋይናንስ ለማድረግ ፍላጎት አሳይተው የነበሩት የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክና ጄፒ ሞርጋን ባንክ ሐሳባቸውን በመቀልበስ ፋይናንስ ማድረጋቸውን ሰርዘዋል፡፡

ኢንጂነር አዜብ የተከፈተው ዘመቻ በተወሰነ ደረጃ በፕሮጀክት መጓተት ላይ ተፅዕኖ ማሳረፉን ተናግረዋል፡፡

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ይህ ፕሮጀክት በየትኛውም መመዘኛ ለሁለቱም አገሮች ሕዝቦች ጥቅም እንጂ ጉዳት የሌለው መሆኑን በመግለጽ፣ በየትኛውም መስዋዕትነት ቢሆን ግንባታው እንደሚካሄድ አስረግጠው ተናግረው ነበር፡፡

የጊቤ ሦስት ከፍተኛው ወጪ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራው እንደመሆኑ ዕቃዎቹ በሙሉ በውጭ ምንዛሪ ከውጭ ስለሚገቡ የግድ ብድር ያስፈልግ ነበር፡፡ ሳሊኒ የሚያካሂደው የሲቪል ሥራ በኢትዮጵያ መንግሥት ወጪ የተሸፈነ በመሆኑ፣ ይህ ሥራ ቀጥሎ ብድር ማፈላለጉ ጎን ለጎን ቀጠለ፡፡

ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ የቻይናው ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኩባንያ ዶንግ ፋንግ ግሩፕ ወደ ኢትዮጵያ መጣ፡፡ ኩባንያው ፕሮጀክቱን ካጠና በኋላ ከራሱ አገር የገንዘብ ምንጮች ፋይናንስ ይዞ በመምጣት ሥራውን ተረክቧል፡፡

ብድሩን የቻይና መንግሥት ኢንዱስትሪያልና ኮሜርሻል ባንክ (ICBC) በማቅረብ ዶንግ ፋንግ ግሩፕ ሥራውን ተረክቦ ወደ ግንባታ ሲገባ በኢትዮጵያ በኩል ደስታ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ እንዲሰረዝ ሲወተውቱ ለቆዩ መያዶች የሚዋጥ ሐቅ አልነበረም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባለፈው ቅዳሜ ታኅሳስ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ይህ ፕሮጀክት በተመረቀበት ወቅት፣ ‹‹ይህ ፕሮጀክት በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ ያለፈ ነው፤›› ሲሉ ፕሮጀክቱ ያለፈበትን አስቸጋሪ መንገድ አስታውሰዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጨምረው እንደገለጹት፣ ከ20 ዓመት በፊት 180 ሜጋዋት የሚያመነጭ ፕሮጀክት ለመተግበር እንቅስቃሴ ውስጥ ሲገባ ለምናችሁ ነው ይኼ ሁሉ ኃይል መባላቸውን አስታውሰው፣ አሁን ግን አምስት ሺሕ ሜጋዋት ኤሌክትሪክ ለማመንጨት ቢቃረቡም ይህም በቂ እንዳልሆነና የኃይል ማመንጫ ግንባታ በጥልቀት እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ጊቤ ሦስትን ጨምሮ በአጠቃላይ 4,138 ሜጋዋት ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም ላይ ደርሳለች፡፡ ከተሞች ኢንዱስትሪዎች፣ የግብርና ፕሮጀክቶች በሙሉ በመስፋፋት ላይ ሲሆኑ፣ የኤሌክትሪክ ፍላጎቱም በዚያው ልክ በማደግ ላይ ይገኛል፡፡

ለአብነት ያህል በ2007 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ከተማ ብቻውን 150 ሜጋዋት መጠቀም የጀመረ ሲሆን፣ የተለያዩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እያንዳንዳቸው ከመቶ ሜጋዋት በላይ እንዲሰጣቸው እየጠየቁ ይገኛሉ፡፡

የዚያኑ ያህልም ጎረቤት አገሮችም ጂቡቲ፣ ሁለቱ ሱዳኖች፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያና የመሳሰሉት የአፍሪካ አገሮች፣ በሌላ በኩል የመንና ሳዑዲ ዓረቢያ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ የሚፈልጉና ያገኙ አገሮች ናቸው፡፡

መንግሥት የወደፊቱን ፍላጎት በማገናዘብ በአሁኑ ወቅት ሁለት ፕሮጀክቶችን በይፋ ለመጀመር እየተዘጋጀ ነው፡፡ እነሱም የባሮ አኮቦ ተፋሰስ የሆነው የገባ ወንዝና የጊቤ ኦሞ ቀጣይ ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ የኮይሻ ፕሮጀክት በዳውሮ ዞንና በኮንታ ልዩ ወረዳ መካከል ይገኛል፡፡ ፕሮጀክቱ 2,160 ሜጋዋት ኤሌክትሪክ ያመነጫል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ሳሊኒ ይህን ፕሮጀክት በይፋ ባይረከብም፣ የተለያዩ ዝግጅቶች ከማድረግ አልፎ የአፋር ቆረጣ ውስጥ መግባቱን ከአካባቢው የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ይህ ፕሮጀክት ለሳሊኒ የሚሰጠው ፋይናንስ እንዲገኝ ካደገ ብቻ መሆኑን ገልጿል፡፡ በዚህ መሠረት ሳሊን ብድር ማግኘት ቢችልም፣ ብድር አቅራቢው ባንክ ከመንግሥት ጋር የሚያደርገውን ድርድር ባለማጠናቀቁ በይፋ ወደ ሥራ አልተገባም፡፡

የዳውሮ ዞን የአገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ በለጠ ከጊቤ ሦስት ባሻገር የኮይሻ ፕሮጀክትም በዞኑ ውስጥ እንደሚካሄድ በመወጠኑ በጨለማ ውስጥ ለቆየው ዳውሮና ለመላው ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ትልቅ ተስፋ አለው ይላሉ፡፡ 

Standard (Image)

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ አራት መቶ ሺሕ ብር የሚጠጋ የሰብል መድን ካሳ ክፍያ መፈጸሙን አስታወቀ

$
0
0

- ለሰብልና ለእንስሳት ካሳ እስካሁን ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ መፈጸሙን ገልጿል

የኦሮሚያ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር በአገሪቱ ለሚገኙ ዋና ዋና አምራች አካባቢዎች ከሰባት ዓመት ወዲህ የሰብል መድን ሽፋን መስጠት መጀመሩን አስታውሶ፣ በዚህ ዓመት በዝናብ እጥረት ምክንያት የሰብል ምርታቸው ላይ ጉዳት ለደረሰባቸው ገበሬዎች 380 ሺሕ ብር የሚጠጋ የመድን ካሳ ክፍያ መፈጸሙን አስታወቀ፡፡

የመድን ድርጅቱ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን፣ በአዳሚ ቱሉ እና በጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳዎች ውስጥ ነዋሪ ለሆኑ 400 ገበሬዎች በዝናብ እጥረት ምክንያት የመድን ካሳ ክፍያ ተፈጽሞላቸዋል፡፡

በተያዘው ዓመት ብቻ ከ4400 በላይ የሰብል አረቦን የሸጠው ኦሮሚያ ኢንሹራንስ፣ የመድን ሽፋኑን የገዙት በአብዛኛው ጤፍ፣ በቆሎና ስንዴ አምራቾች መሆናቸውም ታውቋል፡፡ ባለፈው ዓመት በኤልኒኖ ምክንያት በተከሰተው ድርቅ ሰብሎቻቸውን ላጡ ገበሬዎች አንድ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ካሳ መክፈሉን አስታውቋል፡፡

በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ጉዳት ለሚደርስባቸው ሰብሎች መድን መስጠት ከተጀመረ ጀምሮ፣ የጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ)ን ጨምሮ በርካታ የረድዔት ድርጅቶች በሚሰጡት ድጋፍ አማካይነት የሰብል ምርትና የእንስሳት ሀብት የመድን ሽፋን መስጠት እየተዘወተረ መምጣቱ የሚታወቅ ነው፡፡

በ48 የኦሮሚያ ገጠር ቀበሌዎች ውስጥ የሰብል መድን ሸፋን እየሰጠ የሚገኘው ኦሮሚያ ኢንሹራንስ፣ ከአንድ መቶ ብር ጀምሮ አምራቾች እስከቻሉት ድረስ መግዛት የሚችሉበትን የሰብል የመድን አረቦን እንደሚሸጥ አስታውቋል፡፡ አገልግሎቱን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለሰጠው የሰብል መድን ሽፋን፣ የአራት ሚሊዮን ብር ካሳ ክፍያ መፈጸሙን መድን ኩባንያው ይፋ አድርጓል፡፡

 

 

 

Standard (Image)

የጎመን ዘር ለእንስሳት መኖነትና ለፀረ ተባይ ማጥፊያነት ሊውል ነው

$
0
0

ኢትዮጵያዊ ስያሜ ያለውና ከመነሻውም በኢትዮጵያ መገኘቱ የሚታመነው ጎመን ዘር፣ በሳይሳዊ አጠራሩ ብራሲካ ካሪናታ፣ አቢሲኒያን ሬፕ፣ አቢሲኒያን ሙስታርድ አለያም ኢትዮጵያም ሙስታርድ እንደሚባል መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ባሻገር በበርካታ አገሮች የሚበቅለው ይህ ተክል፣ ለምግብ ዘይትነት በፋብሪካዎች ተጨምቆ ለገበያ እየዋለ ይገኛል፡፡ በተክል ዝርያነት የሚፈረጀው የጎመን ዘር፣ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው መስክ የባዮፊውል ነዳጅ ሊመረትበት ምርምር ሲደረግበት ቆይቷል፡፡ ከአራት ዓመታት በፊትም የመጀመሪያው የሙከራ በረራ ከጎመን ዘር በተመረተ ነዳጅ መደረጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

እርግጥ እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ አቪዬሽን ኢንዱስትሪው ከዕፅዋትና አትክሎቶች ብስባሽ የሚሰናዳ ነዳጅ መጠቀም እንደጀመረ የሚጠቁሙ መረጃዎች ሲወጡ ቆይተዋል፡፡ ግሪን ፍላይት ኢንተርናሽናል፣ ቨርጂን አትላንቲክ፣ ኤር ኒውዚላንድ፣ ኮንቲኔንታል ኤርላይንስ፣ ጃፓን ኤርላይንስ እንዲሁም የአሜሪካ አየር ኃይልን ጨምሮ በርካታ አየር መንገዶች ከወዳደቁ ዕፅዋትና ብስባሾች፣ ከአልጌ፣ ከጉሎ፣ ከጃትሮፋና ከመሳሰሉት የሚመረተውን ነዳጅ መጠቀም መጀመራቸው ታውቋል፡፡ የጎመን ዘርም ለአውሮፕላን ነዳጅ እየዋሉ ካሉ ውጤቶች መካከል እየተቀላቀለ መጥቷል፡፡

የዚህ ሁሉ መነሻው ከሰሞኑ ይፋ የተደረገ የጥናት ውጤት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቅመማ ቅመም ፋብሪካ ላለፉት ስምንት ዓመታት ምርምር ሲያደርግበት እንደቆየ የገለጸው ውጤት ይጠቀሳል፡፡ ከጎመን ዘር ተረፈ ምርት የሚያዘጋጃቸውን የእንስሳት መኖ እንዲሁም ሰብል ለመቆጣጠር የሚያስችል፣ ፀረ ተባይ ከጎመን ዘር ተረፈ ምርት በማምረት ወደ ገበያ ለማውጣት መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ቅመማ ቅመም ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅና የምርምር ቡድኑ መሪ አቶ ፈለቀ ስብኃቱ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ዘይት ተጨምቆበት ተረፈ ምርቱ ይደፋ የነበረው የጎመን ዘር አሁን ለእንስሳት መኖነትና ለፀረ ተባይ ርጭት የሚውል ምርት በፋብካው ተቀናብሮ ለገበያ የሚውልበት ምዕራፍ ላይ መደረሱንም የቡድኑ መሪ ተናግረዋል፡፡

 ለምግብነት መዋል የማያስችለው የመርዛማነት ይዘቱ የተወገደለትና የቅባት ይዘቱ የወጣለት የጎመን ዘር መኖ (Detoxified and Defatted Ethiopian Mustard Mill) መዘጋጀቱ፣ በየዓመቱ እንደሚደፋ የሚገመተው ከ400 እስከ 500 ሺሕ ኩንታል ተረፈ ምርት መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል ያደርገዋል፡፡ በተለይ በዶሮ እርባታ መስክ እስከ 70 ከመቶ የሚደርሰውን የኢንቨስትመንት ወጪ የሚሸፍነውን የመኖ ፍጆታ ለመቀነስ እንደሚያስችል አቶ ፈለቀ ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ፈለቀ ማብራሪያ፣ እስካሁን ድረስ በመርዛማ ይዘቱ ለምግብነት እንዳይውል ያደረገው ተረፈ ምርት (ኤክስፔለር ኬር) እንዲሁ ሲደፋ ቢቆይም፣ 46 ከመቶ የፕሮቲን ንጥረ ነገር ይዘት እንዳለው በጥናት መረጋገጡን ጠቁመዋል፡፡ ይህ ደግሞ አኩሪ አተርን ጨምሮ በርካታ ግብዓቶችን ለመተካት የሚያስችል አቅም እንዳለው ማረጋገጫ መስጠቱን ያብራራሉ፡፡ የጎመን ዘር ተረፈ ምርት ከሥጋና የሥጋ ተረፈ ምርት ከሆኑ ምንጮች የሚገኘውን መኖ ለመተካት የሚያስችል የፕሮቲን ይዘት በመያዙ ተመራጭ እንደሚያደርገውም ተገልጿል፡፡

ይህንኑ የምርምር ውጤት ለገበያ ለማቅረብ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ሲገልጹም፣ በአሁኑ ወቅት በሙከራ ደረጃ በቀን 40 ቶን የእንስሳት መኖ ከጎመን ዘር ተረፈ ምርት የሚያመርቱ ሁለት ፋብሪካዎች ሥራ መጀመራቸውን፣ ዋናው ፋብሪካም በብዛት ለማምረት እየተዘጋጀ እንደሚገኝ አቶ ፈለቀ አብራርተዋል፡፡

የምርምር ውጤቱ ለዶሮ አርቢዎችና አምራቾች ማኅበር አባላት ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ በተደረገበት ወቅት፣ ከመኖ ባለሙያዎችና ከፋብሪካዎች የተነሳው ጥያቄ ጥራቱና የአቅርቦቱን አስተማማኝነት በሚመለከት ነበር፡፡ አዲሱ ምርት እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያበቃ ዝግጅት እንደተደረገበት፣ የጥራት ጥያቄውም ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት እንደተሰጠው ተናግረዋል፡፡ በቅርቡ የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነት መብት ማረጋገጫ ዕውቅና እንደሚያገኝና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የእንስሳት መድኃኒትና ምግብ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ምርቶቹን በማስመዝገብ ፈቃድ ለማግኘት እየተዘጋጀ እንደሚገኝ አቶ ፈለቀ ገልጸዋል፡፡

በአርሲና በባሌ አካባቢ በሚኖሩ ገበሬዎች ማሳዎች ውስጥ በተደረገ ጥናት፣ ስንዴና ገብስ በሚያመርቱበት ወቅት የጎመን ዘር በማሳዎቻቸው ዙሪያ እንደሚዘሩ፣ ይህም ተባዮችን ለመከላከል በማሰብ የሚያደርጉት እንደሆነ የተብራራ ሲሆን፣ ከሌሎች ለመኖነት ከሚውሉ ተክሎች ይልቅ የጎመን ዘር ለዚህ ተግባር የሚውለው ግሉሲኖኔት የተባለው መርዛማ ይዘት በውስጡ ስለሚገኝ ነው፡፡ ይህንን መርዛማ ይዘት በማውጣት ለፀረ ተባይ ማምረቻነት እንዲውል በማድረግ የኬሚካል ውጤቶችን ለመተካት እንደሚውል ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ቅመማ ቅመም ፋብሪካ ከ45 ዓመታት በፊት በአሜሪካውያን የተቋቋመ ሲሆን፣ በመንግሥት ተወርሶ ሲተዳደር ከቆየ በኋላ ከስምንት ዓመታት በፊት በአሁኑ የፋብሪካው ባለንብረት እጅ በአቶ አካሉ ገለታ ባለቤትነት እየተዳደረ ይገኛል፡፡ አቶ አካሉና ቤተሰቦቻቸው የሚመሯቸው ሌሎችም እህት ኩባንያዎች ይጠቀሳሉ፡፡

በሎጂስቲክስ መስክ በመርከብ አስተላላፊነት የሚታወቀው አካካስ ሎጂስቲክስ ኩባንያ፣ ጊፍቲ ቅመማ ቅመም፣ ጊፍቲ ዘይት፣ ጊፍቲ ዱቄት የተባሉ ምርቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን ጨምሮ በ420 ሔክታር መሬት ላይ አኩሪ አተርና በቆሎ የሚያመርትበት እርሻ በወለጋ ዞን እንዳለውም የፋብሪካው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በሁለት ሚሊዮን ብር ካፒታልና በ20 ሚሊዮን ብር ሀብት የሚንቀሳቀሰው ቅመማ ቅመም ፋብሪካው፣ የጨው ማጣሪያና ማምረቻ ፋብሪካን ጨምሮ በደቡብ ክልል፣ አረቃ ወረዳ ወላይታ ዞን ውስጥ የሚያስተዳድረው የፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ማቀነባበሪያም ከሚጠቀሱ እህት ኩባንዎቹ መካከል ይመደባሉ፡፡

 

                                                         

Standard (Image)

የተከማቸ ዕዳ እያለባቸው ተጨማሪ 1.7 ቢሊዮን ብር የተለቀቀላቸው ቡና አቅራቢያዎች

$
0
0

የደቡብ ክልል ቡና አቅራቢዎች ያጋጠማቸውን ኪሳራ በማስመልከት ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ በፋይናንስ ኢንዲስትሪው ውስጥ እንግዳ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ሰኔ 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ይፋ ያደረገው መመርያ፣ በባንክ ዘርፉ ውስጥ ያለተለመደ ስለነበር ጉዳዩ ሲያነጋግር ቆይቷል፡፡

ገዥው ባንክ የአገሪቱ ባንኮች እንዲተገብሩት ያስተላለፈው ሰርኩላር፣ ከተለያዩ ባንኮች ብድር የወሰዱ የደቡብ ክልል ቡና አቅራቢዎች የነበረባቸውን የብድር ዕዳ ከሌሎች ተበዳሪዎች በተለየ እንዲታይና ለብድር አከፋፈል ከተቀመጠው መመርያ ውጭ እንዲስተናገድ የሚያዝ ነው፡፡

የአገሪቱ ባንኮች የሚሰጡትን ብድር እንዲሁም የአመላለስ ሥርዓቱን የተመለከተው ይህ የገዥው ባንክ መመርያ፣ ለአንድ ብድር የተሰጠው የመክፈያ ጊዜ ከሦስት ጊዜ በላይ ማራዘም ወይም ማስታመም እንደማይቻል ይደነግጋል፡፡ የደቡብ ቡና አቅራቢዎች ግን ይህ መመርያ ሳይተገበርባቸው እንዲስተናገዱ ብሔራዊ ባንክ  ለንግድ ባንኮች የላከው ሰርኩላር ያሳስባል፡፡   

ቡና አቅራቢዎቹ ከዚህ መመርያ ውጭ ብድራቸው ከሦስት ጊዜ በላይ እንዲራዘምላቸው ከመፍቀዱም ባሻገር የነበረባቸውን ውዝፍ ብድር በወቅቱ ባለመክፈላቸው ለማስያዣነት ያቀረቧቸው ንብረቶችም እንዳይሸጡ የሚከላከል ነው፡፡ በብሔራዊ ባንክ ለአጭርና ለመካከለኛ ጊዜ ተበዳሪዎች የብድር ማስታመሚያ ጊዜ እንደተሰጠ የሚገልጸው አንቀጽ፣ ቡና አቅራቢዎቹ ላይ እስከ መጪው 2010 ዓ.ም. ድረስ ተፈጻሚ እንዳይሆን የሚያዝ የሁለት ዓመት የዕፎይታ ጊዜ ሰጥቷል፡፡

በዚህ ሰርኩላር ምክንያት ባንኮች ለሰጡት ብድር መያዣ የነበሩ ንብረቶችን በሐራጅ ለመሸጥ ሲያነጋግሩ የነበሩትን የሐራጅ ማስታወቂያ አቁመዋል፡፡ ለቡና አቅራቢዎቹ የተሰጠው ይህ ዕድል፣ ከ200 በላይ የደቡብ ቡና አቅራቢዎች ያልከፈሉት ውዝፍ የብድር ዕዳ ቢኖርባቸውም ተጨማሪ ብድር እንዲያገኙ ጭምር የሚፈቅድላቸው ሆኗል፡፡

ብድር መክፈል ላልቻሉ አቅራቢዎች ተጨማሪ ብድር እንዲሰጡ የሚያዘው የገዥው ባንክ መመርያ በተለይ የግል ባንኮችን ሲያስጨንቅ ቆይቷል፡፡ አቅራቢዎቹ የተበደሩትን ብድር መመለስ ከሚጠበቅባቸው ጊዜ በላይ ያዘገዩ በመሆኑ ምን እናድርግ? የሚለው ጥያቄ ለባንኮቹ አሳሳቢ ነበር፡፡

ብሔራዊ ባንክ ከተለመደው አሠራር ውጭ በመሥራት ይህንን ዕርምጃ የወሰደው፣ የደቡብ ክልል ቡና አቅራቢዎች ለተከታታይ ዓመታት በቡና ዋጋ መውደቅ ምክንያት ከፍተኛ ኪሳራ እንደረሰባቸው በማስታወቃቸው ነው፡፡ ከፍተኛ ግምት ያለው ንብረት ለባንክ ማስያዣነት በመዋላቸው፣ ንብረታቸው ከተሸጠም ሊደርስባቸው ይችላል ተብሎ የተፈራው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ ከግምት ውስጥ ገብቶ እንደሆነም የብሔራዊ ባንክ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

የቡና አቅራቢዎቹ መንግሥት እንዲታደጋቸውና ችግራቸው እንዲቀርፍላቸው በተደጋጋሚ ጥያቄ ያቀረቡት በደቡብ ክልል ቡና አጣቢዎችና አቅራቢዎች ዘርፍ ማኅበር በኩል ነበር፡፡ የማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ቃሚሶ እንደሚሉት፣ በደቡብ ክልል በተለይ በሲዳማ አካባቢ የተፈጠረው ችግር ያለመንግሥት ጣልቃ ገብነት የማይፈታ ነበር፡፡ መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔ ለዓመታት ሲገላበጥ የመጣውን ብድር የመክፈል ጫና እሱንም ተከትሎ ሊመጣ የሚችለው ቀውስ በዝርዝር ታይቶ ስለታመነበት፣ የተወሰደ ዕርምጃ መሆኑንም አቶ ዘሪሁን ያስረዳሉ፡፡ ማኅበሩን ጨምሮ የደቡብ ክልል መንግሥት በጉዳዩ ላይ እጁን በማስገባት ቡና አቅራቢዎቹ በመንግሥት እንዲታገዙ በማለት ያቀረበው አቤቱታ በፌደራል መንግሥት ተቀባይነት ሊያገኝ ችሏል፡፡

ስለተከሰተው ችግር በቀረበው መረጃ መሠረት፣ በሐዋሳ ከተማ ብቻ ቡና አቅራቢዎቹ ከ2,400 በላይ መኖሪያ ቤቶችን ማስያዛቸው አንዱ ማሳያ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ አቶ ዘሪሁን እንደሚገልጹት፣ ይህ ሁሉ ንብረት ለዕዳ ማስመለሻነት በባንኮች ቢሸጥ ኑሮ ቀውሱ በቡና አቅራቢዎቹ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ንብረቱ በአብዛኛው የቡና አቅራቢዎቹ ቤተሰቦችና የወዳጆቻቸው በመሆኑ ችግሩ ሰፊ ሊሆን እንደሚችል ያሳያል፡፡

ይህ ከታየ በኋላ ብሔራዊ ባንክ የተበዳሪዎቹ የዕዳ መክፈያ ጊዜ እንዲራዘም፣ ተጨማሪ ብድር ከፈለጉም እንዲሰጣቸው በማለት ውሳኔውን ለአበዳሪ ባንኮች ማስተላለፉ ሲዘገብ ቆይቷል፡፡

ከዚህ ውሳኔ ባሻገር ቡና አቅራቢዎቹ በግል ባንኮች የሚፈለግባቸውን ብድር ጠቅልለው ወደ መንግሥት ባንክ እንዲያዘዋውሩም ዕድል ተሰጥቷቸዋል፡፡ በግል ባንኮች እጅ ይገኝ የነበረውን ብድር ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲዛወር የሚደረገውም በፈቃደኝነት ቢሆንም፣ ከ200 ውስጥ አብዛኞቹ ብድራቸውን ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዛውረዋል፡፡ ‹‹አሁን ነገሮች ተለውጠዋል፡፡ መንግሥት ብድራችን እንዲራዘም፣ ተጨማሪ ብድር እንድናገኝና በግል ባንኮች ያለው ብድራችን ወደ መንግሥት ባንክ እንድናዛውር በማድረጉ ከሞት አድኖናል፤›› በማለት አቶ ዘሪሁን የመንግሥትን ዕርምጃ አሞካሽተዋል፡፡

የቡና አቅራቢዎቹን ብድር ከግል ባንኮች የተረከበው ንግድ ባንክ፣ የብድር መክፈያ የዕፎይታ ጊዜ በመስጠት ቡና አቅራቢዎች ተረጋግተው ወደ ሥራ እንዲገቡ ማስቻሉን አቶ ዘሪሁን ጠቅሰዋል፡፡ በዕዳና በኪሳራ ችግር ውስጥ የቆየው የአካባቢው ቡና አቅራቢ ተጨማሪ ዕድል እንዳገኘ የሚገልጹት አቶ ዘሪሁን፣ በምርት ዘመኑ ለቡና ግዥ የሚያውሉት ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ የሥራ ማስኬጃ ብድርም እንደተለቀቀላቸው ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ሥራ ማስኬጃ ገንዘብ በኪሳራ ከገበያ ወጥቶ የነበረው ቡና አቅራቢ በሐራጅ ሊሸጥበት የነበረውን ንብረት ከማዳኑ በላይ ቡና ገዝቶ እንዲያዘጋጅ ዕድል ሰጥቶታል፡፡

ለሥራ ማስኬጃ በተገኘው ብድር አማካይነት ሥራ ፈተው የቦዘኑ መፈልፈያ ማሽኖች በአሁኑ ወቅት ዳግመኛ ወደ ሥራ መግባታቸውንና በማኅበሩ ሥር የሚገኙ ቡና አቅራቢዎችም ቡና እየገዙ በመፈልፈል ሥራ እንደተጠመዱ የማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ጠቅሰዋል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ በሲዳማ ዞን ብቻ ከ60 ሺሕ ቶን በላይ ቡና መሰብሰቡን፣ ይህም በአንድ የምርት ዘመን ከሚሰበሰበው ይልቅ ከፍተኛ የሚባል መጠን ነው፡፡ በዓመት ሲበሰብ የቆየው ከ35 ሺሕ እስከ 40 ሺሕ ቶን የሚገመት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ዘሪሁን፣ ዘንድሮ ምርቱም ጥሩ ስለነበርና ከገበያ የወጡ አቅራቢዎችም ዳግመኛ ወደ ሥራ በመመለሳቸው ከታሰበው በላይ ቡና ሊሰበሰብ እንደቻለ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ቡና በሚሰበሰብበት ወቅት የሚወጣው የተጋነነ ዋጋ፣ የግብይት ሥርዓቱን ያስተጓጉል እንደነበር ጠቅሰው፣ በአሁኑ ጊዜ ግን እንዲረጋጋ ለማድረግ የተሠራው ሥራ ለውጤቱ አስተዋጽኦ ነበረው ተብሏል፡፡ ለሚዘጋጀው ቡና የሚቀርበው ዋጋ አሁንም እንደሚያሳስብ ይሁንና ግን ሌሎች አሳሳቢ ችግሮች በመቀረፋቸው አቅራቢዎች እፎይታ ማግኘታቸውን የሚገልጹት የማኅበሩ ሊቀመንበር፣ በምርት ዘመኑ ከሚያገኙት ገቢ የባንክ ዕዳቸውን መክፈል እንዲጀምሩ ያስችላል የሚል ተስፋ ሰንቀዋል፡፡ እንዲህ ያለ የመንግሥት ውሳኔ ባይተላለፍ ኑሮ ይፈጠር የነበረው ቀውስ ቀላል እንዳልሆነ የሚናገሩት አቶ ዘሪሁን፣ አቅራቢዎቹ ያለባቸውን ብድር ለመክፈል የሚያስችል የዕፎይታ ጊዜ ማግኘታቸውም ተጨማሪ ዕድል እንደሆነላቸው ይናገራሉ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተረከበው የአቃራቢዎቹ ዕዳ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ እንዲከፈለው የተመቻቸው ዕድል ሌሎች የባንክ ተበዳሪዎች ያላገኙት በመሆኑ ይህንን ዕድል ቡና አቅራቢው በአግባቡ እንዲቀጠምበት ማኅበሩ እየሠራ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡ በመንግሥት የተሰጠውን ዕድል በአግባቡ ለመጠቀም እንዲችልም ለዚህ ተብሎ ከተቋቋመ ኮሚቴ ጋር ማኅበሩ እየሠራ መሆኑ ታውቋል፡፡

ለደቡብ ክልል ቡና አቅራቢዎች የተሰጠው ዕድል ግን በወቅቱ አነጋጋሪ ሆኖ መቆየቱ አይዘነጋም ነበር፡፡ ኪሳራ የገጠመው ቡና አቅራቢ በዚያ አካባቢ ያለው ብቻ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ አስነስቶ የነበረ ሲሆን፣ ባንኮች በብድር የሚሰጡት የሕዝብ ገንዘብስ በዚህ መልኩ መስተናገድ ነበረበት ወይ? የሚለውም አይዘነጋም፡፡ ይሁንና እንደ ደቡብ ክልል ቡና አቅራቢዎች ሁሉ በሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ችግር ያገጠማቸው አቅራቢዎችን ለመደገፍ ተመሳሳይ ሥርዓት ተዘርግቶ ጥያቄዎቻቸውን ማስተናገድ እንደተጀመረ  ይነገራል፡፡

አቶ ዘሪሁንም በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች ያሉ ቡና አቅራቢዎች የእነሱን ዓይነት ዕድል እንዳገኙ ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹የእኛ ከሁሉ የከፋ ቢሆንም ይህ ዕድል መሰጠቱ ለሌሎችም ተርፏል፡፡ ስለዚህ የመንግሥት ውሳኔ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ይኖሩታል፡፡ በተለይ ባንኮች ብድራቸውን እንዲያገኙ፣ በቢሊዮን ብሮች የሚገመቱ ንብረቶች በሐራጅ ከመሸጥ እንዲድኑ ከመደረጉ በላይ ተጨማሪ ብድር በመገኘቱም ከፍተኛ የቡና ምርት ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ በር ከፍቷል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

ትልቁ ችግር ግን ይህን መሰሉን ዕድል የማኅበሩ አባላት ምን ያህል ይጠቀሙበታል? ለሚለው ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ማግኘቱ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ተደርጎም አሁንም ብድሩን መክፈል ካልቻሉስ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ዘሪሁን፣ ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር ኮሚቴውና ማኅበሩ በጋራ እየሠሩ ነው ብለዋል፡፡ እያንዳንዱ የዕድሉ ተጠቃሚ ብድሩን በአግባቡ የሚከፍልበት አሠራር የተመቻቸ ስለሆነ ብድሩን ለመክፈልና ከነበረው ቀውስ ለመውጣት ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ሊቀመንበሩ ይናገራሉ፡፡

 

 

Standard (Image)

በጉጉት የሚጠበቀው የንግድ ምክር ቤቱ አጣሪ ኮሚቴ ሪፖርት ነገ ይፋ ሊሆን ነው

$
0
0

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ የሚያስችሉ ችግሮች ገጥሞኛል በማለት በሥሩ የሚገኙትን 18ቱን አባል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች በመጥራት ማወያየቱና መፍትሔ ይሆናል ብሎ ያመነበትን ውሳኔ ያስተላለፈው ጥቅምት 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ነበር፡፡ በዚህ መድረክ ላይ እንደተገለጸውም የንግድ ምክር ቤቱ ቦርድ ጠቅላይ ጉባዔውንና ምርጫ ለማካሄድ ያላስቻሉኝ ችግሮች ናቸው ያላቸውን ጉዳዮች በማቅረብ ተፈጠረ የተባለውን ችግር ለማጣራትና ለመፍታት ግብረ ኃይል እንዲቋቋም ማድረጉ ይታወሳል፡፡

ሰባት አባላት ያሉት ግብረ ኃይል ችግሩን በማጣራት የሚደርስበት ድምዳሜ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሆንና ከዚያም በኋላ ጠቅላላ ጉባዔው እንዲካሄድ ስምምነት ላይ ተደርሶም ነበር፡፡ ከዚህ ውሳኔ በኋላ በቀጥታ ወደ ማጣራት ሥራው የገባው ግብረ ኃይል በዚህ ሳምንት ሥራውን እንዳጠናቀቀ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በንግድ ምክር ቤቱ ውስጥ በተደጋጋሚ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ጭምር ያስችላል ተብሎ የታመነበት የማጣራት ሥራ በተሰጠው የሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ስለመጠናቀቁ የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢና የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራትም ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አሰፋ ገብረ ሥላሴ ገልጸዋል፡፡

አሉ የተባሉትን ችግሮች መነሻ በማድረግ በተደረገው ማጣራት በርካታ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳልፈናል ያሉት አቶ አሰፋ፣ የደረሱበትን ድምዳሜ የሚያሳይ ሪፖርታቸውን ነገ ታኅሳስ 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ይፋ ይደረጋሉ፡፡

ግብረ ኃይሉ የደረሰበትን ድምዳሜ የሚያሳየው ሪፖርትም 18ቱንም አባል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች መሪዎች በሚገኙበት የሚቀርብ እንደሆነም ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

ግብረ ኃይሉ የደረሰበትን ድምዳሜና ውሳኔ የሰጠባቸውን ጉዳዮች በነገው ዕለት የሚታወቅ ይሆናል በማለት ዝርዝር ጉዳዮችን ከመግለጽ ቢቆጠቡም፣ ተፈጠሩ ለተባሉ ችግሮች መፍትሔ ይሰጣል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ አሰፋ ገልጸዋል፡፡

እንደ እርሳቸው ገለጻ ኮሚቴው በዋናነት ትኩረት አድርጎ የሠራው የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች የምርጫ ሔደቶች የሕግ ጥሰት ታይቶባቸዋል አልታየባቸውም የሚለውን ጉዳይ ከአዋጁና ከሕጉ ጋር በማስተያየት ነው፡፡

በሕጉ መሠረት ያልተከናወኑ ካሉ ምርጫቸው ሊደረግም ይችላል ያሉት አቶ አሰፋ፣ ግብረ ኃይሉ እከሌ ከሰሰ፤ እከሌ ተከሰሰ በሚሉት ጉዳዮች ውስጥ ሳይገባ አሉ የተባሉትን ችግሮች ከንግድ ምክር ቤቶች አዋጁ ጋር በማመሳከር እንዲሠራና መፍትሔ የሚለውን ውሳኔ አስቀምጧል ብለዋል፡፡

እንደምንጮች ገለጻ ከሆነ ደግሞ ግብረ ኃይሉ ንግድ ምክር ቤቱን ሲያተራምሱ ነበሩ የተባሉ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ማሳለፉን ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ፀድቆ ሥራ ላይ ያለውን መተዳደሪያ ደንብ የተመለከተም ውሳኔ ስለመተላለፉ የሚገልጹት ምንጮች፣ ውሳኔው ግን ምን እንደሆነ ለማወቅ ሪፖርቱን መጠበቅ ግድ ይላል ብለዋል፡፡

ሆኖም አንዳንድ ግብረ ኃይሉ መፍትሔ ይሆናሉ ብሎ የወሰናቸው ውሳኔዎች ሁሉንም ወገን ላያስደስቱ ይችላሉ ተብሏል፡፡ ምናልባትም ሊያከራክሩ ይችላሉ ተብሎ የሚጠበቁ ጉዳዮች ሊኖሩ እንደሚችሉ የሚጠቅሱ አሉ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ቦርድ ጠቅላላ ጉባዔውና ምርጫውን ለማካሄድ አላስቻለኝም ብሎ ካቀረባቸው ምክንያቶች ውስጥ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ በአዋጁና በሕገ ደንቡ መሠረት አባል ምክር ቤቶች ማቅረብ የሚጠበቅባቸውና የላኩት መረጃ ክፍተት ያለበት መሆኑ ነው፡፡ በተለይ የንግድ ምክር ቤቱን የአመራር ቦታ ለማግኘት ተደረጉ የተባሉ የሕግ ጥሰቶች እየታዩ ወደ ጠቅላላ ጉባዔ መሄድ የማያስችል በመሆኑ ወደ ማጣራት ሥራ ሊገባ ችሏል፡፡

አሁን በአመራር ላይ ያለው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ቦርድ እንደገለጸው የኃላፊነት ዘመኑ መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ተጠናቅቋል፡፡

ከመስከረም 30 በፊት ጠቅላላ ጉባዔውን አካሂዶ ኃላፊነቱን ለአዳዲስ ተመራጮች ማስረከብ ይገባው እንደነበር ቢታወቅም፣ ምርጫውንም ይሁን ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ ባለመቻሉ እስካሁን ቆይቷል፡፡ ከምርጫ ሒደቶች ጋር ተፈጸሙ የተባሉ ግድፈቶች ጉዳይ እስከ ንግድ ሚኒስቴር ድረስ የሄደ ሲሆን፣ ሚኒስቴሩ የቀረበውን ቅሬታ በራሱ መንገድ ማጣራቱ ይታወቃል፡፡

በ18ቱ አባል ምክር ቤቶች የተመረጠው ግብረ ኃይል ውሳኔ ግን ሁሉንም ይገዛል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ውሳኔው መፍትሔ ማምጣት አለማምጣቱ ከሪፖርቱ በኋላ ይታወቃል፡፡   

በጥቅምት 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ለግብረ ኃይሉ ሥልጣን ሲሰጥ የሚወስነውን ውሳኔም መቀበል ግድ እንደሚሆን የተገለጸ በመሆኑ፣ ሊቀርቡ የሚችሉ መከራከሪያዎች ተቀባይነት ላይኖራቸው ይችላል፡፡

አቶ አሰፋ በበኩላቸው ሥራቸውን በሚገባ መሥራታቸውን ገልጸዋል፡፡ አከራካሪ ነገር ይኖራል ብለው እንደማይጠበቁም ተናግረዋል፡፡ ሪፖርቱ ከቀረበ በኋላም መካሄድ የነበረበትና የዘገየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ይካሄዳል ብለዋል፡፡

በዚህ ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫም እንደቀደመው ጊዜ ያልተገቡ ነገሮች እንዳይከሰቱ የሚደረግ መሆኑንም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ 

Standard (Image)
Viewing all 665 articles
Browse latest View live